Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

የፍትሕ ሥርዓቱ በሕግ ብቻ እንዲመራ ለህሊናችን ታማኝ እንሁን!

$
0
0

በኤፍሬም አፈረ

በቅርቡ በሪፖርተር ጋዜጣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል የሰብዓዊ መብት መምህርና ተመራማሪ አቶ ጌታሁን ካሳ ‹‹የፍትሕ ሥርዓቱ አመኔታ ያተረፈ ሕዝብ የሚቀበለውና በሕግ ብቻ የሚመራ መሆን አለበት›› በሚል ርዕስ ለሪፖርተር ጋዜጣ የሰጡትን ቃለ ምልልስን ሚያዝያ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በወንጀል ጉዳዮች የፍትሐዊ ዳኝነት መመዘኛዎች (Fair Trial Standards) በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ ዕይታ አስመልክቶ የቀረበው የጥናታዊ ጽሑፉን ዓውደ ጥናት ዝርዝር በመመልከት ከተጨባጭ የጉዳዩ ክስተት ማሳያ የተካሄደውን ይኼንን የማዳበሪያ ጽሑፍ ከቃለ መጠይቁ ዋና ዋና ሐሳቦችን በመውሰድ ለማዘጋጀት ተሞክሯል፡፡

ጊዜው ጥቅምት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በመዲናችን በአንድ የመንግሥት የልማት ድርጅት ተቋም የተፈጠረ ክስተት ነው፡፡ ይኼም የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ በክፍሉ ሥር የሚገኘውን የስብሰባ አዳራሽ አለመዘጋቱን ሲረዳ በሰርቪስ ቤቱ ከደረሰ በኋላ የቅርብ አለቃውን በማሳወቅ፣ ወደ ድርጅቱ ከምሽቱ 1፡40 ሰዓት በመመለስ ለመዝጋት ይመለሳል፡፡ በወቅቱ ሥራ ላይ ያልነበረ ቢሆንም ያለሥራ በምድረ ግቢው የነበረ ሌላ ሠራተኛ ግቢው ውስጥ የገባ ሠራተኛ አለ ብሎ በቦታው ላይ ለነበሩ ሠራተኞች ይናገራል፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አዳራሹን ዘግቶ ሲመለስ ምን ታደርጋለህ? በማለት ባለሙያውን ከኋላ ተከትሎ ለመደብደብ ከመሞከር ውጪ በወቅቱ እንዳችም የተናገረው አልነበረም፡፡ ባለሙያው በሥነ ሥርዓት በጥበቃ ሠራተኞች ተፈትሾ መውጣቱንና ወደ ቤቱ መሄዱን በወቅቱ የተመለከትነው ትዝብት ነበር፡፡

ሆኖም በወቅቱ ኃላፊነቱን ሊወጣ የመጣን ባለሙያ ተግባር ወደ ሌላ አቅጣጫ በመቀየር ያለሥራ በድርጅቱ እስከ ምሽቱ 1፡40 ሰዓት ተገኝቷል የሚል መረጃን ብቻ መሠረት በማድረግና በመቀበል የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ ያ ሠራተኛ ባለሙያውን የንብረት ክፍሉን በር ሲነካ ተመልክቻለሁ በማለቱ ብቻ ከሥራውና ከደመወዝ እንዲታገድ፣ በአካባቢው ባለው ፖሊስ ጣቢያም በሐሰት ለቀናት እንዲታሰርና ከተቻለም እንዲፈረድበት ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ በባለሙያው ላይ በሰውም ሆነ በአሻራ ማስረጃ ተብሎ ሊቆጠር የሚችል ነገር ባለመገኘቱ ከቀናት በኋላ የተፈታ ሲሆን፣ በባለሙያው ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ የነበረው ሥራ አስኪያጅ በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ ከአንድ ሳምንት በኋላ ከሥራ እንዲሰናበት ተደርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር በዚሁ ወር በኃላፊው ላይ ይስተዋሉ በነበሩ የሙስና ብልሹ አሠራሮች ሳቢያ ከቀናት በኋላ በቁጥጥር ሥር ውሎ ጉዳዩ በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ በድርጅቱ ስም የተከሰሰው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ግን ከፀረ ሙስና ኮሚሽን በተሰጠው ጊዜያዊ ከለላ ወደ ሥራ ተመልሶ በድርጅቱ አጠቃላይ ሠራተኞች የተቋሙን የመልካም አስተዳደር ችግር ሊያጣራ ይችላል ተብሎ ይመረጣል፡፡ ባለሙያው ከኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም ባለሙያውን ለማሳሰር ምክንያት የሆነው ግለሰብ የተፈጸሙ የተለያዩ የብልሹ አሠራር ችግሮችን በተጨባጭ በመለየት የተለያዩ ግኝቶችን በማቅረብ ለከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ቀርቦ፣ ለተቋሙ በአዲስ ሁኔታ የተመደበው ሥራ አስኪያጅ የተለያዩ የማስተካከያ ውሳኔዎችን እንዲወስን አቅም ፈጥሯል፡፡

በሌላ በኩል ኅዳር 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጉዳዩን አስመልክቶ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ለሥራ ወደ ድርጅቱ ኃላፊነቱን ለመወጣት ስሄድ የድብደባ ሙከራ ሊፈጸምብኝ ተሞክሯል ብሎ ሪፖርት ለማድረግ ፖሊስ ጣቢያ ቢገኝም፣ በወቅቱ የነበረው  የጣቢያው ዓቃቤ ሕግ፣ የፖሊስ ጣቢያው መርማሪ፣ የፖሊስ ጣቢያው ኃላፊና የከሳሽ ድርጅት ኃላፊዎች የተለያዩ ጫናዎችን በማድረግ በወቅቱ ክስ እንዳይመሠረት ያደርጋሉ፡፡ በዕለቱ ከጠዋቱ ጀምሮ በቦታው የተገኘው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ‹‹የድብድባ ሙከራ ተፈጽሞብኛል ሊታይልኝ ይገባል፤›› በሚል ጥያቄ ቢያቀርብም ሰሚ ሳያገኝ ይቆያል፡፡

በቀጥታም ፖሊስ በተቋሙ በቦታው የነበሩ ምስክሮችን ቃል ይቀበላል፣ ተነካ የተባለውን የንብረት ክፍል በር አሻራም ያስነሳል፡፡ ሆኖም ከመነሻው በቦታው የነበሩ እማኞች የተቋሙ ኃላፊ የፈለጉትንና ከሳሽ ነኝ ያለውን ግለሰብ ለማስደሰት ሳይሆን ለህሊናቸው ቃላቸውን ቢሰጡም፣ የእነሱን ቃል ችላ በማለት የአሻራ ውጤት እስኪመጣ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያውን የጣቢያ ዋስትና ይከለክላሉ፡፡ ፍርድ ቤት በማግሥቱ ከሳሽ ፖሊስ ሆኖ ለዳኛ ያቀርባሉ፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው፣ ‹‹ጉዳዩ ቂም በቀል እንደሆነ ከመነሻው ጠቋሚ ነኝ፤›› ያለው ግለሰብ በተጨባጭ የተለያዩ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮቹን ስላቀረበበት፣ እንደ ተቋም የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በግልጽ ስለሚታገል የተፈጸመበት ድርጊት መሆኑን አብዛኛው ሠራተኛ የሚያውቀውና ፀሐይ የሞቀው ሀቅ በመሆኑ፣ ሠራተኛው በድርጊቱ ተገርሞ የፍትሕ አካላትን ሥራ ይመለከት ነበር፡፡

ከሳሽ ፖሊስ፣ ዋስትና ከልካይም ፖሊስ በሆነበትና የጊዜ ቀጠሮ በማግሥቱ የጠየቀው ፖሊስ ለሰባት ቀን የአሻራ ውጤትና አሳማኝ ማስረጃ ሊያመጣ ባለመቻሉ ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩት ዳኛ በዋስትና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው እንዲፈታ ያደርጋሉ፡፡ በቂ ወንጀል ማቋቋም የሚያስችል መረጃ ያልነበረው የጣቢያ ዓቃቤ ሕግ ፋይሉን ለመዝጋት የሚጠቅመውን የሽፋን አንቀጽ በመጥቀስ በ42/1/ሀ ይዘጋል፡፡ ይኼም ከመነሻው ለሕግ ውግንና ባለመቆሙ ምክንያታዊ ያልሆነ ክስና አዋጁን ሽፋን በማድረግ የተጠቀመበት በመሆኑ የተዘጋ ቢሆንም፣ ባለሙያው በስም ማጥፋት የሐሰት ክስ መነሻ የሆነው ሠራተኛ እንዲከሰስለት ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ለመክሰስ በቂ የሆኑ ማስረጃዎች ዓቃቤ ሕግ ቢቀርብለትም፣ ክስ ከመመሥረት ይልቅ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 613 መሠረት ጉዳት ለማድረስ የተፈጸመ ነው ለማለት አይቻልም ተባለ፡፡ ማንም ሰው ወንጀል ሲፈጽም ዝም ብሎ ማየት ስለሌለበት ጥቆማ መስጠት እንደሚችል የወ/መ/ስ/ ሕጋችን ይደነግጋል፡፡ የተሰጠ ጥቆማ ሐሰት ከሆነ መወንጀል እንደሚያስጠይቅ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 446 እንደሚያስቀምጥ ቢያትትም በሐሰት መወንጀል የተጠየቀ ሰው ደግሞ በስም ማጥፋት ወንጀል እንደማይጠየቅ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 613/5/ ተቀምጧል፡፡ ይሁንና ሌሎችንም ምክንያቶችን በመስጠት ተገቢው ሕጋዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ያልፈለገው በየደረጃው የሚገኝ ዓቃቤ ሕግ ድርጊት የሚገርም ሳይሆን፣ በአገራችን ስም ማጥፋት የሁልጊዜ ተግባር በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት ሳይሰጡ ቀርቷል፡፡

ክብር ለዴሞክራሲ ተቋማት በተለይም ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይሁንና በሥልጣናቸው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያውን ለማሳሰር ሲታትሩ የነበሩት የተቋሙ ኃላፊ፣ በሙስናና ብልሹ አሠራር ተጠርጥረው ለእስር ባይዳረጉ ኖሮ ይኼ ታሪክ በእዚህ ሁኔታ ሊወጣ ባልቻለም ነበር ‹‹ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ››  ሳይሆን ‹‹እውነት አይክሰስህ›› ማለት ይቀላል፡፡

በተቋም የመልካም አስተዳደር ችግር ሲኖር መከሰስ የሚገባው የማይከሰስበት፣ ሊያስከስስ የማይችል ድርጊትና ሁኔታ ግን ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም የሚፈጸምበት ሁኔታ እንዳለ ጉልህና ተጨባጭ መገለጫ መሆኑን በእርግጠኛነት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

በተመሳሳይ በመዲናችን ከአቃቂ ቃሊቲ ወደ አዲስ አበባ ሊገባ የነበረና የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የምርት ሱፐርቫይዘር ‹‹በሰነድ ተረክቦት ሆኖም የገባበት አልታወቅም›› በሚል ሲድበሰበስ የነበረውና ለፖሊስ ‹‹ክስ ለመመሥረት የይርጋ ጊዜ አልፎታል፤›› ሲል የነበረውና ‹‹በሕገወጥ ሁኔታ ታርዶ የተያዘው የ800 ኪሎ ግራም የአሳማ ሥጋ መዲናቸንን ቢያነጋግርም፣ የተቋሙ አመራርና የሕግ ክፍል ተጠርጣሪውን በሥነ ሥርዓት ዕርምጃ በደመወዝ ቅጣት ያለፈው ቢሆንም፣ ችግሩ ከሥነ ሥርዓት ዕርምጃ ያለፈ የሰው ልጅ ሕይወትን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነው፤›› በማለት የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባደረገው ማጣራት አስታውቋል ለመጥፋቱ ምክንያት የሆነውንና ለሕዝብ ግንኙነቱ የሐሰት መታሰር ምክንያት የሆነው ሠራተኛ በዚሁ ዓመት በቁጥጥር ሥር ውሎ የተፈታ ቢሆንም፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል፡፡ በእነዚህም ‹‹አርቀህ አትቆፍር የሚገባበትን አይታውቅም›› እንዲሉ የተቋሙ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ይኸው ግለሰብ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል፡፡

በእነዚህም በዘርፉ የምርምር ሥራቸውን ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል፣ የሰብዓዊ መብት መምህርና ተመራማሪ እንደጠቆሙትም የወንጀል ክሶችና የዳኞች የውሳኔ ነፃነት ሰፊ በሆነባቸው ቦታዎች ዳኞች፣ ዓቃቤያን ሕግና ፖሊስን ከተከሳሽ ይበልጥ ያዳምጣሉ፣ ዋስትና መፍቀድ ሲገባው ይከለክላሉ፣ ምርመራው ባለቀ ምንም ተጨማሪ ጊዜ በማያስፈልገው ጉዳይ ላይ ጊዜ ቀጠሮ ይፈቅዳሉ፡፡ በተመሳሳይም ‹‹የስም ማጥፋት ተፈጽሞብኛል ሕጉን በእኩል ደረጃ ሊያስፈጽሙልኝ ይገባል፤›› ብሎ ተበዳይ ሲያቀርብ ከጣቢያ ጀምሮ ያለ ዓቃቤ ሕግ የዘጋውን፣ በየደረጃው ይኼንኑ ከማፅናት ውጪ ምንም ፋይዳ ሳይገኝ በዘርፉ የመጨረሻው አካል ድረስ ቢሄዱም ስም ማጥፋት ባህላችን ነው፣ ከባድ ስርቆት ግን ከባድ ነው በማለት በንፅፅር የፍርድ ግዜ ርዝማኔ በማስቀመጥ እንደ ቀላል ያዩታል፡፡ ይኼንን ነው ‹‹ክስተቱ አልፎ አልፎ የሚታዩ አንዳንዴ የሚያጋጥሙ ብሎ ማለፍ መቅረት እንዲሁም ተጠያቂነት ሊበጅለት ይገባል፤›› ብሎ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል የሰብዓዊ መብት መምህርና ተመራማሪ አቶ ጌታሁን ካሳ የሚያስቀምጡት፡፡ በመሆኑም የፍትሕ ሥርዓቱ አመኔታ ያተረፈ፣ ሕዝብ የሚቀበለው፣ በሕግ ብቻ የሚመራ መሆን አለበት የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ እናም ዋስትና በመከልከል የሚደርስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ እንደ ንፁህ የመቆጠር መብት መጣስና ተገቢ ምላሾች የማይገኙባቸው ሁኔታዎችን በወቅቱ በመፈተሽ በ42/1(ሀ) ስም መዝጋት ብቻ ፍትሕን ማረጋገጥ አይደለም፡፡ ከእዚህ ጋር የሚስተዋሉ የመብት ጥሰቶችን፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራትና ሥልጣንን ያላግባብ የመጠቀም አዝማሚያዎች ከወዲሁ ሊፈተሹ ይገባል፡፡ በቂም በቀል የተጎዱ ዜጎችን እንታደጋቸው፡፡ በጥልቅ ተሃድሶ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ብልሹ አሠራርን ለማስወገድ ከሕግና ከሞራል ተፃራሪ ተግባራትን ባለመፈጸም ለሙያችንና ለህሊናችን  ታማኝ እንሁን፡፡      

ከአዘጋጁ፡-ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን ኢሜይል አድራሻቸው Samuelfrea@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡  

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles