Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

ከአንድ መቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የመድን ኢንዱስትሪ ጥልቅ መዋቅራዊ ተሃድሶ ያስፈልገዋል

$
0
0

 

በኢዮቤድ ጥበቡ ልሳነወርቅ

በኢትዮጵያ የባንክና መድን ታሪክ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ታሪክ የተለየ ነው፡፡ የአብዛኞቹ አፍሪካ አገሮች የባንክና መድን አገልግሎት አጀማመር ከቅኝ አገዛዝ ታሪካቸው ጋር ይያዛል፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሥልጣኔን ወደ ኢትዮጵያ ለማስረፅ በነበራቸው ራዕይ መሠረት በ1897 (እ.ኤ.አ. 1905) ዓ.ም.  የቀድሞውን አቢሲንያ ባንክ መሠረቱ፡፡ ባንኩ ዘመናዊውን የባንክ ሥራ በኢትዮጵያ ከማስተዋወቅ ባሻገር የዘመናዊውን የመድን ዋስትና አሠራር ፈር የቀደደ ነበር፡፡  በግብፅ አገር ለሚገኙ የእንግሊዝ፣ የኦውስትሪያ፣ የስዊዝና የሌሎችም አገሮች መድን ኩባንያዎች ወኪል   በመሆን ለባሕር ጉዞና ለእሳት ቃጠሎ ጉዳቶች የመድን ዋስትና ውሎችን  ሸጧል፡፡  በባንኩ አማካይነት ተሸጠው በነበሩ የመድን ውሎች መሠረት የደረሱ ጉዳቶችን ለማስተካከል የጉዳት ካሣዎች ስለመከፈላቸው በታሪክ ማኅደር ተመዝግቦ  ይገኛል፡፡

በተከታታይ ዓመታት የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች መድን ሰጭዎች ወኪሎቻቸውን ወደ አዲስ አበባና ወደ ወደብ ከተሞች እየላኩ የመድን ዋስትና ውሎችን በጊዜው ለነበሩ መድን ፈላጊዎች ሲሸጡ ቆይተዋል፡፡ በ1928 ዓ.ም. ፋሺስት ኢጣሊያ አገራችንን ወርራ በቆየችበት አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የመድን ኩባንያዎቿን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት አገልግሎቱን በበላይነት ስትሰጥ ቆይታለች፡፡ በአርበኞቻችን ተጋድሎ ነፃነት ከተመለሰ በኋላ ቀድሞ እንደተለመደው የተለያዩ የአውሮፖ መድን ኩባንያዎች የመድን ውክልና ሥራቸውን በአገሪቱ ውስጥ ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡

በዚያን ወቅት የመድን ሥራ እንደ ማንኛውም የንግድ ዓይነት ተቆጥሮ ይስተናገድ የነበረው በ1952 ዓ.ም. በወጡት የንግድ፣ የባሕር፣ የፍትሐ ብሔር፣ እንዲሁም በሌሎች አግባብነት በነበራቸው ሕጎች መሠረት ነበር፡፡ የመድን ሥራ ራሱን የቻለ የቁጥጥር ሥርዓት ሊዘረጋለት እንደሚያስፈልገው በጊዜው የነበረው መንግሥት በመንገንዘቡ የመጀመሪያውን ‹‹የመድን ሥራ መቆጣጠሪያ አዋጅ ቁጥር 281/1963›› አወጀ፡፡ በአዋጁም መሠረት የመድን ኩባንያ ማቋቋሚያ ቅድመ ሁኔታዎችን (Conditions for Iicensing) ያሟሉ 14 በግል የአክሲዮን ኩባንያነት ተደራጅተው በንግድ ሚኒስቴር ተመዝግውና የመድን ሥራ ፈቃድ ተሰጥተው አገልግሎቱን  ሲያበረክቱ ቆይተዋል፡፡ 14ኛው ኩባንያ ‹‹ራስ ኢንሹራንስ›› ይባል የነበረ ሲሆን፣ በባለአክሲዮኖቹ የእርስ በርስ አለመግባባት ምክንያት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ኩባንያው በመፍረስ ሒደት ላይ ስለነበረ መንግሥት አልወረሰውም፡፡ 

በጥር ወር 1967 ዓ.ም. የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር መንግሥት በጤናማ አቋም ላይ የነበሩትን 13 የግል መድን ኩባንያዎች ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመውረስ የመንግሥት ንብረት አደረጋቸው፡፡ ኩባንያዎቹም ‹‹በጊዜያዊ ኢንሹራንስ ቦርድ›› የበላይ ተቆጣጣሪነት ቀድሞ የነበራቸው አቋም ሳይለወጥ ለአንድ ዓመት   ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ በ1968 ዓ.ም. በቁጥር 68/1968 አዲስ የመድን ሥራ መቆጣጠሪያ አዋጅ ታወጀ፡፡ በአዋጁም መሠረት አሃዳዊ ‹‹የኢትዮጵያ መድን ድርጅት›› (Ethiopian Insurance Corporation) ተመሥርቶ አገልግሎቱን በሞኖፖል በመያዝ ለ17 ዓመታት ቆየ፡፡ እንደ ሌሎቹ የገንዘብ ተቋማት የመድን ሥራ ቁጥጥርም ተጠቃሎ በብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ሥር ገባ፡፡ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ነው እንጂ፣ ባንክና መድን የገንዘብ ድርጅት አባላት ከመሆናቸው ባሻገር የሥራ ባሕሪያቸው በአንድ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ሥር የሚወድቁበት ምክንያት አልነበረም፡፡

ከደርግ ውድቀት በኋላ አገሪቱን የተቆጣጠረው የኢፌዴሪ መንግሥት በተከተለው የገበያ መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሠረት የመድን አገልግሎት ከአሃዳዊ ሥርዓት ተላቆ ወደ ብዝኃነት ሥርዓት እንዲገባ፣ ብሎም ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በዘርፉ፣ ቅድመ ደርግ እንደነበረው፣ የግል መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱበት የፈቀደው ‹‹የመድን ሥራ መቆጣጠሪያ አዋጅ ቁጥር 86/1986›› እንደገና ታወጀ፡፡ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው ‹‹የመድን ሥራ መቆጣጠሪያ አዋጅ 746/2004›› ሊያካትታቸው የሚገቡ አያሌ ነጥቦች መኖራቸው ባይካድም፣ ከበፊቱ ከነበረው አዋጅ በብዙ መልኩ የተሻሻለ ነው፡፡

እንግዲህ፣ በኢትዮጵያ በቀንድና በጋማ ከብቶች ሽያጭና ግዥ ወቅት ይተገበር የነበረውን ባሕላዊውን የመድን ዋስትና፣ እንዲሁም በጥንት ዘመን ‹‹የሮድስ›› ሰዎች (Rhodes/Greece) የጀመሩት ‹‹ጄኔራል አቬሬጅ (General Average)›› በመባል ይታወቅ የነበረው የባሕር ጉዞ መድን ዓይነት ቀድሞ የኢትዮጵያ አካል በነበሩት ምፅዋና  አዱሊስ ወደቦች ላይ ሲሠራበት የቆየበትን ዘመን ሳንቆጠር (www.swissre.com/sigma - www.swissre.com/library) ዘመናዊ የመድን ዋስትና አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ ከገባ እነሆ ዘንድሮ 112 (2009 - 1897) ዓመት ሞላው፡፡ 

በእንግሊዝ አገር በኤድዋርድ ሎይድስ ቡና ቤት ውስጥ ዛሬ እየተሠራበት ያለው የመድን ውል አጻጻፍ የተጀመረው  እ.ኤ.አ. በ1668 ነበር፡፡ ዘንድሮ ዘመኑ በቁጥር 349 ዓመት ሆኖታል፡፡ ከዚህ የዘመን ርቀት አኳያ የኢትዮጵያ መድን ኢንዱስትሪን ዕድሜ ስናነፃፅር ዘመናዊ የመድን አገልግሎት በኢትዮጵያ ከተጀመረ ሲሶውን (1/3) የዕድሜ ሪኮርድ አስመዝግቧል ማለት ነው፡፡ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ የመድን ኢንዱስትሪ ዛሬ ያለበት የዕድገት ደረጃ የሕዝብ ብዛታቸው አነስተኛ ከሆኑት ጎረቤት አገሮች ጋር እንኳን ሲነፃፀር በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ የዘርፉን ባለሙያዎች እንደሚያስቆጭ ግልጽ ነው፡፡ (The Ethiopian insurance industry is relatively under developed in comparison to that of other African countries - http://www.researchandmarkets.com/reports/2564529/

ዛሬ ኢትዮጵያ አንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ያላትና የሁለት አኃዝ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያስመዘገበች አገር ሆና፣ በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኝ አንድ የመንግሥት ድርጅትና 17  የግል፣ በድምሩ 18 ‹‹ቀጥታ/ቀዳሚ መድን ሰጭዎች›› (Direct/Primary Insurers)፣ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ የተመሠረተው አንድ ‹‹የጠለፋ መድን ሰጭ›› (Reinsurer) ባለቤት ነች፡፡ እ.ኤ.አ. በኅዳር/2016 በተገኘ መረጃ መሠረት፣ አገሪቷ 55 የመድን አዋዋዮች (Insurance Brokers)፣ 1987 የመድን ወኪሎች (Insurance Agents)፣ 95 የሞተር የጉዳት ገማቾች (Motor Loss Acessors)፣ ሁለት የጉዳት ገማቾችና መርማሪዎች (Other loss Acessors/Surveyers) አሏት (ምንጭ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ)፡፡

ጎረቤት ኬንያ 48 ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት ያላት ሲሆን፣  27 በጠቅላላ መድን፣ 11 በረጅም ጊዜ መድን ዓይነቶች ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ልዩ ኩባንያዎች (Specialist Insurers) እና 13 የጠቅላላንና የረጅም ጊዜ መድን ዓይነቶችን በአንድነት አጣምረው የሚሠሩ ኩባንያዎች (Composite Insurers)፣ ሁለት የጠለፋ መድን ሰጪዎች፣ በድምሩ 53 የመድን ኩባንያዎች ባለቤት ናት፡፡ በኮሚሽነር የሚመራው የመድን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ‹‹ፈቃድ የተሰጣቸው የመድን አገልግሎት ሰጭዎች (Lisenced Insurance Service Providors)›› የሚላቸው 186 የመድን አዋዋዮች (Insurance Brokers)፣ ሰባት የጠለፋ መድን አዋዋዮች (Reinsurance Brokers)፣ 123 የመድን መርማሪዎች (Insurance Investigators)፣ 98 የሞተር ጉዳት ገማቾች (Motor Assessors)፣ 27 የመድን ገማቾች (Insurance Serveyers)፣ 4 የካሣ ክፍያ ፈጻሚ ወኪሎች (Insurance Claims Settling Agents)፣ 7354 የመድን ወኪሎች (Insurance Agents) እ.ኤ.አ. በካቲት/2017 በአገልግሎት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ የተቆጣጣሪው ባለሥልጣን በልዩ ልዩ የመገናኛ ዘዴዎች ስለመድን ‹‹የተጠቃሚ ትምህርት (Consumer Education)›› በተከታታይ ይሰጣል፡፡ (ምንጭ የኬንያ የመድን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን (www.ira.go.ke)፡፡ ይህ ጽሑፍ እንዳይንዛዛ በማሰብ የሌሎች ጎረቤት አገሮች ለምሳሌ የኡጋንዳ፣ የታንዛኒያ፣ የዛምቢያ መረጃዎች አልተካተቱበትም፡፡

ዴይሊ ኔሽን የተባለው የኬንያ ጋዜጣ እ.ኤ.አ. በካቲት 16 ቀን 2016 ዕትሙ የኬንያ መድን ኢንዱስትሪ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዕጥፍ እንደሚያድግ ‹‹ኧርነስት ኤንድ ያንግ›› የተባለው ድርጅት መተንበዩን ገልጿል፡፡ በዚሁ ትንበያ መሠረት ኬንያ 65 በመቶ፤ ታንዛኒያና ኡጋንዳ 88 በመቶ፣ ዛምቢያ 70 በመቶ የሚሆነውን የአረቦን ገቢያቸውን ከጠቅላላ የመድን ዘርፍ እንደሚያገኙም ታውቋል፡፡ እነዚህ አገሮች ከላይ በመቶኛ ከተጠቀሱት አሐዞች ቀሪውን የአረቦን ገቢያቸውን የሚያገኙት ከሕይወት መድን ዘርፍ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

በኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪ ባለቤትነት በደርግ ጊዜ ከነበረው አሃዳዊ ሥርዓት ተላቆ ወደ ብዝኃነት ሥርዓት እንዲገባ መፈቀዱ ‹‹ሰበር-ግኝት›› (Breakthrough) መሆኑ ባይካድም፣ ከላይ በተገለጸው ውስን ስታትስቲክስ መሠረት በሌሎች አገሮች የሚገኙ የመድን ኢንዱስትሪዎች ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ባሉበት ወቅት የአገራችን የመድን ኢንዱስትሪ ግን የሚጠበቅበትን ያህል ለውጥ ከቶ አላሳየም፡፡ የኢትዮጵያ መድን ኩባንያዎችም ትኩረት በከተሞች አካባቢ በመሆኑ በገጠር አካባቢ የሚገኘው ሰፊ ሕዝብ ገና የመድን አገልግሎት ተቋዳሽ አልሆነም፡፡ ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው ጎረቤቶቻችን ግን ሕዝቦቻቸውን ‹‹የንዑስ መድን (Microinsurance)›› ተጠቃሚዎች ካደረጓቸው ውለው አድረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ኢንዱስትሪ በመድን የሰለጠነ ባለሞያ ተግዳሮት ያለበት መሆኑም የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በተለይ በገጠር አካባቢ የሚሠማራ የመድን ባለሙያ ሁሉ አቀፍ የሆነ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖረው ግድ ይላል፡፡

ስለአገራችን የመድን ኢንዱስትሪ የዕድገት ደረጃ ዝቅተኛነት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል የኢንዱስትሪውን አገራዊ የዕድገት ፖሊሲና የሰው ሀብት ልማት ስትራቴጂ፣ ወዘተ ዋና ተግባሩ አድርጎ የሚቀይስ፣ ሥራውንም የሚያስተባብርና  የሚቆጣጠር ሁነኛ ባለቤት ዕጦት መሆኑን አያሌ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡ ስለአንዳንድ አገሮች አገራዊ የመድን ፖሊሲ፣ ህንድን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የመድን ሥራ ፈቃድ ተሰጥቷቸው በመድን አገልግሎት ሥራ ላይ  የተሠማሩ የመድን ኩባንያዎች ቢያንስ ሃያ በመቶ የሚሆነውን አገልግሎታቸውን ለገጠር አካባቢ ተደራሽ እንዲያደርጉ በአዋጅ ይገደዳሉ፡፡   

ለአገር ኢኮኖሚ የመድን ተግባርና ሚና

መድን ምንድን ነው? ሁሉም ሰው በሚገባው ቃል አማርኛ ለመግለጽ፣  ‹‹መድን እያንዳንዱ ተመዳኝ ወደ መድን ቋቱ/ፈንዱ በሚያስገባው የጉዳት-ሥጋት መጠን የዋስትና ከለላ/ሽፋን ለማግኘት የሚከፍለው መዋጮ (አረቦን) የሚካብትበትና ለተመዳኙም በተሰጠው የመድን ዋስትና ውል መሠረት ጉዳት ሲደርስት ጉዳቱን ለማቃለል/ለማካካስ ከተከማቸው የመድን ገንዘብ ቋት/ፈንድ ላይ የጉዳቱ ተመጣጣኝ ካሣ በገንዘብ፣ ወይም በዓይነት የሚከፈልበት የማኅበራዊ/የንግድ ሥራ ነው›› አያሌ የኢኮኖሚ ተግባራትን ለማከናወን የመድን ዋስትና ቅድመ ሁኔታ እንዲሆን፣ ብሎም  ኢኮኖሚው በሥርዓት እንዲመራ፣ እንዲቀላጠፍና ቀጣይነት ባለው መንገድም እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ መድን ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

የመድን ኢንዱስትሪ በቀጥታም ሆነ በኢቀጥተኛ መንገድ ለአንድ አገር ዋና ሥራ ፈጣሪ ከመሆኑም ባሻገር በመድን ሙያ ከፍተኛ ዕውቀትና ክህሎት ያለውን ባለሙያ (Professional) በማዳበር ረገድ ጥቅሙ የጎላ ነው፡፡ መድን የአጭር ጊዜ የጉዳት ማካካሻ አለኝታ ሆኖ ከማገልገሉ በላይ የረጅም ጊዜ የአገር ሀብትን በማካበት ረገድ ጥቅሙ  ለትውልድ፣ ለዘመናት እንዲተላለፍ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው፡፡ የማኅበረሰብ ፍላጎቶችን በአግባቡ ለማርካትና አዳዲስ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችንም በማበረታታት ረገድ መድን ታላቅ የኢኮኖሚ አጋዥ ኃይል ሆና ያገለግላል፡፡

የመድን ክፍለ ኢኮኖሚን ዋና ዋና ጥቅሞች እንደሚከተለው መዘርዘርም ይቻላል፡፡

  • በአገርና በግለሰብ ደረጃ  የፋይናንስ መረጋጋትን ያሰፍናል፣
  • ለመድን ተጠቃሚዎች የአዕምሮ ሰላምና ነፃነት ይሰጣል፣
  • ቁጠባን ያፋፋል፣
  • በተቋማዊ ኢንቨስተርነት መድን ሰጭዎች ካፒታል እንዲያካብቱ ያደርጋል፣
  • ለብድር መያዥያ የንብረት ዋስትና ስለሚሰጥ አበዳሪዎች ያለሥጋት ብድር እንዲሰጡ ያበረታታል፣ ተበዳሪዎችም በብድር በሚያገኙት ገንዘብ ተጠቅመው የአገር ኢኮኖሚን ያዳብሩበታል፣
  • ለኢንቨስተሮች አለኝታ በመሆን መዋለ ንዋያቸውን ያለሥጋት በሥራ ላይ እንዲያውሉት ያበረታታል፣
  • ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴን ያቀላጥፋል፣
  • ፍቱንና አሰተማማኝ የጉዳት-ሥጋት አስተዳዳር በአገርና በግለሰብ ደረጃ ያሰፍናል፣
  • ለጉዳት-ሥጋቶች መከላከያና ማቃለያ ዘዴዎች ግኝት፣ ብሎም አገርንና ሕዝብን የሚጎዱ አውዳሚ አደጋዎች አወጋገድ፣ ብሎም ተፅዕኖ ቅነሳ የመድን ሰጭዎችን ብርቱ ጥረት  ያስገኛል፣
  • ሰዎች በግላቸው የሕይወት፣ የጡረታ፣ የአደጋ፣ የሕክምና፣ አንዲሁም ለንብረቶቻቸው የመድን ዋስትናዎችን በመግዛት የመንግሥትን ማኅበራዊ አገልግሎት ጫና ያቃልላል፣
  • የወጭ የጠለፋ መድን ዋስትና ሰጭ ለሆኑ አገሮች የውጭ ምንዛሪ ዓይነተኛ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡

የመድንኢንዱስትሪዕድገትእንዴትይለካል?

ከብሔራዊ ምርት (GDP) እና ከሕዝብ ብዛት (Population) አንፃር የመድን ሴክተርን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ደረጃ (Level of Development of Insurance Sector) የምንለካባቸው ሁለት ዓይነት መለኪያዎች (Prameters) አሉ፡፡ አንደኛው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተመረተውን፣ ወይም የተጻፈውን ጠቅላላ አረቦን ‹‹ለጠቅላላ ብሔራዊው ምርት›› (GDP) አካፍለን በመቶኛ የምናገኘው የመድን ጥልቀት ምጣኔ (Insurance Penetration Rate) ይባላል (Volume of Premium Divided by the Gross Domestic Product in Percentage Terms)፡፡ የጠቅላላንና የሕይወት መድን ምጣኔንም ለያይተን ለየብቻቸው ማስላት እንችላለን፡፡ ሁለተኛው፣ ‹‹የነፍስ ወከፍ አረቦን ምጣኔ›› (Insurance Density) ሲሆን፣ በዓመት ውስጥ የተመረተውን አጠቃላይ የአረቦን ገቢን ለሕዝብ ብዛት አካፍለን የምናገኘው ምጣኔ ነው፡፡ ይህም እያንዳንዱ ሰው በነፍስ ወከፍ ምን ያህል አረቦን እንደከፈለ ያመለክተናል (Per Capita Premium)፡፡ ከታዳጊ አገሮች ይልቅ በኢኮኖሚያቸው የበለጸጉት አገሮች በነፍስ ወከፍ የሚከፍሉት አረቦን እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2013 ጃፓኖች ለሕይወት መድን በነፍስ ወከፍ 2.805. የአሜሪካን ዶላር ከፍለዋል፡፡ በዛሬ ምንዛሪ 67.320 ብር መሆኑ ነው፡፡

በአገረ አሜሪካ ከሚገኘው ፌደራል ሪዘርቭ ባንክ ኦፍ ሴንት ሉዊስ (Federal Reserve Bank of St. Luis) በተገኘ መረጃ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2014 በኢትዮጵያና በኬንያ የተመረተው አረቦን ለጠቅላላ ብሔራዊ ምርት (GDP) ያበረከተው ድርሻ ለኢትዮጵያ፣ የሕይወት መድን 0.026 በመቶ፣ ሕይወት ነክ ያልሆነ መድን 0.43137 ሲሆን፣ ለኬንያ የሕይወት መድን 1.065 በመቶ፣ ሕይወት ነክ ያልሆነ መድን 1.356 በመቶ ነበር፡፡ (https://fred.stlouisfed.org/series/DDDI10ETA156NWDB)  የኢትዮጵያም ሆነ የኬንያ ውጤት ዝቅተኛ መሆኑ ባይካድም፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚታየው  ልዩነት ግን አስደማሚ ነው፡፡

ኢንሹራንስ ኢንሳይደር (www.insuranceinsider.com) የተባለው ድረ ገጽ ባወጣው አንድ ዘገባ እ.ኤ.አ በ2014 አሥር የአፍሪካ አገሮች የዘጠና ሁለት በመቶውን የመድን አረቦን ገቢ ብቻቸውን አፍርተዋል፡፡ ከእነርሱም ውስጥ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ግብፅ፣ አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ናምቢያ፣ ቱኒዚያና ሞሪሸስ ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይም ስድስቱ በጠቅላላ መድን ዘርፍ እያንዳንዳቸው ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ (ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ) የአረቦን ገቢ ያስገቡ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪ እንደ ሌሎቹ አፍሪካ አገሮች ለምን ዕድገት አያሳይም? ለኢንዱስትሪው መቆርቆዝ በኃላፊነት የሚጠየቀውስ ማን ነው? አያሌ አገሮች፣ በምሳሌነት እንግሊዝን መጥቀስ ይቻላል፣ በድሮ ጊዜ ኅብረተሰቧ የሕይወት መድን ዋስትና እንዲገዛ ለማበረታታት ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ የሚቆረጥ ‹‹የሕይወት መድን አረቦን›› ከደመወዝ ግብር ነፃ ታደርግ ነበር፡፡ በአገራችን ዛሬ ባንኮች ኅብረተሰቡን የቁጠባ ባሕል ለማስተማር ‹‹ይቆጥቡ፣ ይሸለሙ›› የሚል መፈክር አንግበው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ የመድንን ጥቅምና አስፈላጊነት ኅብረተሰባችን አውቆና ተረድቶ በአገልግሎቱ ይበልጥ እንዲጠቀም በባለድርሻ አካላት (Stakeholders) ምን ሚዛን የሚደፋ ነገር ተሠርቷል?  የኢንዱስትሪውንስ የሰው ሀብት በመገንበት ረገድ ምን ስትራቴጂ ተቀይሷል? ምን ያህል የሥልጠና በጀትስ በኢንዱስትሪው ይያዛል? የመድን ውል ተጽፎ የሚሰጠው በባዕድ ቋንቋ  ሲሆን፣ ደንበኞች ስለገዙትና ወደፊትም ስለሚገዙት የመድን ዋስትና ውል ዕውቀታቸውንና የአስተሳሰብ አድማሳቸውን ለማስፋት፣ የውል መብታቸውን እንዲያውቁና ግዴታቸውንም እንዲያከብሩ በኢንዱስትሪው ማኅበረሰብ በኩል የቱን ያህል ጥረት ተደርጓል?

ብሔራዊ የመድን ምክር ቤት

ከዚህ በላይ ለተጠቀሱትና ለሌሎችም ተመሳሳይ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ ሊያስገኝ የሚችልና ለአንድ መቶ አሥራ ሁለት ዓመታት ዳዴ ከማለት ያልቦዘነውን የመድን ኢንዱስትሪ የዕድገት አቅጣጫ መስመር የሚስያዝ፣ ብሎም የመድን አገልግሎት ለኅብረተሰባችን ተደራሽ እንዲሆን አስፈላጊውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ ኢንዱስትሪው በአራት እግሩ ቆሞ እንዲራመድ በማድረግ ረገድ አበክሮ የሚተጋ ‹‹ብሔራዊ የመድን ምክር ቤት›› (Insurance Council Board) መቋቋም ይገባዋል በማለት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ምክረ ሐሣብ ያቀርባል፡፡

የቀረበውም ሐሣብ አዲስ ፈጠራ፣ ወይም ግኝት አይደለም፡፡ ቅድመ ደርግ የነበረው ‹‹የመድን ሥራ መቆጣጠሪያ አዋጅ›› ሁለት ለመድን ኢንዱስትሪ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ቁም ነገሮችን ያካተተ ነበር፡፡ አንደኛው፣ ከላይ እንደተገለጸው የአገሪቱን የመድን አጠቃላይ ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚቀርጽና አገልግሎቱም በመላው አገሪቱ ውስጥ እንዲስፋፋ የሚከታተል፣ ሥራውንም በበላይነት የሚመራ  ‹‹የኢንሹራንስ ምክር ቤት›› ነበረ፡፡ የምክር ቤቱ አባላትም ለመድን ሥራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሚኒስትሮችና የመንግሥታዊ ተቋማት የበላይ ኃላፊዎች ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትም በምክር ቤቱ ውስጥ የአባልነት መቀመጫ ነበረው፡፡ ምክር ቤቱን በሰብሳቢነት የሚመሩት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር  ነበሩ፡፡ ስለዚህ ቀድሞ ወደ ነበርነበት የመድን ምክር ቤት መዋቅር ብንመለስ  (Back to Square One) ለአገሪቷ ይበጃታል የሚል ሐሳብ ነው የቀረበው፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮም ሐሣብ የቀረበበትን መዋቅራዊ ተሃድሶ ወቅታዊነት ያረጋግጣል፡፡ ለምሳሌ የኬንያ መድን ኢንዱስትሪ በዳይሬክተሮች ቦርድ (Insurance Board of Directors) የሚመራ ሲሆን፣ ሰብሳቢው በገንዘብ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፕሬዚዳንቱ ይሾማል፡፡

ሁለተኛው የቅድመ ደርግ የመድን ሥራ መቆጣጠሪያ አዋጅ ቁም ነገር ራሱን የቻለ የመድን ሥራ መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ማቋቋሙ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ሶሻሊስታዊ ሥርዓት ስትሸጋገር የመድን ምክር ቤቱም ሆነ የተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ተሰርዘው ኢንዱስትሪው በብሔራዊ ባንክ ሥር በሚገኝ አንድ መምሪያ ቁጥጥር ሥር ገባ፡፡ በወቅቱም በባንኩ ውስጥ ስለመድን ጽንሰ ሐሳብና የአሠራር ዘይቤ የሚያውቅ አንድም ሰው ባንኩ ስላልነበረው ባለሙያዎችን ከመድን ኩባንያዎች አዛውሮ ይገለገል እንደነበር በጊዜው የነበሩ ሁሉ ያውቁታል፡፡

‹‹የሥራነፃነት (Autonomy)›› ያላቸውየመድንሥራተቆጣጣሪአካላት

‹‹ዓለም አቀፉ የኤዥያ ፓስፊክ ሪስክ ኤንድ ኢንሹራንስ አሶስያሽን›› (Asia-Pacific Risk and Insurance Association) ባወጣው አንድ ዘገባ ከአፍሪካ አኅጉር አምስት አገሮች ብቻ የመድን ሥራን የሚቆጣጠሩት የማዕከላዊ ወይም የብሔራዊ ባንኮቻቸው ናቸው፡፡ እነርሱም ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋምቢያ፣ ጊኒና ሌሶቶ ናቸው፡፡ ‹‹በእስያና ኦሺያና›› (Asia and Oceania)  አገሮች የማሌዥያ መድን ኢንዱስትሪ ብቻ ‹‹በባንክ ኔጋራ ማሌዥያ›› (Bank Negara Malaysia)  ቁጥጥር ሥር ሲገኝ፣ ከደቡብ አሜሪካ የጓቴማላ መድን ኢንዱስትሪ ብቻ ‹‹ላ ሱፐር ኢንቴንዴንቺያ ዴል ባንኮስ›› (La Superintendencia de Bancos) ይቆጣጠረዋል፡፡ ከአውሮፓ ደግሞ የሩሲያ ፌዴሬሽን መድን ኢንዱስትሪ ብቻ በማዕከላዊ ባንክ ሥር ይተዳደራል፡፡ 

ሌሎች በዓለም ዙሪያ ያሉ አገሮች በሙሉ ራሳቸውን በቻሉና የሥራ ነፃነት በተሰጣቸው ‹‹የመድን ሥራ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት፣ ወይም ኮሚሽኖች (Insurance Regulatory Authorities or Commissions)›› ሥር የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ በእነዚህ አገሮች የመድን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት፣ ወይም ኮሚሽኖች በገንዘብና የኢኮኖሚ ሚኒስትሮች ሥር ናቸው፡፡ በዚህ መልክ ራሱን በቻለ ተቆጣጣሪ አካል የመድን ኢንዱስትሪዎቻቸውን ያዋቀሩ አያሌ አገሮች በከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡  በመድን ሙያ የሰለጠነ የሰው ኃይላቸውንም አበልጽገዋል፣ የመድን አገልግሎትም ለኅብረተሰባቸው ተደራሽ  እንዲሆንም ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ ናቸው፡፡

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ቀደም ባሉት ጊዜያት በዚሁ በሪፖርተርና ሌሎች ጋዜጦች ላይ በተለያዩ አንገብጋቢና ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አያሌ የማሳሳቢያ ጽሑፎችን በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች አቅርቧል፡፡ በተለይም በመድን ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚታየውን የድርጅት አስተዳደር (Corporate Governance) ድክመት፣ በቦርድ ዳይሬክተሮች አባላት ጥቆማና ምርጫ ላይ በሚታዩት ችግሮች ዙሪያ ጥብቅ መመርያዎች እንደሚያስፈልጉ የበኩሉን ጥቆማ አድርጓል፡፡ በጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም.  የቦርድ ዳይሬክተሮች ጥቆማንና ምርጫን በተመለከተ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን መመርያ አውጥቷል፡፡ መመርያውን ለማውጣት ረጅም ጊዜ የፈጀበት ቢሆንም፣ ‹‹ከመቅረት መዘግየት ስለሚሻል›› (Better late than never) እሰየው የሚያሰኝ ነው፡፡ አፈጻጸሙ ላይ ግን አሁንም በርካታ ችግሮች ይታዩበታል፡፡

ማጠቃለያ

ለኢትዮጵያ መድን ኢንዱስትሪ ሁለንተናዊ ዕድገትና ስለሰው ሀብቱም መጎልበት ጸሐፊው አያሌ ጥረቶችን ያደረገና በማድረግም ላይ መሆኑ አለ አይባልም፡፡ አሁን ደግሞ በብዙ ምርምርና ጥረት ‹‹የጉዳት-ሥጋትና መድን›› (Risk and Insurance) የተሰኘና 650 ገጾችን የያዘ አዲስ መጽሐፍ በአማርኛ ቋንቋ አዘጋጅቶ ለኅትመት አቅርቧል፡፡ ዛሬ የሕትመት ዋጋ እየናረ በመሄድ ላይ ስለሚገኝ መጽሐፉ ታትሞ ‹‹በዝቅተኛ ዋጋ›› (Low-price) ለኅብረተሰቡ እንዲከፋፈል ለማድረግ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣንና የመድን ሰጭዎች ማኅበር፣ እንደ ባለድርሻ አካልነታቸው፣ ለመጽሐፉ ኅትመት አስፈላጊውን ድጋፋቸውን እንዲለግሱ በጽሑፍና በቃል አሳስቧቸው ነበር፡፡ ‹‹ሃምሣ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሣ ሰው ጌጡ (50 lemons are burden for one person but adornments for 50)›› በሚለው አገራዊና ‹‹መድናዊ መርህ›› መሠረት የመድን ሰጪዎች የኅትመት ወጪውን በቀላሉ ሊከፋፈሉት እንደሚችሉ ዕሙን ነው፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ግን ተጻፈ የተባለው መጽሐፍ በይዘቱ ይክፋም፣ ይልማም፣ ‹‹እስቲ የጻፍከው ምንድነው?›› ብሎ በይመለከተኛል ስሜት፣ ጸሐፊውን ከኢንዱስትሪው ማኅበረሰብ አንድም ሰው የጠየቀው የለም፡፡

ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)፣ አቶ ግርማ በሻህ፣ (የሕግ ምሑርና የብዙ ቋንቋዎች ተናጋሪ (Linguist)፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ  ኃይለ ማርያም ቱርጁማን (Interpreter) የነበሩ፣ እንዲሁም ሌሎች ዕውቅ ባለሙያዎችና የመጻሕፍት ደራስያን የመጽሐፉን ይዘት ተመልክተውት ‹‹በመድን ሳይንስ ዙሪያ ቀደም ብሎ ያልተሠራ ድንቅ ሥራ ሠርተሃል፤›› በማለት ጸሐፊውን አበረታተዋል፣ ገንቢ አስተያየታቸውንም ለግሰዋል፡፡

የመድን ኢንዱስትሪውን ማኅበረሰብ አርምሞ በአንክሮ ለሚያሰላስል ሰው የአንድ ባለጠጋ ሰው ትርከት ትዝ ሊለው ይችላል፡፡ ሰውየው ብዙ ሀብት ያለው ከበርቴ ነበርና ንብረቱን ሌቦች ይዘርፉኛል ብሎ ስለሚሰጋ የስርቆት መድን ዋስትና ከመግዛት ይልቅ፣ አንድ ውሻ ያሳድግና በደንብ እየቀለበው ያለሥጋት ተኝቶ ማደር ይጀምራል፡፡ 'የጠሉት ይወርሳል፣ የፈሩት ይደርሳል'እንዲሉ ከዕለታት አንድ ቀን ጠዋት ሲነሳ ሌቦች በርካታ ንብረት ዘርፈውት ያገኛል፡፡ ባለጠጋው በጣም ተናዶና ተበሳጭቶ ‹‹ይህንን ወደል ውሻ ለካስ በከንቱ ነው የምቀልበው?›› እያለ ውሻውን በዱላ በግቢው ውስጥ እያሯሯጠ ይደበድበዋል፡፡ በጌታው ዱላ የተጨነቀውና የተማረረው ውሻ እንዲህ አያለ አለቀሰ ይባላል፡፡ ‹‹ነባሕህነ ነባሕነ ከመ ዘኢነባሕነ ኮነ›› (በአማርኛ ጮኽነ ጮኽነ እንዳልጮኽነ ሆነ)፡፡ በመሠረቱ የውሻው የሥራ ደርሻ አደጋ ሲመጣ ባለቤቱን በጩኸት ማንቃት ነበር፡፡ ባለቤቱም የውሻውን የማስጠንቀቂያ ጩኸት ሳይሰማ ቀርቶ ስርቆት ቢፈጸም ውሻው ተጠያቂ መሆን አይገባውም ነበር፡፡ የዚህ ጽሑፍም አቅራቢም ‹‹ጻፍነ ጻፍነ እንዳልጻፍነ ኾነ›› ይላል፡፡ በውስጠዘ ትርጉሙ  ‹‹ሰሚ ጆሮ  ታጣ››  ማለት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው [BA,  LLB (GD), Graduate Dipl. in Development Administration (India), ACII, Chartered Insurer (UK), ACS (USA)] ለረጅም ዓመታት በመድን ሥራ፣ በሥልጠና፣ በመድን ምርምርና ሥነ ጽሑፍ ሰፊ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ሲሆኑ፣ የመድን ባለሙያዎች ማኅበር (SIP) የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው eyosono@gmail.comወይም leeyobed@yahoo.comወይም በቴሌፎን ቁ. +251 0911 43 15 50 ማግኘት ይቻላል፡፡

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles