በዳንኤል አረጋዊ ኃይሉ
ዘወትር በተሽከርካሪ ፍሰት በሚጨናነቅ አንድ መንገድ ዳር በዛ ካሉ ተሳፋሪዎች ጋር ተቀላቅዬ ታክሲ እጠብቃለሁ። የነዳጅ እጥረት የነበረበት ወቅት ስለነበር በመንገድ ላይ የሚታዩት ጥቂት ታክሲዎች ብቻ ናቸው። በዛ ብለን መሠለፋችንን የተመለከተ ከሌላ አቅጣጫ የሚመጣ ሚኒባስ ታክሲ አሽከርካሪ በተከለከለ ቦታ አዙሮ በተከለከለ አቅጣጫ በፍጥነት እያሽከረከረ ወደ እኛ መጣና ቆመ። ጋቢና ገብቼ ጉዟችንን ጀመርን። ትንሽ እንደተጓዝን ከነበርንበት ታክሲ ፊት ይጓዝ የነበረ የቤት መኪና ድንገት ፍጥነቱን ቀንሶ ወደ ቀኝ ዞረና አደባባዩ መሀል መንገድ ዘግቶ ቆመ። ከቤት መኪናው ፊት መንገዱን የዘጋበት ተሽከርካሪም ሆነ እግረኛ የለም። የተሳፈርንበት ታክሲ ሾፌር በድንጋጤ የተሽከርካሪውን ጡሩንባ እያጮኸ ፍሬን ይዞ ቆመና አንገቱን በመስኮት አውጥቶ በንዴት ከፊት መንገድ የዘጋበትን ሾፌር ይሳደብ ጀመር። ይኼኔ አንድ የትራፊክ ፖሊስ አባል መንገዱን ዘግቶ ከቆመው የቤት መኪና ውስጥ ወረደና መለዮውን አድርጎ ምንም እንዳልተፈጠረ አደባባዩን አቋርጦ ወደ መደበኛ ሥራው ገባ። ትራፊክ ፖሊሱን ጭኖ የመጣው ተሽከርካሪ አደባባዩን ለቆ ወደ መንገዱ አቀና። “ይኼኔ እኔ ብሆን ታርጋዬን ይፈታው ነበር!!!” አለ የታክሲው ሾፌሩ ትራፊክ ፖሊሱን እየተገላመጠ።
ይህ የትራፊክ ፖሊስ አባል በቀን ውስጥ ‹ራሱ ያልተገዛለትን የትራፊክ ደንብ ጥሰሃል ብሎ ስንቱን አሽከርካሪን የቅጣት ደረሰኝ ሲቆርጥለት ይውል ይሆን?› ምናልባትም ስለትራፊክ አደጋ ቢጠየቅ በከተማዋ እየደረሱ ያሉት አደጋዎች ምን ያህል አስከፊ እንደሆኑና አብዛኛዎቹ የትራፊክ አደጋዎች የሚደርሱት የትራፊክ ደንብ በመጣስ እንደሆነ ሰፊ ሙያዊ ትንተና ይሰጥ ይሆናል።
ስለትራፊክ አደጋ መንስዔዎችና የመፍትሔ ሐሳቦቻቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘወትር የሚተላለፉትን የትራፊክ አደጋ ዘገባዎች፣ ውይይቶችና በመንገድ ደኅንነት ላይ የሚያጠነጥኑ መርሐ ግብሮችን በአብዛኛው እከታተላለሁ። የእኔ በጥሞና የመከታተል ብቃት በመድከሙ እንደሆነ እንጃ እንጂ፣ በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግሥታት በሚተዳደሩ የፖሊስ ተቋማት ሥር የሚገኙ የትራፊክ ፖሊስ አባላትና የትራፊክ አደጋ መርማሪ ፖሊሶች ለትራፊክ አደጋ መከሰት ወይም አለመቀነስ ያላቸውን አስተዋጽኦ የተመለከተ አስተያየት ወይም የውይይት ርዕስ ሰምቼ አላውቅም። ስለዚህ ይህንን አይነኬ ርዕስ በተመለከተ የታዘብኩትን ባካፍላችሁ ስለጉዳዩ የውይይት በር ሊከፍት ይችላል ብዬ ስላሰብኩ እነሆ።
በጽሑፌ ያካተትኳቸው ፍሬ ነገሮች ከተለያዩ አሽከርካሪዎችና በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ በተለያየ የሥራ ድርሻ ከተሰማሩ ባለሙያዎች ጋር ያደረግኳቸው ኢመደበኛ ውይይቶች፣ በፌዴራል ዓቃቤ ሕግነትና በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃና በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በዳኝነት ባገለገልኩባቸው ወቅቶች ካጋጠሙኝ ጉዳዮች የተውጣጡ መረጃዎች ናቸው። ጽሑፉ የጥልቅ ጥናት ግኝት ባለመሆኑ ከጽሑፌ በመነሳት የችግሩን ስፋት ለመደምደም የማይስችል መሆኑን አንባቢዎቼን ላስታውስ እወዳለሁ።
የትራፊክ አደጋ ከደረሰ በኋላ የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ የትራፊክ አደጋ መርማሪ ፖሊስ የአደጋውን ቦታ ፕላን በማንሳትና ሌሎች ማስረጃዎችን በማጠናቀር፣ ስለአደጋው መንስዔ ሙያዊ ትንተናውንና የመደምደሚያ ሐሳቡን በምርመራ መዝገቡ ላይ ያሠፍራል። ይህንን መደምደሚያ የሚሰጥበት ሰነድ የትራፊክ አደጋ ቦታ ፕላን ምስክርነት ይባላል። የአደጋው መንስዔ የአሽከርካሪው ድርጊት ከሆነ የጣሰውን የትራፊክ ደንብና ጥፋቱን ጠቅሶ አሽከርካሪው አደጋውን በማድረሱ ተጠያቂ (በተለምዶው አነጋገር ጥፋተኛ) ነው ይለዋል። አጥፊ ካልሆነም ይህንኑ ይገልጻል። በጉዳዩ የረዥም ጊዜ የሥራ ልምድ ካላቸው የተለያዩ ባለሙያዎች ጠይቄ እንደተረዳሁትም ሆነ በትራፊክ አደጋ የሚዲያ ዘገባዎች ላይ በየዕለቱ እንደምንሰማው፣ ሁሌም ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ በአገራችን ለሚደርሱ የተሽከርካሪ አደጋዎች አጥፊ የሚባሉት አሽከርካሪዎች ናቸው። በበቂ ጥናት የተደገፈ እስከሆነ ድረስ የአሽከርካሪዎች አጥፊነት መብዛት ላይ ተቃውሞ የለኝም። ነገር ግን አሽከርካሪዎች ጥፋተኛ ሊሆኑ ቢችሉም ቁጥሩ ግን አሁን ያለውን ያህል የገነነ ሊሆን እንደማይገባ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርኳቸው የትራፊክ ፖሊስ አባላት፣ የሕግ ባለሙያዎችና ሾፌሮች አጽንኦት ሰጥተው አጫውተውኛል። እኔም በሥራዬ አጋጣሚ ባየኋቸው ጉዳዮችም ሆነ በየዕለቱ ምልከታዬ ተንተርሼ በዚሁ ሐሳብ እስማማለሁ። ለዚህ ሐሳቤ ማሳያም የሚከተሉትን ለፌዴራል ዓቃቤ ሕግና ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች የቀረቡ እውነተኛ የትራፊክ አደጋ ጉዳዮች በምሳሌነት ላንሳ፡፡
ምሳሌ አንድ፣አንድ እግረኛ የቀለበት መንገዱን መሀለኛ አስፋልት በምሽት ሲያቋርጥ በመኪና ተገጭቶ ሕይወቱ ያልፋል። አደጋው የደረሰበት ይህ መንገድ ለእግረኛ የተከለከለና ከአደባባይም ሆነ ከተሽከርካሪ ማቋረጫ ርቆ የሚገኝ ነው። በሾፌሩ ላይ የትራፊክ አደጋ ክስ ቀርቦ የወንጀል ምርመራ ይደረጋል። የትራፊክ አደጋ መርማሪ ፖሊሱ ከምርመራ መዝገቡ ጋር ባያያዘው የትራፊክ አደጋ ቦታ ፕላን ምስክርነት መሠረት፣ የእግረኛው ሞት የተከሰተው እግረኛው አስፋልቱን እንዲያቋርጥ አሽከርካሪው ቅድሚያ ስላልሰጠው እንደሆነ ገልጾ ለእግረኛው ሞት አሽከርካሪው ጥፋተኛ ነው በማለት የሙያ ምስክርነቱን አሥፍሯል።
ምሳሌ ሁለት፣አዲስ አበባ ውስጥ የታክሲ ወረፋ የማይጠበቅባቸው ቦታዎች ላይ አንድ ታክሲ ሲመጣ ያለውን አስገራሚ የተሳፋሪዎች ግፊያ ብዙዎቻችን እናውቀዋለን ብዬ አስባለሁ። በተመሳሳይ የታክሲ ማቆሚያ ቦታ አንድ የታክሲ ሾፌር ከታች አቅጣጫ ያሳፈራቸውን ተሳፋሪዎች ያራግፋል። ታክሲውን አዙሮ ወደ ላይ አቅጣጫ የሚጓዙ ተሳፋሪዎችን ለመጫን አሰፍስፈውና ግር ብለው ታክሲ ወደሚጠብቁት ተሳፋሪዎች እጅግ በጣም በዝግታ ያቀናል። የታክሲውን መምጣት ከሩቅ የተመለከቱት ተሳፋሪዎች ታክሲው ገና አስፋልት መሀል እንዳለ ወደ ታክሲው በመሮጥ በሩን ለመክፈት ይጋፋሉ። ከፊታቸው የትራፊክ ፖሊስ መኖሩን የተመለከተው የታክሲው ረዳት ቦታ ሳልይዝ ተሳፋሪ አልጭንም በማለት የታክሲውን በር አልከፍትም ይላል። ተሳፋሪው በመስኮት በኩል የረዳቱን እጅ በትግል በማስለቀቅ ታክሲው ሳይቆም በሩን አስከፍቶ ለመግባትና ግፊያና ግብግብ ይጀምራል። በተሳፋሪዎች መካከል በሚደረግ ግፊያና ትርምስ መሀል ከተሳፋሪዎቹ አንዱ እግሩ ይጠለፍና ይወድቃል። እንደወደቀ የታክሲው የኋላ ጎማ ስለረገጠው (ስለነካው ማለት ይቀላል) እጅግ በጣም ቀላል የእግር ቆዳ መላላጥ ጉዳት ይደርስበታል። በሾፌሩ ላይ የትራፊክ አደጋ ክስ ቀርቦ የወንጀል ምርመራ ይደረጋል። የትራፊክ አደጋ መርማሪ ፖሊሱ ከምርመራ መዝገቡ ጋር ባያያዘው የትራፊክ አደጋ ቦታ ፕላን ምስክርነት መሠረት፣ በተሳፋሪው ላይ ቀላል ጉዳት የደረሰው አሽከርካሪው ያለጥንቃቄ በማሽከርከሩና ያላግባብ መሪ ወደቀኝ በማዞሩ እንደሆነ ገልጾ፣ አሽከርካሪው ጥፋተኛ ነው በማለት የሙያ ምስክርነቱን አሥፍሯል።
ምሳሌ ሦስት፣አንድ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ እጅግ በጣም ብዙ ተሳፋሪዎችን ጭኖ ይጓዛል። ከተሳፋሪዎቹ መካከል የተወሰኑት ወንበር ይዘው አብዛኛዎቹ ደግሞ ቆመው የሚጓዙ ናቸው። አውቶብሱ ቢሾፍቱ አውቶቡስ በመሆኑ በውስጡ ያለው የትኬት መቁረጫ ክፍል ‹‹አክሊሪክ›› ከሚባል መስታወት መሰል ቁስ የተሠራ ነው። በዚህ ክፍል ገንዘብ ተቀባይና ተሳፋሪ ገንዘብና ትኬት የሚቀባበሉበት እጅ የሚያሾልክ አነስተኛ ቀዳዳ እንዳለ ይታወቃል። በአውቶቡሱ ውስጥ ከነበሩት ተሳፋሪዎች አንዱ ትኬት ለመቁረጥ ብሎ እጁን በዚህ ቀዳዳ ሲያስገባ በጉዞ ላይ የነበረው አውቶብስ ቆም በማለቱ የቀዳዳው የውስጠኛው ክፍል የተሳፋሪውን አንድ ጣት ቆርጦት ከባድ ጉዳት ያደርስበታል። በሾፌሩ ላይ የትራፊክ አደጋ ክስ ቀርቦ የወንጀል ምርመራ ይደረጋል። የትራፊክ አደጋ መርማሪ ፖሊሱ ከምርመራ መዝገቡ ጋር ባያያዘው የትራፊክ አደጋ ቦታ ፕላን ምስክርነት መሠረት በተሳፋሪው ላይ ቀላል ጉዳት የደረሰው፣ አሽከርካሪው ያለጥንቃቄ በማሽከርከሩ እንደሆነ ገልጾ አሽከርካሪው ጥፋተኛ ነው በማለት የሙያ ምስክርነቱን አሥፍሯል።
በምሳሌነት የቀረቡት እነዚህ ሦስት በተግባር ያጋጠሙ የትራፊክ አደጋዎች ከትራፊክ ደንብና ከሕግ አንፃር እንዴት ይታያሉ?
ምሳሌ አንድ፣የቀለበት መንገድ መሀለኛው አስፋልት ለእግረኛ ያልተፈቀደ በመሆኑ ሰው እንዳያልፍበት የታጠረ ነው። ይህ መንገድ እግረኛ ያቋርጥበታል ተብሎ ስለማይገመት በዚህ መስመር የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች በሰዓት እስከ 80 ኪሎ ሜትር ፍጥነት እንዲጓዙ ይፈቀድላቸዋል። ከሚጓዙበት ፍጥነት አንፃር በተለይ ፍሬን ይዞ ወይም መሪ አዙሮ ለአደጋ የተጋለጠን እግረኛ ወይም ተሽከርካሪን ከአደጋ ለመዳን ጥረት ማድረግ፣ በራሱ በአሽከርካሪውም ሆነ በሌላ ሰው ሕይወት፣ ጤንነት ወይም ንብረት ላይ ሌላ የከፋ አደጋ ሊያደርስ እንደሚችል የአውቶሞቲቭ ባለሙያዎችም ሆነ የፊዚክስ ሕግጋት ያስረዳሉ። መንገዱ ከእግረኛ ንክኪ ነፃ እንዲሆን ከተደረገበት ምክንያት አንዱም ይኼው ነው። ይህ ጥሬ ሀቅ ከግምት ገብቶ ከላይ በምሳሌ አንድ ላይ የተሰጠው የአደጋ ቦታ ፕላን ምስክርነት ሲታይ የቀረቡት ማስረጃዎችም ሆነ የአደጋው ፕላን አሽከርካሪው እግረኛውን ገጭቶ የገደለው ከተፈቀደለት ፍጥነት በላይ እየሄደ ሳለ መሆኑን፣ ፊት ለፊት እያየውና ማዳን በሚችልበት ፍጥነት ላይ እያሽከረከረ ሲጓዝ መሆኑን፣ አልያም ግልጽ የትራፊክ ደንብን ጥሶ ሲያሽከረክር መሆኑ፣ ወዘተ የሚያስረዱ አይደሉም። በዚህ ሁኔታ ሾፌሩ በቀለበት መንገድ ያውም በሌሊት ለእግረኛ ቅድሚያ መስጠት ይገባው ነበር ብሎ መደምደም ቴክኒካዊም ምክንያታዊም ነው ብሎ ለመደምደም የሚያስችል ሕግም ሆነ የትራፊክ ደንብ የለም። ጥፋተኛ ነው ቢባል እንኳን ሾፌሩ ሊፈጽመው ይገባ የነበረ ነገር ግን ያልፈጽመው ሌላ ነገር ስለመኖሩ የፕላን ምስክርነቱ አንዳችም ነገር አይገልጽም። በዚህ ጉዳይ በቸልተኝነት ሲያሽከረክር ሰው የመግደል ወንጀል ፈጽሟል በማለት የወንጀል ክስ የቀረበበት ይህ ሾፌር፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክርክር አድርጎ ከክሱ በነፃ ተሰናብቷል።
ምሳሌ ሁለት፣ ሁለተኛውን ጉዳይ በተመለከተም በግፊያ መሀል ተሳፋሪው መሬት እንደወደቀ ሾፌሩ መኪናውን በማቆሙ፣ እግረኛው በመኪናው ጎማ ቢረገጥም የደረሰበት ጉዳት እንደዚህ እጅግ በጣም ቀላል መሆኑ የተሽከርካሪው የጉዞ ፍጥነት የኤሊ ፍጥነት የነበረ መሆኑን ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ ታክሲው ወደ ዳር ወጥቶ ሳይቆም ገና መሀል አስፋልት ላይ እያለ መጋፋት የጀመረው ራሱ ተጎጂው ነው። ታዲያ ሾፌሩ በፕላን ምስክርነቱ ላይ ጥፋተኛ የተባለበት አግባብ ምንድነው? ሾፌሩም ሆነ ረዳቱ (ምንም እንኳን በትራፊክ ፖሊስ ላለመቀጣት ብለው ቢሆንም) ታክሲው በአግባቡ ሳይቆም ተሳፋሪ አንጭንም ብለው በሩ እንዳይከፈት ታግለዋል። በዝግታ እየተጓዙ ዳር ይዞ ለመቆምም ጥረት አድርገዋል። ከዚህ ባሻገር አስፋልት መሀል ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ግብ ግብ ከሚፈጥሩ ሞገደኛ ተሳፋሪዎች መካከል አንዱ፣ እግሩ በሰው ተጠልፎ እንዳይወድቅና አደጋ እንዳይደርስበት ለማድረግ ምን ማድረግ ነበረባቸው? ተጎጂው ከእነሱ ጥፋት ውጪ ሲወድቅ መውደቁን እንዳወቁ መኪናውን ከማቆም ባሻገር እግሩ የመኪናው ጎማ ሥር እንዳይገባ ምን ማድረግ ነበረባቸው? ተሳፋሪዎች አላስቆም አሉኝ ብሎ ታክሲውን መሀል አስፋልት ማቆም?
ምሳሌ ሦስት፣ ሦስተኛውን ጉዳይ በተመለከተም በጉዳዩ ላይ የቀረቡት የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች የሚያሳዩት በአውቶቡሱ ውስጥ የተሳፈሩት ሰዎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሾፌሩ ትኬት ቆራጭ ጋ ያለ ተሳፋሪን ይቅርና በቅርቡ ያሉትን ተሳፋሪዎች ለማየት ፈጽሞ አይችልም። ተጎጂው ጉዳት የደረሰበት ማንኛውም ተሳፋሪ በጉዞ ወቅት እንደሚያደርገው ሒሳብ ለመክፈል ባደረገው ጥረት ነው። ተሳፋሪው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሾፌሩ ማድረግ የነበረበት ግን ያላደረገው ነገር ምንድነው? በየፌርማታው ተሳፋሪዎች ሒሳብ ከፍለው መጨረሻቸውን አረጋግጦ ጉዞ መጀመር? ተሳፋሪዎች እጃቸውን አሾልከው ሒሳብ እንዳይከፍሉ ማስጠንቀቅ? እጃቸውን አሾልከው ሒሳብ ሊከፍሉ የሚችሉ ተሳፋሪዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ በጎዞ ወቅት የሚያስቆመው ነገር ቢያጋጥመውም ፍሬን አለመያዝ? ወይስ ምን? በዚህ ጉዳይ የአውቶቡስ ድርጅቱ ሊኖርበት ከሚችል ከውል ውጪ የሚኖር የጉዳት ካሳ ኃላፊነት በቀር በወንጀል ሾፌሩን ሊያስጠይቅ የሚችለው ምኑ ነው?
የትራፊክ አደጋ ቦታ ፕላን ሲነሳ ይፈጸማል የሚባለውን የሙስና ተግባር ወደ ጎን ትተን፣ መሰል የትራፊክ ፕላን ምስክርነቶችን መሠረት አድርገው በመገናኛ ብዙኃን ዘወትር የምንሰማቸው የትራፊክ አደጋ ምክንያቶች የሚፈጥሩት ተፅዕኖን ማገናዘብ ጠቃሚ ይመስለኛል። የትራፊክ አደጋ ቦታ ፕላን ምስክርነቶች የአደጋው ምክንያት እግረኛው ወይም ሌላ ጣልቃ ገብ ምክንያት ነው ብለው የሚገልጹበት አጋጣሚ እምብዛም አለመስተዋሉ፣ እግረኞች ‹‹እኛ የምናደርገው ጥንቃቄ በቂ ስለሆነ መጠንቀቅ ያለባቸው አሽከርካሪዎች ናቸው፤›› ብለው እንዲያስቡ የማድረግ ዕድሉ እጅግ በጣም ሰፊ ነው። ይህ መሆኑ እግረኞች በቂ ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው የትራፊክ አደጋ ሰለባ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የማድረግ አቅም አለው። ይህ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በአገራችን ቁጥሩ እያደገ ለመጣው የተሽከርካሪ አደጋ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱ አይቀሬ ነው። ከላይ በተገለጹት ሦስቱም ምሳሌዎች የትራፊክ አደጋ ቦታ ፕላን ምስክርነቶቹ ሾፌሮቹን ጥፋተኛ ያሏቸው ቸልተኛ በመሆናቸው በሰው ሕይወትና አካል ላይ ጉዳት አድረስዋል ብለው ነው። አንድ የወንጀል ሕግ ምሁር እንደገለጹት አንድ ሰው፣ ‹‹ቸልተኛ ነው? ወይስ አይደለም?›› ለማለት የሚቀመጠው መለኪያ ተለጥጦ የሚተረጎም ከሆነ፣ አንድ ሰው ‹‹አውቆ አጥፊ ነው? ወይስ አይደለም?›› ለማለት ከሚቀመጠው መለኪያ ጋር መለያ ልጓሙ ይጠፋል። ያላግባብም ሰዎች እንዲከሰሱ በር ይከፍታል።
ከጉዳት ካሳ ጋር በተያያዙ ክርክሮች ወቅት ለጉዳቱ መድረስ የተጎጂው ጥፋት መኖር የሚሰጠውን የካሳ መጠን አነስተኛ ሊያደርገው እንደሚችል የፍትሐ ብሔር ሕጋችን ይደነግጋል። ከወንጀል ኃላፊነት አንፃር የትራፊክ አደጋ ፕላን ምስክርነት የአንድን አሽከርካሪ ጥፋተኝነት ከማስረዳት አንፃር ያለውን አቅም በተመለከተ፣ በሕግ ባለሙያዎችም ሆነ በዳኞች መካከል የሕግ አተረጓጎም ልዩነት በስፋት ይታይ ነበር። ይህንን ልዩነት አስወግዶ ወጥ አረዳድ ለመፍጠር ይረዳ ዘንድ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 42703 ሐምሌ 22 ቀን 2001 ዓ.ም. አንድ አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል። በዚህም ውሳኔ ፍርድ ቤቶች በአደጋ (Accident) እና በቸልተኛ የወንጀል ድርጊት (Negligent Criminal Offence) መካከል ያለውን ልዩነት መመርመርና መመለየት እንደሚገባቸው አትቷል፡፡ ይኼው ችሎት በመዝገብ ቁጥር 92141 መስከረም 30 ቀን 2007 ዓ.ም በሰጠው ትርጉም ደግሞ አንድ የትራፊክ ባለሙያ የሚሰጠው ሙያዊ አስተያየት ተገቢውን የሙያ ደንብ ተከትሎ ያልተሰጠና ያልቀረበ፣ እንዲሁም በቦታው ከነበሩት ዓይን ምስክሮች ቃል ጋር ተነፃፅሮ ሲታይ በመሠረታዊ ነጥቦች ላይ ልዩነት ያስከከተለ ከሆነ የማስረጃ ዋጋ የማይሰጠው መሆኑን በመገልጽ አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይህም የትራፊክ አደጋ ፕላን ምስክርነት በራሱ ብቸኛ ማስረጃ ተደርጎ የሚወሰድ ሳይሆን ደጋፊ ማስረጃ እንደሆነ የዚህ ወሳኔ ሐተታ ያስረዳል። ይህ የሚያሳየው አንድ አሽከርካሪ በትራፊክ አደጋ መርማሪ ፖሊስ ጥፋተኛ ነው ስለተባለ ብቻ የወንጀል ኃላፊነት አለበት ማለት እንዳልሆነ ነው።
በመሆኑም በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ የፖሊስ ተቋማትም ሆነ የመንገድ ደኅንነት ፕሮግራም አዘጋጆች፣ ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንፃር አይነኬ ከሆኑት ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ የሆነውን የትራፊክ አደጋ ቦታ ፕላን ምስክርነት ችግሮች በማንሳት ወደ አደባባይ ሊያወጡት ይገባል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ የትራፊክ አደጋ መርማሪዎችን ሙያዊ ብቃት ማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል። ችግሩን መቅረፍ ያላግባብ የሚከሰሱ ሾፌሮችን ተገቢ ካልሆነ እንግልት ያድናል። የትራፊክ አደጋ መርማሪዎችን ተዓማኒነት ከፍ ያደርጋል።
በተለምዶ የኅብረተሰባችን አነጋገር ‹‹በዜብራ ላይ ተሻገሩ። በዜብራ ላይ ተሻግረህ በመኪና ብትገጭ ሾፌሩ ብቻ ነው ኃላፊ የሚሆነው፤›› ይባላል። በተግባር ሲተገበር ብዙም ባናየውም፣ ይህ የሚያሳየው ኅብረተሰቡ ለአደጋ ላለመጋለጥ ካለው ጠቀሜታ ባሻገር፣ በዜብራ ላይ ለመሻገር የሚመርጥበት ሌላም ምክንያት እንዳለው ነው። በተመሳሳይ በእግረኞች ጥፋት በሚደርሱ አደጋዎች ሾፌሮች ተጠያቂ የማይሆኑበት አጋጣሚ መኖር ማስተማሩ የችግሩ ምንጭ ሾፌሮች ብቻ አለመሆናቸውን ኅብረተሰቡ እንዲረዳው ስለሚያደርግ፣ እግረኞች ስለትራፊክ አደጋ ያላቸውን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ የብዙዎችን ሕይወት፣ አካል፣ ጤናና ንብረትን ለመታደግ ስለሚረዳም የላቀ ክብርና ጥቅም ያስገኛል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ እንተንፍሰው እንማርበት!!!
ትዝብቴን እዚህ ላይ አበቃሁ። የምንደማመጥ፣ ሐሳብን በሌላ ሐሳብ ብቻ የምንዋጋ፣ ከግል ክብርና ጥቅም በላይ ለአገራችን ቅድሚያ የምንሰጥ የአንድ አገር ሕዝቦች ያድርገን። ብሩሃን ቀናት ከፊታችን ይቅደሙ። ሰላም።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን (LL.B LL.M MSW) አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው danahai81@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
