በዮሐንስ ገበየሁ
የአፍሪካ ቀንድ ከሀብታሞቹ የነዳጅ ባለቤቶች የባህረ ሰላጤው አገሮች ጋር በቀይ ባህርና በባቤል መንደብ ወሽመጥ አማካይነት ይገናኛል፡፡ ሀብታሞቹ የባህረ ሰላጤው አገሮች ከምዕራቡ ዓለም ኢኮኖሚ ጋር በሆርሙዝና ባቤል መንደብ ወሽመጦች የሚያገናኝ ነው፡፡ የኤደን ሰላጤና ቀይ ባህር በተባሉ ስትራቴጂካዊ ቦታዎች በየዓመቱ 700 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ልውውጥ የሚደረግበት ከመሆኑም በላይ ሜድትራኒያን ባህር፣ የስዊዝ ቦይና ቀይ ባህርን ከህንድ ውቅያኖስና የአውሮፓ ምዕራባዊያን ገበያዎችን ከእስያና ከመካከለኛው ምሥራቅ ገበያ ጋር በማገናኘት ትልቅ የንግድ መተላለፊያ ሆኖ ያገለግላል። ረጅም የሆነ ማለትም 2,500 ማይል የባህር ዳርቻ ያለው በመሆኑ ምክንያት፣ አሸባሪ ቡድኖችና የባህር ላይ ወንበዴዎች እንደፈለጉት እንዲንቀሳቀሱና እንዲፈነጩ የሚፈቅድ አመቺነት አለው። የአሸባሪዎችና የባህር ላይ ወንበዴዎች ያለማንም ሃይ ባይ የአሜሪካንና የምዕራባዊያንን ጥቅም በመፃረር በአካባቢው መንቀሳቀስ፣ ለዓለም አቀፋዊ የፀረ ሽብር ጦርነት ምክንያት በመሆን ኃያላኑ በአካባቢው ጣልቃ እንዲገቡ በር ከፍቷል። ቀጣናው የዓባይ ምንጭ ነው። እስያን፣ አውሮፓንና መካከለኛው ምሥራቅን ከማገናኘቱ በተጨማሪ፣ ዓረቦች ወደ ተቀረው አፍሪካና ዓለም ለመግባት ዋና በራቸው በመሆን የሚያገለግል ነው።
ከላይ በተጠቀሱት መልክዓ ምድራዊ፣ ጂኦ ፖለቲካዊና ስትራቴጂካዊ ምክንያቶች ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲና የፀጥታ ተለዋዋጭነት ያለው፣ የኃያላኑ ጣልቃ ገብነት የሚስታዋልበት፣ ተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃው፣ ሽብርተኝነትና የባህር ላይ ውንብድና የተስፋፋበት፣ ብዝኃነት መለየው የሆነ፣ አያሌ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችና ተፈናቃዮች የሚወጡበትና የሚገቡበት፣ የእርስ በርስ ጦርነት በማያቋርጥ ሁኔታ ለዘመናት ሲዘንብበት የኖረ የዓለማችን ክፍል ነው።
አገራችን ኢትዮጵያ በዚሁ ያልተረጋጋ አካባቢ የምትኖር ነገር ግን የሰላምና መረጋጋት ደሴት ተብላ በቀጣናው ተንታኞች የምትታወቅ አገር ናት። ኢትዮጵያ በእርግጥ ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ የአፍሪካ አገር፣ የጥቁር ሕዝቦች ምልክትና ኩራት፣ የኩሩ ሕዝብ እናት፣ የሰው ልጅ መገኛ ናት። አገራችን ምድረ ቀደምት ብትሆነም በምን ጥንካሬ፣ በምንስ ተዓምርና ጥበብ ለዘመናት ራሷን አስጠብቃ የሰላምና መረጋጋት ደሴት ልትሆን በቃች የሚለው የብዙ ተመራማሪዎች ጥያቄ ሆኖ የሚቀጥል ቢሆንም፣ በዚህ ጽሑፍ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ለነፃነቷ መጠበቅ ያበረከተውን ሚናና በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ቀውስ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት ለመተንተን ይሞከራል።
ኤድሞንድ ኬለር ‘‘The Politics of State Survival Change and Continuity of Ethiopian Foreign Policy’’ በሚል ርዕስ ባቀረበው ጽሑፍ፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የአገሪቱን ህልውና ለማስጠበቅ ትልቁ መሣሪያና ጥበብ መሆኑን ይጠቁማል። ሌሎች በመስኩ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎችም ይህንኑ ይጋራሉ። እንደ ብዙዎቹ ምልከታ ከሆነ የኢትዮጵያ መሪዎችና ሕዝቦች ለዘመናት ጠብቀውት የቆየ ማንነት ያላቸው በመሆኑ፣ ካልደረሱባቸው የማይደርሱ ከደረሱባቸው ግን አፈር ድሜ ሳያበሉ የማይለቁ መሆናቸውን የተለያዩ የታሪክ መዛግብትን በማጣቀስ ያስረዳሉ። ኢትዮጵያ በተለይም በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ከቅርብና ከሩቅ የተቃጡባትን ወረራዎች በመመከት “War is Diplomacy by Another Means” እንዲሉ፣ የዲፕሎማሲ ጠበብት ዲፕሎማሲው አልሠራ ሲል መሣሪያ በመምዘዝ ነፃነቷን ጠብቃ የቆየች አገር ናት። ለመጀመሪያ ጊዜ የነጭ የበላይነትን ቅስም ሰብሮ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያስጠበቀው፣ እንዲሁም በዘመኑ በቅኝ ግዛት ሥር ሲማቅቅ ለነበሩ የዓለም ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆነው የዓድዋ ድል ጦርነት ዲፕሎማሲን በሌላ መንገድ ማስኬጃ መሆኑን ያረጋገጠ፣ አገራችን የታፈረችና ክብሯን ጠብቃ የኖረች አገር እንድትሆን ካበቁ ክስተቶች ዋነኛው ነው።
ከዚህ ክስተት ወዲህ የአገርን ሉዓላዊነት የሚፈትኑ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች የተከሰቱ ቢሆንም. አገራችን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በሳል ዲፕሎማሲ ስታከናውን ኖራለች። ይህ በሳል የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ አገሪቷ በቀውስ ውስጥ ባለ ቀጣና ውስጥ የመረጋጋትና የሰላም ደሴት እንድትሰኝ አድርጓታል። የአገራችን ዲፕሎማሲ በመልካም ጉርብትና፣ በሰጥቶ መቀበል፣ በጋራ ተጠቃሚነት፣ በሌሎች አገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት፣ በጋራ ደኅንነትና በሌሎች የዓለም አቀፍ ግንኙነት ወርቃማ መርሆች እየተመራ ነው አገራችን ውጥንቅጡ በወጣ ቀጣና ውስጥ የሰላም ደሴት ለመሆን ያበቃት።
የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሰሶዎች ተብለው የሚታወቁት ዴሞክራሲን ማስፈንና መገንባት፣ ልማትን በፍትሐዊነትና ዘላቂነት ማረጋገጥና መልካም አስተዳደርን ዕውን ማድረግ ከአገሪቱ ውስጣዊና ውጫዊ ከባቢ ጋር የተገናዘቡ ናቸው። ሲጀምር ማንኛውም ተጋላጭነት ከውስጥ እንደሚመነጭ፣ ይህንን ተጋላጭነት ከምንጩ ለማድረቅ ደግሞ ከላይ የተጠቀሱትን ግቦች አልሞ መሥራት እንደሚያስፈልግ ብቻ ሳይሆን የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከጎረቤት አገሮች የጋራ ተጠቃሚነት ጋር በሚናበብ መልኩ የውስጥን ሁኔታ ከውጫዊ ሁኔታዎች በተለይም ከጎረቤት አገሮች ሁኔታ ጋር በማሰናሰል መከወን እንደሚያስፈልግ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ያትታል፣ ዲፕሎማሲያችን ደግሞ በዚሁ መሠረት ይተገብራል፣ ይንቀሳቀሳል፣ ያስፈጽማል።
ልማትና ዴሞክራሲያዊ ግንባታን እውን ማድረግ ማዕከሉ ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን አገራችን ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን፣ ጎረቤቶቿን ጭምር የሚጠቅምና የቀጣናውን ሁኔታ መቀየር በሚችል መንገድ መቃኘት እንዳለበት ተቀምጧል። በሌላ አገላለጽ፣ ኢትዮጵያ ቀጣናውን አስመልክቶ የምታራምደው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በጋራ ልማት፣ ተጠቃሚነትና ትብብር ላይ የተመሠረተ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ልማትን፣ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን ዕውን ማድረግ ከቀጣናውና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ ተለይቶ መታየት የሌለበት ጉዳይ መሆኑን በግልጽ አስምጧል የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው።
ይህ በግልጽ የሚያሳየን የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ ብልህ የሆነ አገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ኑባሬዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ነው። ዓለም አቀፉ የኃይል አሠላለፍ ምን ያህል ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል በመገንዘብ ብሪያን ሽሚድት (2008: 16) የተባለ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተንታኝ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኒዮ ክላሲካል ሪያሊስቶች ቅኝት የሚመራ መሆኑን እንዲህ ሲል ያስቀምጣል፡፡ ‘‘neo-classical realists argue that domestic factors are needed to explain how systemic factors are translated into foreign policy decisions.’’ ዲፕሎማሲያችን ከላይ የተጠቀሰውን አስተምህሮ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን የዲፕሎማሲ ታሪካችን ዳሰሳ ያመለክታል። በአጭሩ ለማስቀመጥ የኢትዮጵያ ቀጣናዊ ዲፕሎማሲ የውስጥ አቅምን፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የኃይል አሠላለፍና ሥርጭትን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው።
የአፍሪካ ቀንድ ከመጥበሻው ወደ እሳቱ የሚባል ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው። የፈረሰችው (Failed) ሶማሊያ፣ በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በመፍረስ ላይ ያለችው ደቡብ ሱዳን፣ ዳርደንበሯን ማስከበር የተሳናት (Porous) ኬንያ፣ አክራሪ እስላማዊ ሱዳን የቀጣናው መገለጫዎች ናቸው። ይህ የአገሮቹ ሁኔታ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ላላቸው እንደ አልሽባብ ላሉ አሸባሪ ቡድኖች ለም መሬት በመሆን ቀጣናው የአሸባሪዎች መፈልፈያ እንዲሆን ረድቷል።
ኃያላኑ የከተሙባት ጂቡቲና በትዕቢት የሚወጠረው የኤርትራ አገዛዝ የቀጣናው ሌላ ድባብ ናቸው። ያልተሳኩ አገሮች፣ የወደቁ አገሮች፣ ድርቅና ረሃብ፣ የእርስ በርስ ጦርነት፣ በቀጣናው ያለ የውጭ ጣልቃ ገብነት፣ የቀጣናው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና የሽብርተኝነት አደጋ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲንና የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴን ለመወሰን የሚረዱ ነባሪዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ በዚህ ውጥንቅጡ በወጣ ቀጣና ውስጥ የምትኖር አገር በመሆኗ ደኅንነቷን ለማረጋገጥ (Maximizing its Security) ትሠራለች፡፡ ይህ ደግሞ ተንታኞች (Defensive Realism/neo-classical Realism) ብለው የሰየሙት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫ ነው። በርካታ አገሮች ባልተረጋጋ የዓለም ቀጣና ውስጥ ራሳቸውን በማጠናከር፣ የውስጥ አቅማቸው ከውጫዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም በማድረግ ለውጫዊ ሁኔታው ምላሽ የሚሰጡበት አኳኋን ነው።
አገራችን ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በመሠረተ ልማት፣ በንግድ፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ በመልከዓ ምድርና በሃይማኖት የተሳሰረች መሆኗን በመገንዘብ፣ ይህንኑ የትስስር ገመድ በመጠቀም ከቀጣናው አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት በማዳበር ላይ ትገኛለች። ይህም በአገሮች መካከል መተማመን እንዲሰፍን የሚረዳ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ነው።
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያንና ጂቡቲን የሚያገኛኝ የባቡር ሐዲድ ገንብታለች፡፡ ኢትዮጵያንና ሱዳንን ለማገናኘት የየብስ ትራስፖርት ሥራ ጀምሯል፡፡ ኢትዮጵያንና ኬንያን የሚያገናኝ የየብስ ትራንፖርት በመገንባት ላይ ይገኛል። የበርበራ አዲስ አበባ ኮሪደርን ዕውን በማድረግ ሶማሊያላንድን ከኢትዮጵያ ጋር ለማገናኘት እየተሠራ ነው። ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኝ መንገድ ለመገንባት ሁለቱ አገሮች ተስማምተዋል፡፡ በተጨማሪም ጁባን ከአዲስ አበባ ጋር ለማገናኘት የሚያስችል ፕሮጀክት በኢጋድ አስተባባሪነት እየተዘጋጀ ነው። ኢትዮጵያ ለጂቡቲ፣ ኬንያና ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ትሸጣለች፣ ለጂቡቲ የመጠጥ ውኃ ታቀርባለች። ከጂቡቲ የወደብ አገልግሎትና ከሱዳን ደግሞ የነዳጅ አቅርቦትን ትገዛለች። ይህ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር በይነ ጥገኝነትን (Interdependence) በማስፈን አንዱ ካለአንዱ መኖር እንደማይቻልና የጋራ ተጠቃሚነት ዋነኛው የዲፕሎማሲያችን መርህ መሆኑን በተግባር ማሳየት ችሏል።
ጎረቤት አገሮችን በሰላምና ደህንነት፣ በንግድና ቴክኒካዊ የድጋፍ መስኮች አገራችን በመርዳት ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ ሶማሊያና ሌሎች አጎራባች አገሮች ጠንካራ መንግሥት እንዲመሠረቱ ከፍተኛ የሆነ የቴክኒክ ድጋፍ፣ የምጣኔ ሀብት ትብብርና ሌሎችን ድጋፎች ታደርጋለች። በኢትዮጵያና በጎረቤት አገሮች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማዳበር በተለይም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን በማጠንከር በፅኑ መሠረት ላይ የቆመ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ዕውን ለማድረግ እንዲረዳ የጎረቤት አገሮች ቀጣይ የአገር ተረካቢዎችን ወደ አገራችን መጥተው ትምህርትና ሥልጠና እንዲያገኙ፣ አገራችን ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ከጎረቤት አገሮች ሕዝቦች ጋር የሚያስተሳስሯቸው ሰፊ የባህል፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የቋንቋና የታሪክ ሰንሰለቶች እንዳሉ ለማሳየትና ለማስገንዘብ ጥረት እየተደረገ ነው።
በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. በ2015 ብቻ 325 የሚሆኑ የሶማሊያ ተማሪዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አስፈላጊው ትብብር ተደርጎላቸዋል። ከ2015 በፊትና በኋላም በተለያየ ቁጥር የሶማሊያ ተማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከፍተኛ ትምህርት ተከታትለዋል። እ.ኤ.አ. በ2017 ብቻ 8,000 የሚሆኑ ኤርትራዊን የመጀመሪያ ደረጃ ትምርታቸውን፣ 2,200 የሚሆኑ ሕፃናት የቅድመ መደበኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። እ.ኤ.አ. እስከ 2016 ድረስ 1,500 የሚሆኑ የኤርትራ ስደተኞች በአገራችን የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነፃ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል። 3,000 በላይ የሚሆኑ ደቡብ ሱዳናዊያን በኢትዮጵያ ነፃ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የተገኙ መረጃዎች ያስረዳሉ። ከ900 በላይ ጂቡቲያዊያን በኢትዮጵያ የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የነፃ የትምህርት ዕድል እየተከታተሉ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጎረቤት አገር ስደተኞችን በመቀበል አገራችን አገራችሁ በማለት ስደተኞችን አቅፋ ደግፋ መኖሯ ሞልቷት ተርፏት ሳይሆን፣ የረዥም ጊዜ ትብብር ሁልጊዜም በሕዝብ ልብና እዕምሮ የሚገነባ መሆኑን ስለምታውቅ ነው። በዚህ ረገድ 811, 555 የሚሆኑ ስደተኞችን ማለትም የሶማሊያ (246,859)፣ ደቡብ ሱዳን (349,086)፣ የኤርትራ (167,619)፣ የሱዳን (40,779)፣ የየመን (1,616) እና የሌሎች የጎረቤት አገሮች (5,596) በማስተናገድ ላይ ናች።
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ደንበርና ደንበር ተሻጋሪ ሀብቶችን ትጋራለች። የዓባይ ውኃን ከሱዳንና ከግብፅ፣ ኦሞን ከኬንያ፣ ሸበሌና ጁባን ከሶማሊያ ጋር የምትጋራ ሲሆን፣ ሁሉም ወንዞች ከኢትዮጵያ የሚመነጩ ናቸው። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶች የሚመነጩት ከኢትዮጵያ ስለሆነ ብቻዬን ልጠቀም በማለት (Doctrine of Territorial Sovereignty/Harmon Doctrine) በመምዘዝ ውኃን በብቸኝነት ልጠቀም አላለችም። ይልቁንም ውኃው የጋራችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ልማት የአልቦ ድምር ውጤት ሳይሆን ሌሎችን በተለይም ጎረቤት አገሮች በሚጠቅም ሁኔታ የጋራ ተጠቃሚነትን ዕውን የሚያደርግ መሆን እንዳለበት በማመን፣ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ ዲፕሎማሲዋን እየመራች ትገኛለች።
አገራችን ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿ ብሎም የዓለም የጋራ ፀጥታና ደኅንነት የሚረጋገጠው በጋራ ለጋራ ስንሠራ ነው የሚል የማይናወጥ ዲፕሎማሲያዊ አቋም አላት። በዚህም ምክንያት የተመድና የአፍሪካ ኅብረት መሥራች አባል ነች፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል፣ የተለያዩ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች አባል፣ በተለያዩ የሰላም ማስከበር ተልኮዎች በግንባር ቀደምትነት ትሠለፋለች። በተመድና በአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ተልኮዎች ከፍተኛ የሆነ መስዋትነትን ከፍላለች፡፡ ለዓለም ሰላም ኃላፊነቷን ተወጥታለች፣ በመወጣት ላይ ትገኛለች። በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን፣በ ደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ በተደረጉ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልኮዎችን በኃላፊነት መንፈስ ፈጽማለች። በአሁኑ ጊዜ 8,321 ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን፣ ፖሊሶችንና ወታደራዊ ባለሙያዎችን ለዓለም የጋራ ሰላም በማሰማራት ከዓለም በቀዳሚነት ትጠቀሳለች።
ለማጠቃለል ያህል አገራችን ኢትዮጵያ ይህንን ሁሉ እያደረገች ከምንም በላይ የውስጥ ሰለማ፣ መረጋጋትና ጥንካሬ አንዲት አገር በውጭ የሚኖራትን የዲፕሎማሲ ተክለ ሰውነት የሚወስን መሆኑን በመገንዘብ የሚደረጉ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ይኼንኑ ለማምጣት ያለሙ ናቸው። የውስጥ ሰላምና መረጋጋትና ጥንካሬ ሊመጣ የሚችለው ዲሞክራሲና የዲሞክራሲ ሥርዓት ሲገነባና ፍሐዊና ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሀብት ልማት ሲሰፍን መሆኑን ይረዳል። ልማትና ዴሞክራሲ የማንንም ብሔራዊ ጥቅም የማይጎዱ ይልቁንም የጋራ ተጠቃሚነት የሚያሰፍን መሆኑን በዲፕሎማሲና በተግባር ማሳየት በመቻሏ፣ በሕዝቦች መካከል የጋራ መግባባትን በአንፃራዊነትም ቢሆን በመገንባቷ፣ አገሪቱ ያላትን ተነፃፃሪ ጥቅም (Comparative Advantage) ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢንቨስተሮችን መሳብ በመቻሏ ይህም ለምጣኔ ሀብት ጡንቻ መጎልበት አስተዋጽኦ በማድረጉ፣ በተግባር የተፈተነ አገር ወዳድ የጦር ኃይልና ደህንነት ያላት አገር በመሆኗ፣ ጥብቅ ዲስፕሊን፣ ታታሪነትና የአገር ፍቅር ያለው ሕዝብ ባለቤት በመሆኗ፣ በዲፕሎማሲ የካበተ ልምድ ካላቸው የቀጣናው አገሮች አንዷ በመሆኗ ምክንያት ዲፕሎማሲያችን በቀጣናዊ ቀውስ ውስጥ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በቅቷል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በዲፕሎማሲና በዓለም አቀፍ ግንኙነት የማስተርስ ዲግሪ ሲኖራቸው፣ የተለያዩ ጽሑፎችን በዓለም አቀፍ ጆርናሎችና በአገር ውስጥ በሚታተሙ ጋዜጦች አውጥተዋል፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው yohannes.mofa@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
