Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

አብረን ካልጮኽን አብረን እንሰምጣለን

$
0
0

በበቃኸኝ አንተነህ

ትውልድ ከሞተ አገር ያለጥርጥር ትሞታለች፡፡ የትውልድ ሞት በተለያየ ነገር ይገለጻል፡፡ በአደንዛዥ ዕፅ፣ በጫት፣ በአልኮልና በዝሙት የናወዘ ትውልድ አገር ብትወረር፣ ብትሸጥ ግድ አይኖረውም፡፡ ሱሪውን ቢያወልቁበት ወይም መንገድ ላይ ቀሚሷን ቢገልቡት ደንታ ላይሰጠው ወይም ላይሰጣት ይችላል፡፡ በሐሽሽ የናወዘ ትውልድ ወንጀል ለመፈጸም እጅግ ቅርብ ነው፡፡ አገርን ከሚያፈራርስ የጥፋት ቡድን (አሸባሪ) አድርግ የተባለውን ተልዕኮ ሁሉ ከመሸከምና ከመፈጸም ወደኋላ  አይልም፡፡

በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በአንዳንድ የክልል ከተሞች ለጆሮ የሚሰቀጥጥ፣ ሰው መሆናችን እስክንጠራጠር ድረስ የሚደመጡ ተደጋጋሚ ወንጀሎች ከዕለት ወደ ዕለት እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በጠራራ ፀሐይ ‹ካላፈቀርሽኝ› ብሎ በጩቤ ወግቶ የሰውን ክቡር ሕይወት ማጥፋት፣ አሲድ በፊት ላይ መድፋት፣ የትዳር ጓደኛን በጭካኔ መግደልና በድን አካሏን መቆራረጥ፣ ልጅ ከእናት ጋር ተባብሮ አባትን መገደል ወይም እናትን መግደል፣ ወንድም በወንድሙ ላይ አነጣጥሮ ተኩሶ መግደል፣ ክህደት፣ ስርቆት የመሳሰሉ የአንድ ማኅበረሰብ (አገር) ማኅበራዊ ህፀፆች የማኅበረሰብ ሕመም (Social Ills) ዓብይ ምልክቶች ናቸው፡፡

የዛሬን አያድርገውና ድሮ እያንዳንዱ የማኅበረሰብ አባል አንዱ ለአንዱ የሚኖር ነበር፡፡የአንዱ ጉዳት ልክ እንደ ራሱ ጉዳት አድርጎ ይመለከት ነበር፡፡ በእሱ ላይ እንዳይፈጸም የሚፈልገውን ነገር በሌሎች ላይ አይሞክረውም ነበር፡፡ አንድ የጎረቤት ልጅ ማኅበረሰቡ የማይቀበለውን ነገር ሲፈጽም ያየ ሌላ ጎረቤት ይህን ተግባር የፈጸመውን ግለሰብ ወይም ልጅ የመገሰፅና የመቅጣት ማኅበራዊ ኃላፊነት ነበረበት፡፡ ምክንያቱም የጎረቤት ልጅ ሥነ ምግባር ከጎደለው ለአካባቢው ጠንቅ እንደሆነ ሁሉም ስለሚረዳ፣ ልጆቹን በሥነ ሥርዓት ለማሳደግ ሁሉም ኃላፊነት ነበረበት፡፡ እኔን ወላጆቼ ብቻ አይደለም ያሳደጉኝ፡፡ ጎረቤቶቼ፣ አልፎ ሂያጅ መንገደኛ ሳይቀር በልጆች መልካም ሥነ ምግባር ሁሉም አስተዋጽኦ ነበርው፡፡ ጥፋቱን የፈጸመው አዋቂ ሰው ከሆነም በማኅበረሰቡ እንዲመከር ይደረጋል፣ ይወገዛል፣ አልመለስም ካለም ከማንኛውም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲገለል ይደረጋል፡፡ እነኚህ ሁሉ ድሮ የነበሩ የማኅበረሰብ እሴቶች ናቸው፡፡

ዛሬ ያ ሁሉ ተቀይሯል፡፡ ጎረቤት አይደለም አባት ወይም እናት፣ ወይም ታላቅ ታናሽን መቅጣት በፍጹም አይችልም፡፡ መቅጣት ስል በጥሬ ትርጉሙ መደብደብ (አካላዊ ጉዳት) ማድረስ እንዳልሆነ ይያዝልኝ፡፡ የዚህ ሁሉ ውጤቱ ትውልዱን ጥፋት በቀላሉ እንዲፈጽም አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ግብረ ገብ ከጠፋ ውሎ አድሯል፡፡ ወላጅና ልጅ በአንድ ላይ የወሲብ ፊልም አብረው ማየት ጀምረዋል፡፡ እናት ወይም አባት ልጅን እንዲያጠና፣ ለትምህርቱና ለሥነ ምግባሩ አርዓያ ከመሆን ይልቅ ከዚህ በተቃራኒ ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ በአንድ ቻናል የሚተላለፍ ፊልም ከልጆች ይልቅ የወላጆችን አዕምሮ የበለጠ አደንዝዞታል፡፡

ለዚህች መጣጥፌ መነሻ የሆነኝ በአዲስ አበባ አንዳንድ የግልም ሆነ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች እየታየ ያለው ሥርዓት አልበኝነትና ጋጠ ወጥነት ይህችን አገር ወደ ጥፋት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ሊከታት እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ ዛሬ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት በአዲስ አበባ ምድር ነውር መሆኑ እየቀረ ይመስላል፡፡ ኧረ ክልል ድረስ አልፎ ሄዷል፡፡ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ሴት ልጆች የጎንዮሽ የገቢ ምንጫቸው (Sideline Income) ሴተኛ  አዳሪነት ከሆነና ሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎች ከጎበኘ ውሎ አድሯል፡፡

በተለይ በተገቢው መንገድ ሳይሆን የሕዝብን ደምና አጥንት ግጠው (በሙስና) ሀብታም የሆኑ የአንዳንድ ግለሰብ ልጆች ገንዘብ የሁሉም ነገር መጨረሻና የገነት በር ጭምር መቆጣጠሪያ አድርገው በማየት፣ ለልጆች ሥነ ምግባር መበላሸት የእነዚህ ‹‹የገንዘብ ሀብታም ነገር ግን የሥነ ምግባር ደሃ›› ቤተሰብ ልጆች ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ገንዘብ ለልጆቻቸው  ለምን እንደሚሰጧቸውና ለምን አገልግሎት እንደሚያውሉት ፈጽሞ ማወቅ አይፈልጉም፡፡ ገንዘብ ለልጆቻቸው በመርጨት ከኃጥያታቸው የነፁ ይመስላቸዋል፡፡ ግን ሌላ ኃጢያት በገንዘቡ እየተሠራ እንደሆን አይረዱም፡፡ ቢረዱም ግድ የላቸው፡፡

በዚህች የጉድ ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች የሚደረገውን ከሞራል፣ ከግብረ ገብና ከሃይማኖታዊ አስምህሮ የራቀ ድርጊት ማየት እጅግ ቀላል እየሆነ መጥቷል፡፡ ከእኔ መሥሪያ ቤት አጠገብ አንበሳ ጋራዥ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ የግል ትምህርት ቤት አለ፡፡ እዚህ ትምህርት ቤት የሚማሩ የመክፈል አቅማቸው ደህና የሆኑ ቤተሰብ ልጆች ናቸው፡፡ ከዚህ ትምህርት ቤት በቅርብ ርቀት  አንድ ቁርስ ቤትና የመጠጥ ግሮሰሪ አለች፡፡ የዚህ ትምህርት ቤት ሴት ተማሪዎች ጠዋት ጠዋት ዩኒፎርማቸውን እንደለበሱ (ምንም ኃፍረት ሳይሰማቸውና ለለበሱት የተማሪ ዩኒፎርም ሳይጨነቁ) ከዚች ቁርስና መጠጥ (መሸታ ቤት ልበለው) በመምጣት ደረቅ ጅን ጠጥተው ወደ ክፍል ይገባሉ፡፡ ቁጭ ብለው ለመጠጣት ከረፈዳባቸው ደግሞ በውኃ መያዣ ኮዳ (የውኃ ፕላስቲክ) ደረቅ ጅን አስቀድተው ወደ ትምህርት ቤት ይዘው መግባት የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡

ይህን ለሚያይና አዕምሮ ላለው ሰው ወዴት እየሄድን እንደሆን መገመት ቀላል ነው፡፡ ይህ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹን በኑባቤ (ቲዎሪ) ብቻ ቆዝሮ ከሚያወጣቸው ይልቅ ምን አለ ጭንቅላታቸው ላይ ትንሽ ሥራ ቢሠራ? ይህ ትምህርት ቤት ልጆቹን እንደ ፈረንጅ እንግሊዝኛ አቀላጥፈው እንዲናገሩ ከማድረግ ባለፈ አረቄ ይዘው ወደ ትምህርት ቤቱ እንዳይገቡና ሰክረው አስተማሪም ተማሪም እንዳይበጠብጡ ምን ሥራ እየሠራ ነው? ወላጆች የልጆችን አዋዋል ከትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን ይከታተላሉ? ይህ ትምህርት ቤት እነዚህን ልጆች አስተምሮ ገንዘብ ከሚሰበሰብ ይልቅ ለምን ተዘግቶ ለአገርና ለወገን በሚጠቅም  ሌላ ሥራ ላይ ቢሰማራስ? ወላጆች ደግሞ ለማይጠቅሙ ልጆች ገንዘብ ከሚያጠፉ ለነዳያን ይህን ገንዘብ ሰጥተው የገነት በራቸውን ቢያስከፍቱ ምን አለበት?

በዚህ ትምህርት ቤት የማስተምረው ልጅም ሆነ የሚማር የማውቀው የዘመድ ልጅ የለኝም፡፡ ከትምህርት ቤቱ ጋርም የተለየ ቂምም ሆነ ሌላ ግንኙነት የለኝም፡፡ የእነዚህ ልጆች መበላሸት ነገ በማኅበረሰቡ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ቀውስ እጅግ ያሳዝነኛል፡፡ የእነዚህን ተማሪዎች ሥነ ምግባር የጎደለው ትርዒት ማየት የፈለገ ሰው ቁርስ ቤቷን ከሰኞ እስከ ዓርብ ሄዶ ቢጎበኝ ድርጊቱን መታዘብ ይችላል፡፡ ማን ያውቃል ጠጥተው የሚያሸክርክሩ ለትውልድ የማይጨነቁ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር፣ በአሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ የአልኮል ምርመራ እንደሚደረገው በትምህርት ቤቶችም ይህ የአልኮል መመርመሪያ መሣሪያ (Alcohol Detector) በሒደት ማስፈለጉ የሚቀር አይመስለኝም፡፡

ሌላው ማኅበረሰብስ እነዚህ ወጣት ሴት ልጆች ዩኒፎርም ለብሰው አረቄ ሲጠጡ ሲያይ ለምን አይገስፅም? አረቄ የሚሸጥላቸው መሸታ ቤትስ ለእነዚህ ክፉና በጎውን በቅጡ ላለዩ ሴት ልጆች አረቄ ሸጦ ከሚያገኘው ሽርፍራፊ ገንዘብ ይልቅ ለትውልድ ሞት ለምን ደንታ ቢስ ሆነ? መንግሥትስ ቢሆን የአረቄ ወይም የአልኮል መሸጫና መጠጫ ሰዓት ሥርዓት ለምን አያበጅም? የወጣት ጥፋተኛነት (Juvenile Delinquency) አንዱና ምንጩ ሥርዓት ያጣው የአልኮል መጠጥ፣ ጫትና ሐሽሽ ያስከተለው ውጤት ነው፡፡

የአንድ አገር የልማት አውታርንና በመንግሥት ላይ የሚደረግን ተቃውሞ በቅጡ የማይለይ ትውልድ ሊያስከትል የሚችለውን ጥፋት ባለፈው ዓመት በዓይናችን በብረቱ ዓይተናል፡፡ መንግሥትን በመቃወም ሰበብ ለአገር ልማት  የተገነቡ የልማት አውታሮች በአንድ ላይ ሲወድሙ ተመልክተናል፡፡

እነዚህ ልጆች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሚያደርሱት ሕገወጥ ተግባር እኔን አይነካኝም ማለት አይቻልም፡፡ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በጨካኝ የወጣት ጥፋተኛ በጩቤ ተወግታ የሞተችው ልጅ የሁላችንም ልጅ፣ የሁላችንም እህት ናት፡፡ በተማሪ ሀና ላይ የተፈጸመው በቡድን መደፈር የተበላሹ የማኅበረሰቡ አባላት የፈጠሩት ሰቆቃ ነው፡፡ ዛሬ ዝምታውን መስበር ካልቻልን ነገ የእያንዳንዳችን ቤት ተራ በተራ መንኳኳቱ የማይቀር ነው፣ ጊዜውም ሩቅ አይሆንም፡፡ ዛሬ በሚደረግ ከሥነ ምግባር የወጣ ተግባር አብረን በመጮህና በመከላከል ካላስቆምነው አብረን ወደ አዘቅት  እንደምንገባ ጥርጥር የለውም፡፡

'ሳይቃጠል በቅጠል'አልልም፡፡ ምክንያቱም ቃጠሎውን ከዚህም ከዚያም እያየን ነውና፡፡ ይህን ቃጠሎ በጋራ ማጥፋት የግድ ይለናል፡፡ በሚቀጥለው ጹሑፌ በሌላ የግል ትምህርት ቤት የተፈጸመውን የተማሪዎችን አስነዋሪ ተግባር፣ ይህንን የተማሪዎች አስነዋሪ ተግባር በገሰፀ የትምህርት ቤቱ መምህር ላይ የተማሪዎች ወላጆችና የትምህርት ቤቱ አመራር በእሳት ላይ ቤንዚን ዓይነት ዕርምጃ አቀርብላችኋለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው bekahegn2016@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles