Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Betty የግብፅ ከዘመነ የቅኝ ግዛት መስፋፋት ወደ ዘመነ ዓባይ ፍርኃት መሸጋገር

$
0
0

ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት አገር ነች፡፡ ዘወትር እንደምንሰማውና በተለያዩ ድርሳናት ተጽፎ እንደምናገኘው 3,000 ዓመታትን ያስቆጠረች የዕድሜ ባለፀጋ ነች፡፡ በዚህ የዕድሜ ዘመኗ ብዙ የታሪክ ሁነቶችን አስተናግዳና ተሻግራ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ በብዙ የትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ ላይ የደረሰችው አገራችን ብዙ ፈተናዎችንና ጋሬጣዎችንም ተሻግራለች፡፡ እንደ አገር ከተመሠረተች ጀምሮ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ድረስ በየአካባቢው ይነሱ የነበሩ የጐሣ መሪዎችና ገዥዎች ከሌሎች አካባቢ መሪዎች ጋር ያደርጉት ከነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ባሻገር፣ የውጭ ኃይሎች በተደጋጋሚ ጊዜ ለመውረር ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ የውጭ ኃይሎች መካከል አንዷ ግብፅ ነች፡፡

ግብፅ ኢኮኖሚዋ በዓባይ ወንዝ የተመሠረተና በሲናይ በረሃ ታጅባ ህልውናዋን የምትመራ አገር ነች፡፡ በዘመነ ቅኝ ግዛት መስፋፋት ጊዜ የራሷን ግዛት ለማስፋፋት ሙከራዎችን ያደረገች አፍሪካዊት አገርም ነች፡፡ ከስዊዝ ቦይ መከፈት ማግሥት ጀምሮ ኢኮኖሚዋን በንግድና በቴምር ምርት እያፈረጠመች የመጣችው የዓረብ ሊግ አባሏ አገር ግብፅ፣ አሁን ከዓረብ አገሮች የተሻለ ኢኮኖሚ መፍጠር ችላለች፡፡ ግብፅን ከአመድ ያነሳት እየተባለ በሚጠራው ንጉሷ ኬዲቭ እስማኤል አማካይነት ብዙ ዘመናትንና የታሪክ ገድላትን አሳልፋ እዚህ ላይ የደረሰችው ግብፅ የግዛት መስፋፋት ስታስብ ቅድሚያ የመጣላት የኢትዮጵያ ጉዳይ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በወቅቱ ብዙ ፈተናዎች የተጋረጡባትና የተረጋጋች አገር እንዳልሆነች በመገንዘብ ግብፅ ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ አዙራለች፡፡

የኢትዮጵያ ንጉሥ ካሣ ኃይሉ (በንግሥና ስማቸው ዳግማዊ ቴዎድሮስ) ዘመናዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት ሲታትሩ በነበረበት ወቅት ትልቅ ፈተና ከሆኑባቸው መካከል አንዱ የግብፅ ጉዳይ ነበር፡፡ የሞሐመድ ዓሊ ጦር ከካሣ ጋር ተዋግቶ ድል ሲሆን ግብፅ ሠራዊቷን በጋላባትና በመተማ አድርጋ ኢትዮጵያን የመውጋትና የማተራመስ ስትራቴጂ ቀይሳ ጦሯን ሰብቃ፣ ጋሻዋን መዝዛ ወደ ኢትዮጵያ አቀናች፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከውጭው አደጋ ይልቅ ውስጣዊ የሥልጣን ትግል ይበልጥ ክብደት የሚሰጠው ስለነበር የግብፅን ሠራዊት ለመመከት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ ግብፅ ያኔ እንደ አሁኑ የዓባይ ጉዳይ ሳይሆን የሚያሳስባት የቅኝ ግዛት ማስፋፋት ጉዳይ ነበር፡፡ በቀይ ባህር በኩል ያላትን ኃያልነትና ተሰሚነት ከፍ ማድረግ፡፡ በተለይ ይህ ሥጋት በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሳስባት የቻለው ዳግማዊ ቴዎድሮስ በ1855 ‹‹የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት›› ተብለው ዘውድ ከደፉ በኋላ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በአካባቢው የሚኖራትን ኃያልነትና ተሰሚነት በመፍራት የታቀደ ዘመቻና ወረራ ነበር፡፡ በዚህም ከኢትዮጵያው ንጉሥ አፄ ቴዎድሮስ ጋር ተፋልመው ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባቸዋል፡፡

ግብፅ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ባካሄደችው ዘመቻ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባትና በድል ልታጠናቅቅ እንደማትችል ስታውቅ ከንጉሡ በታቃራኒ የቆሙ የአካባቢው መሪዎችን መደገፍና ማስታጠቅ ጀመረች፡፡ ኢትዮጵያን እርስ በርስ የማተራመስ ስትራቴጂ የጠነሰሰችው እንግዲህ ከዚህ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

በዮሐንስ 4ኛ ዘመነ መንግሥት ጊዜም በኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ ጦርነት አውጃለች፡፡ በዳግማዊ ቴዎድሮስ ጊዜ የተከተለችው ፖሊሲና ስትራቴጂ አዋጭ እንዳልሆነ ስታወቅ ራሷን ገለል አድርጋ የቆየችው ግብፅ በዮሐንስ 4ኛ ጊዜም ሌላ ጦርነት ከፍታለች፡፡ እስከዚህ ዘመን ድረስ ግብፅ ዓባይን ፈጣሪዋ ለሷ ብቻ ብሎ የፈጠረው ስጦታ አድርጋ በመውሰድ በዚህ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ይነሳል ከሚል ፍርኃት ሳይሆን፣ አሁንም የግዛት ማስፋፋት ከነበራት ጉጉት የመነጨ ነበር፡፡ ለውጭ ጠላት መቼውንም እጅ ሰጥቶ የማያውቀው የኢትዮጵያ ጦር ግን በሁለት የጦር አውድማዎች ላይ የግብፅን ወታደር አመድ አደረገው፡፡ በ1875 በጉንደትና በ1876 በጉራ የጦር አውድማዎች ላይ፡፡

በታሪክ ግብፅና ኢትዮጵያ ይህን የመሰለ መስተጋብር ፈጥረው አልፈዋል፡፡ የጠቡና የግጭቱ መንስዔ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ግብፅ ነበረች፡፡   

የስዊዝ ካናል መከፈት ያስፈነጠዛቸው ኬዲቭ እስማኤል በምሥራቅ አፍሪካ የሚኖራቸውን ኃያልነት በህልማቸው ብቻ እንዳዩት አረፉ፡፡

የግብፅና የኢትዮጵያ ግንኙነት በዚህ ሁኔታ ከተቋጨ በኋላ እንደገና የሚያገረሸው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነው፡፡ በብዙ ምሁራን ዘንድ የኢትዮጵያ ሦስቱ አዕማድ ተብለው የሚጠሩ ጉዳዮች ማለትም ተፈጥሮ፣ ሃይማኖትና ታሪክ ተስማምተው ከሚኖሩባት አገር ውስጥ ተፈጥሮአዊ ስጦታችን የሆነውን ዓባይ ባነሳን ጊዜ የተፈጠረው እሰጥ አገባ ነው፡፡ ይህም ግብፅ ‹‹ከዘመነ የቅኝ ግዛት መስፋፋት ወደ ዘመነ ዓባይ ፍርኃት የተሸጋገረችበት ዘመን ነው›› ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ምንም እንኳ ግብፅ በዙሪዋ የሲናይ በረሃ የከበባትና ካለ ዓባይ ሌላ ህልውና እንደሌላት ቢታመንም፣ ‹‹ብቻዬን ልጠቀም›› የሚለው አመለካከቷና ፍላጐቷ በኢትዮጵያ አገራችን እንደተሻረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች ሌላኛው የታሪክ ገጽታም የሚጀምረው ከዚሁ ነው፡፡ ግብፅ የነበራትን በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የቅኝ ግዛት የማስፋፋት ፖሊሲ ሽራ በሰላም መኖር ከጀመረች ከብዙ ዓመታት በኋላ ያገረሸች አገር ሆናለች፡፡ የዓባይ ጉዳይ ሲነሳ የራስ ምታቷ ይጨምራል፡፡ የደም ፍላቷ ያይላል፡፡ ለዚህም ማሳያ ሊሆን የሚችለው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያ ዓባይን ለመገደብ በተንቀሳቀሰችበት ወቅት አገራችንን ለማተራመስ ለኤርትራ ታደርገው በነበረው የደኅንነትና የወታደራዊ ሎጀስቲክስ ድጋፎች ታይቷል፡፡ ይህ ድጋፍ ግን ጐልቶ የወጣው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ታደርገው በነበረው እንቅስቃሴ ጊዜ ነው፡፡

በእነ ዑስማን ሳልህ ሳቤ አማካይነት ግብፅ ኤርትራን እንደ ዶሮ ጫጩት ፈልፍላ ካሳደገች በኋላ ራሷን አፍሪካዊት ሲንጋፖር ለማድረግ ያቀደችው ዕቅድ አልተሳካም፡፡

ሻዕብያ ውስጥ ያደፈጠው የግብፅ የደኅንነት ቡድን ከኤርትራው ድሉ በኋላ ለሁለተኛና ለመጨረሻ ጊዜ ኢትዮጵያን የማተራመሱ አጀንዳ ኦሮሚያ ውስጥ የተወለደውና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ብሎ የሚጠራውን ቡድን በማስታጠቅና በመደገፍ ነው የጀመረችው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነን የሙርሲ መንግሥት ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ብሎ የሚጠራውን ቡድን መደገፍና ማስታጠቅ አንደኛው መፍትሔ እንደሆነ፣ በብሔራዊ ቴሌቪዥናቸው ለሕዝባቸው ያስተላለፉትን መልዕክት መውሰድ ይቻላል፡፡ እንግዲህ በዚህ ጊዜ የተደራጀው ኃይል ነው ዛሬም መቀመጫውን ግብፅ አድርጐ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሌት ከቀን የሚሠራው፡፡

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ አገር ብትሆንም፣ ተቻችሎ የመኖርና የመፈቃቀር ባህላችን ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ በያኔው ዘመን እንኳ ውድ አባቶቻችን ለውጭ ጠላት አገራቸውን አሳልፈው አልሰጡም፡፡ ሚስጥራቶቿንም አላባከኑም፡፡ የውስጣቸውን ችግር በራሳቸው ነበር የሚፈቱት፡፡ ይህንን ነው ከአያትና ከቅድመ አያቶቻችን የተማርነው፡፡ ይህንን ነው ከአያትና ቅድመ አያቶቻችን የወረስነው፡፡ ይህንን ነው ከአያትና ቅድመ አያቶቻችን የቀሰምነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ግን እየታየ ያለው ጉዳይ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ዕድሉን ቢያገኙ የዓባይን ግድብ በአንድ ቀን አፍርሰው ከሚያድሩ አገሮች ጋር መደራደር፣ እከከኝ ልከክህ ማለት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን እንድይዝ እጄም፣ እግሬም፣ ዓይኔም ሁነኝ፡፡ ላንተ ደግሞ የዓባይን ግድብ አፍርሼ ከሥጋት እገላግልሃለሁ የሚል ድርድር፡፡ በበኩሌ ‹‹የከሸፈ ትውልድ›› እንዳንባል ግን መጠንቀቁ አይከፋም እላለሁ፡፡

በእርግጥ በዘመነ ግሎባላይዜሽን ሁሉም ነገር በእጅ በደጅ በሆነበት ጊዜ አገሮች የደረሱበትን ደረጃ አይተን የራሳችንን አገር ኢኮኖሚና የዴሞክራሲ ከፍታ ስንመለከት ብዙ ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ ሥር የሰደደ ሙስና፣ በሥልጣን መባለግ፣ ኢ- ፍትሐዊ አሠራሮችና መድሎዎች፣ የሥራ ፈጠራ ዕድሎች ማነስ፣ የአሠራር ውስንነት፣ የአመራር ቁርጠኝነትና የአቅም ማነስ፣ ወዘተ. ችግሮች እዚህም እዚያም እየታዩ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ደግሞ መንግሥት ‹‹ችግሬ ናቸው፣ አብረን እንፍታቸው›› ብሎ ባመነበትና በአደባባይ እየተናገረ ባለበት ወቅት የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ ሊጥል በሚችል ሁኔታ የአገር ውስጥ ተቃዋሚ ነን ባዮች ከውጭ አገር መንግሥት ጋር፣ ያውም በዓይነ ቁራኛ ከምታየን አገር ጋር ወዳጅነት መመሥረት የአባቶቻችንን ቃል መሻር ነው የሚሆነው፡፡ ለብዙ ሺሕ ዓመታት ማንነቷን ጠብቃ ዜጎቿ ተፈቃቅረውና ተቻችለው በኖሩባት አገር እንደ ሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ እንዲከሰት የሚታትሩ  ትውልደ ኢትዮጵያውያን እዚህም እዚያም እየታዩ ነው፡፡

ግብፅም አንዴ ሞቅ አንዴ ለቀቅ ስታደርግ የነበረውን ኢትዮጵያን የማተራመስና መንግሥት አልባ የማድረግ ስትራቴጂ አሁንም እንደቀጠለችበት መረዳት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ ግብፅ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ላይ ጥናት የሚያደርግ ቡድን አቋቁመው በተፋሰስ አገሮቹ ላይ የህዳሴው ግድብ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ እያስጠኑ ቢሆንም፣ ከመድረክ በስተጀርባ ምን እየተከናወነ እንደሆነና ወደፊትስ ምን ሊከናወን እንደሚችል በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡

የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያዊያን አሻራ ያረፈበት የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች እያነሳን ብንሞግትም፣ ውይይቶች ብናደርግም፣ ክርክራችን ቢጦፍም ዓባይን ግን ለድርድር ልናቀርበው የማይገባ አሻራችን መሆን አለበት፡፡ በዓባይ ጉዳይ ከሚሞግቱን አገሮች ጎን ተሠልፈን ጥቅማችንን ለርካሽ የፖለቲካ ሥልጣን ስንል አሳልፈን አንስጥ፡፡ ያኔ የአባቶቻችንን ቃል ጠበቅን ማለት ነው፡፡ ያኔ ‹‹እኛ እኮ ኢትዮጵያውያን ነን›› ብለን አፋችን ሞልተን መናገር እንችላለን ማለት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡-ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው Zemetenagnelove@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles