Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

በጥልቀት መታደስ እስከ ምን ድረስ?

$
0
0

በዘመኑ ተናኘ

1977 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ታሪክ የክፉ ጊዜ እየተባለ ይጠራል፡፡ ወቅቱ የሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ ለረሃብና ለስደት የተዳረገበት ነው፡፡ ይህ ጊዜም በኢትዮጵያ ታሪክ ‹‹አሰቃቂው ረሃብ›› እየተባለ ይጠራል፡፡ በዚህ ወቅት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ለሞት የተዳረጉበት ነው፡፡ ዜጎች የሚመገቡት፣ እንስሳት የሚግጡትና የሚጠጡት አጥተው በየሜዳውና በየጫካው ቀርተዋል፡፡ ይህ ክስተት በተፈጠረበት ጊዜ የወቅቱ የአገሪቱ አስተዳደር በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጡንቻዎቹ የፈረጠሙና የዳበሩ ስላልነበሩ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ሳይሰጠው ቀርቷል፡፡ በዜጎቻችንም ላይ የከፋ ጉዳት አስከትሎ አልፏል፡፡

ይህ ችግር ከተከሰተ ከብዙ ዓመታት በኋላ በ2008 ዓ.ም. ዳግመኛ የከፋ ድርቅ በአገራችን ተከሰተ፡፡ በእርግጥ ከዚህ ቀደምም ቢሆን እንደዚህ ጊዜው የከፋ ባይባልም፣ አልፎ አልፎ በአገራችን አካባቢዎች ተከስቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፈው ዓመት ተከስቶ የነበረውን ድርቅ መንግሥትና ሕዝብ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመመደብና ወጪ በማድረግ ዜጎቻችንን ከሞት መታደግ ተችሏል፡፡ ይህም ጊዜ ኢሕአዴግ የተፈተነበት እንደሆነ በርካታ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

ይህ ተፈጥሮአዊ ክስተት ካስከተለው ችግር ባሻገር ኢሕአዴግ ባለፈው ዓመት በሰው ሠራሽ ችግሮችም ተፈትኗል፡፡ ዋነኛው የጽሑፌ ጭብጥ አድርጌ ለመጻፍና ለመተንተን የምፈልገው ጉዳይም በ2008 ዓ.ም. ኢሕአዴግ ስለተፈተነባቸው ችግሮችና በቅርብ ጊዜም ከእነዚህ ችግሮች ለመውጣት እንደ መፍትሔ አድርጎ እየተንቀሳቀሰበት ስላለው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ላይ አስተያየቴን ለማስፈር ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ ካሉ የኦሮሚያ ክልል ከተሞችና ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ከተቀሰቀሰው የሕዝብ ተቃውሞና ጥያቄ እስከ ወልቃይት፣ እንዲሁም ከአማራ ክልሏ መዲና ባህር ዳር እስከ ደቡብ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች በተነሱ ሕዝባዊ ተቃውሞች ኢሕአዴግ በኃይለኛው ተፈትኗል፡፡

ይህ ችግር በአገራችን ውስጥ ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን አስከትሎም አልፏል፡፡ የችግሩ መንስዔ ተደርጐ የሚወሰደው ደግሞ የመንግሥት ኢፍትሐዊ አሠራር፣ ሥር የሰደደ ሙስናና የወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ውስንነት እንደሆነ መንግሥት ያመነው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ የእነዚህ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ መስፋፋትና ውስብስብነታቸው እያደረ መጨመር የሕዝብ ቁጣና ጥያቄ በየአካባቢው እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ ችግር በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት እንዲወድም ከማድረግ ባሻገር ሊተካ የማይችለውን የሰው ልጅ ሕይወትም ቀጥፎ አልፏል፡፡ የአገራችን ስምና ታሪክም ተሸርሽሯል፡፡ ‹‹የቱሪስት መዳረሻ›› እየተባለች ትጠራ የነበረች ዛሬ ከዚህ ኪሎ ሜትር በላይ እንዳትሄዱ እየተባለ ለውጭ አገር ዜጎች የሚሰበክባት አገር ሆናለች (ምንም እንኳ በቅርቡ ይህ ክልከላ ቢነሳም)፡፡ በዚህም የተነሳ አገራችን ከቱሪዝም ታገኝ የነበረው ገቢ በአሁኑ ወቅት በ35 በመቶ እንደቀነሰ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚም በከፍተኛ መጠን ተጎድቷል፡፡ አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት ባለፈው ጊዜ ተከስቶ በነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ብቻ አገራችን በሁለት ዓመት ሊተካ የማይችል ኢኮኖሚ አጥታለች፡፡

ባለፈው ጊዜ ለሕዝብ ጥያቄ አፋጣኝ መፍትሔ ባለመሰጠቱ የተነሳ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ መሠረታቸው እየሰፋና ውስብስብ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የሚፈልገውን ያላገኘ ሕዝብም ጥያቄዎቹን ይዞ ወደ አደባባይ ወጥቷል፡፡

መንግሥትም ንብረትና የሰው ልጅ ሕይወት ከጠፋና ከወደመ በኋላ መፍትሔ ለመስጠት መንቀሳቀስ ጀምራል፡፡ ‹‹ጥልቅ የተሃድሶ እንቅስቃሴ›› በሚል መፈክር ችግሬን እቀርፋለሁ ብሎ ለሕዝቡ ምሎና ተገዝቶ ወደ እንቅስቃሴ ገብቷል፡፡   

መንግሥት ለችግሮቹ አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን የተለያዩ ለውጦችንና ተሃድሶዎችን አካሂዷል፡፡ ለሕዝብ ጥያቄ በአፋጣኝ መልስ ለመስጠት ውስንነት የነበረበትን ከፍተኛ የአመራር አካላት እንደገና የማዋቀርና ችሎታንና የሕዝብ ወገንተኝነትን መሠረት በማድረግ ሹም ሽር አካሂዷል፡፡

ኢሕአዴግ በጥልቅ ተሃድሶ ዘመቻው ወቅት ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች መካከል ባለፈው ጊዜ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅች (ኦሕዴድ) ያደረገውን የአመራር ለውጥ መውሰድ ይቻላል፡፡ ከዚህ ቀደም የኦሮሚያን ክልል ይመሩና ያስተዳድሩ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች የሕዝብ ወገንተኝነት ባላቸው የአመራር አካላት ተተክተዋል ተብሏል፡፡ የክልሉ ሕዝብ በተደጋጋሚ ጊዜ ያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችን በአፋጣኝ ለመመለስ አዲሱ የክልሉ አመራር የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴውን ጀምሯል፡፡ ከከፍተኛ አመራር እስከ ዝቅተኛ አመራር ድረስ የሥልጣን ሹም ሽር በማድረግ ሕዝቡ የሚጠይቃቸውን የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የክልሉ አዲሱ አመራር በሙሉ አቅሙ እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ተሰምቷል፡፡ በዚህም የተነሳ አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት የኢሕአዴግ በጥልቀት መታደስ ማሳያ ከሆኑ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል አንዱ በክልሉ የተካሄደው የሥልጣን ሹም ሽር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ምሥጋና ተችሮታል፡፡

ኢሕአዴግ ከዚህ አለፍ ሲልም በ2009 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲከፈት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በምክር ቤቱ ተገኝተው የ2009 ዓ.ም. የመንግሥት የትኩረት ነጥቦችን የዘረዘሩበት፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለትኩረት ነጥቦች ማብራርያና ከምክር ቤቱ አባላት ለሚያነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በተገኙበት ወቅት ያደረጉት የካቢኔያቸው ሹም ሽር ይበል ያሰኘ ጉዳይ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በወቅቱ የመንግሥታቸውን በጥልቅ የመታደስ ስኬት እውን ለማድረግ የካቢኔ ሹም ሽር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ ለምክር ቤቱ አባላት አብራርተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ኢሕአዴግ ይታማበት ከነበረው ለካቢኔነት የሚያበቃው በፖለቲካ ወገንተኝነት ሳይሆን፣ መሪዎች ባላቸው የሕዝብ ወገንተኝነትና የትምህርት ደረጃ ላይ ብቻ በመመርኮዝ አመራር የሚሆኑበትን መንገድ ቀይሷል፡፡ በዚህም ዘዴ በመጠቀም በትምህርታቸው የገፉና የሕዝብ ወገንተኛ ናቸው የተባሉ አመራሮችን ሾሟል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክም የጦር መሣሪያ ይዘው ሳይሆን ብዕር ጨበጠው ያሳለፉ አካላት የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ተቀላቅለዋል ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን፡፡ ይህ ደግሞ በጥልቅ የመታደስ ጉዞ አንዱና ዋነኛው ማሳያ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢሕአዴግ አሁንም በጥልቅ ተሃድሶ ጉዞው ያልፈታቸውና የሕዝብ ቅሬታ ሆነው የዘለቁ ጉዳዮች እዚህም እዚያም ከመሰማት አልቦዘኑም፡፡ ከነዚህ መካከል አሁንም ድረስ በብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) እና በሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) የአመራር አካላት ላይ ግልጽና የሚታይ የሥልጣን ሹም ሽር አለማድረጉን በመጥቀስ፡፡ የሕዝብን ብሶት ያባባሱና ለሕዝብ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ያልሰጡ ከፍተኛ አመራሮች አሁንም በሁለቱም ክልሎች  የተለያዩ አመራሮች ውስጥ እንዳሉ በማብራራት፡፡

በእርግጥ የሁለቱ ክልሎች የአመራር አካላትና የሚዲያ ሰዎች ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎች እንደሚገልጹት ከሆነ፣ የየክልሎቻቸው ከፍተኛ አመራር በጥልቅ የመታደስ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳሉና በተወሰኑ የአመራር አካላት ላይም ዕርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ይደመጣል፡፡ የብዙዎች አስተያየት ግን ለምን የተወሰዱ ዕርምጃዎች በግልጽ ለሕዝብ ይፋ አይሆኑም? የሚል ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ኢሕአዴግ አሁንም ከማድበስበስ አባዜው አልተላቀቀም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡

በ1960ዎቹ ውስጥ ዝነኛና ተወዳጅ የነበረው ጋዜጠኛ ጀምስ ዊልሰን በአንድ ወቅት ለኢንኪዋየር መጽሔት ባቀረበው ዘገባ፣ ‹‹ማንም መንግሥት የሕዝብ የችግር ምንጭ የሆነን ጉዳይ አድበስብሶ ባለፈ ቁጥር የባሰ ችግር ያስከትላል፤›› ይላል፡፡ ይህንን ጉዳይ ዘርዘር አድርጎ ሲያቀርበው፣ ‹‹ችግርን ካድበሰበስነው ከሀቅ ይልቅ በተስፋ እንድንኖር ያደርገናል፡፡ ይህ ተስፋ ሲያልቅና ሲሟጠጥ ደግሞ እንደ ብርሃን ወለል ብሎ የሚታየው ሀቅ የችግር ሥር መሠረት ይሆናል፡፡ ሲበዛ ሲበረክት ደግሞ ጎስቋላው ክፍል መንቀሳቀሱ አይቀርም፡፡ የበገሌ አመለካከት (Relative Deprivation) እየዘቀጠ መሄድ ሊገታ የማይችል ኃይል ይፈጥራል፡፡ በሌላ መንገድ ሲገለጥ የጎስቋሎች አመፅ፣ የድህነት በባሰ ድህነት መከሰት፣ የአብዮት ተስፋ መፋፋት (A revolution of rising expectation) መሆኑ በሒደት ከፍ ይልና የአብዮትን ምድጃ የሚቆሰቁስ ይሆናል፤›› ይላል፡፡ በአገራችን ከወራት በፊት ተከስቶ የነበረው ሁኔታም ይህንን መሰል አብዮት የተከተለ ነው፡፡

ሥራ አጥነት የአብዮቱን ምድጃ ቆስቁሷል፡፡ የመንግሥት የአመራር አካላት እጀ ረጅምነትና ሙሰኛነት አብዮቱን አፋፍሟል፡፡ ጀምስ ዊልስን እንደገለጸው ʻአደባብሰው ቢያርሱ በዓረም ይመለሱʼ ነውና ነገሩ አሁንም ኢሕአዴግ በጥልቅ የተሃድሶ ጉዞው ማድበስበስን ትቶ በኦሮሚያ ክልልና በፌዴራል መንግሥት የወሰደውን ዓይነት ዕርምጃ በትግራይ፣ በአማራ እንዲሁም ደበቡብ ክልሎች መውሰድ አለበት፡፡ የተወሰደ ዕርምጃ ካለም ለሕዝቡ ይፋ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡  ወይም ደግሞ በጥልቅ መታደስ ጊዜ ዕድሳት የማያስፈልጋቸው አመራሮችና ክልሎች ካሉ ለሕዝቡ ይፋ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ወቅት መታደስ የማያስፈልግበት ምክንያትም አብሮ በተብራራ ሁኔታ መገለጽ አለበት፡፡

በእኔ አመለካከት ግን በፌዴራሉ ከፍተኛ የመንግሥት አመራር አካላትና በኦሮሚያ ክልል የተደረገው በጥልቅ የመታደስ ጉዞ በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደር አካላትም መደረግ አለበት፡፡ ይህ ከሆነ የአብዮቱን ምድጃ የሚቆሰቁሱ አካላት አርፈው ይተኛሉ፡፡ እጃቸውንም ለሰላም ይዘረጋሉ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው Zemenutenagn09@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡   

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles