በተፈሪ የማነ
ለወትሮ ባለታይም (ባለጊዜ ማለት ነው) እንደምነህ ብሎ ሰላም የሚለኝ ቢኒ የምንለው ጓደኛችን ሰሞኑን ስንገኛን በተደጋጋሚ አየህ የእናንተ የፖለቲካ አስተሳሰብና ውጤቱ ይለኝ ጀመር። የነማን? ብዬ ስጠይቀው የእናንተ ብሎ ይደግምልኛል። እኔም እንደ አፄ ኃይለ ሥላሴ የጥቅል ጨዋታ ለምዶብሃል። ለይተህና ወስነህ መናገር ተለማመድ ካልኩ በኋላ የትኛው አስተሳሰብ? የትኛው ውጤት? ሳልለው ነገሩን ዘልዬ ደህና ዋልክ ብዬ ጨበጥኩት። ሁሉም እንዳንተ ቢሆን ምን አለበት አለና ዛሬ ላሳየኸው የተለየ ፀባይ ደብል ማክያቶ ይገባሃል ብሎ አስተናጋጅዋን ጠራት።
ሂላሪ የሚል ቅፅል የሰጠናት አስተናጋጅ አቤት ብላ ስትመጣ ለባለታይም ደብል ማክያቶ ሲላት አንተ ግን ለምን እሱን ለቀቅ አታደርገውም? አለችው። ቢኒ የአፀፋ መልስ ለመስጠት ወደ ኋላ አይልም፡፡ ሼር አለሽ እንዴ? አላት። ምኑ ላይ? ስትለው ጠረጴዛው ላይ አላት። አልገባትም ወይም ትርጉም አልሰጠችውም መሰለኝ ጨዋታዋን እንዲህ ስትል ቀጠለች። እሱን እያየች እውነቴን ነው ከአንተና ከእሱ ማን ነው ባለታይም? አለችው። ምነው? አላት በጣም የሚያደናግርና ግልጽ ያልሆነ ጥያቄ። እኔ ጣልቃ ገባሁና መልስ አቅርብ አልኩት። የማላውቀው ነገር አለ እንዴ? ብሎ ነገሩን ሩቅ ሊወስደው ሞከረ። አጅሪት ቀላል አይደለችም መወዝወዙን ተውና ቅልብጭ ያለ መልስ ስጥ ስትለው፣ ይኼ አሁን ያልሽው ለጥያቄ ይበቃል ብለሽ ነው ብሎ ለእኔ አጭር ሻይ ሲላት፣ ዛሬ አልለቅህም እንዲያውም የሰሞኑ ግርግር ላይ ሳትኖርበት አትቀርም አለችው። አንቺ እኮ ባስሽብኝ ሲላት እውነቴን ነው ዛሬ አልለቅህም። ይኼ ምስኪን ሰው ባለታይም እያልክ ሥጋና ደሙን ጨረስከው እንዳለችው ይህን ያህል ካሰብሽለት ሥጋና ደሙም ካለቀ ኬክ ጨምሪለት ብሎ እንደተለመደው አሾፈ። ቢኒዬ ሁላችንም ባለታይም እንድንለው እንዳንተ ዓይነቱን መኪና ስጠው ወይም እንዲያገኝ አድርገው አለችው ለስለስ ባለ ድምፅ። የኔ መሰለችሽ እንዴ የእሱ እኮ ናት ሲፈልግ ይወስዳታል ሲፈልግ ይሰጠኛል ሲላት ለጠጥ ባለ አነጋገር፣ ኧረ እባክህ ካለች በኋላ ጭቃ አትርገጥ ብላ ወደ ባሬስታው አቀናች።
እንደተለመደው ባለታይም ብሎ ጠራኝና ዛሬ እኮ ኃይለኛ ደጋፊ አገኘህ ነገሩ እንዴት ነው? ሲለኝ ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ነው አልኩት። የት ያለ ኢትዮጵያዊነት ሲለኝ ማዶ የሚጮኸው ዳያስፖራ በማለት ሁለታችንም በሚገባን አነጋገር መለስኩለት። ኧረ ዛሬ እንዴት ነው? ሲለኝ እኔም እንዴት? አልኩት። ጨዋታ ጨምረሃል ብዬ ነው ብሎ በስድ ንባብ አዜመ። ቀጥሎም ዛሬ እንዴት ተገለጠልህ? ምኑ? ስለው ኢትዮጵያዊነት አለኝ። መቸስ ተሰውሮኝ ያውቃል። ደግሞ በአገራዊነት ጉዳይ እኔ አይደለሁ የምቀድምህ? ብዬ ስጠይቀው ጨዋታችንን ወደ ኢትዮጵያዊነት ስላዞርከው ብቻ ተመቸኸኝ ብሎ ዳንስ ቢጤ መሆኑ ነው ትከሻውን ወዘወዘው።
እንወራረድ! ዘረኝነት ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ይበለጽጋል ብዬ ለውድድር ጃስ አልኩት። መስሎሃል ብሎ ሞጋቼ ጨዋታችንን ለማጠየም ሞከረ።
ሙግታችን በበላ ልበልሃ እንዲሆን አሁንም ዘረኝነት ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ይበለጽጋል ብዬ ወጠርኩት። ሁሉም ዓይነት ጥፋት በወያኔ ላይ የሚደፈድፈው ሞጋቼ ኢሕአዴግ እያለ? በኢሕአዴግ መስመር? ኢትዮጵያዊነት ሊበለጽግ አለኝ። በቀላሉና ‘ጀንተል’ ባለድምፅ አዎን አልኩት። አይታሰብም ሲል መለሰልኝ። ምክንያት እናቅርብ ስለው ከማኪያቶ በኋላ አለኝ። የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ተነስቶማ ከማኪያቶ በኋላ አይባልም ብዬ ሳልጨርስ ነጠቅ አደረገና ስለሌለ ኢትዮጵያዊነት ለምን ታከራለህ ብሎ በአሪፍ ስሜቴን ለማቀዝቀዝ ሞከረ። ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገኝ በቅርብ ያለውን ውብ ኢትዮጵያዊነት ይኸው ብዬ ካፌው ውስጥ እየተዝናና ያለውን ወጣት፣ አዋቂ፣ ጎልማሳ፣ ትግርኛ፣ አማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ጉራጊኛ፣ ሶማሊኛ፣ ጋምቤሊኛ... በአጠቃላይ ኢትዮጵኛ የሚናገር ታዳሚ ላይ በዓይኔ ዞር ዞር እያልኩ አሳየሁት። ምን ማለት ነው? አለኝ። ይኸው እንደኔና እንዳንተ የተለያየ ቋንቋ ያላቸው ቀይ፣ የቀይ ዳማ...ኢትዮጵያዊያን አብረው ይጫወታሉ፣ አብረው ይስቃሉ፣ አብረው ይወያያሉ ብዬ ነገሩን ካብራራሁ በኋላ መለስ ብዬ ፊቱን ሳየው መስሎሃል ብሎ ለሁለተኛ ጊዜ ጨዋታችንን ያለ ምክንያት ለማጨለም ሞከረ። እኔም ለሁለተኛ ጊዜ በምክንያት ላይ ተመሥርተን እናውራ አልኩ።
ማኪያቶው መጣ። ሞጋቼ ዘናጭ አይፎን ሲክስ የምትባል የሌባ ቀልብ የምትስብ ሞባይል አለችው። እሷን ከፈታት። ስማቸውን መጥራት ምን ያደርጋል በዩቲብ የሚያወሩ ሰዎች አሳየኝ። ወያኔ (TPLF) አንድነታችንን ገደል ከተተው ይላል አንደኛው ተናጋሪ። ሁለተኛውም እመኑኝ ወያኔዎች ለመገንጠል እየተዘጋጁ ነው ይላል። በአዳራሹ አሥራ ስምንት የሚሆኑ ተመልካች ወይም አድማጮች ይታዩኛል፡፡ እነሱ ደግሞ ያጨበጭባሉ። ከሞባይሉ መስተዋት ቀና ስል አየህ ይኼ ነው እውነቱ አለኝ። የእነማን አልኩት? የአገሪቱ ነዋ አለኝ። ኢትዮጵያን አታውቃትም ስለው ባለታይሞች ያውቋታል አለኝ።
ሞጋቼን አገርና ፖለቲካ የተለያዩ ናቸው ብዬ አስተውሎቱን ጠራሁለት። በዚህ እንስማማለን ብዬም ጠየቅኩት። ነበር! ግን እናንተ አያያዛችሁት አለኝ። ሞጋቼን አሁንስ ጨርሰህ ዘቀጥክ ስለው ደንገጥ አለና ወዴት? አለኝ። ወደ ታወረ ዘረኝነት አልኩት። አልክ? ሲለኝ ይኸው በድፍን እናንተ፣ እነሱ እያልክ ነው። እሺ ከመዝቀጥ ልትረፍ፣ ልውጣና ልሞግትህ ሲለኝ በምክንያት ተመሥርተን ብቻ ከሆነ አልኩት። ይስማማኛል ሲለኝ እጄን ሰጠሁትና ደስ በሚል ስሜት ጨበጠኝ። ሞጋቼን ዘረኝነት መባከን፣ ቁልቁል መሄድ፣ ለአተራማሽ፣ ለዘራፊ መመቸት እንደሆነ አብራራሁለት። አንተ ደግሞ እንዲህ ዓይነት ነገር አያምርብህም ብዬ ካሟሟቅኩት በኋላ እንወራረድ! ... ዘረኝነት ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ይበለጽጋል አልኩት።
ተጎንብሶ ከማኪያቶው ስኒ ሁለት ጊዜ ካነሳ በኋላ እባክህ ተወኝ ወያኔ እያለ አንድነት አይታሰብም ብሎ ተመልሶ ወደ አሮጌው ዜማ ገባ። ቀጥሎ ያ ፕሮፌሰር ብሎ ትንሽ ራሱን ከነቀነቀ በኋላ ሲለው የነበረ እኮ እውነት ነው። ይኼው ዘረኝነቱ ጫፍ ደረሰ አለ። ፊቱን ኮስተር እያደረገ አሁን የምንሰማውና የምናየው ነገር የማን ልጅ ነው? እንዳለኝ የቱ? እየሆነ ያለው? አሁን የጠቀስካቸው ሰዎች ፍሬ እንጂ የወያኔ ፍሬ አይደለም ብዬ ስመልስለት ገ..ለ..በ..ጥ..ከ..ው ብሎ ቀጥሎ አታምርር አለኝ። በአገር ጉዳይማ አመራለሁ አልኩት። እውነትን እውነት፣ ውሸትን ውሸት እያልን የመሰሪና ራስ ወዳድ ሰዎች ቃላት ተቃርነን ሰንካላውን አፍራሽ ሐሳብ ካላደረቅነው ይኼ የትም አይደርስም የሚል አባባል የስንት የዋህ ህሊና እንደሚያዛባ እያየኸው ነው አልኩት። ስለዚህ አታምርርን ተውና አምርረህ ተናገር በለኝ። የሆነውን፣ የተበላሸውን፣ የቀናውን፣ የተጠቀመውን፣ የጠቀመውን፣ ቆጥረንና ሠፍረን በግልጽ እናውራ። ወያኔም አጥፍቶ ከሆነ ከአገርም ከሕግ በላይ አይደለም ይቀጣል ስለው ወያኔ ማንም አይቀጣውም ዕድሜ እስከሰጠው ድረስ እየቀጣን ይኖራል፡፡ እባክህ ተወን የሚሆነውን እናያለን አለኝ።
ይህቺ ፍርኃት ሲሰማው የሚላት መደምደሚያ ሐሳብ ናት። ሞጋቼን ሰሞኑን መንግሥት የራሴን ስህተት ለማረም ዝግጁ ነኝ፣ በእኔ ውስጥ ያለውን አጥፊ እቀጣለሁ ብሏል ስለው ቀጣ እንዴ? ካለ በኋላ የሚቀጣቸው እነማን አንደሆኑ ታውቃለህ? ትናናሾቹ ናቸው። ብዙ አትጠብቅ ብሎ አፏጨ። እሱን በቀጣይ የምናየው ይሆናል። ለጊዜው ነብይ አትሁን ብዬ ይልቅ እነዚህ አሁን ያስደመጥከኝ የዩቲብ ሰዎች ያሉትን ነገር እንዴት ታየዋለህ? እውነት እነሱ በሚሏት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው እየኖርን ያለነው ወይስ እኔና አንተ ቀንና ሌሊት፣ ክረምትና በጋ፣ ትምህርት ቤትና ሥራ ቦታ፣ መዝናኛና ቤተ ክርስቲያን የምንሄድባት ኢትዮጵያ ናት ብዬ ወደ ጥንት ነገራችን ስመልሰው እኛ ያለንባት ኢትዮጵያ እነሱ እንደተረጐሟት ናት አለኝ። እውነትህን ነው? ብዬ ለማስረገጥ ጠየቅኩትና አዎ አለኝ። ያሳዝናል ከራስህ ጠፍተሃል ስለው እንዴት? ብሎ ሳቅ አለ። ኦ! ወዳጄ ልቤ መጀመሪያ ከራስህ ጋር ታረቅ አልኩት። ኢትዮጵያ በፌስ ቡክ፣ በዩቲብ ለጥፋትዋ እንደሚያቀነቅኑባት የኤርትራ ሕግደፍ ሰዎችና ሌሎች አይደለችም። ኢትዮዽያ ለዘመናት የኖረች ወደፊትም የምትኖር በታላላቅ እሴቶች የተገነባ ሕዝብ ያላት አገር ናት። ነጠቅ አደረገኝና ነበር አሁን ግን ነባር እሴቶቻችን ተመናምነዋል፣ አንተም አትሸወድ አለኝ። የትኞቹ ናቸው የተመናመኑት ስለው መከባበር፣ መተጋገዝ፣ ቅድሚያ ለወንድሜ ለእህቴ ይሁን እያሉ መደሰት፣ እውነት መናገርና ለእውነት መቆም፣ የራስህ ያልሆነውን መመኘት ነውር አድርጎ ማየት ቀርቷል። ስለዚህ ማሰሪያ የሌለው ዜጋ እየፈራባት ያለች አገር ናት አለና ሰማይና ምድሩን አጠቆረው። ሁሉም ለየራሱ ዘብ ቆመዋል። ይህ ደግሞ የተሸወዱ ፖለቲከኞች የፈጠሩት ነው አለኝ።
ማብራሪያ ስላስፈለገኝ እንዴት? ብዬ ሞጋቼን ጨዋታውን እንዲያደምቅ ዕድል ሰጠሁት። አየህ ለፖለቲካዊ አይዲዮሎጂ ሲባል ከዚያም ወረድ ባለ የደመቁ ፖለቲከኞች ሆነው ለመታየት ሲሉ የወያኔም ሆኑ ሌሎች የፖለቲካ ልሂቃን ነባሩን እሴት ታግለው ጥለውታል። አሁን ያለው ትውልድ በነባሩም በሰርጎ ገቡም የታመሰ ነው። ከመታመስ ለመውጣት ራሱን ብቻ የሚወድ ሆኗል። ከዚያ ከፍ ቢል ብሔሩን ይወድ ይሆናል። አገር፣ ኢትዮጵያዊነት የሚባሉ ነገሮች ለሁሉም በዚህች ቅድስት አገር ያለ ሕፃን፣ አዋቂ፣ ፖለቲከኛ፣ ሃይማኖተኛ፣ ሙያተኛና ነጋዴ በጣም ሰፊ ነገሮች ሆነውበታል። ዘረኝነት ግን በቀላሉ ራስህን የምትጠቅምበት ማረሻ ስለሆነለት ስለሰፊውና አንኳሩ ኢትዮጵያዊነት ግድ የለውም። ስለዚህ አንተ ይበለጽጋል የምትለው ኢትዮጵያዊነት መሠረቱ እየተናደ በሚያድር አገር ላይ የሞኝ ምኞት ከመሆን አልፎ ዋጋ የለውም ብሎ የሚያስፈራ የሐሳብ ናዳ አወረደብኝ።
ሁለታችንም ማኪያቶ ከያዙ ስኒዎቻችን ተጎነጨን። በተናገረኝ ነገር እጅግ ሐዘን ተሰማኝ። ተስፋዎቼን መፈለግ ጀመርኩ። ባልከው ሁናቴ ውስጥ ሆነንም ቢሆን ደማቅ ኢትዮጵያዊነት አለ ብዬ ጀመርኩ። እርግጥ ነው ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ዘራቸውን ወይም ብሔራቸውን ለመጠቀሚያ የሚያመቻቹ መኖራቸው እጋራሃለሁ።
ግን አንተ በምትለው ደረጃ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ጋብቻ፣ ኢኮኖሚ… በጥብቅ ያስተሳሰረው በመሆኑ አገራዊ ስሜቱ አንተ እንዳልከው በቀላሉ የሚናድ የበረዶ ክምር ሳይሆን ጽኑ የብረት አጥር ነው። እነዚህ ዘር ቀለም እየቆጥሩ የሚያወሩን በመሠረቱ ዘር የሌላቸው ዘረኞች ናቸው። ዘር የሌላቸው ዘረኞች ማለት ደግሞ ምን ማለት ነው? አለኝ። መጠየቅ መልካም ነው። እነዚህ የዘረኝነት አጥር ሽቅብ የሚገነቡ ሰዎች ዘራቸው ደምና አጥንት እንዳይመስልህ። የዘረኝነት መሠረታቸው ጥቅም ነው። ገንዘብ የሚሰጣቸው፣ የሚያቀብላቸው ሁሉ ዘራቸው ነው። በመሆኑም እነዚህ ዘር የሌላቸው ዘረኞች በሕዝብ መሀል ሁሌም እሳት ያነዳሉ፡፡ ሰው እየተቃጠለ እነሱ ይዘርፋሉ፣ይዝናናሉ…ይበላሉ።
ስለዚህ እንዲህ ያሉ ሰዎችን እያየን የኢትዮጵያዊነት መሠረት የምንለካ ከሆነ በመቶና በመቶ ሃምሳ ሰው መላ ኢትዮጵያዊያንንና የኢትዮጵያ ታሪክ በተሳሳተ መሥፈርት መገመት ይሆናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አንዳንዶቹ መቶ ሚሊዮን ሞልቷል እያሉ ነው። ከዚህ አኃዝ ተነስተን ስናየው ዘር የሌላቸው ዘረኞች ትንሽ ናቸው። ጥቂቶች በሽተኞች ለዘመናት የተገነባውን ኢትዮጵያዊነት አይጎዱትም። ለእነዚህ ሰነፎች ምላስና ሰንበር የሚያቀርቡ ኢትየጵያዊነታችንን የማይወዱ የኤርትራ፣ የግብፅ፣ የዓረብ አገሮች እጆች ድንበር ዘለው ገብተው ያግዙዋቸው ይሆናሉ። ይህ መጥፎ ነዳጅ ነው። ባንዳ መሆን ግን አዲስ አይደለም ድሮም የነበረ ነው። ጥቁር ሕዝብ ነጭን ማሸነፍ እንደሚችል ያሳየንበት ታሪካችንም ላይ የተወሰኑት ለሆዳቸው ያደሩ ተታለዋል። አርበኛው ኢትዮጵያዊ ግን ኢትዮጵያዊነትን ገንብቷል። እንወራረድ! ኢትዮጵያዊያን ራሳቸውን አሳልፈው ለባዕዳን መጫወቻ አይሰጡም። ሰሞኑን ያየናቸው የተሞከሩት የዘረኝነት ስሜቶች ይከስማሉ፣ ፌስቡክም ይደርቃል። በመልካም ሐሳቦች ተሞልቶ ይፀድቃል። እንወራረድ! ዘረኝነት ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ይበለጽጋል።
ሞጋቼ ስማ አለኝ። ዘረኝነት እኮ አንዳንድ ካድሬ የሚሰብከው የኑሮ ዘይቤ ሆኗል ሲለኝ ደነገጥኩኝ። እናም በድንጋጤ ለምን? አልኩት። በል አድምጥ እዚህ አገር ሰው የሚሾመው በመዋጮ ነው። ምን ማለትህ ነው? ስለው ኢሕአዴግ ከየብሔሩ አዋጡ እያለ ይሾማል። ስለሆነም በመዋጮ የሚሰበሰብ የሠለጠነም ያልሠለጠነም ካድሬ በየእርከኑ ያለ የመንግሥት አስፈጻሚ የሥልጣን ልጓም ይቀበላል። አስተውል ሥልጣን ያሰጠችው አቅሙ ሳትሆን ብሔሩ ናት። ስለዚህ ሥልጣን ከሰጠችው አገሩ በላይ ሥልጣን ያሰጠቸው ብሔሩን እንደ መሣሪያ ይጠቀማል። ሞጋቼ ቁም ነገር የሚመስል ነገር በማቅረቡ እንዴት? ብዬ አሁንም ጠየቅኩ። አየህ በመዋጮ የተሾመው ሰው የመንግሥት ሥልጣን ያላግባብ ሲጠቀም ቢያዝ ወይም ቢከሰስ የሌሎች ብሔር ተወላጅ ስላልሆንኩኝ እንጂ፣ ከእነሱ በላይ መቼ አጠፋሁኝ ብሎ በማንነቱ የተጠቃ አስመስሎ ያቀርባል። ሌላው ደግሞ የበለጠ ተፅዕኖ ፈጣሪ ወይም ተቆርቋሪ ሆኖ ለመታየት ሲፈልግ ወይ ደግሞ ተጨማሪ በጀትና ሥልጣን ለማግኘት ወረዳችን ወደ ሌላኛው ክልል ወይም ወደ ሌላ ዞን ይዛወርልን፣ ከወረዳነት ወደ ዞንነት ከፍ ይበልልን በማለት የዋሁን ያነሳሳሉ። ከፈለገም አንቀጽ 39 እንደ መጫወቻ ይጠቅሳል። ከሕዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሲቀርብለት እኔ ምን ላድርግ እንደ ሌላኛው ክልል እኩል መብት የለኝም ዕድል አይሰጠኝም ብሎ በሌላኛው ሕዝብ ያላክካል። መርዝ ይረጫል። ቀድሞም በችሎታው ሳይሆን የብሔር ተዋፅኦ እንዲኖር መሾሙን የሚያውቁት ነዋሪዎች ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚያቀርበውን የማምለጫ እንቶ ፍንቶ ባገኘው ሥልጣን ያገኘው እውነት አድርገው ይቀበሉታል። በመሆኑም ከኢትዮጵያ በላይ የሠፈራቸውን ጥቅም ይመለከታሉ። ስለዚህ እንዲህ ባለ ትስስር ያለ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት ያበለጽጋል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው አለኝ።
ማኪያቶውን እየጠጣህ አልኩት፡፡ እሱ አይቀርም አለኝ። ሞጋቼ ዛሬ ቋንቋውም ሐሳቡም ጠንከር ብሏል። ይሁን እንጂ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ዘረኝነት አገራዊነትን ሊያሸንፍ አይችልም። ይህ ጽኑ እምነቴ ብቻ ሳይሆን በአገራችን ተደጋግሞ ኢትዮጵያዊነት ዘረኝነትን በተግባር እያሸነፈ የመጣ በመሆኑ ልትፈጥርብኝ የፈለግኸው ሥጋት ትኩረት አልሰጠውም አልኩት። ነገር ግን የጠቀስካቸው ብሔር ቅድ የሆኑ ካባቸውን የሚያዘጋጁ ሕዝባቸውን የሥልጣንም የገንዘብ መጠቀሚያ ሊያደርጉ የሚፈልጉ ኃላፊነት የማይሰማቸው አገርን እንደ ሸቀጥ የሚያዩ የሸቀጥ ሰዎች እንደሚኖሩ አልክድም። ለምሳሌ ውድ ሞጋቼ እኔን ባለታይም ትለኛለህ። በተግባር ግን ባለታይም እንዳልሆንኩ አንተ ታውቃለህ። ነገር ግን እኔን ባለታይም እያልክ ከምናውቃቸው ሰዎች ጋር የአገሪቱን ዕድል በግዙፍ ጡጦ የምትጠባው አንተ ነህ። እንዳንተ የሚያደናግሩ ቅድም ያልካቸው በመዋጮ ወይም በጓደኝነት የተሾሙም የሾሙም አይጠፉም ብዬ ሐሳቤን ለመቀጠል ስዘጋጅ ቆይ ተረጋጋ አለኝ። እሺ ብዬ ዕድል ስሰጠው ሞጋቼ ማዶ ያለ ሕንፃ አሳየኝ። ምን ማለቱ እንደሆነ ገባኝ።እየተዝናናንበት ስላለነው ግዙፍ ሕንፃ ግን ግድ አልሰጠውም። ይኼስ አልኩት። ዝም አለ። እሱን ተውና ከእኔና ከአንተ ማን ነው ተጠቃሚ ስለው አታምርር አለኝ። ጥሩ እሺ እሱንም እንተወውና ማንም ምን ያህል ዘረኝነትን ቢሰብክ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገራዊ አንድነቱን ለድርድር አያቀርብም አልኩት። ምን ማለትህ ነው ቀረበ እኮ አለኝ። ባንተ ትርጓሜና ምኞት ስለው እንዴ ሰው እየተፈናቀለ ብሎ ዓረፍተ ነገር ሠራ። ማምለጫ የሌለው የወቅቱ እውነት ነው።
ሞጋቼን ይህን ክፉ ተግባር ማን ያደረገው ይመስልሃል ብዬ በጥያቄ ያዝኩት። በቦታው አልነበርኩም አለኝ። አንተስ እንደዚያ ያለ ነገር ታደርጋለህ ብዬ ጠየቅኩት። እኔ አላደርገውም እንዳለኝ በህሊናህስ እንዲያው እንደ ምኞት ነገር ይኖርህ ይሆን ስለው ኧረ በጭራሽ አለኝ። ታድያ ማን ይመስልሃል ስለው ሁሉንም እያቆሰለ ያለ በሽተኛው የኢሕአዴግ የአመራር አካል ተግባር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተገኘ አሉታዊ ውጤት ነው አለኝ። እግዚአብሔር ይስጥህ ብዬ ጨርሼ ሳላመሰግነው ሞጋቼ የበሽታው መንስዔ ግን አስተዳደራዊ ክልሎቹ ቋንቋ ተኮር በመሆናቸው ነው ብሎ ሙግታችንን ሊያሰፋው ሞከረ።
ይኼ እንኳን አመክንዮ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ያልከው የአስተዳደር ሥርዓት ዜጎች በራሳቸው ቋንቋ እንዲማሩ፣ እንዲተዳደሩና እንዲዳኙ ያስቻለ ነው። ይህ ደግሞ የዴሞክራሲ መሠረታዊ መርህ ነው። ይህ አሠራር በመተግበሩ የተገኘ ውጤት ደግሞ የአገሪቱ ልማት በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮዽያ መሆን አስችሏል። ከነ ጉድለቱ ኢትዮዽያ ሁሉም ዜጎችዋ የሚጠቀሙባት ትልቅ አገር ሆናለችም ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን አንተ ቅድም ያልካቸው በማይገባቸው ቦታ በመዋጮ የተሾሙና እኔ ያልኳቸው ዘር የሌላቸው ዘረኞች ይህን አሠራር መጠጊያ የሚያደርጉ አላጋጭ ተጠቃሚዎች ብዙ ነገር ለማመሰቃቀል ይሞክሩ ይሆናል እንጂ፣ ራስን በራስ እያስተዳደሩ አገርን መገንባት ጤነኛ አስተዳደራዊ አካሄድ ነው። ነገር ግን አስተዳደራዊ አወቃቀሩን ተገን አድርገው ብሔርተኝነትን የሚያጎለብቱ ከመተጋገዝ ጠላትነትን የሚሰብኩ ጤነኛውን አስተሳሰብ ጤና የሚያሳጡ የራሱ የድርጅቱ ጥገኞችና ሌሎች አልጠፉም። እነዚህ ሁሉ ግን ከነባራዊ እሴቶቻችንና ከተስፋዎቻችን በላይ ለመሆን የሚያስችላቸው መሠራት የላቸውም። ስለዚህ ዘረኝነት ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ይበለጽጋል፣ እንወራረድ!!
የሚያደርጉ የውስጥ ተጠቃሚዎች የውጭም የፌስቡክ ጦረኞቹ እንደሚሉት ትግራይና የትግራይ ሕዝብ ለብቻቸው በልጽገው ሌላው ከትግራይ በታች ከሆነ ለህሊናህ እተወዋለሁ እንዳልኩት፣ ወዲያውኑ እንደዚያ አላልኩም፡፡ ከአንዴም ሁለቴ ትግራይ ሄጃለሁ የትግራይን ሕዝብ ኑሮ አውቀዋለሁ፡፡ የዚያ የምስኪን ሕዝብ ሁኔታ ያሳዝናል አለኝ። የምታዝንለት ከሆነ ለፌስቡክ ጦረኞቹ ንገራቸው አልኩት።
አንተ ደግሞ ችግር አለብህ ነገሮችን ትደባልቃለህ ሲለኝ ምንና ምን ብዬ በጨዋነት ጠየቅኩት። የአንተ ችግር የሥርዓቱ አመራሮች ሲነኩ ትግራይ ተነካ ብለህ ነገሩን ትደበላልቀዋለህ አለኝ።
ከአዘጋጁ፡-ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው tefyem05@yahoo.comማግኘት ይቻላል፡፡
