በዓለሙ ግርማ
በሚኒስተሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 152/2000 የኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ ተቋቁሟል፡፡ ይህ ኤጀንሲ ሲቋቋም ሦስት ዓበይት ዓላማዎች ነበሩት፡፡
- የሆርቲካልቸር ምርትና ምርታመነት በተፋጠነ በቀጣይነት እንዲያድግ የማብቃት፣
- ዓለም አቀፍ የምግብ ደኅንነት መሥፈርቶችን የሚያሞሉ የሆርቲካልቸር ምርቶችን ለውጪ ገበያ በዓይነትና በብዛት የሚቀርቡበትን ሁኔታ የማመቻቸት፣
- ድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን ያስተባብራል፣ እነዚህን በማቋቋም ደንብ በተሰጠው ኃላፊነት ዓላማ መሠረት በማድረግ ተጠሪነቱ ለእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሆኖ የተቋቋመ ኤጀንሲ ነው፡፡
መንግሥት ድህነትን ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት በመንግሥት በኩል ግብርና መር ኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ተቀርፆ በተግባራዊነቱ የግል ባለሀብቱ በማሳተፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛል፡፡ ከእዚህም መካከል አንዱና ዋነኛው ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን በመጠንና በጥራት ማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘትና ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በሰፊው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የኢትዮጰያ ሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ በየሚኒስተሮች ምክር ቤት ባወጣው 152/2000 የማቋቋሚያ ደንብ መሠረት ተደራጅቶ የተሰጠውን ሥልጣን፣ እንዲሁም ማከናወን ያለበት ቁልፍ ተግባራት በመለየት ሥራዎችን እንደየባህሪያቸው በአንድ ላይ በማሰባሰብ የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብና ልማቱን ለማፋጠን ከፍተኛ ርብርብ ለማድረግ፣ በሦስት ዋና የሥራ ሒደት በሁለት ደጋፊ የሥራ ሒደቶች እንዲዋቀር ተደርጎ የተቋቋመ ነው፡፡ በኤጀንሲው አደረጃጀት ላይ ተለይተው የወጡ የሥራ ሒደቶች የተገልጋይ ፍላጎት በማሟላት በቀጣይነት ኤጀንሲው የሴክተሩን ልማት ከጊዜ፣ ከወጪ፣ ከጥራትና ከመጠን የሚያስቀምጠውን ትልቅ ግብ (Ambitious Objective) ተደራሽነት እንዲኖረውና አጋዥና የሥራ መስመር እንዲሆን፣ መንግሥት መዋቅር ፈቅዶና በጀት መድቦ ያቋቋመው ኤጀንሲ ተልዕኮውን በመሳት እንዲደግፈው የተቋቋመው ሴክተር አመራሩ እየተሸመደመደ ልማቱን ሳይደገፍ ኤጀንሲው በቁሙ ራሱን መግደሉን በአደባባይ ይታያል፡፡ ይኼንንም የሴክተሩ ተዋናዮችና አልሚ ባለሀብቶች ይገልጻሉ፡፡
ተቋሙ ሲቋቋም የተሰጠው ተልዕኮና ራዕይ ያለው ቢሆንም፣ ለሙያው ሩቅ በመሆንና ራዕይ በማጣት ምክንያት አንድም ፕሮጀክት ሳይቀርፅና መሠረታዊ የሴክተሩ መረጃና ዳታ ሳይኖረው ምን እንደደገፈ አይታወቅም፡፡ ሴክተሩ ምን እንደሚያስፈልገው፣ ከባለሀብቱ ጋር አስተሳስሮ የአርሶ አደሩን ገቢ በማሳደግ ተገልጋይ ባለሀብቶች እርካታ አግኝተውና የልማት ሥራዎች ተስፋፍተው በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው የሚቀርቡበትን ሁኔታ ሳያመቻች፣ የሚጠበቀውን የሥራ ዕድል ሳይፈጥር በአመራሩ ደካማነትና ልፍስፍስነት ራሱ ኤጀንሲው የልማቱ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ሀ. የቴክኖሎጂ ድጋፍ የኤጀንሲው ችግር
- የሆርቲካልቸር ምርታማነትና ጥራትን አለመደገፍ
የሆርቲካልቸር የኤክስፖርት ምርት በገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል ጊዜ ያፈራውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የቅድመና የድኅረ ምርት አያያዝ ክህሎትን ለማጎልበት፣ ብቃት ያለው ፈጻሚ በመፍጠር በኤጀንሲው በኩል ይህንን ለመደገፍ የሚያስችል አመራር አቅም አልተገነባም፡፡ በተደጋጋሚ ወጣት ሠራተኞች አቅማችን ገንብተን ሴክተሩን እንደግፍ ቢሉ አመራሩ ለሙያው በቁ ባለመሆኑና ግንዛቤው ስለሌለው፣ ምርታማነት ለማሻሻል የሚወሰዱ የአቅም ግንባታና የልማት ቴክኖሎጂ ፖኬጆች የሉም፡፡ ባለሀብቱ እባካችሁ አትምጡብን፣ ሥራ አታስፈቱን፣ የምትጨምሩት እሴት የለም በማለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጿል፡፡ ለኤጀንሲው የሚመደበው በጀት ለእኛ እሴት ስለማይጨምር ለህዳሴው ግድብ ቢውል ይሻላል ብለው አስረድተዋል፡፡
በአበባ ልማት ላይ የተሰማሩት የግል ባለሀብቶች በተለይ ኢትዮጵያዊያን ዜግነት ያላቸው የመዳረሻ ገበያዎችን ባህሪና ዝርዝር ፍላጎት ባልገመገመ መንገድ ኢንዱስትሪው ለአገራችን አዲስ እንደመሆኑ መጠን፣ ኤጀንሲው ለመደገፍ የሚያስችል ክህሎት የለውም፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው በብልሹ አሠራር የተጠላለፈ በመሆኑ ያለሟቸው የአበባ ዝርያዎች የምርታማነትና የጥራት ችግር ብቻ ሳይሆን፣ በገበያ ላይ ያላቸው ተፈላጊነት ዝቅተኛ ስለነበር የተከፈላቸው አነስተኛ ዋጋና የሽያጭ ገቢ በግብርና ልማታቸው ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሷል፡፡
በአትክልት፣ በፍራፍሬና በኸርብስ ንዑስ የልማት ዘርፍም ቢሆን ልማቱን የማስፋፋቱ ሥራ በኤጀንሲው በአግባብ ስላልተደገፈ፣ ባለሀብቱ በግል ጥረቱ የሞከረው በጥቂት ሰብሎችና ዝርያዎች ላይ ነው፡፡ የተሻለ ገቢ የሚያስገኙ፣ ምርታማነታቸው ከፍተኛና በዓመቱ ውስጥ ተከታታይ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዓይነቶች ኤጀንሲው የአገሪቱን የምርምር ተቋማትን ዩኒቨርሲቲዎች በማማከር ለሴክተሩ ግብዓት የሚሆኑት በመፈተሽ ላይ ኤጀንሲው የተጠናከረ ሥራ እንዲሠራ ባለድርሻ አከላት ባለማስተባበሩና ባለመሥራቱ፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስተርም በአግባቡ ሴክተሩን ስላልመራው ለልማቱ ወደኋላ መቅረት ምክንያት ነው፡፡
- መልካም አሠራርና ስታንዳርድ አለማVላት
የኮድ ኦፍ ፕራክቲክስ (code of practice) በአበባው ንዑስ የልማት ዘርፍ በሁሉም የሴክተሩ ባለሀብቶች ተወስዶ ባለመተግበሩ፣ በአትክልት ፍራፍሬና ኸርብስ ንዑስ ልማቶች ላይ ኤጀንሲው በባለቤትነት ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለድርሻ ተቋማት ጋር በበቂ ባለመጀመሩ፣ ይህ ሁኔታ በመዳረሻ ገበያዎች ላይ በተለይም በሸማቾች ዘንድ አገራዊ መልካም አሠራርንና ስታንዳርድ (good agricultural practices) የኮድ ኦፍ ፕራክቲስ ትግበራ በሆርቲካልቸር የኤክስፖርት ልማት ላይ በባለቤትነት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሠርቶ የአገሪቱን የኤክስፖርት ገጽታ በመገንባት የወደፊቱን የአገሪቱን ኤክስፖርት ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠር አልተቻለም፡፡ ጥቂት ኪራይ ሰብሳቢዎችና ደላሎች የኤጀንሲው ትኩረት ኪራይ በሚሰበሰብበት ላይ ብቻ እንዲሆን አቅጣጫውን ሲያስቱት ቆይተዋል፡፡ የኤጀንሲውም ዕቅድ ከወረቀት ፎርማት ውጪ አልዘለለም፡፡ የሚገመገመውም ካለፈው ዓመት አፈጻጸም ውድቀቱ ጋር በማነፃፀር ነው፡፡ ለዚህም ነው በመጀመርያው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን እንደርስበታለን ያለውን 1.4 ቢሊዮን ዶላር በምክር ቤቱ የፀደቀ ዕቅድ አፈጻጸም ለፓርላማው ወደ 500 ሚሊዮን ቀነሶ፣ እሱንም ሳያሳካ የቀረው ተጠያቂነት ባለመኖሩ ምክር ቤቱ ያፀደቀውን በማን ሥልጣን እንደተከለሰ አይታወቅም፡፡
- የግብዓት አቅርቦት ችግር
ለሆርቲካልቸር ኤክስፖርት የተዘጋጁ አገራዊ ፓኬጂንግና ስታንዳርዶች ኤጀንሲው ከባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት ባለመሞከሩ፣ አገራዊ ፋብሪካዎች እንዲያመርቱ በማድረግ ውጭ ምንዛሪ ማዳን ባለመሞከሩ፣ ተጀምረው የነበሩ የካርቶን ፋብሪካዎች ባለመበረታታቸው፣ አንዳንድ የሴክተሩ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ደላሎች የአገር ውስጡ ምርት እንዳይበረታታ አሻጥር ፈጽመዋል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብት በኤጀንሲው ተደግፎ የፓኬጂንግ ሥራ ለመሥራት ኪራይ ሰብሳቢዎችና ደላሎች ከፍተኛ እንቅፋት ሲሆኑ፣ አመራሩ ይህን ለመከላከል ምንም አላደረገም፡፡
የማዳበሪያና የኬሚካል አቅርቦት ዋጋን ሊያረጋጉ የሚችሉ ንብረትነታቸው የመንግሥት የሆነ የባለድርሻ አካላት ጋር በጥናት የተደገፈ ሥራ ኤጀንሲው አልሠራም፡፡ በዚህም ዘርፍ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ደላሎች ጊዜው ያለፈበት ፀረ ተባይ መድኃኒት ወደ አገር ውስጥ እንዲገባና በየሱቁ እንዲሸጡ ሲያደርጉ ኤጀንሲው ለሴክተሩ ያደረገው እንቅስቃሴ የለም፡፡ ባለፉት ዓመታት ልማትን በመደገፍ በሚል በአገር ላይ የተደረጉ ብልሹ አሠራሮች ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል፡፡ የፌደራል ፖሊስና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በተጠናከረ መንገድ ለልማታችን እንቅፋት የሆኑ አደገኛ አከሄዶችን ተገቢ ምርመራ በማድረግ አስተማሪ ዕርምጃ ሊወስዱ ይገባል፡፡ ይህ ሳይደረግ ኤጀንሲውን ከሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ጋር ለመቀላቀል የሚደረገው ሩጫ የደላላውና የኪራይ ሰብሳቢው ሰንሰለት የት ድረስ እንደሆነ እንዳይታወቅ የሚደረግ ስለሆነ መቆም አለበት፡፡
ኤጀንሲው ከምርምር ተቋማትና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር ባለመፍጠሩ ለወቅቱ ገበያ የሚሆኑ የአበባና አትክልት ፍራፍሬ ዝርያዎች በአገር ውስጥ አልተገኙም፡፡ በአገር ውስጥ ዝርያ ማውጣት የሚችል ድርጀት አለመፈጠሩ የኤጀንሲው ድክመት በመሆኑ፣ በሴክተሩ ዕድገት ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር በቀጣይ በአገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ሽግግር አቅም ግንባታ በዘርፉ የሥራ ዕድል እንዳይፈጠር ኤጀንሲው ተልዕኮውን አልተወጣም፡፡
- የሎጂስቲክስ መሠረተ ልማት ችግር
እዚህ ላይ የሚያሳዝነው እኛ ኢትዮጵያዊያን ስለሆንን ሌላ አገር የለንም፡፡ ከውጭ ዜጎች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መወዳደር ስለማይፈልግ የውጭ አየር መንገድ እንዳይገባ እየተደረገ የሴክተሩ ፈተና ሆኗል በማለት አመራሩን ከመኮነን፣ በጥናት የተደገፈ አዲስ ሐሳብ ካለ አማራጭ ማቅረብ ይገባል፡፡ ሁሉም ለአንድ አገር እስከሠራ ድረስ የጠላት አገር አየር መንገድ ይመስል ስም ማጥፋት ተገብ አይደለም፡፡ አየር መንገዱ የግለሰብ አይደለም የአገር ሀብት ነው፡፡ ኤጀንሲውም ለአየር መንገዱ ዕድገት ማሰብ ነበረበት፡፡ ይህን ስንል እነዚህ ሰዎች ሌላ አገር አላቸው ወይ ብለው የውጭ ዜጎች ምን ያህል ይታዘቡናል?
ለአየር መንገዱ ሠራተኞች በኤጀንሲው በኩል ሥልጠና ቢሰጥ፣ ሠራተኞቹ ምን ያህል ለኤክስፖርት ሥራው ውጤታማ በሆኑ ነበር? ኤጀንሲው የማይመለከተውን ትቶ ለሴክተሩ የሚበጅ ቢሠራ የተሻለ ይሆናል፡፡
አሁን በመገንባት ላይ ባሉ የክልል ኤርፖርቶች የሆርቲካቸር ልማት ዕምቅ አቅም ያለው አካባቢ መሆኑን አረጋግጦ ዘመናዊ የማቀዝቀዣ ክፍል እንዲገነቡ በማማከር፣ የተጠናው አሉባልታ ሳይሆን ሀቅ ይዞ ለልማት ጉልበት ቢፈጥር ኤጀንሲው ውጤታማ በሆነ፡፡ እንዳሁኑ ለልማቱ እንቅፋት ማነቆ አይሆንም ነበር፡፡
- የአነስተኛ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነው እንዲሠሩ አለማድረግ
በጎረቤታችን ኬንያ በአውትግሮዎሮች ትስስር ለአርሶ አደሩ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ የተፈጠረለት ነው የአገራችን አርሶ አደሮች ኤጀንሲው ምንም ዓይነት ሥራ በዚህ ዘርፍ ባለመሥራቱ አልተጠቀሙም፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር ክፍተቱን ለመሙላት ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ዓውደ ጥናት በማዘጋጀት በጉዳዩ ላይ ምክክር አድርጎ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚሆኑበት፣ ሠፋፊ የሥራ ዕድሎች የሚፈጠሩበት፣ የተማረ አርሶ አደርሮች የሚፈጠሩበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ሲገባው፣ ኤጀንሲው የኪራይ ሰብሳቢና የደላሎች መፈንጫ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ደሃው አርሶ አደር ለኪራይ ሰብሳቢነት ምቹ ሁኔታ አልፈጠረም፣ ለኪራይ ሰብሳቢ የሚሆን ጥሪት የለውም፡፡ ሩጫው አርሶ አደሩን ከደላሎች ጋር ሆኖ አፈናቅሎ የመሬት ካሳ አስጨምርልሀለሁ በማለት ገንዘቡን መቀማት ነው፡፡ መሬቱን ለልማት ሲለቅ ተጠቃሚ እንዲሆን ተግባራዊ የማሳመን ሥራ ባለመሠራቱ አርሶ አደሩ እንዲከፋ ከማድረግ የዘለለ ከፌደራል መንግሥት እስከ ክልል መሥሪያ ቤት በተዘረጋ ኔትወርክ የኪራይ ሰብሳቢና የደላላ ትስስር አርሶ አደሩ ሲሰቃይ ቆይቷል፡፡ ኤጀንሲው ፍትሐዊ ሥራ እንዲሠራ፣ የሰፊው አርሶ አደር ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ የሥራ ዕድል እንዲሰፋ ጥረት አላደረገም፡፡ ሞኝ ዘፈኑ አንድ ነው እንዲሉ ሁሌ የኪራይ ሰብሳቢዎች ምንጭ የመሬት ጥያቄ ነው፡፡
አንድም ቀን ሥራው ታስቦበት አነስተኛ ገበሬዎች በኤክስፖርት ገበያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አልተደረገም፡፡ ለሆርቲካልቸር ምርት ግብዓት የሚሆን የሎጅስቲክስ አቅርቦት ለምሳሌ እንደ ጎረቤታችን ኬንያ ለአነስተኛ አርሶ አደሮች የማቀዝቀዣ የየቴክኖሎጂ የገበያ ድጋፍ የሚመቻችበትን ሁኔታ አጥንቶ ለመንግሥት አቅርቦ ተጠቃሚ የሚያደርግ ዕቅድ እንኳን የለውም፡፡ እርሶ አደሩ ልማቱን በጥርጣሬ ቢመለከተውና ቢያጠፋውም አይገርምም፡፡ ምክንያቱም ከልማቱ ተጠቃሚ መሆኑ አልተረጋገጠም፡፡ እንዲገነዘብም የሴክተሩ ባለቤት ነኝ የሚለው አካል አላሳየውም፡፡
- የግብይት አድማስ እንዲሠፋ ምንም አለመሠራቱ
የሆርቲካልቸር ምርት በተለይ ከአበባ አቅርቦት ውስጥ እስከ 80 በመቶ አንድ አገር ላይ ብቻ (ሆላንድ) በማተኮሩ፣ ይህንንም በጨረታ ማዕከሉ የሚካሄድ ግብይት ኮምፒተራይዝድ በመሆኑ በተጠና መልኩ የኤክስፖርተሩን የገበያ ሽያጭ የሚስጥር ቁጥር ከባለሀብቱ በመውሰድ የሻጩን ገቢ መከታተል ሲቻል፣ ለግል ጥቅም መሞዳሞድ ትቶ የአገርን ጥቅም ማስቀደም የኤጀንሰው ተልዕኮ ነው፡፡
ኤጀንሲው ከዘንግ ወደ ኪሎ መቀየሩ አገር መጉዳቱ እየታወቀ ቢሆንም፣ አሁን ያለው ሁኔታ በጥናት መመለስ ሲገባ ይህን ያነሳ በኤጀንሲ አመራር ሲወገዝ ይታያል፡፡ አመራሩ አንድ ያልገባው ማንም ዜጋ በአገሩ ጉዳይ ያገባዋል መንግሥት የተጭበረበረበት ጉዳይ የአገር ጥቅም የነካ በመሆኑ፣ የአገሪቱ ዓቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በዚህ ጉዳይ ጥብቅ ምርመራ ሊያከሂዱበት ይገባል፡፡ ማንም ኃላፊ ሆነ ከፍተኛ አመራር ሊጠየቅበት ይገባል፡፡ ይህም ማለት በአገሪቱ ቆላማ አካባቢ አበባው ውኃ የመያዝ አቅሙ ትንሽ ነው፡፡ በደጋው አካባቢ ውኃ የመያዝ አቅሙ ከፍያለ በመሆኑ፣ አብዛኛው የአበባ ልማት ያለው በአገሪቱ ስምጥ ሸለቆ ሞቃታማ አካባቢ ነው፡፡ ይህም ከኪሎ ይልቅ በቁጥር ቢለካ የበለጠ ገቢ ለአገር እንደሚያስገባ፣ በተለይ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው የዘርፉ ባለሀብቶች ይገልጻሉ፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች የኮንስሊዴሽንና የተጨማሪ እሴት ሥራዎች ባካተተ መንገድ እንዲዘጋጁ ኤጀንሲው ምንም ዓይነት ሥራ አለመሥራቱ ለሴክተሩ ዕድገት አለመኖር አሰተዋፅኦው የጎላ ነው፡፡
የገበያ መዳረሻ ለማስፋት ምንም ዓይነት ጥናት አልተካሄደም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚደርስባቸው መዳረሻዎች የአባባ ወይም የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ፍላጎት በመቃኝት ለመለየት ምንም ዓይነት ጥናት አልተደረገም፡፡ ቢታሰብበት ኖሮ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሱም ገበያ ነውና በጋራ ማጥናት በተቻለ ነበር፡፡ ኤጀንሲው የባለድርሻ አካላትን አሰተባብሮ መሥራት አቅሙም ሆነ ክህሎቱ የለውም፡፡ ለዕቅዱ መውደቅ ሌላው ሚስጥሩ የአመራሩ ክህሎት ችግር ነው፡፡
በኤጀንሲው ከፍተኛ አመራር ከአገር ውጭ በሚደረጉ ኢግዚቢሽኖች ለገበያ ማስፋፍያ ሥራ ምክንያት ጉዞ ቢደረግም፣ ከአመራሩ የአቅም ውስንነት ከአበል ለቀማ የዘለለ ውጤት ሳይታይ የተጠናም ጥናት ሆነ ሰነድ የለም በውጭ ገበያ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት የሚገባቸው የሕዝብ ግኑኝነት ሠራተኞች እንዳይሄዱ ስለሚደረግ ለባለሙያዎቹ የአቅም ግንባታ አልተደረገም፡፡
- ክህሎት ያዳበረ ተቋምና የሰው ኃይል እንዲፈጠር አለመሠራቱ
በሆርቲካልቸር ኤክስፖርት ልማትስ ከእርሻ ጀምሮ እስከ ገበያ መዳረሻ ድረስ በየእርከኑ ያለውን አሠራር ጠንቅቆ የሚያውቅ አመራርና ፈጻሚ ተግባራዊ ችሎታና ብቃት ያለው ተቋምና ባለሙያ እንዲፈጠር ኤጀንሲው ምንም ዓይነት ጥረት አላደረገም፡፡ ከምርምር ተቋማትና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለመሥራት ሙከራ አልተደረገም፡፡ አንድ የሆርቲካልቸር የተግባር ማሠልጠኛ ለመገንባት ጥረት ቢደረግም፣ የተፈቀደውን በጀት ኪራይ ሰብሳቢዎች ተቀራመቱት፡፡ ይህም ጉዳይ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን ፌዴራል ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ ጉዳዩን እንዲመረምሩትና ኪራይ ሰብሳቢዎችን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
የሚያሳዝነው ሴክተሩ እሴት መጨመር አልቻለም፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአንድ ወቅት ኢኮኖሚ ዓምድ ሥር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሎ ላይ በ2006 ዓ.ም. እንደዘገበው፣ ዕቅዱ በአካፋ አፈጻጸም በማንኪያ መሆኑን ዘግቧል፡፡ በለሀብቱ ሥራ አታስፈቱን፣ አትምጡብን ሲል እሴት የሚጨምር ኤጀንሲ ለመመሥረት መጠናት ያለበት ይዘውት በወደቁ አመራሮች ሳይሆን ዝርዝር ችግሮቹ በገለልተኛ ምሁራን ተጠንቶና ክፍተቱ ምን እንደሆነ ታውቆ ነው፡፡ ተጠያቂው ማነው ተብሎ መፍትሔ ሊፈለግበት ይገባል፡፡ ይህ ባይሆን አመራሩ እንዳይታወቅ የሚፈልገው የሚደበቅ ሒደት በባለቤቱ ሕዝብ ፊት ሊጋለጥ ይገባል፡፡
በድጋፍ ስም የተደረጉ ፍትሐዊ ያልሆኑ ድጋፎች፣ በእነዚህ ሽፋን የተፈጸሙ ኪራይ ሰብሳቢነቶች አልሚ ባለሀብቶችና መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን የታክስ ጥቅም አስቀርተዋል፡፡ በሚመለከታቸው ተቋማት አስፈላጊው ምርመራ ሊደረግና ለሌሎች ተቋማትም አስተማሪ የሚሆን ዕርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ይህ ሳይፈጸምና በተገቢው መንገድ ሳይገመገም፣ ተቋሙ ችግሩን ሳይለይ ኪራይ ሰብሳቢዎችን በመሸፈን በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሥር ካለው የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ጋር ለመቀላቀል መሮጥ መገታት አለበት፡፡ በዚህም መልካም አሰተዳደርን ለማስፈን፣ የኪራይ ሰብሳቢዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ፣ የአገራችን ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከኪራይ ሰብሳቢዎች ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ትግል አስተማሪ ዕርምጃ መንግሥት ይውሰድ፡፡ ለሌሎች ተቋማት ማሳያ ዕርምጃ ከአስፈጻሚው አካል ይጠበቃል፡፡
በአገራችን የአበባ ልማት ዘርፍ ከተሠማሩ ልማታዊው ባለሀብትና ኪራይ ሰብሳቢው መለየት አለበት፡፡ በቅርቡ በተደረገ የተሳሳተ ዕርምጃ ከመንግሥት ዕውቅና ውጪ በመንደር ደላላ አማካይነት ከአርሶ አደሩ መሬት በኪራይ ወስደው ከአርሶ አደሩ ጋር መግባባት ያቃታቸው ስምንት እርሻዎች ዕዳቸውን (የእርሻ መሬት ካሳ) መንግሥት መክፈሉ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህን ያህል ገንዘብ መንግሥት ካወጣ ለምን ከእርሻ ኮሌጆች ለወጡ የእርሶ አደር ልጆች መንግሥት አደራጅቶ አላበደረም? ትክክለኛ ድጋፍ እያደረግኩ ነው የሚለው ኤጀንሲ የቴክኖሎጂና የገበያ ድጋፍ አላደረገም? ወይስ አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢዎች በፈጠሩት ተፅዕኖ መንግሥትን በማሳሳት ከኪራይ ሰብሳቢ ባለሀብቶች ጋር ተሞዳሞዱበት፡፡ ይህ ድጎማ በልማታዊ ባለሀብቶች ተቃውሞ ደርሶበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሆርቲካቸር አልሚዎችና ላኪዎች ማኅበር አገራዊ አመለካከት ሊፈተሸ ይገባል፡፡ ለመሆኑ ለጉልበት ሠራተኞችና ለአርሶ አደሩ ልጆች ምን ያህል ክፍያ ይከፍላል? ከጎረቤት አገር ክፍያ ጋር ምን ይመስላል? አባላቱ ማኅበራዊ ኃላፊነት እንዲወጡ ጥረት እያረገ ነው? ወይስ አንፃራዊ ነው? ወይስ እንደ ኮሜዲ ድራማ በሕዝብ ላይ እየተወነ ነው? ሴክተሩ ባለቤት ይኑረው፡፡
ከአዘጋጁ፡-ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው alemu2008gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡
