Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

የዳበረ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ዳር ድንበር አይደለም

$
0
0

 

በጌታቸው አስፋው

ይኼን ጽሑፍ ያቀረብኩት ረቡዕ ሐምሌ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ዕትም ‹‹የፖለቲካም የኢኮኖሚም ዳር ድንበር ግለ ነፃነት ብቻ ሳይሆን የዳበረ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ጭምር ነው›› የሚል ርዕስ ለወጣ ጽሑፍ ማብራሪያ ለመስጠት ነው፡፡ እኔም እንደ እርስዎ መቃቃር ሊፈጥሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን ላፍታታልዎትና በቀቀን የምትባለዋ ወፍም የሰማችውን መናገር ትችላለች፡፡ ኢኮኖሚስቶች ሰዎችን ወደ የራስ አስተሳሰብና አመለካከት አንዲገቡ ለማበረታታት በየስብሰባው የሰማኸውን ሳይሆን፣ ያወቅከውን ግለጽ በማለት የሚናገሩት የቆየ ንግግር ለእኔ የተሰነዘረ ነው ብለው ሥጋት አይግባዎ፡፡

በጆርናል ለመጻፍ አቅሙና ፍላጎቱ ካላቸው ላሉት ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ መጽሐፍትን ሳጥን ውስጥ የከተትኩ ሳልሆን፣ አንባቢ ስለሆንኩኝ አቅሙ አለኝ፡፡ በፍላጎት ረገድ ግን እኔኑ ለሚመስል ባለሙያ የሚያውቀውን መልሼ ከመንገር ለማያውቀው በቀላል ቋንቋና በሚገባው መንገድ መጻፍን ስለመረጥኩ ነው በጋዜጣ የምጽፈው፡፡

እንደ ሕክምናና ምህንድስና የመሳሰሉ ሙያዎች ባለሙያዎቹ በጆርናል ላይ ሳይንሳዊ ጽሑፍ ቢጽፉ፣ በሙያ ማኅበራት ስብሰባዎች ሳይንሳዊ ጥናቶችን ቢያቀርቡና ሙያቸውን በውስጣቸው ቢያበለጽጉ ሊበቃቸው ይችላል፡፡ እነዚህ ሙያዎች ከባለሙያ ወደ ሕዝብ በቀላሉ የሚሸጋገሩ ሳይሆኑ፣ ባለሙያው ራሱ አገልግሎት ሰጥቶ ሰውን የሚጠቅምባቸው ሙያዎች ናቸው፡፡ የተፈጥሮ ሳይንስ ባለሙያዎች አገሪቱን በመገንባት ትልቅ ሥራ እየሠሩ እንደሆነ አድናቆቴ የዘወትር ነው፡፡ የእኔ ሙያ ኢኮኖሚክስና የእርስዎ ሙያ የፖለቲካ ሳይንስ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ የሕዝብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ስለሆነ በቀላል ቋንቋ ከባለሙያ ወደ ሕዝብ ቢሸጋገር የበለጠ ጥቅም የሚሰጥ ነው፡፡ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን መንግሥት በሕዝብ ስለሚመረጥ ጉልበተኛ አይደለም በማለት፣ ለእርስዎም ሆነ ለሌሎች ተሳታፊ በመሆን ሐሳባችሁን እንድትገልጹ ዴሞክራሲን ሰጥተናችኋል በሚል ቅላፄ ከዚህ በፊት የተባለውን ደግመው በመናገርዎ ውስጥዎን አስፈተሹኝ እንጂ፣ ለእኔ በኃይልም ይምጣ በምርጫም ይቀመጥ ጠመንጃ ያነገበ ከኋላው ያሠለፈ ሁሉ ያጠፋውንም ሆነ ያላጠፋውን መቅጣት የሚችል ጉልበተኛ ነው፡፡

ወደ ዋናው ውይይታችን ስገባ በመጀመርያ ደረጃ በአርዕስቱ ላይ ጭምር እንጂ ብቻ አይደለም በማለት በመሸሽ መከራከርዎ፣ በሕግ ቋንቋ እንደ መሸነፍ ተቆጥሮ  መከራከሪያው ውድቅ ይደረጋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት መፍጠር ገና የጅማሮ ዳር ድንበር እንጂ የፍፃሜ ዳር ድንበር አይደለም፡፡

ሥርዓት ከመፍጠር በኋላ ሥርዓቱን የሚጠብቁና የሚቆጣጠሩ ተቋማት መፍጠር፣ የአመራረት አደረጃጀት መፍጠር፣ ምርት ማምረት፣ የተመረተውን ገበያ አውጥቶ መሸጥ፣ የተሸጠው በምግብ፣ በልብስ፣ በመጠለያና በሌሎች ፍጆታዎች መልክ ተጠቃሚው ግለሰብ ዘንድ ደርሶ የግለሰብን አቅምና በራስ የመተማመን ችሎታ ሲገነባ ነው የፍፃሜ ዳር ድንበር ላይ ተደረሰ የሚባለው፡፡

የልማትን ትርጉም ጉናር ሚርዳልን ከመሳሰሉት ቀደምት የልማት ኢኮኖሚስቶችና የዘመናችን የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ከሆኑት አማርተያ ሴን ይመልከቱ፡፡ የልማት መደምደሚያው ለማንም ሳያጎበድድ የግለሰብ በራስ መተማመን አቅምና ነፃነት መገንባት ነው፣ አራት ነጥብ፡፡

ስለ ውጤት የሚሰጡት ትንታኔም የተሟላ አይደለም፡፡ የሳንቲሙን አንድ ገጽታ ብቻ ነው የሚያዩት፡፡ ግለሰቦች የሀብታቸውን መጠን ሲለኩ የሚይዙትን የሒሳብ መዝገብ አያያዝ ተመልክተው ከሆነ ወደ ድምዳሜ ላይ ሳይደርሱ ሀብታቸውንና ዕዳቸውን (Two Sides of The Balance Sheet) ያነፃፅራሉ፡፡ እርስዎ ሀብትን ብቻ ዓይተው ዕዳ የሚያየውን ዓይን ሸፍነዋል፡፡ 

 

ዋዜማ ድራማን ተመልክተዋል? ካልሆነም የሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሾችን ያነጋግሩ፡፡ እኔና እርስዎ ደልቶን ስንኖር የስንቱ ስደተኛ እጅና እግር ተቆርጧል፡፡ የስንቱ ዓይን ጠፍቷል፡፡ የስንቱ ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ የመቶ ሚሊዮን ሰዎች አሻራ አርፎበት ወደ ውጭ ልከን ከምናገኘው ሦስት ቢሊዮን ዶላር ያልሞላ የኤክስፖርት ገቢ እነዚህ ከርታታ ስደተኞች ተንከራተው የሚልኩልን አራት ቢሊዮን ዶላር እንደሚበልጥ አያውቁም ብዬ አልገምትም፡፡ ሦስት ቢሊዮን ያልሞላውንም የምናገኘው ሕፃናት አልሚ ምግብ አጥተው እየቀነጨሩ ጥራጥሬ፣ የታረደ ሥጋና የቁም ከብቶቻችንን ሸጠን ነው፡፡

የኢሕአዴግ ዘመንን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ በአጭሩ አስቀምጥ ካሉኝ፣ የዋጋ ንረት ግብር (Inflationary Taxing) ዕድገት ታሪክ ነው ብዬ በአጭሩ አስቀምጠዋታለሁ፡፡ ጽንሰ ሐሳቡን ጉግል አድርገው ይመልከቱ፡፡ እኔም በአጭሩ አብራራዋለሁ፡፡

ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ በደንብ የሚያውቋቸው አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች ይኼን የዋጋ ንረት ግብር ደብቀው መደበኛው ግብር ከጥቅል የአገር ውስጥ ምርት አሥራ ሦስት በመቶ ብቻ ስለሆነ፣ የአፍሪካ አማካይን አሥራ ስድስት በመቶ ገና አልደረስንም በማለት ደሃውን የባሰ የቁም ስቃይ ውስጥ ለመክተት ሲሯሯጡ ቢታዩም ሁኔታው ግን ሌላ ነው፡፡

የሆቴል የሽሮ ወጥ ዋጋ ከአሥራ አምስት ሳንቲም ወደ አርባ ብር በመግባቱ፣ ከቀድሞው የምግቡ ዋጋ በተጨማሪ ሰላሳ ዘጠኝ ብር ከሰማንያ አምስት ሳንቲም ለመንግሥትና ለሀብታም የዋጋ ንረት ግብር ገብረው የአዲስ አበባን  ሕንፃዎችና መንገዶች የገነቡት፣ ለሀብታሙ መኪናና የቅንጦት ሸቀጦች የገዙት የአሥራ አምስት ሳንቲሟን ሽሮወጥ በአርባ ብር ሸምቶ ለመመገብ ሌት ተቀን የሚኳትኑት ድሆች ናቸው፡፡ የደሃውን አጥንት ግጦ ሕንፃ መሥራት ለእርስዎ ፍትሐዊ ዕድገት ነው፣ ለእኔ አይደለም፡፡ ኢኮኖሚውን ያሳደገው ጥሩ ፖሊሲ ተነድፎለት አይደለም፡፡ ችግር የመፍትሔ እናት በመሆኑ ነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያደገውና የተስፋፋው፡፡

ውጤትን ከምክንያት ጋር አዛምደው እንዲነግሩኝ ልጠይቅዎትና ዛሬ በሥራ ፈጠራ ስም በየበረንዳው የምናየው የጀበና ቡና ማፍላት፣ ዛሬ በየመንገዱ ወጣቶች ላንቃቸው እስከሚሰነጠቅ እየጮሁ ቅራቅንቦና ልባሽ ጨርቅ የሚሸጡበት ዛሬ በየጉልቱ በደንብ አስከባሪዎች እየተቀጠቀጡ ሽንኩርትና ድንች የሚሸጡት፣ የጥሩ ፖሊሲ ውጤቶች ይመስልዎታል? በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በረሃና ባህር አቋርጠው የሚሰደዱት ከድህነት ኑሮ ይሻላል ብለው እንደሆነ ግልጽ አይደለም እንዴ? ኢኮኖሚክስን ለማያውቁ የልማት ካድሬዎች ዛሬን በረሃብ ካልሞቱ ለነገ አይታደግም፡፡ ኢኮኖሚስቶች ግን ዛሬ ሳይሞት ነገ ማደግ ይቻላል ይላሉ፡፡

እኛን የተጠናወተን የዳበረ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር አስፈላጊነትን ማመንና አለማመን ሳይሆን፣ ከእኔ በላይ ሊፈጥረው የሚችል ማንም የለም በማለት የሚነሳው ሽኩቻ ነው፡፡ የአባቶች አባባሎች ብዙ ነገሮችን ያስተምሩናል፡፡ ‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል›› ይላሉ፡፡ የሰዎች ፀብ እንጀራውን በመፈለግ ላይ አይደለም፡፡ ሰዎች የሚጣሉት ምጣዱ እኔ ብቻ ነኝ በሚለው ላይ ነው፡፡ የእኔና የእርስዎ ክርክርም ምጣዱ የማን ነው? እንዴት እሱ ሊሆን ቻለ? በሚለው ላይ ነው፡፡ ጥቂቶች ጋግረው ብዙውን መቀለብ ይችላሉ? ወይስ እያንዳንዱ ራሱን እንዲቀልብ ሁኔታዎች ሊመቻቹለት ይገባል? የሚሉት ናቸው፡፡ አንቀሳቃሽ ሞተሩ የግሉ ኢኮኖሚ ነው? ወይስ መንግሥት? በሚለው ላይ ነው፡፡

በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ ሁለቱ ጫፎች አንዱ የአዳም ስሚዝ ከገበያው ሥውር እጅ የተሻለ ሀብት አከፋፋይ የለም ሲል፣ ሁለተኛው የካርል ማርክስ ወደ ኮሙዩኒዝም የሚወስደው የሕዝብ ሀብት በመንግሥት ይዞታ ሥር ማዋል ሲሆኑ፣ በዓለም ያሉ አገሮች ሁሉ ልማታዊ መንግሥታትም ኒዮ ሊበራሎችም በእነዚህ ሁለት ጽንፎች መካከል ነው ያሉት፡፡ የኢኮኖሚ ጠበብትም ሆኑ ሕዝቦች እንደ አገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ የመንግሥቱ በዛ የግሉ በዛ፣ በሚል ነው እንጂ የሚከራከሩት ሶሻሊዝም ከተሸነፈ ወዲህ ወደ ጽንፉ ለመሄድ የተፈጠረ ክርክርና ትግል የለም፡፡

በልማታዊ መንግሥት አመለካከትም በኒዮ ሊበራሊዝም አመለካከትም ያደጉ አገሮች አሉ፡፡ የሌሎችን ተሞክሮ እንደ ትምህርት ወስደን የራሳችንን ተጨባጭ ሁኔታ ከመተንተን ይልቅ፣ ‹‹እንቁራሪት በሬን አክላለሁ ብላ…›› እንደሚባለው ይኼው ልንፈነዳ ደርሰናል፡፡

በ2008 እና በ2009 ዓ.ም. ኦሮሚያንና አማራን ያናወጠውን ማዕበል ከዚህም ከዚያም የሚፈጠሩ ችግሮች፣ ሥርዓቱ እስካሁን ካስገኘውና ወደፊትም ከሚያስገኘው ጠቀሜታ ሊወዳደሩ አይችሉም ብሎ መደምደም ይቻል ይመስልዎታል?

የኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ባወጣው ዘገባ በኦሮሚያ ብቻ በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ሰው የሥራ አጡን ቁጥር ይቀላቀላል፡፡ ሰሞኑን በጋዜጣ በወጣ ዘገባ መሠረት ከሁለተኛ ደረጃ ከቴክኒክና ሙያና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የሥራ አጡን ቁጥር ይቀላቀላሉ፡፡ የሥራ ዕድል ያልፈጠረ የኢኮኖሚ ዕድገት ‹ዕድገት› አይባልም፡፡ የጆን ሜናርድ ኬንስን የብሔራዊ ኢኮኖሚ ትንታኔ ይመልከቱ፡፡ የሥራ አጥ ቁጥር ሊቀንስ የሚችለውም በሥራ አጥ ቅነሳ ጽንሰ ሐሳብ ላይ ተመርኩዞ እንጂ፣ የጥቃቅንና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አምስት ሺሕ አሥር ሺሕ ሥራ ፈጠራ በመቁጠር አይደለም፡፡

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ እስከ ዛሬ በኢኮኖሚክስ ሙያ እኩያ ያልተፈጠረለት የብሔራዊ ኢኮኖሚ ኢኮኖሚስት ኬንስ፣ መምህራኖቹ አልፍሬድ ማርሻልና አርተር ፒጎ የግል ገበያ ኢኮኖሚ አቀንቃኝ ኒዮ ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ነበሩ፡፡ የእነርሱን የግል ገበያ ኢኮኖሚ ትንታኔ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ትንታኔ ቀልብሶ በጭንቅላቱ የነበረውን በእግሩ አቆመው፡፡ የተነተነው የብሔራዊ ኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብም ሥራ አጥነትን ስለመቀነስ ነው

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ችግር ለመቅረፍ አስተማሪዎቻችንንም ቢሆን መድፈር ነው እንጂ ያለብን፣ እነ እከሌን እዩዋቸው እያልን ዕድሜ ልካችንን የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮችን ስም ማንሳት አይጠቅመንም፡፡

ካደረግናቸው ሁለት መጻጻፎች እንደተረዳሁት እርስዎ ቢሆን ኖሮ በሚል ያምናሉ? እኔ ቢሆን ኖሮ በሚል መላምት ኑሮ አይመሠረትም፣ አገር አይገነባም እላለሁ፡፡ የተሟሸ ምጣድ ካለን እሰየው ነው፡፡ የሚያጠግብ እንጀራ እንበላለን፡፡ ምጣዳችን ያልተሟሸ ከሆነ ግን ሌላ ምጣድ ማሟሸት አለብን፡፡ ቢሆን ኖሮ ከሚሏቸው አንዳንዶቹን ልጥቀስልዎት

በሥነ ምግባርና በሥነ ዜጋ ላይ ከቤተሰብ ጀምሮ በትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም በተለያዩ የማኅበረሰቡ አደረጃጀቶች አማካይነት የተስተካከለ ሰብዕና ያለው ትውልድ ቢፈጠር ይላሉ፡፡ ምክርዎ ጥሩ ነበር፡፡ ግን ልጆች የሚያዩት አባት የሚናገረውን ሳይሆን አባት የሚሠራውን ነው፡፡ አስተማሪ የሚናገረውን ሳይሆን አስተማሪ የሚሠራውን ነው፡፡ ኅብረተሰቡ የሚናገረውን ሳይሆን ኅብረተሰቡ የሚሠራውን ነው፡፡

‹‹ልማታዊ መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ባለው ረዥም እጅ ምክንያት ለሙስና ተጋላጭነቱ የሰፋ ይሆናል የሚል አስተሳሰብ ያለ ቢሆንም…›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹የልማታዊ መንግሥት ባህሪያትን በእርግጥም በትክክል አሟልቶ ከተንቀሳቀሰና ዴሞክራሲያዊ ከሆነ የሙስና ተግባራትን የመቋቃም አቅሙ ከፍ ያለ ይሆናል፣ ኅብረተሰቡ በየደረጃው በሁሉም ተግባራት የሚሳተፍበት ሁኔታ ስለሚፈጠር ሙስናን አሸንፎ የዳበረ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚፈጠርበት አቅጣጫ ተከትሎ መሄድ ይቻላል ብዬ አስባለሁ፣ በብሔር ብሔረሰብ ሽፋን የተሸጎጡ ሙሰኞችም በዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ አግባብና በብሔሩ ሰፊ ሕዝብ ሙሉ ተሳትፎ እየተወገዱ የሚሄዱበትን አግባብ መፍጠር ይቻላል፡፡ ሙሰኝነትና ያላግባብ የመጠቀም ፍላጎት ለብሔሩ የራስ አስተዳደርም ሆነ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በጋራ የመልማትና በፌዴራላዊና በዴሞክራሲያዊ አግባብ አብሮ መኖር ከፍተኛ መሰናክል መሆኑ ግልጽ ነው፤›› ይላሉ፡፡  በቢሆን ኖሮና ቢሆን ይቻል ነበር የተሞላ ሐሳብ ነው፡፡ ዛሬን የማያይ የነገን የሚመኝ አመለካከት ነው፡፡

ሙግታችን ሌላ መልክ እንዳይዝ የእኔ ሙግት አጭር ሐሳብ፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የልማት ኢኮኖሚና የገበያ ኢኮኖሚ አልተመጣጠኑም፡፡ ይህም ለብሔር ፌዴራላዊ መንግሥት ሥርዓትና ለአገሪቱ ህልውና ጠንቅ ነው፡፡ ወይም በግልባጩ የብሔር ፌዴራሊዝም ልማታዊ አስተዳደር ውድድራዊ የገበያ ተሳትፎን ያጠባል ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ነው ወይም አይደለም ብለን ከምንሰማውና ከምናነበው የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ሳይሆን፣ ከምናየው የእኛው ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተን እንነጋገር ነው፡፡

ጥናት ስላልተደረገ በመረጃ ልናስደግፍ አንችልም፡፡ ነገር ግን የመቶ ሚሊዮን ሰዎች ዓይን ከመረጃም ይበልጣልና በዓይን ከሚታየው ለአንድ አገር  ሰዎች አብሮ ተፋቅሮ መኖር መሠረት ከሆኑት በትዳር፣ በማኅበራዊ ኑሮ፣ በግብይይት መተሳሰር ባለፉት ዓመታት ከነበርንበት አገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ጠበናል ነው፡፡ ለዚህ አዎን ወይም አይደለም መልስ ለመስጠትና ለመልሱ ማስረጃ ለማቅረብ ወደ ደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ምን አስኬደን? ወደ ሙያ አቅም ፍተሻ በጆርናል የምርምር ጽሑፍ ማቅረብ ምን አስገባን? ‹አባትህን ጥራ ሲሉት አጎቴ እከሌ ነው…› እንዳለው ልጅ፣ የራሳችንን ትተን የደቡብ ምሥራቅ አገሮችን እየጠራን አንኑር፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡  

 

 

 

 

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles