Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች የሚያበረክቷቸው ጥቅሞች ለምን ተዘነጉ?

$
0
0

    በያሬድ ኃይለ መስቀል

ሰሞኑን በሸገር 102.1 እና በ97.1 ኤፍ ኤም ሬዲዮኖች ላይ የግል ትምህርት ቤቶችን በተመለከተ የተደረጉ ውይይቶችን አዳምጫለሁ። ውይይቶቹ መልካም ናቸው። 

ይሁንና ዋነኛውን ጥያቄ ለውይይት ባለመቅረቡ በመሠረታዊ ችግሩ ላይ ውይይት አልተካሄደም።  ይህም ጥያቄ ወላጆች ለምን የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ትተው ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤቶች ያስተምራሉ የሚለው ነው፡፡

ይህ ጥያቄ ቢጠየቅ ኖሮ የተዘረዘሩት የግል ትምህርት ቤቶች  ችግሮች  መንስዔዎቻቸው ምን እንደሆነ በቀላሉ ለመረዳት በተቻለ ነበር።

የግል ትምህርት ቤቶች ችግር የለባቸውም ወይም ከበርካታው ሕዝብ ገቢ ጋር ሲመዘን ውድ አይደለም ለማለት አይደልም። ዋጋም ሆነ ጥራት ካለው አቅርቦትና አማራጮች ጋር ነው የሚመዘነው። ውይይቱ ለምን ወላጆች የመንግሥትን ትምህርት ቤቶች ጠሉ ከማለት ይልቅ፣ የግል ትምህርት ቤቶችን ወደመኮነን ያዘነበለ ነበር። 

ከዚህም አልፎ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ  ባለሥልጣናትም በተከኩራራ መንፈስ ስለዘጉዋቸው ትምህርት ቤቶች ሲዘርዝሩ የታዘብኩት የግል ትምህርት ቤቶች ለኢኮኖሚውም በብዙ ቢሊዮን ብር በጅት ለመንግሥት እየደጎሙ፣ የተሻለ የትምህርት ሥርዓት እንዲኖር እያደረጉ ስላለው ጥቅም በደንብ እንዳልተገነዘቡ መረዳት ይቻላል። 

በትምህርት ሚኒስቴር መረጃ መሠረት 498 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ ሲኖሩ፣ 1,728 የግል ትምህርት ቤቶች አሉ። ይህ እንግዲህ ከ20 ዓመታት በፊት  ጥቂት ከነበሩት የግል ትምህርት ቤቶች ተነስተው 1,728 ደርሰዋል። በአዲስ አበባ ከ900,000 ሺሕ በላይ ተማሪዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ልጆች የሚማሩት በግል ትምህርት ቤቶች ነው።

ይህ ደግሞ የግል ትምህርት ቤቶች ትልቁን ሸክም ከመንግሥት ተረክበው በብዙ ቢሊዮን ብር በጀት እያዳኑለት ነው። 

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እንዳይመዘግቡ አዝዣለሁ ካላቸው ትምህርት ቤቶች መካከል አንዳንዶቹን አውቃለሁ። እነዚህ ትምህርት ቤቶች በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስገባት ብዙ የሚደክሙባቸው፣ ልጆቻቸው የትምህርት ቤቶቹን የመግቢያ ፈተና እንዲያልፋ ምን ያህል እንደሚደክሙ አውቃለሁ። ከእነዚህ ውስጥ የጊብሰን አካዳሚን ለምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።

እነዚህ እንዲዘጉ አዘናል ያሉዋቸው ትምህርት ቤቶች የጥራት ችግር ስላለባቸው ነው የሚለውን ብዙ ወላጅ ለመቀበል ይከብደዋል። 

የግል ትምህርት ቤቶችን የመንግሥት ካሪኩለምና የመንግሥት መጻሕፍት በግድ ተከተሉ ማለቱም ስህተት ነው። ብዙ ወላጅ ከመንግሥት ካሪኩልም ውጪ የግል ትምህርት ቤቶች የሚሰጡዋቸውን ተጨማሪ ትምህርቶች በመፈለግ ነው ወደ ግል ትምህርት ቤቶች የሚልኩት። 

ዛሬ ወላጆችን ለምን የግል ትምህርት ቤቶች ልጆቻችሁን ታስገባላችሁ ተብለው የቃለ መጠይቅ ዳሰሳ ቢደረግ የሚከተሉትን ዋና ዋና ምላሾች የሚሰጡ ይመስለኛል።

በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው ትምህርት ጥራቱ ወርዷል፣ ለልጆቻችን በግል ክትትል አይደረግም፣ ልጆቻችን ለሚገጥማቸው ዓለም አቀፋዊ ፋክክር ብቁ አያደርጋቸውም፣ ቋንቋ በራሱ ግብ ባይሆንም ትልቅ የዕውቀትና የሐሳብ መገልገያ መሣሪያ ነው። የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ቋንቋን ማስተማር ቀርቶ በልኩ ማንበብና መጻፍንም በውሉ አያስተምሩም፣ ካሪኩለሙም ጊዜ ያለፈበት ነው፣ መጻሕፍቱም ለእኔ ልጅ መማርያ በሚል መንፈስ ሳይሆን ለሰፊው ሕዝብ ልጅ ‹‹ተደራሽነት›› ተብለው በግብር ይውጣ የተዘጋጁ በመሆናቸው፣ ከቃላት ግድፈት ጀምሮ እስከ ‹‹ራስ ዳሸን›› ግድፈት ይዘው ስለሚታተሙ ነው፣ የማሰብ ችሎታን ከማዳበር ይልቅ በቃል ጥናት ላይ የቆሙ ናቸው የሚሉ ይመስለኛል። 

ይህ እምነት ባለበት ሁኔታ የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች እኛ ትክክል ነን ከሚሉ ረጋ ብለው ከግሉ ትምህርት ቤቶች ጥንካሬ ቢማሩ፣ ካልሆነም ቢኮርጁ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ተመራጭነትን ሊጨምሩ በቻሉ ነበር። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። 

ከግል ባንኮች በፊት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብር ያስቀመጠ  ሰው ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ገንዘቡን ማውጣት አይችልም ነበር። ዘጠኝ ከሩብ የደረሰ ባንክ ተዘግቷል፣ ብር ቆጠራ ላይ ናቸው ተብሎ ነበር የሚመለሰው። የግል ባንኮች ተከፍተው እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ ሲያስተናግዱ በኤቲኤም (ATM) እና በኮምፒዩተር  ኔትወርክ  ተገልጋይ ሲያበራክቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዘጠኝ ሰዓቱ ብር ቆጠራ አልተከበረም ብሎ የግል ባንክ ዕድገትን አላደናቀፈም። ይልቁንም የግል ባንኮች ያስተዋወቁዋቸውን አሠራሮችና ቴክኖሎጂዎች በመተግበር ፈጣን ዕድገት ለማምጣት ሠራ። ውጤቱም እየታየ ነው። በግል ባንክ የሚሰጥ አገልግሎቶች ሁሉ በንግድ ባንክ አሉ። ይህ ፉክክር ለባንኮች ዕድገት ምክንያት ሆኗል። 

የግል ትምህርት ቤቶች በወላጅ ተመራጭ ያደረጉዋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ከማማ ላይ ሆነው ትልቅ ዱላ ይዘው የፖሊስ ሥራ ላይ ከሚያጠፉ፣ ከማማው ወርደው በጣት ይቆጠሩ የነበሩት የግል ትምህርት ቤቶች ለምን ዛሬ ወደ 1,500 ትምህርት ቤቶች መድረስ ቻሉ ብለው ቢጠይቁ፣ አማካሪ ቀጥረው ቢያስጠኑ፣ ቃለ መጠይቅና የዳሰሳ ጥናት ቢያደርጉ ጠቃሚ ትምህርት መማር በቻሉ ነበር።

ባለፋት አሠርት ዓመታት በርካታ የግል ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል። በ2007 ዓ.ም. በወጣ መረጃ 1,671 ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ ብቻ ነበሩ። በአዲስ አበባ ወደ 900,000 ተማሪዎች አሉ። ከእነዚህ ተማሪዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በግል ትምህርት ቤቶች ይማራሉ።

የዚህ ጥቅም ደግሞ ለእነዚህ ሁሉ ተማሪዎች መንግሥት ትምህርት ቤቶች ገንብቶ፣ አስተማሪ ቀጥሮ፣ የማስተማሪያ መሣሪያዎች አቅርቦ ማስተማር ግዴታው ነበረ። በተጨማሪ እዚህ አገር ወደ 2.6 ሚሊዮን የሚደርሱ ልጆች በየዓመቱ ይወለዳሉ። ለእነዚህ ሁሉ ትምህርትን ማዳረስ ግዴታው ነው። ይህ ቢያንስ ቢያንስ 52,000 አዳዲስ ክፍሎች በዓመት መገንባት አለበት። ይህ ለአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ብቻ ነው። ይህም በአንድ ክፍል ውስጥ 50 ልጆች ቢማሩ ብለን ካሰላነው ነው። በአደጉት አገሮች አንድ አስተማሪ ለእያንዳንዱ ተማሪ ትኩረት ሰጥቶ ክትትል እንዲያደርግ በክፍል ውስጥ ከ30 ተማሪዎች በላይ አይመደብም።

ስለዚህ በክፍል 50 ተማሪ ብለን ካሰብን 52,000 የመማሪያ ክፍሎች ለአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ብቻ መገንባት አለባቸው። በተጨማሪም 52,000 መምህራን ለአንደኛ ክፍል መቅጠር አለበት። የአንድ አስተማሪን ደመወዝ፣ ጡረታና ጥቅማ ጥቅሞችን አስበን በ2,500 ብር ብለን ብናሰላ  ለአንደኛ ክፍል አስተማሪዎች ብቻ መንግሥት 130 ሚሊዮን ብር በወር ወይም 1.56 ቢሊዮን ብር በዓመት ያስፈልገዋል። 

የኢትዮጵያ የ2008 ዓ.ም. ጠቅላላ የትምህርት የዓመት በጀት 38.9 ቢሊዮን ብር ነበር። ከላይ የተጠቀሰው 1.56 ቢሊዮን ብር የአምናውን በጀት አራት በመቶ ነው። አራት በመቶ ለአንደኛ ክፍል አስተማሪ ብቻ ከዋለ ለትምህርት ቤት ግንባታ፣ ለመማሪያ ግብዓትና ሥልጠና ሲጨመር ብዙ ቢሊዮን ይደርሳል።

የግል ትምህርት ቤቶች ባይኖሩ ኖሮ የመንግሥት በጀት የግድ ማደግ ነበረበት ወይም አገልግሎቱን መቀነስ ግድ ይሆን ነበር።

ግብር (ታክስ) ከፋዩ ቤተሰብ ግን ግብር በከፈልኩበት ትምህርት ቤት ውስጥ ጥራት ያለው ትምህርት አይሰጥም፣ ልጆቻችን በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው አይችልም  ብለው ባያምኑ ተጨማሪ ወጪ ከፍለው የግል ትምህርት ቤቶች አያስገቡም ነበር። 

ለዚህ ነው በአዲስ አበባ ብቻ 1,671 የግል ትምህርት ቤቶች ሊኖሩ የቻሉት።  ለጊዜው የግል ትምህርት ቤቶች በጀት ምን ያህል እንደሆነ መረጃ በእጄ ባይኖርም፣ የግል ትምህርት ቤቶች ለተማሪ  በወር 300 ብር ያወጣሉ ብለን ብናሰላ ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር የሚገመት የመንግሥትን ወጪ እየሸፈኑ ነው። 

ይህ ማለት ለመንግሥት ከሚከፍሉት የትርፍ ግብር፣ የሠራተኛ ደመወዝ ግብርና የመገልገያ ዕቃዎች ቫት ክፍያን ሳይጨምር መንግሥት በዓመት ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ለአዲስ  አበባ ተማሪዎች መመደብ ነበረበት። ይህ ማለት የግል ትምህርት ቤቶች ለመንግሥት የዚህን ያህል ቀጥተኛ ድጎማ እያደረጉ ናቸው።

በዚህ ላይ ለ1,500 ትምህርት ቤቶች መገንቢያ፣ ለመምህራን ደመወዝ፣ ለአስተዳደርና ለትምህርት መገልገያዎች አቅርቦት በዓመት ያወጣ የነበረውን ከደመርን ደግሞ የግል ትምህርት ቤቶች ብዙ ቢሊዮን ብር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ  ይመስለኛል።

የግል ትምህርት ቤቶች አስተዋጽኦ በኢኮኖሚው ላይ ዝርዝር ጥናት የሚጠይቅና ለድኅረ ምረቃ የኢኮኖሚክስ ተማሪዎች ጥሩ የመመረቂያ ጥናት ሊሆን ይችላል።

አንዳንድ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ባለሥልጣናት ቃለ መጠይቆችን ሳዳምጥ ግን ትልቅ የግንዛቤ ችግር እንዳለባቸው ይታያል። ከሥልጣን ማማ ላይ ሆኖ ቁልቁል እያዩ ዘጋነው፣ ከለከልነው፣ ማስጠንቀቂያ ሰጠነው ሲሉ ነው የሚሰሙት።

መገንዘብ ያልቻሉትና ሊረዱት የከበዳቸው ነገር መንግሥት በየዓመቱ ከሃምሳ ሺሕ በላይ ክፍሎችን እያዘጋጀ ትምህርት ቤቶችን መክፈት አቅም የለውምም፣ አይኖረውም። የግል፣ የኮሙዩኒቲ፣ የሃይማኖት፣ የበጎ አድራጎት ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉና ሽክሙን እንዲጋሩለት ማግባባትና ማሳመን እንጂ፣ መጥረቢያውን ይዞ መመንጠሩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚና አቅም ካለመረዳት የመጣ ነው።

ይህ በበርካታ ቢሊዮን ብር የሚገመት ሸክም ከመንግሥት ትከሻ ላይ ያነሳን የኢኮኖሚ ዘርፍ ማዳከሙ ትክክል አይደለም። ይልቁንም መረዳት ያለበት የኢኮኖሚ ክፍል ነው።

ከላይ እንዳየነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትምህርት ቤት ለማሠሪያና ለሌሎች ማኅበራዊ መገልገያዎች ግብር (ቀረጥ) ይከፍላል፡፡ በእዚህም ገንዘብ  አስተማሪ፣ አስተዳዳሪ፣ ሚኒስቴር ቀጥሮ በመሠረታቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ በነፃ ልጆቹን ከማስተማር ይልቅ ለምን በጣም ውድ በሆኑ፣ ተቸግሮ ለተጨማሪ ወጪ ተዳርጎ  በግል ትምህርት ቤት ውስጥ ለማስተማር መረጠ የሚለውን ጥያቄ የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ቢመልሱ፣ ለተነሱት ችግሮች ሁሉ መፍትሔው ግልጽ ብሎ ይታይ ነበር። 

አባቶቻችን ‹‹የራሷ እያረረባት...›› የሚሉት አባባል አለ። በአዲስ አበባ ብቻ ከ1,671 የግል ትምህርት ቤቶች በ2007 ዓ.ም. ነበሩ። ዘንድሮ በተደረገው ቆጠራ ቁጥራቸው ቀንሷል፡፡ ይህም የትምህርት ቢሮዎች ስላላደሱላቸው ወይም ጠንካራ ፉክክር ከገበያው ስላስወጣቸው ይሆናል። 

ደግሞ ደጋግሞ መጠየቅ ያለበት ሁላችንንም ያስተማረ፣  በርካታ ምሁራንን ያፈራ፣ በበለፀጉት አገሮች ሳይቀር ሄደን ተወዳዳሪ እንድንሆን ያስቻለን የመንግሥት ትምህርት ቤትና ካሪኩለም ለምን ወላጆች ጠሉት ብለን ብንጠይቅ ምናልባትም  ብቃት በሌላቸው ባለሙያዎች በመመራቱ፣ ከጥራት ይልቅ ለፖለቲካ መጠቀሚያ የሚውል የተማሪ ቁጥርን እንደ ግብ በማድረጉ፣ የትምህርት ጥራት ወረደ የሚባል ይመስለኛል። 

በርካታ ወላጆች የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ለልጆቻቸን በቂ አይደሉም፣ ልጆቻቸው ወደፊት ለሚገጥሙዋቸው ፉክክሮች ለማዘጋጀት ብቁ አይደሉም ብሎ በማመናቸው ምክንያት፣ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ግል ትምህርት ቤት መሰደድ መረጡ።  ወደው ሳይሆን የልጆቻቸውን ተስፋ ከጅምሩ ላለማጨለም ሲሉ ነው። 

ከፖሊሲ አውጪ መሪዎች ጀምሮ እስከ አስፈጻሚው የትምህርት ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ድረስ ‹‹ጥራት ሳይሆን ተደራሽነት ነው›› በሚል ፍልስፍና ታጥረው የትምህርት ጥራት ወደቀ። በትውልድ ላይ ቤተ ሙከራ ሲካሄድ ያየ ሁሉ ልጆቹን ለማዳን እግሬ አውጭኝ አለ።

‹‹ተደራሽነትና ጥራት›› የተነጣጠሉና በአንድ ላይ መሄድ አይችሉም የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከየት እንደተቀዳ አላውቅም። ጥራት ማለት ችግር የሌለበትና የተገልጋዩን ፍላጎትን የሚያሟላ ወይንም ከተገልጋዩ ፍላጎት በላይ ሆኖ የሚገኝ ማለት ነው። “Meeting and Exceeding Customer Expectations” ወይም “Fitness for Intended use” ለምሳሌ “iPhone 1” እና “iPhone 7” አንድ አይደሉም። 

ይህ ማለት ግን የመጀመሪያው “iPhone” ከነበሩት ሁሉ ስልኮች በጣም የበለጠ ነበር። ይህም የኖክያ (Nokia, Motorola etc) ከነበረው ተገልጋይ ፍላጎት ከፍ ብሎ በመገኘቱ ተመራጭና የጥራት ተምሳሌት ሆነ።  “iPhone 7” በዚያ ዘመን ቢታወቅ ኖሮ “iPhone 1” መሳቅያ በሆነ ነበር።

የኢትዮጵያ ትምህርት ‹‹ወደቀ›› ሲባል ከነበረውም ወረደ ማለት ነው። በተለይም ነባርና ክግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ባስቆጠሩ የአዲስ አበባን ትምህርት ቤቶች ማለት ነው። 

አትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ከጀመረች 100 ዓመታት አለፉ። እኛ በመምህራን ማሠልጠኛ ምሩቃን መምህራን ነው የተማርነው፡፡ አስተማሪዎቻችን 8ኛ እና 10ኛ ክፍል ያጠናቀቁ ነበሩ፡፡ ዛሬ ዲፕሎማ፣ ዲግሪ፣ ማስተርስ ባላቸው መምህራን የተሞላ ነው፡፡ ቲቪ፣ ኢንተርኔት ባለበት ዘመን የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በቅጡ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ተማሪዎች የሚያፈሩት ‹‹በተደራሽነት›› ምክንያት ነው ማለት፣ የአመራሩን ስንፍና ለመሸፍን የሚደረደር ምክንያት ነው።  

ትናንት የቄስ ትምህርት ቤቶች ይወጡት የነበሩት ማንበብና መጻፍ፣ 38.9 ቢሊዮን ብር በጅት የተመደበላቸው የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መተግበር እየተሳናቸው ነው የሚል ግንዛቤ ላይ ስለተደረሰ ነው። 

ችግርን ከመጋፈጥ ይልቅ በካድሬ ቋንቋ ‹‹ተደራሽነት›› ማመካኛ ሆነ። እያንዳንዱ ልጅ ለቤተሰቡ ብርቅዬ ነው፣ መተኪያ የለውም። ግድ የለም ይህ ቤተ ሙከራ በልጄ ላይ ይካሄድና ውጤቱን ልይ አይልም? 

ስለዚህ አማራጭ በማጣት ቤተሰቦች ልጆቻቸውን  ይዘው እግሬ አውጪኝ አሉ፣ የግል ትምህርት ቤቶችን አጨናነቁ፡፡ የቻለ ውድ ዋጋ ከፍሎ፣ ያልቻለም ደግሞ ሆዱን አስሮ የልጆቹ ተስፋ ከጅምሩ እንዳይጨልም ወደ ግል ትምህርት ቤቶች ተሰደደ፡፡ ይህም  በኤፍኤም ሬድዮኖች ላይ የተነሱት የግል ትምህርት ቤቶች ችግሮች ተጋለጡ። ውድ ናቸው፣ ትክክል። በመንግሥት መጽሐፍ አያስተምሩም። ለምን ያስተምሩ? ቤተሰብ የተሻለ ነገር ፍለጋ አይደለም እንዴ በግል ትምህርት ቤት የሚያስተምረው? ውጤታማ ናቸው? አዎ። መንግሥት ራሱ ከግል ትምህርት ቤት ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ነጥብ ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች በላይ ያደረገው የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ችግር ስለተረዳ ነው። 

በአዲስ አበባ ብቻ 1,671 የግል ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም ፍላጎት ከአቅርቦት ጋር አልተጣጣመም፡፡ ወላጆች ለትምህርት ያልደረሱ ልጆቻቸውን አስተማሪ ቀጥረው የግል ትምህርት ቤቶችን የመግቢያ ፈተና እንዲያልፉ ማስጠናት፣ በዕውቅናና በአማላጅ ጭምር ሲለማመጡ ነው የሚታየት።

የአዲስ አበባ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲላሞ ኦቴሮ ልጃቸውን በግል ትምህርት ቤት እንደሚያስተምሩ በFM 97.1 ላይ ገልጸዋል።  ይህ ደግሞ አስገርሞኛል። ጋዜጠኛው አቅም ቢኖረው ለምን ብሎ መጠየቅ ነበረበት። ለዚህ ሁሉ የዳረገንን ችግር መልስ በሰጡን ነበር። ይኼም ባለሥልጣኑን ጨምሮ በርካታ ሕዝብ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ልጆችን ብቁ ማድረግ አይችልም የሚለው ግንዛቤ ማስረጃ ነው።

ቶኒ ብሌር የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስትር ከሚኖሩበት አካባቢ አርቀው በውጤታማነቱ በሚታወቅና (በማይከፈልበት) የሕዝብ ትምህርት ቤት ልጃቸውን በማስገባታቸው ምን ያህል ወቀሳ እንደደረሰባቸው ትዝ ይለኛል።

ሁሉም ጋዜጦችና ፖለቲከኞች የተስማሙበት ቶኒ ብሌር የሚመራው ትምህርት ቤቶች ለልጁ በቂ ካልሆኑ እንዴት ለእኛ ልጆች ብቁ ይሆናሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነት ሁሉንም ትምህርት ቤቶች  ለሁሉም ልጆች ብቁ ማድረግ አይደለምን የሚሉ ነበሩ። ይህ ለልጁ ትምህርት ቤት መረጣ ግብዝነት ነው የሚል ትችትና ተጠያቂነት ነው። ቶኒ ብሌር የሌበር ፓርቲ መሪ ሆነው በግል ትምህርት ቤት ቢሆን ልጃቸውን የሚያስተምሩት ትልቅ ተቃውሞ በተቀሰቀሰ ነበር። ለሕዝብ፣ ለሠራተኛው፣ ለግራ ዘመም፣ ለአብዮታዊ ዲሞክራት ነኝ ለሚል ትውልድ ደግሞ የትልቅ ግብዝነት ባህሪው መገለጫ ሐውልት ነው።

የኢትዮጵያ ግን የተለየ ነው። የትምህርት ቢሮዎቹ ኃላፊዎች እንኳን ሳይቀር በሚመሩት ትምህርት ቤቶች እምነት የላቸውም። ለዚህም ነው ትምህርት የወደቀው።

እ.ኤ.አ. በ1965 የተመረጠው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሮድ ዊልሰን ለትምህርት ሚኒስቴር ያጨውን ሮይ ጄኪንስን ጠርቶ ለትምህርት ሚኒስትርነት ሲሾመው፣ ሮይ ጄኪንስ ‘ይቅርታ እኔ ልጆቼን በግል ትምህርት ቤቶች እያስተማርኩ ስለሆነ ለዚህ ኃላፊነት ብቁ አይደለሁም’ ማለቱ እስካሁን ይጠቀሳል። በዴሞክራሲ አገሮች ፖለቲከኞች በሚመሩትና በሚሰብኩት የፐብሊክ ሰርቪስ የማይመጥናቸው ከሆነ፣ ከፖለቲካ ውጪ በርካታ ሙያ መምረጥ አለባቸው የሚል ያልተጻፈ ሕግ አለ። ለዚህም ነው ቶኒ ብሌር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው፣ ባለቤታቸው ደግሞ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚቆሙ የሕግ ጠበቃ ሆነው በአገሪቱ ውድ ትምህርት ቤት ማስተማር ሲችሉ፣ የብሌርና ሼሪ ብሌር ልጆች ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት የተላኩት። 

የአገራችን የግል ትምህርት ቤቶች ውድ ናቸው፣ ብዙም ችግር አለባቸው። ግን አማራጬ ደግሞ የባሰ ሆነ። ይህ ደግሞ ለብዙ ቤተሰብ ውድድር ውስጥ የማይገባ  ፈተና ነው።

የመንግሥት ፖሊሲ በፈጠራቸው ችግርች ምክንያት  ከተፈጠሩ የግል ትምህርት ቤቶች ትርፍ ተካፋይ ብቻ ሳይሆን፣ ለእነዚህ ሁሉ የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ትምህርት ቤት ሠርቶ፣ አስተማሪ መድቦ፣ ቾክና መጽሐፍ ለማቅረቢያ ይውል የነበረውን በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት ያድናል። በዚህም ሸክሙን ያቃለለትን የግል ትምህርት ቤቶች ሲያመሰግን አይታይም።

ለዚህም ነው ጥያቄው ለምን የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተመራጭ አልሆኑም ወደሚለው መመለስ አለበት። ከዚያም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከግል ትምህርት ቤት ምን መማር ይገባቸዋል መባል አለበት።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የዋይ ኤች ኤም የማማክር ሥራ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው YarHM@aol.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles