Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

የፖለቲካም የኢኮኖሚም ዳር ድንበር ግለ ነፃነት ብቻ ሳይሆን የዳበረ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ጭምር ነው

$
0
0

በኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር)

በኢትዩጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓትና በዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት ባህሪያት ተቃርኖዎችና ተመጋጋቢነት ላይ ሐሳብ መለዋወጡ ጠቃሚና ተገቢ ነው፡፡ ሆኖም ‹‹የፖለቲካም የኢኮኖሚም ዳር ድንበር ግለ ነፃነት ነው›› በሚል ርዕስ በቅርቡ በሪፖርተር በቀረበ ጽሑፍ ላይ የግለሰብ ነፃነት የሁሉም ነገር መሠረትና ማጠንጠኛ አድርጎ ማቅረብ ‹ሾላ በደፈናው› በሆነ መልኩ  ሰው ተመራምሮ የነገረንን ደግመን ለመናገር እስከ ማስትሬትና ዶክተሬት መማር ለምን አስፈለገ? በማለት ጸሐፊው ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ፣ በቀቀን የምትባለው ወፍም የሰማችውን ደግማ መናገር አያቅታትም ይላሉ፡፡ ኢኮኖሚስቶች በማለት ያሰቀመጡት  ስላቅ መሰል  አገላለጽ  ‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ› ነው፡፡

በእኔ ዕይታ በዚህ ዓምድ ላይ የምናቀርባቸው አጠቃላይ የሆኑ ሐሳቦችን የያዙ መጣጥፎች በማስተርስ ወይም ፒኤችዲ ደረጃ የተሠሩ ጥናቶች ይዘትና ፋይዳ የሚገመገሙበት ሳይሆን፣ የተወሰኑ ሐሳቦች እርስ በርስ የምንለዋወጥበትና ለማኅበረሰቡ የምናቀርብበት ነው፡፡ ጸሐፊው በየዘርፉ የተደረጉ  ጥናቶችን  በሚገባ  ዳሰው (Review) አድርገው ትችቱን አቅርበውት ቢሆን ኖሮ አገላለጹ ባይመችም መውሰድ የግድ ይል ነበር፡፡ ሆኖም  ሳይንሳዊ ጥናቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መዳሰስ በማይቻልበት፣  ይህንንም ዓላማ ባላሰቀመጠ የጋዜጣ ዓምድ ላይ ስለ ማስተርሰና ዶክትሬት ጥናቶች እንዲህ ያለ  አሰተያየት መስጠት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ጸሐፊው በየዘርፉ የተሠሩ ጥናቶች ላይ  የሰላ ሳይንሳዊ የሆነ ትችት ለማቅረብና ጥናቶችን ለመዳስስ አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ ካላቸው፣  ይህን ዓምድ ሳይሆን በዘርፉ ያሉ ዓለም አቀፋዊም ሆነ አገራዊ አካዳሚክ ጆርናሎች  ተመራጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሳላሰታውሳችሁ አላልፍም፡፡ በትምህርት በሚገኙ ማዕረጎች ዙሪያ ጸሐፊው ያንፀባረቁት አመለካካት በአገራችን አልፎ አልፎ የሚታየውን ምሁራዊ ማዕረጎችን በደፈናው በማንኳሰስና በመፈረጅ፣ አዋቂ የሆኑ መስሎ የመታየት አባዜ የተጠናዋታቸውን አንዳንድ ግለሰቦች አመለካካት የሚያንፀባርቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡  

ጸሐፊው ወዳነሱትና ካለፈው መጣጥፋቸው ቀጣይ አድርገው ወዳቀረቡት ፍሬ ሐሳብ እንመለስ፡፡  የፌዴራል ሥርዓትም ሆነ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት እንከን የለሽና ለሁሉም ችግሮች ያለቀለት መፍትሔ ይሆናል የሚል ንድፈ ሐሳባዊ ዕይታም ሆነ ተግባር የለም፡፡ ጥያቄው በአንድ አገር ውሰጥ ከነበሩና ካሉ ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎች አንፃር፣ በአንፃራዊነት ለአገሪቱ የተሻለ ይሆናል የተባለ ፖሊካዊና ኢኮኖሚዊ ሥርዓት  መምረጥ የግድ ይላል፡፡ እግረ መንገድ ለማስታወስ ያህል በ21ኛው ክፍለ ዘመን  ፖለቲካ ጉልበት ሳይሆን ምርጫና የተሻለ ሐሳብ በማቅረብ፣ የማሳመንና ተከታይ የማፍራይ ጉዳይ ነው፡፡ በአገራችንም የጉልበት ሳይሆን የዚህ ዓይነት ፖለቲካ እንዲዳብር የተወሰነ አስተዋጽኦ ለማድረግ ይመስለኛል በትንሹም ቢሆን በተለያየ መንገድ ከእርሶ ጀምሮ ሁላችንም ተሳትፎ የምናደርገው፡፡

ወደ ፖለቲካ ኢኮኖሚው ጉዳይ ስንመጣ የፖለቲካም የኢኮኖሚም ዳር ድንበር ግለ ነፃነት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አገርና ሕዝብ በጋራ ሊያስቀጥል የሚያስችል የዳበረ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት መገንባትም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ግለ ነፃነትን በተሟላ ሁኔታ መተግበር የሚቻለው አስቻይ ሁኔታዎች ሲፈጠሩና የግለ ነፃነቱን ከሐሳብ በዘለለ በተግባር እየተገለጸ እንዲሄድ የሚያስችል አሰተማማኝና የዳበረ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ሥርዓት መፍጠር ሲቻል መሆኑ፣ በኢኮኖሚም ሆነ በፖለተካ መስኩ የዳበረ ሥርዓት ፈጥረዋል ተብለው ከሚወሰዱት የምዕራባውያን አገሮች ታሪክ መገንዘብ የሚቻል ነው፡፡ በመሆኑም ለጸሐፊው የሁሉም ነገር ዳር ደንበር የሆነውን የግል ነፃነት ከንድፈ ሐሳብ በዘለለ በተጨባጭ በአገራችን  በዳበረና አስተማማኝ ሁኔታ በቀጣይነት ለመተግበርና ዋስትና የሚያገኝበት ሥርዓት ለመፍጠር፣ አሁን አገራችን ከምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀርና የዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግሥት አሰተሳሰብ  የተሻሉ አማራጮች አድርጎ መውሰድ ተገቢ ነው የሚል አስተሳሰብ አለኝ፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ሥርዓቱ የበለጠ ፌዴራላዊ፣ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እየሆነና  በሁለም መስክ የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነትና ነፃነት እየተረጋገጠና እየዳበረ እንዲሄድ የሚያስችሉ፣ በየሙያችን  በምርምር ላይ የተመሠረቱ አማራጭ ሐሳቦችን ማቅረብ በሚያጋጥሙ ችግሮች  ላይ መፍትሔ የሚሆኑ አማራጮችን ማመላከት ይመስለኛል፡፡

ጸሐፊው የፌዴራል ሥርዓቱ በተግባራዊ እንቅስቃሴ ወቅት ሊያጋጥመው የሚችለውን ችግር አሰመልክተው ሲገልጹ፣ የፌዴራል መንግሥቱ ብሔራዊ አጀንዳ ለመቅረፅ ከዘጠኝ ጥርሶች (ክልሎች) ጋር ለመመካከር ሲታሰብ፣ ከዘጠኙ ጥርሶች ውስጥ ቡድንን ተገን አድርጎ የግል አጀንዳውን የሚያራምድ በጥባጭ አያጣውም በማለት አስቀምጠዋል፡፡  በመጀመርያ ደረጃ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግልጽ የሆነ ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ክፍፍልን መሠረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ አካላት ሲሆኑ፣ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51 በግልጽ እንደተመለከተው ብሔራዊ ፖሲዎችን የመቅረፅ ሥልጣን በግልጽ  ለፌዴራል መንግሥቱ የተሰጠ በመሆኑ ተግባሩ የፌዴራል መንግሥቱ ነው፡፡

ሆኖም በፖሊሲዎች አፈጻጸምና ተዛማጅ ጉዳዩች በሁለቱ መንግሥታት መካከል በተለያየ ቅርፅና ይዘት ትስስር መኖሩ የማይቀር በመሆኑ፣ ትስስሩ የሚሳለጥበትና የሚቀናጅበት የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ፈጥሮ መንቀሳቀስ  በዓለም ላይ በሚገኙ በሁሉም የፌዴራል መንግሥታት የተለመደና ቅቡል ተግባር ነው፡፡ በአገራችን የፌዴራል ሥርዓት ይኸው ግንኙነት በተለያዩ አግባቦች እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቀጣይም የመንግሥታት ግንኙነቱ የበለጠ የሚዳብርበት፣  የሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ክፍፍሉን በማይነካ መንገድ ሕግና ፖሊሲ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት በዚህ ላይ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ከሙስናና ከብልሹ አሠራር ጋር በተያያዘ ዋናው ምንጩ የሥነ ምግባርና የሞራል ዝቅጠትና ቅጥ ያጣ ግለኝነት፣ እኔ ከዘረፍኩ ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ገደል ይግባ ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ሙስና በባህሪው ለማኅበረሰባዊ ልማት በብዙ አቅጣጫ ጥፋት የሚያስከትል ጠንቅ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ በአገራችን ሁኔታ ሙስና ምንም ከሌለውና መሠረታዊ የሆኑ አገልግሎቶች ካልተሟሉለት ማኅበረሰብ ጉሮሮ ነጥቆ የመውሰድ፣ አንዳንድ ጽሐፍት እዳስቀመጡት ሀብት (From the Needy to the Greedy) የሚፈስበት እኩይ ተግባር ነው፡፡ ምንም እንኳ ሙስና ማንኛውንም የኢኮኖሚ  ልማት አስተሳሳብ የሚከተሉ መንግሥታት የሚፈታተን ቢሆንም፣ በተለይ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡበት ከ1960ዎቹ ጀምሮ በሌለ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መሠረት ላይ ነፃ የገበያ ሥርዓት እንከተላለን ባሉ ብዙ የአፍሪካ አገሮች መንግሥታት ወደ ከፋ ኢኮኖሚ ውድቀትና ትርምስ ከቷቸዋል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት የልማታዊ መንግሥት አሰተሳሰብን የተከተሉ የምሥራቅ እስያ አገሮች ለእነሱም ሙስና ፈታኝ ነበር፡፡ ግን ፈተናውን አልፈው ዕመርታዊ ለሆነ የኢከኖሚ ልማት እንደበቁ  በአሁኑ ወቅት  አጠቃላይ ዕወቀት ተደርጎ የሚወሰድ ጉዳይ ነው፡፡

በመሆኑም ልማታዊ መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ባለው ረዥም እጅ ምክንያት ለሙስና ተጋላጭነቱ የሰፋ ይሆና የሚል አሰተሳሰብ ያለ ቢሆንም፣ የልማታዊ መንግሥት ባህሪያትን በእርግጥም በትክክል አሟልቶ ከተንቀሳቀሰና ዴሞክራሲዊ ከሆነ የሙስና ተግባራትን የመቋቋም አቅሙ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ኅብረተሰቡ በየደረጃው በሁሉም ተግባራት የሚሳተፍበት ሁኔታ ስለሚፈጠር ሙስናን አሸንፎ የዳበረ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚፈጠርበት አቅጣጫ ተከትሎ መሄድ ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡ በብሔር በብሔረሰብ ሽፋን የተሸጎጡ ሙሰኞችም በዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት አስተሳሳብ አግባብና በብሔሩ ሰፊ ሕዝብ ሙሉ ተሳትፎ እየተወገዱ የሚሄዱበትን አግባብ መፍጠር ይቻላል፡፡ ሙሰኝነትና ያላግባብ የመጠቀም ፍለጎት ለብሔሩ የራስ አስተዳደርም ሆነ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በጋራ የመልማትና በፌዴራላዊና በዴሞክራሲያዊ አግባብ አብሮ መኖር ከፍተኛ መሰናክል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

‹በዘመነ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ሉላዊነት ትልቁ ጉዳይ የግል ነፃነት ሆኖ ሳለ፣ ብሔርን መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ ከዘመኑ ጋር የሚመጥን ፍልስፍና ካለመሆኑም በላይ ከ“Shared-Rule” እና “Self-Rule“ ጋር ተያይዞ “Self-Rule“ የፌዴራል አደረጃጀቱን ትተን ራስን በመግዛት ፍልስፍና ብናየው› የሚል ሐሳብ በጸሐፊው መቅረቡ ይታወሳል፡፡ በዘመነ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅና ሉላዊነት (Globalization) ማኅበረሰባዊ ፖለቲካል እንቅስቃሴው እሳቸው እንዳሉት አንድ ዓይነት መልክ ያለው (One Dimensional)  በግለሰብ ነፃነት ላይ ብቻ ያጠነጠነ ሳይሆን፣ በሁለት ዓይነት (Two Dimensional) በሆነ አግባብ እየሄደ ያለ መሆኑን ማየት ተገቢ ነው፡፡ በአንድ በኩል ሰፊ የሆነ ሉላዊ የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ ፍሰትና የአገሮች መተሳሰር ያለ ነው፡፡ በዚህም ማዕቀፍ ግለሰቦች የራሳቸውን ምርጫ በራሳቸው ለመወሰን የሚያስችል ሰፊ አማራጮች የሚፈጠርበት ገጽታ ያለው እንቅስቃሴ ያለ ቢሆንም፣ “ለግለሰብ ነፃነት“ ወሳኝ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ግለሰቡ የአንድ ማኅበረሰብ አባል ሆኖ በሚኖርበት ከባቢ ባሉ አስቻይ ሁኔታዎች የሚወሰን ይሆናል፡፡

ለምሳሌ የካፒታል ዝውውር ድንበር ዘለለ የመሆኑን ያህል የሠራተኛ እንቅስቃሴ ድንበር ዘለለል የሆነበት ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ በቀጣይም ሉላዊ በሆነ መልኩ በቀላሉ ይፈጠራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሁለተኛው የልዑላዊ ዓለም የእንቅስቀሴ አቅጣጫ ደግሞ ማንነትን መሠረት አድርጎ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ ይህም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሰው ልጆች የእኔን ማንነት ያላቀፈ ሉላዊ  ማኅበረሰብ ትርጉም የለውም ብለው የሚያስቡና የማኅበረሰብ ባህል ከሌሎች ባህሎች ጋር እኩል ዕውቅና እንዲያገኝ፣ ቋንቋቸው በሕዝባዊ፣ በአስተዳደራዊ፣ በማኅበራዊና በሌሎች መስኮች ሥራ ላይ እንዲውል፣ ታሪካቸው እንዲጻፍና ባህላቸው እንዲጠበቅ ከዚያንም አልፎ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁለተኛው የዘመኑ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ይህም በዓለም ደረጃ ተቀባይነት አግኝቶ በተወሰኑ አገሮች በፌዴራሊዝም የፍልስፍና አግባብ በሌሎች አገሮች የብዝኃ ባህል (Multiculturalism) አስተሳሰብና ፖሊሲ የግል ነፃነትን በማራመድ ግንባር ቀደም ናቸው በሚባሉ አገሮች እንኳ ሳይቀር መተግበር ከተጀመረ ቆይቷል፡፡

እኔ ከማኅበረሰብ ውጪ የሆነ በአየር ላይ የቆመ የግል ነፃነት አለ ብዬ አላምንም፡፡ የግለሰቡ ነፃነት ከማኅበረሰቡ ነፃነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘና የራስ ነፃነትን ሲሹ፣ የሌላውን ነፃነት ላለመጋፋት እርግጠኛ መሆንን የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡

በመንግሥትና በማኅበረሰብ ግንኙነት ታሪክ መንግሥት ባህልን በተመለከተ ዓለማዊ (Secular) ሊሆን ስለማይችል በብሔራዊ ቋንቋ፣ በሚዲያ፣ በአስተዳደርና በፍርድ ቤቶች የቋንቋ አጠቃቀምና በትምህርት ቤቶች፣ ወዘተ. በታቀደ መንገድም ይሁን በታሪክ አጋጣሚ የአንድን ብሔር ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና ወዘተ. ሊጠቀም ይችላል፡፡ የባለ ብዙ ብሔርና ባህል በሆነ አገርና ባለፉት ሥርዓቶች መድልኦ ተደርጎብናል ብለው እስከ ትጥቅ ትግል በተካሄደበት አገር፣ የግለሰብ ነፃነትህ እስከተጠበቀ ድረስ ብሔራዊ ማንነትህ  አስፈላጊም ወሳኝም አይደለም በማለት ጀሮ ዳባ ልበስ ብሎ ማለፍ ይቻላልን? የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደርና በአገር ደረጃ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ ፌዴራላዊ አደረጃጀት ከመከተል ጋር ተያይዞ፣ ከዚህም ከዚያም የሚፈጠሩ ችግሮች ሥርዓቱ እስካሁን ካስገኘውና ወደፊትም ከሚያስገኘው ጠቀሜታ ሊወዳደሩ የማይችሉና ሊፈቱ የሚችሉ አይደሉምን? መቼም የሰው ልጅ የመላዕክት  ስብስብ ስላልሆነ ከችግር ሙሉ በሙሉ የፀዳ ሥርዓት ይፈጥራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ዋናው ነገር ችግሮች ሲፈጠሩ የሚፈቱበት ተገማች የሆነ ሥርዓት ፈጥሮ መንቀሳቀስ ነው፡፡ ስለሆነም ከላይ የቀረቡት ጥያቄዎች ሳይንሳዊ በሆነ  አግባብ በዘርፉ ሙያተኞች  ቢፈተሹና የተሠሩ ጥናቶችም ካሉ ለማኅበረሰቡ በተለያየ አግባብ ተደራሽ ቢሆኑ  በሥርዓቱ አደረጃጀት፣ አሠራርና በየጊዜው በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ደረጃውን የጠበቀ መግባባት እየፈጠሩ መሄድ ይቻላል እላለሁ፡፡

በብሔረሰብ ሽፋን ያላግባብና ያለውድድር ለመጠቀም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች  ፍትሐዊ ካለመሆናቸውም በላይ፣ ተወዳዳሪነትንና ውጤታማነትን ይጎዳሉ ተብሎ የቀረበው ሐሳብ ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም ችግሩ በማንኛውም አደረጃጀት ውስጥ የሚከሰት  ቢሆንም በአገራች ሁኔታ በክልል ደረጃ የሚከሰቱ ችግሮችን ራሳቸው ክልሎች ወይም ብሔሮች በብሔራቸው ስም ያላግባብ ተጠቃሚ ለመሆን የሚነግዱባቸውን አካላት እንዲታገሏቸው ዕድል መስጠት ተገቢ ነው፡፡ እንደ አገር የተጠናወተነን ሙስናና ያላግባብ የመጠቀም አባዜ ለመመከት ወሳኙ ተግባር የተስተካከለ ሰብዕና ያለው ትውልድ መፍጠር ነው፡፡ በሥነ ምግባርና በሥነ ዜጋ ላይ ከቤተሰብ ጀምሮ በትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም በተለያዩ የማኅበረሰቡ አደረጃጀቶች ሰፊ ሥራ ማከናወን የሚጠይቅ ሲሆን፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት የአሠራር ሥርዓት እያጎለበቱ መሄድ የግድ የሚል ይሆናል፡፡

የሰው ልጅ ራስ ወዳድ የሆነ ሥነ ልቦና ብቻ ነው ያለው  የሚል አሰተሳሰብ የለኝም፡፡ የሰው ልጅ ከራስ ወዳድነት ሥነ ልቦናው ጋር ማኅበራዊና ሥነ ልቦናም ያለው መሆኑ በተለያዩ ፈላስፎች በተደጋጋሚ የተገለጸ ጉዳይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከማኅበረሰብ ውጪ ሰውነቱን ራሱን ማረጋገጥ እንኳን አይችልም፡፡ የሰው ልጅ ከማኅበረሰብ ውጪ ዕርዳታ ቢስ አሳዛኝ ፍጡር ነው፡፡ የሰው ልጅ ማኅበራዊ ስለሆነና በተፈጥሮው ማኅበራዊ የመሆን አስገጃጅ ሁኔታዎች ስላሉበት ነው፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥታት ድረስ ባሉ የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አደረጃጀቶች ውስጥ የኖረውና እየኖረ ያለው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የፌዴራሊዝም ጥናት ተመራማሪዎች የሰውን ልጅ ባህሪ ለፌዴራሊዝም ፍልስፍና የተመቸ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ምክንያቱም ፌዴራሊዝም እንደ ፍልስፍና የግልህን ጉዳይ በግል፣ የጋራ ጉዳይህን በጋራ ለማከናወን ዕድል የሚሰጥ የአስተዳደር ሥርዓት ፍልስፍና በመሆኑ፡፡

ለማጠቃለል ያህል የግል ነፃነት ተፈላጊነት ያለው ጉዳይ ቢሆንም፣ ነፃነቱ ከማኅበረሰብ ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ተለይቶ ለብቻው መቆም የሚችል አይደለም፡፡ የግል ነፃነት በተገቢው መንገድ ለመጎናጸፍ የሚያስችሉ አስቻይ ሁኔታዎች በማኅበረሰብ ደረጃ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካው ዘርፍ እስካልተፈጠሩና የሚፈጠሩበትን አቅጣጫ ተከትለን እስካልተጓዝን ድረስ የግል ነፃነት ከንድፈ ሐሳብ (Theory) ያለፈ አይሆንም፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በፌደራሊዝም ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው  tayehaileyesus3@gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles