በተሾመ ብርሃኑ ከማል
በኢጣሊያ ወረራ ዋዜማ
የኢጣሊያ ወረራ፣ የአርበኞች ታሪክና ከዚህ ጋር ተያያዥነት ስላላቸው ሁኔታዎች ስናወሳ ከአንዱ የታሪክ አንጓ (ምዕራፍ) ካልጀመርን በስተቀር ብዙ ጉዳዮችን ማንሳታችንና መጣላችን አይቀርም፡፡ ስለዚህም ‹‹ኢጣሊያ ኤርትራንና ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የመግዛት ህልሟ በዓድዋ ጦርነት ቢከሽፍም አርፋ አልተቀመጠችም፤›› ከሚለው እሳቤ እንነሳ፡፡
ኢጣሊያ በአፍሪካ ቅኝ ግዛት ለመመሥረት በነበራት ፅኑ ዓላማ ሰሜን ኢትዮጵያን በመውረር ኤርትራን ይዛ በሰላም መኖር እንደማትችል በተግባር ስላረጋገጠች፣ በሰሜን በኩል በማርሻል ኢሚሎ ደቦኖ (የኢጣልያ ቅኝ ግዛት አገሮች ኮሚሽነር) የሚመራ 250,000 ነጮችን፣ 150,000 አፍሪካውያንን ከሊቢያ፣ ከሶማሊያና ከኤርትራ ሠራዊት ኢትዮጵያን አጠቃሎ ለመግዛት ከ1920ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ዝግጅት ማድረግ ተጀመረች፡፡ ይኼንን ዘመቻ በማያዳግም ሁኔታ ለማከናወን 300 የጦር አውሮፕላኖች ዝግጁ ሆኑ፡፡ በደቡብ በኩል በ100 የጦር አውሮፕላኖች የታገዘ በማርሻል ሮዶልፍ ግራዚያኒ የሚመራ ኃይል ወደ ሰሜን ተንቀሳቀሰ፡፡ ይህም የተደረገው አዲስ አበባን እጅግ አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ በመቆጣጠርና ሕዝቡ በደስታ ተቀብሎኛል በማሰኘት ሊግ ኦፍ ኔሽን ያደርስ የነበረውን ተፅዕኖ ለማስቀረት ነበር፡፡
የኢጣሊያ ወታደራዊ ምንጮች ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በኤርትራ ከነበራት በ3,300 መትረየሶች፣ በ200 ታንኮች፣ በ275 መድፎች የተጠናከረ 400,000 በተጨማሪ በሶማሊያ ከነበረው 285,000 ሠራዊት ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሚያዚያ ወር 1928 ዓ.ም. ብዙ ቶን የሚመዝኑ ጥይቶች፣ ለወራት የሚበቁ ምግቦችና ሌሎች ድጋፍ የሚሠጡ አገልግሎቶች፣ በርካታ ሞተር ብስክሌቶች፣ በ6,000 አውቶማቲክ የጦር መሣሪያ (መትረየስ)፣ 2,000 መድፍ፣ 599 ታንክ፣ 390 አውሮፕላኖች የተጠናከረ፣ ከኢጣሊያ ዘውዳዊ መንግሥት የጦር ኃይል ተቀንሶ 650,000 ሠራዊት ኤርትራ ገባ፡፡ ይህም ጦር የገባው በከፍተኛ ስንቅና ትጥቅ ተጠናክሮ ሲሆን፣ ጦርነቱንም ለመከታተል 200 ያህል ጋዜጠኞች መጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዚያን ጊዜ ያንቀሳቀሰችው በራሶች የሚመራ 300,000 ሠራዊት ሲሆን (ይኼንን ቁጥር አንዳንዶች 500,000 እንደሚደርስ ይገምታሉ፣ የኢጣሊያ ወታደራዊ ምንጮች ግን ኢትዮጵያ 350,000 እስከ 760,000 የሚገመት ሠራዊት ነበራት ይላሉ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ የነበሩዋቸው 200 መድፎችና 1,000 መትረየሶች ሲሆኑ፣ ሠራዊቱም ከጠላት ጋር የማይመጣጠን ጠመንጃ የታጠቀ ነበር፡፡ አብዛኛው ሠራዊት የተሠለፈው ጎራዴ፣ ጦርና ጋሻ ይዞ ሲሆን፣ የተወሰነው ደግሞ ከሚወድቁ ወገኖቹ የጦር መሣሪያ አንስቶ ለመዋጋት ጀሌውን የተሠለፈ ነበር፡፡ ሠራዊቱ ሲመች ከሚሠጠው ጥይት በስተቀር ስንቁንም ሆነ የጦር መሣሪያውን ይዞ የተሠለፈው ከግሉ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት የራሱ የሆነ በቅሎ ፈረስ፣ ግመልና አህያ ይዞ ከመዝመቱ በስተቀር የጦር መኪና፣ የጦር አውሮፕላንና ታንክ የሚባል አልነበረውም፡፡
ይኼም ሆኖ የኢጣሊያ ወታደራዊ ምንጮች ኢትዮጵያ 400,000 ያህል ጥንታዊና ዘመናዊ ጠመንጃዎች፣ 200 ያህል ያረጁ መድፎች፣ 50 ያህል ቀላልና ከባድ የአየር መቃወሚያዎች፣ 3,000 ያህል በአንደኛው የዓለም ጦርነት አገልግሎት ላይ የዋሉ መድፎች፣ ለአየር አምቡላንስ የሚውሉ ጥቂት አውሮፕላኖች፣ አራት አብራሪዎች የነበሯቸው 13 የአየር ኃይል አውሮፕላኖች ነበሩ፡፡ እጅግ ኋላቀር የጦር መሣሪያ የታጠቀውና ዘመናዊ የውትድርና ሥልጠና ያላገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት እጅግ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ከታጠቀው የኢጣሊያ ሠራዊት ጋር በሽሬ ከታኅሳስ 7 እስከ 8 ቀን 1927 ዓ.ም.፣ በእንዳባጉና ከጥር 12 እስከ16 ቀን 1928 ዓ.ም.፣ በወርቃምባ ተንቤን ከጥር 19 እስከ 21 ቀን 1928 ዓ.ም.፣ ከየካቲት 1928 ዓ.ም. በዓቢይ ዓዲ ተንቤን፣ ከየካቲት 24 እስከ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. ከዚያም ቀጥሎ በሰለኽለኻ፣ በአምባ አርአዶምና በእምባአላጌ ላይ ጦርነት አካሄደ፡፡ በእነዚህ ሥፍራዎች በተደረገው ጦርነት ቁጥሩ እጅግ ብዙ የሆነ ኢትዮጵያዊ ቢሞትም፣ በተለይም በሽሬ በተደረገው ጦርነት 300 ያህል መትረየሶች፣ ታንኮችና ሌሎችም ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ተማረኩ፡፡
በዚህ ጦርነት በኢጣሊያ በኩል የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት ማርሻል ባዶግሊዮ በላከው ሪፖርት በሽሬ ጦርነት ብቻ 63 የጦር መኮንኖች፣ 894 ኢጣሊያውያን፣ 12 ኤርትራውያን ሲሞቱ በኢትዮጵያ በኩል 4,000 ያህል ሞተዋል በማለት ገልጿል፡፡ በዚህ ጊዜ 400 የሚሆኑ ኤርትራውያን ኢጣሊያን በመክዳት ሽሬ ከነበረው ከራስ እምሩ ጦር ጋር ተቀላቅለዋል፡፡
በደቡብ ግንባር በኩል በማርሻል ግራዚያኒ የሚመራውን የጦር ኃይል የነራስ ደስታ፣ ደጃዝማች ነሲቡ፣ የራስ መኮንን የጦር ኃይል በኦጋዴን በተደረገው ጦርነት ገጥሞታል፡፡ በዚህ ጊዜ የማርሻል ግራዚያኒ የጦር ኃይል የገጠመው በጦር አውሮፕላኖች በሚረጭ የጋዝ መርዝ ጭምር ነበር፡፡ ምንም እንኳን በጦርነቱ አያሌ ኢትዮጵያውያን ቢጨፈጨፉም፣ 400 ያህል ኤርትራውያን የወገኖቻቸው መጨፍጨፍ አሳዝኗቸው ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ተቀላቅለዋል፡፡
ቦነያ ነቀምት ውስጥ በደጃዝማች ሀብተ ማርያም ከሚመራው የአርበኛ ጦር ጋር በተካሄደው ጦርነት በኢትዮጵያ የኢጣሊያ ምክትል መስፍንን ጨምሮ ከ13 የኢጣሊያ መኮንኖች 12፣ የአየር ማርሻሉ ማግሎዮኮው ሰኔ 18 ቀን 1928 ዓ.ም. ተገደሉ፡፡ በዚህ ጦርነት የተረፈ ኢጣሊያዊ ቢኖር አባ ቦሬሎ የተባሉ መንገድ መሪያቸውና ቡራኬ የሚሰጧቸው ነፍስ አባታቸው ብቻ ነበሩ፡፡
በራስ ደስታ ዳምጠው የጦር አበጋዝነት በሲዳሞ ውስጥ የተካሄደው ጦርነት ከፍተኛ ዕልቂት የተፈጸመበት ሲሆን፣ በእዚህም ጦርነት ጄኔራል ናቫሪኒ በሦስት አቅጣጫዎች ባደረገው ከበባ 4,000 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 1,600 ያህሉ ምርኮኞች ሲሆኑ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ተደርጓል፡፡ ጥቅምት 1 ቀን 1928 ዓ.ም. ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ ከ1,200 ተከታዮቻቸው ጋር ዕዳጋ ሐሙስ ላይ ለማርሻል ደ ቦኖ እጃቸውን ሰጡ፡፡
ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ከጎጃም ወደ ተንቤን በተለይም ማይ ጥምቀት ተብላ ወደምትጠራው ሥፍራ 4,0000 ሠራዊት አስከትለው ዘመቱ፡፡ ራስ ሥዩም መንገሻ ከ30,000 ሠራዊታቸው ጋር ዓቢይ ዓዲ አካባቢ ነበሩ፡፡ ራስ ካሳ ኃይሌ ዳርጌ 40,000 ያህል ሠራዊታቸውን አስከትለው ከደሴ ራስ ሥዩምን ለመርዳት ወደ ተንቤን ዘመቱ፡፡ ራስ ሙሉጌታ ይገዙ (የጦር ሚኒስትር) 80,000 ያህል ሠራዊታቸውን አሠልፈው ከራስ ሥዩም በስተቀኝ አምባ አርዓደላይ መሸጉ፡፡ አራቱም የጦር አበጋዞች በአጠቃላይ 19,000 ያህል ሠራዊት ነበራቸው፡፡ ተንቤን ላይ በተደረገው እጅግ አስከፊ ጦርነት 8,000 ያህል ኢትዮጵያውያን ተገደሉ፡፡ ከዚህ በኋላም መቀሌ በኢጣሊያ ተያዘች፡፡
እምባአርአደ ላይ በተደረገው የእንደርታ ጦርነት ራስ ሙሉጌታና ልጃቸውን ጨምሮ 6,000 ሰዎች ሲሞቱ 120,000 ያህል ቆሰሉ፡፡ በሽሬ ላይ በተደረገው ጦርነት 1,000 ያህል ኢትዮጵያውያን ሲገደሉ 4,000 ያህል ቆሰሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊትም ተበታተነ፡፡ የራስ ካሳ ሠራዊት ተንቤን ላይ በጋዝ መርዝ አለቀ፡፡
1,000 ያህል ሠራዊት ከበጌምድር ተከዜን ተሻግሮ እንዳባጉና ደረሰ፡፡ በሽሬ ግንባር በኩል የኢጣሊያው የጦር መሪ ሜጀር ከሪኒቲ በሦስት ታንኮችና በዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታገዘ 1,000 ሠራዊት አሠልፏል፡፡ እሱም እዚያ እንደደረሰ አካባቢውን የሚቆጣጠሩት 2,000 ያህል የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት እንደሆኑ ተገነዘበ፡፡ ስለሆነም የነበረው ዘመናዊ የጦር መሣሪያና የሠለጠነ የሰው ኃይል ከባበ ማድረግ በቦምብ በመደብደብ ድል ሆነ፡፡ ነገር ግን እሱና የተረፉት ጥቂት ወታደሮቹ አመለጡ፡፡ ኢትዮጵያ የዚያን ጊዜ 3,000 ባንዳዎችን መግደሏን አስታውቃ ነበር፡፡
በመጋቢት ወር 1928 ዓ.ም. ማይጨው ላይ የተደረገው ጦርነት በንጉሠ ነገሥቱ የሚመራና ከፍተኛ ቁጥር የነበረው ሠራዊት ቢሆንም 400 ኢጣሊያውያን፣ 837 ኤርትራውያንና 11,000 ያህል ኢትዮጵያውያን የሞቱበት ሲሆን የንጉሠ ነገሥቱ ጦር ድል ሆነ፡፡
በደቡብ በኩል ማርሻል ግራዚያኒ በደጃዝማች ነሲቡ ላይ ባካሄደው ዘመቻ 200 ኢጣሊያውያን ቢሞቱበትም፣ 15,000 ኢትዮጵያውያንን ገድሎ ኦጋዴንን ተቆጣጠረ፡፡
ማርሻል ባዶጋሊዮ የማያጨው ድል ከቀናው በኋላ ጉዞውን በደሴ በኩል በመቀጠል በግንቦት ወር አዲስ አበባ ገባ፡፡ ኢጣሊያ ግንቦት 23 ቀን 1928 ዓ.ም. ኢትዮጵያን፣ ኤርትራንና ሶማሊያን በማዋሀድ በምሥራቅ አፍሪካ የኢጣሊያ ግዛት መሆናቸውን በይፋ አወጀች፡፡
ኢትዮጵያ በንጉሠ ነገሥቷ አማካይነት ላቀረበችው የድረሱልኝ ጥያቄ የዓለም መንግሥታት ጆሮ ነፈጓት፡፡ ይባስ ብለው በኢጣሊያ ላይ አስተላልፈውት የነበረውን ማዕቀብ በነሐሴ ወር 1928 ዓ.ም. አነሱ፡፡ በታኅሳስ ወር 1929 ዓ.ም. ጃፓን የኢጣሊያን ቅኝ ገዥነት ተቀበለች፡፡ ፈረንሣይና እንግሊዝም ተጨመሩበት፡፡ ከዓለም አገሮች ሁሉ የኢጣሊያን ቅኝ አገዛዝ የሚቃወሙ ሜክሲኮ፣ ቻይና፣ ኒውዚላንድ፣ ሶቪየት ኅብረት፣ ስፔይን ሪፐብሊክና አሜሪካ ብቻ ሆነው ተገኙ፡፡ ኢጣሊያን ሲወጉ ከነበሩት የኢትዮጵያ የጦር መሪዎች የተወሰኑት ለኢጣሊያ ፋሽሽት መንግሥት አደሩ፡፡ የኢጣሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ የነበረውን መረጋጋት ሲመለከት የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. እጅግ አሰቃቂ ግድያ የፈጸመው ማርሻል ግራዚያኒን በማንሳት የአዎስታውን መስፍን (ሲቪል መሆኑ ነው) ሾመ፡፡ ትግራይና ኤርትራ አንድ ላይ፣ ኦጋዴንና ሶማሊያ ደግሞ አንድ ላይ አድርጋ ለአስተዳደር በሚያመች መንገድ ከፋፈለችው፡፡
በ1930 ዓ.ም. ብሪታንያና ፈረንሣይ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ቅኝ ገዥነት ከቃል ድጋፍ ወደ ጽሑፍ ስምምነት ቀየሩት፡፡ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን፣ ኤርትራንና ሶማሊያን በአንድ ላይ በምትገዛበት ጊዜ መንገድ፣ ስልክና መብራት መዘርጋት እንደ ዋነኛ የሕዝብ ማሳመኛና መግዣ ጥበብ አድርጋ ተጠቀመችበት፡፡ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል መገንባትን፣ ዘመናዊ እርሻዎችንና ፋብሪካዎችን ማቋቋምን እንደ ዋነኛ ሥራዋ አድርጋ ወሰደችው፡፡ ሕዝቡን ሰጥ ለጥ አድርጋ ለመግዛትም 150,000 ሠራዊቷን በመላው ኢትዮጵያ አሰራጨች፡፡ ይኼ አኃዝ ባንዶቿን ጨምሮ በሦስት ዓመት ውስጥ ወደ ሩብ ሚሊዮን ከፍ አለ፡፡ የሠራዊቱ ቁጥር ከፍ በማለቱ በአስተማማኝ ሁኔታ ብዝበዛውንና ጭቆናውን መፈጸም ሲጀምር ‹‹አልገዛም›› ያለው ወደ ጫካ ገባ፡፡ የሽምቅ ውጊያ ተጀመረ፡፡ በቅኝ ገዥዋ ኢጣሊያ መሪዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ጥይት በየቦታው ተተኮሰ፡፡ የሽምቅ ውጊያውን የሚያካሂዱት መኳንንቱና መሳፍንቱ ናቸው በሚል ጥርጣሬ በርካታዎቹ ታሰሩ፡፡ የአንዳንዶቹ ልጆችም በፋሽስታዊው መንግሥት ላይ በመሸፈታቸውና እነርሱ ራሳቸውም በመሸፈታቸው ምክንያት ይገደሉ ጀመር፡፡ ከእነዚህም ውስጥ እነ ራስ ካሳ፣ እነ ደጃዝማች ባልቻ፣ እነ ጄኔራል ኃይሉ ከበደ፣ እነ ራስ ደስታ ዳምጠው፣ ደጃዝማች በየነ መርዕድ፣ ወዘተ ይገኙበታል፡፡
ይሁንና የቅኝ አገዛዝን የማይቀበለው የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ ሕዝብ ወራሪውን ጦር ወግቶ በማሸነፍ ከምድረ ኢትዮጵያ በአምስት ዓመታት ውስጥ ያባረረ ሲሆን፣ ከኤርትራና ከሶማሊያም እንዲወጣ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
የኢጣሊያ ቅኝ ገዥ የመጨረሻ ህቅታ
የኢትዮጵያ አርበኞችና ወራሪውን ኃይል ለአምስት አመታት ተዋግቶ ድል ለማድረግ በተቃረበበት ጊዜ የኢጣሊያም መንግሥትም ከጀርመን መንግሥት ጋር ተባባሪ በመሆኑ፣ የባለቃል ኪዳን አገሮች (እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ አሜሪካና ተባባሪዎቻቸው ምዕራባውያን) ፊታቸውን አዙረውበት ነበር፡፡ ስለሆነም በምሥራቅ አፍሪካ የነበረውን ኃይል ለማዳከም ስትል እንግሊዝ የኢትዮጵያ አጋር ሆና ተነሳች፡፡ በዚህም መሠረት የኢጣሊያን ኃይል ከኤርትራ ለማስወጣት የጦር ኃይሏን አሠለፈች፡፡
ኢጣሊያም እጇን ከመስጠቷ በፊት በኤርትራና በኢትዮጵያ የነበሩትን ኢጣሊያውያን ደኅንነት ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ፣ በዱክ አውስታና በኢድሪስ ዓዋተ የሚመራ ኃይል ከኤርትራ ወደ ትግራይ አንቀሳቀሰች፡፡
ለመሆኑ ሐሚድ ኢድሪስ ዓዋተ ማን ነው? ታሪኩስ ምንድነው? ግርማይ እዮብ የተባሉ የታሪክ ጸሐፊ እንደሚሉት፣ ሐሚድ ኢድሪስ ዓዋተ በደቡብ ምዕራብ ኤርትራ፣ በጋሽና ሰቲት አውራጃ፣ በኦምሐጀርና በተሰነይ መካከል በምትገኝ ገርሰት ተብላ በምትጠራ ቀበሌ በ1902 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ ከ1927 እስከ 1928 ዓ.ም. የኤርትራ ቅኝ ገዥ በነበረው የኢጣሊያ መንግሥት በወታደርነት (አስካሪነት) እንዲያገለግሉ ጥሪ ቀረበላቸው፡፡ ጥሪውን ተቀብለውም ሲሄዱም የነበራቸውን ቅልጥፍና የተመለከቱት ኢጣሊያውያን አሠልጣኞች ከሮም ሰሜን ምሥራቅ 15 ኪሎ ሜትር ራቅ ብላ በምትገኘውና የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት አፍሪካውያን ፖሊሶች በሚሠለጥኑባት ‹‹ቲቮሊ›› ተብላ በምትጠራ ሥፍራ እንዲሠለጥኑ ላኳቸው፡፡ ሥልጠናውንም ካገኙ በኋላ በትሪፖሊ፣ በቤንጋዚ፣ በአስመራ፣ በአዲስ አበባ፣ በሞቃዲሾ፣ በጎንደርና በሌሎችም ኮሚሳሪያት ውስጥ አገልግለዋል፡፡
ግርማይ እዮብ ጨምረው እንደሚገልጹት ሐሚድ ኢድሪስ ዓዋተ በቤኒቶ ሙሶሊኒ (1922 እስከ 1943) ዓ.ም. ዘመን ካራቢኘሪ ተብሎ ከሚጠራው ኃይል ጋር በመሆን ኢጣሊያ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በተለይም በኤርትራ፣ በሶማሊያና በኢትዮጵያ ግዛቷ ይገጥማት የነበረውን ተቃውሞ የማፈን ኃላፊነት የተጣለባቸው ሰው ነበሩ፡፡ እርሳቸውና ባልደረቦቻቸው በ1930ዎቹ በተካሄደው የኢጣሊያና የሐበሻ ጦርነት በኤርትራና በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጸመው ግፍ በአፍሪካ የኢጣሊያ ፖሊስና ካራቢኘሪ ግንባር ቀደም ተጠያቂዎች ናቸው፡፡
በአፍሪካ የኢጣሊያ ፖሊስ ቡድን አባል መሆን የሚቻለው በሚያሳየው ታማኝነት ስለነበር ሐሚድ ኢድሪስ ዓዋተም የኢጣሊያን አገዛዝ አንቀበልም ብለው የሚታገሉትን ሱዳናውያን፣ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን በፈጸሙት ሊገለጽ የማይችል ግፍ የሚኮሩ፣ በአፍሪካ የኢጣሊያ ፖሊስና ካራቢኘሪ አባል ነበሩ፡፡ ለኢጣሊያ ቅኝ ገዥ ታማኝ ሆኖ በማገልገላቸውም በመጀመርያ የደኅንነት መኮንን ተብለው ተሾሙ፡፡ ቀጥሎም የምዕራብ ኤርትራና የከሰላ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ሆኑ፡፡ በ1932 ዓ.ም. የከሰላ (ሱዳን) አስተዳዳሪ በነበሩበት ጊዜ እንግሊዝ በ1933 ዓ.ም. የኢጣሊያን ሠራዊት እስክትወጋ ድረስ ከሰላን ከኤርትራ ግዛት ጋር አንድ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ከእዚህም ሌላ ከኢጣሊያ ባለውለታዎቹ ጋር በመሆን ከእንግሊዝ ጋር በተደረገው ጦርነት ተዋግተዋል፡፡
ኢጣሊያ በጦር ቃል ኪዳን አባላቱ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና አሜሪካ ድል ስትሆን፣ ሐሚድ ኢድሪስ ዓዋተ እንደ ፋሽሽት ወታደርነታቸው የመረረ ሐዘን ተሰምቷቸዋል፡፡ እንግሊዝ ኢጣሊያን በ1933 ዓ.ም. ድል ካደረገች በኋላም አሚዶ ጉሌት ከተባለ ኢጣሊያዊ ጋር በመሆን የሽምቅ ውጊያ አካሂደዋል፡፡
ግርማይ እዮብ እንደሚነግሩን ከመጋቢት 30 ቀን 1901 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 8 ቀን 2002 ዓ.ም. የኖረው አሚዶ ጉሌት ከ1932 እስከ 34 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ ከ2,500 ኤርትራውያን፣ ኢትዮጵያውያንና የመናውያን ጋር ሸፍቶ እንግሊዝን በሽምቅ የተዋጋ ሲሆን፣ የተረገመ የጦር አዛዥ እንደነበረ ይነገርለታል፡፡ የእንግሊዝን ግስጋሴ ለመግታት ካደረገው ጦርነት ውስጥ አምባ አላጌና ቁርደት በሚወስደው ሥፍራ መካከል በምትገኝና ጪሩ በምትባል ቦታ ላይ ያደረገው ይጠቀሳል፡፡ ጉሊት በከረን ተመትቶ የተበታተነው የኢጣሊያ ሠራዊት እንደገና እንዲሰባሰብ ከመርዳቱም በላይ፣ በአምባላጌ ጦርነት ተሸንፈው ሲሸሹ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢጣሊያውያንና ኤርትራውያን ሕይወት ለመታደግ ችሏል፡፡ ይኸው የሰሜን ጎንደር ባላባት ልጅ የሆነችና ከድጃ የምትባል ሚስት የነበረችው ኢጣሊያዊ እንግሊዝን በሽምቅ ለአንድ ዓመት ያህል ሲወጋ ከቆየ በኋላ በመጀመሪያ ወደ ሰሜን፣ ቀጥሎም ወደ አገሩ ለመግባት ችሏል፡፡
የዱቼ ሙሶሊኒን መንግሥት ለመመለስ ጥረት ያደርጉ የነበሩት ሐሚድ ኢድሪስ ዓዋተ ጉሌት ወደ አገራቸው ከገቡ በኋላ 50 ተከታዮቻቸውን ይዘው እስከ 1938 ዓ.ም. ድረስ በእንግሊዝ ላይ ሸፈቱና በትውልድ ሥፍራቸው መኖር ጀመሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ዋና ሥራቸው የኩናማ ሕዝብን ማሰቃየት ከብቶቻቸውን በመዝረፍ ወደ ከሰላ በመውሰድ መሸጥ ሲሆን፣ በዚህ ሁኔታ የተበሳጨው የእንግሊዝ መንግሥትም በ1941 ዓ.ም. እጃቸውን ይዞ ላቀረበለት 300 ፓውንድ እንደሚሰጥ አውጆ ነበር፡፡ እንደ ሐሚድ ኢድሪስ ዓወተ ሁሉ እንደ ወልደብኤል ሞሳዝጊ፣ በርኸ ሞሳዝጊ፣ ሐጎስ ተምነዎ፣ አስረሳኸኝ አምባየ የተባሉ ሽፍቶችም የዓረዛን፣ የደብሪ ዓዲ ጻዲቅ፣ በራኪት አባይ፣ የአከለጉዛይ፣ የሰራዬና የሐማሴን ሕዝብን ያሰቃዩ ነበር፡፡ በነዚህም ሽፍቶች ቁጥራቸው የማይታወቅ ጀበርቲዎች፣ ሳሆዎች፣ ኩናማዎች፣ ኸበሳዎች ተገድለዋል፡፡
በ1942 ዓ.ም. ለእንግሊዝ ጦር እጃቸውን ስለሰጡ ግን ሙሉ ምህረትና ይቅርታ ያደረገላቸው ከመሆኑም በላይ፣ የግል የጦር መሣሪያቸውን ሕይወታቸውን እንዲጠበቁበት ፈቅዶላቸዋል፡፡
የሃምሳ ዓመት ዕድሜ የነበራቸው ሐሚድ ኢድሪስ ዓዋተ በ1953 ዓ.ም. በኤርትራ ነፃነት ግንባር (ኢኤልኤፍ) የጦር መሣሪያ ትግል እንዲያካሂዱ ጥያቄ ቀረበላቸው፡፡ በ1953 ዓ.ም የጦር መሣሪያ ትግሉ እንደገና መጀመሩን ለቀድሞ ተከታዮቻቸው አወጁ፡፡ የኢኤልኤፍን የጦር መሣሪያ ትግልን ለሃያ ወራት ያህል ከመሩ በኋላ ግንቦት 12 ቀን 1954 ዓ.ም. አረፉ፡፡ የሞቱት ከምግብ ጋር የተሰጣቸውን መርዝ በልተው ነው የሚል ጥርጣሬ አለ፡፡
የጦርመሣሪያትግልየተደረገበትአርበኝነት
በአማርኛችን ‹‹አርበኛ›› የሚለው ቃል ‹‹ዓርነት/ነፃነት በእኛ ዕውን ይሆናል፤›› እንደ ማለት ነው፡፡ ከጣሊያን ጋር አምስት ዓመት የተዋጉ ኢትዮጵያውያን «አርበኞች» ተብለው ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ አርበኞች ቅኝ አገዛዝን አንቀበልም፣ ጭቆናን አንሻም፣ እንቃወማለን በማለት ጣሊያን ለመውጋት፣ በመውጋትም ድል ለማድረግ ቆርጠው ጫካ የገቡ ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ «የጦር ሜዳ አርበኛ»፣ «የውስጥ አርበኛ» አለ፡፡ የጦር ሜዳው አርበኛ ጣሊያን ከገባበት ጊዜ ጫካ ገብቶ በጦር መሣሪያ ትግል የጀመረ ሲሆን፣ አገልግሎቱም ከአንድ ቀን እስከ አምስት ዓመት ሊደርስ ይችላል፡፡ የውስጥ አርበኛው ደግሞ የጦር መሣሪያ ትግል ባያደርግም የጣሊያን ደጋፊ መስሎ ወይም ሳይመስል፣ አርበኞቹን በልዩ ልዩ መንገዶች የሚረዳና ለመርዳቱ በምስክር የተረጋገጠለት ነው፡፡ ከእነዚህም የውስጥ አርበኞች መካከል የታወቁ የኢጣሊያ ባንዳዎች የነበሩ፣ ነገር ግን ውስጥ ለውስጥ ይረዱ ነበር ተብለው የሚታሰቡ ናቸው፡፡ ዕርዳታውም አርበኛውን በጨለማ ተቀብሎ ማስተናገድ፣ ልብስ መላክ፣ ኬላ አልፎ እንዲሄድ መፍቀድ፣ ቢታሰር ማስፈታት፣ ቤተሰብ መርዳት፣ መረጃ ማስተላለፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ‹‹የጣሊያን ወታደሮች ዛሬ በዚህ በኩል ስለሚያልፉ ዘወር በሉ፤›› ወይም ‹‹ይህን ያህል ጦር ይዞ ስለተንቀሳቀሰ ጠብቃችሁ ግጠሙት፤›› የሚል ሊሆን ይችላል፡፡
በበኩሌ አርበኞች ምን እንደሚሉና እንደሚሰማቸው አላውቅም፡፡ መንግሥትም እንደ አንድ ጉዳዩ አድርጎ አያየውም የሚል ግምት የለኝም፡፡ ዳሩ ግን ነገርን ነገር ያነሳዋል በሚል ነገሩን ለማንሳት ያህልና ወጣቱም ትውልድ እግረ መንገዱን ስለድሮ አርበኞች ጥቂት ሐሳብ እንዲኖረው በማሰብ እንጂ፣ የጦር ሜዳ አርበኞች ጉዳይ በጣም ጥልቅና ወደር የሌለው በመሆኑ ወደ ልማት አርበኞች ላተኩር፡፡
የልማትአርበኞች
የልማት አርበኞች ስንል ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት እንችል እንደሆን አንዳንድ ሊሄዱ የሚችሉ መሠረታዊ ጉዳዮችን እናንሳ፡፡ በመግቢያው ላይ አርበኛ ማለት «ዓርነት/ነፃነት በእኛ ዕውን ይሆናል፤» የሚል አንድምታ እንዳለው ለመግለጽ ተሞክሯል፡፡ አርበኝነትንም ሆነ ነፃነትን ቅኝ ገዥ ጠላትን ተዋግቶ ከአገር ማስወጣት ማለት እንደሆነም ለማሳየት ጥረት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ዓርነት የሚያስፈልገው ከጠላት ጋር ለመዋጋት ብቻ ነው? የአሁኖቹ ሊቃውንት በዚህ አይስማሙም፡፡ የልማት አርበኛ በመሆንም ከፍተኛ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ ማምጣት ይቻላል፡፡
የአገርፍቅርአርበኝነት
አገርን አርበኛ ሆኖ ለማልማት ከሁሉ አስቀድሞ የሚያስፈልገው ጥልቅ የአገር ፍቅር ነው፡፡ ወጣቱን ትውልድ በአሁኑ ጊዜ በግንባር ቀደምትነት ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱ የአገር ፍቅር ስሜትና የአገር ፍቅር ወኔ ነው፡፡ የአገር ፍቅር ስሜትና የአገር ፍቅር ወኔ ከራስ ወዳድነት ስሜት ተላቆ፣ «እኔ ለአገሬ ዕድገት እሠራለሁ፡፡ ወገኖቼን ከረሃብና ከእርዛት ነፃ ለማውጣት ቆርጨ ተነስቻለሁ፡፡ ይህም ብርቱ ዓለማዬ ግብ እስኪደርስ ኃላፊነትና የሞራል ግዴታ ኖሮኝ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እከፍላለሁ፤» ከሚል የሚመነጭ ነው፡፡ «አገሬ በድህነቷ ምክንያት ተዋርዳለች፣ ዝቅ ብላ ታይታለችና ከወደቀችበት አነሳታለሁ፤» የሚል ቁርጠኛ ውሳኔ በራስ ላይ ማስተላለፍንም ይጨምራል፡፡ በተወለድንባት፣ እየተጫወትን ባደግንባት፣ በተማርንባትና ከጓደኞቻችን ጋር በጨፈርንባት አገራችን ፍትሕና ዴሞክራሲ እንዲለመልም ተግቼ እሠራለሁ ብሎ መነሳትን ይጠይቃል፡፡
የመቻቻልአርበኝነት
አገራችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የመቻቻል አርበኛ ያስፈልጋታል፡፡ የአገር ፍቅር ስሜቱ ሊጎለብት የሚችለውም የእርስ በርስ መቻቻልና መፈቃቀር ሲኖር እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡
መቻቻል በግለሰብ ወይም በተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በኅብረተሰብም ሊንፀባረቅ የሚገባው ዓቢይ ጉዳይ ነው፡፡ መቻቻል ብዙ አመለካከት፣ አስተሳሰብ፣ ፍልስፍና፣ ሃይማኖትና እምነት በሚስተናገድባት ዓለማችን በዓለማችን ዛሬ የምናያቸውን እጅግ አስቀያሚ ነገሮችን፣ ጠባብ አመለካከቶችንና የእርስ በርስ ጥላቻን ድል እንደምናደርግ አያጠያይቅም፡፡
አንድ ሰው ጠባብ የጎሳ፣ የብሔር ብሔረሰብ፣ የሕዝብ፣ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የእምነት፣ የቋንቋና የቀለም ጠባብ አመለካከት ሲኖረው በጠባብ ዓለሙ ውስጥ በብቸኝነት እንደሚኖር አያጠያይቅም፡፡ በአንድነት ላይ የተመሠረተ ብዝኃነት በተቃራኒው የመቻቻል መሠረት ሲሆን የሌሎቹ መኖር ሀቅነትን፣ የእነሱ መኖር ለእርሱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ሲቀበል ይልቁንም በአንድነት ላይ የተመሠረተ ብዝኃነትን ማስወገድ የማይችል መሆኑን ሲገነዘብ ራሱንም ሌሎችንም መጥላት ይጀምራል፡፡ በተቃራኒውም በአካባቢው ከእሱ ጋር ተመሳስሎ ተቻችሎ የሚኖር መሆኑን ሲረዳ ያኔ አዲስና አብሮ ለመኖር የሚያበቃ ሀቅ ይኖረዋል፡፡
የልማትአርበኝነት
በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ከፍተኛ የልማት ሥራዎች እየታዩ ነው፡፡ እነዚህን የልማት ሥራዎች ለማፋጠን የፖለቲካ አመለካከት፣ የሃይማኖት፣ የዘር ወይም የሌላ ልዩነት አያግደንም፡፡ በተጠቀሱትና ባልተጠቀሱት ጉዳዮች ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ አገራችንን ማልማት ያለብንም በአንድ ላይ ሆነን መሆን ይኖርበታል፡፡ በአሜሪካ ውስጥ ብዛት ያላቸው ፖለቲካዊ አመለካከቶችና ሃይማኖቶች እንዲሁም ዘሮች አሉ፡፡ ቅራኔያቸው ግን ሥርዓቱን እኔ የተሻለ አንቀሳቅሰዋለሁ ከሚል ነው፡፡ ያም ቢሆን በሕዝብ ድምፅ አሸናፊዎች ሲሆኑ ነው፡፡ አብርሃም ሊንከን የተባሉ ፕሬዚዳንቷ አገራቸው እርስ በርስ ጦርነት ስትናጥ በነበረበት ጊዜ የተናገሩት አንድ ትልቅ ቁም ነገር፣ «የመርከቧን መሪ ጨብጠን ወደፈለግነው አቅጣጫ ልንመራት የምንችለው ከሁሉ አስቀድሞ መርከቧ ስትኖር ነው፤» በማለት ሕዝብ የእርስ በርሱን ጦርነት አቁሞ ለልማት እንዲተጋ ማሰባቸው ለሁላችንም ምክር ሊሆን ይችላል፡፡ አገራችን ዘላለማዊት ስትሆን ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ግን ተለዋዋጭ ነው፡፡ ዘርም፣ ቋንቋም ተለዋዋጭ ነው፡፡ ትውልድ አልፎም ትውልድ ይተካል፡፡ ስለሆነም የጥላቻን መርዝ አስወግደን የተጀመረውን የልማት ለውጥ ማካሄድ ተቃውሞ ቢኖረንም፣ በአግባቡ እያቀረብን ለማስተካከል የበኩላችንን አወንታዊ ሚና መጫወት ይጠበቅብናል፡፡
ፈትሁላህ ጉለን የተባሉ ቱርካዊ የመቻቻልና በሰላም አብሮ የመኖር መሐንዲስ «የነፍሳችን ሐውልት» በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዳስቀመጡትም፣ «ፈጣሪ የምድር ወራሽነትን ለአንድ የተወሰነ ነገድ፣ ጎሳ፣ አገር፣ ወይም ዘር ለመስጠት ቃል አልገባም፡፡ ወራሾቹ ባሪያዎቹ በአስተሳሰባቸውም ሆነ በእምነታቸው ትክክል የሆኑ፣ የአንድነት፣ የስምምነት፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት አመለካከትን የሚያስተምሩ፣ በተግባር የሚገልጹና አጥብቀው የሚይዙ፣ ያሉበትን ዘመን የሚረዱ፣ በሳይንስና በዕውቀት የበለፀጉ፣ የዚህን ዓለምና የሚቀጥለውን ዓለም ሚዛን ጠብቀው የሚኖሩ. . . ናቸው፤» ካሉ በኋላ፣ «በዚህ ያልታደለ ጊዜ የአስተዳደርና የአስተዳዳሪዎች ድክመት በግልጽ ለመናገር ልቦናን የሚሰብር (የሚያሳዝን) ነው፤» ሲሉ የሚከተለውን አስተያየት «የነፍሳችን ሐውልት» በተሰኘው መጽሐፋቸው ይተነትናሉ፡፡
በአጭሩ አርዓያ፣ ምሳሌ፣ መነሻና፣ መለኪያ የሚሆኑን ወኔያችን፣ ቆራጥነታችን፣ የሚያነሳሳ መንፈሳችን፣ በሃይማኖት ረገድ ፍሬያማ መሆናችንን፣ (ያለፈውን ታሪካችንን) ለማረጋገጥ የሚያስችል ከባቢ ሁኔታ፣ ጽናታችን፣ በመካከላችን ውስጥ የሚገኘው ስበታችን፣ ኮስታራንታችን ምክንያት በማቅረብና በነገረ ጥበብ ችሎታችን፣ የማንናወፅ መሆናችን ለራሳችን ነፃነት የሚያጎናጽፈን ሰብዓዊ ሩኅሩህነታችን ናቸው፡፡ የፍልስፍና ጥልቀት፣ የማጣራት፣ የማሻሻል፣ ወደፊት የማራመድ፣ በኪነ ጥበብና በፍልስፍናችን ውስጥ የሚገኝ በጥልቅ እሳቤ የተሞላ አመለካከታችን፣ ይህም ሁሉ ከዋናው ማዕከል ጥራት ያለውና በአሠራር ሊያስኬድ በሚችል አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተና በራዕይ የተነሳሳ ሊሆን ይገባል፡፡
ማጠቃለያ
ውድ አንባቢያን የአርበኝነትን፣ በተለይም የልማት አርበኝነትን ትርጉም ከዚህ ከተጠቀሰው ሁሉ ሰፋ አድርገን ልናየው እንችላለን፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ሰፊ የልማት ሥራዎች እየተካሄዱ ሲሆን፣ እነዚህም ሥራዎች ዓለም አቀፍ አድናቆት የተቸራቸው ናቸው፡፡ ችግሮች እንኳን ሊኖሩ ቢችሉ የልማቱ ትሩፋት ለእያንዳንዳችን ቢደርስም ባይደርስም በአገርና በወገን ፍቅር ስሜት በርትተን ልንሠራ ይገባል፡፡ በእርግጥም ተደጋግሞ ሲነገር እንደሚሰማው ችግር ፈቺዎች እንጂ ችግር ፈጣሪዎች ወይም ጨለምተኞች ሆነን ልንገኝ አይገባም፡፡ በአጭሩ ለማለት የሚቻለው ማንም የፈለገውን ቢል የልማት አርበኝነቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ በዚህ አጋጣሚ በነፃነት ሰንደቅ ዓላማችንን እያውለበለብን ለዚህ ዘመን እንድንደርስ ላደረጉን ጀግኞች አርበኞችቻችን ዘለዓለማዊ ክብር ይገባቸዋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡