በአብዮት ጌታቸው
በአዳራሹ ጥግ የተቀመጠው ሰው ከመድረኩ የተሰየሙት አረጋዊ ላይ ጣቶቹን እየቀሰረ ንግግሩን ቀጠለ፡፡ ‹‹ፕሮፌሰር ቾምስኪ እርስዎ ስለ አሜሪካ ሲናገሩ እኔ ስሰማ እነሆ ዘመናት መጥተው ዘመናት ሄዱ፡፡ ዛሬ ግን ራሴ ጠየቅኩ፡፡ ከፕሮፌሰር ቾምስኪ የእስካሁን ሐሳቦች ምን አተረፍኩ ብዬ? ምላሹም ይኼ ሆነ፡፡ ፕሮፌሰር ቾምስኪ ስለአሜሪካ መጥፎነት ሲገልጹ፣ ፀረዴሞክራሲያዊ መሆን ሲለፉ ከጎናቸው አጫፋሪ ሆኜ መኖሬን፡፡ ከዚህ በኋላ ፕሮፌሰር ስለትውልድ አገሬ መልካም ነገርን መስማት እንጂ መጥፎነቷን ስለማልፈልግ ይህን አዳራሽ ለቅቄ እንድወጣ ይፈቀድልኝ፤›› ብሎ ተሰናበተ፡፡ አረጋዊው ባለ ሙሉ ፕሮፌሰር ከአዳራሹ እየወጣ ያለውን ጠያቂ እየተመለከቱ ምላሻቸውን መስጠት ጀመሩ፡፡ ‹‹እኔ አሜሪካን አልጠላም፡፡ ብጠላት ኖሮ ጠልፎ የሚጥላትን ነገር እየተመለከትኩ በውድቀቷ ጊዜ መሳቅ እችል ነበር፡፡ ግን ለሱ የሚሆን ልብ የለኝም፤›› ለቾምስኪ መውደድ ማለት ችግሮችን ተናግሮ ሙሉነትን መናፈቅ ነውና፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ባለፉት ሁለት ዓመታት የመጣበትን መንገድ መዳሰስና ካለበት አጣብቂኝ የሚወጣበትን ነገር በሚመለከተው የመንግሥት አካል እንዲፈለግ ማሳሰብ ነው፡፡
መንደርደሪያ
ትዝ ይለኛል ከአሥር ወራት በፊት አንድ ድርጅቱን የለቀቀ ጋዜጠኛ ስለ ኢቢሲ የወቅቱ አመራሮች የሰላ ትችቱን በማኅበራዊ ድረገጽ አቅርቦ ነበር፡፡ ይህን የአመራሮች አምባገነናዊነት በተለይም የዋና ሥራ አስፈጻሚውን ፀረዴሞክራሲያዊ አካሄድ የሚያሳይ ጽሑፍ በርካታ የድርጅቱ ሠራተኞች አንብበው በሥራ ቦታ ትልቅ መነጋገሪያ አድርገውት ነበር፡፡ በጊዜው ማኅበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚ ያልነበሩ ጎልማሶችም በደርግ ወቅት ኦሮማይ ልቦ ለድ እንደተነበበት መንገድ ፕሪንት አድርገው በድብቅ ተቀባብለውታል፡፡ እዚህ ላይ አንባቢ ሊገነዘብ የሚገባው ጉዳይ በኢቢሲ ኤዲቶሪያል ሕግ መሠረት ማንኛውም ሠራተኛ የጣቢያውን ኃላፊዎች ሳያስፈቅድ ስለድርጅቱ ምንም ዓይነት መረጃ በየትኛውም መንገድ ማድረስ አይችልም፡፡ ከዚህ በመነሳትም እንዲህ ዓይነት ጽሑፎች ሲወጡ በአደባባይ ማንበብ የጸሐፊው ደጋፊ ያስብለናል የሚልም ፍርኃት በሠራተኛው ውስጥ መኖሩ በተደጋጋሚ የታየ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ምናልባትም ከአመራሩ አምባገነናዊነት የመነጨ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
ከላይ የተጠቀሰው በማኅበራዊ ድረገጽ የወጣ ጽሑፍ የድርጅቱ ሠራተኞች ስለ አመራሩ ያላቸውን አመለካከት በጉልህ ያመለከተ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ለዚህ ማሳያ ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል የተለያዩ ሠራተኞች በሐሰት የፌስቡክ አድራሻ የተለያዩ ወቀሳዎችን መሰንዘር መጀመራቸው፣ ቀድመው ድርጅቱን የለቀቁ ታዋቂ ጋዜጠኞች ጽሑፎችን በማኅበራዊ ድረገጾች ላይ በመውሰድ የድጋፍ ሐሳብ መስጠታቸው ሊጠቀስ ይገባል፡፡ ለመሆኑ የመልካም አስተዳደር ቅስቀሳ ልሳን ነኝ የሚለው ኢቢሲ ለምን በራሱ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ተሳነው? የድርጅቱ ንቅዘትስ ከየት ተነስቶ የት የደረሰ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ወደኋላ ያሉ ዓመታትን ለመፈተሸ እንሞክር፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በ2006 ዓ.ም. የአመራር ለውጥ በማድረግ የተለያዩ ተግባራትንና ዕቅዶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ በአዋጅ ቁጥር 858/2006 እንደገና በኮርፖሬሽን መልክ መቋቋሙን ተከትሎ የተለያዩ ሥር ነቀል እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑንና ለማድረግም ማሰቡን በፓርላማ ሪፖርቶች ወቅት አመልክቷል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሥር ነቀል የሚል ስያሜ የተሰጣቸው የለውጥ እንቅስቃሴዎች ሁሉን አቀፍ የሆነ መስማማት የተደረሰባቸው ናቸው ወይ ብለን ጥያቄ ስናነሳ ምላሹ አይደለም የሚል ይሆናል፡፡ ግን አሁን ድርጅቱን በመምራት ላይ የሚገኙት ኃላፊዎች ይህን ዓይነት ሐሳብ ያለው ሰው የለውጥ አደናቃፊ በመሆኑ ሊወገድ ይገባል የሚል አስተያየት በድርጅቱ የተለያዩ ስብሰባዎች ወቅት ሲገልጹ ይደመጣል፡፡ ይህ ለምን ሆነ የሚል ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ ከላይ ያነሳናቸውን ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎች በውሉ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አልፎም የአመራሩን ያለፉት ሁለት ዓመታት አካሄዶች ማጤን ግድ ይላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ምልከታ በቅርቡ ከኃላፊነታቸው የተነሱት የኢቢሲ ሥራ አስፈጻሚና አመራሮቻቸው የኃላፊነት ዘመን ሦስት መልኮች ያሉት ነው፡፡ የመጀመሪያው ፍፁም ዴሞክራሲያዊ የመሰለ ግን በሐሳብ ተቀናቃኞቻቸው ላይ ዕርምጃ የወሰዱበት ነው፡፡ ሁለተኛው በአንፃሩ ከመጀመሪያው በራቀ መልኩ ኢ-ዴሞክራሲያዊነት የገነነበትና ቡድንተኝነት የጎላበት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለውን ሦስተኛ ዘመን ደግሞ በመንታ መንገድ የታጀበ ይመስላል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸውን የኃላፊነት ዘመን ገጽታዎች በተናጠል እየተመለከትን እንቀጥል፡፡
ከሁለት ዓመት በላይ ኢቢሲን የመሩትንና በቅርቡ ከኃላፊነት የተነሱትን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለመጀመሪያ ጊዜ ሠራተኛው የተዋወቃቸው በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በነበረ ስብሰባ ወቅት ነበር፡፡ በጊዜው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከሠራተኛው ጋር በመሆን ድርጅቱን ለመለወጥ ቁርጠኛ መሆናቸውን ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ በቢሮ ውስጥ ያለ ቢሮክራሲ ይስተካከላል፣ ሹመት በዕውቀት ላይ ብቻ የተመሠረተ ይሆናል የሚሉ ሐሳቦችን አንስተዋል፡፡ አብዛኛው ሠራተኛም በተስፋቸው ተስፋውን ዘርቶ ከጎናቸው መሆኑን ተናግሯል፡፡ በእርግጥ በዚህ ጊዜም ቢሆን ሁሌም አዲስ ኃላፊ ሲመጣ እንዲህ የሚል ቃል ነው የሚናገረው፣ ከዚያ ምን የተለየ ተናገሩ በሚል ሥጋቱን ያሰማም አልታጣም፡፡ የሆነ ሆኖ በበርካታ ተስፋዎች የታጀበውና ፍፁም ዴሞክራሲያዊነት የሰፈነበት የመሰለው ጅማሮ ከአፍታ በኋላ የተለያዩ ድምፆች ይሰሙበት ጀመረ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከቀድሞው አመራር ጋር የሠሩ ግለሰቦች በአግባቡ አልረዱኝም ማለታቸው ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ ልዩነትም ሐሳብን በሐሳብ ከመምታት ይልቅ የሐሳቡን ማደሪያ የሆነውን ግለሰብ ወደ ማጥቃት ተሸጋገረ፡፡ በዚህ ሒደትም የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና የትምህርታዊ ፕሮግራም ኃላፊ ከሥልጣናቸው መነሳታቸው ተገለጸ፡፡ በወቅቱ ሁለቱ ወገኖች እርስ በርስ መወነጃጀል ቢጀምሩም ከኃላፊነት የተነሱት ሰው ድርጅቱን በመልቀቃቸው፣ ነገሩ ለተወሰነ ወቅትም ቢሆን ተዳፍኖ በደመወዝና መሰል የጥቅማ ጥቅም ወሬዎች ተተካ፡፡
ነገር ግን አሁንም በድርጅቱ አመራር አባላት ውስጥ ያለው የሐሳብ ልዩነት ስለመስፋቱ የተለያዩ መረጃዎች መሰማት ቀጠሉ፡፡ ቀጣዩ ተሰናባችም ሌላው የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የስፖርትና መዝናኛ ፕሮግራሞች ኃላፊ፣ አንጋፋ የስፖርት ጋዜጠኛ ሆነ፡፡ የዚህ ሰው ስንብት በበርካታ የክፍሉ ሠራተኞች ላይ ድንጋጤን የፈጠረ ሲሆን፣ በመጨረሻ እሱ ባሸነፈበት ጉዳይ ደመወዙ ታግዶ ለበርካታ ዓመታት ካለበቂ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የሠራበትን ቤት በግፍ ተሰናብቷል፡፡
ሌላው የዜናና ወቅታዊ ክልል ኃላፊ የነበረ አንጋፋ ጋዜጠኛም የአመራሩን አካሄድ በመመልከት ራሱን ከሥራ አሰናብቷል፡፡ አሁን በኃላፊነት ላይ ያለውን አመራር የአመራርነት ዘመን የመጀመሪያ መልክ ከተመለከትን የሐሳብ ልዩነቶቹ ሠራተኛው ጋር በውሉ ያልደረሱ ስላልነበሩ፣ ከሞላ ጎደል በሠራተኛው ውስጥ የመግባባት ስሜት ነበር ብሎ መግለጽ ይቻላል፡፡
ይህ ማለት ግን ፈፅሞ ጥያቄ አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል አመራሩ በዚህ ዘመን የቀረውን በቁጥጥር ላይ የተመሠረተ የአመራርነት ጥበብ መጠቀሙ በብዙ ጋዜጠኞች ላይ ቅሬታ አስነስቷል፡፡ ቼክ ሊስት መሙላት፣ በቀን ምን ያህል ዜና ከኤዲተሩ እንደሚደርሰው ለማያውቅ ጋዜጠኛ አዳጋች ሆነ የሰዓት የመውጫና መግቢያ መቆጣጠሪያ አሻራ መተከልና ከደመወዝ ጋር የተገናኘው ማስፈራሪያ መደበኛ ሰዓት ለማይጠብቀው የጋዜጠኝነት ሙያ ዳገት ሆኖ መጣ፡፡ ግን አመራሩ ሁሉንም ያመጣነው ለጋዜጠኛው ተጠቃሚነት በማሰብ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በቅርብ ጊዜ ባሳያችሁት አፈጻጸም ነው ምደባ የሚካሄደው በመባሉ ሠራተኛው ነገን ተስፋ በማድረግ መብቱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ እስከ ምሽት 4፡30 አልያም 6፡00 ሰዓት የሠራ ጋዜጠኛ ሥራው አስገድዶት በነጋታው ማለዳ ሲገባ ቢኖርም፣ አሁን ግን አመራሩ ግዴታ ስላደረገው ጫጫታ መሰማት ጀመረ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ቅሬታዎች በተለያዩ ተስፋዎች የታጀቡ በመሆናቸው ብዙ ጉልበት የነበራቸው አልሆኑም፡፡ ምናልባትም በዚህ ወቅት የነበረው ተቃውሞ በዚያው በከፍተኛ አመራሩ መሀል የሚሰማ ብቻ ነበር፡፡
ከላይ የተጠቀሰው በተወሰኑ የከፍተኛ አመራሮች ይነሱ የነበሩ የድርጅቱ አካሄድ አግባብ አይደሉም ጥያቄዎች ግን ጊዜያቸውን ጠብቀው ወደ ሠራተኛው መውረድ ጀመሩ፡፡ ሁለተኛ ብለን በጠቀስነው ዘመን ውስጥም ኢ-ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ጉዳዮች በረከቱ፡፡ የኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄዶች ነፀብራቅ የሚደረጉት ቡድንተኝነት (ጠባብነት)፣ አምባገነናዊነትና መሰል ጉዳዮች በየቦታው በረከቱ፡፡ በአመራሩ መካከል ያለው የሐሳብ ልዩነትም ጠነከረ፡፡ ለሁለት የተከፈለው አመራር አንዱ አንዱን መውቀስ ሲበዛ፣ ለሥራ አስፈጻሚው ታማኝ የሆነው አመራር በሌሎች ላይ ጣቱን በመቀሰር ለውድቀቱ ሁሉ መነሻ ከቀድሞው አመራር ተልዕኮ የተሰጣቸው አመራሮች ናቸው በማለት ነገሩን ከሐሳብ ሙግት ወደ ፖለቲካዊ ሽኩቻ አዞረው፡፡ በአመራሩ ውስጥ የሐሳብ ልዩነት ያላቸው ግለሰቦች ደግሞ የዋና ሥራ አስፈጻሚው የሚዲያ አመራርነት ዕውቀትና ልምድ ማነስ፣ ለሚዲያው ይዘት ከመጨነቅ ይልቅ ተራ የቢሮ ጉዳዮች ላይ የተጠመዱ መሆን ጣቢያውን ካለበትም ደረጃ የሚያወርድ ነው ማለት ጀመሩ፡፡ እውነት ለመናገር ሥራ አስፈጻሚው በየትኛውም መድረክ ስለሚዲያው ይዘት ትኩረት አለማድረጋቸው እኒህ ሰው መደበኛ የቢሮ ሥራ ላይ ቢቀጥሉ የተሻለ ነበር ያስብላል፡፡ በርካታ የላቀ ሥራ የሚሠሩ ጋዜጠኞች ቢኖሩም ቼክ ሊስት እስካልሞሉ የጣት አሻራ እስካልነኩ ድረስ ጥብቅ ዕርምጃ ውስዱ እያሉ መመርያ በመስጠት፣ ጋዜጠኝነትን ከጥበብ አውርደው ተራ የቢሮ ጉዳይ ብቻ አደረጉት፡፡ በዚህ ምትክ በድርጅቱ የስድስት ወራት ስብሰባ ወቅት ለቢሮው ካፌ ተጠቃሚዎች የተገዛው ወንበርና ጠረጴዛ አጀንዳ ሆኖ የአመራሩ ስኬት ተደረጎ መቅረብ ያዘ፡፡
ይህ ዓይነቱ በአመራሩ ውስጥ ያለ የሐሳብ ልዩነት መስፋትም ሥራ አስፈጻሚው የራሳቸውን ቡድን በመመሥረት ሌሎችን ማዳከም ላይ እንዲበረቱ አደረጋቸው፡፡ በይፋም ለድርጅቱ የፖለቲካ ድርጅት አባላት ከዚህ በኋላ አንታገስም በማለት እንደ አብዮተኞች ከመከላከል ወደ ማጥቃት መዞራቸውን አወጁ፡፡ ከዚህ በኋላ በነበረ የአመራሩ ስብሰባ ላይም ዕርምጃ እወስዳለሁ ሲሉ ማስፈራሪያ ተናገሩ፡፡ እዚህ ላይ ምን ተፈጥሮ እንዲህ ሲሉ ካልን ይኸው ድርጅቱን በዚህ በኩል ብናስኬደው ጥሩ ነው፣ ለምን አላችሁ የሚል የእኔን ብቻ ስሙኝ ስሜት ነው፡፡ ከፍ ብዬ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ይህ የዘመን ገጽታ ፍፁም ኢ-ዴሞክራሲያዊ የሆኑ አካሄዶች የበዙበት ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ አብነት ሆነው ከሚቀርቡ ጉዳዮች መካከል ቡድንተኝነት እየተንሰራፋ መሄዱ ነው፡፡ ሥራ አስፈጻሚው በሐሳብ ከሳቸው የተለያዩትን ከኃላፊነት ካሰናበቱ በኋላ የራሳቸውን ሹመት በተለያዩ ቦታ አድርገዋል፡፡ ከድርጅቱ ወጪም ሰው በማስመጣት በአዲስ አደረጃጀት የይዘት ዘርፍ ኃላፊ በማለት ሹመዋል፡፡ በዚህ ጊዜ በጣቢያው የተለያዩ ወገኖች በአመራሩ ቡድንተኝነት ላይ ሐሳብ መሰንዘር ጀመሩ፡፡
በተለይም የጣቢያው ዋና የሥራ ክፍል የሚባለውን ዜና ክፍል ጨምሮ እስከ ሥራ አስፈጻሚው ድረስ የአንድ ብሔር አባል መሆናቸው፣ ከሌሎች ብሔሮች አቅም ያለው ሰው የለም ማለት ነው የሚል ቅሬታን ውስጥ ውስጡን መናፈስ ቀጠለ፡፡ አንድ የድርጅቱ ጋዜጠኛም ይህን ሐሳብ ለድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ አቀረበ፡፡ የሚገርመው ነገር ይህ ጋዜጠኛ አሁን ከነበረበት ኃላፊነት ተነስቷል፡፡ ምክንያት ከሚደረጉ ጉዳዮችም በአብዛኛው ሠራተኛ ዕምነት ትልቁን ቦታ የሚይዘው ይኼው በአደባባይ ይህን ሐሳብ ማፍረጥረጡ ነበር፡፡ ከዚህ ግለሰብ በተጨማሪም በጊዜው የዜናና ወቅታዊ ክፍል ኃላፊ የነበረው ሰው የግለሰቡ ጥያቄ ትክክል ነው፣ ከአንድ ብሔር በዝተናል የሚል ሐሳብ በመሰንዘሩ ተቃውሞው ከሌሎች ነገሮች ጋር ተዳምሮ ከኃላፊነት ለመነሳቱ ምክንያት እንደሆነ በሠራተኛው ይታመናል፡፡
የአመራሩ ኢ-ዴሞክራሲያዊነት ግን በእንዲህ ዓይነት ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሥራ አስፈጻሚው ከመድረክ ሆነው ድራማዊ በሚመስል መልክ ራሳቸውን ተገምጋሚም አሰገምጋሚም ባደረጉበት ወቅት አንድ አንጋፋ ጋዜጠኛ በሐሳብ ብዝኃነት የማያምኑ አምባገነን ነዎት ስትል ገልጻቸዋለች፡፡ ረጅም ሕይወትን በትግል ያሳለፈ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ራሴን አሳልፌ ሰጠሁ ከሚል ሰው የማይጠበቅ አምባገነንት አለብዎት ብላቸውም ነበር፡፡ ይህን ሐሳብ በጊዜው ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሌሎች አመራሮችም ደጋግመው በዚህ ግምገማ ወቅት አንስተውላቸዋል፡፡ ራሳቸውን ቁጭ ብለው ዕድል እየሰጡ ሲገመገሙት ለአመራሩ አጥጋቢ መልስ ሳይሰጡ ተሰናብተዋል፡፡
ሌላው የዚህ ዘመን ገጽታ ተደርጎ የሚመጣ ጉዳይ አዲስ የተሾሙ አመራሮች ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ መጎልበት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ በአሁኑ ወቅት በድርጅቱ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የሚገኙት የተለያዩ ኃላፊዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ኃላፊዎች በዘፈቀደ የፈለጋቸውን የማድረግ መብቱ የታደላቸው ሲሆን፣ የሚፈልጉትን ሰው በቴሌቪዥን ስክሪን እንዲያቀርብ መፍቀድ ያልፈለጉትን ያላሳማኝ ምክንያት ከስክሪን ማውረድ ይችላሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድም አንዳንዴ ወደ አክራሪነት የተጠጋ ሲመስል ተስተውሏል፡፡ ለአብነት ያህል አንዲት ኃላፊ እኔ በምመራቸው ክፍሎች ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዳይቀርብ የሚል ዕገዳ መጣሏ ይታወሳል፡፡
ለምን የሚል ጥያቄ ቢቀርብም ውኃ የሚያነሳ ክርክር ማድረግ አልቻለችም፡፡ በነገራችን ላይ በዚች አመራር ላይ የተለያዩ ጋዜጠኞች የአቅም ውስንነት አለባት ብለው ለዋና ሥራ አስፈጻሚው አቤቱታ ቢያቀርቡም፣ እዚያው ታገሏት የሚል ምላሽ ከማግኘት ውጪ መፍትሔ አላገኙም፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዘንድ ገብተው ቅሬታ ያቀረቡ ጋዜጠኞችም በጊዜው የተለያዩ ውንጀላዎች የተሰነዘረባቸው ሲሆን፣ ቢሮዬ 24 ሰዓት ክፍት ነው ከሚሉ አመራር ደጃፍ ደርሶ ቅሬታ ማቅረብ በሠራተኞቹ ዓመታዊ ግምገማ ወቅት ዋና ጉዳይ ተደርጎ ተጠይቀውበታል፡፡
ይህ ሁለተኛው መልክ የአመራሩ ዘመን የስፖርት ክፍል ታዋቂ ጋዜጠኞች ተጠራርገው የለቀቁበት፣ ለመልቀቂያ ሲመለሱም በጣቢያው የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሌለ ፈርሙ የተባሉበት፣ የጣቢያው ዶክመንተሪ ክፍል ሥራ የተቀዛቀዘበት ኃላፊውም በሚደርሰባቸው ጫና ተቋሙን የለቀቁበት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጣቢያው ኤዲቶሪያል ፎረም ድርጅቱን ለመቀየር በሚል ሰበብ ፓይለት ፕሮጀክት በዜናና ወቅታዊ ክፍል ብቻ በመተግበር በሐሳብ ልዩነት የቆመውን የክፍሉ አመራር በማንሳት፣ የፓይለት ፕሮጀክቱ አስተባባሪ የነበሩ ከላይ የጠቀስናቸው ግለሰብ አመራር ወደ ሥልጣን መምጣታቸው ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይህን ተከትሎ ስብሰባ የጠራው አመራሩ የእነዚህን ረጅም ዓመታት በጋዜጠኝነትና በኃላፊነት የመሩ ግለሰብ ከኃላፊነት መውረድ ግዳይ እንደጣለ ጀግና በታላቅ ፉከራና ማስፈራሪያ ማቅረቡ አስገራሚ ነበር፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ዘገባ ወቅት ጓደኞቻቸው በጦር ሜዳ ሲያልፉ በሕይወት ተርፈው የመጡና በኃላፊነት ረጅም ዘመን የመሩን ሰው ስንብት የግለሰቡን ሰብዕና በሚዘልፍ ቃላት ማቅረብ በእርግጥም አስገራሚም አሳፋሪም ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል በስድስት ወሩ ግምገማ የተሻለ አፈጻጸም ነበረው የተባለ ሰው ከኃላፊነት ለምን ወረደ? ከሥራ ውጪ መሥፈርት አላችሁ ወይ? ተብለው ቢጠየቁም ለመልስ ያህል አደባብሰው ለማለፍ ሞክረዋል፡፡
ሦስተኛው የኃላፊነት ዘመን ገጽታ ባለፉት ወራት የዚህ አመራር ተግባራት ላይ ያተኩራል፡፡ ይህ ዘመን ከላይ እንደተጠቀሰው ሁለት ገጽታዎች ያሉት ነው፡፡ የመጀመሪያው በአመራሩ ውስጥ ያለው የሐሳብ ልዩነት እንደገና በሌሎች ሰዎች መሪነት መቀስቀሱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በሠራተኛውና በአመራሩ መካከል ያለው ልዩነት ከምንጊዜውም በላይ እየሰፋ መሄድ ነው፡፡
የመጀመሪያውን ነጥብ በማንሳት እንቀጥል፡፡ ይህ አመራር በአንድ ሐሳብ መኖር እንጂ በሐሳብ ብዝኃነት የሚያምን አይመስልም፡፡ በመሆኑም ከላይ የሆኑት ሁሉ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ለመውጣትም ተመሳሳይ ሐሳብ ሊያራምዱ የሚችሉ፣ ስህተት ነውን የማያወቁ ሰዎችን ወደ መሾም ተዘዋውሯል፡፡ ነገር ግን በዚህ መንገድም ቢሆን ሐሳብ ማዳፈን አለተቻለም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ከኦሮሚያ ቲቪ መጥቶ በከፍተኛ አመራርነት የተሾመ ግለሰብ ድንገት ከቢሮ መጥፋትና ስልክ ሲደወል ለንደን መኮብለሉ መሰማቱ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ዳይሬክተር ከአገር መውጣት አመራሩን ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የከተተ ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህ ውስጥ የሚካተተው ሌላው ጉዳይ የዚሁ አመራር አካል ሆነው ሥራ አስፈጻሚውን በድፍረት የሞገቱ መፈጠራቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ የኢቢሲ የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ በአንድ ስብሰባ ላይ ይህን ብናገር ከኃላፊነት እንደምነሳ አወቀዋለሁ፣ ግን ተናግሬ ልነሳ ብላ ነበር፡፡ እንዳለችውም አሁን ከኃላፊነት ተነስታለች፡፡
ሁለተኛውን ነጥብ ለማንሳት እንሞክር፡፡ በዚህ አመራር ሦስተኛ ገጽታ ውስጥ የሚካተተው ይህ ነጥብ በአመራሩና በሠራተኛው መካከል ልዩነቱ እየሰፋ መሄዱን ያሳየናል፡፡
ከወራት በፊት በድርጅቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ዋና ሥራ አስፈጻሚው በተገኙበት ስብሰባ ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ወቅት በርካታ ሠራተኞች ቅሬታቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ የተጋነነው የአመራሩ የጥቅማ ጥቅም ጉዳይና መሰል ሐሳቦች ትልቅ ቦታ ይዘው ነበር፡፡ ይህ ስብሰባ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ አሰፈጻሚውን ከተዋወቅንበት የሸበሌ ሆቴሉ ጋር ከተነፃፀረ አመራሩ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ከቡድን መሪ ጀምሮ እስከ ሥራ አስፈጻሚ ደርሶ በገንዘብና በዓይነት የተለቀቀው ጥቅማ ጥቅም የሠራውንና ባለቤት የሆነውን ጋዜጠኛ ያገለለ ሆነ፡፡ በወቅቱ ለምን ሠራተኛው ይበደላል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሥራ አስፈጻሚው፣ ለእኔ ሠራተኛ ማለት ከምክትሌ ጀምሮ ያለው ስለሆነ ጥቅማ ጥቅም እንደተደረገላችሁ ነው የማውቀው የሚል አስቂኝ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ኃላፊው በዚህ ሳይበቃም ኃይል የተቀላቀለባቸው ንግግሮችን በማሰማት ዛቻም አስተላልፈዋል፡፡ ከዚያ በፊት እንደሚሉት ሁሉ ለመውጣት የምታስቡ ድርጅቱን ልቀቁ ሲሉ ከአንድ ከመሪ የማይጠበቅ ንግግር ተናግረዋል፡፡
የድርጅቱን 50ኛ ዓመት ምሥረታ በ51 ዓመቱ ያከበረው ቀርፋፋ አመራር፣ በድርጅቱ ታሪክ ውስጥ ያለፉ ታላላቅ ሰዎችን ዘንግቶ የራሱን አመራር ዘመን ሲያወድስ ተሰምቷል፡፡ ኢቢሲ ሁለት ዓመቱን ያከበረ ይመስል ባለፉት ሁለት ዓመታት በሚል አሳፋሪ የታሪክ ሽሚያ ውስጥ የገባ አመራር መሆኑን አመልክቷል፡፡ በጅማና ድሬዳዋ ጊዜያዊ ስቱዲዮ ባልሠራበት ሁኔታ በ“DSNJ” የሚያስተላልፈውን ዘገባ ከጊዜያዊ ስቱዲዮ በማለት ሕዝብን በማታለልም ዛሬም ድረስ ዘልቋል፡፡
የዚህን አመራር ግራ የተጋባ አካሄድ የሚያሳዩ ጉዳዮችን በመግለጽ ጽሑፌን ልቋጭ፡፡ ይህ አመራር በመጣ ጊዜ ለተነሱ ችግሮች የቆየው አመራር የተከለው ችግር ነው ሲል ቆይቷል፡፡ እነዚህ ችግሮች ሳይፈቱ ሲቀሩም የተዘረጋውን ሲስተም የሚያበላሹ ሰዎች መብዛት በማለት ነገሩን ከራስ ለማራቅ ሞክሯል፡፡
በዚህ መልክም ትንሽ ተጉዞ ጥያቄ ሲበረክት ስትራቴጂካዊ ፕላኑ ይፈታዋል የሚል የተስፋ እንጀራ ጋግሯል፡፡ ለመሆኑ ስትራቴጂካዊ ፕላኑ ምን ጨምሮ መጣ? የመጀመሪያው የደመወዝ ጭማሪ ለሠራተኛው ማድረጉ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉ ጉዳዮች ግን በተቃራኒ አሉታዊ ተደርገው ይጠቀሳሉ፡፡ ለአብነት ያህል የራዲዮ ዜና ኃላፊ በቡድን መሪ፣ የቴሌቭዥን በዳይሬክተር ሲመሩ ላየ አመራሩ ሥራን ሳይሆን ሰውን ታሳቢ ያደረገ ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከኃላፊነት የተነሱ አመራሮችን ቅሬታ ለማፈን ወደ ትምህርት መላኩ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ለትምህርት መላክ ደግሞ ተፈላጊ ሰዎችን በቦታቸው ለማስቀመጥ የተደረገ መሆኑ የሚታወቀው፣ በኢቢሲ ሁለተኛ ዲግሪ የተማረ ሰው ከቦታው እንዲነሳ ስለተፈለገ ብቻ በድጋሚ እንዲማር ተገዷል፡፡
አንድ ጊዜ እንኳን ለመማር ዕድል ብርቅ በሆነበት ቤት ለአንድ ሰው ደጋግሞ የመማር ዕድል መስጠት ምን ያህል ሌላን ያም ይሆን?
በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚይዙ ጉዳዮች መካከል ከወራት በፊት በስትራቴጂካዊ ፕላኑ ዋዜማ ሰሞን በድርጅቱ ያልታሰበ ሹመት ለበርካቶች ተሰጥቶ ነበር፡፡ በጊዜው ስትራቴጂካዊ ፕላኑ አለቀ እያለ ለነበረ አመራር ይህን ማድረጉ የፕላኑ አንድ አካል ይመስል ነበር፡፡ ግን አይደለም ከጥቂት ወራት በፊት ሹመት ተሰጥቷቸው መኪና ተረከቡ የተባሉ አመራሮች ከሰሞኑ በስትራቴጂካዊ ፕላኑ ከኃላፊነት መነሳታቸው የተሰማው የጥቂቶች አይደለም፡፡ ይህ ለምን ሆነ ስንል ምክንያት አልባ የዘፈቀደ የአመራር ጥበብ ውጤት ነው፡፡
አሁን ኢቢሲ ብትሄዱ ሁለት ብሶቶች የሚሰሙ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው ካለምንም በቂ ጥናት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬድዮና ቋንቋዎች ሥርጭት ክፍል ለሥራ ይሁን ለግዞት ወደ ዘነበወርቅ ግቢ ይምለስ መባሉ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በስትራቴጂካዊ ፕላኑ ያለበቂ ዕወቅትና ልምድ የተሸሙ ሰዎች መበርከት ነው፡፡ ሁለቱም ለእኔ ተመሳሳይ የዜሮ ድምር ጨዋታዎች ናቸው፡፡ በዚህ መሀል የሚጉላላው ሠራተኛ ግን አሁንም ያሳዝናል፡፡ መልካም አስተዳደር በሚሰብክ ጣቢያ መልካም አሰተዳደር መጠማት ይገርማል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድም የጋንግሪን ያህል እየሰፋ ሳይሄድ ቶሎ ሊታረም ይገባል፡፡ የድርጅቱ ሠራተኛ በነፃነት ሊናገርበት የሚችል መድረክ ተፈጥሮ ችግሮች ሊፈቱ ያስፈልጋል፡፡ ያለበለዚያ ለዋና ሥራ አስፈጻሚው ሽኝት ለዚህ ሹመት ያበቁን እሳቸው ናቸው በሚል ከ500 ብር በላይ ያወጡ ሰዎች የሚቦርቁበት ቤት መሆኑ ይቀጥላል፡፡
ኑሮ በኢቢሲ እንዲህ ነው፡፡ ሁለት ዓመት ሙሉ ግዞት የበዛበት የደመወዝ ጭማሪ ያልገታው ፍልሰት ያለበት የብዝኃነት ድምፅ ብሎ እየለፈፈ የብዙኃን ድምፅ የማይሰማበት፡፡ ከሁሉም ከሁሉም የሮበርት ግሪንን “48 Law of Power” (48 የሥልጣን ላይ መሰንበቻ መንገዶች) በውሉ ያልተረዱ ቀሽም አንባቢዎች የበዙበት ግን እሱን ለመተግበር የሚጥሩበት መንደር፡፡ ኢቢሲ፡፡
ከአዘጋጁ፡-ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
