በጌታቸው አስፋው
ታሪኩን ከሥር መሠረቱ ለመከታተልና ለመሳተፍ ለሚፈልግ ሰው እኔ ሰኔ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ‹‹የልማታዊ መንግሥትና የብሔር ፌዴራሊዝም የማይታረቅ ቅራኔ›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ አወጣሁ፡፡ ለዚያ መልስ አንድ ምሁር፣ ‹‹ፌዴራላዊ ሥርዓትና ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ያላቸው ተመጋጋቢነት›› በሚል ርዕስ ሐምሌ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. መልስ ሰጡ፡፡ እንደገና እኔ ሐምሌ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ለግንዛቤ የሚረዳ መረጃ ሰጠሁ፡፡
ወደ መጀመርያው ጽሑፌና በመልስ ሰጪው ወደ ተነሱት ነጥቦች ተመልሼ ለውይይት የሚረዱ ነጥቦችን አነሳለሁ፡፡ መልስ ሰጪዬ የፌዴራሊዝም ፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ሲሆኑ፣ እኔ ኢኮኖሚስት ነኝ፣ ጥሩ ቅንብር ነው እላለሁ፡፡ ምኞታችንና ዓላማችን መንግሥትና ሕዝብ ለሚሰጡት ውሳኔ ሙያዊ ዕውቀታቸው እንዲጨምር እንጂ ለሌላ አይደለም፡፡
እኔ ብሔረሰባዊ ፌዴራሊዝምና ልማታዊ መንግሥት በማይታረቅ ደረጃ ይቃረናሉ ስል፣ እሳቸው ይመጋገባሉ እንጂ አይቃረኑም ይላሉ፡፡ በዚህ ላይ ሰፋ ያለ ክርክር ብናደርግ አሁን ላለው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ፋይዳ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡
ሐሳቡ ከፖለቲካም ከኢኮኖሚም በይበልጥ በሰው ልጅ ቡድናዊ ማንነትን ለግል ጥቅም ፈላጊነት ሥነ ልቦና ላይ ያተኮረ ስለሆነ፣ ውይይቱ ካለ የሥነ ልቦና ምሁር ተሳትፎና ጥልቅ ምርምር የተሟላ አይሆንም፡፡
ዛሬ ላለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ትክክለኛ መፍትሔ የሚሰጥ ፖሊሲ ለመቅረፅ ከፖለቲካዊና ከኢኮኖሚያዊ ጥናትና ምርምርም በላይ ሥነ ልቦናዊ ጥናትና ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲካው ላይና ኢኮኖሚው ላይ ብቻ መሰጣት የለመድን ሰዎች ባይመቸንም፣ ሥነ ልቦናዊ ጥናትና ምርምር ባለመረዳዳት የሚከሰት ቅራኔና ግጭትን ያስወግዳል፡፡
የአገርና የክልል መሪ፣ ሚኒስትር፣ የሸንጎ አባል፣ ጄኔራል፣ ፕሮፌሰር፣ ዶክተር፣ የፖለቲካ ተቃዋሚ፣ ታጋይ፣ ወዘተ መሆን የፈለገ ሰው ድብቅና ግልጽ ዓላማው ምን እንደሆነ ተመራምሮ የሚደርስበት የሥነ ልቦና ምሁር ነው፡፡
በንግግር ቀለል አድርገን ያቀረብነው ነገር በድርጊትም ቀለል አድርገን የምንሠራው ከመሰለን ችግር ላይ እንወድቃለን፡፡ የእኔ ጥያቄ ሃያ አምስት ዓመት ተጉዘን እርስዎ እንደሚሉት፣ ዲሞክራሲያዊና ልማታዊ አስተሳሰብና ተግባር የተላበሰ አመራር፣ ሲቪል ሰርቫንት፣ ባለሀብትና የፌዴራላዊ ሥርዓቱና የልማቱ ተጠቃሚና ባለቤት የሆነ ማኅበረሰብ ፈጥረናል ወይ? ካልፈጠርን ምክንያቱ ምንድነው? የሚል ነው፡፡
ምክንያቱን ተመራምረን ካላወቅን ፈረንጆች እስከ ሚመራመሩልን እንጠብቅ ማለት ነው፡፡ ሰው ተመራምሮ የነገረንን ደግመን ለመናገር እስከ ማስትሬትና ዶክተሬት መማር ለምን አስፈለገ? በቀቀን የምትባለዋ ወፍም የሰማችውን ደግማ መናገር አያቅታትም ይላሉ ኢኮኖሚስቶች፡፡
ፖለቲካ ጉልበት ነው፣ ኢኮኖሚ ገንዘብ ነው፡፡ በዓለም ደረጃ ሕዝብን እየገዙ ያሉት ጉልበትና ገንዘብ በጋራ ስለሆነ ሁለቱን አጣምሮ የሚያከራክር መድረክ መፈጠሩ ጥሩ ነው፡፡ የእኔ እምነት በብሔር ፌዴራላዊ ቅርፅ መንግሥት የልማታዊ መንግሥት ብሔራዊ አጀንዳ፣ በቡድናዊ መብት ሽፋን በተጠቀለለ የግል ጥቅም አጀንዳ ውኃ ውስጥ ገብቶ እንደ ጨው ስለሚሟማ፣ ዲሞክራሲያዊና ልማታዊ አስተዳደር ለመገንባት ያስቸግራል፡፡ ስለሆነም ጉልበትና ገንዘብ መነጣጠል አለባቸው ነው፡፡
ሆድ ‹ድንጋይ አምሮኛል› ቢል ‹ጥርስ ከማን ጋር ተማክረህ ነው ያማረህ› አለው አሉ፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ብሔራዊ አጀንዳ ለመቅረፅ ከዘጠኝ ጥርሶች (ክልሎች) ጋር ለመመካከር ሲታሰብ፣ ከዘጠኙ ጥርሶች ውስጥ ቡድንን ተገን አድርጎ የግል አጀንዳውን የሚያራምድ በጥባጭ አያጣውም፡፡
በታሪክ ሒደት የተጎዱ አካባቢዎችና ሕዝቦች እኩል የመወዳደር አቅም እንዲያገኙ ልዩ ድጋፍ ማግኘት እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ፍትሐዊነትና ቅልጥፍና በጥንቃቄና በዝግታ ሚዛን ጠብቀው ካልተጓዙ፣ በሌለ ሀብት ፍትሐዊነትን አሰፍናለሁ ተብሎ ያለውንም ማጣት ይመጣል፡፡
የሰው ራስ ወዳድነት ቡድናዊ ማንነትን ያለውድድር ለግል ጥቅም ማግኛ መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀም መንገድ ሊከፍት ይችላል፡፡ ቀልጣፋ ‘Efficient’ እና ውጤታማ ‘Effective’ ያልሆነውን በቡድናዊ ማንነቱ ብቻ ሳያወዳድሩ መሾምና መሸለም አገርን ይጎዳል፡፡
በታሪክ ለተጎዱ ሰዎች የሚሰጥ ድጋፍ በባህል፣ በቋንቋ፣ በትምህርት፣ በጤና ጥበቃ፣ በመሠረተ ልማት፣ ወዘተ በመሳሰሉ የወልና መንግሥታዊ አገልግሎት መስጫ ዓይነቶች ቢሆን ምንም ዓይነት ጥያቄ አላነሳም ነበር፡፡
ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው አያስተዳድሩ አላልኩም፡፡ ጭልጥ ያለ የገበያ ኢኮኖሚ ተሟጋችም አይደለሁም፡፡ ገበያውን ገድሎ የአገር ሀብትን በመንግሥት እጅ ውስጥ አስገብቶ የግል አምራቹን ማቀጨጭ አያዋጣም፡፡ የልማት ኢኮኖሚውና የግል ገበያ ኢኮኖሚው ይመጣጠኑ ግን እላለሁ፡፡
የውይይት ባልደረባዬ የፌዴራሊዝም ረዳት ፕሮፌሰር ነዎት፡፡ ስለፌዴራሊዝም ሲናገሩም “Shared-Rule” እና “Self-Rule” ብለው አብራርተዋል “Self-Rule” ያሉት እስከ ምን ደረጃ እንደሚወርድ ባይገልጹም፣ ለእኔ ፖለቲካዊ መዋቅሩን ትተን ራስን በመግዛት ፍልስፍና ብቻ ብናየው “Self- Rule” እስከ ግለ ነፃነት ይወርዳል ብዬ አስባለሁ:: እስከ የአጎቴ ልጅ ይግዛኝ የአክስቴ ልጅ ይግዛኝ ቤተሰባዊና ብሔረሰባዊ ትስስር ብቻ የሚሄድ ከሆነ፣ ከዚህ ዘመን ቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር የሚመጥን ፍልስፍና አይደለም::
በጥንቱ ታሪክና ፍልስፍና የምናምን ሰዎች ግለ ነፃነት ደረጃ በደረጃ ከአገር ወደ ብሔረሰብ፣ ከብሔረሰብ ወደ ቤተሰብ፣ ከቤተሰብ ወደ ግለ ነፃነት ቀስ በቀስ እንዲመጣ እንፈልጋለን፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ግን መጥቆ ሕፃናት እንኳ ከወላጆቻቸው ትዕዛዝ ውጪ የሚሆኑበትን ጊዜ እያሳጠሩ ነው፡፡
ይህ ዘመን የቴክኖሎጂ እንደ መሆኑ የግለ ነፃነት ፍልስፍና ሥር ሰዷል፡፡ አንድ ፍሬ ሕፃናት የዕድሜ ደረጃቸውን ሳይጠብቁ ከወላጆቻቸው ቁጥጥር ውጪ መሆን የፈለጉበት ዘመን ላይ ነን፡፡ የግለ ነፃነት ፍልስፍና ከሁሉም በላይ መሆኑን የምናየው፣ ወጣቱ ትውልድ ለቴክኖሎጂ እንጂ ለፖለቲካ የሚሰጠው ትኩረት እየቀነሰ በመምጣቱ ነው፡፡ ወጣቱ ግዙም ተገዙም እኔን ግን አትንኩኝ የሚል የዝምታ መልዕክት እያስተላለፈ ነው፡፡ ለዚህ ነው የሃምሳዎቹንና የሥልሳዎቹን ዓይነቶች የተማሪዎች ረብሻ የማናየው፣ ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ቁጥርስ ስንት ነው?
ወጣቶች ራስን በራስ ማስተዳደርንና የራስ ጌታ መሆንን ከአሀዳዊ ወደ ፌዴራላዊ፣ ከፌዴራላዊ ወደ የጎሳ መሪ፣ ከጎሳ መሪ ወደ የቤተሰብ መሪ፣ ከቤተሰብ መሪ ወደ ግለ ነፃነት ለመሸጋገር ጊዜ አይጠብቁም፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ይንገሥ ማለቴ አይደለም፡፡ የወጣቱን ትውልድ ሥነ ልቦና ካላወቁ ሊመሩት ያስቸግራል ለማለት ነው፡፡
እያንዳንዱ ሰው የራሱ ጌታ ይሁን ወደሚለው ወደ ኮሙዩኒዝም ሥርዓት እንዴት እንደሚኬድ ስለቸገረ ተጠላ እንጂ፣ ራሱ ኮሙዩኒዝም አልተጠላም፡፡ ሰው ሁሉ በአስተሳሰቡ የራሴ ገዢ ራሴ ነኝ በማለት ወደ ኮሙዩኒዝም እየሄደ ነው፡፡
አሀዳዊ ፊዴራላዊ ብለን ሳንከፋፍል በፊት መንግሥትና የሕዝብ ንብረት ግንኙነት ምንድነው ብለን እንመልከት፡፡ መንግሥት የሕዝብ ንብረት ባለአደራ አስተዳዳሪ እንጂ መሸጥ መለወጥ የሚችል ባለቤት አይደለም፡፡
መንግሥት በሕዝብ ንብረት ላይ ማዘዝ የሚችለው ሕዝብ በሰጠው የማስተዳደር ሥልጣን ልክ ብቻ ነው፡፡ ለሚቀርፃቸው የሕዝብ ንብረት የሚያስወጡ ብሔራዊ ፖሊሲዎች፣ ዕቅዶች፣ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች የባለቤቱን የሕዝብን ይሁንታ ማግኘት አለበት፡፡ አለበለዚያ የአደራ ሰጪና የአደራ ተቀባይ ሚና ይዛነፋል፡፡
እርሶ ከጠቀሱት ከ1950ዎቹ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያሉት የሁለንተናዊ ልማት ትርጉሞች በኢኮኖሚ ልማት ጠባብ ትርጉም ብቻ ካልገደብናቸው፣ በግለሰብ ነፃነትና ግለሰብ ለሌላ ፍጡር ሳያጎበደድና ሳያቀነቅን ራሱን በራሱ የመምራትና የማስተዳደር አቅም ማግኘት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
ኢኮኖሚስቶች ምን እንደሚሉ ያውቃሉ፡፡ መንግሥት የሕዝብን ንብረት ገዢና ሻጭ ሲሆን፣ ከሸቀጦች በፊት የሚገዙትና የሚሸጡት የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ራሳቸው ናቸው ይላሉ፡፡ አሁን እኛ እንደተቸገርንበት ሙስና ይንሰራፋል ማለታቸው ነው፡፡
ስለዚህ የገበያውን ለገበያው የመንግሥትን ለመንግሥት ብለን፣ የገበያው ምን እንደሆነ የመንግሥት ምን እንደሆነ መለየት አለብን፡፡ አሁን ባለው የተደበላለቀ ሁኔታ ብዙ አንጓዝም፡፡
የእኔ ዋናው ሐሳብ እርስዎ በመልስዎ ይህ ቢሆን ያ ቢሆን ያሏቸው ብዙ ነገሮች ለራስ ወዳድ ሰው ሥነ ልቦና የሚዋጡ አይደሉም ነው፡፡ ምክንያቴም ሀብት ከገበያ ሥርዓት ውጪ በልማታዊ መንግሥት ሲከፋፈል፣ በብሔር ፌዴራላዊ ሥርዓት የተከፋፈሉ ሰዎች ቡድናዊ ማንነታቸውን ለቡድኑ የጋራና የወል ጥቅም ሳይሆን ለግል ጥቅም ያውላሉ ነው፡፡
ከሰሞኑ ተጨባጭ ሁኔታ አንድ ምሳሌ ልስጥዎት በአዲስ አበባ ከተማ ለኦሮሚያ ክልል ስለሚሰጠው ጥቅም በአሜሪካን ድምፅ ሬድዮ በምሁራን ውይይት ሲካሄድ ሰምቼ ነበር፡፡ በአገር ውስጥም ምሁራን በግል ይከራከሩበታል፡፡ በግልጽ ቢወያዩበት ቀላል የሆነ ነገር ከባድ መስሎ ታይቷል፡፡ ለፖለቲካዊውና ለኢኮኖሚው ተገቢውን ቦታ ለመስጠት ጥሩ አጋጣሚ ስለሆነ እንኳን በዚህ ወቅት ተነሳ እላለሁ፡፡
እንኳንስ ብዙ የሕዝብ ቁጥር ያላት ኦሮሚያ ማንኛውም ሌላ ብሔረሰብ ቋንቋውን፣ ባህሉን፣ ወዘተ ብሔራዊ ቋንቋና ብሔራዊ ባህል እስከ ማድረግ ማንኛውንም ሰላማዊ ትግል ቢያደርግ ሌላው ሊያከብርለትና ሊደግፈው የሚገባ ነገር ነው፡፡ የሚቃወም ሰው ያለም አይመስለኝም፡፡ በግል ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ግን ገበያው ለእያንዳንዱ እንደ የውድድር አቅሙና የሥራው መጠን ይከፍለዋል እንጂ፣ በቡድን ትግል ማግኘት አይቻልም፡፡
የገዛ አባቱን ‹አቆርቋዥ አድሀሪ ነህ› ካለው የስልሳዎቹ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን ወጣት አብሮ በመኖር አውቃለሁ፡፡ ‹አንተ ግዛኝና ብቻ አንድ እንሁን አገር አትከፋፈል› የሚል አገር ወዳድ የአንድነት ኃይል እንጂ፣ ‹አንድ ሆነን እኔ ልግዛ› የሚል የአንድነት ኃይል አልገጠመኝም፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ አገር ከሚከፋፍል ኤርትራንና ኢትዮጵያን አዋህዶ ቢገዛ የሚመርጡ የአንድነት ኃይላት ብዙ ናቸው፡፡ ‹አንድ እንሁንና እኔ ልግዛ› የሚል የአንድነት ኃይል ካለ የጨለማው ዘመን ሰው መሆን አለበት፡፡
የእኔ የግሌ እምነት ደግሞ በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ድንበርም እንኳ ወንጀልን ለመከላከል ካልሆነ በቀር ለምንም አይጠቅምም የሚል ነው፡፡ ሰው የፈጠረው አከላል ስለሆነም ዓለም አንድ የገበያ መንድር ትሁን የሚሉ ልዕለ ኃያላን አገሮች፣ የካፒታልን እንደ ልብ ድንበር ተሻግሮ መሥራት ብቻ ሳይሆን ሠራተኛም በፈለገው አገር ሄዶ የመሥራት መብቱን ሊያከብሩለት ይገባል የሚል ነው፡፡
ቻይናዊ፣ ህንዳዊ፣ ቱርካዊ፣ ጃፓናዊ ኢንቨስተር በግል መጥተህ ገበያው በሚፈቅድልህ ልክ ሠርተህ ተጠቀም እያልን እኛው፣ እንዴት ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም በቡድን ማንነት ለመከፋፈል እንሞክራለን? ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚሳሳቱት የሰው እንገልብጥ ብለው ሲነሱ ነው፡፡ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት ከሜሪላንድና ቨርጂኒያ ተቆርሳ ዋና ከተማ በሆነችው ዋሽንግተን ክፍለ አገሮቹ ጥቅም ያገኛሉ ተብሎ ያንኑ ፍልስፍና በዚህ አገሬ ዓለም ሁሉ ነው በሚባልበት የግሎባላይዜሽን ዘመን ለመገልበጥ መነሳት ስህተት ነው፡፡ እንደሚመስለኝ በሽግግር ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ጎርፈው የአሜሪካን ወግና ልማድ ወደ ኢትዮጵያ ለመገልበጥ ባሰቡ ዳያስፖራዎች የተጠነሰሰ ነው፡፡
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በእኩልነትና በውድድር ሊያገኘው የሚገባው የገበያ ሸቀጥ በልማታዊ መንግሥት እጅ ሆኖ በራሽን ለአንዱ ሲሰጥ ለሌላው ሲከለከል፣ በቡድን ማንነቱ የግል ጥቅም ለማግኘት የሚሯሯጥም አይጠፋም፡፡ አድልኦ ተደረገብኝ ብሎ የሚከፋውም ይኖራል፡፡ ግለሰብ በብሔር ማንነቱ ገበያው ያልሰጠውን ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የማግኘት መብት የለውም የሚል እምነት አለኝ፡፡
በልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚያዊ አስተዳደር መንግሥታዊ ንብረትና የገበያ ንብረት ተደበላልቀዋል፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ቡድናዊ ማንነትን በተፈጥሮው ራስ ወዳድ ሰው ለግል ጥቅም የመጠቀም ሥነ ልቦናዊ ጉጉት አድሮበት፣ የጋራ የነበረውን የግል ለማድረግ ይጣጣራል የምለው፡፡ ባሳለፍናቸው ሃያ ስድስት ዓመታት ላይ ላዩን በአገርና ሕዝብ ወዳድነት ፖለቲካ ጨርቅ ተሸፋፍነው ውስጥ ውስጡን በስርቆትና በዝርፊያ ድርሻቸውን እያነሱ የኮበለሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትሮች፣ አፈ ጉባዔ፣ ኮሚሽነሮች፣ የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ አምባሳደሮችና ሌሎች ባለሥልጣናትን ቆጥረን አንጨርስም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡.
Clik here to view.
