በዳንኤል አረጋዊ ኃይሉ
የኅብረተሰባችንም ሆነ የአብዛኛዎቹ የአገራችን መገናኛ ብዙኃን ሰሞነኛ ወሬ ከስኳር ኮርፖሬሽንና ከሌሎች ተቋማት ጋር ተያይዞ ተፈጸመ የተባለው የሙስና ተግባር ነው፡፡ እኔም ከተለያዩ ሰዎች ጋር በዚህ ጉዳይ ሐሳብ ስለዋወጥና ስከራከር ሰንብቻለሁ፡፡ ሐሳብ ልሰጥባቸው ባልቻልኩባቸው አጋጣሚዎች ደግሞ በተለያየ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚሰነዝሯቸውን ሐሳቦች በዝምታ ሳደምጥ ቆይቻለሁ፡፡ በነበሩኝ ገጠመኞች ሁሉም ሰው ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ሰሞኑን ተፈጸመ የተባለውን የሙስና ወንጀል ሲኮንን፣ ሲያወግዝና ሲፀየፍ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ወደ አዕምሮዬ የሚመጣውን ጥያቄ በሄድኩበት እያነሳሁ ከራሴም ከሌሎች ሰዎች ጋርም ስሟገት ከረምኩ፡፡ ለመሆኑ ማኅበረሰባችን የሚፀየፈው ሙስናን ነው ወይስ ሙሰኛን?
መቼም ማኅበረሰባችን “ከስኳር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ሀብት ይመዝበር” የሚል አቋም ይኖረዋል ብዬ ለማሰብ በእጅጉ እቸገራለሁ፡፡ እንደዚህ ብዬ ባስብም ድፍረት ይሆንብኛል፡፡ ነገር ግን በዚሁ ጉዳይ ላይ ማኅበረሰባችን ሊኖረው የሚችለውን አቋም ከሌላ አቅጣጫ ብመለከተው የተለየ መደምደሚያ ላይ የምደርስበት ዕድል እንዳለኝ ይሰማኛል፡፡ ለዚህ የተለየ መደምደሚያዬ መንደርደሪያዬን ላቅርብና ተጨማሪ ጥያቄዎችን ልሰንዝር፡፡ እንበልና ሰሞኑን ተፈጸመ የተባለውን የሙስና ወንጀል ሲኮንን፣ ሲያወግዝና ሲፀየፍ የነበረው የማኅበረሰባችን ክፍል በጠቅላላ የሙስና ወንጀል ፈጸሙ የተባሉትን የሥራ ኃላፊዎች በሙሉ በሙስና ተግባር ተጠርጥረው ከመያዛቸው በፊት በቅርበት ያውቃቸዋል እንበል፡፡ ታዲያ ከዚህ የማኅበረሰባችን ክፍል ውስጥ ምን ያህሉ ሰው እነዚህ የሥራ ኃላፊዎች ወደ ሙስና ተግባር እንዳይገቡ ይመክር ነበር? በእርግጥም ወደ ሙስና ተግባር ገብተው ከነበረ ምን ያህሉ ሰው ይኼንኑ ተግባራቸውን ያወግዝ ነበር? በእርግጥም በሙስና ተግባር ያካበቱት ሀብት ከነበረ ምን ያህሉ ሰው ይኼንን ሀብት ይፀየፈዋል? ከግል ልምዴና ምልከታዬ በመነሳት እነዚህን ጥያቄዎች ብመልስ አብዛኛው የማኅበረሰባችን ክፍል ሙስናን በተመለከተ በአደባባይ የሚያሳየውና በጓዳው የሚያራምደው አቋም መለያየቱን ከመግለጽ ወደ ኋላ አልልም፡፡ ለዚህ መደምደሚያዬ መነሻ ከሆኑኝ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹን ላመላክት ወይም ልግለጽ፡፡
በመንግሥት ሠራተኝነት ለመጀመርያ ጊዜ የተቀጠርኩት በቀድሞው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፍትሕ ሚኒስቴር በፌዴራል ዓቃቤ ሕግነት ነበር፡፡ በዚህ ኃላፊነት ስሠራ እንደነበረ የሚያውቁ የቅርብ ወዳጆቼና በተለያየ ማኅበራዊ ግንኙነት ውስጥ የማውቃቸው ሰዎች ሥራዬን የተመለከቱ የተለያዩ ምክሮችንና ማስጠንቀቂያዎችን ይሰነዝሩልኝ ነበር፡፡ በሥራ በቆየሁበት ጊዜ ሁሉ ሥራዬን በፍፁም ታማኝነት እንድወጣ፣ በሥነ ምግባር ኅብረት ሊኖረኝ ከማይችሉ ሰዎች ጋር ያለኝን የሥራና ማኅበራዊ ግንኙነት በጥንቃቄ እንድመራና በፍፁም ጉቦ የሚባል ነገር እንዳልጠይቅም ሆነ እንዳልቀበል እስከ መጨረሻዋ የአገልግሎት ጊዜዬ ድረስ ሲመክሩኝና ሲያስጠነቅቁኝ የነበሩት ሰዎች እጅግ በጣም ጥቂት ነበሩ፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ በዙሪያዬ ከነበሩት መካከል የላቀውን ቁጥር የያዙት ሰዎች ምክር የተሰማራሁበትን ሙያና የሥራ ኃላፊነቴን ተጠቅሜ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ሀብት እንዳካብትና ሥራውን በቶሎ እንድለቅ የሚያግባቡ ነበሩ፡፡
ከፍትሕ ሚኒስቴር በመቀጠል በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በዳኝነት የሥራ ኃላፊነት አገልግያለሁ፡፡ በእነዚህ ዓመታት ቀድመው ንፅህናዬን እንድጠብቅ ሲያበረታቱኝ የነበሩት ሰዎች ቁጥር እየተመናመነ መምጣቱን አስተውያለሁኝ፡፡ በአቋማቸው የፀኑቱ ደግሞ በአቋሜ ምክንያት “አትበላ አታስበላ” ተብለህ አደጋ ውስጥ እንዳትወድቅ ወደሚል ሥጋት ተሸጋገሩ፡፡ ሙስናን የሚያበረታቱት ደግሞ የዳኝነት ሥራ ከምንም በላይ በሙስና ሊከበርበት የሚችል ሙያ ነው ብለው በማሰብና በመደምደም፣ በእኔ ላይ ይፈጽሙ የነበረው ግፊት በመጠንም በጫናም ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ ሐሳባቸውን አለመቀበሌ ደግሞ ልክ ነውር እንደፈጸምኩና ቂላቂል እንደሆንኩኝ አስቆጥሮኝ በእጅጉ ሲያስተቸኝ ነበር፡፡ ከዳኝነት ሥራ በለቀቅኩበት በአሁኑ ጊዜ እንኳን የሙስና ተግባር ባለመፈጸሜ “ሊቆጭህ ይገባል” እየተባልኩ እኮነናለሁ፡፡ የሚገርመኝ ሙሰኛ እንድሆን ያበረታታኝ የነበረው ሰው መብዛቱ ብቻ ሳይሆን፣ የሙስና ተግባርን አግባብ የሚሆንባቸውን ሁኔታዎች ለማሳየት ሰዎች የሚያነሷቸው ምክንያቶች (Reasons) የተለያዩ መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት ነው ማኅበረሰባችን የሚፀየፈው ሙስናን ነው ወይስ ሙሰኛን? የሚለውን ጥያቄ ማንሳቴ፡፡
እኔ የማውቃቸው ሰዎች ማኅበረሰባችን ይወክላሉ ወይ? የሚል ጥያቄ ልታነሱ ትችላላችሁ፡፡ በእርግጥም የምሰነዝረው ሐሳብ የጥልቅ ጥናት ውጤት ባለመሆኑ ማኅበረሰቡን የሚወክል ናሙና (Sample) መርጬ በዚህ ጉዳይ ላይ ያደረግኩት ጥናት የለም፡፡ ነገር ግን እንድሞስን ሲያግባቡኝ ወይም ሙስና “ተገቢ” የሚሆንባቸውን ሁኔታች ሊያስረዱኝ ይሞክሩ የነበሩ፣ በዙሪያዬ ያሉና በማኅበራዊ ሕይወት የማገኛቸው ሰዎች የተለያየ ሃይማኖት፣ ዕድሜ፣ ፆታ፣ አስተዳደግ፣ ኢኮኖሚያዊ አቅም፣ ባሕል፣ ፖለቲካዊ አቋም፣ የትምህርት ደረጃ፣ ወዘተ ያላቸው በመሆናቸው ከእኔ ምልከታና ገጠመኝ የመነጩት ሐሳቦች “ማኅበረሰባችን እንዲህ ነው” ብሎ ለመደምደም ባያስችሉ እንኳን፣ ማኅበረሰባችን ሙስናንና ሙሰኛን በተመለከተ ያለውን አቋም የሚጠቁሙ ይመስለኛል፡፡ ለጥናት መነሻም ሊሆን ይችላል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ የታዘብኳቸውን ነገሮች በየፈርጃቸው ላስቀምጥ፡፡
ለመሆኑ ማኅበረሰባችን ስኬትን የሚለካው በምንድነው?
ስኬት (Success) ማለት ይኼ ነው ብሎ ሁሉን የሚያስማማ ትርጉም ማምጣት አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክያቱም ስኬት አንፃራዊና ግለሰባዊ ነው፡፡ ስኬታማነታችን የሚለካውም ካስቀመጥነው ግብ አንፃር እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ አንዱ ለአረጋውያን መጠለያ የሚሰጥ ግብረ ሰናይ ድርጅት አቋቁሞ በአረጋውያን ስም በሚያገኘው ዕርዳታና ድጋፍ ለራሱ የተንጣለለ ቪላ ገንብቶ፣ እጅግ የዘመነ መኪና እየነዳ ራሱን ካላገኘ ስኬታማ አይደለሁም ብሎ ሊያስብ ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ ለረዥም ዘመን ለፍቶ የገነባውን ቪላ ቤት ለአረጋውያን መጠለያ እንዲሆን በስጦታ ካልሰጠ ስኬታማ ሕይወት የለኝም ብሎ ሊያስብ ይችላል፡፡ አንዱ መርካቶ መሀል አንድ መደብ እንኳን ሳይከራይ፣ አንድ ሠራተኛ እንኳን ሳይቀጥር፣ በሚሊዮኖች የሚያወጡ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በኮንትሮባንድ አስገብቶ አየር በአየር ሸጦ ቅንጣቷን እንኳን ግብርና ታክስ ሳይከፍል ሀብት አካብቶ ዘመናዊ ሆቴል ካልገነባ፣ ስኬታማ አይደለሁም ብሎ ሊያስብ ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ ለምኖ በሚያገኘው ገንዘብ ውኃና ሳሙና እየገዛ አረጋውያንንና የአዕምሮ ሕሙማንን እዛው መርካቶ መሀል አስፋልት ላይ ገላቸውን እያጠበና ፀጉራቸውን እየላጨ ጤናቸውን ካልጠበቀ፣ ስኬታማ አይደለሁም ብሎ ሊያስብ ይችላል፡፡ መሰል የስኬት መለኪያዎችንም ዘወትር ስንሰማ እንውላለን፡፡
የእኔን ገጠመኝ መሠረት አድርጌ ስመለከት ግን የስኬት መለኪያችን በአብዛኛው ሀብት ማካበት ሆኗል፡፡ በብዛት መለኪያ አንድ ሰው የሚፈልገውን ነገር ለመግዛት ያለጭንቀት ወደ ኪሱ መግባት ከቻለ፣ ቢያንስ የግሉ ቤትና መኪና ካለው፣ ልጆቹን ውድ ትምህርት ቤት ካስተማረና የማይቋረጥ የገቢ ምንጭ መገንባት ከቻለ በቃ ይኼ ሰው ስኬታማ ነው፡፡ በዚህ መነሻነት ነው ብዙዎች፣ “በዚህ ዘመን በቀላሉ ሀብት ማግኘት አይቻልም፡፡ ሠርቼ ያልፍልኛል ብትል ሞኝነት ነው…” እያሉ የሥራ ኃላፊነቴን መሠረት አድርጌ ሕገወጥ ገቢ እንዳገኝ ይወተውቱኝ የነበረው፡፡ እንዲያውም አንድ ወቅት አንድ ሰው የሚከተለውን የሚመስል የክርክር ሐሳብ አቅርቦ ሲሞግተኝ ነበር፡፡ “ቆይ አንተ ከዚህ በኋላ አሥር ዓመት በዳኝነት ብትሠራ በደመወዝህ ስንት ብር ትቆጥባለህ? በቀጣይ ዓመታት ውስጥ ‘ራስህን ትዳር ይዘህ፣ ልጆች ወልደህ … አስበውና ይቺን የምትቆጥባትን ገንዘብ ምን ምን ልታደርጋት ነው? ቤት መግዛት ይቅርና የአንድ ወር ደመወዝህ ቢቋረጥ የቤት ኪራይ መክፈል ትችላለህ ወይ? እንዲያው ከደመወዝህ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ጥብቅና ፈቃድ አውጥተህ ሥራ ብትጀምር እንኳን፣ ሌላው ቀርቶ መኪና ለመግዛት እንኳ ምን ያህል ዓመት መሥራት ይገባሃል? ነገር ግን አንተ ከአንድ ጉዳይ በምትቀበለው ጉቦ ብቻ መኪና መግዛት ከቻልክ የአንተ ሀቀኝነት ምን የሚሉት ነው?”
መሰል ሐሳቦችን አንድ መቶ ሺሒ ጊዜ ሰምቻቸዋለሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ፣ አሁን የደረሰበት የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ እንዴት እንደ ደረሰ ልቦናዬ እንደሚያውቅ የሚያውቅ አንድ ወዳጄ የምመራው ሕይወት ምን ያህል ስኬት አልባ እንደሆነ በሚያስፀይፍ አኳኋን እየነገረኝና ሊያስቆጨኝ እየጣረ “ንቃ!!! ከልክህ በታች አትኑር!!!” ብሎ ሊገስፀኝ ሞክሯል፡፡ ከዚህ የቅርብ “ወዳጄ” ጋር የነበረን ግንኙነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተቋጨው በዚህች ዕለት ነበር፡፡ መልሱን መስማት ሳያስፈልገኝ “ስኬት የሚለውን ቃል እንዴት ነው የምትረዳው?” ብዬ ባቀረብኩለት ጥያቄዬ ንግግራችን ተቋጨ፡፡
እናም የእኔ ትዝብት ስኬትን የምንረዳበትና የምንለካበት መንገድ በመንሸዋረሩ ሙስናን እናወግዛለን፣ በዚህ መለኪያ “ስኬታማ” ለመሆን ቀላሉን መንገድ የተከተለውን ሙሰኛ ግን አንኮንንም፡፡ ሌላ ሕጋዊ የገንዘብ ምንጭ ሳይኖረው ከደመወዙ በላይ የሚኖርን፣ ከ’ርሱም አልፎ ለቤተሰቡና ለሌሎች ቤት የሚገዛ፣ መተዳደሪያ ንግድ ቤት የሚከፍትን፣ ወላጆቹን ውጭ አገር ልኮ የሚያሳክምን … አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ተlሚ አብዛኛው የማኅበረሰባችን ክፍል ምን ብሎ ነው የሚገልጸው? “ወላጆቹንና ቤተሰቡን አሳለፈላቸው!!! ሕይወታቸውን ቀየረው!!!” ነው የምንለው? ወይስ “በሕገወጥ ድርጊት ወላጆቹን አዋረዳቸው!!! ከሕዝብ በመዘበረው ሀብትም ለቤተሰቡ ቤት ሠራ!!!” ነው የምንለው? በሙስና ከፍተኛ ሀብት ማግኘት በሚቻልበት የሥራ ድርሻ የሚሠራን ሠራተኛ “ደኅና ቦታ”፣ “ዝግ የሚዘጋበት ቦታ”፣ “ቢዝነስ ያለበት ቦታ”፣ ወዘተ እያለ የሚጠራው እኛ ማኅበረሰብ አይደለምን? ለመሆኑ ምን ያህሉ የማኅበረሰባችን ክፍል ነው ሙያዊ ክብርንና ሕግን፣ እንዲሁም ሥነ ምግባራዊም ሆነ ሃይማኖታዊ መርሆዎችን ተከትሎ ሥራውን ማከናወን የቻለን ሠራተኛ ስኬታማ ነው ብሎ የሚያስበው?
ለመሆኑ ሙስናን እንደ ጉርሻ (ቲፕ) መቁጠር ይቻላልን?
ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ሙሰኛ እንድሆን የሙስናን ቅቡልነት ለማሳየት የሚሞክሩ የተለያዩ ሰዎችን የክርክር ሐሳቦችን ስሰማ ከርሜያለሁኝ፡፡ አንዱ ሐሳብ ሙስናን እንደ ጉርሻ (ቲፕ) ወይም ለሰጠሁት አገልግሎት የሚከፈል የምሥጋና ክፍያ ለመቁጠር የሚሰነዘረው ሐሳብ ነው፡፡ ብዙዎች ይኼንን ሐሳብ የሚሰነዝሩልኝ “በሙስና አማካይነት የተጣመመ ፍትሕን መስጠት አግባብ ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ ስሰነዝርባቸው ነው፡፡ የዚህ ሐሳብ ሰንዛሪዎች የተጣመመ ፍትሕ መስጠት የለብህም የሚለውን ሐሳብ ይቀበሉ፡፡ ነገር ግን፣ “ከሁለት ተከራካሪዎች መካከል ሀቁን ለያዘውና ጉቦ ሰጠም አልሰጠም ከምትፈርድለት ሰው ብር መቀበል ሙስና ሊሰኝ አይችልም፡፡ መብቱን በገንዘብ ልግዛ ብሎ ጉቦ ልስጥ ከሚል ሰው ብር መቀበል ሙስና ሊባል አይችልም፡፡ ይልቁንም ይኼ ተገልጋዩ ትክክለኛ ፍትሕ ስለሰጠኸው የሚሰጠህ ጉርሻ ነው፤” የሚል ሐሳብን ያስከትላሉ፡፡ ለሐሳባቸው ድጋፍ ይሰጥ ይመስልም፣ “እነ እከሌ እኮ ገንዘብ ከመቀበላቸው በፊት መዝገቡን መርምረው ለማን እንደሚወስኑ ካረጋገጡ በኋላ ነው የሚከፈላቸውን ገንዘብ የሚደራደሩት፡፡ ለዚህም ነው ስማቸው በሙስና የማይነሳው፤” የሚል ማስረጃን ለመጥቀስም ይሞክራሉ፡፡
ይኼንን ሐሳብ የሚያራምዱ ሰዎችም ጥቂት አይደሉም፡፡ ተመሳሳይ አቋም የማይባቸው ሰዎች በዕድሜ የገፉ ወይም ሞራላዊ ብቃታቸው ሙስናን በምንም መንገድ ቢሆን ከሚደግፉት ሰዎች በመጠኑ “የተሻለ” ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ፣ ቀደም ብለው በሥራ ላይ ሳሉ ሙስናን በፍፁም ይቃወሙ እንደነበረ የማውቃቸውና ወደ ጥብቅና ሥራ ከገቡ በኋላ የአቋም ለውጥ ያደረጉ ሰዎች ይኼንን ሐሳብ ሲያራምዱ ማየት ጀምሬያለሁኝ፡፡ ሙስናን እንደ ጉርሻ (ቲፕ) መመልከቱ ለእኔ የሚሰጠኝ ስሜት ለሙስና የዳቦ ስም ከመስጠት አይለይም፡፡ በየትኛውም ዕይታ ይዩት ይኼንን ሐሳብ የሚያራምዱት ሰዎችም ጥቂት የሚባሉ አለመሆናቸው፣ አሁንም ማኅበረሰባችን ሙሰኛን ስለመጠየፉ እንድጠራጠር ያደርገኛል፡፡
“ከግለሰብ አትንካ ከመንግሥት ካዝና ግን ‘ድርሻህን ውሰድ’!!!”
በፍርድ ቤት ተከራካሪ የሆኑ ግለሰቦች ሲሆኑና አንደኛው ወገን ተከራካሪ መንግሥት ሲሆን፣ ሙስና በሁለት መነጽር የምትታይ መሆኗን መስማት የጀመርኩት የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በነበርኩበት ወቅት ነበር፡፡ የዚህ ሐሳብ ማጠንጠኛ በአንድ በኩል “በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙት ሰዎች የተጠረጠሩበት ምክንያት በግለሰብ ላይ ፈጸሙ በተባሉት ወንጀል ምክንያት ከሆነ፣ ጉቦ መቀበል ተጎጂውን ስለሚበድል ተገቢነት የለውም፤” የሚል ሐሳብ ነው፡፡ ሌላኛው ጎን ሐሳብ ደግሞ፣ “በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙት ሰዎች የተጠረጠሩበት ምክንያት በመንግሥት ሥራ ጥቅም ላይ ፈጸሙ በተባሉት ወንጀል ምክንያት ከሆነ፣ ጉቦ መቀበል የሚጎዳው ግለሰብ ስለሌለ ተገቢነት አለው፤” የሚል ነው፡፡ ጀማሪ ዓቃቤ ሕግ በነበርኩበት ጊዜ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት ብዙ ንብረት አጉድለዋል ተብለው በተጠረጠሩ ሠራተኞች ላይ የተደረገ የወንጀል ምርመራ መዝገብ ውሳኔ እንደሰጥበት ቀርቦልኝ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ነው በምሰጠው ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥርብኝ ከፈለገ አንድ ሰው ይችን የሐሳብ መስመር ለመጀመርያ ጊዜ የሰማኋት፡፡
ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው ሰዎች እልፍ መሆናቸውን የተረዳሁት ግን በገቢዎችና ጉምሩክ ችሎት በዳኝነት በሠራሁበት ዓመት ነው፡፡ በዚህ ችሎት የሚቀርቡ ተከሳሾች በዋነኝነት ለመንግሥት ተገቢውን ግብር ወይም ቀረጥ አልከፈሉም፣ መሰብሰብ የነበረባቸውን የተጨማሪ እሴት ታክስ አልሰበሰቡም፣ አልያም ሊጠቀሙበት ይገባ የነበረውን የሽያጭ መሰብሰቢያ ማሽን ሳይጠቀሙ ሽያጭ አከናውነዋል ተብለው የተከሰሱ ሰዎች ናቸው፡፡ እናም የተሰጠኝን ኃላፊነት ያላግባብ ተጠቅሜ እነዚህ ሰዎች የሚቀጡትን ቅጣት በማሳነስ፣ በነፃ በመልቀቅ አልያም ቅጣታቸውን በመገደብ ከተከሳሾቹ ገንዘብ ብቀበል ሙሰኛ እንደማልባል ብዙዎች ደጋግመው ሊያሳምኑኝ ጥረዋል፡፡
በንግድ ሥራ የሚተዳደር ወዳጄ ይኼንን ማድረግ “ድርሻዬን መውሰድ” እንደሆነ ሊያግባባኝ የሞከረው መርካቶ መሀል በነበርንበት ወቅት ዙሪያዬን እያመላከተኝ በጠየቀኝ የሚከተሉት ጥያቄዎች ነበር፡፡ “እስቲ አንተ ከዚህ ሠፈር ተይዞ አንተ ችሎት (የገቢዎችና ጉምሩክ ችሎት) የቀረበ አንድ ነጋዴ ታውቃለህ? የዚህ ሠፈር ነጋዴ ሁሉ ሀቀኛ ግብር ከፋይ ስለሆነ ይመስልሃል አንተ ችሎት የማይቀርበው? የአንተ ቅጣት የኢትዮጵያን የግብር ሥርዓት የሚቀይር ይመስልሃል?” ለዚህ ወዳጄም ሆነ ለብዙዎች ሙሰኝነት እንደ ሁኔታው ቅቡልነት ሊኖረው የሚችል ቅዱስ ተግባር ነው፡፡ ተቀራራቢ ሐሳብ ካቀረበልኝ በኋላ፣ “ለመንግሥት ገንዘብ እንዲከፈል ብትፈርድ የትኛው መንገድ የሚሠራበት ይመስልሃል? ይልቅም “ድርሻህን” ለሌላ በይ (ሙሰኛ) ነው አሳልፈህ የምትሰጠው፤” ያለኝ ሰውም ነበር፡፡ በእኔ ዕይታ የዚህ ሰው ንግግርም ሆነ ከመደጋገሙ የተነሳ የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል መርህ እየመሰለኝ የመጣው፣ “ድርሻህን ውሰድ” የሚለው አለመካከት ስፋት የዋዛ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው፣ “በእርግጥ ማኅበረሰባችን የሚጠላው ሙስናን ነው ¨ወይስ ሙሰኛን?” ብዬ ደጋግሜ እንድጠይቅ የሚያደርገኝ፡፡
እነዚህን ሁሉ ሐሳቦች የምሰነዝረው ስለራስ ማውራት ጥዩፍ በሚመስልበት ባህላችን መካከል ቆሜ የእኔን ገድል ለመተንተን አይደለም፡፡ ይልቅም የእኔን ጥያቄ እንድትጋሩኝ ነው፡፡ ይልቅም እንደ ማኅበረሰብም ሆነ እንደ አገር ራሳችንን እንድንመረምርበት፣ እንድንመለከትበትና እንድንፈትሽበት ነው፡፡ “ሁለት ስህተቶች ሲፈጸሙ አንዱን ትክክል አያደርጉትም፤” የሚባል አባባል አለ፡፡
“ሙስናን እንደ ጉርሻ”፣ “ከመንግሥት መዝረፍን ድርሻን እንደ መውሰድ”፣ ወዘተ እየተመለከትን መጓዛችንን ከቀጠልን ጀሶ አቡክተው ጋግረው የሚያበሉን ነጋዴዎች፣ የትምህርት ቤታቸው ስም እንዲወደስ የቀጠሯቸው መምህራን ለተማሪዎቻቸው ያለፉበትን ከፍተኛ ውጤት እንዲያድሉ በብርቱ የሚያስጠነቅቁ ባለሀብቶችን፣ የመጠቀሚያ ጊዜው ባለፈበት መድኃኒት የሚያክሙንን ዶክተሮች፣ ጀሶ፣ አፈር፣ መናኛ አሸዋና የጆንያ ቁርጥራጭ ቀላቅሎ በሞላው ኮንክሪት ላይ ፎቅ ቤት ገንብቶ ‘እንሆ መኖሪያ ቤትዎ’ የሚለንን ሥራ ተቋራጭ፣ የስድስት ዓመት ሴት ልጃችንን የደፈራትን ተከሳሽ ነፃ ለመልቀቅ ግሮሰሪ ውስጥ የሚደራደር ዳኛን፣ ወዘተ እያመረትን የተዛባና ሕሙም ማኅበረሰብ ለመገንባት ምቹ መደላድልን ከመፍጠር የሚገታን አይኖርም፡፡ ማኅበረሰባችን ስኬትን የሚለካበት መንገድ የሀብት መጠንን በመመዘን ከሆነና ‹የትም ፍጪው› በሚል ብሂል ከተጓዝን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር፣ በክፋትና በመመዘባበር መክሰማችን አይቀርም፡፡ ስለሆነም ሙስናን ብቻ ሳይሆን ሙሰኞችንም እንፀየፍ፡፡ ሙስናን በየትኛውም ዕይታ ቢሆን እናውግዘው፡፡
ትዝብቴን እዚህ ላይ አበቃሁ። የምንደማመጥ፣ ሐሳብን በሌላ ሐሳብ ብቻ የምንዋጋ፣ ከግል ክብርና ጥቅም በላይ ለአገራችን ቅድሚያ የምንሰጥ የአንድ አገር ሕዝቦች ያድርገን። ብሩሃን ቀናት ከፊታችን ይቅደሙ። ሰላም።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን (LL.B LL.M MSW) አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው danahai81@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
