Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

ተደምሮ ዜሮ - አገርን በዘመቻ የመምራት ጥበብና ውጤቱ

$
0
0

በብርሃኑ ዘለቀ

      ሪፖርተርን ጨምሮ ከተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘመቻ ሊጀመር መሆኑን ስሰማ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ራሴን እንድጠይቅና ከቅርብ ጓደኞቼ ጋር ውይይት እንዳደርግ አስገድዶኛል፡፡ በዓለም ላይ እንደኛ ሁልጊዜ ሥራን በዘመቻ የሚሠራ አገር ይኖር ይሆን?

አገርን በዘመቻ የመምራት ውድድር ቢኖር ኢትዮጵያን የሚስተካከላት አይኖርም ብል እያጋነንኩ አይደለም፡፡ እንዲያውም ዘመቻዎችን መዝግቦና ቀምሮ የሚያዘጋጅ ተቋም ቢኖረን ኖሮ፣ የዘመቻዎችን ተሞክሮ ለሌሎች ጥሩ ማስተማሪያ ሳይሆን የውድቀት ማስተካከያ የሚሆን ምርጥ ትምህርት ይሆን ነበር እላለሁ፡፡

አገራችን ጦብያ ለዘመቻ አዲስ ባትሆንም በእኛ ዕድሜ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ብቻ እንኳን ስንት ዘመቻዎች መጥተው ስንት ዘመቻዎች ተፈራረቁ? የውኃ ማቆር ዘመቻ፣ የጤና ልማት ሠራዊት ግንባታ ዘመቻ፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ዘመቻ፣ የግብርና ምርታማነት ማሳደግ ዘመቻ፣ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዘመቻ፣ የመልካም አስተዳደር ማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነት ማክሰም ዘመቻ፣ የሲቪል ሰርቪስ አሠራር ማሻሻያ ዘመቻ፣ የፀረ ሙስና ዘመቻ የጥልቅ ተሃድሶ ዘመቻ… ዘመቻ… ዘመቻ… በኢትዮጵያ ገዥ መንግሥታት ይመጣሉ ይሄዳሉ፡፡ ዘመቻ ግን ለዘለዓለም ትኖራለች፡፡

አንድ ወዳጄ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕይወት ሠልፍ ናት ብሎኝ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ እንዲህ እላለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕይወት ዘመቻ ናት፡፡ እስኪ ያለ ዘመቻ የሚሠራ አንድ ነገር ጥቀሱልኝ?

ስለዘመቻ ሥራዎች ስናስብ የሚከተሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች መጠየቅ የግድ ይሆናል፡፡ ሥራን በዘመቻ ስንል ምን ማለታችን ነው? ሥራን በዘመቻ መሥራት ለምን አስፈለገ? ከዘመቻ የተሻለ የአሠራር ዘዴ መጠቀም አይቻልምን? እንዲያው ለመሆኑ የዘመቻ ሥራዎች ውጤታማ ናቸውን? የእስከ ዛሬ ዘመቻዎች ምን ያስተምሩናል? ወደፊትስ እንደዚህ መቀጠል አለብን?

ለእነዚህና የመሳሰሉት ቁልፍ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስና ጥልቅ ሳይንሳዊ ማብራሪያ መፈለግና ግንዛቤን ማሳደግ ለአገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የመኖርና ያለመኖርን ያህል እጅግ ወሳኝ ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የዚች አጭር ጽሑፍ ዓላማም በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ጥቂት ሐሳብ በመወርወር፣ ሌሎች ምሁራንና ባለሙያዎች ሐሳባቸውን እንዲሰነዝሩ በማነሳሳት ውይይት የምናደርግበት መድረክ መፍጠር ነው፡፡

ሥራን በዘመቻ ስንል ምን ማለታችን ነው?

እንደተገኘበት ቦታና ሁኔታ ብቻ ሳይሆን እንደ የሥራ ዘርፉ ዓይነት ሊለያይ ቢችልም፣ በአጠቃላይ ሥራን በዘመቻ ማለት በአንድ ጉዳይ ላይ ያላግባብ ወደኋላ መቅረታችንን በምንገነዘብበት ወቅት ያጠፋነውን ጊዜ ለማካካስና በፍጥነት ወደ ምንፈልግበት ግብ ለመድረስና ስኬታማ ለመሆን፣ በስሜት ሲልም በፍርኃትና በጉጉት የሚቀየስ ሥራን የመተግበሪያ መንገድ ነው ብሎ በግርድፉ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ በአገራችን የተለያዩ ዘመቻዎች በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፎች ሲካሄዱ ኖረዋል፣ አሁንም መካሄዳቸውን ቀጥለዋል፡፡

በሩቅ አሳቢዎች ህልምና ሐሳብ ወይም በረጅም ጊዜ ዕቅድ ሳይሆን በእሳት ማጥፋት ወከባና በሕመም ማስታገሻ መድኃኒት የምትኖረው አገራችን፣ ዘንድሮም በቀውስ ዑደት መሽከርከሯን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ ማነህ ባለሳምንት ተብሎ ሲያበቃ አዲስ መጤው የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ በዘመቻ ፕሮፓጋንዳ በይፋ ሊጀመር ፊሽካው ተነፍቷል፡፡ ያው እንደተለመደው ተጠንቶና ታስቦበት ሳይሆን፣ በጠርምሰህ ንዳውና በጅምላ አስታጥቀው በተደራጀ የአቦ ሰጥ ባህላዊ ዘዴ ብቻ ሳይሆን በደመ ነፍሳዊ የአመራር ጥበብ ታግዞ ሊተገበር ዝግጅቱ ተጠናክሯል፡፡

ይህ ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበና የብክነት ሩጫ መውጫው ያው የተለመደው ነው፡፡ ሌላ ዘመቻ ማስጀመር፣ ሌላ የእሳት ማጥፋት ዘመቻ፡፡ ሁልጊዜ ማለት ይቻላል እነዚህ ዘመቻዎች የሚካሄዱት በመንግሥት አነሳሽነትና ፖለቲካዊ አንድምታ ታጅበው በመሆኑ፣ ዜጎች ፖለቲካዊ ግቡን በማሰብ ቀድመው ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው በማድረግ ከልባቸው ወደ ሥራ እንዳይገቡ በማድረግ ተንገዳግዶ ከመውደቅ አያድነውም፡፡ የአሁኑ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘመቻም ከዚህ ጥርጣሬ ነፃ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ወጣቶቹ ባለፉት ዓመታት የተካሄዱ ተመሳሳይ የጥቃቅንና አነስተኛ ዘመቻ ሥራዎች ላይ የተመለከቱትን አድሎአዊና ኢፍትሐዊ አሠራሮች በማሰብ የሞራል ተነሳሽነታቸው ላይ ተፅዕኖ መፈጠሩ አይቀርም፡፡

የዘመቻ ተፈጥሮዓዊ ባህሪው በጥልቀት የማሰብ ጊዜ አለመስጠቱ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ መነሻው ፍርኃትና ድንጋጤ ስለሆነ ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ፕሮጀክት ማለፍ ያለበትን ሳይንሳዊ ደረጃዎች (የጥናት፣ የማቀድና የአተገባበር ስትራቴጂ መንደፍና በቂ ክትትልና ግምገማ ማድረግ) ሊያልፍ አይችልም፡፡ ሁኔታው ጊዜ አይሰጥም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሥራው የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያስገድድ መሆኑ በተግባር ሒደት ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡

ስለዚህ አብዛኞቹ የዘመቻ ሥራዎች ተጠናቀው ሲገመገሙ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ሲነገር ብንሰማ ሊገርም አይገባም፡፡ በቅርቡ የተከሰቱትን የባቡር ሐዲድ ግንባታ ያለሥራ መቅረትና የስኳር ፕሮጀክቶች የውኃ ሽታ መሆን ለዚህ አባባላችን ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ የባቡር ሐዲድ ግንባታው በበቂ ጥናትና ሌሎች ተያያዥ መሠረተ ልማቶችን ታሳቢ አድርጎ ባለመሠራቱ ነዳጅ እንኳን ከጅቡቲ ማመላለስ ባለመቻሉ (ሠርቶ የሚመልሰው ገንዘብ ባለመኖሩ) አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የዕዳ ክምር እንዲቆለልባት አድርጓል፡፡ በእያንዳንዱ ቀንም ዕዳው ከወለዱ ጋር እየጨመረ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እየሆነብን ይገኛል፡፡    

ሥራን በዘመቻ መሥራት ለምን አስፈለገ?የተሻለ የአሠራር ዘዴ መጠቀም አይቻልምን?

እዚህ ላይ እንዲህ የዘመቻ ሥራ የማይጠቅም ብቻ ሳይሆን የኪሳራ መንገድ ከሆነ ለምን መንግሥታችን ሁሉን ነገር በዘመቻ ካልሠራሁ ይላል? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ለዚህ አጭሩ መልስ ሊሆን የሚችለው የዚህ መንግሥት ተፈጥሯዊ ባህሪው ስለሆነ የሚለው ነው፡፡ ይህ መንግሥት ሲፀነስም ሆነ ሲወለድ ይህንን ባህሪ ተላብሶ ከመሆኑም በላይ፣ ወላጆቹ ያሳደጉትም እንዲህ እንዲሆን አድርገው ነው፡፡

ከላይ እንደጠቀስነው አንድ ሥራን በብቃት አቅዶ በስኬት ለማጠናቀቅ ሳይንሳዊ ዕውቀት ያለው ባለሙያና አመራር ይፈልጋል፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር የሚፈስበት እንዲህ ዓይነት ከባድ ሥራ ይቅርና ለጥቂት የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚቀረፁ ትንንሽ ፕሮጀክቶች እንኳን በስኬት ለማጠናቀቅ መሠረታዊ ግንዛቤ ይጠይቃሉ፡፡ ይህ መንግሥት ደግሞ በግልጽ እንደምናውቀው ብቃትን ሳይሆን ፖለቲካዊ ታማኝነትን ብቻ መሠረት አድርጎ የሚያሠራ በመሆኑ ውጤቱ ያለው ከአሞራ ርግብ እንደ መጠበቅ ነው፡፡ ከላይ እስከታች ባለው የመንግሥት መዋቅር የተሰገሰገው ካድሬ ፖለቲካዊ ቃላትን እያነበነበ ብቻ የሚኖር መሆኑን ራሱ መንግሥት ሳይቀር የሚናገረው ነው፡፡ ስለዚህ ችግሮችን በጊዜው ተረድቶ፣ መሠረታዊ መንስዔያቸውን ተገንዝቦ፣ በአግባቡ አቅዶ ለመፈጸም ብቃቱም ሆነ ተነሳሽነቱ በሌለው ፈጻሚ የተጠቀጠቀ መንግሥት መቼውንም ከዘመቻ ራሱን ሊያድን እንደማይችል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ ሁሉ ነገር በአፍ ላይ ያለ ነው፣ ጊዜውን ጠብቆ አንድ ቀን ይፈነዳል፡፡ ያን ጊዜ እሳቱን ለማጥፋት ወደ እሳት አደጋ መደወል ግድ ነው፡፡ ዘመቻው ተጀመረ፣ ችግሩ ተዳፈነ፣ ሌላ ቦታ ሌላ እሳት እስከሚንቀለቀል የዘመቻ ዑደቱ እንዲህ ይቀጥላል፡፡ ዘመቻ ለጥቂት ለደም መጣጭ ሙሰኞች አመቺ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ዘመቻ ወከባ ነው፣ እሳት ለማጥፋት ጊዜ አይሰጥም፡፡ ይህ ሁኔታ በአንድ ሌሊት ለመክበር ተዘጋጅተውና አሰፍስፈው ፊሽካ እስከሚነፋ ለሚጠብቁ ነቀዞች መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ እነዚህ ደም መጣጭ ሙሰኞች የዚህን ጥቅም መገኛ በርና መስኮት ጠንቅቀው የሚያውቁና መንገዱን የሚያሳዩ ከቀበሌ እስከ ፌደራል መሥሪያ ቤት ኔትወርክ የዘረጉ የሌሊት ወፎች፣ ስለሆኑ ማንም መሰሪ ሥራቸውን እንዳያውቅባቸው ወከባው ይመቻቸዋል፡፡ ሥራቸውን በድንግዝግዝና በጨለማ ለመከወን፡፡ እስኪነጋ ድረስ ፀሐይ እስክትወጣ፡፡

ልምዶቻችን ምን ያስተምሩናል?ለመሆኑ የዘመቻ ሥራዎች ውጤታማ ናቸውን?

ሌላው መሠረታዊ ጥያቄ ይህ ነው? ባለፉት ዓመታት ከተገበርናቸው ዘመቻዎች ምን ያህሉ ውጤታማ ነበሩ? ምን ምን ችግሮች አጋጠሙን? እንዴትስ ተወጣናቸው? ያቀድነውን አሳካን? ወይስ እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ለኪሳራ ተዳረግን? እነዚህ ሒደቶች ምን ትምህርት ይሰጡናል? ቀጣይ ዘመቻዎቻችንን በዚሁ መንገድ ማካሄድ አለብን? ወይስ መሠረታዊ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅብናል? የታሪክ ምሁራን “ከስህተቱ ያልተማረ ሊደግመው ተዘጋጅቷል የሚል አስተማሪ አባባል አላቸው፡፡ ከልምዳችን ተምረን ካልተስተካከልን ነገ በተመሳሳይ ኪሳራ እንደማንመታ መተማመኛ የለንም፡፡

በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በርካታ ዘመቻዎች ቢካሄዱም፣ ሒደታቸውንና ውጤታቸውን መርምሮ ሪፖርት ማቅረብ ፖለቲካዊ ትርጉም ስላለው እንደ ሞት መንገድ ይቆጠራል፡፡ በመሆኑም ትክክለኛ አኃዛዊ ማስረጃ ለማቅረብ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ የቀበሌና የወረዳ ሪፖርቶች የካድሬዎች መገምገሚያ ነጥቦች ስለሆኑ በውሸት የተሞሉ መረጃዎች ናቸው፡፡ መሬት ላይ ያለውን ሳይሆን ሹመቱን የሰጧቸው አለቆቻቸው መስማት የሚፈልጉትን ብቻ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡

አንድ የማይካድ ሀቅ ግን አለ፡፡ አብዛኞቹ የዘመቻ ሥራዎች የሚጠበቅባቸውን ለውጥ ሩቡን እንኳን አላመጡም፡፡ ተዘርዝረው የማያልቁ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

አዲሱ ዘመቻስ ዕጣ ፈንታው ምን ይሆናል?

እንደ ተለመደው የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘመቻ መነሻው መንግሥት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሱ አውዳሚ አመፆችን ተከትሎ መንግሥት ችግሩን ተረድቸዋለሁ አለ፡፡ ወጣቶች ተነስተውብኛል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ቢሆንም፣ እሱን በጥልቅ ተሃድሶ እየታገልኩ በተጓዳኝ እነዚህን ጉልበተኛና ንዴታም ወጣቶችን ማስታገስ የሚያስችል የሥራ ዕድል እፈጥራለሁ፡፡ የገንዘብ ችግር የለብኝም፡፡ አሥር ቢሊዮን ይኸው ላለፉት አሥር ዓመታት የጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር ሞክሬ ችግሩን መፍታት እንዳልቻልኩ ባውቅም፣ ችግሩን ለማስታገስና ትንፋሽ ለመሰብሰብ ያስችለኛል፡፡ የኢሕአዴግ ሐሳብ ነው፡፡

ሲጀመር መንግሥት የወጣቶቹን የሥራ አጥነት ችግር በቅርቡ የተፈጠረ ሊያስመስለው ቢሞክርም፣ ላለፉት 25 ዓመታት እየተነገረው ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የቆየበት ነው፡፡ ይባስ ብሎም ‹አደገኛ ቦዘኔ› እያለ ሲፈርጃቸውና በኢፍትሐዊ የፖለቲካ አደረጃጀቶች ሲያሰቃያቸው የኖረው ይኸው ገዥ ፓርቲ መሆኑን ማንም አይረሳውም፡፡

ሪፖርተር የፌደራል ከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞን አነጋግሮ ያወጣውን ረጅም ቃለ ምልልስ በጥንቃቄ ካነበብኩ በኃላ፣ የጨለምተኛ አመለካከቴን በብርሃን ላፈካው አልቻልኩም፡፡ እንዲያውም ባሰኝ፡፡ እንደ አቶ ዘነበ ገለጻ ያለፉት ዓመታት ተግዳሮቶች አሁንም አሥጊ ሁኔታዎች ሆነው መቀጠላቸውን፣ እንዲያውም አንዳንዶቹ በከፍተኛ ሁኔታ ተወሳስበው የሚገኙ እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡ በወጣቶቹ በራሳቸው ከሚታዩ ዝቅተኛ ዕውቀትና ክህሎት፣ እንዲሁም የተዛባ አመለካከት (በአቋራጭ መክበር) ጀምሮ በየደረጃው ባለው የአስፈጻሚው አካል ሥር የሰደደ ኪራይ ሰብሳቢነት በተጨባጭ ካለው አነስተኛ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ጋር ተዳምሮ አስፈሪ ተራራ መደቀኑን መረዳት ቀላል ነው፡፡ ለእነዚህ ተግዳሮቶች ዘመቻው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ መሆኑን ከመገለጹ በዘለለ ምንም አዲስ ነገር አለመኖሩ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ አምላክ ይርዳን ከሌላ እሳት እንተርፍ ዘንድ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው berzelekew@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles