በወልዴ በፍርዱ
ድሮ ድሮ ስለ ሥነ ምግባር ለእኛ አገር ሰዎች መናገር እንደ መቀለድ ይቆጠር ነበር፡፡ ለምን? ሕዝባችን ሳይማር በሥነ ምግባር የተካነ ነው፡፡ አርሶ አደሩ በሥነ ምግባር የተካነ ነው፡፡ ሐኪም የሕክምና ትምህርት ቤት ከመግባቱ በፊት የሕክምና ሥነ ምግባርን ያውቀዋል፡፡ ነጋዴው የገዛውን ዕቃ በአግባቡ ሸጦ ማትረፍ እንዳለበትና የንግድን ሥነ ምግባርን ያውቀዋል፡፡ ከዚህ አለፍ ብለን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተማሪን ሥነ ምግባር ያውቁታል፡፡ ስለእኛ አገር ሥነ ምግባርና ስለእንግዳ መስተንግዶ መናገር ይባስ ብሎ ማስተማር ‹ለእናቷ ምጥ አስተማረች› እንደ ማለት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ስለመልካም አስተዳደር ማስተማር በተመሳሳይ እንደዚያው ነው፡፡
ታዲያ ዛሬ የቅቤ ነጋዴው ሙዝ መቀላቀልን፣ የጤፍ ነጋዴውና አርሶ አደሩ ጭምር አፈር ቀላቅሎ መሸጥን፣ የእንጀራ ነጋዴው ጄሶና ሰጋቱራ ቀይጦ መሸጥን ከየት አመጡት? በእኔ እምነት በቤተሰብ ላይ መልካም ዘር አለመዝራታችን ነው፡፡ ሰው ጤፍ ዘርቶ ባቄላ ለማጨድ ይጠብቃል እንዴ? አጭዳለሁ ብሎ ከጠበቀ ምን ይባላል? የዋህ አይደለም ይልቅስ ሞኝ ነው፡፡ ያልዘራነውን ከትምህርት ቤትና ከመንግሥት መልካም ሥነ ምግባር መጠበቅ እውነቴን እላችኋለሁ የማይጥል ዝናብን ሁልጊዜ ከደመና እንደ መጠበቅ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ብዙ ሰዎች እንዲህ ይላሉ፡፡ “ተማሪዎች ተበላሽተዋል፣ ትምህርት ቤቶች ተበላሽተዋል፣ መንግሥትም ተበላሽቷል፣ ምን ይሻለናል?” ይላሉ፡፡ አይ የዋሆች? የእነዚህ ሁሉ ምንጭ ማን ሆነና? አስተማሪው ከየት መጣ? የመንግሥት ሥልጣን ላይ የወጣው ሰውዬ ባህሪውን ከየት ይዞት መጣ? እነዚህ ሁሉ ቦታዎች ለሕዝብ መታነፅ አስተዋጽኦ የላቸውም ማለቴ አይደለም፡፡ የችግሩ ዋና መንስዔ የቤተሰብ መዛባትና መፈረካከስ ነው፡፡
ለዚህ ማሳያው በአንድ ቤት ውስጥ በቀን ቤተሰቡ ስንት ጊዜ አብሮ በገበታ ይመገባል? ባል፣ ሚስትና ልጆች በቀን ስንት ጊዜ ይነጋገራሉ? በተቃራኒው ብዙ የቤተሰብ አባል ማታ ገብቶ ምንም ሳያወራ፣ እራት ሳይበላ እንደ ሆቴል አልጋ ገብቶ ይተኛል፡፡ ማንም የማንንም መብት መንካት የለበትም በሚል ታሳቢ ይተኛል፡፡ ጠዋት ተነስቶ ወደሚቀጥለው ሥራ ይሄዳል፣ አለቀ፡፡ እንግዲህ ይህ ባለበት ነባራዊ ሁኔታ በቤተሰብ ላይ የሚታየውን አስከፊ የሥነ ምግባር ብልሹነት እያንዳንዱ ሰው በየደረሰበት ቦታ ‹ዛሬ ምን ትምህርት ቤት አለ? ዛሬ ምን የሚያስተምር ሃይማኖት አለ? ዛሬ ምን የመንግሥት ባለሥልጣን አለ?› አንተስ በቤተሰብህ ላይ ምን ሠርተሃል? ሥልጣን ላይ ያለው በሥነ ምግባር የባለገው ልጅ የማን ነው? ትምህርት ቤት የሚያስተምረው ልጅ የማን ነው? ከዩኒቨርሲቲ ወጥታ እንደፈለጋት የምትፋንነው ልጅ የማናት? ከትዳር ውጭ ልጅ ወልዳ በቤትህ ውስጥ ያለችው የማን ልጅ ናት? እንጀራውን ጄሶ ቀይጦ ሸጦ ያበላን የማን ልጅ ነው? የእኔ፣ የአንተና የአንቺ አይደሉምን?
ድሮ አንድ ታሪክ ሰምቻለሁ፡፡ አንድ እርጎ በኩባያ እየጠጣ ያለ ሰው እርጎው በፂሙ ላይ ይንጠባጠባል አሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እሱው ሰውዬ እንዲህ አለ፡፡ ‹‹ምንድነው እዚህ አካባቢ የሚሸተው?›› ትንሽም እንደሄደም ሌሎች ሰዎች መሀል ሆኖ፣ ‹‹ምንድነው እዚህ የሚሸተው? በመጨረሻ አገሩ ሁሉ ይሸታል ማለት ነው?›› አለ ይባላል፡፡ ሽታውን ያመጣው ግን ማነው? የራሱ ፂም ነው፡፡ ለምን እርጎውን ከጠጣ በኋላ ባለመታጠቡ ነው፡፡ አሁን እኮ የችግሮችን ምንጭ ማየት የተሳነበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ በቀጣይ ዓመታት እኮ ይህንን እንለምደውና የጄሶውን እንጀራ ስንበላ እንዲህ እንላለን፡፡ “በል ብላ ያለው ጄሶ ትንሽ ነው፤” በሌላ ቀን ደግሞ እንዲህ እንላለን፡፡ “በል ብላ አፈሩ ብዙም አይደለም 50 በመቶ ነው፤” ከትዳር ውጭ የኮሌጅ ተማሪ ልጅ ወልዳ ከማፈርና ከመደንገጥ ይልቅ እንዲህ ይባል ይሆናል፡፡ “የእኔ ልጅ ሁለተኛ ሴሚስተር ከመድረሷ በፊት አንድ ልጅ ወለደች? የአንተስ ልጅ?” ሌላው ደግሞ፣ ‹‹የእኔ አልወለደችም ምናልባት በሚቀጥለው ሴሚስተር ይላል፡፡ ስለልብስ መግዛት ሲወራ አባወራው እንዲህ ይል ይሆናል፡፡ “ለሴት ልጆቼ ሁለቱንም ጡቶች የሚያሳይ አሪፍ የአውሮፓ ልብስ ገዛሁላቸው፣ አንተስ?” ሌላው የቤተሰብ አባወራ ሲመልስ፣ “የእኔ ልጆች ከአንተ ለየት የሚሉት፣ ራሳቸው የገዙት ልብስ ከአንተ ጋር አንድ ዓይነት ሆኖ ልዩነቱ ከኋላ በደንብ ትከሻና ባታቸውን ያሳያል አሪፍ ነው፡፡››
እንግዲህ ቀጣዩን የቤተሰብ ሁኔታ እየነገርኳችሁ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ በቤተሰብ ላይ መሥራት አለብን፡፡ ቀይ መብራት እየበራ ነው፡፡ ምልክቱ በደንብ እየታየ ነው፡፡ ቀጣዩ ማኅበረሰብ ትልቅ አደጋ እያንዣበበት ነው፡፡ ቤተሰብ ዛሬ ልጆቹን በደንብ አድርጎ ይቀፍድዳቸው እያልኩ አይደለም፡፡ ዛሬ ልጆች ፈጽሞ ቴሌቪዥን እንዳይመለከቱ እያልኩ አይደለም፡፡ ይልቁንም ቤተሰብ ወደ ድሮአችንና ማንነታችን እንመለስ፡፡ ለምን? ቤተሰብ የሥነ ምግባርና የመልካም አስተዳደር ምንጭ ነውና፡፡ ይህን ካላደረግን ከጥቂት ዓመት በኋላ የዘራነውን እናገኘዋለን፡፡ ማግኘት ብቻ አይደለም በደንብ እናጭዳለን፡፡ ያልዘራነውን መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡
በአሜሪካ በአንድ ቤተሰብ ላይ ሲጠና እንደዚህ ብሎ ታሰበ፡፡ “አንዱ ልጅ ሐኪም፣ አንዱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ አንዱ ደግሞ አውሮፕላን አብራሪ፡፡ ሁሉም በትልቅ ቦታ ላይ የተቀመጡ ናቸው፡፡ ታዲያ የእነዚህ ቤተሰብ እስከ ታችኛው እርከን ሲጠና፣ የሁሉም የልጅ ልጆች በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው፡፡ በተቃራኒው አንድ የማፍያ ቡድን ቤተሰብ ሲጠና እስከ ታችኛው እርከን ያሉ የልጅ ልጆች ወሮበላ፣ ገዳዮችና የማይረቡ እንደሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ይህ ምን ያሳየናል? ማን ኃላፊነቱን ይውሰድ? ብዙ ጊዜ በኤሌክትሪክ የሞቀ ውኃ ውስጥ የምትገባ እንቁራሪት እስከ ሞቷ ድረስ ከለብታ እስከ ሙቀት ምንም አይመስላትም፡፡ መጨረሻ ምንም ብትለማመድ የኤሌክትሪክ ኃይሉ እየጨመረ ስለሚሄድ እኛ እንደምትሞት እናውቃለን፡፡ ለእሷ ግን ያው ነው፡፡ ብትመከርም ያለፈበትና የፋራ ምክር ነው፡፡ ሕዝቤ ሆይ ከግሎባይላዜሽን የምንጠቀምበት ነገር አለ፣ ከዓለም አቀፍ ቴሌቪዥን የምንወስደው ጠቃሚ ነገር አለ የሚለው ጉዳይ ሁሉ አይጠቅምም፡፡ ቤተሰብ ለልጆቹ መምረጥ አለበት፡፡ የጥንቶቹ አባቶቻችን በቤተሰብ አስተዳደግ ዙሪያ በአብዛኛው ተሳክቶላቸዋል፡፡ አሁን በትልቅ ደረጃ በአገርና በውጭ ያለው ሕዝባችን በዚያኛው የቤተሰብ አስተዳደግ ዘመን የነበረ ነው፡፡ የቤተሰብ ኃላፊ ማውራት ብቻ ሳይሆን ለልጆቹ ኃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡ በቤት ውስጥ ለሚስቱና ለልጆቹ ክብር የማይሰጥ አባወራ ስለመልካም አስተዳደር ቢያወራ አይገባንም፡፡ ማታ ማታ ሚስቱን እየደበደበ በአደባባይ ትንሽ ሥልጣን ሲያገኝ፣ ‹‹እባካችሁ የሴቶችን እኩልነትና ተጠቃሚነት ሁላችንም ማረጋገጥ አለብን፤›› ቢል እሱን የሚውቁ ሰዎች፣ ‹አይ ግብዝ አንተ ያልኖርከውን ኑሮ ትደሰኩራለህ› ይላሉ፡፡
በጥሩ ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ልጅ ምን ዓይነት ትዳር ይኖረዋል ብላችሁ ታስባላችሁ? ለምሳሌ በዓመት 1,000 ሰዎች ትልቅ ወጪ አውጥተው ደግሰው ይጋቡና በዓመቱ መጨረሻ እነዚሁ ሰዎች ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ሆነው ይፋታሉ፡፡ ለምንድነው ብላችሁ አስባችኋል? እውነቱን ለመናገር 90 በመቶ የፍርድ ቤት ክሶች የትዳር ጉዳይ አይደሉምን? በጥሩ ቤተሰብ ውስጥ ማደግ ለሥልጣን እንደ መሥፈርት ቢሆን መታደል አይደለምን? ዞሮ ዞሮ ነገር ቢያበዙት በአህያ አይጫንም ይላል የአገሬ ሰው፡፡ ስለሌላው ተወት አድርገን ስለቤተሰብ እንነጋገር፡፡ የፖለቲካ ጉዳይ ትርፍ የለውም፡፡ ከአንተ ጋር ብዙ የሚቆየው በሰውም በፈጣሪም የሚያስጠይቀው የቤተሰብ ጉዳይ ስለሆነ አሁኑኑ አስቡበት፡፡ የሥነ ምግባር አስተማሪ፣ የመልካም አስተዳደር ባለሙያ ለእናተ ቤተሰብ ምንም አያመጣም፡፡ ይልቁንም ዛሬውኑ እንደ ባለሙያ ልንገራችሁ፡፡ የመልካም አስተዳደርና የሥነ ምግባር መዳበር ምንጩ እኛ ነን፡፡ የእናንተ ቤት ቀይ መብራት እያሳየ ነው፣ አስቡበት፡፡ በጥሩ ሥነ ምግባር ያላደገ ሰው ሐኪም ቢሆን፣ ነጋዴ ቢሆን፣ ከንቲባ ቢሆን ከእነዚህ መልካም ነገር መጠበቅ ከእንክርዳድ ስንዴ እንደ መጠበቅ አይሆንምን? እህቴና ወንድሜ የቤተሰብ ጉዳይ ከሥራችን እያመለጠ ነው፡፡ ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ላይ መሠራት ያለበትን የሥነ ምግባር ትምህርት በ20 ዓመት ይጀመር ብንል አደገኛ ቀልድ ነው፡፡ ስለዚህ ቀይ መብራት በርቷልና አስቡበት፡፡ መልካም ሥነ ምግባር ከየትም አይመጣ፡፡ ግን ከቤተሰብ ብቻ፡፡
ከአዘጋጁ፡ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው woldebefirdu@yahoo.comማግኘት ይቻላል፡፡
