Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ችግሮችን ለመፍታት በአንድ ላይ መቆም አለብን

$
0
0

በቴዎድሮስ መኰንን

እግር ኳስ በአገራችን ከሚወደዱትና ከሚዘወተሩት የስፖርት ዓይነቶች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ስፖርት ነው፡፡ እግር ኳስ በአገራችን ዝነኛና ተፈቃሪ እንዲሆን መሠረት ከጣሉት ክለቦች ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀድሞው አራዳ በአሁኑ አጠራር ፒያሳ አካባቢ በነበሩ ልጆች በ1920ዎቹ መጨረሻ እንደተመሠረተ ይነገርለታል፡፡ ወቅቱ በጣሊያን ወረራ ምክንያት የስፖርት ውድድሮች የተቀዛቀዙበት ጊዜ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ጣሊያኖች የስፖርት ቢሮ ለተወላጆች የሚሰኝ ክፍል በማቋቋም ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ሜዳ እርስ በራሳቸውና በራሳቸው ተመልካች ፊት ብቻ እንዲጫወቱ ከመደረጉም በላይ፣ የቡድኖቹ ስሞችም ተለውጠው ነበር፡፡ ከነፃነት መልስ አንድ ዓመት በኋላ በ1934 ዓ.ም የስፖርት እንቅስቃሴዎች በተለያየ ሁኔታ ቀጥለው ቅዱስ ጊዮርጊስና የስድስት ኪሎ ቡድን ደጃዝማች ነሲቡ ሜዳ የመጀመሪያውን ከነፃነት መልስ ውድድር አደረጉ፡፡

በ1936 ዓ.ም. የማስታወቂያ ሚኒስትር በነበሩት ክቡር አቶ ዓምደ ሚካኤል ደሳለኝ በተደረገ ድጋፍና በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ኃላፊነትና ጥረት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የስፖርት ቢሮ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ ተቋቋሟል፡፡ በ1940 ዓ.ም. የቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የክብር ዘበኛ፣ የምድር ጦርና የአስመራ ቀይ ባህር እግር ኳስ ቡድኖች መሪዎች በጃንሜዳ ሬሲንግ ክለብ ባደረጉት ስብሰባ፣ የፌዴሬሽን ማቋቋም ሐሳብ ለንጉሡ እንዲቀርብ ተደርጎ በወቅቱ ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ በሰጡት የገንዘብና የቢሮ ድጋፍ በጃንሜዳ ሥራውን እንዲያከናውን ከተደረገ በኋላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1941 ዓ.ም. የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲቋቋም ተደረገ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ጋር የማይነጣጠል ሰፊ ትስስር ያለው ሲሆን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲመሠረት ያደረጉት እነ ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምሥረታ በተጨማሪ፣ ለአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምሥረታ ትልቅ ሚና ከመጫወትም በላይ በአመራር ደረጃ የጎላ አስተዋፅኦ አድርገው አልፈዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በአሁኑ ጊዜ በቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ ያሉትን አጠቃላይ ችግሮች በመገምገምና በችግሩ ዙሪያ ተስፋ የቆረጠውንና የተከፋፈለውን ደጋፊ ለማዋሀድ ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፣ ከላይ ለመንደርደሪያ የጠቀስኩት ታሪክ በወቅቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የነበረውን የአመራር ብስለትና ብቃት ለማሳየት ተፈልጎ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጣሊያን ወረራ በፊት ከ1928 - 1933፣ ከ1933 -1966፣ ከ1966 - 1983፣ እንዲሁም ከ1983 ዓ.ም. በኋላ አምስት ሥርዓተ ጊዜዎችን አሳልፏል፡፡ ከ1933 - 1936 ዓ.ም. ድረስ የነበረው ጊዜ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ምሥረታ፣ ለተወዳጅነቱና አሁን ላገኘው ተቀባይነት ትልቁን መሠረት የጣለበት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 80 ዓመታት በነበረው የፖለቲካ መለዋወጥ ምክንያት በተለያዩ አደረጃጀቶችና አወቃቀሮች አልፏል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ መንግሥት በሚከተለው ነፃ ገበያ፣ እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት በስፖርቱ በተደረጉ መዋቅራዊ ለውጦች አማካይነት ስፖርት የጨዋታ ብቻ ሳይሆን የልማት ጉዳይም እንደሆነ በግልጽ ያስቀመጠ ሲሆን፣ የስፖርት ፖሊሲም ተቀርጿል፡፡

ክለቦች ሕዝባዊ ቅርፅ እንዲኖራቸው፣ የተጠሪ ድርጅት ወይም ባለቤት ድጋፍ እንዲኖራቸው፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ፣ ትጥቅና መሣሪያ እንዲመቻችላቸው፣ የተስተካከለና ብቁ አመራር እንዲኖራቸው፣ የስፖርት መርሐ ግብር በተመቻቸ ሥልት እንዲቀየስላቸው፣ ስፖርተኛውን በመንከባከብና በማሳተፍ እንዲያድጉ፣ ባለሙያዎችን ያካተተ እንዲሆኑ፣ ከመንግሥት በጀትና ድጎማ እንዲላቀቁ የሚሉ መርሆችን በማንገብ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ለውጦችን ከውስጥም ከውጭም በመጣ ኃይል ለማስተናገድ የተገደደ ሲሆን፣ ከምሥረታው ጀምሮ በቋሚነት የዘለቀው ደጋፊው ለክለቡ ያለው ፍቅር ብቻ ነው፡፡ በዚህም ረገድ ክለቡ ከአሥራ ስድስት ዓመታት በፊት በ1992 ዓ.ም. ሕዝባዊነቱን ሲያገኝ በወቅቱ ያልተደሰተ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነበረ ለማለት እጅግ ይከብዳል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ1992 ዓ.ም. በኋላ….

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ሕዝባዊ እንዲሆን በአባላቱ ከተወሰነ በኋላ፣ በመጀመሪያውም ሆነ በታኅሳስ 8 ቀን 1997 ዓ.ም. ተሻሽሎ በፀደቀው በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ ጠቅላላ ጉባዔው የክለቡ የመጨረሻው የሥልጣን እርከን ነው፡፡ በወቅቱ የአባልነት መዋጮ ግዴታቸውን የሚወጡ አባላት የጠቅላላ ጉባዔ አባል ብቻ ሳይሆን የክለቡ ባለቤት ጭምርም እንዲሆኑ ሲደነገግ፣ በኅብረቱ ስምምነት መሠረት የሥራ ድርሻ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር አንድ ተራ አባልና የቦርዱ ሰብሳቢ እኩል የባለቤትነት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላለፉት 16 ዓመታት ከጥቂት ግለሰቦች እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶች በሚገኝ ድጎማ የሚተዳደር ሲሆን፣ የክለቡ የበላይ ጠባቂ ክቡር ዶ/ር ሼክ ዓሊ አል አሙዲና አቶ አብነት ገብረ መስቀል ክለቡን እስካሁን ለማቆየት ላደረጉት አስተዋፅኦ ምሥጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በዘለቄታዊነት አለት ላይ ለማስቀመጥ ግን ገና ብዙ ያልተሠሩ ነገሮች እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከእነዚህም መካከል ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ከማድረግ አንፃር፣ ከላይ በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት የአንድ ክለብ ሕዝባዊነትን ከሚያረጋግጡ ነገሮች ዋነኛው ሕዝባዊነቱን የሚያረጋግጡ ሥራዎች ተፈጻሚነት ሲኖራቸው ነው፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 10 ንዑስ ቁጥር 10.4 መሠረት የማኅበሩ አባላት በማኅበሩ እንቅስቃሴ የመሳተፍ መብቶች እንዳሉት ሲደነግግ፣ በተጨባጭ የማኅበሩ አመራርና ደጋፊ (አባላት) የሚያገናኙ መድረኮች አለመኖራቸው አባላት በወቅታዊ የክለባቸው ጉዳይ ግልጽ ውይይት ለማድረግ የሚያስችሉዋቸው አጋጣሚዎች አልተመቻቹም፡፡ በሥራ አመራር ቦርዱ፣ በክለቡ አጠቃላይ ሁኔታ፣ በክለቡ የጽሕፈት ቤት አመራርና ቅጥር ዙሪያ በተጨማሪም የክለቡን ቴክኒካል ጉዳዮች የሚመሩ ግለሰቦች ስለሚመረጡበት ሒደት ግልጽነት የጎደለውና መሥፈርቱ ምን እንደሆነ በአግባቡ ስለማይገለጽ፣ ለበርካታ ችግሮች መጋለጡና አሠራሩ ሕዝባዊ ክለብ ከሚያደርገው ተግባራት በተፃራሪ የቆመ መሆኑ ይታያል፡፡

በአንቀጽ 15 ንዑስ ቁጥር 15.1 ‹‹የማኅበርተኞች ጠቅላላ ጉባዔ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ በሥራ አመራር ቦርድ ወይም በማኅበሩ ፕሬዚዳንት መጠራት ይኖርበታል፤›› ብሎ ያስቀመጠ ሲሆን፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቦርድ አመራር አባላት ወይም ፕሬዚዳንቱ ጠቅላላ ጉባዔ ከጠሩ ከአራት ዓመት በላይ መሆኑ ሕዝባዊነቱን የጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከት ነው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ዕድሜ ጠገብነቱ ሊኖሩት ከሚገቡ ነገሮች አንዱ ተቋማዊ ቅርጽ ሲሆን፣ በማንኛውም ጊዜ በአባላቱ (በጠቅላላ ጉባዔ) የሚመረጡ አመራሮች ገብተው ሊሠሩበት የሚያስችል አሠራርና ሥርዓት የተዘረጋ ባለመሆኑ ክለቡ በጥቂት ግለሰቦች ፈቃድ እንጂ እንደ ተቋም በተዋረድ የሥራ ክፍፍልና ድርሻ የሌለው መሆኑ አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ፣ የክለቡን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ በተጨማሪም በሙያቸው አንቱ የተሰኙ ሰዎች በጊዮርጊስ ዙሪያ ቢኖሩም፣ አሁን ባለው የጓደኝነት አሠራር ክለቡን በመራቃቸው ከፍተኛ የአመራር ብቃት ክፍተት ይታያል፡፡

ግልጽነትን ከማስፈን አንፃር በግል ማኅበራት እንደሚታየው ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርት በክለቡ ሰሌዳ ላይ ለማንኛውም አባላት የክለቡን ገቢና ወጪ እንዲያውቁ አለማድረግና ከወቅቱ ጋር የሚሄድ አሠራር አለመሆኑን ያለመገንዘብ ወይም ችላ የማለት ችግር ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ ማኅበራት ማደራጃ አዋጅ መሠረት የተቀመጡ የመንግሥት ድንጋጌዎችን አለማክበርና ተፈጻሚ አለማድረግ አንዱ የአመራር ችግር ነው፡፡ ክለቡን ለቅጣት ብሎም ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን በአግባቡ አለመገንዘብ በተጨማሪ፣ በጠቅላላ ጉባዔው የተላለፉ ውሳኔዎችን አለማክበር ለምሳሌ የጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ በጠቅላላ ጉባዔ እንዲነሱ ከተደረገ በኋላ ግልጽ ባልሆነ አሠራር በጓሮ እንዲገቡ መደረጋቸው ተጠቃሽ ነው፡፡

እግር ኳስ በአሁኑ ጊዜ ከገንዘብ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት ያለው ስፖርት እንደመሆኑ ክለቡ የራሱ ገቢ ሊኖረው የሚያስችል ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት አድርጐ አለመሥራትና በተጨማሪም ከመቼውም ጊዜ በላይ ክለቡን የግለሰቦች ጥገኛ ማድረግ ቀጣይ ህልውናው በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ላይ መጣል በመሆኑ፣ ነገ ሊፈጠሩ የሚችሉ ነገሮችን አርቆ የማየት ችግር አለ፡፡ የግለሰቦችን ሹመት ‹‹ሥዩመ እግዚአብሔር››፣ ሥልጣናቸውን የመለኮት ያህል አግዝፎ ማየትና አልፎ ተርፎም እነዚህን ሰዎች ካስከፋችሁ ክለቡ ችግር ላይ ይወድቃል በሚል አሮጌ አስተሳሰብ ደጋፊውን በፍርኃት ሸብቦ የመያዝ ስልታዊ አካሄድ፣ ከክለቡ ይልቅ በራሳቸው ጥቅም ዓይናቸው የታወረ ጥቂት ግለሰቦች በሚያራግቡት አሉባልታ ለዕድገት እንቅፋት እንደሆኑና የክለቡን ሞት እያፋጠኑ መሆኑ ያለመገንዘብ ሰፍኗል፡፡ ከአመራር ብቃት ጋር ተያይዞ በ2002 ዓ.ም. ሊከናወኑ በታቀዱት አሥራ ሰባት መርሐ ግብሮች መሠረት ተፈጻሚ ሊሆኑ የቻሉት ስድስት ብቻ መሆናቸው ለመጥቀስ የሚከተሉትን ማየት ይበቃል፡፡

የተከናወኑ ሥራዎች

የስፖርት ትጥቅና መሣሪያዎች ማግኘት፣ የመለማመጃ ቦታዎችን ማግኘት፣ የልሳነ ጊዮርጊስ ጋዜጣን በወቅቱ ማሳተም፣ የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ ውድድር ማዘጋጀት፣ በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች በአገር ውስጥና በኢንተርናሽናል ውድድሮች መሳተፍ፣ የታዳጊ ወጣቶች አካዳሚ ግንባታ ማከናወን (ይህ እስካሁን ያላለቀ ኘሮጀክት ነው)፡፡

ያልተከናወኑ ሥራዎች

የስፖርቱ ማኅበሩን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻል፣ ቀደም ሲል የወጡ ደንቦችንና መመሪያዎችን ማሻሻል፣ ጠቅላላ ጉባዔ ማከናወን፣ የአባላት ቁጥር ማብዛት፣ ቀጣይ የገቢ ምንጮችን መፍጠር፣ የስቴዲየም ግንባታ መከታተልና ማስፈጸም፣ የመዝናኛ ማዕከልና አገልግሎት ማስፋፋት፣ ለአባላት የስፖርትና የመዝናኛ ኘሮግራም ማስፋፋት፣ በማኅበራዊ ዘርፍ ተሳትፎ ማከናወን፣ ከአቻ ክለቦች ጋር የተጠናከረ ግንኙነት መፍጠር፣ የስፖርት ፋይናንስና አሠራር ኦዲት እንዲደረግ ማድረግ፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት ውስጥ ለመጥቀስ እንደተሞከረው አሁን በአመራር ላይ ያለው የጊዮርጊስ ክለብ ቦርድ ከስድስት ዓመት በፊት ለመሥራት አቅዶ ያልሠራቸው ሥራዎች ሲሆኑ፣ የአመራር ብቃቱን በግልጽ ጥያቄ ውስጥ ከተውታል፡፡ ከዚህ ጋር ሊጠቀሱ የሚገባቸው ነገሮች በተለይም የስፖርት ጽሕፈት ቤቱ አባላትን ከማሰባሰብና በአንድነት ለክለቡ እንዲቆሙ ከማድረግ ይልቅ በተራ አሉባልታ ወሬዎች መከፋፈል፣ ከሌሎች ክለቦችና ከፌዴሬሽኑ ጋር መልካም የሥራ ግንኙነት ከመፍጠር ይልቅ በንትርክና በሕገወጥ ነገሮች ክለቡ መጥፎ ስም እንዲያተርፍ ማድረግ፣ ከምንወደውና ለሌሎች አርዓያ ይሆናል ብለን ከምናስበው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር የሚሄድ ባለመሆኑ በአጠቃላይ የአመራር ሰንሰለቱ የተበላሸ ከመሆን አልፎ  አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡

በአጠቃላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከአገርም አልፎ በአፍሪካም ደረጃ አንጋፋና ቀዳሚ ከሆኑ ክለቦች የመጀመሪያው ረድፍ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ አሁን ያለው አሠራር፣ አመራርና ወቅታዊ ሁኔታዎች ፈጽሞ ከክለቡ ጋር የማይሄዱ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአገር ውስጥ ለሌሎች ክለቦች አርዓያ እንደመሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ በኋላ የተፈጠሩ እንደ ወላይታ ድቻ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት፣ ወዘተ. የመሳሰሉት የተሻለ የክለብ ቅርፅና ራዕይ እንዲሁም ብዛት ያለው ደጋፊ ሊያፈሩ ችለዋል፡፡ በተቃራኒው ቅዱስ ጊዮርጊስ የነበሩትን አንጋፋ ደጋፊዎች እያሸሸና ብልሹ አሠራር ተግባራዊ እያደረገ ሞቱን እያፋጠነ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ በላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ይህን ችግር ለመፍታት በአንድነት መቆም ሲኖርብን፣ በጥቂት ሰዎች የግል አጀንዳዎች እንዳንታለልና ክለቡን ያለጥሪት በማስቀረት ታሪካዊ ስህተት እንዳንሠራ መረባረብ ያለብን መሆኑን አስገነዝባለሁ፡፡

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ቦርድም (ምንም እንኳን የሥልጣን ዘመኑ በመተዳደሪያው ደንብ መሠረት ያበቃ ቢሆንም)፣ የክለቡን ደጋፊዎች ድምፅ ለማፈንና ብልሹ አሠራሮችን ለመሸፈን በተለያዩ ወቅቶች የሚደረጉ የድግስ ጋጋታዎች የክለቡን ቀጣይ ህልውና ከማስጠበቅ አንፃር ምንም ፋይዳ ስለሌላቸው፣ በዘላቂነት ክለቡን የሚጠቅሙ ሥራዎች ለማከናወን በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት የእርምት ዕርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ የኢፌዴሪ መንግሥትም ከሕዝብ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የሕዝብን ፍላጎት በተለይም በስፖርት ፖሊሲና በማኅበራት ማደራጃ አዋጁ በግልጽ ያስቀመጣቸውን ድንጋጌዎች እንዲያስፈጽም፣ ወቅቱም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በየሴክተሩ ርብርብ እየተደረገ በመሆኑ፣ በስፖርቱም መስክ ያሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትና የሕዝብን ጥቅም ማስጠበቅ ለነገ የሚባል አለመሆኑን እያስታወስኩ ጽሑፌን እቋጫለሁ፡፡ ምንጊዜም ጊዮርጊስ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles