በጌታቸው አስፋው
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ልማት ጉዞ የተጓዘችበትን ርቀት ቆም ብላ የምታጤንበት፣ እነ ማንን እንደምትመስል መስተዋት የምትመለከትበት፣ በኢኮኖሚ ልማት ደም ሥሯ ውስጥ የሚዘዋወረው ደም ምን ዓይነት እንደሆነ የምትመረምርበትና ዛሬ ያለችበትን ሁኔታ ለማወቅ ከሌሎች መሰል አገሮች ጋር መመሳሰሏንና መለያየቷን ገምግማ ቀጣይ መንገዷን መቃኘት እንዳለባት የሰሞኑ ግርግር ራሱ ያስገድዳታል፡፡
በልማታዊ መንግሥት ጉዞ የተራመዱትን አገሮች በስኬታቸው መጠን ልክ በጣም የተሳካላቸውና በመጠኑ የተሳካላቸው ወይም ያልተሳካላቸው፣ ካለመሳካትም አልፎ በዕዳ የተዘፈቁ ብሎ በየፈርጁ መከፋፈል ይቻላል፡፡
ስለልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ብዙ ታዳጊ አገሮች እንደ አዲስ ግኝት አጋነው ቢናገሩም፣ የልማት ኢኮኖሚስቶች ግን ከ1950ዎቹና ከ1960ዎቹ የልማት አስተሳሰቦች ብዙ የተለየ ነገር የለውም ይላሉ፡፡ የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ቀደም ካሉት እንደ ጉናር ሚርዳል፣ ፖል ባራን፣ ሮዘንስቴን ሮዳን፣ ሲሞን ኩዝኔትስ፣ ሮስቶው፣ ሳሙኤል ሀንቲንግተን የልማት ኢኮኖሚክስ አመለካከት አይለይም ይላሉ፡፡
ታዳጊ አገሮች ከቅኝ ግዛት ከተላቀቁበትና የራሳቸውን ዕጣ ፋንታ ራሳቸው ወሳኝ ከሆኑበት ከ1950ዎቹና 1960ዎቹ ጀምሮ የራሳቸው ምሁራንም ሆኑ ምዕራባውያን በምን ዓይነት የዕድገትና የልማት ጎዳና ቢጓዙ፣ እንደ ሀብታም አገሮች ሊበለፅጉ እንደሚችሉ ብዙ ጽንሰ ሐሳቦችን አፍልቀዋል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ታዳጊ አገሮች በምን ዓይነት የኢኮኖሚ ልማት ጽንሰ ሐሳቦች እንዳለፉና በኢኮኖሚ ልማት ጉዟቸው እርስ በርሳቸው የሚመሳሰሉ ወይም የተለያዩ አካሄዶች እንደ ነበሯቸው፣ የሚመሳሰሉበት ሁኔታዎች ካሉ ኢትዮጵያ እነ ማንን እንደምትመስል ለመመልከት ነው፡፡
የዘመናዊነት ጽንሰ ሐሳብ ኢኮኖሚ ልማት
ቅኝ ተገዢ ታዳጊ አገሮች ነፃ ከወጡበት ጊዜ አንስቶ ሰፍኖ የቆየው የዘመናዊነት ጽንሰ ሐሳብ (Modernization Theory) የኢኮኖሚ ልማት አመለካከት ታዳጊ አገሮች፣ ያደጉ አገሮች ባደጉበት ዘመናዊ መንገድ ተጉዘው ለማደግ ‹‹የአቦ ሰጥ›› ዕድል አግኝተዋል የሚል ነው፡፡ ዘመናዊ ማለትም የአኗኗር ዘይቤን ለዘመናዊነት ፀር ከሆኑት የታዳጊ አገሮች ልማዳዊ፣ ባህላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊ ሁኔታዎች ቀይሮ ኑሮን ከበለፀጉት አገሮች የዕድገት ደረጃና የጊዜው ኑሮ ሁኔታ ዓይነት ጋር ማመሳሰል ነው፡፡
ይኼ ጽንሰ ሐሳብ ከከተሜነት ኢንዱስትሪያላዊነትና ከትምህርት መስፋፋት ጋርም ይመሳሰላል፡፡ ዘመናዊነት ሲጨምር በቤተሰብና በማኀበረሰብ ከመታወቅ ይልቅ በራስ ወይም በግለሰብነት መታወቅ ዋናው የማንነት መገለጫ ይሆናል፡፡ ከቡድን መብትና ግዴታዎች የግለሰብ መብትና ግዴታዎች ይቀድማሉ፡፡ ለሕዝብ የሚታገሉ የፖለቲካ ሰዎችም አስተሳሰባቸው ዘመናዊ ከሆነ በቤተሰብና በብሔረሰብ ቡድን ሰውን ከሰው አይለያዩም አይከፋፍሉም፡፡ በቤተሰብና በብሔረሰብ ማንነት መታወቅ ለቤተሰብና ለብሔረሰብ መብት መታገል ኋላቀር አስተሳሰብ ይሆናል፡፡
የዘመናዊነት ጽንሰ ሐሳብ ኢኮኖሚ ልማት አቀንቃኞች የኢንዱስትሪ እመርታ፣ የመገናኛ ብዙኃን መስፋፋት፣ የበለፀጉት አገሮች የክህሎት ሐሳቦች፣ በአብሮ መኖር ሒደት አማካይነት ወደ ታዳጊ አገሮች መስረፅ የታዳጊ አገሮችን ልማዳዊና ባህላዊ ኢኮኖሚ ስለሚያዘምን፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር የምርት አደረጃጀታቸው እንዲሁም የሸቀጥ ፍላጎትና አቅርቦት በበለፀጉት አገሮች ዕድገትና ብልፅግና ጎዳና መልክ ይገራል የሚል ሐሳብ ነበራቸው፡፡
የጥገኝነት ጽንሰ ሐሳብ ኢኮኖሚ ልማት
የዘመናዊነት ጽንሰ ሐሳብ አቀንቃኞችን በመቃወም የኢንዱስትሪ አብዮት የተካሄደበትን የአውሮፓን ወግና ልማድና የአሜሪካንን ዕድገት ጎዳና መቅዳትና መከተል እንደ የዘመናዊነት ምልክት መታየቱን ባለመደገፍ፣ ታዳጊ አገሮችም የራሳቸውን ልማድና ባህል ቢያዳብሩ ‹‹የምዕራቡን ዓለም ‘ሳይቀዱ’ የሰው ‘ሳይገለብጡ’›› በራሳቸው መንገድ ሊዘምኑ ይችሉ ነበር የሚል አመለካከትም ከታዳጊ አገሮች ምሁራን መጥቶ ነበር፡፡
የዘመናዊነት ጽንሰ ሐሳብ ኢኮኖሚ ልማት አስተሳሰብን በመቀናቀን ከተነሱት ጽንሰ ሐሳቦች መካከል አንዱና ዋናው፣ በ1950 ዓ.ም. ብቅ ያለው የጥገኝነት ጽንሰ ሐሳብ (Dependency Theory) አመለካከት ትርጉም የሚከተለው ነው፡፡
እንደ የጥገኝነት ጽንሰ ሐሳብ ታዳጊ አገሮች በበለፀጉት አገሮች ካፒታል፣ ቴክኖሎጂ፣ ሙያና የንግድ ሥርዓት እየተጠቀሙ አብሮ መኖራቸውና ያላቻ ጋብቻ መፍጠራቸው፣ የራሳቸውን ዕውቀትና የአመራረት ዘይቤ እንዳያዳብሩ በበለፀጉት አገሮች ምርት ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ አድርጎ ጎድቷቸዋል፡፡ የኢኮኖሚ ልማታቸውን ከማፋጠን ይልቅ አቀጭጮታል፡፡ ጥሬ ሀብት ከታዳጊ ቅኝ ተገዢ ዳር አገር ወደ ቅኝ ገዢ መሀል አገር ፈልሷል፡፡
የጥገኝነት ጽንሰ ሐሳብ ያላደጉ አገሮች የበለፀጉ አገሮች የቀድሞ ድህነት ዘመን ግልባጮች ሳይሆኑ የራሳቸው ወግ፣ ልማድ፣ ባህልና ህልውና የነበራቸው ነገር ግን ቀድመው ከዘመኑት ጋር በአብሮ መኖር ውስጥ ደካማ የሆኑና የተጎዱ በመሆናቸው፣ ይኼንን ሁኔታ ሊቀለብሱ ይገባል በማለት ያስተምራል፡፡
ከ1960 ዓ.ም. በኋላ ሜክሲኮን፣ ብራዚልን የመሳሰሉ የላቲን አሜሪካ አገሮችና ደቡብ ኮሪያን፣ ታይዋንን የመሳሰሉ የእስያ አገሮች ኢምፖርትን በአገር ውስጥ ምርት በመተካትና የበለፀጉ አገሮችን ኤክስፖርት ገበያዎች ሰብረው በመግባት፣ በቅይጥ የንግድ ስትራቴጂ አማካይነት ከጥገኝነት የሚያድን የልማት መንገድ ተከትለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጊዜው የካፒታሊስት አገሮችና የሶሻሊስት አገሮች ተቃራኒ ጎራ በመፍጠር ታዳጊ አገሮችን ወዳጅና የንግድ ሸሪክ ለማድረግ ብዙ ጥረው ነበር፡፡ ታዳጊ አገሮችም የገለልተኝነት አቋም ከመያዝም ባሻገር የነዳጅ ዋጋ እስከወደቀበት እስከ 1970 ዓ.ም. ድረስ፣ በነዳጅ አምራች አገሮች ጡንቻ አማካይነት ብዝበዛ የሌለበት አዲስ ዓይነት የሰሜንና የደቡብ ግንኙነት ለመፍጠርና በዓለም ዙሪያ አዲስ ፍትሐዊነት የሰፈነበት የኢኮኖሚ ሥርዓት (New Economic Order) ለመዘርጋት ተፍጨርጭረውም ነበር፡፡
በአሁኑ የግሎባላይዜሽን ዘመንም ሉዓላዊ ልማታዊ መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ሥርዓት አብረው ተቻችለው የመኖራቸው ሁኔታ እያከራከረ ነው፡፡ የመንግሥታቱ ውስጣዊ ሉዓላዊ የልማት አስተዳደርና የግሎባላይዜሽን ዓለም አቀፍ የነፃ ገበያ ሥርዓት ግንኙነት የወቅቱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ እንቆቅልሽ ነው፡፡ የእንቆቅልሹ ፍቺም በሦስት ፈርጆች ተከፍሎ ይታያል፡፡
አንዱ መንግሥታት በጊዜ ብዛት ይከስማሉ ሲል ሁለተኛው መንግሥታት ምንም ቢሆን በግሎባላይዜሽን አይተኩም፣ ሉዓላዊነታቸውን ጠብቀው ይኖራሉ የሚል ነው፡፡ ሦስተኛውና መካከለኛ አቋም የሚይዘው ልማታዊ መንግሥታት የግሎባላይዜሽንን ፍላጎት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን ሥርዓት ከፖሊሲያቸው ጋር አጣጥመው በውስጣቸው ያሰርፃሉ የሚል ነው፡፡
በዚህም መሠረት እንደ ታይላንድ፣ ታይዋን፣ ማሌዥያ፣ ደቡብ ኮሪያና ቬትናም ባሉ ልማታዊ መንግሥታት አገር መንግሥት ሕዝቡን ከግሎባላይዜሽን ዘመን ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ምዝበራ ለመከላከል፣ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች የአገር ውስጥን የደመወዝ አከፋፈልና የሥራ ከባቢ ሁኔታ ጠብቀው ግብር ከፍለው ከትርፋቸው ከፊሉን በአገር ውስጥ ተጠቅመው እንዲሠሩ አስገድደዋል፡፡ የአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ እንዲጠቀሙና የአገር ውስጥ ሠራተኞችን በዓለም አቀፍ የሠራተኛ ዋጋ እንዲቀጥሩም አድርገዋል፡፡
ሁለት ዓይነት የካፒታሊስት ሥርዓት መንግሥታዊ ቅርፅ
ከ1970 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጋን፣ የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸርና የጀርመኑ ቻንስለር ሄልሙት ኮል የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት እንደገና እንዲያንሰራራ ባደረጉት ሙግት፣ የታዳጊ አገሮች ብዝበዛ የሌለበት አዲስና ፍትሐዊ የሰሜንና የደቡብ የኢኮኖሚ ግንኙነት ሥርዓት የመፍጠር ጥረትና ህልም መከነ፡፡
የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓትም በሁለት አቅጣጫዎች ተከፈለ፡፡ አንዱ ጃፓን እንደ ቁንጮ ምሳሌ ተደርጋ የምትጠቀስበት የልማታዊ መንግሥት (Developmental State) ካፒታሊስት ሥርዓት ሲሆን፣ ሌላው አሜሪካ እንደ ቁንጮ ምሳሌ ተደርጋ የምትጠቀስበት የኒዮሊበራል ቁጥጥራዊ (Regulatory) ነፃ ገበያ ካፒታሊስት ሥርዓት ነው፡፡
የዓለም ባንክ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም የንግድ ድርጅትና ምዕራባውያን አገሮች በጋራ ሆነውም ዓለምን በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መስመር ለማስጓዝና በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥትን ሚና ለመቀነስ የዋሽንግተን መግባቢያ ስምምነትን ተፈራርመው ተንቀሳቀሱ፡፡ በመዋቅር ማሻሻያ (Structural Adjustment) ፕሮግራም ስም ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ብለውም በ1980ዎቹና በ1990ዎቹ ዓመታት ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በርካታ ሠራተኞች አፈናቅለዋል፡፡
የልማታዊ መንግሥት ጽንሰ ሐሳብ
የልማታዊ መንግሥትን ጽንሰ ሐሳብ ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት የዘመናዊነትና የጥገኝነት የኢኮኖሚ ልማት ጽንሰ ሐሳቦች ጋር የሚያመሳስላቸው፣ በልማታዊ መንግሥት መርህ በሚጓዙ አገሮች ሁለቱ ጽንሰ ሐሳቦች ጎን ለጎን በጣምራነት አብረው ስለሚኖሩ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የዚህ ዘመን ልማታዊ መንግሥታት ከኒዮሊበራሊዝም ግሎባላይዜሽን ጋርም አብረው እየኖሩ ነው፡፡
በአንድ በኩል ጀማሪ የልማታዊ መንግሥት አገሮች ለበለፀጉ አገሮች በጥሬ ዕቃ አቅራቢነትና ከበለፀጉ አገሮች ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ሸቀጦችን በመሸመት የበለፀጉ አገሮች ዘመናዊ ሥልጣኔ ተቋዳሽ በመሆን አብረው ሲኖሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢንዱስትሪ ምርት ለማምረት በበለፀጉት አገሮች ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና ሙያ ላይ ስለሚሞረከዙ ዕድገታቸውና ልማታቸው በበለፀጉት አገሮች ላይ ጥገኛ ነው፡፡
ጃፓን ራሷ ሳትቀር የለማችው ራሷን ሆና ሳይሆን የበለፀጉ አገሮችን ወግና ልማድ ተውሳና አዳብራ እንደሆነ ታምኖ፣ የበለፀጉ አገሮችን ወግና ልማድ ተቀብሎ አብሮ ለመኖር የመፈለግ ዘመናዊነትና የበለፀጉ አገሮችን ካፒታል ቴክኖሎጂና ሙያ የዕድገት መሠረት ማድረግ የጥገኝነት ጽንሰ ሐሳቦች ቅልቅል ሥርዓት ነው፡፡ ስለዚህም የዘመናዊነት ጽንሰ ሐሳብና የጥገኝነት ጽንሰ ሐሳብ ሁለት የልማታዊ መንግሥት አውታሮች ናቸው፡፡
ከመላው ዓለም በየጊዜው በርካታ አገሮች የልማታዊ መንግሥት አካሄድን መርጠው የተቀላቀሉ ቢሆንም፣ የላቀ ዕውቅና ተሰጥቷቸው ስማቸው ዘወትር በኢኮኖሚ ነክ ጽሑፎች የሚጠቀሰው ከምሥራቅና ከደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ውስጥ ጃፓን፣ ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ህንድ፣ ታይላንድ፣ ታይዋን፣ ቬትናም፣ ማሌዥያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ፊሊፒንስና ኢንዶኔዥያ ይጠቀሳሉ፡፡ ከላቲን አሜሪካ ቺሊ፣ ኮስታሪካ ሲሆኑ ከአፍሪካም ሞሪሽየስና ቦትስዋና ናቸው፡፡
ለሰላሳ ዓመታት ያህል የዋሽንግተን መግባቢያ ስምምነት የኒዮሊበራሊዝም ፖሊሲን ሲተገብሩ ከቆዩ በኋላ በርካታ የላቲን አሜሪካ አገሮችም የልማታዊ መንግሥት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ፍልስፍናን ተከትለው፣ በከተሞች ከኢኮኖሚ ልማት መገለልን ለማስቀረት የሥራ ፈጠራ ችሎታ ኖሯቸው ካፒታል ላጡ ወጣቶች በቀላል ወለድ ብድር ማመቻቸት ጀምረው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ለምርቶቻቸው ፈላጊ ገበያ በማጣት ምክንያት ወደ መካከለኛ አምራች ድርጅት ሳይሸጋገሩና እንደ ልማታዊ መንግሥት ስኬታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
ከአፍሪካ ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ወዘተም እንደ ዕጩ ወይም በመንገድ ላይ ያሉ የልማታዊ መንግሥት አገሮች ተብለው ይጠቀሳሉ፡፡
ልማታዊ መንግሥት የኢንዱስትሪ ዕድገት ፖሊሲ በማርቀቅና አፈጻጸሙን በቢሮክራቶች ክትትል በመምራት በኢኮኖሚው ዕድገት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ግብ አቅደው የሚንቀሳቀሱት ቢሮክራቶች የፖለቲካ ተመራጮች ስላልሆኑ፣ የሕዝብ ድምፅ ለማግኘትና ለአጭር ጊዜ የግልና ብሔራዊ ጥቅም ሲሉ በአሠሪውም ሆነ በሠራተኞች ማኅበራት ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ሥር ስለማይወድቁ ለረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅምና ለአገር ብልፅግና እንደሚሠሩ ይታመናል፡፡
ልማታዊ መንግሥት ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ በመፍጠር፣ ለኢንቨስተር ተስማሚ ሁኔታዎች በማመቻቸት፣ የአነስተኛ ንግድ ማኅበረሰብ ልማትን በመደገፍ፣ መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶችን ውጤታማ በማድረግ የኢኮኖሚ ልማቱን ይመራል፡፡ ለዚህም መንግሥት ሥልታዊ፣ ተቋማዊና ቴክኒካዊ አቅም ሊኖረው ይገባል፡፡
ሥልታዊ አቅም ማለት ብሔራዊ አጀንዳ ለመቅረፅና ለመምራት መቻል ኅብረተሰቡ በብሔራዊ አጀንዳው አተገባበር እንዲሳተፍ ማድረግና ማኅበራዊ ሀብት ለዚህ አጀንዳ አፈጻጸም እንዲውል ማድረግ ናቸው፡፡ ልማታዊ መንግሥት የመንግሥት ክፍለ ኢኮኖሚን፣ የንግዱን ማኅበረሰብ፣ የሠራተኛውን ክፍልና የሲቪክ ማኅበረሰቡን አጋር በማድረግ ለዚህ የጋራ አጀንዳ ማስተሳሰር አለበት፡፡
ያለ አጋር ድርጅቶች ተሳትፎ ልማት አይታሰብም፡፡ ግልጽ፣ የሚለካና በጊዜ ገደብ የታጠረ የልማት ግብ ይዞ ተግባራዊ ለማድረግ ከተፈለገ ግብረ ገብ ያለው ትውልድ ለመፍጠር ከሃይማኖት ተቋማት ጋር አብሮ መሥራትን፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከሠራተኛ ማኅበራትና ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር አብሮ መሥራትን ይጠይቃል፡፡
ልማታዊ መንግሥት ግቡን ለማስፈጸም ጠንካራና ታማኝ ሲቪል ሰርቪስ ያለበት ተቋማዊ አቅም የሚያስፈልገው፣ በመንግሥታዊ አካል እርከኖች ሁሉ ቀልጣፋና ውጤታማ መዋቅርና ሥርዓት ስለሚያስፈልገው ነው፡፡
ቴክኒካዊ አቅም የሚያስፈልገውም ሰፋፊ ግቦችን ወደ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች መንዝሮ ማስፈጸም ስላለበት ነው፡፡ ቴክኒካዊ አቅም ፕሮግራሞችን የማቀድና አፈጻጸማቸውን የመከታተል አቅምንም ይጠይቃል፡፡ እነኚህ ሁሉ ክንዋኔዎችም በቂና የተማረ የሰው ኃይል ይፈልጋሉ፡፡
ከዚህ በላይ የተገለጹትን የልማታዊ መንግሥት ቅድመ ሁኔታዎች ለማሟላት ልማታዊ መንግሥት የሚከተሉት ባህሪያት ሊኖሩት ይገባል፡፡
- ሕጋዊ ዕውቅና ያገኘ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት፣
- ብርቱና ቁርጠኛ ፍላጎት፣
- ችሎታና ብቃት ያለው የባለሙያ ቢሮክራሲ፣
- በግሉ ኢኮኖሚ ከትርፍ ይልቅ የሚገባ ድርሻ ላይ ማትኮር፣
- የአገር ውስጥ አምራቾችን ከውጭ ከሚገቡ ሸቀጦች መከላከል፣
- በወጪ ንግድ ላይ ያተኮረ ፖሊሲ፣
- የውጭ ቴክኖጂ ሽግግርን መሻት፣
- ሰፊ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣
- የቁጠባና ሥልታዊ ብድር አሰጣጥ ተቋማትን ማበረታታት፣
- የመንግሥት፣ የሠራተኛውና የአሠሪው አጋርነት፣
- የግሉ ኢኮኖሚ ለብሔራዊ ጥቅም እንዲቆም መግራት፣
- ሁሉንም ኅብረተሰብ አካታች ልማት ናቸው፡፡
ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ
አንዳንድ የኢኮኖሚ ልማት ጠቢባን የዘመናዊነት መገለጫ የሆኑት ኢንዱስትራላዊነት ከተሜነትና መማር የመሳሰሉ የኢኮኖሚ ልማት ጉዳዮች ከቡድን ይልቅ በግለሰብ ደረጃ የሚገለጹ ስለሆኑ፣ ከዴሞክራሲና ከፖለቲካዊ ጉዳዮች መቅደም እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ፡፡
በዚህ የዘመናዊነት ጽንሰ ሐሳብ የኢኮኖሚ ልማት አመለካከት ፖለቲካን ከኢኮኖሚ የሚያስቀድሙ ሰዎች ያላወቀ፣ ያልተረዳ፣ በቤተሰብና በጎሳ አመለካከት ስሜታዊ የሆነና በጠባብ የዘረኝነት ፍቅር የታወረ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካና በመንፈሳዊ ጥቅል ሕይወቱ ያልለማ፣ ከራሱ ኋላ ቀር አስተሳሰብም ነፃ ያልወጣ፣ በባለማወቅ ዕውቀቱ ለገዢነት ውክልና እንዲመርጣቸው ዴሞክራሲ እንዲቀድም የሚፈልጉ ናቸው፡፡
በደርግ ዘመን አሥራ ሰባት ዓመታት ከካፒታሊዝም አልፎ ሶሻሊስት ፍልስፍና ውስጥ ገብቶ በሠርቶ አደር ጋዜጣ የእነ ማርክስንና የእነ ሮዛ ሉክዘምበርግን ዓለም አቀፋዊ የወዛደር ኅብረትን ሲያነብ ሲሰማና ሲጠመቅ የኖረን ሕዝብ ወደ ኋላ በመጎተት፣ በመንደር ልጅነት አሰባስበው ሥልጣን በአቋራጭ ለመያዝ የቸኮሉ ሰዎች ፖለቲካን ከዳቦ ያስቀድማሉ፡፡
ሕዝቡ በሥራ ማጣት፣ በዋጋ ግሽበት፣ ፍትሐዊ ባልሆነ የሀብትና የገቢ ክፍፍል፣ ነጋዴው በውጭ ምንዛሪ እጦት እየተሰቃዩ ባሉበት ጊዜ የኢኮኖሚ ጉዳይ ወደ ጎን እየተገፋ፣ የፖለቲካ ትግል ያውም በብሔር የተከፋፈለ የዴሞክራሲ ጥያቄ ዋናው የአገሪቱ ጉዳይ ተደርጎ ይነገራል፡፡
ጭቁን ሕዝቦችን በብሔር ከፋፍለው ‹‹ይኼኛው የምታገልለት የብሔሬ ተወላጅ ነው፣ ያኛው የምታገለው የሌላ ብሔር ተወላጅ ነው፤›› ብለው የሚከፋፍሉ ፖለቲከኞች፣ የኩባን ትግል አብሮ መርቶ ፊደል ካስትሮ ሥልጣን እንደያዙ ሁለተኛውን የሥልጣን እርከን የፕላን ሚኒስትርነትን ሹመት ቢሰጡት ትግሌ ለዓለም ጭቁኖች ሁሉ ነው ብሎ ቦሊቪያ ሄዶ መንግሥት ለመጣል ሲታገል ተይዞ ከተገደለውና በ1960ዎቹ ተማሪዎች አብዝተው ከዘመሩለት የአርጄንቲና ተወላጅ ቼ ጉቬራ ዓላማ ጋር የሚጋጩ ናቸው፡፡
‹‹ስለብሔሬ ሰው እንጂ ስለሌላው ሰው አያገባኝም›› የሚል ጠባብ ፖለቲከኛነት ገብጋባነት ስለሆነ፣ በግለሰብ ብልፅግና የሚያምነውን የ1950ዎቹን የዘመናዊነት ጽንሰ ሐሳብ የኢኮኖሚ ልማት አመለካከት አይወክልም፡፡ ድክመቶቹ ሁሉ እንዳሉ ሆኖ የግሎባላይዜሽን ዘመንን ብልፅግና በገበያ ኃይሎች አማካይነት ለሠራ ሰው ሁሉ በእኩልነትና በውድድር ይዳረሳል:: በግለሰብ ልፋትና የላብ ዋጋ ላይ ያነጣጠረ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና የልማት ጽንሰ ሐሳብ አመለካከትንም አያንፀባርቅም፡፡
ኢኮኖሚስቶች እንደሚሉት አንድ ሰው ለፖለቲካ ሥልጣን ድምፅ ሲሰጥ ‹‹ሰውየውን ሳይሆን ዳቦውን ነው የመረጠው››፡፡ ዘመናዊና ሀቀኛ ፖለቲከኞችም ከራሳቸው ይልቅ ለሰው አሳቢ ሆነው ሕዝብ ‹‹ሰውን ሳይሆን ዳቦውን›› እንዲመርጥ የሚመክሩ ናቸው፡፡ ስለሆነም በዴሞክራሲ ስም ለመወከልና ፓርላማ ለመግባት ከመሽቀዳደም በፊት፣ ሕዝቡ ማንን ለምን እንደሚመርጥ ለሰው ብሎ ሳይሆን ለራሱ ሲል እንዲመርጥ ማስተማር፣ መጻፍ፣ መናገር፣ ሕዝብም የሚለውን መስማትና መማር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይኼን የሚያደርጉ ሰዎች ከእነርሱ ሥልጣን መያዝና ከእኔ በላይ ሰው የት አለ አስተሳሰብ የሕዝብን ብልፅግና የሚያስቀድሙ ናቸው፡፡
የልማታዊ መንግሥት ዓለም አቀፋዊ ስኬትን የመረመሩ የኢኮኖሚ ልማት ጠቢባን እንደ ምሳሌ ሲያነሱም ታይዋንና ደቡብ ኮሪያ በዘመናዊነት ከበለፀጉ በኋላ፣ ዴሞክራሲን በቀላሉ ሲገነቡ ከብልፅግና በፊት ዴሞክራሲን ለመገንባት የፈለጉት ፊሊፒንስ፣ ባንግላዴሽ፣ ካምቦዲያ፣ ታይላንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ህንድ በዴሞክራሲያዊውም በልማቱም ሁለገብ ስኬት ትርጉም የፈለጉትን ያህል አልሆነላቸውም ይላሉ፡፡
ጽንሰ ሐሳብና እውነታ
በፍጥነት ከበለፀጉት የቀድሞ ታዳጊ አገሮች መካከል ቻይናንና ደቡብ ኮሪያን የመሳሰሉ የምሥራቅ እስያ አገሮች፣ ታይዋንን ሲንጋፖርን የመሳሰሉ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች፣ በነዳጅ ሀብታም የሆኑ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችና አንዳንድ የላቲን አሜሪካ አገሮች ይጠቀሳሉ፡፡
እነዚህ አገሮች ምንም እንኳ የበለፀጉ አገሮች ወደ አገሮቻቸው የፋብሪካ ምርት ኤክስፖርት እንዳያደርጉ እክሎች ቢፈጥሩባቸውም፣ የኤክስፖርት ምርቶቻቸውን በጥንቃቄ በመምረጥ የበለፀጉ አገሮች ኤክስፖርት ገበያ ሰብረው በመግባት የተዋጣላቸው ልማታዊ መንግሥታት ሆነዋል፡፡
በቅድሚያ ሆንግ ኮንግ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖርና ታይዋን አራቱ ነብሮች ቀጥሎም ኢንዶኔዥያ፣ ማሌዥያና ታይዋን ኢምፖርትን በመተካትና ገበያ ሰብሮ በመግባት በኤክስፖርት ቅይጥ የንግድ ፖሊሲያቸው ዕድገታቸውን አፋጥነዋል፡፡ ከአፍሪካም ሞሪሽየስ የኢንዱስትሪ ዕድገቷን በማፋጠንና ቦትስዋና ያላትን የተፈጥሮና የማዕድን ሀብት ክምችት በአግባቡ በመጠቀም ምክንያት የተሳካላቸው ልማታዊ መንግሥታት ተብለዋል፡፡
ቻይናም በድርጊቷ አሜሪካን ኡኡ እስክትል ድረስ ብታበሳጫትም በዓለም አቀፍ ንግድ ስምምነት የተከለከሉትን ታሪፍና ኮታ ሳትጠቀም ምንዛሪዋን በማርከስ (Currency Undervaluation) ሥልቷ ብቻ፣ በአገሯ ውስጥ ኢምፖርትን ውድ በማድረግና በውጭ አገር ኤክስፖርቷን ርካሽ አድርጋለች፡፡ ኢምፖርትን በመተካት በኢንዱስትሪያላይዜሽን ወደ ውስጥ መመልከትና የገለልተኝነት ወይም ኤክስፖርት ተኮር የወጪ ንግድ ፖሊሲዎቿ የተዋጣላት የልማታዊ መንግሥት ተምሳሌት ሆናለች፡፡ በዚህም የገበያ ኢኮኖሚንም የኢኮኖሚ ልማትንም ፖሊሲዎች አጣምራ አስኬዳለች፡፡
አሜሪካ አፀፋዊ ዕርምጃ እንዳትወስድ ምንዛሪዋ ከብዙ አገሮች ምንዛሪ ጋር በዋጋ የተቆራኘ ስለሆነ ቀውስ ያመጣል ብላ ስላመነች አልቻለችም እንጂ፣ ከቻይና ጋር የምንዛሪ ማርከስ ጦርነት ውስጥ ይገቡ ነበር፡፡
በድህነት ከሚታወቁት የልማታዊ መንግሥታት መካከል ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸውና ሁከት ያልተለያቸው ባንግላዴሽና ፓኪስታን በተወሰነ ደረጃ ህንድ፣ እንዲሁም ኮትዲቯርን፣ ማላዊን፣ ኬንያን፣ ዛምቢያን፣ ዚምባብዌን በመሳሰሉት በዘርና በጎሳ ፖለቲካ ምክንያት ያልዘለቁ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች ይገኙባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያስ ከየትኛው ጎራ ትመደብ ይሆን? የትኞቹን ልማታዊ መንግሥታት ትመስላለች? ከልማታዊ መንግሥት ቅድመ ሁኔታ ባህሪያትስ የትኞቹን ታሟላለች? የትኞቹ ይጎድሏታል? ዓይነ ጥላችንን ገፍፈን ሳይመሽ በጊዜ እንመልከት፡፡ ‹‹ገበያ ሲያመልጥና ራስ ሲመለጥ አያስታውቅም›› እንዲሉ፡፡
መደምደሚያ
ባህልና ታሪክ በልማታዊ መንግሥት አፈጣጠር ላይ ተፅዕኖ አላቸውን? የምሥራቅ እስያ ልማታዊ መንግሥታት ተሞክሮ ወደ ሌሎች አገሮች ሊሸጋገርና በሌሎች አገሮች ሊገለበጥስ ይችላልን? የሚሉ ጥያቄዎች በልማታዊ መንግሥት ተመራማሪዎች ይነሳሉ፡፡ እኛም የዘመናዊነትና የጥገኝነት ቀደምት የኢኮኖሚ ልማት ጽንሰ ሐሳቦች ከልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ ጋር እንዴት ይገናዘባሉ? የቀድሞዎቹ ጽንሰ ሐሳቦች በኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲው ላይ ተፅዕኖ አሳድረዋልን? ብለን ስለራሳችን ሁኔታ መጠየቅ እንችላለን፡፡
ዛሬ በምናያት ኢትዮጵያ የ1950ዎቹና የ1960ዎቹ የዘመናዊነትና የጥገኝነት ጽንሰ ሐሳቦች ጎልተው ይታያሉን? የዘመናዊነቱና የጥገኝነቱ ሁኔታ የሚታየው እንደ ሸማችነት ነው? ወይስ እንደ አምራችነት? ብለን ራሳችንንም መጠየቅ እንችላለን፡፡ መነሻችን ላይ ማንን እንመስል ነበር? ዛሬ ማንን እንመስላለን? ከዛሬ ተነስተን ነገን ስናይ ማንን ልንመስል እንችላለን?
በኤክስፖርት ምርት የምዕራባውያንን ገበያ ሰብረው የገቡትን ደቡብ ኮሪያን፣ ታይዋንን፣ ታይላንድን፣ ሲንጋፖርን፣ ቻይናን ወይስ የሕዝባቸው ብዛትና የእርስ በርስ ሽኩቻ የኢኮኖሚያቸውን ዕድገት ያነቀውን ባንግላዴሽን፣ ፓኪስታንን፣ ህንድን? የእኛ የወጣቶች የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ሥራ ፈጠራ ፓኬጅ ከላቲን አሜሪካ አገሮች ከተሞች የኢኮኖሚ ልማት ፕሮግራም ጋር እንዴት ይነፃፀራል? ይመሳሰላል? ወይስ ይለያያል?
እነ ማንን እንደምንመስል፣ ከነማን እንደምንለይ፣ ፍርዱን ለአንባቢያን ትቼ በዘመናዊነትና በጥገኝነት ጽንሰ ሐሳቦች የኢኮኖሚ ልማት መነጽሮች ከተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ተነስቼ ስለእኛ የምለው የሚከተለውን ነው፡፡
እንደ ሸማች በዘመናዊነት ከፈረንጅ ሰልቫጅ ጨርቅ ለባሽ የአዲስ አበባ ባለመኪና አንስቶ እስከ እንስሳትና ሰዎች አብረው በሚኖሩበት ሣር ክዳን የገጠር ቤት ሳይቀር የሳተላይት ቴሌቪዥን ተጠቃሚ ሆነን በበለፀጉት አገሮች የዘመናዊነት ጽንሰ ሐሳብ ኢኮኖሚ ልማት ውስጥ የተዘፈቅን ነን፡፡
እንደ አምራች ግን ለጥቃቅን የቤት ውስጥ የፍጆታ ቁሳቁሶችና አነስተኛ ማምረቻ መሣሪያዎች እንኳን በበለፀጉት የነፃ ገበያ ካፒታሊስት አገሮች ኢኮኖሚ ላይ ጥገኛ እንደሆንን ነው፡፡ ይኼ እንደ ሸማች የመዘመንና እንደ አምራች የጥገኝነት ክፍተት ሰዓት ቆጥሮ እንደሚፈነዳ ፈንጂ ነው፡፡ እኛም ፈንጂው ላይ ተቀምጠን የሚፈነዳበትን ጊዜ የምንጠብቅ እንመስላለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
