በመታሰቢያ መላከሕይወት ገብረ ክርስቶስ
በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በተለይ የቅኝ ግዛት ካበቃ በኋላ የባንክ ሥራን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የምዕራባውያን ባንኮች ተቆጣጥረውት ነበር፡፡ ይህም ወቅት ዳግማዊ ቅኝ ግዛት እየተባለ የሚታወቅ ሲሆን፣ እነዚህ ባንኮች ለአፍሪካ ሕዝብ ድህነትን እንጂ ማኅበራዊ ዕድገትን አላመጡለትም፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ ዘዴዎችንና የረቀቁ ተንኮሎችን በመጠቀም ራሳቸውን ብቻ ተጠቃሚ ሲያደርጉ ቆዩ እንጂ፣ ለማኅበራዊ ዕድገት ያበረከቱት አስተዋፅኦ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
በወቅቱ የነበሩ ፖለቲከኞችም ሆኑ ምሁራን የሚሠሩትን ተንኮል በአግባቡ የተረዱ ባለመሆኑ፣ ለዕድገት ምንም ተጨባጭ አጋር መሆን አልቻሉም ነበር፡፡
በአሁኑ ጊዜ ግን መላው የአፍሪካ አገሮችም ሆኑ የእኛም አገር ይህንን ሁኔታ ማወቅና መቆጣጠር የተቻሉበት በመሆኑ፣ አስፈላጊውን ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ለዕድገትና ለልማት አጋሮች ማድረግ የሚቻልበት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡
ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘባቸው ባለፉት 26 ዓመታት (ምንም እንኳን ሕዝባዊ እርካታን የፈጠረ ባይሆንም) መላው አገሪቱን ያዳረሰ የመንገድ መሠረተ ልማት፣ ከፍተኛ የሆነ የኃይል አቅርቦት፣ የቴሌኮም መረብ፣ የትምህርት ተቋማት፣ የሲሚንቶና የብረት ፋብሪካዎች፣ ወዘተ በስፋት ተገንብተዋል፡፡
እነዚህ ተግባራት አንድ አገር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ለመሳብ ከሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ከእነዚህ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶች አንዱና ዋነኛው በቂ የካፒታል አቅርቦት የሚያመጡ የውጭ ባንኮች ናቸው፡፡
መንግሥት ከውጭ የሚበደራቸው ብድሮችን ተጠቅሞ የሚገነባቸው መሠረተ ልማቶች የግሉ ዘርፍ እየተጠቀመና ቶሎ ቶሎ ታክስ እየከፈለ መንግሥት ዕዳውን መክፈል እንዳይችል ዋነኛው ማነቆ፣ የግሉ ዘርፍ እንደ ልቡ የሚበደረው የገንዘብ አቅርቦት አለ መኖር ነው፡፡ አሁን በአገራችን ያሉት ባንኮች እንኳን ምንም መያዣ ለሌለው ተበዳሪ ቀርቶ፣ በርካታ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሀብት ላለው ተበዳሪ እንኳን በተገቢው መጠንና ፍጥነት ገንዘብ ማበደር አይቻሉም፡፡
ብዙ ጊዜ ከመንግሥት ባለሥልጣናት የሚሰማው የአገር ውስጥ ባንኮች እስኪጠናከሩ ነው የውጭ ባንኮችን የማናስገባው የሚል አባባል ነው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት የአገር ውስጥ ባንኮች እስኪጠናከሩ ስንት ትውልድ (የሚለማ ሀብት፣ መሬት፣ በርካታ ነገር እያለን) በድህነት ለመኖር የሚገደደው?
ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በአገራችን በበቂ ሁኔታ እየተመረተ ያለው የሲሚንቶ ምርትን ብንወስድ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሰፊውን ገበሬ በበቂ ሁኔታ ሊደርስ አልቻለም፡፡ ፋብሪካዎቹም በሙሉ አቅማቸው ሠርተው ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፡፡ ገበሬው እንደ ልቡ ተበድሮ የመስኖ ሥራ፣ የውኃ ማጠራቀሚያ፣ የከብት በረት፣ ሽታ አልባ መፀዳጃ ቤት፣ የእህል ጎተራ፣ አነስተኛ ድልድዮች፣ ወዘተ በመገንባት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ መሠረታዊ ለውጥ ማየት ይቻላል፡፡
ሲሚንቶ ደግሞ ሙሉ በሙሉ የአገር ውስጥ ምርት በመሆኑ ገጠርን መሠረት ያደረገ የኢኮኖሚ ዕድገት ማየት ይቻላል፡፡ በአሁኑ የባንኮች የማበደር ፖሊሲ ምናልባት ለማዳበሪያ የሚሆን ብድር ይቀርቡለታል እንጂ፣ ሕይወቱን በመሠረቱ ሊለወጥ የሚችል የረጅም ጊዜ ብድር የሚያቀርብ የገንዘብ ተቋም የለም፡፡ በመሆኑም የድህነት አዙሪት ሊቆም አልቻለም፡፡
እዚህ ላይ የግል አስተያየቴን ለመግለጽ ከተፈቀደልኝ በእኔ እምነት የአገር ውስጥ ባንኮች አደጉ አላደጉ ለተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምኑ ነው? አሁን አደጉ የተባሉትን ባንኮችን ብንመለከት ለባለአክስዮኑ ከትርፍ ላይ ተቀንሶ የተገነባ ሕንፃን የባለቤትነት ሰነድ እንኳን ለመስጠት የሞከረ ባንክ የለም፡፡ የዛሬ 20 ዓመት የተሸጠ አንድ አክሲዮን ለምሳሌ አንድ ሺሕ ብር ቢሆን አሁንም ዋጋው ያው አንድ ሺሕ ብር ነው፡፡ በቅርቡ አክሲዮናቸውን እንዲተው የተገደዱት ትውልደ ኢትጵያውያን ይህንን መጠን ይዘው ነው እንዲወጡ የተደረገው፡፡
በአገር ደረጃ ደግሞ ስንመለከት አትራፊ ለሆኑ የሥራ ዘርፎች ያለ ብዙ ውጣ ውረድ ብድር በበቂ ሁኔታ ማቅረብ የቻሉበት ሁኔታ የለም፡፡ እነዚህ የግል ባንኮች አሁንም ከራሳቸው ትርፍ በስተቀር ምንም ዓይነት አገራዊ ኃላፊነት መሸከም የቻሉበት አግባብ አልተፈጠረም፡፡
የውጭ ባንኮች ያለ ገደብ ወደ አገር ውስጥ መግባት ቢችሉ ኢትዮጵያ እጅግ በርካታ የገንዘብ ያለህ የሚሉ ሊለሙ የሚችሉ ሀብቶች ያላት አገር በመሆንዋ በአገሪቱ ውስጥ ተጨባጭ ዕድገትን ማየት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ባንኮቹ ራሳቸው አዋጭ የሆኑ ሌሎች የሥራ ዘርፎችን በማጥናት ኢንቨስት ስለሚያደርጉ ከፍተኛ የሥራ ዕድልና የታክስ ገቢ ማመንጨት ይቻላል፡፡
መንግሥት ደጋግሞ እንደሚነግረን መሬት ሳይሆን ገንዘብ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ ውስን ሀብት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ማንኛውንም ባለሀብት ሥራህን ለማስፋፋት ያለህ ችግር ምንድነው ቢባል፣ ሁሉም ባለሀብቶች በአንድነት የሚናገሩት ገንዘብ የሚል ነው የሚሆነው፡፡
መሬት እንኳን ለእኛ ለልጅ ልጆቻችን ከበቂ በላይ ያለ ሀብት ነው፡፡ ባለፉት 26 ዓመታት በሲሚንቶ አቅርቦት፣ በኃይል፣ በመንገድ፣ በቴሌ፣ በፋብሪካዎች፣ ወዘተ በተጨባጭ ለውጥ ታይቷል፡፡ የገንዘብ አቅርቦት ግን ምን ዓይነት መሻሻል ማሳየት አልቻለም፡፡ ገንዘብ የሌላ ሀብት ሳይሆን በዓለማችን በተትረፈረፈ መጠን ያለ ሀብት በመሆኑና የውጭ ባንኮች ደግሞ ይዘውልን ሊመጡ ስለሚችሉ ይህንኑ ተገንዝበን ፖሊሲያችንን በቶሎ ማረም አለብን፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው በአገራችን ውስን የሆነ የመሬት ሀብት ሳይሆን ያለው፣ አሠሪ ሳይሆን አሳሪ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ከአገሪቱ የተፈጥሮና የሰው ሀብት ጋር በፍፁም የማይሄድ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ነው፡፡
በቅርቡ ደረጃ በደረጃ በመገባደድ ላይ ያለው የዓባይ ግድብ የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሰው በመሆኑ፣ ይህንን የኃይል አቅርቦት የሚመጣጠን የገንዘብ አቅርቦት መኖሩ የግድ ይላል፡፡ ለዚህ ነው የውጭ አገር ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ይህንን ክፍተት ይሙሉት የምለው፡፡
ፈረንጆች አንድ አባባል አላቸው፣ “Putting the dots together” ይላሉ ይህ አባባል በሁሉም የሕይወት ዘርፍ ውስጥ ትክክለኛ ነው፡፡ ለማብራራት ያህል አንድ ሰው የተለያዩ ነጥቦችን አስቀምጦ እነዚህን ነጥቦች ሲያገናኛቸው አንድ ምሥል ይፈጥራሉ፡፡ አሁን በአገራችን በቂ ኃይል እየተመረተ ነው፡፡ ሲሚንቶ፣ የቴሌ ኔትወርክ፣ መንገድ፣ ባቡር፣ በቂ የሰው ኃይል፣ ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት ሌሎችም እንደ ብረት የመሳሰሉት የግንባታ ውጤቶች፣ ወዘተ በበቂ ሁኔታ ይመረታሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን ነጥቦች አገናኝተን አንድ ምሥል ለመፍጠር ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ምሥሉ የተሟላ ይሆናል፡፡ በዜጎች ላይ የሚታይ የኑሮ መሻሻል ይታያል፡፡ የውጭ ባንኮች ይህንን ነጥብ በመሙላት የተሟላ ያደርጉታል፡፡ በመሆኑም መንግሥትም ሆነ ማንኛውም ዜጋ ይህንን መገንዘብ አለበት፡፡
ሌላው የውጭ ባንኮች እንደ አገራችን ባንኮች ሌሎች ባጣኑት ላይ ብቻ ተመርኩዘው ሳይሆን ብድር የሚያቀርቡት፣ ራሳቸው የጥናቱ አካልና በቂ ሥራ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ይህንንም ለማድረግ በቂ የሠለጠነ ሰው ኃይል አላቸው፡፡ ከዚህም አልፈው በራሳቸው አነሳሽነት የተለያዩ የገበያ ጥናቶችን አጥንተው ኑ በዚህ ዘርፍ ኢንቨስት አድርጉ፣ እኛ ገንዘብ እናቀርባለን የሚሉበት አሠራርም ስላላቸው በአገሪቱ ውስጥ ተጨባጭ የሆነ እመርታ ማየት ይቻላል፡፡ ይህ አሠራር እስካሁን ባለው የአገራችን ባንኮች አሠራር የሚታሰብ አይደለም፡፡
መንግሥት ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ ፍንጭ ቢያሳይም፣ ቁርጥ ያለና ግልጽ የሆነ የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ አልቻለም፡፡ ይህ ደግሞ በዕቅድ የሚመራ ኢኮኖሚ መገለጫ አይደለም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ሊለማ ከሚችለው ሀብቷ አኳያ ያለው የገንዘብ አቅርቦት (በተለይ ለግሉ ዘርፍ) እጅግ አናሳ ከመሆኑ የተነሳ፣ በርካታ ባለሀብቶች በእጅጉ ከአቅማቸው በታች ለመሥራት የተገደዱበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
ባንኮቻችን ያላቸው ጥሬ ገንዘብ (Liquid Cash) ሥራ ከሚፈልገው ወጣት ቁጥር፣ ማደግ ከሚፈልገው ባለሀብት፣ ከአገሪቱ አጠቃላይ ሀብት ወይም (Resource) ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ እጃችንን አጣጥፈን በድህነት ለመኖር ተገደናል፡፡ ሌላው ቀርቶ ምንም ዓይነት የመክሰር አደጋ የሌለባቸው የሥራ ዘርፎች እንኳን ገንዘብ ለማግኘት በእጅጉ የሚቸገሩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ያላቸውን ገንዘብ ማስቀመጫ ያጡ በርካታ አገሮች አሉ፡፡ አንድ አገር ለማደግ እጅግ ተመራጩ መንገድ የዜጎችን ጉልበት መበዝበዝ ወይም ሌላ አማራጭ ሳይሆን፣ ይህንን የተትረፈረፈ የገንዘብ ክምችት ወደ አገር ውስጥ እንዲመጣ በማድረግ በቀላሉ ከመሬት መነሳት የሚቻልበት ወቅት ነው፡፡
ከጥቂት አሥርት ዓመታት በፊት ዛሬ የተትረፈረፈ ገንዘብ ያላቸው አገሮች ራሳቸው በድህነት ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት ግን በዓለማችን ያሉ በርካታ አገሮች አስደናቂ ዕድገት በማስገንዘባቸው ከተረጂነት ወደ ዕርዳታ አቅራቢነትና አበዳሪነት የተሸጋገሩበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
ታዲያ ይህንን የዜጎችን ሕይወት በአስተማማኝ ሁኔታ ሊለወጥ የሚችል ሀብት ወደ አገራችን እንዳይገባ በሩን ዝግ አድርገን መቀመጥ ትክክል ያልሆነ ተግባር ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በርካታ አገሮች በአገራቸው ሊጠቀሙበት ያልቻሉትን ገንዘብ ወደ ሌሎች አገሮች ኤክስፖርት በማድረግ የሚቀጥለውን ትውልድ ተጠቃሚ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ እኛ ደግሞ ይህ በጣም ያስፈልገናል፡፡ የአገራችን ኢኮኖሚ ለማንኛውም ዘርፍ በበቂ ሁኔታ ገንዘብ ማቅረብ እስኪጀምር ድረስ ይህንን መሞከር አማራጭ የሌለው ተግባር ይመስለኛል፡፡
ዋናውና ትልቁ ቁምነገር መንግሥት የቁጥጥር ሥርዓቱን በሠለጠነ መንገድ በማጠናከር ያልተጠበቀ ችግር እንዳይፈጠር ተግቶ መሥራት ነው፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ሲበደር ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በዜጎች ላይ ይህ ነው የሚባል የኑሮ መሻሻል አልታየም፡፡ ምክንያቱም ብድሩ ለሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች በበቂ ሁኔታ መቅረብ ባለመቻሉ ነው፡፡ የውጭ ባንኮች በአገር ውስጥ ቢኖሩ ግን በራሳቸው ጥናት ጉድለቶችን በመሙላት በዓይን የሚታይ ለውጥ ማየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ መንገድ ለመገንባት መንግሥት ከውጭ ባንክ ቢበደርና መንገዱ ቢገነባ የግሉ ዘርፍ ደግሞ ከአገር ውስጥ ወይም የውጭ ባንክ ተበድሮ ሆቴል ቢሠራ መንገዱ ገቢ ማመንጨት ቻለ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም መንገዱ መሥራቱ ብቻ ኢኮኖሚ ለውጭ ሊኖር አይችልም፡፡ መንገዱን ተከትሎ ባንኮች ቶሎ ቶሎ የገንዘብ አቅርቦት ካዘጋጁና በመንገዱ ግራና ቀኝ ኢንቨስትመንት ሲስፋፋ መንገዱ አገራዊ ፋይዳ ኖረው ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ዜጎቻችን ሥራ ፍለጋ ወደ ሌሎች አገሮች እየተሰደዱ ነው፡፡ መሆን የነበረበት ግን ካፒታሉ ወደ አገራችን ቢሰደዱ ዜጎች እዚሁ ሥራ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ ስደት ይቆማል ማለት ነው፡፡
በኢኮኖሚ የበለፀጉ አገሮች ውስጥ ያሉ አንዳንድ ባንኮች ለአስቀማጮች ገንዘብ የአገልግሎት ክፍያ ያስከፍላሉ፡፡ በተቃራኒው በእኛ አገር አንድ ሰው አሥር ወይም 20 ሚሊዮን ብር ባንክ ቢያስቀምጥ በወለዱ ብቻ መኖር ይችላል፡፡ ይህ አሠራር መለወጥ አለበት፡፡ ሰው ገንዘብ አስቀምጦ ሳይሆን ጥሩ ኑሮ መኖር ያለበት፣ በገንዘብ ሠርቶ ነው መጠቀም ያለበት፡፡
ይህ ሊሆን የቻለው ባንኮች ባላቸው ውስን የማበደር አቅም ምክንያት ለአስቀማጮች ከፍተኛ የሚባል ወለድ እየከፈሉ ኪራይ ሰብሳቢነትን እያስፋፋ ነው፡፡ የውጭ ባንኮች ከፍተኛ የሚባል ካፒታል ይዘው ወደ አገር ውስጥ ቢገቡ ይህ ጨዋታ በአንድ ጀንበር ያቆማል፡፡
አሁንም መንግሥት በተደጋጋሚ እንደሚነግረን መሬት ውስን ሀብት ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ በአገራችን የተትረፈረፈ የመሬት ሀብት አለ፡፡ ውስን የሆነው ሀብት የገንዘብ አቅርቦት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዓለማችን በተትረፈረፈ መጠን የሚገኝ ሀብት ነው፡፡ የጎደለን ትክክለኛውን ፖሊሲ የሚከተል አሠራር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ይህንን የተትረፈረፈ የገንዘብ ሀብት ሥራ ላይ ልታውል የምትችልበት በቂ ቅድመ ሁኔታዎች ያሟላች አገር በመሆንዋ፣ የግሉ ዘርፍ ኪራይ ሰብሳቢ በሆኑ ተግባራት ላይ እንዳይሰማራ በሩን በማጥበብ አምራች እንዲሆን የሚያስችለውን በር በርግዶ መክፈት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ነው በዓይን የሚታይ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው፡፡
እነ ቻይና አገራቸውን ሲገነቡ በዚህ መልክ ወደ አገራቸው ገንዘብ ይዞ ሊመጣ የሚችል ኢንቨስተር አልነበረም፡፡ በመሆኑም የሕዝባቸውን መብት በመርገጥና ጉልበቱን በመበዝበዝ የካፒታል ክምችት መፍጠር ቻሉ፡፡ እኛ በአሁኑ ዘመን ይህንን ማድረግ አይጠበቅብንም፡፡ ትክክለኛ ፖሊሲን ከገንዘብ ጋር ማገናኘት ብቻ ነው ያለብን፡፡
በግብርናው ዘርፍ ያለውን የገንዘብ እጥረት ለመግለጽ የሚረዳ አንድ መንግሥት ያወጣው መረጃ አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ከ40 ሚሊዮን ሔክታር በላይ የሚታረስ መሬት አለ፡፡ እየታረሰ ያለው ግን ከ13 ሚሊዮን አይበልጥም፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ከ26 ዓመታት በኋላም አሁንም ስንዴ ከውጭ እያስገባን ነው፡፡ ይህ እውነታ የሚያሳየው ምን ያህል በብልሹ አሠራር ተተብትበን እንዳለን ነው፡፡ ሊሠሩ የሚችሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እጆች እያሉ፣ በቂ መሬትና ዝናብ እያለ ለ26 ዓመታት ይህንን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ማስወገድ እንዴት አቃተን? ለዚህ ነው መንግሥት ከተራ የችርቻሮ ሥራ ወጥቶ የመንግሥት ሥራ የሆነውን ትክክለኛ ፖሊሲ ማውጣት ላይ በበቂ ሁኔታ ቢጠመድ ተገቢ ነው የምለው፡፡
የብዙ ሰዎች ሥጋት የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ቢገቡ ያገኙትን የተጣራ ትርፍ በውጭ ምንዛሪ ይወሰዱታል የሚለው ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ያተረፉትን የተጣራ ትርፍ መልሰው ኢንቨስት ሊያርጉ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል በመኖሩ፣ ለሚቀጥሉት ከአሥር እስከ 20 ዓመታት ወደ አገራቸው ገንዘብ ለመውሰድ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ያቀርባሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡
ከዚህ ቀደም ባቀረብኳቸው ጽሑፎች ደጋግሜ እንደገለጽኩት የውጭ ባንኮች ሲገቡ ሁሉም ዓይነት የፖሊሲም ሆነ የሕግ ማዕቀፎች በአንድ ላይ በአንድ ፓኬጅ ሆነው መሄድ ስላለባቸው፣ ይህም ጉዳይ በተፋጠነ ሁኔታ ይታሰብበት እላለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው metasebyamelaku@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

