በሉሉ ድሪባ
በቅርቡ ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው በመመረጣቸው ለበርካታ አገሮችና መሪዎች ጥያቄ ፈጥሯል። በብዙዎች ዘንድ የዶናልድ ትራምፕ መመረጥ ያልተጠበቀ ከመሆኑም ባሻገር፣ የፕሬዚዳንቱ የውጭ ፖሊሲ ከዚህ በፊት ከነበሩት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ለየት ያለና አወዛጋቢ ነው። የትራምፕ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚያጠንጥነው ቅድሚያ ለአሜሪካ በሚለው ላይ ነው፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ከዓለም ዙሪያ ወደ አሜሪካ የሚደረገውን ስደትን መቆጣጠር፣ አሜሪካ ከሌሎች አገሮች ጋር የሚኖራትን የንግድ እንቅስቃሴ መቀየር፣ የዓለም አየር ንብረትን በተመለከተ የተለየ አቋም መያዝና ለታዳጊ አገሮች የሚደረጉ ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን መቀነስ ወይም መከልከል የሚሉት በግንባር የሚጠቀሱ ናቸው። እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ የሊብራል ሥርዓትን በመቃወም አምባገነናዊ መሪዎችን ለምሳሌም ለሩሲያ መሪ ለፑቲን በይፋ አድናቆቱን በመግለጽ ቀደም ሲል የአሜሪካ ወዳጅና አጋር ከሆኑት አገሮች ጋር ያለው ግንኙነት እንደሚለወጥ እየገለጸ ይገኛል።
እንዲሁም ከሙስሊሙ ዓለም ጋር ያለው ግንኙነትና አክራሪነትን ለመዋጋት የሚከተሉት ስትራቴጂ ግልጽነት ካለመኖሩም በተጨማሪ፣ ከታዳጊ አገሮች ለአብነትም ከአፍሪካ አገሮች ጋር የሚኖረው የአሜሪካ ወዳጅነትና ሰብዓዊ ዕርዳታ ጋር ተያይዞ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሲያነሱዋቸው የነበሩ ጉዳዮች ከዚህ በፊት ያልተለመዱ ከመሆናቸው የተነሳ በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ ጥያቄ ጭረዋል። በተለይም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ዶናልድ ትራምፕ ለአፍሪካ አገሮች ምን ዓይነት ፖሊሲ እንደሚኖራቸው ሰፋ ባለ መልኩ ባይገልጹም፣ ስለአኅጉሩ ጥቂት ከተባሉት መካከል ዋነኛው የአፍሪካ መሪዎች ለሕዝቦቻቸው መልካም አስተዳደር ስለሌላቸው እንደገና 100 ዓመታት በቅኝ ግዛት መተዳደር አለባቸው በማለት በትዊተር ገጻቸው ላይ ያሰፈራት ይገኝበታል።
በመሆኑም የብዙዎቹ ጥያቄ በቅርቡ የተመረጡት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ያደረጉዋቸው ንግግሮችን ተግባራዊ ያደርጋሉ? ወይስ አያደርጉም? የሚለው ነው። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ሁለት አተያዮችን ማየት ያስፈልጋል። የመጀመሪያው የዶናልድ ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀጣይነት ያለው፣ የቆየና በግለሰቡ እምነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የግለሰቡ ልምድ ማነስ፣ የአሜሪካን የውጭ ግንኙነቶች ውስብስበነት ጠንቅቆ ያለማወቅና የአገሪቱን ጥቅሞች ለይቶ ከማስከበር አኳያ ፕሬዚዳንቱ አሁን ያላቸው ግንዛቤ የተዛባ በመሆኑ፣ ወደፊት ከውጭ ጉዳይ ባለሙያዎች ጋር በመወያየት መሥራት እንደሚችሉ ይገልጻሉ።
ስለሆነም አሁን መታየት ያለበት በቅስቀሳ ወቅት ፕሬዚዳንቱ ያደረጓቸው ንግግሮች ሳይሆኑ አሜሪካ ከሌሎች አገሮች ጋር በምታደርገው ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሞችን ማዕከል ማድረግ አለባቸው። ማለትም የፕሬዚዳንቱ አመለካከትና እምነቶች በአገሪቷ ውጭ ግንኙነቶች ላይ ያለው ተፅዕኖ የማይካድ ቢሆንም፣ የአገሪቱን ጥቅም በተሻለ ሁኔታ ተገንዝቦ ውሳኔ ይሰጣሉ በማለት የሚሾሙዋቸው የካቢኔው አባላትና አማካሪዎችም የላቀ ድርሻ ይኖራቸዋል። ከዚህ በመነሳት አሜሪካ ከአፍሪካ ቀንድ ጋር የሚኖራት ግንኙነት የሚወሰነው ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ወቅት ያደረጓቸው ቅስቀሳዎችን ብቻ ሳይሆን፣ የአሜሪካ መሠረታዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎችንና በቀጣናው አገሪቷ ያላት ጥቅሞችን ባማከለ መንገድ የፕሬዚዳንቱንና የሌሎች ሹማምንቶች አመለካከቶችንና እምነቶችን፣ እንዲሁም በዘርፉ ላይ የቆዩ ሙያተኞችንና አማካሪዎችን አስታውሰው ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት መቻል አለባቸው።
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላምም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እ.ኤ.አ. የ2016 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማሸነፍ፣ አሜሪካ ከአፍሪካ ቀንድ ብሎም ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራትን የግንኙነት ሁኔታዎች በመዳሰስ ምን ዓይነት ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ለመገመት ነው። በዚህ መሠረት ይህ ሪፖርት ሦስት ክፍሎችን የያዘ ሲሆን፣ የመጀመሪያው አሜሪካ ከአፍሪካ ቀንድ ጋር ያላትን የቆዩ የግንኙነት ታሪኮችን መዳሰስና አገሪቷ ወደፊትም በቀጣናው የሚኖራት ብሔራዊ ጥቅሞችን መተንተን፣ በሁለተኛው ክፍል አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ጥቅሞችንና ተግዳሮቶችን መዳሰስ፣ በሦስተኛ ክፍል ደግሞ ለአዲሱ ፕሬዚዳንትም ሆነ ለሌሎች ሹማምንት አፍሪካ ቀንድ ብሎም ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ምን ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንደሚኖራት በመተንተን የተለያዩ ትዕይንቶች (Scenarios) ማሳየት ነው።
- በአፍሪካ ቀንድ ያላት ፍላጎት
አፍሪካ ቀንድ ለአሜሪካ ስትራቴጂካዊ ቀጣና ነው፡፡ ምክንያቱ የቀጣናው ጂኦግራፊያዊ መገኛ በአንድ በኩል በነዳጅ ከበለፀገው የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች ባለው ቅርበት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ ሦስት አኅጉሮች ማለትም እስያ፣ አውሮፓና አፍሪካን የሚያገናኝ ቁልፍ ቦታ ነው። ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ ኃያላን አገሮች ቀጣናውን ለመቆጣጠር ፉክክር በማድረግ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅትም በአፍሪካ ቀንድ ፍላጎት ካላቸው አገሮች መካከል በዋናነት የባሕረ ሰላጤው ዓረብ አገሮች፣ ግብፅ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ቻይናና ህንድ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ለአሜሪካ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ካላቸው አካባቢዎች አንዱ አፍሪካ ቀንድ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ለአገሪቷ የቀጣናው አስፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። ለአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ አስፈላጊነት በአንድ በኩል ቀጣናው ከመካከለኛ ምሥራቅ ጋር ያለው ጂኦ-ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ትስስሮች ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አሜሪካ ከሌሎች አፍሪካ አገሮች ጋር የጠበቀ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ለማድረግ አፍሪካ ቀንድን መቆጣጠር ይኖርባታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ1998 የአሜሪካ ኤምባሲዎች በምሥራቅ አፍሪካ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ2001 ‹‹የ9/11›› ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከምታደርገው እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ፣ ቀጣናው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ትኩረት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። አፍሪካ ቀንድ ለአሸባሪዎች መጠለያና ለእስልምና አክራሪነት ተጋላጭ ሥፍራ ነው። ለዚህም አመላካች የሚሆነው አብዛኛው የቀጣናው ማኅበረሰብ የእስልምና ተከታዮች መሆናቸውና ቀጣናው የእስልምና አክራሪነት ማፍለቂያ ከሆኑ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር ማኅበራዊ ትስስር ያላቸው መሆኑ ነው። ለምሳሌም አልቃይዳ በአካባቢው ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴና በአሁኑ ወቅትም የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን እንቅስቃሴ ቀጣናው ምን ያህል ለእስልምና አክራሪነትና ለሽብርተኝነት ተጋላጭ እንደሆነ ያሳያል። ስለሆነም ያለፉት የአሜሪካ መሪዎች ክሊንተን፣ ቡሽና ተሰናባቹ ኦባማም አሜሪካ በቀጣናው ያላትን ፍላጎት ለማስከበር ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ፖሊሲዎች ይከተሉ ነበር።
በቀጣናው የአሜሪካ ዋና ተልዕኮ በጥቅሞቿና በወዳጆቿ ላይ ጥቃት እንዳይደርስ በማድረግ፣ በአካባቢው የሚገኙ ዓለም አቀፋዊ የሽብር ቡድኖችና የባህር ላይ ዘራፊዎችን እንቅስቃሴዎች መግታት፣ መደምሰስና የቡድኖቹን ትስስርና ግንኙነቶችን መበጣጠስ ላይ ያተኮረ ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴዎችን ታደርጋለች። ይህንን ዓላማዋን ከግብ ለማድረስ አሜሪካ ከአፍሪካ ቀንድ ዋነኞቹ ወዳጆቹዋ ከሆኑት ከጂቡቲና ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት ስትሠራ ቆይታለች። ለዚህም እ.ኤ.አ በ2002 ዓ.ም. በጂቡቲ ወታደራዊ የጦር ሠፈር ወይም ጣቢያ በማቋቋም ጠንካራ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ትገኛለች። በተመሳሳይ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጋርም በአጋርነት የአካባቢው ደኅንነት ለመጠበቅ ይሠራሉ።
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትም ቢሆኑ የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለቲካዊና ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን ያገናዘበ ፖሊሲ ይከተላሉ የሚል ግምት አለ። ምክንያቱም የቀጣናው ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለአሜሪካ የላቀ በመሆኑ፣ ይህንን ጥቅም ለማስከበር ቀደም ሲል እንደነበረው የተለያዩ ስትራቴጂካዊ ዕርምጃዎችን መከተል ይኖርባቸዋል። ዶናልድ ትራምፕ ምን ዓይነት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በአፍሪካ ቀንድ ሊኖራቸው እንደሚችል ከማየት በፊት፣ ቀደም ሲል የአሜሪካ መሪዎች በቀጣናው ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር ሲከተሉዋቸው የነበሩ ስትራቴጂዎችን ማየት ተገቢ ነው።
ቀዝቃዛው ጦርነት ካከተመ በኋላ አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ሦስት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ስትከተል እንደነበረች ውድዋርድ የተባለው አጥኚ ገልጿል። የመጀመሪያው ሙሉ በሙሉ በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በቀጣናው ያላትን ጥቅም ማስጠበቅ ሲሆን፣ ይህንን ለማድረግ እንደ ሽፋን ሆኖ የሚያገለግል አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ ለመከላከል የሚል ነው። ለአብነትም እ.ኤ.አ 1992-93 በሶማሊያ ውስጥ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት የሚገለጸው በሰብዓዊ ቀውስ አማካይነት ነው። በዕርምጃው ምንም እንኳን የሰው ሕይወት ተርፏል ቢባልም፣ አፈጻጸሙ በተለያዩ ሥልቶችና ታክቲኮች ከተቀረው የዓለም ማኅበረሰብ ጋር በደንብ ያልታቀደና ያልተደራጀ ኦፕሬሽን ነበረ፡፡ ለአሜሪካ ፖሊሲም ሆነ መሬት ላይ ያለው እውነታ ለሶማሊያ ማኅበረሰብ ያልተጠበቀና ያልተፈለገ ውጤት አስከትሏል። እ.ኤ.አ. በ1998 በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ ኤምባሲዎቿ በአልቃይዳ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ በደኅንነት ምክንያት አሜሪካ በቀጣናው የኃይል ዕርምጃ ተጠቅማ የሰብዓዊ ቀውስ የመከላከል ፖሊሲዋን አቋርጣለች። በአጠቃላይ በ1990ዎቹ አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ የነበራት የወታደራዊ ዕርምጃ ፖሊሲ እንደተጠበቀው ስኬታማ ሊሆን አልቻለም።
አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ስትጠቀም የነበረው ሁለተኛው ስትራቴጂ ፀረ አሜሪካ የሆነን መንግሥት ማወክ (Destabilization) ሲሆን፣ ይህንን ሥልት ስትጠቀም በቀጣናው ባሉ ተቃዋሚ ኃይሎችና ጎረቤት አገሮች አማካይነት አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ በማድረግ ነው። ለምሳሌም በ1990ዎቹ አጋማሽ የሱዳን መንግሥት ለእስልምና አክራሪዎች የሚሰጠውን ሽፋን ለማስቆም የአሜሪካ መንግሥት እንደ ስትራቴጂ የተጠቀመው በቀጣናው ያሉ አጋር አገሮችን በመጠቀም ለሱዳን ተቃዋሚዎች ድጋፍ መስጠት ነው። ይህንን ስትራቴጂ በመጠቀም በወቅቱም የአሜሪካ መንግሥት ለእስልምና አክራሪነት ሽፋን ሲሰጥ የነበረውን የሱዳን መንግሥት ከሥልጣን እንዲወገድ ቢያደርግም፣ እ.ኤ.አ ከ1998 እስከ 2000 በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር የተቀሰቀሰው ግጭት የፀረ አሜሪካ መንግሥትን ማወክ ስትራቴጂ ውጤታማ እንዳይሆን ምክንያት ሆኗል።
ሌላኛው ስትራቴጂ ማዕቀቦችን መጣል ነው፡፡ አሜሪካ የምትጥላቸው እነዚህ ማዕቀቦች ከአሁን ይልቅ በፊት ውጤታማ እንደነበሩ ይገለጻል። ደቡብ አፍሪካውያን በአፓርታይድ ሥርዓት ሥር በነበሩበት ጊዜ፣ በ1990ዎች የኢራቅን መንግሥት ለማዳከም፣ እንዲሁም በሊቢያ ላይ የተደረጉ ማዕቀቦች ውጤታማ ነበሩ። በመጀመሪያዎቹ 1990ዎች አሜሪካ ዓለም አቀፋዊ ማዕቀቦች በሱዳን ላይ እንዲጣሉ ብዙ ጉትጎታ ካደረጉት አገሮች የመሪነት ሚና ቢኖራትም፣ እሷ እንደፈለገችው የመላው ዓለም ሕዝብን ድጋፍ ማግኘት ባለመቻልዋ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። በወቅቱ በሱዳን ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦችን ካወገዙት አገሮች መካከል አንዷ ግብፅ ነበረች፡፡ ምክንያቱም ዕርምጃው በቀጥታ በራሷ ብሔራዊ ጥቅም ላይ አሉታዊ ጎን ስለነበረው ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ እ.ኤ.አ. በ2004 ዓ.ም. በዳርፉር ጉዳይ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን በሱዳን ላይ እንዲጣል የአሜሪካ መንግሥት ቢፈልግም፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባል የሆኑት ሩሲያና ቻይና ማዕቀቦቹ እንዳይጣሉ በማድረግ ሊያጡ የሚችሉትን የራሳቸውን ጥቅም መከላከል ችለዋል። በወቅቱም በተመድ ውሳኔ ቅሬታ የነበራት አሜሪካ ራሷ በሱዳን ላይ ማዕቀቦችን የጣለች ሲሆን፣ የዳርፉር ቀውስ ከቀጠለ ወደፊትም በርካታ ማዕቀቦችን እንደምትጥል ገልጻ ነበር። አሜሪካ በሱዳን ላይ የጣለቻቸው ማዕቀቦች በዋናነት ዕርዳታና ኢንቨስትመንት ማቋረጥ፣ ትልልቆቹ ዓለም አቀፍ ተቋማት በአገሪቱ ውስጥ ያላቸውን ሚና መቀነስና የመሳሰሉት ነበሩ። አሜሪካ በሱዳን ላይ የጣለቻቸው ማዕቀቦች ሱዳንን ክፉኛ ሊጎዱዋት የሚችሉ ቢሆንም፣ የነዳጅ ሀብቷን ለማልማት ከእስያ አገሮች ድጋፍ ማግኘት በመቻልዋ በተወሰነ ደረጃ ማዕቀቦቹን መቋቋም ችላለች።
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ፋይዳዎችና ተግዳሮቶች
ኢትዮጵያና አሜሪካ የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ናቸው ግንኙነታቸውም ቀስ በቀስ እያደገ ሲመጣ ሁለቱም አገሮች በአፍሪካ ቀንድ አካባቢያዊ ደኅንነትና ንግድ ላይ የተመሠረተ የትብብር ግንኙነታቸውን ይበልጥ አጠናክረዋል። የኢትዮጵያ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ሲታይ አገሪቷ በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙት ባርካታ አገሮች ማለትም ከሱዳን፣ ከኤርትራ፣ ከሶማሊያ፣ ከጂቡቲና ከኬንያ ጋር የምትዋሰን ስለሆነች፣ እንዲሁም በአካባቢው የቆየ ታሪክ ስላላት ለአሜሪካ ልዩ የሆኑ ስትራቴጂካዊ ጠቃሜታዎች አሉዋት።
ከ1970ዎቹ ጀምሮ የአሜሪካ ኢኮኖሚ መዳከሙንና የዋጋ ንረቱን እያባባሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ፣ በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበራት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኒክሰን ችግሮቹን ለመቅረፍ የኒክሰን ዶክትሪንና ʻዴታንትʼ በሚል እንደገና አዲስ የውጭ ፖሊሲ ቀርፀዋል። የፖሊሲው ዋና ዓላማ የነበረው አሜሪካ በቀጥታ በሌሎች አገሮች የምታደርገውን ወታደራዊ ተሳትፎ መቀነስ እንዳለበት የሚያሳይ ቢሆንም፣ ለተመረጡ ወዳጅ አገሮች በቂ የመሣሪያና ሌሎች ድጋፎችን መስጠት እንዳለባት ይገልጻል። በወቅቱም የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካን ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ ባይረዳውም ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች ኢትዮጵያ በኒክሰን ዶክትሪን ውስጥ የተካተተች አገር ነበረች። በመሆኑም እ.ኤ.አ. በ1953 አሜሪካና ኢትዮጵያ 25 የመከላከያ ስምምነቶች ባደረጉት መሠረት፣ በስምምነቱ ኢትዮጵያ በቀጣናው ለአሜሪካ ወዳጅነት ቁልፍ አገር እንደሆነች ተገልጿል። ስምምነቱ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ድጋፍና ወታደራዊ ሥልጠና ማድረግ እንዳለባት ሲገልጽ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በበኩሏ ለአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያ ለመስጠት በመስማማት ለመጀመሪያ ጊዜ ቃኘው የተባለው የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያ እንዲመሠረት ምክንያት ሆኗል።
አሜሪካ በፖሊሲዋ ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አጋርዋ መሆንዋ ብትገልጽም፣ ከጊዜ በኋላ ግን ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የነበራትን አስፈላጊነት በተለያዩ ምክንያቶች ሊቀንስ ችሏል። ለዚህም እንደ ምክንያትነት ከተገለጹት መካከል የመጀመሪያው የሳተላይት ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ከመሻሻሉ ጋር ተያይዞ የቃኘው ወታደራዊ ጣቢያ አስፈላጊነት መቀነሱና አሜሪካ ከቃኘው የተሻለ የወታደራዊ ጣቢያ በህንድ ውቅያኖስ የዲያጎ ጋርሺያ ደሴት ላይ ማግኘቷ ነው። ሌላው ምክንያት አሜሪካ በወቅቱ ኢትዮጵያ ማስተካከል እንዳለበት የገለጸችው አገራዊ ጉዳዮችን ማለትም ዘመናዊ ሕግ ሥርዓት መዘርጋት፣ ለኤርትራ መብቶች መስጠት፣ ሥልጣን ወደታች ማውረድ ወይም የሥልጣን ክፍፍል ማድረግ አለመቻሏ እንደ ምክንያት ተጠቅሷል።
በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ባትለውጥም፣ ደርግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የሁለቱም አገሮች ግንኙነት እየሻከረ መጥቷል። ይህ ወቅት ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት እንደመሆኑ መጠን፣ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ ስትራቴጂካዊ ሥፍራ ከመሆኑ የተነሳ ሩሲያና አሜሪካ ቀጣናውን ለመቆጣጠር ፉክክር ውስጥ የገቡበት ጊዜ ነበር። በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ወደ ሥልጣን ሲመጡ አሜሪካ ከሌሎች አገሮች ጋር የሚኖራት ፖሊሲ ከሰብዓዊ መብት ማክበር ጋር በመያያዙ፣ እንዲሁም የግራ ዘመም ፖለቲካ አቀንቃኝ የነበረው የደርግ መንግሥት ከአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ ማግኘት ባለመቻሉ ግንኙነቱን ወደ ሩሲያ ቀይሮታል። ከዚህ ጋር ተያይዞም አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን ግንኙነት በማቋረጥ ከ1969 እስከ 1970 ዓ.ም. ድረስ በኦጋዴን ጦርነት ለሶማሊያ ወታደራዊ ድጋፍ አድርጋለች። ይሁን እንጂ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በአዲስ መልክ ተጀምሯል።
በዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ሊኖራት የሚችል ፖሊሲ
ሀ. ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ቀዳሚ ትኩረት ብለው የለዩዋቸው ጉዳዮችን መሠረት በማድረግ የአሜሪካ ጥቅሞች ሲገመገሙ
45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ በአፍሪካ ቀንድ ምን ዓይነት ፖሊሲ አቅጣጫ ሊከተሉ እንደሚችሉ ለማወቅ የመጀመሪያው ተግባር፣ አዲሱ ፕሬዚዳንት በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ያላቸውን በደንብ መመልከት ነው። ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ምንም እንኳን የአፍሪካ ቀንድ ፖሊሲው ምን እንደሚመስል በግልጽ ባያስቀምጥም፣ አጠቃላይ የውጭ ፖሊሲውን በመመልከት ምን ዓይነት ሊሆን እንደሚችል ግን መገመት ይቻላል። ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የተናገራቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫዎች ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ የአፍሪካ ቀንድ ፖሊሲው በዋናነት የአካባቢው ደኅንነት፣ ሽብርተኝነትን መዋጋት፣ የገንዘብና ሰብዓዊ ድጋፍ ፖሊሲው፣ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ከኦባማና ከቡሽ አስተዳደር የተለየ አቅጣጫ ሊይዙ እንደሚችሉ የተለያዩ ተንታኞች ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ለ. የደኅንነትሥጋትና ሽብርተኝነትን የመዋጋት ፖሊሲና ስትራቴጂ
ምሥራቅ አፍሪካ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ትኩረት እንዲያገኝ ካደረጉት መካከል አንዱ የቀጣናው ደኅንነት ሁኔታ ነው። አፍሪካ ቀንድ ምናልባትም ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ቀጥሎ በጦርነትና በግጭቶች እንዲታወቅ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ የአክራሪነትና የሽብርተኝነት ችግር ነው። በምሥራቅ አፍሪካ የእስልምና መንግሥት አቋቁማለሁ በማለት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ቡድኖች በተለይም አልሸባብ፣ ከአልቃይዳ ጋር በመሆን በኬንያና በታንዛኒያ በሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ፣ እንዲሁም ከ9/11 የሽብር ጥቃት በኋላ አሜሪካ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከመቼውም በላይ ጠንካራ አቋምና ፍላጎት እንዲኖራት አድርጓል።
በመሆኑም የቡሽ አስተዳደርም ሆነ የኦባማ አስተዳደር አፍሪካ ቀንድን በተመለከተ የውጭ ፖሊሲዎቻቸው በዋናነት ሽብርተኝነትን በመዋጋት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ማድረግ ነው። ትንሽ ልዩነቶች ቢኖሩም ሁለቱም መሪዎች በቀጣናው ሽብርተኝነተን ለመዋጋት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ስትራቴጂዎችን ይጠቀሙ ነበር። በቀጣናው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የቡሽ ፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ሊያሳትፍ ስላልቻለ፣ ሽብርተኝነትን ከመከላከል ይልቅ ለአሸባሪዎች መበራከት ምክንያት እንደሆነ ምሁራን ይገልጻሉ። በተለይም ሽብርተኝነትን የመዋጋት ስትራቴጂው ሙስሊሙን ኅብረተሰብ እንደ አጋርነት ከመጠቀም ይልቅ፣ ሁሉንም የሙስሊሙን ማኅበረሰብ እንደ አሸባሪነት የማየት አዝማሚያው አለው። በአንፃራዊነት የኦባማን ፖሊሲ ከቡሽ ፖሊሲ ትንሽ ለየት የሚያደርገው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሌሎች አገሮች አጋርነት ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት መስጠቱ ነው። የኦባማ ስትራቴጂ ሙስሊሞችን እንደ አጋርነት በመጠቀም ሽብርተኝነትንና የእስልምና አክራሪነትን መዋጋት እንደሚቻል ያሳያል።
በአጠቃላይ እስካሁን የኦባማ አስተዳደር በአፍሪካ አገሮች በፀረ ሽብርተኝነትንና በአክራሪነት እንቅስቃሴዎች ላይ ፅኑ ተሳትፎ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ በተለይም በናይጄሪያ ቦኮ ሐራም የተሰኘው ቡድን፣ በሰሜን አፍሪካ ማግረብ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የአልቃይዳ ክንፍ፣ እንዲሁም በሶማሊያና በአካባቢዋ የሚንቀሳቀሰውን አልሸባብን ለማጥፋት ከሚመለከታቸው አገሮች ጋር በአጋርነት ሲሠራ ቆይቷል። ለዚህም የአሜሪካ ወታደራዊ አማካሪዎችና አሠልጣኞች በማግረብ አካባቢ፣ በጂቡቲና በናይጄሪያ ይገኛሉ። ሽብርተኝነትንና አክራሪነትን በተመለከተ በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፖሊሲ ለውጥ ሊኖር እንደማይችል በሴኔጋልና ጋምቢያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ኸርማን ኮኸን ገልጸዋል። እንደ ኮኸን ግምት ከሆነ ዶናልድ ትራምፕ ሽብርተኝነትን በተመለከተ ያላቸው አቋም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ፣ የኦባማን የደኅንነት ፖሊሲ ሊያስቀጥለው ይችላል።
ሐ. አሜሪካከአፍሪካ ቀንድ አገሮች ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት
ዶናልድ ትራምፕ አሁን ባለው የዓለም አቀፍ ንግድ ሥርዓት አሜሪካ ተጠቃሚ አለመሆኗን፣ በተለይም ከአንዳንድ አገሮች ጋር የምታደርገው የንግድ ግንኙነት ተገቢ አልመሆኑን ገልጸዋል። አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቻይና አሜሪካን የራሷን ጥቅም ብቻ በማስቀደም የገንዘብ ማስተካከያ እያደረገች አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆኑን፣ ደቡብ ኮሪያ ወደ አሜሪካ የምትልካቸውን ምርቶች ድጎማ እንደምታደርግ፣ እንዲሁም ሜክሲኮ የሠራተኞች ርካሽ ጉልበት እንደምትጠቀም በመግለጽ ወደፊት አሜሪካ የሁለትዮሽ ንግድ ግንኙነቶች ላይ አተኩራ ጥቅሞቿን ማስከበር እንዳለባት ገልጸዋል። በዚህ መሠረት በዶናልድ ትራምፕ ዕይታ ቀደም ሲል ከሰሐራ በታች ያሉ አገሮች ከአሜሪካ ጋር የሚኖራቸውን የንግድ ግንኙነትና ተሳትፎ ለማሳደግ ተብሎ አጎዋ (African Growth and Opportunity Act) እ.ኤ.አ. በ2000 የተጀመረው ፕሮግራም በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ቀጣይነቱ የሚያጠራጠር ነው። ይህ ዕድል የአፍሪካ አገሮች በነፃ ያለምንም ገደብ ማንኛቸውንም ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ ገበያ ማቅረብ እንደሚችሉ የሚያስችል ሲሆን፣ አሜሪካውያን በነፃ ምርቶቻቸውን ወደ አፍሪካ አገሮች መላክ ስለማይችሉ በዶናልድ አስተዳደር ይህ ዕድል ተቀባይነት አይኖረውም። በመሆኑም በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ ከአፍሪካ አገሮች ጋር የሚታደርገው የሁለትዮሽ ንግድ ግንኙነት ለሁለቱም አካላት ተመሳሳይ መሆን አለበት።
መ.አሜሪካለአፍሪካ ቀንድ የምታደርገው የኢኮኖሚዊ ልማት ድጋፍ
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በዶናልድ ትራምፕ ከተተቹት ጉዳዮች መካከል አንዱ የኦባማ አስተዳደር ለሌሎች አገሮች ከፍተኛ ድጋፍ በማድረጉ ምክንያት፣ ለአሜሪካኖች ቅድሚያ አልተሰጠም የሚል ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ የኢኮኖሚ ዕድገታቸውን ለማሻሻል የአሜሪካን ድጋፍ ከሚሹት አገሮች መካከልም ዋነኞቹ የአፍሪካ አገሮች ሲሆኑ፣ ከዚህ በፊት የነበሩት ዘመናዊ የአሜሪካ መሪዎች የውጭ ፖሊሲያቸውም በዋነኝነት የሚያተኩረው ኢኮኖሚያዊና ፖሊቲካዊ ድጋፍ ለአኅጉሩ ማድረግ ነው። ግልጽነት የጎደለው ከአፍሪካ ጋር ያለው የዶናልድ ትራምፕ የውጭ ፖሊሲ ግን በአንድ በኩል ‹‹ቅድሚያው ለአሜሪካ›› የሚለው የምርጫ ቅስቀሳ፣ እንዲሁም የትራምፕ አማካሪዎች ለአፍሪካ የሚደረገውን ድጋፍ እንደ ብክነት በማየታቸው ምክንያት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለአፍሪካ የሚደረገውን ድጋፍ በመቀነስ፣ ለአሜሪካ እንደገና መልሶ ግንባታ ላይ ማዋል እንደሚችል ያሳያል። በሌላ በኩል ደግሞ አፍሪካ የአሜሪካ አገር በቀል ኩባንያዎች የገበያ መዳረሻ እንደመሆኗ መጠን፣ በአኅጉሩ ውስጥ አስፈላጊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በአሜሪካ ድጋፍ እንዲካሄድላቸው ይፈልጋሉ። የዶናልድ ፖሊሲም ቢዝነስ ላይ ያለው አቋም ጠንካራ ሊሆን ስለሚችል፣ ለአፍሪካ አገሮች የሚደረግ ድጋፍ ቀጣይነት ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል።
በአጠቃላይ አሜሪካ ለአፍሪካ አገሮች የምታደርገውን ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ካቆመች በተለያዩ የፖሊሲ ጉዳዮች አፍሪካ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር አትችልም። በተለይም በተባበሩት መንግሥት ድርጅት የአፍሪካን ድምፅ ማጣት፣ ወታደራዊ የአየር በረራ እንዳይደረግባቸው በማድረግና የአካባቢ ችግሮችን በተመለከተ አሜሪካ በአፍሪካ አገሮች የነበራት ተሰሚነቷ ይቀንሳል።
ሠ. አሜሪካበአፍሪካ ቀንድ ያላት የቢዝነስ ፍላጎቶች
አሜሪካ በተለያዩ አፍሪካ አገሮች በርካታ ቢዝነስና ኢንቨስትመንቶች በዋናነትም በነዳጅና ሌሎች መሰል በማዕድን የተሰማሩ ኩባንያዎች ሲኖሯት በማኑፋክቼሪንግ ዘርፍ የአሜሪካ ኩባንያዎች እንቅስቃሴ ጀምረዋል። በዚህ ረገድ ዶናልድ ትራምፕ ምንም ዓይነት የፖሊሲ ምልከታ ባይሰጡትም የአሜሪካ ኢንቨስተሮችን ከመደገፍ ወደኋላ እንደማይሉ ግልጽ ነው።
ረ. አሜሪካበአፍሪካ የምታደርጋችው ልዩ የልማት መርሐ ግብሮች
በቡሽ አስተዳደር ወቅት የተጀመሩት አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ መርሐ ግብሮች በኦባማ አስተዳደርም እያደጉ መጥተዋል። በቡሽ አስተዳደር በመላው አፍሪካ አገሮች ኤችአይቪ/ኤድስን፣ ወባንና የሳንባ በሽታን ለመከላከል ከተደረጉት ድጋፎች በተጨማሪ፣ የሚሊኒየም ተግዳሮት ኮርፖሬሽን የተሰኘው መርሐ ግብር የአፍሪካ አገሮች ፖሊቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎቻቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል። የኦባማ አስተዳደርም ከላይ የተጠቀሱት መርሐ ግብሮችን ቢያስቀጥልም በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የመቀጠል አዝማሚያቸው በጣም ዝቅተኛ ነው። በሌላ በኩል በአሁኑ ጊዜ በኦባማ አስተዳደር የተጀመሩት የአፍሪካ አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በግሉ ዘርፍ አማካይነት ኢንቨስት መደረግ እንዳለበትና የግብርናውን ዘርፍ ዘመናዊ ለማድረግ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማስቀጠል እንደምችሉ ምሁራን ይገልጻሉ። ምክንያቱም አሜሪካ ከእነዚህ ፕሮግራሞች ተጠቃሚ ስለምትሆን።
ዶናልድ ትራምፕ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላቸው አቋም
ለአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ደረጃ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት አገሮች አንዷ አሜሪካ ብትሆንም፣ ዶናልድ ትራምፕ የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ የሚባል አለመኖሩን ይናገራሉ። ይህ ደግሞ በፓሪስ የአየር ንብረት ጉባዔ ስምምነት መሠረት አሜሪካና ሌሎች ያደጉት አገሮች የአየር ንብረት ለውጡ የሚያስከትለውን በርካታ ጉዳቶችን ፋይናንስ ለማድረግ በጀመሩዋቸው እንቅስቀቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው።
ሀ. የዶናልድትራምፕ አስተዳደር ከሪፐብሊካኖች አንፃር
በርካታ የሪፐብሊካን አባላትና መሪዎች የዶናልድ ትራምፕን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሲቃወሙ ቆይተዋል። በተለይም ትራምፕ መመረጣቸውን ተከትሎ ሃምሳ የሚሆኑ የቀድሞው የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ባለሥልጣናት በሰጡት ቃል መሠረት፣ ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ ዝቅተኛ ግንዛቤ ያላቸውና ለፕሬዚዳንትነት የማይመጥኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። በትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነትና መልካም ገጽታዋ አደጋ ላይ ይወድቃል በማለት ሥጋታቸውን የገለጹት እነዚህ ባለሥልጣናት፣ የግለሰቡ አጠቃላይ የፖለቲካ ሰብዕና ማለትም ባህርይ፣ እሴቶችና ልምድ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን የማያስችሉ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞም ተመራጩ ፕሬዚዳንት መሠረታዊ የአሜሪካ ሕግ ዕውቀትና እምነት፣ የአሜሪካ ሕግጋትንና ተቋማት፣ የሃይማኖት መቻቻል፣ የፕሬስ ነፃነትና የፍትሕ ሥርዓቱ ገለልተኝነት ዕውቀት የሌላቸው በመሆኑ፣ አሁን አሜሪካ በዓለም ላይ ያላትን ተቀባይነትና የመሪነት ሚናዋን ያሳንሳል በማለት ፍራቻቸውን ይገልጻሉ። በአጠቃላይ ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ መሠረታዊ ብሔራዊ ፍላጎት፣ የአገሪቷን ውስብስብ ዲፕሎማሲያዊ ተግዳሮቶች፣ የአሜሪካ ህልውና የሆኑ አጋርና ወዳጅ አገሮችና የአገሪቷ ውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የተመሠረተባቸው ዴሞክራሲያዊ እሴቶች በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ አናሳ መሆኑን ያስረዳሉ።
ለ. የአሜሪካ ተቋማዊ ጥንካሬና የዶናልድ ትራምፕ ሹማምንት ሚና
ከላይ የተጠቀሱትን የዶናልድ ትራምፕ ክፍተቶች የሚያሳየው ግለሰቡ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ለማድረግ ከሌሎች ጋር ለመሥራት እንደሚገደዱ ነው። በተጨማሪም የአሜሪካ ተቋማዊ አቅም ጠንካራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ፕሬዚዳንቱ ብቻውን የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ ሊሆኑ አይችሉም። በመሆኑም የአገሪቱ ተቋማዊ መዋቅሮች በተለይም የሴኔቱ ውሳኔዎችና የሌሎች ሹማምንት ማለትም የምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት፣ እንዲሁም በስቴት ዲፓርትመንት የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው የሚሾሙት ግለሰቦች በውጭ ፖሊሲው ላይ ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል።
ለ. በአፍሪካ ቀንድና በኢትዮጵያ ሊሆን የሚችሉ ቢሆኖች
በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ቅርብ ወዳጅና አጋር የሆኑ አገሮች በዋናነት ኢትዮጵያና ጂቡቲ ቢሆኑም፣ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያ መገኛ የሆነችው ጂቡቲ እ.ኤ.አ. በ2016 ከቻይና ጋር ባደረገችው ስምምነት መሠረት ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ ወታደራዊ ጣቢያ በጂቡቲ ለማቋቋም እንደወሰነች ተገልጿል። ይህ የሚያሳየው ጂቡቲ ከአሜሪካ ይልቅ ከቻይና ጋር ተባብሮ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወደህ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ እንዲሁም በዲያስፖራዎች ጉትጎታ ምክንያት አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ወዳጅነት በተለይም የፀረ ሽብርተኝነት አጋርነት ታቆማለች የሚለው ግምት ነው። በዚህ ምክንያት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ስትራቴጂካዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ ያላቸው አገሮችን ማለትም ኤርትራና ደቡብ ሱዳንን እንደ አጋርነት ለመጠቀም በአዲስ መልክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኘኑት መፍጠር ይችላል። በተለይም ልምድ ያላቸው ኸርማን ኮኸን፣ ዴቪድ ሺንና ፕሪንስተን ለይማን የተባሉት የአሜሪካ ዲፕሎማቶች አሜሪካ ከኤርትራ ጋር እንደገና ዲፕሎማሳዊ ግንኙነት መፍጠር እንዳለበት ያምናሉ። ኤርትራ ከአሜሪካ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትዋን መልሳ ማደስ ከቻለች በተመድ የተጣለባት የኢኮኖሚ ማዕቀብ ይነሳላታል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ምክንያቱም ሥልጣን ላይ ያለው የኤርትራ መንግሥት ቀደም ሲል ሲያደርግ እንደነበረው፣ አሁንም ኢትዮጵያን የማወክ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ያደርጋል።
አሜሪካ ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከርና በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ጠንካራና የተረጋጋ መንግሥት እንዲኖር ትፈልጋለች። ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የተሻለና ጠንካራ መንግሥት ያላት አገር ናት። እንዲሁም በቀጣናው የተለያዩ ዓለም አቀፋዊና አኅጉራዊ ተቋማት፣ ለአብነትም የአፍሪካ ኅብረትና የተመድ ተቋማት መገኛ በመሆኗ አገሪቱ የአፍሪካ ስትራቴጂካዊ ሥፍራ ናት። በዚህ ምክንያት አሜሪካም ሆነ ሌሎች በአፍሪካ ላይ ፍላጎት ያላቸው አገሮች ኢትዮጵያን እንደ ስትራቴጂካዊ ሥፍራ ከማየት ባሻገር፣ በአገሪቷ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ ከመግባት ይልቅ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በውይይትና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ችግሮችን መፍታት ይመርጣሉ። አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሽብርተኝነትንና አክራሪነት ለመዋጋት ፅኑ አቋም ስላላቸው፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የፀረ ሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎችና በአኅጉሩ ያላትን ስትራቴጂካዊ ሥፍራ በመገንዘብ የነበረውን ወዳጅነት ሊያስቀጥሉ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል።
ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት በተደጋጋሚ እንደገለጹት አሜሪካ ከአገሮች ጋር የምታደርገውን ተሳትፎ በመቀነስ አገራዊ ግንባታ ማከናወን አለባት። በዚህም ቀደም ሲል ከሌሎች አገሮች ጋር የነበሩትን የውጭ ግንኙነትና አጋርነት መቀነስ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። እንዲሁም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከአፍሪካ አገሮች ጋር የሚኖረውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አለመግለጻቸው ምናልባት በትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ በአፍሪካ አገሮች ያላት ተሳትፎ አናሳ ይሆናል የሚል ግምት አለ። ዶናልድ ትራምፕ ከአጋርነት ይልቅ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ በማተኮር፣ የአሜሪካን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ይበልጥ ለማስከበር እንደሚሠሩ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በተደጋጋሚ ከመግለጻቸው ጋር ተያይዞ፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከሌሎች አገሮች ጋር አጋርነት ሳያስፈልግ አሜሪካ በተናጠል የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ይኖራል ብላ ባሰበችው አገር ውስጥ ገብታ መዋጋት እንደምትችል ያሳያል። ለአብነትም ከዚህ በፊት አንዳንድ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ሲከተሉት የነበረው ‹‹አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስን ለመከላከል›› በሚል ሰበብ በጦርነት ጣልቃ በመግባት ሽብርተኝነትንና አክራሪነትን መዋጋት እንደምትችል ግምት አለ።
ማጠቃለያ
የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከቀጣናው ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በተመለከተ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ የቀጣናው ተጨባጭ ሁኔታዎች ማለትም የፖለቲካዊ ልዩነቶች፣ የሃይማኖት አክራሪነትና ሽብርተኝነት፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የአሜሪካ አጋርነት አስፈላጊ ነው። አሜሪካ ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች ጋር በምታደርገው ግንኙነት የሚኖራት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ሰፊ ነው። የትራምፕ አስተዳደር በዋናነት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ላይ ስለሚያተኩር የአሜሪካና የአገራቸውን ተጠቃሚነት በጠበቀ መንገድ የቢዝነስና የንግድ ግንኙነቶችን በማጠናከርና በማስፋፋት ላይ ያተኮሩ አገሮች የአስተዳደሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ። እንዲሁም የትራምፕ አስተዳደር በደኅንነት ላይ ያለው አቋም ከፍተኛ በመሆኑ፣ በዚህ ዘርፍም ከአገሪቱ ጋር የተለያዩ ትብብሮችን በማድረግ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የሚያደርጉ የቀጣናው መሪዎች መልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይኖራቸዋል። በአጠቃላይ ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ያላቸውን ጉዳዮች መሠረት በማድረግ፣ የአሜሪካ ተቋማዊ ጥንካሬና የዶናልድ ትራምፕ ሹማምንት ሚና ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ እንዲሁም የቀጣናው አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ታሳቢ በማድረግ አሜሪካ ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች ጋር የሚኖራት ግንኙነት ከዚህ በፊት ከነበረው ያን ያህል ልዩነት አይኖረውም።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው Luskerget@yahoo.comማግኘት ይቻላል፡፡
