በጌታቸው አስፋው
ሪፖርተር የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው ዕትሙ በውጭ ‹‹ዜጎች የተያዙ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አክሲዮኖች ጨረታ ሁለት ገጽታ›› በሚል ርዕስ፣ ባለ አንድ ሺሕ ብር የአዋሽ ባንክና የኅብረት ባንክ አክሲዮኖች ጨረታ ዋጋ ሃያ ሺሕና አሥራ አራት ሺሕ ተሸጡ ብሎ አስነብቦ ነበር፡፡
አክሲዮኖቹን በዚህ ዋጋ የገዙ ሰዎች አሁን ባለው 40 በመቶ ከፍተኛ የትርፋማነት መጣኝ እንኳ ወጪያቸውን ለመመለስ እስከ ሃያ ዓመታት ሊፈጅባቸው እንደሚችልና አክሳሪ እንደሆነ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ይኼ ዋጋ የባንኮቹን ሀብት ግምትም ያዛባል፡፡
የአክሲዮኖች ትርፋማነት እንዳሁኑ በዓለም ታይቶ የማይታወቅ 40 በመቶ መሆኑ ቀርቶ ከባንክ ቁጠባዎች ወለድ መጣኝ በጥቂቱ ብቻ በልጦ ስድስትና ሰባት በመቶ ደረጃ ሊወርድም ስለሚችል፣ አክሲዮኖቹን የገዙ ሰዎች ዋናቸውን ለመመለስ ምን ያህል ዓመታት ሊፈጅባቸው እንደሚችል ማስላት ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ ይኼ ክስተት የሚነግረን በገፍ የተረጨውን ጥሬ ገንዘብ ሀብት ያገኙና የከበሩ ሰዎች የነገዱት ‹‹በሻሞ ገበያ›› ውስጥ እንጂ በነፃ ገበያ ውስጥ እጅና ጭንቅላት ሠርቶ ከሌላው ተወዳድሮ አለመሆኑን ይነግረናል፡፡ የአገሪቱ ዕድገት የሻሞ እንደሆነ ይነግረናል:: ለዚህም አገሪቱ ዛሬም ዋጋ እየከፈለች ነው፡፡ ወደፊትም እጅግ በጣም ብዙ ዋጋ ትከፍልበታለች፡፡
በዚሁ ዕለት አክሲዮን ኩባንያዎች የሚገዙበት አዲስ ረቂቅ ሕግ ለአስተያየት ሊቀርብ ነው በሚል ርዕስ በንግድ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተካሄደ በኋላ፣ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አማካይነት ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል የሚል ዘገባ ቀርቧል፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታ ፈቃድ ወስደው የተመዘገቡ የአክሲዮን ኩባንያዎች 472 ሲሆኑ፣ ነገር ግን እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ከ200 አይበልጡም ሲል ንግድ ሚኒስቴርም ገልጿል፡፡
የካቲት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣ የሪፖርተር ጋዜጣ የኦሮሚያ መንግሥት በኢኮኖሚ አብዮት ፕሮግራም ጠብደል ያሉ የአክሲዮን ኩባንያዎችን ለማቋቋም ከባለሀብቶች ጋር በትብብር ለመሥራት እየመከረ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ለባከኑት በርካታ ዓመታት ተቆጭቶ ለማካካስ መነሳሳቱ የሚያስመሰግነው ነው፣ እንዲሳካለት እመኛለሁ፡፡
ለኢንዱስትሪ መነሻ ካፒታል እንደ ውኃ ለጠማት ኢትዮጵያ ይቅርና ካፒታል ሞልቶ ለተረፋቸው አገሮችም ሳይቀር ዋናው የመነሻና የማስፋፊያ ካፒታል ምንጭ ኩባንያዎችን በአክሲዮን ማደራጀት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ብቸኛ የአገር ውስጥ ካፒታል ምንጭ ስለሆነ ሰፋ አድርጎ ማየት ያስፈልጋል፡፡
ስለዚህም ሕግ የሚወጣው ሲያጠፉ ለመቅጣት ሳይሆን ጥፋት እንዳይፈጸም መሆንም አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ የአክሲዮን ኩባንያዎች ለማቋቋም ሕግ ከማውጣት ጋር አብረው የሚሄዱ ቅድመ ሁኔታዎቸ መሟላት አለባቸው፡፡
እኛ አገር ገንዘባችንን በዕቃ ላይ ብቻ ማዋል ስንችል በብዙ የበለፀጉና ታዳጊ አገሮች ግን ገንዘባቸውን በሰነድ መልክም ይይዛሉ፡፡ የሰነዶቹ በገበያ ውስጥ ተሸራርፈው መሸጥና መለወጥ መቻል ደግሞ ሰነዶቹን ጥሬ ያደርጋቸዋል፡፡ ሰነድ በመሸጥ ብቻ ማምረቻ ድርጅቶችንም ሸራርፈው መገበያየት ተቻለ ማለት ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ሲቸግር ሙሉውን ድርጅቱን ለመሸጥ ወይም የሥራ መስክን ለመለወጥ ያለውን ጣጣ በማስወገድ ችግርን ቀረፈ ማለት ነው፡፡
የባንክ ተቀማጭ ሰርተፊኬት፣ አክሲዮን፣ ቦንድ፣ ከዕቃ ይልቅ በገበያ ውስጥ ተመልሰው ወደ ጥሬ ገንዘብ በቀላሉ ሊለወጡ ስለሚችሉ ለባለቤቱ እንደገና በፈለገው መንገድ ለመገልገል የጥሬነት (Liquidity) ዕድል ይሰጡታል፡፡
ይኼ ገንዘብን መልሶ በፈለጉት መንገድ የመገልገል ዕድል ነው እንግዲህ ገንዘብን ጥሬ ገንዘብ የሚያሰኘው፡፡ በኪሳችን ውስጥ የምንይዘው ብርና ሳንቲም ምንዛሪ በጣም ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ የባንክ ተንቀሳቃሽ ተቀማጭ ሙሉ በሙሉና የቁጠባና የጊዜ ተቀማጮችም በተወሰነ ደረጃ በፈለግን ጊዜ በደቂቃዎች ውስጥ አውጥተን ልንገለገልባቸው ስለምንችል ጥሬ ገንዘብ ናቸው፡፡ ሰነዶችን ለመሸጥ ጊዜ ስለሚወስድና ወደ ጥሬ ገንዘብነት ሲቀየር ትርፋማነትንም ስለሚያሳጣ ሰነዶች ገንዘብ እንጂ ጥሬ ገንዘብ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ሰነዶችም ከዕቃ ይልቅ በመሸጥ ፍጥነት ለጥሬነት የቀረቡ ንብረቶች ናቸው፡፡
ሆኖም በኢትዮጵያ የአክሲዮን ኩባንያ ታሪክ በአክሲዮን የተቋቋሙ ባንኮች እንኳ ባለ አክሲዮኖች ለሦስተኛ ወገን እንዳይሸጡ ስለሚከለክሉ በመካከላቸው መልሶ የመግዛትና የመሸጥ ውል (Repurchase Agreement) ከሌለ በስተቀር፣ ንብረትህን አትሸጥም የሚል ክልከላ ምን ያህል ሕጋዊ መሠረት አለው? ምን ያህሉ ባለ አክሲዮንስ ስለ መልሶ መግዛትና መልሶ መሸጥ ውል ያውቃል? መልሶ የመግዛትና መልሶ የመሸጥ ውል ከነበረ እንዴት የዳያስፖራዎቹ አክሲዮን በነፃ ገበያ ለሽያጭ ሊቀርብ ቻለ?
በዕድሜ የገፉ ሰዎችና ወጣቶች አክሲዮኖቻቸውን ወደ ጥሬ ገንዘብ ለውጠው ለመጠቀም የሚፈልጉባቸው ምክንያቶችና ጊዜያቶችም የተለያዩ ናቸው፡፡ ከዕድሜያቸው አንፃር ወጣቱ በማስፋፊያ ፕሮግራም ካፒታሉ (ሀብቱ) እንዲያድግለት፣ በዕድሜ የገፋው ደግሞ ዲቪደንዱ (ገቢው) ላይ ሊያተኩርም ይችላሉ፡፡
አክሲዮንና ቦንድን ለጥሬ ገንዘብነት ቅርብ የሚያደርጋቸው የተደራጀ የሰነዶች ሁለተኛ ገበያ ኖሮ ሰዎች በፈለጉ ጊዜ በእነዚህ ገበያዎች ውስጥ ሰነዶቻቸውን መግዛት ለሚፈልግ ሰው ሸጠው ጥሬ ገንዘባቸውን መመለስ ሲችሉ ነው፡፡ ያኔ ነው የሰነዶች አቅርቦትና ፍላጎት መስተጋብር ዋጋ ተፈጥሮ ሰዎች ሰነዶችን በትክክለኛ የገበያ ዋጋ ለመገበያየት የሚችሉት፡፡
ሌላው ትልቁ የአክሲዮኖች የገበያ ዋጋ ጥቅም ከአክሲዮኖቹ ጀርባ ላለው ምርት ትርፋማነትና ውጤታማት ምልክት ሰጪ መሆኑ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ዕውቀት ሳይኖራቸው በሻሞ የከበሩ ሰዎች በብራቸው ብዙ ሺሕ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በዕውቀታቸው ሥራ ፈጥረው በጋራ መሥራት ይችላሉ፡፡
በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ በታሪኳ ባስተናገደቻቸው አንድ መቶ ሃምሳ ሺሕ አውቶሞቢሎች ላይ በ2008 ዓ.ም. ብቻ አንድ መቶ አሥር ሺሕ አውቶሞቢሎች ቀላቅላለች አሉ፡፡ ባለቤቶቹ በሻሞ የከበሩ ሰዎች መሆናቸውን ያወቁ አልመሰለኝም፡፡ ከንግግራቸው ቃና የተረዳሁት ባለመኪኖቹን የፋብሪካ ወዛደሮች አድርገው እንደሚገምቱና አገሪቱም እየበለፀገች እንደሆነ ነው፡፡
ሰዎችን በሻሞ ለማክበር ብቻ የጠቀመው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወጣቱን ሥራ አሳጥቶ፣ የሸቀጥ ዋጋን አንሮ፣ አገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አሳጥቶ፣ በአጠቃላይ አገሪቱን አውላላ ሜዳ ላይ ጥሎ፣ ክልሎች ግራ ቢገባቸው በወሰዱት መሬትና የማዕድን ሥፍራ ከኢንቨስተሮች ነጥቀው ለወጣቱ ሥራ ፈጠራ ማዋል ያልታቀደ የተናጠል ዕርምጃ አፈር እየበላ ነው፡፡
ከአክሲዮን ኩባንያ ሕጉ በፊት የተጠና በአጭር የማይቀጭ ዕቅድ አውጥቶ ለመንቀሳቀስ ለአክስዮን ገበያ የሚያስፈልጉ ተቋማትን ማደራጀት ይቀድማል፡፡ የጥቂቶቹን ጥቅም እንደሚከተለው እዘረዝራቸዋለሁ፡፡
አንደኛ አዲስ የሚቋቋሙ የአክሲዮን ኩባንያዎች አክሲዮኖቻቸውን በሽርፍራፊ ሸጠው ሥራ ለመጀመር ሁለትና ሦስት ዓመት መጠበቅ ስለማይኖርባቸው፣ እግረ መንገዱን የኩባንያዎቹን ትርፋማነትና የአክሲዮኖቹን አዋጭነትም ለክቶ የሚያረጋግጥና በጥቅል ገዝቶ በኮሚሽን ትርፍ ለሕዝብ በሽርፍራፊ የሚሸጥ የኢንቨስትመንት ባንክ ያስፈልጋል፡፡
ሁለተኛ በግለሰብ ደረጃ በአክሲዮን የሚቋቋሙ ድርጅቶችን የወደፊት ትርፋማነት ከመንግሥት ፖሊሲና ከብሔራዊ ኢኮኖሚውና ከክፍላተ ኢኮኖሚዎች ዕድገትና ገበያ ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ የሚታይ ስለሆነ፣ ሙያው ለሌላቸው ግለሰቦች ለመለካት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህም አክሲዮን ገዢዎች ግለሰቦች ራሳቸው በግል ከሚሆኑ በአባልነት ተደራጅተው በተቋም መልክ አክሲዮን እንዲገዙ የጋራ ጥሪትን (Mutual Fund) የመሳሰሉ የጥሬ ገንዘብና የካፒታል ገበያ ተቋማት ተቋቁመው፣ የግል ኢንቨስተሮችን ገንዘብ በባለሙያ ዕውቀት በልዩ ልዩ የሰነድ ገበያዎች በመደልደልና በማስተዳደር ወይም ለግል ኢንቨስተሮች ምክር በመስጠት ማገልገል አለባቸው፡፡
ሦስተኛ የተደራጀ ሁለተኛ የሰነድ ገበያ ለማቋቋም የሚያስፈልጉ ለገበያው መመርያ ሕግ አውጥተው የንግድ ሥነ ምግባር ጉዳዮችን የሚከታተሉና የሚቆጣጠሩ መንግሥታዊ የቁጥጥር ተቋማት መቋቋም አለባቸው፡፡
አራተኛ አክሲዮኖቻቸውን በሁለተኛ የአክሲዮን ገበያ ለመነገድ የሚፈልጉና የብቃት መሥፈርት የሚያሟሉ ኩባንያዎችን በአባልነት መዝግበው፣ ሰነዶቻቸውን የሚያገበያዩ የተደራጁ ገበያዎችና የግብይት አፈጻጸም ማወራረጃ ማዕከላዊ የተገበያዮች ተቀማጭ ሒሳቦችና ሌሎች መሰል አገበያይና ንግድ አቀላጣፊ ተቋማት መቋቋም አለባቸው፡፡
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የኒውዮርክ አክሲዮን ገበያ፣ የለንደን አክሲዮን ገበያ፣ የቦምቤ አክሲዮን ገበያ እየተባሉ ከሚታወቁት ታላላቅ የሰነድ ገበያዎች ባሻገር የእኛው የምርት ገበያ ድርጅትም እንደ ምሳሌ ሊወሰድ ይችላል፡፡
አምስተኛ የአክሲዮን ተገበያዮችን ጉዳይ የሚያስፈጽሙ፣ የገበያውን ባህሪይ ለይተው የሚያውቁና ሙያዊ የድለላና የኮሚሽን ሥራ የሚሠሩ ተቋማት መቋቋም አለባቸው፡፡ እነዚህም ለምሩቃን ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡
ስድስተኛ ነባር የግል ድርጅቶቻቸውን ወደ አክስዮን ኩባንያነት መቀየር ወይም ድርጅቶችን ለመቀላቀል ለሚፈልጉ የድርጅት ሀብትና የንግድ ሥራ ዋጋ ገማች ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ ለሒሳብ ሥራ ባለሙያ ትልቅ የሥራ ገበያ ነው፡፡
እነዚህ ከዚህ በላይ የተገለጹት ጥቂቶቹ ብቻ ሲሆኑ፣ የአክሲዮን ኩባንያዎች ሕግ ከመውጣቱ በፊት ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው፡፡
እነኚህ ሁኔታዎች ካልተሟሉ እንደ ቀድሞው ሚሊዮኖችን ሰርቄ ወይ እጠፋለሁ . . . . ወይ አምስት ዓመት ታስሬ እወጣለሁ በሚል ብር እንጂ ዕውቀት የሌለው መንገደኛ ሁሉ የውሸት የእጥፍ እጥፍ ትርፋማነት የመኃይም ፕሮጀክት እያዘጋጀ፣ የሕዝብ ንብረት መዝረፍ ሥራ ላይ እንዲሰማራ መፍቀድ ነው፡፡
ለሽያጭ ከመቅረቡ በፊት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ በፕሮጀክቱ ትርፋማነት ሥሌት ላይ መስማማት ስላለበትም፣ የገንዘብ ኢኮኖሚን መምራትና ማስተዳደር የግብርና ኢኮኖሚን እንደማስተዳደር በካድሬ ሲቪል ሰርቪስ ሊወጡት የሚችሉት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በዕድገት ጎዳና ወደፊት ለመዝለል እየፈለገች ነው መንግሥት በካድሬ ሲቪል ሰርቪሱ እንዳትዘል አስሮ ይዟታል፡፡ በሻሞ መክበርና በሻሞ መደህየት ይብቃን፡፡
በነፃነት በመሥራት ሳይሆን በሚገድቡ ሕጎች የሚያምነው ካድሬ ሌላ የፖለቲካ ሥራ ቦታ ይፈለግለትና የዩኒቨርሲቲ ምርቶች የሆኑ ወጣት ምሩቃን የበሰለ ዕውቀት ካላቸው አንጋፋ ምሁራን ጋር ተቀናጅተው ዕውቀታቸውንና ትኩስ ወኔያቸውን በነፃነት ተጠቅመው፣ ሠርቶ የመኖር ዕድልና መሠረታዊ የሰብዓዊ መብታቸውን ያግኙ፡፡ የኢኮኖሚው በፖለቲካው መተብተብ ወደኋላ ጎታች ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
