Quantcast
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

የመሬት አስተዳደርና የመልካም አስተዳደር ትስስር

በነጋ ወልደ ገብርኤል

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም አስተዳደርን አስመልክተው ከምሁራን ጋር ያካሄዱትን ውይይት ስከታተል ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ከተሰማሩ ምሁራንም ጋር ለመሥራት ፍላጎት እንዳለ የሚጠቁም መልካም ጅማሮ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ እኔም ከመሬት ጋር በተያያዘ በመንግሥት ተቋም ውስጥ ረዘም ላሉ ጊዜያት በመስኩ ተመድቤ ሳገለግል የቆየሁ በመሆኔ፣ አሁን በመታየት ላይ ላሉት የመሬትና መልካም አስተዳደር ችግሮች እምብዛም እንግዳ አይደለሁም፡፡ እንግዳ አለመሆን ብቻ ሳይሆን በመፍትሔ ፍለጋው ጥረት አቅሜ እስከፈቀደ ድረስ በመስኩ ጥልቅ ዕውቀት ካላቸው የሥራ ጓደኞቼ ጋር በንቃት ተሳትፌአለሁ፡፡

መሬት እንደ ሰው ልጅ ሕልውና መሠረትነቱና ተፈጥሮ ለጋስነቱ፣ መሬትን የማይመለከት ምንም ርዕሰ ጉዳይም ሆነ ውሳኔ (የሁሉም ዘርፍ የፖሊሲ ውሳኔን ጨምሮ) የለም፡፡ ይኼው ልዩ የመሬት ሁኔታ እንደ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ልማታዊ፣ ቁሳዊ (ፊዚካላዊ)፣ ከባቢያዊ፣ ኅብረተሰባዊ፣ ማኅበረሰባዊና ግላዊ ሀብት እንዲወሰድ ያደርገዋል፡፡ ይኼው የተለየ ባህሪው የመሬት አስተዳደርንና አመራርን ከመልካም አስተዳደር ጋር ያስተሳስረዋል፡፡

ቀላል ባይሆንም የዚህ ጽሑፍ ዓላማም መሬትን በአግባቡ አለመምራት ለልማት እንቅፋት መሆኑንና ለመልካም አስተዳደር መስፋፋት ምክንያት እንደሚሆን በመረዳት በመሬት አስተዳደር ጉዳይ ላይ ክርክሮችና ውይይቶች እንዲፈጠሩ ለመጋበዝ እንደ መነሻ የተወሰደ በመሆኑ፣ ከሚነሱት ሐሳቦች ይጠቅማሉ የሚባሉት ተለይተው መንግሥት ለፖሊሲም ሆነ ለስትራቴጂ ግብዓት የሚሆኑትን በሚመለከተው ተቋም በኩል መፈተሽ ያስችለዋል፡፡

መሬት ሰፊና ውስብስብ ጉዳዮችን እንደመያዙ አፈታቱም ሊለያዩ (ሊበዙ) ስለሚችሉ፣ በመካከልም ስህተቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ስለመሬት አስተዳደርና ችግር አፈታት በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች ያካሄዷቸው የምርምር ውጤቶች (ኅትመቶች) በቂ መረጃዎችና ማስረጃዎች ናቸው፡፡ መሬትን በሚመለከት የዓለም ባንክ በየዓመቱ የሚያዘጋጃቸውን (Land and Poverty) ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ጨምሮ ሲካሄዱ የቆዩ አኅጉራዊ፣ ክልላዊና አገራዊ ሲምፖዚየሞች፣ ዓውደ ጥናቶች ውጤቶች የሚያስረግጡት ሀቅ ይኸው ነው፡፡ አገሮችም ከእነዚህ የተገኙ ውጤቶችን በመመርመር፣ ጠቃሚውን በመውሰድ፣ ከስህተታቸው በመማርና ማሻሻያዎችን በማድረግ በመሬት አስተዳደርና ልማት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ እንደሚገኙ ይገልጻሉ፡፡

እንደ አገራችን መሬት የመንግሥት (የሕዝብ) በሆነባቸው አገሮች ያለውን እንኳን ለማየት ቢሞከር፣ ለምሳሌ የሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ መጀመሪያ ጥንቃቄ የተሞላበት የመሬት አስተዳደር የሪፎርም ፕሮግራም እንዳካሄደችና በአሁኑ ወቅት በእስያ ከሚካሄዱት የሪል ስቴት ጥናትና ምርምር ሥራዎች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው ያተኮረው በቻይና ተሞክሮ መሆኑ ይገለጻል፡፡ እንደ ቬትናም ያሉ አገሮች የቻይናን ተሞክሮ እንዴት ተረድተው ቢወስዱት ነው እነሱም ለውጥ ለማምጣት የቻሉት? እኛስ ከእነዚህ አገሮች ምን እንማራለን? ከየት እንጀምር? ለሚሉት ጥያቄዎች መመካከርና ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

መሬትን ማስተዳደር ለምን አስፈለገ?

ከላይ እንደተመለከተው መሬትን የማይመለከት ጉዳይ ከሌለ የተለያዩ ፍላጎቶች (Interests) አሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥታት (የከተማ አስተዳደሮች) የራሳቸውን ፍላጎት ለማስከበርም ሆነ ከግለሰብ ጀምሮ የተለያዩ ክፍሎችን (አካላት ፍላጎትን) ለማስጠበቅ ወይም ለማቻቻል፣ ደንብና መመርያ እያዘጋጁ ተፈጻሚ ያደርጋሉ፣ ይከታተላሉ፡፡ እዚህ ላይ ፍላጎት (Interest) የሚለው ቃል ከመሬት ጋር በተያያዘ አገላለጽ የመጠቀም መብት ተብሎ ይወሰድ፡፡

መሬትን በቁጠባና በአግባቡ ለመጠቀም የፕላንና የግንባታ ፈቃድ እንዲሟላ፣ መብትን ከማረጋገጥና ከመጠበቅ አንፃር ይዞታ ምዝገባ እንዲደረግ የመሳሰሉት የተለያዩ ጥያቄዎች የግድ በደንቦችና በመመርያዎች መስተናገድ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ አሠራር በሠለጠኑትና መሬት በግል ይዞታነት በሚተዳደርበት አገሮች ጭምር የሚፈጸም ሲሆን፣ በእኛም አገር ይህንን ኃላፊነት እንዲወጡ በከተሞች ከተደራጁት ተቋማት መካከል የመሬት አስተዳደር ይገኝበታል፡፡   

የመሬት አስተዳደር ምንድነው?

የመሬት አስተዳደር (Land Administration) ስንል የመሬት ማኔጅመንትና የፖሊሲ ጉዳዮችን ተግባራዊ ለማድረግ የመሬት ይዞታ ባለቤትነት (Ownership)፣ የመሬት ዋጋ ግምት (Value)፣ የመሬት አጠቃቀም (Use) በተመለከተ መረጃ መሰብሰብን፣ መረጃውን ማረጋገጥና መመዝገብን፣ መረጃውን መተንተንና ለሚፈለገው ጉዳይ ማከፋፈልን ያጠቃልላል፡፡ ይህም በይዞታው የመጠቀም መብትን ለማስከበር፣ የአካባቢን ዋጋ ለመገምገምና ለመከታተል፣ እንዲሁም ከተሞች በሚያስተዳድሩት ወሰን ክልል ውስጥ ያለውን መሬት አጠቃቀም በመመዝገብ ለመለየት የሚያስችሉ መረጃዎችን የሚያካትት ይሆናል፡፡

የመሬት (መልካም) አስተዳደር (Land Governance) ስንልም በመሬትና መሬት ነክ ንብረት ተደራሽነትና አጠቃቀም ላይ የውሳኔ መስጫ ሒደቱን የሚመለከት ሆኖ፣ የውሳኔ አሰጣጡን አፈጻጸምና በመሬት ላይ ያሉ የጥቅም ግጭቶች (የግልና የመንግሥት) የሚቻቻሉበት (የሚታረቁበት) ሒደት ነው፡፡ ይህም በእኩል ተጠቃሚነት ደረጃ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራርን በመፍጠርና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የመሳሰሉትንና ሌሎች አንኳር ጉዳዮች የያዙ መርሆዎችን አተገባበር ይመለከታል፡፡

እዚህ ላይ ለማሳየት የተሞከረው የመጀመሪያው የመሬት አስተዳደር ሥራው (ክንውን) ሲሆን፣ ሁለተኛው የመሬት አስተዳደር መልካም የሚሆነው በምን መልክ ሲተገበር እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በከተሞች የመሬት አስተዳደር ሥራው ተዓማኒና በአግባቡ የተተነተነ ወቅታዊ መረጃን ያደራጀ መሆኑና ይህንን የመሬት መረጃ ለውሳኔ አሰጣጡ በምን መልክ እንደሚጠቀሙባቸውና ለሕዝቡ ተደራሽ እንደሚያደርጉ በመለየት፣ በመሬት አስተዳደሩ (Land Administration) እና በመሬት አስተዳደሩ (Land Governance) ላይ የማሻሻያ ዕርምጃ (የሪፎርም ፕሮግራም) መውሰድ ይገባል፡፡

በመሬት አስተዳደር ላይ የሚታዩ ችግሮች

የተደራጀ የመረጃ እጥረት

የመሬት አስተዳደር (Land Administration) ሥራውን በተገቢው መንገድ ለማከናወን ከተሞች የመሬት ይዞታን፣ የመሬት ዋጋና የመሬት አጠቃቀምን የተመለከቱ መረጃዎች በሚመለከታቸው ተቋማት በአግባቡ መደራጀቱ (መሰብሰብ፣ መተንተንና ማሰራጨት) ለሚሰጠው አገልግሎት መሠረታዊ መሆኑን በቅድሚያ በሁሉም አካላት መግባባት መፈጠር ይኖርበታል፡፡ በከተሞች የመሬት አስተዳደሩ አሠራር (ውሳኔ) በተሟላ መረጃ ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ፣ ዘላቂነት ያለው የመሬት ሀብት አስተዳደርን ለማረጋገጥና የከተማ መሬትን በአግባቡ ለመምራት አልተቻለም፡፡ ከመገለጫዎቹ መካከል መሬት ሲቀርብ የይገባኛል ጥያቄዎች መነሳትና በመሬት ወረራ መስፋፋት ምክንያት በተፈለገው መጠን ነፃ ቦታ አለመገኘት፣ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ወቅት የሚነሱ የይዞታ ማስከበርና የካሳ ክፍያ ጭቅጭቆች፣ በስም ዝውውር ወቅት የሚነሱ የድንበር ክርክሮች፣  አንድን ቦታ ለተለያዩ ሰዎችና አገልግሎት መስጠት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ይህም የሚያሳየው የይዞታ ባለመብቶች ተመዝገበው መረጃቸው አለመያዙን፣ የአካባቢው የንብረት ዋጋ መረጃ ተመዝግቦና ተተንትኖ አለመታወቁን፣ የእያንዳንዱ ይዞታ ድንበር ተለይቶ መረጃው አለመቀመጡን፣ እንዲሁም የከተማው መሬት ተቆጥሮና አጠቃቀሙ ተመዝግቦ አለመያዙን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ያለው የመሬት አስተዳደር አሠራር በተመደበው ኃላፊና ባለሙያ ዕውቀት ደረጃና በጎ ፈቃድ የሚፈጸም ስለሚሆን ለመልካም አስተዳደር ችግር የሚያጋልጥ ይሆናል፡፡

የአሠራር ግልጽነት አለመኖር

ከተሰበሰበውና ከተተነተነው መረጃ በመነሳት የሚተላለፉ ውሳኔዎችም ሆኑ አገልግሎቶች ግልጽና ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ የመሬት አስተዳደሩን (Land Governance) ማሻሻል ይቻላል፡፡ በከተሞች አስፈላጊው መረጃ ባልተደራጀበት፣ ፖሊሲዎችና ሕጎች ግልጽ ባልሆኑበት፣ ሠራተኛውም ሆነ ተገልጋዩ በእኩል ደረጃ ባልተረዱበትና አሳታፊ አሠራር ባልተፈጠረበት ሁኔታ ውሳኔዎቹ በቀላሉ ለአድልዎ (ምንም እንኳን ለግል ጥቅም ባይሆንም በዘርና በጎሳ፣ በፖለቲካ አቋምና ቤተሰባዊነት ምክንያት የአንዱን በንብረት የመጠቀም መብት ለሌላው ሲደረግ)፣ ለጉቦ (በተለይ የንብረት ምዝገባ ሲደረግ፣ በንብረት ዝውውር ወቅት፣ በካሳ ክፍያ፣ ስለንብረት መረጃ ሲፈለግ፣ የካዳስተር ቅየሳ ሲከናወን፣ የመሬት አጠቃቀም ፕላን ለውጥና የተለያዩ የመሬት ነክ አገልግሎቶች ሲጠየቁ) እና ለሰነድ ማጭበርበር (በዋናነት በንብረት ሽያጭ ወቅትና የመንግሥትን መሬት ወደ ግል አገልግሎት ለዚያውም አካባቢው መስጠት ከሚኖርበት አገልግሎት በታች እንዲውል ለማድረግ) የሚያጋልጥ በመሆኑ፣ የመሬት መልካም አስተዳደሩ ላይ ጥርጣሬው እየሰፋ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ጥርጣሬም ብቻ ሳይሆን ነዋሪው ስለንብረቱ ዋስትና ማጣት፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ፣ የሥነ ምግባር ብልሹነት፣ የግል ኢንቨስትመንት አለመጠናከር፣ የከተሞች ገቢ መቀነስ ይታያል፡፡

ሙስና

ሙስና የመልካም አስተዳደር ጉድለት መገለጫ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሙስና አንድን ሥራ በሞኖፖል ከመያዝና ከመምራት፣ የኃላፊው የማስተዋል ደረጃ፣ የተጠያቂነት ሥርዓት መኖር አለመኖርና ከአካባቢው የሥነ ምግባር ሁኔታ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ በመሬት መልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት በመሬት አስተዳደርና ልማት ከሚታዩ የሙስና ተግባራት መካከል፣

  • የመሬት አቅርቦቱ የነዋሪውን የመጠለያ ችግር በሚቀርፍ መልኩ (በቁጥርም ሆነ በተለይ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ተጠቃሚ ከማድረግ) የሚዘጋጅ ባለመሆኑ ምክንያት የሚፈጠርን የመሬት ወረራ መስፋፋት ለመከላከል በሚደረግ እንቅስቃሴ የሚፈጠር ሙስና፣
  • የይዞታ መብት ዓይነቶች በግልጽ ተለይተው ባለይዞታው እንዲያውቀውና መብቶቹ የሚሰጡትን ጥቅም በተሻለ እንዲገለገልበት ባለመደረጉ ምክንያት ጥያቄዎች ሲቀርቡ ምላሽ የመስጠት ሒደቱ የተንዛዛ መሆኑንና የሚቀርቡ ማስረጃዎች መብዛትን ለማሳጠር የሚደረግ ሙስና፣
  • የከተማ መሬት አጠቃቀም ፕላን ከዝግጅቱ ጀምሮ የነዋሪው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን ምክንያት ባለሙያው ብቻ የሚያውቀው ስለሚሆንና ሚስጥራዊ ስለሚያደርገው ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ከባለሙያው ወይም ከኃላፊው የሚቀርብ ሙስና፣
  • የአካባቢ መሬትና መሬት ነክ ንብረት ዋጋ መረጃ በአግባቡ ባለመያዙ ምክንያት በተለይ የስም ዝውውር ክፍያና ግብር አከፋፈልን አሳንሶም ሆነ ከፍ አድርጎ በመገመት የሚፈጠር ሙስና፣
  • ስለእያንዳንዱ ይዞታ በቂ መረጃ ባለመያዙ ምክንያት በፍርድ ቤት ያሉ የመሬት ክርክሮች መጓተትን ለማስቀረት የሚደረግ ሙስና ይጠቀሳሉ፡፡

የመፍትሔ ሐሳቦች

መንግሥት በከተሞች የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ የአደረጃጀት ማሻሻያዎችን፣ የመረጃ ሥርዓት ዝርጋታዎችን፣ የሰው ኃይል ሥልጠናን የመሳሰሉ ሥራዎችን ሲያከናውን እንደነበር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በቅድሚያ ለምን የተፈለገው ለውጥ ወይም ማሻሻያ አልመጣም የሚለውን በመዳሰስ፣ ከዚህ በታች የተጨመሩትን በማካተት ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡

ተቋማዊ ልማት

እኛ ወደ ከተማ መሬት አስተዳደር ሪፎርም እ.ኤ.አ. በ1990 ስንገባ ቻይና በአንድ አሥር ዓመት ብቻ (1980ዎቹ) ብትቀድመንም፣ በውጤት ደረጃ ስናነፃፅር ያለን ልዩነት እጅግ በጣም ሰፊ መሆኑ ቻይና ለተቋማዊ ልማት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቷን ያሳያል፡፡ የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች አደረጃጀታቸውን ጨምሮ አሠራሩ የሚገባውን የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎች፣ ደንብና መመርያ፣ ፎርሞችና ቼክ ሊስቶች፣ መከታተያ ቅጾች ማሟላቱ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቢሮዎች አቀማመጥና የፀደቁት ሰነዶች ግልጽነት በተላበሰ ሁኔታ ቀልጣፋ አገልግሎት ለማቅረብ ማስቻሉን መፈተሽ፣ የአቅም ግንባታ (በተለይ ሥልጠና) የሚሰጠው ጥቅም ቢታወቅም እስካሁን በነበረው ክንውን ምን ለውጥ አመጣ? ምን ያህል ሰው ሠለጠነ? አሁን የት ይገኛሉ? ለምን? የነዋሪው ተሳትፎ በምን መልክ ይሁን? ተጠያቂነትስ እንዴት በፈጻሚዎች ላይ ተግባራዊ ይሁን? ለሚሉት ምላሽ በመስጠት ማሻሻያዎችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የመሬት መረጃ ሥርዓት መዘርጋት

የመሬት ማኔጅመንት ሰፊ ጉዳዮችን እንደመያዙ ማለትም ከተሞች በሚያስተዳደሩት ክልል ውስጥ ያለውን መሬት በስፋትና በአገልግሎት ዓይነት፣ ወዘተ ቆጥረው ከመለየት ጀምሮ፣ መሬት ማልማትና ማዘጋጀት፣ ለገበያ ማቅረብና መብት መመዝገብ፣ የግንባታና የመጠቀሚያ ፈቃድ መስጠት፣ የአካባቢ የመሬትና መሬት ነክ ንብረት ዋጋን ግምት መከታተልና መገምገም፣ የመሬት ነክ ግብርን የመሳሰሉትን መረጃዎች ባለው የፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ የሰው ኃይል አቅም መሠረት ቅደም ተከተል በመስጠት በሚመለከታቸው ተቋማት የመረጃ ቋት ማደራጀት ይገባቸዋል፡፡

 

ከሰባት ዓመት በፊት መንግሥት የመሬት አስተዳደሩን የመረጃ ሥርዓት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ በቅድሚያ መሠራት ያለበትን እንዳስቀመጠ አውቃለሁ፡፡ ቅደም ተከተል መስጠቱ መረጃ የሚሰበሰብ፣ የሚተነተንና ለአስፈላጊ ጉዳይ የሚሰራጭ እንደመሆኑ ዓላማና ዕቅድ (Purpose) አለው፡፡ በቀላል አገላለጽ አንድ ሰው ሱሪ ማሰፋት ቢፈልግ ባለሙያው (ልብስ ሰፊው) የሚፈልገው መረጃ ከወገብ በታች ቁመትና የወገብ ልኬት ብቻ እንጂ የአንገትና የጫማ ቁጥር ባለመሆኑ (ይህንን መረጃ የሚፈልጉት ሸሚዝና ጫማ ሠሪዎች በመሆናቸው)፣ እያንዳንዳቸው ተቋማትም የሚፈልጉትን መረጃ በየራሳቸው ሰብስበውና ተንትነው ለሚሰጡት አገልግሎት እንዲጠቀሙ የሚረዳቸው ሥርዓት መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም መብት መዝጋቢው ተቋም፣ የከተማ መሬት አጠቃቀም ፕላን አዘጋጅና ፈጻሚውም፣ በመሬት ልማት የሚሳተፉ ድርጅቶችም፣ በመሬት ዋጋ ግመታና ግብር ላይ የተሰማሩ የፋይናንስ ተቋማትም እንዲሁ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልጋቸውን መሬትን/ይዞታንና መሬት ነክ ንብረትን የተመለከቱ መረጃዎችን ብቻ በየተቋማቸው እንዲሰበሰቡና እንዲተነተኑ በማድረግ የሚከናወን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህንን መፈጸም (ሥርዓቱን መዘርጋት) በራሱ ረጅም ጊዜና ገንዘብ የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ ቅደም ተከተል በመስጠት ጥራቱን የጠበቀ ሥራ አሁኑኑ ማስጀመርና መከታተል ያስፈልጋል፡፡ በቀጣይም የወቅቱን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የመረጃ ቅብብሎሹን ማስተሳሰር እስከዚያውም የተተነተነውን መረጃ በሲዲም ቢሆን መቀባበል ይቻላል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ተቋማት የሚፈለጉ መረጃዎች በአንድ ቦታ ለማጨቅ መሞከር መረጃውን በመተንተን ወቅታዊ የሚያደርግ አካል ስለማይኖር፣ አንዱንም የታለመለትን ጉዳይ ሳያስፈጽም በእንጥልጥል እንዲቀር ያደርገዋል፡፡

የመረጃ ተደራሽነትና የሕዝብ ተሳትፎን ማረጋገጥ

በሠለጠኑ አገሮች መረጃን ተደራሽ ለማድረግ በታወቁ የመረጃ መረቦች ውስጥ በመግባትና የሚፈለገውን ክፍያ በመፈጸም፣ ወይም ከየተቋማቱ የታተመ መረጃ በመግዛት ይዳረሳል፡፡ ይኼውም ከይዞታ መዝጋቢው ተቋም ማግኘት ስለተፈለገው ይዞታ (ንብረት) መረጃ፣ ከመሬት አቅራቢው ተቋም መሬት በሊዝ ለመገብየት ለፈለገ ስለአካባቢው የልማት ዕቅድና የአካባቢው የቀድሞው ዋጋ መረጃ፣ ከከተማ ፕላን ፈጻሚው ተቋም ስለሚፈለገው አካባቢ የመሬት አጠቃቀም ፕላን አገልግሎቶች መረጃ፣ ከንብረት ዋጋ ገማቹ ተቋም ስለአካባቢው አማካይ የንብረት ዋጋ መረጃ በአግባቡ ተደራጅቶ በማስቀመጥ ለፈላጊው በማዳረስ ይሆናል፡፡ ለዚህም  እንደ መረጃ ደህንነት ማለትም መረጃን ከእሳትና ከቫይረስ ጥቃት መጠበቅ፣ የግለሰብን መብትና ነዋሪው የመንግሥት መረጃን የመጠቀም ተደራሽነትን የመሰሉ ሕጎች ማውጣት የመሳሰሉት ቅድመ ጥንቃቄዎች ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የሕዝብ ተሳትፎን በተመለከተም ነዋሪው በሠፈርም ይሁን በቀጣና፣ በመገናኛ ብዙኃንና ሥልጠና በመስጠት ስለአገልግሎቶቹ እንዲያውቅና የፈለገውን መረጃ የሚያገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ነዋሪው ችግሮችን የሚያቀርቡ ተወካዮችን መርጦ የሚያቀርብበት አሠራር መፍጠሩ ለግልጽነት አሠራሩ ጠቃሚ ያደርገዋል፡፡

የአሠራር ግልጽነት መፍጠር

ግልጽነትን (Transparency) ለመፍጠር አሠራሩ የታወቁ ተግባራት እንዲኖሩትና አገልግሎት ሰጪውም ሆነ ተገልጋዩ በቀላሉ የሚረዱት እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡ ይህ አሠራር በጎ ሥነ ምግባርን ከመፍጠሩ በተጨማሪ የሕዝቡ የመረጃ ማግኘትንና በተለይ ኑሮውን ሊጎዱም ይሁን ሊጠቅሙ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የመሳተፍ ሕገ መንግሥታዊ መብትን ማክበርም ስለሚሆን፣ የኃላፊዎችን በጎ ፈቃድ የማግኘት ጉዳይ መሆን አይገባውም፡፡

የሥነ ምግባር ብልሹነትን ማሻሻል

የሥነ ምግባር ብልሹነት በአገልግሎት ሰጪው ብቻ ሳይሆን በነዋሪው ውስጥም ይኖራል፡፡ በነዋሪው መካከል የሚኖር የሥነ ምግባር ጉድለት ከሚገለጽባቸው መካከል ታክስ ያለመክፈል፣ የይዞታ ካርታም ሆነ መብት ማረጋገጫ ሰነድ ሳይኖር ስም ማዘዋወር፣ የግንባታ ፈቃድ ሳይጠይቁ መገንባት፣ ቦታው ለተፈቀደለት አገልግሎት አለማዋል ይታያል፡፡ ስለዚህ ነዋሪውን የተመለከቱ የሥነ ምግባር ማሻሻያ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡ አገልግሎት ሰጪውን በተመለከተም የጥቅም ግጭት እንዳይኖር የሚያስችል ሕግ (Conflict of Interest Law)፣ የሙያ ሥነ ምግባር ደንብ (Code of Professional Ethics/Conduct) መቅረጽ፣ ስለጠቋሚዎች ከለላ (Whistleblower Protection) እና የሥነ ምግባር ሥልጠና የመሳሰሉት ሰነዶች ማዘጋጀትና ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለነዋሪው የአገልግሎት እርካታውን የሚገልጽበት የሪፖርት ካርድ ማዘጋጀት፣ ለዚህም ሚስጥራዊነቱን ማረጋገጥ፣ የሥነ ምግባር ችግር ሲያጋጥም ጠቋሚዎች የት እንደሚሄዱና በምን መልክ እንደሚጠቁሙና ማበረታታት እንደሚቻል ግልጽ የሆነ አሠራር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህም በነዋሪውም ሆነ በአገልግሎት ሰጪው የሚፈጠሩ የሥነ ምግባር ችግሮች እንዲቀረፉ ይረዳል፡፡

ነፃ የፀረ ሙስና ተቋም ማደራጀት

ከላይ ከተጠቀሱትና ለሙስና ከሚያጋልጡ ጉዳዮች በተጨማሪ ያሉትን ልምዶች መለየት አስፈላጊ ሲሆን፣ በዚህም ሕዝቡ ስለሙስና ያለው አረዳድ (ሙስናን የማይቀበል መሆኑ፣ የሙስና መስፋፋት ዕይታ፣ መንግሥት ሙስናን ለመግታት ያለው ፍላጎት፣ ያሉ ፀረ ሙስና ስትራቴጂዎች፣ የክትትል ሥልቶችና ተግባራዊነታቸው) ተመዝኖ መታየት ይኖርበታል፡፡ ነፃ የሚለው በእንግሊዝኛ (Independent) ለሚለው መተኪያ እንዲሆን የተቀመጠ ሲሆን፣ ከተጠቃሚው የሚቀርቡ የመሬት አስተዳደር የሥነ ምግባር (የሙስና) ጥቆማዎችን በመቀበል ለአመራሩ የሚያቀርብ ሆኖ፣ አደረጃጀቱም ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ አባላት የተዋቀረ ይሆናል፡፡

ማጠቃለያ

መልካም አስተዳደር የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ማለትም የመንግሥትን፣ የሕግ አውጪውን፣ የተርጓሚውንና የአስከባሪውን፣ የግሉን ዘርፍና የነዋሪውን ርብርብ ይጠይቃል፡፡ ከእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች አንዱ ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ በሚፈለገው መጠን አለመሳተፍ ልክ አንድን ሕንፃ ለማቆም ከሚፈለጉ ምሰሶዎች አንዱ ቢጎድል በሕንፃው ላይ ሊፈጠር እንደሚችለው፣ የዲዛይንና የግንባታ ችግር የታለመለት ግብ ላይ ለመድረስ አይቻልም፡፡ ግልጽነት መረጃ በተፈለገው ጥራት መቅረብ እንዳለበት ላይ የሚያጠነጥን በመሆኑ፣ በመንግሥት ተቋም (በከተማ፣ በገጠር መሬት አስተዳደር) የሚገኝን መረጃ በጥራት በማደራጀት ለሁሉም ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ለጥናትና ምርምር ከፍተኛ ዕገዛ ያደርጋል፡፡ በመሬት (መልካም) አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ያለውን የአቅም ግንባታ ክፍተት መለየትና የማሻሻያ ስትራቴጂዎችን መቅረፅ ትኩረት ሊሰጠው ከሚገባቸው መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህም የአገልግሎት ሰጪውንና የፖሊሲ አውጪዎችን የአቅም ክፍተት ወደ ክህሎት፣ ዕውቀትና አመለካከት ለመቀየር የሚያስችል መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

በመሬት አስተዳደር ተቋም እንዴት ግልጽና ቀልጣፋ አሠራር መፍጠር ይቻላል የሚለውንና የሥራ ኃላፊነት (Mandate)፣ የሥራ ሒደት፣ የመረጃ ቅብብሎሽና ቁጥጥር በምን መልክ እንደሆነ መዳሰስ ያስፈልጋል፡፡ የነዋሪውን የአገልግሎት ቻርተር የሚገልጽ (የደንበኛን ክቡርነት፣ የተጠቃሚውን የአገልግሎት ስታንዳርድና ችግሮች ሲፈጠሩ ስለሚደረገው የማስተካከያ ዕርምጃ) ሰነድ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ የቢሮው አቀማመጥ፣ የመረጃ ዴስክ፣ ጉዳዮች በአንድ ክፍል/ቦታ እንዲያልቁ ከማድረግ፣ የአቤቱታ ሰሚ ክፍል ወይም አሠራር አደረጃጀት መጠናትና መዋቀር ይኖርበታል፡፡ በአጠቃላይ የመሬት አስተዳደሩን በመልካም አስተዳደር ቅኝት ውስጥ ለማስገባት ሰፊ ሥራና የሁሉንም አካላት ዝግጁነት እንደሚፈልግ ከላይ ለማመላከት ተሞክሯል፡፡ ሩጫ ከዕርምጃ እንደሚጀምር ሁሉ ዛሬ መጀመር ያለበት ተጀምሮ በሒደት የሚሻሻለው እየተስተካከለ ወደተፈለገው ግብ መድረስ ይቻላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው nwgebreal@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

Standard (Image)
Image may be NSFW.
Clik here to view.

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles