Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

በአስመራ ምን እየሆነ ነው? በአዲስ አበባስ?

$
0
0

(የምሥራቅ አፍሪካ አምሳለ ሰብዓት ዕጣ ፈንታ)

በያየሰው ሽመልስ

እዚህ ግባ የሚባል ማስታወሻ የሌለውና ያልተነገረለት የባድመ ጦርነት፣ ቁጥራቸው ያልተገለጸ ኢትዮጵያዊያንን ደመ ከልብ አድርጎ በአልጀርስ ‹‹ስምምነት›› ከተቋጨ 17 ዓመታትን ተሻግሯል፡፡ ከዚያ በኋላ የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ ቅርፅ አዲስ አሠላለፍ ይዟል፡፡ የአሠላለፉ ቅርፅ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ብልጫ፣ በኤርትራ ዝግ ፖሊሲ (Closed Door Policy)፣ በሶማሊያ የእርስ በርስ ጦርነት፣ በሱዳንና በአሜሪካ ውዝግብ፣ በደቡብ ሱዳን መፈጠርና የእርስ በርስ ጦርነት፣ በጂቡቲ ስትራቴጂካዊ ተመራጭነት፣ ወዘተ ያሸበረቀ ሆኗል፡፡ ከጦርነቱ ማግሥት ጀምሮ ገቢራዊ የሆነው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግን እነዚህን አጋጣሚዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ አይመስልም፡፡

ይሁን እንጂ በኤርትራ ላይ አዲስ ፖሊሲ ለማውጣት የሚገደድበት ዘመን ላይ እንደ ደረሰ መንግሥት በአደባባይ አምኗል፡፡ ስለሌሎቹ ጎረቤት አገሮች ግን የተባለ ነገር የለም፡፡ ሆኖም የቀጣናው የወደፊት አቅጣጫ ከኢትዮጵያ ጋር ለሚኖረው ሁናቴ (Predicament) ሌላ ፖሊሲ ለማውጣት የሚያስገድድ ይመስላል፡፡ በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ላይ የኢትዮጵያ ተሰሚነት ቀንሷል፡፡ በጂቡቲና በሱዳንም ላይ ሊከለሱ  (ልብ ሊባሉ) የሚገባቸው ነገሮች እየተከሰቱ ናቸው፡፡ እንዴት?

አስመራና አዲስ አበባ

የ‹ሰላምም ጦርነትም የለም› ፖለቲካን የወለደው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኢትዮጵያ በኩል ውጤት እንዳላስገኘ ብዙ ጊዜ ብዙ ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ፣ ኤርትራ ላይ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ወታደራዊ ሳይሆን ዲፕሎማሲያዊ ነው፡፡ ወታደራዊ ጥቃቱ ተመጣጣኝ ዕርምጃ የሚባል እንደሆነ ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡ በዚህ ተመጣጣኝ በሚባል ወታደራዊ ዕርምጃ ግን የተደሰተ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስልም፡፡

ቀድሞ ነገር ‹‹‹ተመጣጣኝ ዕርምጃ›› የሚባል ወታደራዊ አማራጭ አለ ወይ? ካለስ ምን ማለት ነው? የሻዕቢያ መንግሥት አሥር ሰዎችን ከትግራይ አፍኖ ሲወስድ የኢሕአዴግ መንግሥት ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸውን ኤርትራዊያን አንቆ ማምጣት ነው ወይ? የኤርትራ ወታደሮች ካልተኮሱ አትተኩሱ ማለት ነውን? በዚህ ሁሉ ጣጣ ምክንያት ከንግድና ከኢንቨስትመንት የራቁትን የትግራይ ድንበራማ አካባቢዎችንስ መንግሥት አስቧቸው ያውቃል ወይ? ሻዕቢያዊያን ከ1990ዎቹ ጦርነት ማብቃት ወዲህ በኢትዮጵያ ላይ ላደረሱት ጉዳት (አፍነው ለወሰዱት ሰው፣ በኢትዮጵያ ሲንቀሳቀሱ ለገደሏቸው ቱሪስቶችና የማዕድን አውጪዎች፣ ወዘተ) የተወሰደው ዕርምጃ ተመጣጣኝ የሚባል ነው ወይ? ከተባለስ ምንድነው ዝርዝር ማስረጃው?…እነዚህና ሌሎች እልፍ ጥያቄዎች ከአዲስ አበባው መንግሥት ዝርዝር ማብራርያ ተሰጥቶባቸው አያውቅም፡፡

ነገሩን ማብራራት ስላልቻለና የተመጣጣኝ ዕርምጃ ወታደራዊ ኅልዮት አዋጭ እንዳልሆነ ስለገባው ይመስላል የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መንግሥት፣ ‹‹በኤርትራ ላይ አዲስ ፖሊሲ ልንተገብር ነው›› ሲል ባለፈው ጥር ይፋ አድርጓል፡፡ በሪፍት ቫሊ ኢንስትቲዩት የጥናትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ሴድሪች ባርነስ ለፎሪይን ፖሊሲ መጽሔት እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ በኤርትራ እየተካሄደ ስላለው ነገር ጆሮ ዳባ ልበስ ብላለች፣ በኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ላይ የምትከተለው ፖሊሲም አልተሳካም፡፡ በዲፕሎማሲያዊ መገለል ኤርትራን ጫና ውስጥ እከታታለሁ ብሎ አስቦ የነበረው መንግሥት አሁን አሁን እየከሸፈበት ይመስላል፡፡ ዓረቦቹና አውሮፓዎቹ በአስመራው መንግሥት ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ወደ ጎን ብለው ኤርትራ መመላለስ አብዝተዋል፡፡

የዲፕሎማሲ አማረጩ እየከሸፈ ሄዷልን?

ዓረቦቹ በየመን ለሚያደርጉት ውጊያ በኤርትራ የጦር ሠፈር ከመመሥረት አልፈው፣ ወደቦቿን በሊዝ ተከራይተዋል፡፡ ማርቲን ፕላውት ‹‹Understanding Eritrea›› በተሰኘው መጽሐፍ እንደተረከው፣ የዓረብ ነገሥታት (ምንም እንኳ ኳታር ከኤርትራ ምድር ጓዟን ነቅላ ብትወጣም) የኤርትራን የባህርና የብስ እንዳሻቸው እንዲፈነጩበት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ይሁንታ ሰጥተዋቸዋል፡፡ ወዲ አፎም ለዚህ ውለታቸውም ገንዘብና ነዳጅ በነፃ እያገኙ ናቸው፡፡

ኤርትራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አፍሪካዊቷ ሰሜን ኮሪያ የሚለውን ስሟን በሚያሻሽል ሁኔታ ራሷን ክፍት እያደረገች ነው፡፡ ባሳለፍነው ዓመት ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ ለሚቀርብ ዕርዳታ ወደቧን ፈቀደች፡፡ በዚያው ዓመት ከ15 ዓመት ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ የአካዳሚክ ሰዎች ያደረጉት ጉባዔ ተካሄደ፡፡ በዚያ ጉባዔ ላይ በኤርትራ ምድር ባልተለመደ ሁኔታ ከፍ ያሉ ሐሳቦች የተደመጡበት (ከሰብዓዊ መብት እስከ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጉዳዮችን ያስተናገደ) ነፃ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በዚህ የዴሞክራሲን ትወራ ባቀነቀነው ጉባዔ ላይ የተሳተፉት የጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ሃሪ ቬርሆቨን እንደሚሉት፣ አስመራ ከ15 ዓመታት ወዲህ ዓይታው የማታውቀውን ምሁራዊ ውይይት (Intellectual Discourses) አስተናግዳለች፡፡ ለመገናኛ ብዙኃንና ለገለልተኛ ወገኖች ዝግ የነበረችው ኤርትራ እ.ኤ.አ. በ2015 ብቻ 50 ጋዜጠኞች እንዲጎበኟት ፈቅዳለች፡፡ እንዲህ ያለው ይሁንታዋ ከተገለለችበት ዓለም ጋር መልሳ ለመታረቅ ለምታደርገው ጉዞ መግቢያ በር መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

የአስመራው አስተዳደር ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ከምዕራቡ ዓለም መንግሥታት ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ባደረገው ግንኙነት የተሻለ መስመር ውስጥ እየገባ ይመስላል፡፡ ምንም እንኳ ከአንድ ወር በፊት አቶ ኢሳያስ አሜሪካን ኮንነው ለዓለም መንግሥታት ደብዳቤ ቢጽፉም፣ ከአውሮፓ አገሮች በኩል የይሁን መብራት (Green Light) ዓይተዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2015. የአውሮፓ ኅብረት ሁለት መቶ ሚሊዮን ዩሮ ለኤርትራ ዕርዳታ ሰጥቷታል፡፡ ይህ ገንዘብ የሚውለው በኤርትራ ውስጥ ያለውን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል ለሚሠሩ የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማት ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ የኤርትራ የደኅንነትና የመከላከያ ተቋም ራሱን የሚያደራጅበት የውጭ ምንዛሪ ከነጮቹ በእጅ አዙር አገኘ ማለት ነው፡፡

ከኅብረቱ በተጨማሪ የተለያዩ አባል አገሮች የአውሮፓ የሰብዓዊ መብት ኤጀንሲዎች ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለመተባበር ፍንጭ እያሳዩ ነው፡፡ የብሪታኒያ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (Britain Department for International Development)  የተሰኘው ግብረ ሰናይ ተቋም በኤርትራ ቢሮ ሊከፍት ዕቅድ እንዳለው ይፋ አድርጓል፡፡ የጀርመን መንግሥትም ከላይ እንደተጠቀሰው ላሉ ድርጅቶች የቴክኒክ ድጋፎችን ለማድረግ ተስማምቷል፡፡ የስደተኞች ጉዳይ ጭንቅ ለሆነበት የአንገላ መርከል አስተዳደር ብዙ ስደተኞችን ለምትልከው ኤርትራ ከዚህም በላይ ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እነዚህ ነገሮች የሚያመለክቱት ኢትዮጵያ ኤርትራን ለማግለል የተከተለችው ፖሊሲ እየከሰመ መምጣቱን ነው፡፡ ወታደራዊ ዕርምጃው ከላይ በተዘረዘሩት አመክንዮዎች ምክንያት መንግሥትን ውጤታማ አላደረገውም፡፡ ይልቁንም የሰላምም ጦርነትም የለም ፖለቲካ (No War No Peace Status Quo) ለአቶ ኢሳያስ የተመቻቸው ይመስላል፡፡ አገራቸው በጦርነት ዋዜማ ላይ የምትገኝና ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎች ጎረቤቶቻቸው የመወረር ሥጋት ያደረባት አድርገው የሚነገሩትን የኤርትራ ወጣት ለውትድርና እንዲመለመል ሆኖላቸዋል፡፡ ከአሜሪካ መንግሥት ጋርም የርዕዮተ ዓለም ሽኩቻ ውስጥ የገቡ አስመስለው ስለሚተርኩና የዋሽንግተን ፖለቲከኞች ዓላማ በኢትዮጵያ መንግሥት መዳፍ ምሥራቅ አፍሪካን መቆጣጠር ነው የሚለውን ትወራ በየማለዳው ስለሚናገሩ፣ ቁጥሩ ከጥቂት በላይ የሆነ የአገሬው ሰው አምኗቸው እየኖረ ነው፡፡

በዲፕሎማሲው መስክ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም የምትታወቀው አሜሪካ አሁን አሁን ለዘብተኛ እየሆነች ይመስላል፡፡ ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ በውጭ ጉዳይና በደሃ መንግሥታት ጉዳይ ቸልተኛ የሆኑት ሪፐብሊካን ሥልጣን መያዛቸው፣ ከሁሉም በላይ ለአፍሪካ ጉዳይ ዳተኛ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆናቸው የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ከልዕለ ኃያሏ አገር ትኩረት እየራቀው ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ በተለይ የሁለቱን አገሮች ውዝግብ ከሥር መሠረቱ አንስተው የሚያውቁትና የኢሕአዴግ መንግሥትና ባለሥልጣናት ወዳጅ መሆናቸው የሚነገርላቸው ሱዛን ራይስ፣ ከትራምፕ አስተዳደራዊ ሥርዓት ውጭ መደረጋቸው ጉዳዩን የእሳቸውን ያህል በኃላፊነት (With Passion) የሚይዘው ሰው ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

በ1990ዎቹ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲካሄድ ከአሜሪካ በኩል ጉዳዩ በሽምግልና እንዲፈታ ጥረት ሲደረግ አደራዳሪ ሆነው ይሠሩ የነበሩት ቶኒ ሌክ የተባሉ ግለሰብ ነበሩ፡፡ ወዲያው ግን ሱዛን ራይስ ተተክተው ጉዳዩን በትኩረት ያዙት፡፡ በኋላም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሆነው ከኢትዮጵያ መንግሥትና ባለሥልጣናቱ ጋር በቅርበት ሲሠሩ ቆዩ፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ኤርትራዊያን እንደ ራይስ የሚጠሉት አሜሪካዊ ያለ አይመስልም፡፡ የአስመራ ሰዎች ራይስ ገለልተኛ ነበሩ ብለው አያምኑም፡፡ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የምታደርገውን ጥረት ራይስ ተቀብለው አስተጋብተዋል የሚል ነው የኢሳያስ ልሂቃን መከራከሪያ፡፡

የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የምትከተለው ዲፕሎማሲ ልክ እንደ ወታደራዊው አማራጭ ሁሉ ውጤታማ አልሆነም፡፡ ዓረቦቹ ለኤርትራ መንግሥት ዶላር፣ ነዳጅ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የጦር መሣሪያ ዕርዳታ፣ ወታደራዊ ሥልጠና፣ ወዘተ እየሰጡ ነው፡፡ ማዕቀቦች በተጣሉባት አገር እንዲህ ያለ ነገር ሲፈጸም የማዕቀብ ተቆጣጣሪው አካል ዝምታን መምረጡ ዕርምጃው ሊነሳ ወይም ቀለል ሊል የሚችልበት ዕድል እንዳለ የሚጠቁም ነው፡፡ ኤርትራ ላይ ዓለም አቀፋዊ ማዕቀብ እንዲጣል ምክንያት የሆነው አልሸባብን የመደገፏ ነገርም አሁን ማስረጃ እንዳልተገኘለት እየተነገረ ነው፡፡ ስለዚህ ኤርትራን ለማግለል በኢትዮጵያ በኩል የተሄደበት መንገድ ከዚህ በላይ የሚያስጉዝ አይመስልም፡፡

ይወጣል የተባለው አዲስ ፖሊሲ

መንግሥት በኤርትራ ላይ አዲስ ፖሊሲ ለመከተል ጥናት ማድረጉን ይፋ ካደረገ ስድስት ወራት አልፈዋል፡፡ ባለፈው ጥር ወደ ሁመራ (ትግራይ) አቅንተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ‹‹በእንዲህ ያለ ሁኔታ ከኤርትራ ጋር የምንኖረው እስከ መቼ ነው?›› የሚል ፈታኝ ጥያቄ ከአካባቢው ሰዎች ሲጠየቁ ነበር፣ አዲስ ፖሊሲ እየተረቀቀ መሆኑን ለመጀመርያ ጊዜ የተናገሩት፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የሥራ አፈጻጸማቸውን ለፓርላማ ያቀረቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይኼን ጉዳይ ደግመውታል፡፡ ሁለቱም ባለሥልጣናት ግን የፖለሲው ጥናት ተጠናቋል፣ በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን ከማለት የዘለለ ያሉት የለም፡፡ ሆኖም ለሕዝብም ይፋ ሳያደርጉት፣ የጥናቱ ይዘትም በየትኛውም መንገድ ጫፉ ሳይታወቅ በጀት ዓመቱ አለቀ፤ ፓርላማውም ለዕረፍት ተዘጋ፡፡

የሆነ ሆኖ ከዚህ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ትከተለዋለች ከተባለው አዲስ ፖሊሲ ብዙ ነገሮች ይጠበቃሉ፡፡ የኢሳያስን መንግሥት የወቅቱን ሁኔታ ያገናዘበ፣ የዲፕሎማሲውን ጥረት መክሸፍ ከግምት ውስጥ ያስገባ፣ ‹‹ተመጣጣኝ ዕርምጃ›› የሚባለው ወታደራዊ አማረጭ አዋጭ አለመሆኑን የተረዳ፣ ከኢሳያስና ከሕግዴፍ/ሻዕቢያ በኋላ የምትኖረውን ኤርትራን አርቆ የተመለከተ፣ ከሻዕቢያ ጦረኛና መሰሪ ባህርይ ጋር የተጣጣመ፣ የአስመራው መንግሥት ወዳጅ ከሆኑት ዓረቦች ጋር የማያጣላና ላልተፈለገ ውዝግብ የማይዳርግ…ወዘተ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ጉንጭ ማልፋት ይሆናል፡፡

ሌሎቹ የቀንዱና የቀጣናው አገሮችስ

ውዝግብ በማያጣው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ የሚጨበጥ ፖለቲካ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ በዚህ ከባድ ከባቢ ውስጥ በወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ብልጫ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ለመኖር የተገበረችው ፖሊሲ ውጤታማ አድርጓታል ወይ የሚለው ሰፊ ትንተና የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ከመዳፏ እየወጡ ይመስላል፡፡ የጂቡቲና የሱዳንም ጉዳይ ግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ላለመሆኑ ማስረጃ የለም፡፡

ለዘመናት በጦርነት በምትማቅቀው ሶማሊያ ጦር በማዝመት ከሞቃዲሾ እስከ ባይድዋ ስትፋለም የኖረችው ኢትዮጵያ፣ ከመሐመድ አብዱላሂ (ፋርማጆ) መምጣት በኋላ ወታደራዊ ተሳትፎዋም እየተፈለገ እንዳልሆነ እየተገለጸ ነው፡፡ ከወራት በፊት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሆነው ‹‹የተመረጡት›› ፋርማጆ፣ ለኢትዮጵያ እንደ ቀድሞው ፕሬዚዳንት (ሐሰን ሼክ መሐመድ) የተመቹ እንዳይደሉ ይነገራል፡፡

ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አሚሶም ለተባለውና የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን ባሰባሰበው የጦር ኅብረትም መልካም ስሜት እንደሌላቸው ሰሞኑን በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ኡጋንዳ ተጨማሪ ሁለት ሺሕ ጦር ወደ ሶማሊያ ስትልክ (ከአሁን በፊት ስድስት ሺሕ አዝምታለች)፣ ‹‹አሚሶም በቃው፣ የሶማሊያን ጉዳይ ለሶማሊያውያን ተውልን፣ አሚሶምም እስካሁን ላደረገልን ነገር እናመሰግናለን፤›› ካሁን በኋላ አልሸባብ በሶማሊያ ወታደር ይደመሰሳል… ሲሉ ሳያድበሰብሱ ተናግረዋል፡፡ ፋርማጆ የኢትዮጵያንና የአሚሶም ጣልቃ ገብነት እንዳልፈለጉት የገለጹት፣ ‹‹ከዚህ በኋላ የአየር ክልላችንንም ሆነ ድንበራችንን እንጠብቃለን፤›› በማለትም ጭምር ነው፡፡ የእሳቸውን አቤቱታ የጦር አበጋዞቻቸውም ደጋግመው አስተጋብተውታል፡፡

ፕሬዚዳንት ፋርማጆ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጋር ወታደራዊ ሽርክና ውስጥ የገቡ አይመስልም፡፡ ከዚያ ይልቅ ዓረቦቹንና አንዳንድ የአውሮፓ አገሮችን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ ለአብነት የአየር ኃይላቸውን እያሠለጠነችላቸው ያለችው የጣይብ ኤርዶሃን አገር ቱርክ ነች፡፡ ለእግረኛ ሠራዊታቸው የፋይናንስ ድጋፍ እያገኙ ያሉት ከኳታርና ከሳዑዲ እንደሆነም ይነገራል፡፡ አገሮቹ እግረኛ ወታደሮችን ለማሠልጠንም ፊት ይነሷታል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በርካታ አፍሪካውያን እየመጡ የሚሠለጥኑበት የአየር ኃይል ትምኅርት ቤት አለ፡፡ እነ ኡጋንዳና ሩዋንዳ ሳይቀሩ የሚሠለጥኑባቸው ወታደራዊ  ኮሌጆች አሉ፡፡ የፋርማጆ መንግሥት ግን ይኼንን የፈለገ አይመስልም፡፡ ፊቱን ወደ ዓረቡ ዓለምና ወደ ቱርክ አዙሯል፡፡

የደቡብ ሱዳንም ጉዳይ ከዚህ የራቀ አይደለም፡፡ ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች (የማቻርንና የኪርን) ለማሸማገል ያደረገችው ጥረት አልተሳካም፡፡ አቶ ሥዩም መስፍን በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) ሥር ሆነው የደከሙትን ውኃ በልቶታል፡፡ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 2015 የተፈረመው ስምምነት አለመተግበሩ በግል የኢትዮጵያን ጥረት ያላሳካ፣ እንደ ቡድንም ኢጋድን አቅመ ቢስ ያደረገ (የኢጋድም ሊቀመንበር የአቶ ኃይለ ማርያም መንግሥት መሆኑን ልብ ይሏል) ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ በመጨረሻም የጂቡቲ ሰው አደራዳሪ ሆነው ገብተዋል፡፡ ሒደቱ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ያላትን ተሰሚነት ጥያቄ ምልክት ላይ የጣለ ሆኗል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ሁለት ሰላም አጥ አገሮች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊከተለው የሚገባ ጊዜያዊ ፖሊሲ (ልክ በኤርትራ ላይ ይደረጋል እንደተባለው ሁሉ) የሚያስፈልግ ይመስላል፡፡ ፖለሲው ቢያንስ የአገሮቹን የውስጥ ፖለቲካ ከግምት ውስጥ ያስገባ ሆኖ፣ የነገ ዕጣ ፈንታቸውን የሚተነትንና በዚያ የተቃኘ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ሱዳንና ጅቡቲ

የኦማር ሐሰን አል በሽር ሱዳን ከኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ጋር የተሻለ ዘመን ላይ ትገኛለች፡፡ በ1990ዎቹ መጀመርያ ላይ (በአውሮፓውያን አቆጣጠር) የነበረው ቁርሾ ተሻሽሎ አሁን በእጅጉ መልካም የሚባል ደረጃ ላይ ነው፡፡ የአገሪቱ ነዳጅም 90 በመቶ የሚገባው ከሱዳን/በሱዳን ነው፡፡ ይኼ ሁሉ ግንኙነት የተመሠረተው ግን በግለሰብ ላይ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት አል በሽር ከኢሕአዴግ ነባር ሰዎች ጋር ባላቸው ቀረቤታ የተሻለ ቤተሰብነትን መሥርተዋል፡፡ ሰውዬው ለአዲስ አበባው መንግሥት ባለሥልጣናት ባላቸው ወዳጅነትም አውሮፕላን እስከ መስጠት ደርሰዋል (ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. መለስ ዜናዊ፣ ተፈራ ዋልዋና ሥዩም መስፍን ከካርቱም ወደ አዲስ አበባ የመጡባትን አውሮፕላን ለሕወሓት 40ኛ ዓመት መሸለማቸው አይዘነጋም)፡፡

እንዲህ ያለው ግንኙነት መሠረቱ ግለሰብ ነው፡፡ በማዕቀብና በዕድሜ የጎበጠው የአል በሽር መንግሥት ዕጣ ፈንታው የሚገመት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በሱዳን ላይ የምትከተለው ፖሊሲም ይኼንን ሁኔታ (General Situation) የተነተነ አይመስልም፡፡ ከአል በሽር በኋላ ያለችውን ሱዳን ከግምት ውስጥ ከማስገባት ይልቅ፣ ባለ በትሩ ፕሬዚዳንት እስካሉ ድረስ አዲስ አበባና ካርቱም ቆሎ የሚያጓርስ ፍቅራቸውን ማንም አይነካውም የሚል አንድምታ ያለው ትወራ ቀጥሏል፡፡

ይኼ ግን የሚያዛልቅ አይመስልም፡፡ ከግለሰብ ባሻገር የሆነ ፖሊሲ፣ ከሕዝብ ጋር ቀጥተኛ ግንኑነት ያለው ዲፕሎማሲ፣ ከጠንካራና ከሰላማዊ የአል በሽር ተቃዋሚዎች ጋር የተገናኘ ፖለቲካ…ሊሠራ ይገባል፡፡ በተመሳሳይ የፕሬዚዳንት አል በሽር መንግሥትም በኢትዮጵያ ውስጥ ይኼንኑ ዓይነት ተከትሎ እንዲሠራ ሊፈቀድለት ይገባል፡፡

ከዚያም በመቀጠል የሱዳንን ኢኮኖሚ እየጎዳው ያለውን የአሜሪካን ማዕቀብ ለማስነሳት የአቶ ኃይለ ማርያም መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአሜሪካ ወዳጅ መሆኑንና በፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ መቀመጫውን የመጠቀም ዕድል አለው፡፡ ጠንከር ያለ ጥረት አድርጎ ይኼንን ማዕቀብ ካስነሳም፣ ለሱዳን ሕዝብ ትልቅ ውለታ እንደዋለ አድርጎ የሕዝባዊ ድፕሎማሲ (Public Diplomacy) ሥራውን ለመሥራት አጋጣሚ ይፈጥርለታል፡፡ በጥቅሉ ግን የአል በሽርን ዘመን የምትሻገረው ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር እንዴት ያለ ዝምድና ይኖራታል የሚለውን አርቆ የሚያይ ፖሊሲ ሊኖር ግድ የሚልበት ዘመን ሆኗል፡፡

የጂቡቲውም ተመሳሳይ ነው፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አማርኛ መናገራቸው፣ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መፍጠራቸው፣ በምሥራቁ ክፍል ካለው የኢትዮጵያ ነዋሪ ጋር በቅርበት መተዋወቃቸው፣ ወዘተ የሁለቱ አገሮች ተፈላላጊነት ከፍ እንዲል አስመስሎታል፡፡ የኢትዮጵያ ዓይንና አፍንጫ የሆነችው ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ፕሬዚዳንት ጉሌህ እስከ ፈቀዱና እስከ ወደዱ ድረስ ብቻ እንዳይሆን፣ ከእሳቸው በኋላ ከሚመጣው መንግሥትና አመራር ጋር ግንኙነቱ እንዲቀጥል፣ የጂቡቲ ሕዝብም ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት ሥልታዊ ሳይሆን ስትራቴጂካዊ መሆኑን እንዲያውቀው፣ ወዘተ በሚገባ ሊሠራ ይገባል፡፡ ፕሬዚዳንት ጉሌህ አንድ ግለሰብ ናቸው፡፡ የተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ጉዳዮች ሊገጥሟቸው ይችላል፡፡ ፓርቲያቸውም ምንም እንኳ የአፍሪካ ፓርቲ ቢሆንም አንድ ቀን ሥልጣን ያጣል፡፡ እናም የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለውን ግለሰብ ላይ የተመሠረተና የተወሰኑ የፓርቲና መንግሥት አመራሮች ላይ ማዕከል ያደረገ ‹ፖሊሲ› ሊያጤነውና ልብ ሊለው የሚገደድበት ዘመን ይመስላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው yayeshime02@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡.

 

 

 

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles