Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all 231 articles
Browse latest View live

የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ አስተዋፅኦ

$
0
0

በጌታቸው ኃይሌ

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ ‹‹የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ›› በሚል ርዕስ ባለፈው ሐምሌ (2008 ዓ.ም.) አዲስ አበባ አንድ መጽሐፍ አሳትሞ ኖሮ፣ አንድ ዘመድ አንድ ቅጂ አመጣልኝ። አነበብኩት። ስለመጽሐፉ የሚባለውንና ደራሲው ከሰጣቸው ቃለ ምልልሶች (interviews) አንዳንዶቹን ሰምቻቸዋለሁ። ከዚህ በታች የምጽፈው፣ የጽሑፌ ርዕስ እንደሚያመለክተው የደራሲውን አስተዋፅኦ ነው። ድርሰቴ የመጽሐፍ ግምገማ (Book review) ቢመስልም የመጽሐፍ ግምገማ አይደለም።

ግምገማ ቢያስፈልግስ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ዋና ምንጩ ያደረጋቸውን የአማን በላይ መጻሕፍትን እንጂ ‹‹የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ››ን አይደለም። ግን ከአማን በላይ መጻሕፍት አንዳቸውም እንደ ታሪክ ምንጭነት ለግምገማ ከሚያበቃ ደረጃ ላይ ያልደረሱ፣ አልፎ አልፎ በእውነት ታሪክ የተቀመሙ ልብ ወለድ ታሪኮች ናቸው። ዶ/ር ፍቅሬ እውነተኛ የታሪክ ምንጮች አድርጎ ተቀብሏቸዋል። ግን ዶ/ር ፍቅሬ በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ስም ያወጣ የምናደንቀው ደራሲያችን እንጂ፣ በታሪክ መስክ ከታሪክ ምሁራን ጋር ተሰልፎ አላየሁትም። እሱ ራሱም ቢሆን ‹‹ስለ[ራሱ] አጭር መረጃ›› ብሎ መጽሐፉ ውስጥ ራሱን ባስተዋወቀባቸው አንቀጾች ውስጥ ስለታሪክ ዕውቀቱ ከዚህ የተለየ ነገር የለባቸውም። መቼም ቢሆን አንድን ምሁር ችሎታው በአንድ መስክ ሥሉጥ ካደረገው በሌሎች መስኮች ላይም (ከመ፡ ዘሥልጣን፡ ቦ፡) ሥሉጥ እንደማያደርገው ለፕሮፌሰር ፍቅሬ የተደበቀ ነገር አይመስለኝም።

ሁኔታው ይኼ ሁኖ ሳለ እስካሁን ያለውን የታሪክ ምንጭ በታሪክ ጸሐፊዎች ደረጃ ምሁር ሆኖ ሳያጠናቸው መቅድሙ ውስጥ ‹‹ይህ ጽሑፍ ሀተታ እስካሁን የነበሩና የተለመዱ አንዳንድ መሠረታዊ ግንዛቤዎችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ የሚያደርግ አዲስ ታሪክ ነው፤›› ይለናል። እውነትም አዲስ ታሪክ ነው። ግን የዶ/ር ፍቅሬ ድርሰት የአማን በላይን ልብ ወለድ ታሪክ  ሚቶሎጂ (Mythology) አንዳንድ ነገር እያከለበት ከማስተጋባት አልፎ በውስጡ፣ ‹‹እስካሁን የነበሩና የተለመዱ አንዳንድ መሠረታዊ ግንዛቤዎችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ የሚያደርግ›› ቁም ነገር አላየሁበትም።

በአንዳች ምክንያት የተፈጠረ ልብ ወለድ ታሪክ (Mythology) እና እውነተኛ ታሪክ በአንድ ዘመን አንድ መስክ ላይ ስለማይውሉ ተከባብረው ይኖራሉ እንጂ አንዱ ሌላውን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አያደርግም። በእኔ ግምት መሪራስ አማን በላይና ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ብሔራዊ ሚቶሎጂ ደርሰዋል። ግን ሚቶሎጂና ታሪካዊ ጽድቆች በቅደም ተከተል እንጂ በአንድ ዘመን አይፈጠሩም። ሚቶሎጂ ይቀድማል ታሪክ ይከተላል። ሚቶሎጂ ታሪክ ከጸደቀ በኋል በታሪክነት አይወለድም። ስለዚህ ሁለቱ አብረው ጎን ለጎን አይሄዱም። ሚቶሎጂ እንደ ታሪክ ምንጭ ለብዙ ዘመናት ብቻውን ሲያገለግል ቆይቶ፣ የታሪክ ተመራማሪዎች ተነሥተው እውነተኛውን ታሪክ ሲጽፉ ሚቶሎጂ የታሪክነት ቦታውን ይለቃል። ሲለቅ ‹‹ይጣላል›› ማለት አይደለም። በሥነ ጽሑፍ ደረጃ ሕፃናት በትምህርት ቤት ይማሩታል። በአንድ በኩል፣ የግሪክን ሚቶሎጂና ታሪክ፣ በሌላ በኩል ክብረ ነገሥትንና የኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ምሳሌ መጥቀሰ ይቻላል።

የመሪራስ አማን በላይና የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ሚቶሎጂ ብሔራዊ ችግራችንን ለመፍታት በብሔራዊ ችግራችን ጊዜ የደረሰ እንጂ በራሱ ጊዜ አልተፈጠረም። መምጣት ያለበት ታሪክ ሳይጻፍ ነበር። የመጣው ታሪክ ከተጻፈ በኋላ ስለሆነ ክንፍ የለሽ አሞራ ሆኗል። እርግጥ ደራሲዎቹ ያቀረቡት እንደ እውነተኛ ታሪክ ነው። ይህም አያስገርምም፡፡ ‹‹ታሪክ ነኝ›› ማለት የሚቶሎጂ ጠባዩ ነው። ለታሪክ አዋቂዎች ግን ዘመኑ ያለፈበት መሆኑን ያልተገነዘበ የበጎ አድራጎት ፈጠራ ነው። ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ አዋቂዎች ጥቂት ስለሆኑ አብዛኛው ሕዝብ ድርሰቶቻቸውን እንደ እውነተኛ ታሪክ ወስዶላቸዋል። ሕዝቡ ታሪክ ለመማር ዕድል እስኪያገኝ ወይም የአገሩን ታሪክ የሚያውቅ አዲስ ትውልድ ተነሥቶ የአንድነታችንን እውነተኛ ምክንያት እስኪረዳ ድረስ በእነዚህ መጻሕፍት መጠቀም ሊኖርበት ነው።

እውነተኛ ታሪካችን ከዘመዶቻችን አንዳንዶቹ ቀድመው በያዙት ቦታ ላይ ሌሎች ተከትለው አንድ ቦታ ላይ (ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ) ተገናኝተው ልጆቻቸው ለብዙ ዘመናት አብረው ስለኖሩ፣ ዘመን አንድ ሕዝብ አድርጓቸዋል፣ በባህልና በደም አዛምዶናል። ለዚህ ማስረጃ የሚሆኑ ነገሮች ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ውስጥ በብዛት ይገኛሉ። በሌላ አጋጣሚ ሌላ ቦታ እንደጻፍኩት ዛሬ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ኦሮሞ፣ ዶርዜ የምንለው የለበስነው የቡድን የመለዮ (‹‹የማሊያ››) ስሞች ናቸው፡፡ አርሰናል፣ ሊቨርፑል፣ ቼልሲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ… እንደሚባሉት የእንግሊዝ ኳስ ተጫዋቾች ቡድን ማለት ነው። መለዮው አንድ ቡድን ያደረጋቸው ከየቦታው የመጡ ተጫዋቾች ናቸው። የእኛም ነገዶች ውስጣቸው ቢገለጥ ከእነዚህ ቡድኖች ብዙ አንለይም። አማራ ነኝ፣ ጉራጌ ነኝ፣ ኦሮሞ ነኝ የሚል ሰው ትውልዱን ወደኋላ መቁጠር ቢችል አላለው ላይ ይደርስ ነበር።

ዶ/ር ፍቅሬ ሚቶሎጂውን እውነተኛ ታሪክ ለማስመሰል ሲጥር ስለምንጮቹ እንዲህ ይላል፡፡ ታሪኩ የተመሠረተውም በመጽሐፍ መደብሮች በሚገኙ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ሥነ ጽሑፎች ላይ ነው። ከእነዚህ ጽሑፎች ሱዳን ኑብያ፣ ጀበል ኑባ በተባለ ሥፍራ በአንድ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ አጠገብ ተቀብረው መሪራስ አማን በላይ በተባለ ወጣት መናኝ ከ50 ዓመት በፊት የተገኙና አጥረውና ወደ አማርኛ ተተርጉመው ‹‹መጽሐፈ፡ ሱባዔ›› እና ‹‹የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ›› በሚሉ ርዕሶች የታተሙ ጥንታውያን የግዕዝ ብራና ጥቅሎች ይገኙባቸዋል። እነዚህ የኢትዮጵያ ብራና ጥቅሎች እስራኤል አገር ኩምራን በተባለ ቦታ በአንድ ዋሻ ውስጥ በእረኞች ከተገኙት የሙት ባህር ብራና ጥቅሎች ጋራ ተመሳሳይነት አላቸው። እነሱ፣ እነዚህና ሌሎችም መጻሕፍት ከስድስት ዓመት በፊት ድንገት እጄ ገቡ።

ታሪክ የማገኝባቸው መስሎኝ እኔም የአማን በላይን አንዳንድ መጻሕፍት ከዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ገዝቼ አንብቤያቸዋለሁ። ከዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጋርም በስልክ ተችተናቸዋል። አማን በላይ የጻፋቸው ሁሉ በታሪክ ዓይን ሲታዩ ከሚቶሎጂነት አያልፉም። ሰውየው ሚቶሎጂውን የደረሰው ከእውነተኛው የነገሥታት ታሪክ ላይም የሚያስፈልገውን ያህል እየወሰደ ነው። ለምሳሌ የነገሥታቱ ስም ዝርዝር እውነት የሚመስለው ከእውነተኛ ታሪክ ምንጭ ስለተወሰዱ እንጂ፣ ከጀበል ኑባ ተገኘ ከተባለው ሰነድ ውስጥ ተገኝቶ አይደለም። አንድ ንጉሥ አንድ ቀን ብቻ ነግሦ፣ የንግሡ ዕለት ሕዝቡ ሊያየው ሲጋፋ ገደለው የሚለውም ከእውነተኛው የኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ የተወሰደ ነው። ዶ/ር ፍቅሬም እንዲህ ሲል ይስማማል፡፡ አክሱማዊው ሲራክ በአክሱም የንጉሠ ነገሥት ውድም አስፈሪ [=አስፈሬ] ልጅ ከነበረው ከሕዝብ ባርኮ [= ባርክ] የሚወለድ ልዑል ሲሆን፣ የቤተ መንግሥቱ መጻሕፍት ያዥና ንብረት ኃላፊም ነበር።

እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ879 ዓ.ም. አስቴር በመባል የምትጠቀሰ ዮዲት ጉዲት በወቅቱ የነበረውን መንግሥት ገልብጣ መኳንንቱን ልትገድል ስታሳድድ አክሱማዊው ሲራክ መጽሐፈ ሱባዔንና ሌሎችንም ጠቃሚ ቅርሶችን ይዞ ከአክሱም ወደ ግብፅ ተሰደደና በኑቢያ ተቀመጠ። በመጽሐፈ ሱባዔ ውስጥ ታሪከ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ የተሰኘ ሌላ መጽሐፍ ነበር። ታሪከ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ከቀዳማዊ ኢትዮጵ ጀምሮ በዮዲት እስከተገለበጠው የመጨረሻው የአክሱም ንጉሠ ነገሥት እስከ ንጉሥ ውድም አስፈሪ [= አስፈሬ] ድረስ የነበሩትን ነገሥታት የሚዘረዝር ነው። አክሱማዊ ሲራክ ታሪከ ነገሥትን ጨምሮ መጽሐፈ ሱባዔን ከግዕዝ በፊት ከነበረው ከጥንቱ የሱባ ቋንቋ በሦስት ቋንቋዎች ተርጉሞ ለትውልድ እንዲደርስ አድርጓል።

ደራሲው እንደሚለው እነዚህ የኢትዮጵያ ብራና ጥቅሎች የተባሉት እውነት ከቁምራን ብራና ጥቅሎች ጋር ተመሳሳይነት ቢኖራቸው የዓለም ሊቃውንት ለቁምራን ብራና ጥቅሎች የሰጡትን ከፍተኛ ትኩረት ይሰጧቸው ነበር። እነዚህ በሱባ ቋንቋ የኢትዮጵያ የብራና ጥቅሎች የተባሉ ምንጮች ግን አማን በላይ ለሚቶሎጂው የፈጠራቸው ስለሆኑ በአካል የሉም። በዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ሽፋን ላይና ውስጥም ያሉት ‹‹የሱባ ቋንቋ›› ሥዕሎች የአማን በላይ አንጎል የፈጠራቸውና ብዕሩ የሳላቸው ናቸው። የጥቅሎቹ የመገኘት ታሪክ በዓለም በተከበሩ ምሁራዊ መጽሔቶች ላይ አንድም ቦታ ያልተነበበው ስለእነዚህ ነው። ሌሎቹ ቢቀሩ እንኳን አዲስ አበባ የሚታተመው “Journal of Ethiopian Studies” እና የዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ፒኤችዲ ፈታኝ የነበረው ፕሮፌሰር ሪቺ ኖፖሊና ሮም ውስጥ ያሳተመው የነበረው “Rassegna di Studi Etiopici” ታሪኩ እውነት ሆኖ ቢያገኙት ተሽቀዳድመው በደስታ ያወጡት ነበር። ቀርቦላቸው አላወጡት እንደሆነ ፈጠራ መሆኑን ተረድተውት ነው።

ይኼን የምለው ከእነዚህና እነሱን ከመሰሉ ሌሎች መጽሔቶች ጋር የቅርብ ግንኙነት ስላለኝ ነው። ታሪኩ ለምን እነዚህ መጽሔቶች ላይ እንዳልተነበበ ዶ/ር ፍቅሬ ቢጠየቅ አሳታሚዎቹን ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ጠበብት ተብዬዎች›› እያለ ስለሚመጻደቅባቸውና የሚጽፉትንም ‹‹የጠነዙ ገለጻዎች›› እያለ ስለሚሰድባቸው ምን መልስ እንደሚሰጥ መገመት አያዳግትም። በእሱ ግምት ይኼንን የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመሰክር ምንጭ እንኳን ልናሳትመው ዞር ብለንም እንኳን አናየውም። አንድ ወዳጄ የሆነ ሰው ወዳጁን አማን በላይን፣ ‹‹አገኘኋቸው ስለምትላቸው የብራና ጥቅሎች፣ ጌታቸው ኃይሌን አነጋግረው›› ብሎት እንደነበረና አማን በላይም ተስማምቶ እንደነበረ ወዳጄ ነግሮኛል። አማን በላይ ወደኔ አልመጣም፡፡ እዚያው አዳማጭ ካገኘበት ቀርቷል ማለት ነው።

ታሪካችንና አዲሱ ሚቶሎጂ ከማይስማሙባቸው ብዙ ነጥቦች ውስጥ ጥቂቶቹን ላሳይ በኢትዮጵያ መልክዐ ምድር ላይ ብዙ በኦሮሞ ስሞች የተጠሩ ቦታዎች አሉ። እነዚህ የቦታ ስሞች ኦሮሞዎች በ16ኛው ምዕት ዓመት ኢትዮጵያን ሲይዙ የተሰየሙ እንጂ ለዶ/ር ፍቅሬ እንደመሰለው ጥንታዊነት የላቸውም። ከ16ኛው ምዕት ዓመት በፊት እንደሌሉ ማስረጃው ከዚያ በፊት በተሣሉ ካርታዎች ላይ አለመገኘታቸው ነው።

2.    ‹‹ጎሳ ‹‹ጐሥዐ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ነው›› ይላል። ልክ አይደለም፡፡ በሁለት ቋንቋዎች ውስጥ ተመሳሳይ ድምፅ ያላቸው ቃላት ሁሉ ተመሳሳይ ሥርና ትርጉም እንዳላቸው የሚያውቅ የፊሎሎጂ ዕውቀት ያለው ሰው ብቻ ነው። አለበለዚያ የእንግሊዝኛውን “grocery” ከአማርኛው “ጥሮ ግሮ ሠሪ” ጋር ያዛምዳቸዋል። ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ተመሳሳይ ድምፅ ያላቸው ቃላት ሲያጋጥሙት ሳያዛምድ አይለቃቸውም። ይኼ “’folk’s etymology” ‘ሕዝባዊ የቃላት ሥር ትንተና’ ይባላል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን አንድ ታሪክ ላንሣ፡፡ አንድ ጊዜ አንድ መምህር ‹‹ዕንቁ ጣጣሽ›› ማለት ከየት የመጣ ነው ቢሉት፣ ‹‹ንጉሥ ሰሎሞን ንግሥተ ሳባን ሲያግባባት ጣጣሽ ዕንቁ ነው ብሎ ዕንቍ ሰጥቷት ስለነበረ ቃሉ ከዚያ ሲያያዝ የመጣ ነው፤›› አሉ። አቶ ጸጋዬ ገብረ መድኅንም እንዲህ ዓይነት መሠረተ ቢስ የቃላት ትንተና ነበረው።

3.    የንግሥተ ሳባ ስም ኤትያኤል የእናቷ ስም አዝሚና ነው። ይህ የአማን በላይ ልብ ወለድ ታሪክ ከእውነተኛው ታሪክ ጋር አብሮ አይሄድም። እነዚህ ስሞች ከአማን በላይ ሚቶሎጂ ውጪ የትም እሌላ ቦታ አይገኙም። ብሉይ ኪዳን ስሟን ሳይጠራ ‹‹የሳባ ንግሥት›› (በዕብራይስጥ ‹‹ማልከት ሽባ››) ብሎ ነው ያለፈው። ዓረቦች ‹‹ቢልቂስ›› ይሏታል። ክብረ ነገሥቱ ‹‹ማክዳ›› የሚለው እሷን ሊሆን ይችላል፡፡ ግን አጥጋቢ ማስረጃ የለንም።

4.    ንግሥተ ሳባን “እየሱስ ክርስቶስ ‹‹የአዘቦ ንግሥት›› ሲል ጠርቷታል ይልና ማብራሪያውን እንዲህ ሲል ይቀጥላል፡፡ ‹‹አዜብ›› የሚለው ቃል ከየት የመጣ ነው? ከንግሥተ ሳባ ህልውና ከ900 ዓመት በፊት ኢትዮጵያን ይገዛ የነበረ ንጉሥ ስም ነው፤›› ይላል። ይኼ አነጋገር ለሚቶሎጂም እንኳን ይበዛል። ወንጌላውያን ቃሉን በግሪክኛ እንደመዘገቡት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ያላት “ባሲሊሳ ኖቱ” ነው። ይኼ ወደ ግዕዝ ሲተረጐም ‹‹ንግሥተ አዜብ››፣ ወደ አማርኛ ሲተረጐም ‹‹የደቡብ ንግሥት››፣ ወደ እንግሊዝኛ ሲተረጐም “Queen of the south” ይሆናል። ኖቱ፣ አዜብ፣ ደቡብ፣ “south” አራቱም ትርጕማቸው አንድ ነው። ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ወንጌሎቹ የተጻፉት በግዕዝ መስሎታል።

5.    ገጽ 101 ላይ በአማርኛ ፊደል የተጻፈ ኦሮምኛ ክርታስ (ጥቅል) አትሞ፣ ‹‹የጥቅሉን ዕድሜ በትክክል ልነግርዎ አልችልም፤ እንደሚያዩት ግን ዕድሜ-ጠገብ ይመስላል። ቢያንስ አንድ ሺሕ ዓመት እገምተዋለሁ። በአንድ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ገዳም ውስጥ ነው የተገኘው፤›› ይለናል። አንደኛ፣ ከብራና ጽሑፍ ጋር በቂ ልምምድ የሌለው ሰው ጽሑፉን አይቶ ዕድሜውን መገመት አይችልም። ሁለተኛ፣ የተጻፈው በአማርኛ ፊደል እንጂ፣ በግዕዝ ፊደል አይደለም። እዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሚታዩት እነ ‹‹ጨ›› እነ ‹‹ቸ›› ከአንድ ሺሕ ዓመት በፊት አልተፈጠሩም ነበር። ሦስተኛ፣ የጠቅላላ ፊደሎቹ አጣጣል እንደሚያመለክተው፣ የዚህ ጽሑፍ ዕድሜ ከአንድ መቶ ዓመት አይበልጥም።

6.    ገጽ 84-89 ላይ (መጽሐፉ ሽፋን ላይም) የሱባ መጽሐፍና ፊደላት ይገኛሉ። ሊተረጉማቸውና ሚስጥራቸውን ሊፈታ የሚችለው ፈጣሪያቸው አማን በላይ ብቻ ነው። ግን መዝገበ ቃላትም አብሮ ተገኝቷል ሲል ሚቶሎጂውን ተአማኒ አስመስሎታል።

7.    ከሦስት ሺሕ ዓመት በፊት ቀዳማዊ ምኒልክ ‹‹ኦቺ›› የተባለና ከመደባይ/ኦሮሞ የተውጣጣ ጠንካራ ሠራዊት ነበረው [ቀ]ዳማይ ምኒሊክ ይህንን ጦሩን ‹‹ጨዋ›› (ሸዋ) ብሎ ሰየመውና የዛሬውን ማዕከላዊ ኢትዮጵያን ወረረ። ከዚያም ጦሩን በወረረው በዚህ ቦታ ላይ አሰፈረና አገሩን በጦሩ መጠሪያ ‹‹ጨዋ›› (ሸዋ) ብሎ ጠራው›› ይላል።

ታሪካችን እርግጥ ወታደሮችን ጨዋ ይላቸዋል። ግን ‹‹ጨዋ›› እና ሸዋ በግድ ካላዛመዷቸው የተፈጥሮ ዝምድና የላቸውም። (‹‹ጨዋ›› ከ ‹‹ፄዋ›› የመጣ ሊሆን ይችላል።)

8.    ቀደም ብሎም ቀዳማዊ ምኒልክ የእናቱ ወገን ከሆኑት ከኢትዮጵያውያን ጋር ሲዋጋ ያገዙት ወታደሮች አግአዚ የተባሉ ከጋዛ የመጡ እሥራኤሎች ነበሩ። አግአዚ የተባሉት ከጋዛ ስለመጡ ነው ይላል። ይህ የልብ ወለድ አባባል ከታሪክ ጋር አብሮ አይሄድም። አግዓዚና ጋዛም ከድምፅ ተመሳሳይነት ያለፈ ግንኙነት የላቸውም። ደግሞስ በምን ምክንያት ነው ቀዳማዊ ምኒልክ የእናቱ ወገን ከሆኑት ኢትዮጵያውያን ጋር ውጊያ የገጠመው?

9.    ‹‹አክሱማይትና ሁሉም የአክሱማይት ተወላጅ ነገሥታት ከሜሶፖታሚያ ድረስ ግብር የሚያመጡላቸው ንጉሦች በሥራቸው ነበሯቸው፤›› ይላል። ይህንን ልብ ወለድ አባባል ሚቶሎጂ ይቀበለዋል፣ ታሪክ ግን አይቀበለውም። በዚያ ዘመን ከሜሶፖታሚያ ተነሥተው ለአክሱም ነገሥታት ግብር ገብረው ለመመለስ ምን ያህል ጊዜ ይወስድባቸዋል? ደግሞስ በዚያን ዘመን በምን ኀይልና መንገድ ነው የአክሱም ነገሥታት ሜሶፖታሚያ (ኢራቅ) ድረስ የሚያስገብሩት?

10. ‹‹“አፄ” ወይም ‹‹እሴ›› ስመ-ክህነቱ ‹‹እስያኤል›› የተባለው ልእለ-ሰብእ ንጉሠ ነገሥት 480 ዓመት በሕይወት ኖረ ሲባል ያሥገርም ይሆናል፤›› ይላል። በሚቶሎጂ አያስገርምም፣ በታሪክ ግን እርግጥ ያስገርማል። ‹‹አፄ›› እና ‹‹እሴ››ም ከድምፅ ያለፈ ዝምድና የላቸውም።

11. “Magician” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ማጂ ከሚለው ከኦሮሚኛ ስም የተወሰደ ነው ይላል። ሁለቱ እንዴት ተገናኝተው ይህ ሊሆን እንደተቻለ የሚያሳይ ተጨማሪ ተረት ያስፈልጋል።

12. ገጽ 59 ላይ የመናዝል ምስል በረጅም የሚቶሎጂ ታሪክ ታጅቧል። ሥዕሉ ለአሥራ ሁለቱ ወራት የተሰጡትን የአሥራ ሁለቱን ከዋክብት ስሞች ይዟል። ሥዕሉ ለአዲሱ ሚቶሎጂ የጠቀመው እኛ ኢትዮጵያውያን ፕላኔቶቹን ሁሉ ከጥንት ጀምሮ የተመራመርን ለመሆናችን ማስረጃ በመሆን ነው። ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ስለ ሥዕሉ እንዲህ ሲል ጽፏል፡፡ ‹‹ከላይ የቀረበውን ምሥል በፊርማቸው አረገግጠ‹ወ›ው በኢንተርኔት ያደረሱን ዶ/ር አየለ በከሪ ናቸው። ደሸት (?) የዞዲያኩን ምሥል የመሥራት ሐሳብ የመጣለት ከኖኅ ወደ መልከጼዴቅ ከዚያም ወደ ኢትዮጵ በቅብብሎሽ ከመጣና ለእኔም ከደረሰኝ የዩኒቨርስን አፈጣጠር ከሚተርክ አንድ ጥንታዊ መጽሐፍ ነው፤›› ይላል። አተራረኩ ጥሩ ሚቶሎጂ ሊሆን ይችላል። በታሪክ አንፃር ሲታይ ግን፣ ሥዕሉ አዲስ አይደለም፣ ስሙም ‹‹መናዝል›› ይባላል። በባሕረ ሐሳብ የብራና መጻሕፍት ሁሉ በየገዳማቱ ይገኛሉ። ሥዕሉ የወራትን ስም ስለሚያመለክት ኮከብ ቆጣሪዎች በእነዚያ ወራት የተወለደን ሰው ጠባይ መናገሪያ ያደርጓቸዋል። እውነቱ ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ዘዴውን ከነሥዕሉ የወሰድነውም ዓረብኛ ከምትናገር የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ነው። የወሰድነው የከዋክብቱን ስማቸውን እንኳ ወደእኛ ቋንቋ ሳንተረጉም እንዳለ በዓረብኛው ነው። አሰድ (አንበሳ)፣ ሰውር (በሬ)፣ ዓቅራብ (ጊንጥ)፣ ሑት (ዓሳንበሪ)፣ ወዘተ.

13.  ደሸት (ደሴት) ማነው? እንደ ሚቶሎጂው አቀራረብ፣ የአማሮችና የኦሮሞዎች አባት ነው። --አማሮችና ኦሮሞዎች ከአንድ አካባቢ ከጐጃም፣ ከአንድ አገር ከኢትዮጵያ የተገኙ ናቸው ለማለት ነው። የታሪክ መጻሕፍት የሚናገሩት ስለጣና ‹‹ደሴት›› ስለሆነ ‹‹ደሴት›› የኦሮሞና የአማሮች አባት ስም ሆነ። ‹‹ደሴት›› (island) ነው። ‹‹ደሸት›› ከሚለው ስም ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ሆኖም ስለ ደሸት (ደሴት) የተጻፈው ልብ ወለድ ታሪክ ‹‹ኦሮሞዎች ከባሕር ወጣን›› ለሚሉት ማስረጃ ስለሆነ፣ ሊነበብ የሚገባው ነው። እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ስለ ደሸት ስንናገር ምንም እንኳን ተረት ቢመስልም ሀቅ ስለሆነውና ለየት ስለሚለው ውልደቱ [= ልደቱ] መናገር ጠቃሚ ነው። የቤላም (በልዓም) የልጅ ልጅ የሆነችው እናቱ ነቢይትዋ ሼምሼል መነኩሲት ነበረች።

ከወንድ እርቃ በግዮን አካባቢ በገዳምም ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወት ትመራ ነበር። አንድ ቀን በግዮን ወንዝ ሳይሆን አይቀርም ገላዋን ስትታጠብ የወንድ ዘር በማህፀንዋ ዘልቆ ገባና ደሼት (ደሴት) ተፀነሰ። . . .     ይህ የሆነው ከሦስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመት በፊት ስለሆነ ማስረጃው ሁሉ ቢጠፋ አያስገርምም፤›› ይላል። ኦሮሞዎች ከባሕር ወጣን የሚሉት፣ የኦሮሞና የአማራ አባት ደሼት (ደሴት) ውኃ ውስጥ ስለተፀነሰ ነው ማለት ነው። ግሩም የሚቶሎጂ ትረካ ነው። ግን ከታሪክ ጋር አብሮ አይሄድም። ነቢዩ በልዓም ይኖር የነበረው ሜሶፖታሚያ (ኢራቅ) ነበር። ሚቶሎጂውን ለማሟላት ሼምሼልን ከዚያ አንሥቶ ጎጃም ላይ የጣላትን የንፋስ ሰረገላ ፈጥሮ ታሪኩ ቢጨመርለት ጥሩ ነበር።

‹‹ዓላማ ዘዴን ያጸድቀዋል›› እንዲሉ፣ ‹‹ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ ዓላማው አማሮችና ኦሮሞች በአንድ አገር ውስጥ በወንድማማችነትና በሰላም እንዲኖሩ ምክንያት ለመስጠት ስለሆነ በምንም ዘዴ ቢጠቀም ክፋት አናይበትም፤›› የሚሉ አሉ። እንዳፋቸው ያድርግላቸው።

በመጨረሻ፣ ለመሪራስ አማን በላይ አንድ ጥያቄ ላቅርብ፡፡ አንዳንድ የታሪከ ነገሥት ቅጂዎች ተገኝተው ታትመዋል፡፡ የታተሙት ሁሉ የየራሳቸውን አዳዲስ ነገሮች አስተምረውናል። አንተም ያገኘኸው ታሪከ ነገሥት በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን የተቀዳ ስለሆነ፣ አንዳንድ አዳዲስ ነገሮች ሊኖሩበት ይችላልና የታሪክ ምሁራን እንዲመረምሩት እባክህ አሳያቸው። ከፈቀድክ ዋናውን አለዚያም የፎቶ ኮፒውን ቅጂ ለአዲስ አበባ ወይም ለደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ልትሰጥ ትችላለህ። መሪራስ ሆይ፣ በጎውን ይምራህ።

ማስታወሻ፡- የሚቀጥለው ጽሑፌ፣ ሴማዊ፣ ኩሻዊ፣ ሐበሻ፣ ኢትዮጵያ›› የሚሉትን ስሞች የሚተች ይሆናል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

Standard (Image)

የተሃድሶው ስኬት በቁጥቁጥ ውጤቶቹ መለካት የለበትም

$
0
0

በከበደ ካሳ

ኢሕአዴግ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየተነሱ ላሉ የሕዝብ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች መንስዔ የሆኑትን ለይቶ ለመፍታት እንዲቻል ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ላይ ይገኛል። የተሃድሶ ሒደቱ ከተጀመረ አምስት ወር ሆኖታል። ተሃድሶው ምን ውጤት አስገኘ? የሚለው ጥያቄ ወደ ኋላ የምመለስበት ሆኖ በቅድሚያ ግን በተሃድሶው ሒደት ላይ የሚታዩ የተዛቡ አስተሳሰቦችንና ትችቶችን፣ ከእነዚህም በመነሳት የሚደረሱ የተሳሳቱ ድምዳሜዎችን መተቸት እፈልጋለሁ።

በእኔ እምነት በጥልቅ ተሃድሶው ላይ የሚታዩ ሦስት ዋና ዋና የተዛቡ አስተሳሰቦች አሉ። አንደኛው የተሃድሶውን የስኬት መጠን በተባረረና ፖለቲካዊ ወይም ሕጋዊ ዕርምጃ በተወሰደበት አመራር መጠን መመዘን ሲሆን፣ ሁለተኛው ከዚህ ተሃድሶ የመስመር ለውጥ (ideological shift) ወይም የመስመር ማጥራት (ideological purification) መጠበቅ ነው። ሌላው የተሳሳተ አስተሳሰብ ተሃድሶውን የቀናት ወይም የጥቂት ወራት ሥራ አድርጎ መውሰድ ነው። እነዚህ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች የሚንፀባረቁት ደግሞ ከድርጅቱ ውጪ ባሉት ብቻ ሳይሆን፣ በተሃድሶው ሒደት ውስጥ በማለፍ ላይ በሚገኙ የድርጅቱ አባላትም ጭምር ነው።

ስኬቱንርምጃበተወሰደበትአመራርመጠንመመዘን

የአንድ ፕሮጀክት የስኬታማነት መጠን የሚወሰነው መርሐ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት ከተቀመጡለት ዓላማዎችና ግቦች አንፃር ነው። ኢሕአዴግ እያካሄደ ያለውን ዳግም በጥልቀት የመታደስ ሒደት ከመጀመሩ በፊት ተሃድሶው በአጭርና በረጅም ጊዜ ያስገኛቸዋል ያላቸውን ውጤቶች አስቀምጧል። የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የኢሕአዴግ ምክር ቤት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ባካሄዱት ስብሰባ፣ በዚህ ዳግም በጥልቀት የመታደስ ሒደት ድርጅቱን ቀጣዩን የትግል ምዕራፍ ሊመራ ከሚያስችለው የአስተሳሰብ ጥራትና ከፍታ ላይ ማድረስ፣ እንዲሁም በሒደት እየተሸረሸሩ የመጡ የድርጅቱን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ ወደ ቀደመው መመለስ የሚሉ ዓላማዎችን አስቀምጠዋል።

ምክር ቤቱና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለተሃድሶው ከቀረጿቸው ግቦች መካከል ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የድርጅትና የመንግሥት ሥልጣንን ያላግባብ ለግል ኑሮ መሠረት ለማድረግ የሚታየውን ዝንባሌ ለማረምና ለመግታት የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን መውሰድና ከራሳቸው ጀምሮ የሚታዩ የጥገኝነት አስተሳሰቦችና የዚህ መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህተኝነትን በጥብቅ ታግሎ ማስተካከል ይገኙበታል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በማስረፅና ለትውልድ ባህል አድርጎ በማቆየት ረገድ የላቀ ሚና ያላቸውን እንደ የሕዝብ ምክር ቤቶችን፣ ብዙኃን ማኅበራትን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የመገናኛ ብዙኃን ዓይነት የዴሞክራሲ ተቋማትን ከመደገፍና ከማብቃት አኳያ ድርጅቱ ያጋጠሙትን ውስንነቶች ምንም ዓይነት መንጠባጠቦች ሳይኖሩ በሙሉዕነት የመፍታት ግቦችንም አስቀምጠዋል።

ይህ አስቀድሞ የተቀመጠ ግብና ዓላማ ከታየ የተሃድሶው ውጤት ባባረረው ወይም ፖለቲካዊና ሕጋዊ ዕርምጃ ባስወሰደበት አመራር መጠን ሊለካ አይችልም፣ አይገባምም። ምክንያቱም ድርጅቱን ከላይ እስከ ታች ላጋጠመው የአመለካከት ዝንፈት ዋናው መፍትሔ ሰዎችን ማባረር ወይም ማሰር ወይም መቅጣት አይሆንም። መፍትሔው በድርጅትና በመንግሥት ሥልጣን አጠቃቀም ዙሪያ የተከሰተውን ጉድለትና የዚህ መገለጫ የሆኑ አስተሳሰቦችን ታግሎ ማስተካከል ነው። ይህ ማለት አመራሩም ሆነ አባሉ የወደቀበትን ቦታ ሳይሆን የተዳለጠበትን ቦታ ለይቶ ችግሩን ከመሠረቱ መንቀል ማለት ነው። አመራሩ ከመውደቁ በፊት ያዳለጠው ደግሞ የድርጅትና የመንግሥት ሥልጣንን የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ከማዋል ይልቅ፣ የግል ኑሮ መሠረት አድርጎ መመልከት የጀመረ ጊዜ ነው። ስለዚህ እንደ ሌሎች ጊዜያት በሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ተመሥርቶ ‹‹ሠርተሃል››፣ ‹‹አልሠራህም›› የሚል ሰዎችን የማንሳትና የማሸጋሸግ ጉዳይ ሳይሆን፣ መሠረታዊ የሆነ የአስተሳሰብ ትግል የተደረገበትና ድርጅቱ ውስጣዊ የአስተሳሰብ ጥራቱን ያስጠበቀበት ሒደት መሆኑን ማረጋገጥ ነው የሚያስፈልገው፡፡

ይህ መሠረታዊ ሐሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ ለዳግም ተሃድሶው ከተቀመጡት ግቦች አንዱ ለቀጣይ የተግባር ጉዞ አስተማሪ ይሆን ዘንድ ውጤት በማያስመዘግቡ፣ ወንጀል በፈጸሙና በከፋ የሥነ ምግባር ችግር ውስጥ በገቡ አመራሮች ላይ ተገቢ የሆነ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃዎችን በማያዳግም ሁኔታ መውሰድ የሚል ይገኝበታል። የአመለካከት ብልሽታቸው በተጨባጭ ደረቅ ወንጀል ላይ እንዲሳተፉ ላደረጋቸው አመራሮች፣ ከፖለቲካዊና ከአስተዳደራዊ ዕርምጃዎች (ማስጠንቀቂያ፣ ከኃላፊነት ዝቅ ማድረግ፣ ከማዕከላዊ ኮሚቴ ወይም አባልነት ማገድ፣ ወዘተ…) በተጨማሪ ሕጋዊ ተጠያቂነት መከተል አለበት፣ እየተከተለም ነው።

በቅርቡ የፌዴራል ፖሊስ በሰጠው መግለጫ በጋምቤላ ክልል በመንግሥት ውስጥ ያሉ የአሠራር ክፍተቶችን ተጠቅመው በመመሳጠር የሕዝብና የመንግሥት የጋራ ሀብት የሆነውን መሬት በመዝረፍ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ግለሰቦች ተጋልጠዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ድርጅቶችም እንዲሁ ቁጥራቸው ቀላል በማይባል አመራሮች ላይ በተለያየ ደረጃ ዕርምጃ ወስደዋል። ለአብነት ብአዴን የሚመራው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት 748 ያክል አመራሮችን ከኃላፊነት አንስቷል። ድርጅቱ የሙስና ወንጀል በፖለቲካና ግለሰባዊ ግምገማ ብቻ ሊደረስበት አይችልምና ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም የግል ሀብት ያፈሩ አካላትን ወደ ሕግ ማቅረብ የሚያስችል መስቀለኛ ማጣራት እንዲካሄድ ውሳኔ አስተላልፏል። ይህ ውሳኔ በተጠረጠሩ ባለሥልጣናት ቤተሰቦች ላይ ተጨማሪ ማጣራት እስከማካሄድ የሚደርስ ነው። ስለሆነም የጥልቅ ተሃድሶው መድረክ በዋነኛነት እንቅፋት የሆኑ አመለካከቶችን በመቀየርና ወደቀደመ ሕዝባዊና አብዮታዊ ባህሪ መመለስ ላይ ተመርኩዞ፣ ከዚህ በመለስ ደግሞ አስፈላጊውን ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን በመውሰድ እየተጓዘ እንደሚገኝ ማየት ይቻላል።

ተሃድሶውንየተጠናቀቀአድርጎመውሰድ

ኢሕአዴግ ተሃድሶ አደረግሁ ቢልም መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎችን እስካሁን አልፈታም ተብሎ ትችቶች ሲሰነዘሩ ይደመጣል። ባለፈው ዓመት ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ የድንበርና የወሰን ጉዳዮችን፣ የማንነት ጥያቄን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን፣ የሥራ አጥነት ችግርን፣ ወዘተ… በምሳሌነት በማንሳት ሒደቱን ፍሬ አልባ ለማስመሰል የሚጥሩ አሉ። አንዳንዶቹ ከዚህ ተነስተው ለውጥ አይመጣም ወደሚል ድምዳሜ መድረስ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችም በዚሁ ቅኝት እንዲሄዱ የሚገፉ ጽሑፎችን አውጥተዋል። ቀድሞም እንዳደረጉት የሕዝቡን ተገቢና ፍትሐዊ ጥያቄዎች ለፖለቲካ አጀንዳቸው ማድመቂያነት ለመጠቀም የሚቀሰቅሱትን ሳይሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ በግንዛቤ ማነስ የተነሳ የተፈጠሩ ብዥታዎችን ማጥራት ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ።

ተሃድሶውን የተጠናቀቀ አድርጎ የመውሰድ የተሳሳተ አመለካከት የሚመነጨው ተሃድሶውን ሒደት (process) ሳይሆን ኩነት (case) አድርጎ ከማሰብ ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት አምስት የተሃድሶ ወራት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴንና ምክር ቤቱን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች፣ በየደረጃው ያሉ መካከለኛና ጀማሪ አመራሮችና የሚበዛው የድርጅቱ አባል በተሃድሶው የግምገማ መድረክ ውስጥ አልፈዋል። ነገር ግን ይህ ተሃድሶ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የተጀመረ ይሁን እንጂ፣ አገራዊ እንቅስቃሴ ሆኖ እንዲወጣ አስቀድሞ ግብ የተቀመጠለት ነው። ይህ ማለት መሪው ድርጅት ብቻ ሳይሆን በፓርቲው የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት፣ ከዚያም መላው ፈጻሚ ሕዝብ በተሃድሶው ውስጥ ያልፋል ማለት ነው። የአሁኑን ተሃድሶ ከመጀመሪያው ተሃድሶ ከሚለዩት ጉዳዮች አንዱም ይኼው ንቅናቄውን በስፋትና በጥልቀት ለማስኬድ የተያዘለት ዓላማ ነው። በሌላ ጸሐፊ አገላለጽ፣ ‹‹አሁንኢሕአዴግናመንግሥትብቻአይደሉምእየታደሱያሉት።ሕዝቡናዜጎችምእየታደሱነው።ዴሞክራሲያችን፣ልማታችን፣አብሮነታችን፣መቻቻላችን፣ዴሞክራሲያዊአንድነታችን...ወዘተየመሳሰሉትበተሃድሶውሒደትውስጥያልፋሉ፡፡››

በዚህ መሠረት ሰሞኑን በመንግሥት ሠራተኞች የተጀመረው የተሃድሶ መድረክ ወደ አጠቃላይ የሕዝብ ውይይት ይሸጋገራል። ወጣቶችና ሲቪክ ማኅበራትም የዚሁ አካል ናቸው። ኢሕአዴግ በምርጫ ቦርድ ዕውቅና አግኝተው እየተንቀሳቀሱ ካሉ ሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች (የሥነ ምግባር አዋጁን ከፈረሙትም ካልፈረሙትም) ጋር የምርጫ ሕጉን ጨምሮ በሌሎች የፖለቲካ አጀንዳዎች ላይ የሚያደርገው ውይይትም፣ በዚሁ የድርጅቱ የመታደስ ሒደት ውስጥ የሚታይ ነው። እነዚህ መድረኮች የራሳቸውን ጊዜ የሚጠይቁ ናቸው።

በሌላ በኩል እነዚህ ሁሉ የተሃድሶ መድረኮች ምንም እንኳን አጀንዳቸው በተግባር ያለፍንባቸው አፈጻጸሞች ቢሆኑም አፍኣዊ ውይይት ከመሆን አይድኑም። በተጨባጭም ሕዝቡን ለቅሬታ የዳረጉ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው መድረኮቹ ላይ በቀረቡ አስተያየቶችና ውሳኔዎች ሳይሆን፣ እነዚህን አስተያየቶችና ውሳኔዎች ጨብጦ መሬት በማስነካት ነው። በመድረኮቹ ውይይት የተደረገባቸው ጉዳዮች በአዲስ መንፈስና ቁርጠኝነት የሚመሩ አመራሮችንና ፈጻሚ ሕዝብን ይፈልጋሉ። እናም በተግባር የተፈጸሙ ጥያቄዎች የታደሰ ተግባራዊ ምላሽ ይሻሉ ማለት ነው። ለአብነት የወጣቶች ችግር የሚቀረፈው መድረኮቹ ላይ በተቀመጡት አቅጣጫዎች ብቻ ሳይሆን፣ ይህን ይዞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ባለቤት ማድረግ ሲቻል ነው። ተሃድሶው ግቡን የሚመታውም ያኔ ነው። እነዚህን አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ለመፈጸም ደግሞ ገና እየተካሄዱ ባሉት የተሃድሶ የግምገማ መድረኮች ስምምነት ላይ ደርሶ መውጣት የማስፈለጉ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ የአፈጻጸም ጊዜም ይጠይቃል። የተሃድሶውን ስኬታማነት ለመለካት የተጠቀሱት መርሐ ግብሮች የሚወስዱትን ጊዜ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።

ያም ሆኖ የጥልቅ ተሃድሶው ፋይዳ እንዲሁ በአጭር ጊዜ ወይም የተነሱ የሕዝብ ቅሬታዎችንና ችግሮችን በመመለስ ላይ የታጠረ ተደርጎ መወሰድ አይገባውም። እንደሚታወቀው ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ የተካሄደው የመጀመሪያው የኢሕአዴግ ተሃድሶ በዛው ዓመት ካስገኛቸው ወቅታዊ (Immediate) ውጤቶች ባሻገር አገራችን አሁን የምትመራበት ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ነጥሮ የወጣበት፣ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምርጫ ላይ ግልጽነት የተፈጠረበትና ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የፈለቁበት ነው። በዚህ ተሃድሶ ፍሬዎች በመመራት ላለፉት 15 ዓመታት በርካታ ድሎች ተመዝግበዋል። ኢሕአዴግ አሁን እያደረገ ባለው ጥልቅ ተሃድሶው እየገመገመ ያለውም ይኼንኑ የ15 ዓመታት የተሃድሶ ጉዞ ነው። በተመሳሳይ የአሁኑ ተሃድሶም በተቀመጡለት ግቦችና በጥልቀቱ ካልሆነ በስተቀር በመሠረታዊ እሳቤዎቹና አካሄዶቹ ከቀደመው የተለየ አይደለምና አሁን እየታዩ ያሉ ችግሮችን መፍታት ብቻ ሳይሆን ላልተወሰኑ ዓመታት አገሪቱን ወደሌላ የድል ምዕራፎች የማሸጋገር ዘለቄታዊ ፋይዳ እንዲኖረው ይጠበቃል።

ጥልቅ ተሃድሶው እስካሁን ያሉትን ተቋማት መልሶ ማደራጀትና ማጠናከርን ያካትታል፡፡ በተለይ የሕዝብ ምክር ቤቶችና ሌሎቹ የዴሞክራሲ ተቋማትም ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲወጡ ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈጻሚውን አካል የመቆጣጠር ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ማብቃት ይጠበቅበታል፡፡ ተሃድሶው አገራችንን በጥቂት ዓመታት ውስጥ መካከለኛ ገቢ (lower middle income) ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍና በረጂም ጊዜ ደግሞ የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ የሚያስችል ሩቅ አዳሪ ግብ የሰነቀ ነው። የድርጅቱን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ ማጎልበትና የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲን ማስፋትም ከዚህ ተሃድሶ የሚጠበቁ ዘለቄታዊ ውጤቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም ዳግም በጥልቀት የመታደስ ሒደቱ የስኬት ደረጃ መለካት ያለበት እነዚህን ዘላቂ ፋይዳዎቹን ጭምር ታሳቢ በማድረግ እንጂ፣ እግረ መንገዱን እየፈታቸው በሄዱ የቁጥቁጥ ውጤቶቹ ብቻ አይደለም።

የመስመርለውጥመጠበቅ

ሌላው የተሳሳተ የተሃድሶው መመዘኛ ሆኖ እየተወሰደ ያለው ጉዳይ ከዚህ ተሃድሶ የመስመር ወይም የፖለቲካዊ አስተሳሰብ ለውጥ ወይም የመስመር ማጥራትን መጠበቅ ነው። ኢሕአዴግ መልኩን ብቻ ሳይሆን ስሙንና ቅርፁንም ቀይሮ እንዲወጣ የሚጠብቁ ሰዎች አሉ። ልማታዊና ዴሞክራሲያዊው መስመር በኒዮ ሊበራሊዝም ወይም በሌላ ፍልስፍና፣ የአራት ብሔራዊ ድርጅቶች ግንባርነቱ ወደ ጥምረት ወይም ውህደት፣ ኢሕአዴግ ‹‹በመቃብሬ ላይ…›› የሚልላቸው አጀንዳዎች በሰጥቶ መቀበል ድርድር፣ በሕዝብ ነፃ ምርጫ የተገኘ ሥልጣን ወደ ሥልጣን ማጋራት፣ ወዘተ… እንዲቀየር የሚፈልጉ አሉ። በአጠቃላይ ከሁለተኛው ተሃድሶ የቀድሞውን ተሃድሶ ዓይነት ፍሬዎች የመጠበቅና ከዚህም በመነሳት የተሃድሶውን ስኬት የመለካት አዝማሚያዎች በስፋት ይታያሉ።

በመሠረቱ እነዚህ የለውጥ አጀንዳዎች ቀድሞውንም ለዳግም ተሃድሶው ግብ ወይም ዓላማ ተደርገው አልተያዙም። ይህ የሆነው ግን መስመሩና ከእሱ የተቀዱት ፖሊሲና ስትራቴጂዎቹ ዘለዓለማዊ ስለሆኑ አይደሉም። አገራዊና ዓለማዊ ሁኔታዎች መለወጣቸውን ግድ ሲሉ ይለወጣሉ። የልማታዊ መንግሥት ፍልስፍናን ለመከተል ግድ ያሉን እንደ ገበያ ጉድለት (market failure) እና የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ሲቀየሩ የምንከተለው ፍልስፍናም ይቀየራል። ኢሕአዴግ ወደ ውህደት የሚሸጋገርበት ወይም የማኅበራዊ መሠረቱን የለውጥ ሁኔታ ተከትሎ አብዮታዊነቱ ሳይቀር ሊከስም የሚችልበት ዕድልም ዝግ አይደለም። ይህ የለውጥ አጀንዳ ከዚህኛው ተሃድሶ የማይጠበቀው ወደ ዳግም ተሃድሶው የተገባበት ምክንያት ይህ ስላልሆነ ነው።

የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ የሆነው በሥልጣን መባለግ ከመስመሩ የጥራት ችግር የመነጨ ሳይሆን፣ ኢሕአዴግና በእሱ የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ራሳቸውን ከኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያዎች የመጠበቅና ነፃ የማድረግ ግዴታቸውን መወጣት ላይ ባሳዩት ቸልተኝነት የተነሳ፣ ኪራይ ሰብሳቢነት ከልክ በላይ እንዲገዝፍና ሥርዓቱን የሚፈታተን አደጋ እንዲሆን በር በመክፈታቸው ነው፡፡ ስለሆነም መፍትሔው ይኼንኑ በአፈጻጸም ሒደት ያጋጠመ ጉድለት ማረም ይሆናል እንጂ፣ በተግባር ተፈትሸው ውጤታማነታቸው የተረጋገጡትን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፕሮግራሞች መቀየር አይደለም።

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ባደረገው ግምገማ እንደገና በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ መድረኮቹ በተቀመጠላቸው አቅጣጫ መሠረት እየቀጠሉ መሆናቸውንና በአጀንዳዎቹ ላይም የጋራ መግባባት እንደተደረሰባቸው አረጋግጧል፡፡ በዚህ ሒደት አመራሩና አባላት የሕዝብን ምሬት ያስከተሉ ችግሮችን በዝርዝር በመገምገም መንስዔያቸውና መፍትሔያቸው ላይ የተሟላ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡ ግምገማውን መሠረት በማድረግ የሰው ኃይል ምደባ ማስተካከያዎች እንዲደረጉና በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የመንግሥት የአመራር ምደባ በውጤታማነት ላይ ተመሥርቶ እንዲፈጸም ተደርጓል። ተሃድሶውን ይበልጥ የማጥለቅ ሥራዎች በተጠናከረ ሁኔታ የሚፈጸሙበትንም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የተሳተፉ አመራሮች ላይ እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ መንግሥት አጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነትን ችግር ለመታገልና በዚህ ተግባር ላይ ተሳትፈው የተገኙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሥር ራሱን የቻለ የምርመራ ቢሮ መቋቋሙን በዚሁ ሳምንት አስታውቀዋል፡፡

እነዚህ ዕርምጃዎችና አቅጣጫዎች እንዳሉ ሆነው በድምሩ ሲታይ አሁን ላይ ሆኖ በእርግጠኝነት መናገር ወይም መከራከር የሚቻለው በዳግም ተሃድሶው የአፈጻጸም ሒደት ላይ እንጂ በውጤቱ ላይ ሊሆን አይችልም። አሁን ላይ ሆኖ ስለተሃድሶው ስኬት ወይም ውድቀት ለመደምደም መሞከር ችኮላ ነው የሚሆነው። ሒደቱ በራሱ እዚህም እዚያም እልባት የሰጣቸው ችግሮች ይኖሩ ይሆናል። ተሃድሶው ግን ከዚህም በላይ የገዘፉ ዘላቂ ግቦች የተቀመጡለት ነውና እስካሁን ባስገኛቸው የቁጥቁጥ ውጤቶቹ የሚያኩራራ አይደለም። ገና የተጀመሩትን ውይይቶች አድማስ ማስፋት፣ ይበልጥ ማጥለቅና በአዲስ አስተሳሰብ መተግበር የሚጠይቅ ነውና ለውጥ አላመጣም ተብሎ የሚኮነንም አይደለም።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው kebedememe@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

Standard (Image)

አንድ ወይስ ከዚያ በላይ ንጉሥ?

$
0
0

- የቅጅ መብትና የጋራ አስተዳደር በኢትዮጵያ

በሰብለ ገብረጊዮርጊስ

ኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጽሑፍና ሳይንሳዊ ሥራዎች የአንድ ማኅበረሰብ የጀርባ አጥንት ናቸው። ስለዚህም ነው በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ ያላቸው ቦታ ከፍተኛ የሚሆነው። በዚህ ረገድ አገራችን የታደለች ናት። ከጥንትም ጀምሮ ብዙ ሥራዎች በተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች የሚወጡባት ከመሆኗም ባሻገር ሕዝቧ በዚህ ሉላዊ ዓለም እንኳን የራሱን ሥራ የሚወድና የሚከታተል ነው። በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ካላቸው ቦታ አንፃር ለእነዚህ ሥራዎች በሁሉም የዓለማችን አገሮች ማለት ይቻላል ጥበቃ ይደረጋል።

በሕግ ጥበቃ የሚደረግላቸው በሁለት ምክንያቶች ነው። የመጀመርያው የሥራ አመንጪው ሥራውን ለማመንጨት ጭንቅላቱን፣ ጊዜውን፣ ጉልበቱም እንዲሁም በብዙ ሁኔታዎች ገንዘቡን ፈጅቶ ለውጤት የሚያደርሰው በመሆኑ ጥበቃ ሊደረግለትና ከሥራዎቹም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊያገኝ ይገባል የሚለው ነው። የሥራ አመንጪው ወይም መብቱ የተላለፈለት ሰው ሥራው በሌላ ሰዎች ጥቅም ላይ ሲውል በፈቃደኝነት ሥራውን በነፃ ካልሰጠ፣ ወይም ሥራው የጥበቃው ጊዜ ካላለፈበት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ በቅድሚያም ፈቃድ መስጠት አለበት።

ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም በዘለለ የሥራ አመንጪው ዕውቅና ሊያገኝ ይገባል። የሥራ አመንጪው የኢኮኖሚያዊ መብቱን አሳልፎ ለሌላ አካል ቢሰጥም ባይሰጥም፣ ከሥራው ጋር ያለው ጥልቅና ግላዊ (Personal) ግንኙነት ከግምት ውስጥ ገብቶ ተጨማሪ የሞራል መብቶች በሕግ ይሰጡታል። ሁለተኛው ምክንያት የሕዝብና የአንድ አገር ሥነ ጽሑፍ፣ ኪነ ጥበብ፣ ትምህርትና ሳይንሳዊ ዕድገቶችን ከማሳለጥና መረጃና ዕውቀትን ከማዳረስ ጋር የተገናኛ ነው። ከዚህ ጋር መረዳት የሚቻለው የቅጂ መብት ሕግ በባህሪው ሁለት ጥቅሞችን ለማጣጣም ታስቦ የሚወጣ የአንድ አገር የውስጥ ሕግ መሆኑን ነው።

በአገራችንም እነዚህ ምክንያቶች ከግምት ውስጥ ገብተው ይመስላል በ1952 ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ ውስጥ በተካተቱት አንቀጾች ጥበቃው ተጀምሯል። ይሁንና ይህ ሕግ በተለያዩ ምክንያቶች ጠንካራ ጥበቃ ለማድረግ ባለመቻሉ በ1996 ዓ.ም. የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410 እንዲሻሻል ተደርጓል። የ1996 ዓ.ም. አዋጅ ጥበቃ የሚደረግላቸውን ሥራዎች ዝርዝር፣ የመብት ዓይነቶችን፣ የጥበቃ ዘመንና ወሰን፣ ገደቦችን፣ መብት የሚተላለፍባቸው መንገዶች በማስፈር እንዲሁም ስለመብት ተፈጻሚነት በመደንገግ በሥነ ጥበብ፣ በኪነ ጥበብና በሳይንሳዊ መስኮች ለሚወጡ ሥራዎች ጥበቃ እያደረገ ቆይቷል። ይሁና የሥራ አመንጪዎችና ተያያዥ ሰዎች ጥረቶችና ጥቅሞች በበቂ ሁኔታ ከማስጠበቅ አንፃር በተጨባጭ የሚታዩ ችግሮች አሉ።

ሁላችንም እንደምናውቀው በጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ አብዛኞቹ ሙያተኞች ጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ ናቸው ለማለት አይቻልም። ተገቢ ሕክምና ማግኘት አቅቷቸው ዕርዳታ የሚጠይቁ፣ እንዲሁም ሕክምናውን ሳያገኙ የሚሰቃዩና ሕይወታቸው ያለፈ መኖራቸውን እናስታውሳለን። መሰል ሁኔታ እንዲፈጠር የሚያደርገው ዝቅተኛ የኢኮኖሚያዊ አቅም ነው። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ሊነሱ ይችላሉ። በዋናነት ባለመብቶች ወይም የሥራ አመንጪዎች መብቶቻቸውን ለማስከበር በሚወስዷቸው ዕርምጃዎች ላይ የሚታዩ ክፍተቶች፣ የሥራ አመንጪው የመደራደር አቅም ዝቅተኛነት፣ ለረጅም ዓመታት ሲሠራባቸው የነበሩ ሕገወጥ ሊባሉ የሚችሉ አሠራሮች፣ እንዲሁም የሕዝቡ የአዕምሯዊ ንብረት አጠቃቀም ግንዛቤ የሚጠቀሱ ናቸው።

የአዋጅ ቁጥር 410/1996 ይዘት ሲገመገም አጠቃላይ ድንጋጌዎችን የያዘና እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች በቂ ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው። ይሁንና ይህ አዋጅ ከመብቶች አስተዳደር አንፃር የሚታዩበት ክፍተቶች አሉ። ከዚህ ውስጥ የጋራ አስተዳደር ማኅበራት አመሠራረትና አሠራርን አለመደንገጉ ይገኝበታል። ከ12 ዓመታት በኋላ ቢሆንም ሕጉ ይህን አካቶ በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 872/2007 እንዲወጣ ሆኗል። ይህ የሚመሰገን እንቅስቃሴ ሲሆን በኪነ ጥበብና በተያያዥ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ለሚሳተፉ ግለሰቦችና ድርጅቶች እጅግ ጠቃሚ ነው። ለመንግሥትም ጠቀሜታው የጎላ ነው። ከዚህ ባልተናነሰ በተለያዩ ዘርፎች የሚወጡ ሥራዎች ለሕዝብ በቀላሉ፣ በተመጣጣኝ ዋጋና ሕጋዊ በሆኑ መንገዶች የሚቀርቡበትን ሁኔታ ስለሚያመቻች ተደራሽነትን ያሰፋል። ይኼም የአንድ አገር የፈጠራና የጥበብ መስክ እንዲዳብር፣ እንዲያድግ፣ ሕዝቦችም ምኅዳራቸው እንዲሰፋ እንዲሁም የአገር ባህልና ቅርስ ተጠብቆ እንዲቀጥል ይረዳል።

የጋራ አስተዳደር ማኅበራት በተለያዩ ምክንያቶች አስፈላጊ ናቸው። ይህንንም ከሁለት አቅጣጫ ማየት እንችላለን። በመጀመርያ የመብት ባለቤቶች ሥራዎቻቸው በተለያዩ ቦታዎች ጥቅም ላይ እንዴት ዋሉ የሚለውን በመለየት፣ ተጠቃሚዎቹን በማሳደድና ከሁሉም ተጠቃሚዎች ጋር በመደራደር ፈቃድ ለመስጠት የማይችሉና እናድርግ ቢሉ እንኳን ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣቸው በመሆኑ በጋራ ማስተዳደሩ አስፈላጊ ነው። በሁለተኛ ደረጃ እነዚህ ማኅበራት ተጠቃሚዎች ሥራዎችን በአንድ ቦታና በግልጽ በተቀመጡ ዝርዝር ሁኔታዎች የክፍያ መጠን እንዲያገኙ ያደርጋሉ። በመሆኑም የጋራ አስተዳደር ማኅበራት አመሠራረትና አሠራር በአገራችን በሕግ መደንገጉ በጀ የሚባልና ሊበረታታ የሚገባው ነው።

በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ይህ ሥርዓት ከሦስት ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜን አስቆጥሯል። ተግባራቱን ለማከናውንም የተለያዩ አደረጃጀቶች ተፈጻሚ ይሆናሉ። የቅጂ መብት የጋራ አስተዳደር ማኅበራት አደረጃጀቶች የሚያስተዳድሯቸው መብቶችና የባለመብቶቹ ዓይነቶች፣ የሕግ ማዕቀፍ (ከሚመለከተው የመንግሥታዊ አካል ፈቃድ ማስፈለግ አለማስፈለጉ፣ ከአንድ በላይ ማኅበር መፈቀድ አለመፈቀድ (በዘርፉ ወይም በአጠቃላይ በአገሪቱ)፣ የግዴታ ማኅበርና በባለመብቶች ፍላጎት የሚቋቋም ማኅበር መሆን አለመሆኑ፣ መንግሥታዊ የሆኑና የግል ማኅበራት፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚወጡ ሥራዎች ብዛት፣ እንዲሁም በሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎች ሊለያዩ ይችላሉ። አደረጃጀታቸው ላይ ልዩነት ቢኖርም ዋና ሥራቸው ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት ለባለመብቶች ጥቅም ማከናወን ነው።

በኢትዮጵያ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ የጋራ አስተዳደር ማኅበራት ማቋቋም በሕግ ተፈቅዷል። የሕጉን ይዘት ስንመረምር በአመሠራረታቸውና በአሠራራቸው ላይ አንዳንድ ነጥቦችን ልናነሳ እንችላለን። በመጀመርያ የቅጂና ተዛማጅ መብቶችን በባለመብቶቹ ስም ሊያስተዳድር የሚፈልግ አካል በኢትዮጵያ ውስጥ ሊቋቋም የሚችለው ከአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ፈቃድ ሲያገኝ ብቻ ነው። ያለቅድሚያ ፈቃድ ይህን ሥራ መሥራት አይቻልም። ይህን ማድረግ ሕገወጥ ተግባር ነው።

በሁለተኛ ደረጃ እነዚህ ማኅበራት የሚቋቋሙት በባለመብቶቹ ይሁንታ ብቻ መሆኑ ነው። ሦስተኛው አንድ ማኅበር ከጽሕፈት ቤቱ ፈቃድ ለማግኘት ማሟላት የሚገባው የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ ዋናው ማኅበሩን ለመመሥረት በሥራቸው አባላትን የያዙና የተመዘገቡ ሦስትና ከዚያ በላይ የሆኑ የዘርፍ ማኅበራት ስብስብ መሆን ነው። ይህ በብዙ የዓለማችን አገሮች የተለመደ አይደለም። ለምሳሌ በህንድ ሰባትና ከዚያ በላይ እንዲሁም በናይጄሪያ 100 እና ከዚያ በላይ ባለመብቶች አቅፎ የያዘ አካል የጋራ አስተዳደር ማኅበርን ሊያቋቁም ይችላል።

ይሁንና በአብዛኛው በአንድ የመብት ባለቤቶች ወይም የመብት ዓይነቶች ላይ ፈቃድ ያገኘ ማኅበር ካለ ለሌላ ማኅበር ፍቃድ አይሰጠውም። በሌሎች የመብት ወይም የባለመብቶች ዓይነቶች ላይ ማኅበራትን ለማቋቋም የሚፈልጉ ካሉ ግን ይህን ከማድረግ አይከለከሉም። ሌሎች በአዋጁ መሠረት ፈቃድ ለማግኘት ማሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች የመመሥረቻ ጽሑፍና የውስጥ ደንቦችን ማዘጋጀት፣ የአባላትን ዝርዝር፣ እንዲሁም የአባላት የሥራ ዓይነት መግለጫን ለጽሕፈት ቤቱ ማቅረብ ናቸው።

ይህንን ያሟላ ማኅበር ፈቃድ ሊያገኝ ይችላል። ከምዝገባ በኃላ የጋራ አስተዳደር ማኅበሩ ሥራዎችንና እንቅስቃሴውን በውስጥ ደንቦቹ፣ በመመሥረቻ ጽሑፉ፣ እንዲሁም በአዋጁ ድንጋጌዎች መሠረት ማከናወን ይጠበቅበታል። ፈቃድ ከመስጠት ውጪ ጽሕፈት ቤቱ አሠራራቸውን የሚቆጣጠርበት መንገዶች በአዋጁ ተቀምጠዋል። ተግባራቱን ለማከናወን አንድ ማኅበር የሮያሊቲ መጠንና የሮያሊቲ ቀመር አዘጋጅቶ ለጽሕፈት ቤቱ ማቅረብና ማፀደቅ አለበት። ይህ ሮያሊቲን ከመሰብሰቡ በፊት መደረግ የሚገባው ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ማኅበር በላይ ያስፈልጋል? አያስፈልግም? የሚለው ጥያቄ የተለያዩ ወገኖችን የሚያከራክር ጉዳይ ሆኗል። ሕጉን ስናይ የተሻሻለው አዋጅ ከአንድ በላይ ማኅበራት እንዲቋቋሙ ይፈቅዳል። የተለመደው አሠራር ከአንድ በላይ የጋራ አስተዳደር ማኅበራት በአንድ ግዛት ውስጥ የሚሠሩ ሲሆን፣ ለዚህም በርካታ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል። የሙዚቃ ሥራን ብንወስድ አቀናባሪዎች፣ የዜማ ደራሲዎች፣ የግጥም ደራሲዎች፣ ድምፃዊያንን እንዲሁም የሙዚቃ ፕሮዲዩሰሮችን በጋራ ያቀፈ የሙዚቃ ሥራ የጋራ አስተዳደር ማኅበር ይቋቋማሉ። ይህ አሠራር በእንግሊዝ፣ ቻይና፣ ኔፓል፣ ኔዘርላንድስ፣ ስዊድን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ህንድ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያና ሌሎች በርካታ አገሮች ተግባራዊ ተደርጓል።

በሌላ በኩል የሥነ ጽሑፍ ነክ ሥራዎችን የሚመለከቱ የሪፕሮግራፊክ (የማባዛት) ማኅበራት እንዲሁም የኦዲዮቪዥዋል ማኅበራት፣ ለየብቻቸው ተቋቁመው ይሠራሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃም በዚህ ሁኔታ የተዋቀሩ ድርጅቶች በሉዓላዊ አገሮች ውስጥ ለሚሠሩ አባል ማኅበራት ድጋፍ ያደርጋሉ።

ለአገራችን የትኛውን መንገድ ብንከተል ይበጃል? ብለን ስንገመግም የሕዝብ ብዛት፣ የሥራ መጠን፣ እያደገ ያለ ኢኮኖሚ፣ ሊፈጠር የታሰበው ጥቅም፣ እንዲሁም የሕዝቡ አጠቃቀም ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገብተን መሆን አለበት። አገራችን እስካሁን የጥበብ ችግር ወይም እጥረት የለባትም። አብዛኛዎቹን ሥራዎች ወደ አገር ውስጥ የምታስገባና በዚያ ላይ ብቻ ጥገኛ የሆነች አገርም አይደለችም። ሰፊና እያደገ የሚሄድ የሕዝብ ብዛት ያላትና ሕዝቡ የአገር ውስጥ ሥራዎችን በሰፊው የሚጠቀም ነው። በመሆኑም አንድ ዓይነት መብቶች፣ የመብት ባለቤቶች ወይም ተመሳሳይ ዘርፎች በጋራ የራሳቸውን ማኅበር እንዲያቋቁሙ ቢፈቀድ ቀልጣፋ ሥርዓት ለመዘርጋት ያስችላል።

ከዚህ በተጨማሪ አንድ ማኅበር ብቻ ይኑር ቢባል በተለያዩ የመብት ባለቤቶች መካከል ሊኖር የሚችለውን የጥቅም ግጭት በከፍተኛ ደረጃ ያባብሳል። እንዳንድ የሥራ አመንጪዎች ችላ የተባሉ ወይም ጥቅም የማያገኙ እንዲመስላቸውም ያደርጋል። አንድ ማኅበር የሁሉንም የሥራ አመንጪዎችና ባለመብቶች ጥቅም እኩል ሊያስተዳድር ይችላል ተብሎ ሊገመት አይችልም። ለዚህም በምክንያትነት ሊወሰድ የሚገባው የዘርፎቹ የዕድገት ደረጃ ነው።

ለምሳሌ የሙዚቃው ኢንዱስትሪ ሰፊ ተጠቃሚ ያለውና በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች የሚተላለፍ በመሆኑ፣ ባለመብቶች የራሳቸውን የጋራ አስተዳደር ማኅበር ቢያቋቁምና በዘርፉ ውስጥ በተለያየ ደረጃ የሚሳተፉትን ባለሙያዎች እንዲጠቀሙ ቢደረግ ለሙዚቃው ኢንደስትሪ ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል። በተመሳሳይ በኦዲዮቪዥዋል ዘርፍ የተሰማሩ ሙያተኞች በአንድ ላይ ተሰባስበው የራሳቸውን ጥቅም የሥራው ዓይነትና ፀባይ በሚጠይቀው መንገድ ቢያስተዳድሩ፣ አሁንም ለዚህ ዘርፍ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ይሆናል። አንድ ማኅበር ብቻ ይኑር ቢባል ከሞኖፖሊ ጋር በተያያዘ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ተያያዥ ችግሮችን ልብ ይሏል።

ከሁሉም በላይ ከአንድ በላይ ማኅበር ይኑር የሚለውን ሐሳብ አንድነትን እንደሚያፈርስና ከፋፋይ ሐሳብ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ከነባራዊ ሁኔታችን እንዲሁም ይህን መሰል ማኅበራት የማስተዳደር ካለን አቅምና ልምድ አንፃር ተያይዞ ችግሮች እንዳይባባሱ፣ በባለመብቶች ይሁንታ መሠረት የተለያዩ ማኅበራት ቢቋቋሙ የበለጠ ይጠቅማል። በጉዳዩ ላይ የበለጠ ውይይት ማድረግና የተለያዩ ሐሳቦችን ማስተናገድ ሁሉም ለቆመለት ዓላማ መሳካት ጠቀሜታው የጎላ ነው። አዋጪ የሚሆነው በመካከላቸው ጥሩ ግንኝነት ያላቸው ማኅበራት በተለያየ ዘርፎች ስም ማቋቋም ነው።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊዋን በኢሜይል አድራሻቸውseblebaraki1@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

ከጥገኝነት ወደ ኃላፊነት

$
0
0

 በዳዊት ወንድማገኝ (ዶ/ር)

አስከ መቼ በጥገኝነት እንተክዝ? የሰው ልጆች ለመኖር ሌላውን መጠጋት ግዴታቸው ቢሆንም፣ ጥገኝነት የመኖራችን መሠረት መሆኑ የማይቆረቁረን ለምንድን ነው? አሁን አሁን ሳስበው እንደ ብዙ ነገሮች ለምዶብን ይሆን እላለሁ፡፡ ይህን ጽሑፍ የጻፍኩት በሐዘንም በንዴትም አይደለም፡፡ በትካዜ ነው፡፡ ለምን?

የጽሑፉ መነሻ “የኛ” የሚለው የታወቀ የሬዲዮ ፕሮግራም እንግሊዞች ዕርዳታ ሰጪዎች ሐሳባቸውን በመቀየራቸው ምክንያት ዘላቂነቱ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን በዜና መስማቴ ነው፡፡ ስንት ጥሩ ነገር ነው በጥገኝነት ምክንያት የሚቋረጠው ብዬ መተከዝ ጀመርኩ፡፡

ለምን ጥገኝነት ነውራችን ሳይሆን ቀረ? ለምን ጥገኝነት ተመቸን? የሚሉትን ጥያቄዎች ብመረምር ምንኛ እወድ ነበር፡፡ ነገር ግን እሱን መመርመር ጥቅም የለውም፡፡ በዚያ ላይ ይህን እንኳን ልመርምር ብል የዚህን ምርምር ወጪ ለመሸፈን ፈረንጅ ፍለጋ መንከራተት ብቻ ሳይሆን፣ ምርምሩንና ሐሳቡን ከዚያም ባለቤትነቱን ፈረንጆች በፈለጉት መንገድ ማስተካከሉን፣ በዩኒቨርሲቲ የምርምር ሥራዎች አካሄድ እስኪሰለቸን ድረስ የማውቀው ስለሆነ ደክሞኛል፡፡ እውነቱን ለመናገር ጉዳዩ የጠለቀ ምርምር የሚፈልግ ዓይነት አይመስለኝም፡፡

በ“የኛ”  ፕሮግራም ችግር የምተክዘው በመናደድ ያልሆነውም ለዚሁ ነው፡፡ ለኛ ማኅበረሰብ የሚጠቅም ሥራን ማገዝ ሲጀመር የፈረንጅ ግዴታ መሆን የለበትም፡፡ ሲቀጥል ደግሞ የሴት ልጆቻችንን ሕይወት በእርጥባን ላይ ልንመሠርተው አይገባም፡፡ ጥያቄው ፈረንጆች ይህን ለምን አደረጉ ሳይሆን እኛ ለ“እኛ” ምን አደረግን? የሚለው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ መፈተሸ የምፈልገው ሐሳብም ይኸው ነው፡፡ ግን ቢሆንም ስለፈረንጆች አንድ ልጨምር የሆነው የተደገመ የተደጋገመ እንጂ አዲስ አለመሆኑን ለማሳየት፡፡

እኔ በምመራው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ሕክምና ትምህርት ክፍል ውስጥ በርካታ በውጭ ገንዘብ የሚረዱ የምርምር ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ “ኤመራልድ” የተባለ በአውሮፓ ኮሚሽን የሚደገፍ ወይም ለኮሚሽኑ ጥገኛ የሆነ የጥናት ፕሮጀክት ነበረን፡፡ ይህን ፕሮጀክት በኮሚሽኑ አሳሳቢነት በመጀመሪያ ሥራውን ሠርተን ከዚያ በኋላ ገንዘቡን እንደሚከፍሉ ተስማማን፡፡ ፕሮጀክቱ አንድ መቶ ስልሳ አምስት ሺሕ ዩሮ ያህል ከሌላ ተበድረን ከተሠራ በኋላ፣ የአውሮፓ ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ከዓመታት በፊት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኃላፊነት ወስዶ ወደ ካርቱምና ማካራሬ ዩኒቨርሲቲ ለምርምር የላከው ገንዘብ እነዚያ ዩኒቨርሲቲዎች በአግባቡ ስላላወራረዱ በማለት፣ ትልቁ የአውሮፓ ኮሚሽን ትንሹን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲንና ትንንሾቹን የምርምር ኃላፊዎች በማጭበርበር ዕዳ ውስጥ ከተተ፡፡ ይህን ለማንም አቤት ማለት አልተቻለም፡፡ ይህን ዓይነት ብዙ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ይህን መጠየቅ ለምን አታስጠጉኝም ብሎ ከመበሳጨት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ እንዳውም ፈረንጆቹ የኛኑ ተረት ገልብጠው ‹‹እጸድቅ ብዬ ባዝላት ተንጠልጥላ ቀረች›› የሚሉን ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ወደ ራሳችን ልመለስ እኛ ለ ‘’እኛ’’ ምን አደረግን?

እኔ ‘’የኛ’’ን የምወድበትን ምክንያት ባስረዳ ስለአቀራረቡ ይዘት ብዙ አልልም፡፡ የየኛ ጉልበት ያለው ጭብጡ ላይ ነው፡፡ የሚያነሳው ጭብጥ ሊሰማንና ሊያንገበግበን የሚገባ ማኅበራዊ ቀውስን ስለሆነ ስለሴቶች መገፋት፣ መጎሳቆል፣ መበደል፣ መደብደብ፣ መሞት እንዲሁም የመከራ ሕይወትን እንደዋዛ መግፋት ወንዶችም ሴቶችም ብዙ ብለዋል፡፡ ከማለት የዘለለ ግን ምን ተሠራ? በጣም አጠያያቂ ጥያቄ ነው፡፡

የ‘’የኛ’’ ፕሮግራም የሴቶች ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የሚያነሳው ግን የሴቶችን ጉዳይ ነው፡፡ ፕሮግራሙ የሴት ልጆች ጉዳይ አይደለም ያልኩት የሴት ልጆች ጉዳይ አንኳር የማኅበረሰብ ጉዳይ ነው፡፡ የሴቶችን ጉዳይ ችላ የሚል ማኅበረሰብ ራሱን ችላ የሚል ነው፡፡ ሁሉም የሠለጠኑና ከችግር ያመለጡ ማኅበረሰቦች የሚመሳሰሉበት አንድ ቁም ነገር የሴቶችን ጉዳይ አጥብቀው መያዛቸው ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ የተባለና የሚባል ሆኖ፣ በእኛ አገርና ማኅበረሰብ ውስጥ እስካሁን ትርጉም ባለው መንገድ ሊሆን ያልቻለ ነው፡፡ ለምን?

ይህ ያልሆነበት ምክንያት የሴቶችን ጉዳይ አጥብቆ የያዘ እንደ የ‘’የኛ’’ ዓይነት ፕሮግራም በዘላቂነት ማከናወን ስላልተቻለ ነው፡፡ የሚያስፈልገው በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ “የኛ” ፕሮግራሞች ሆነው፣ አንዱ እንኳን ችግር ውስጥ መግባቱ ያስተክዘኛል፡፡ እኛ ለ”የኛ” ምን እናድርግ?

የ‘’የኛን’’ ፕሮግራም ስሰማ ብዙ አስባለሁ፡፡ እናቴን አስባለሁ፡፡ እስኪ እናቶቻችንን ለአፍታ እናስብ፡፡ ለዘመናት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እናቶች ያፉበትን ሕይወት እንገምት፡፡ ፊታቸው ላይ የተሰመረው የመከራ መስመር ብዛት ይታየን ይሰማን እስኪ፡፡ እህቶቻችንንና ሚስቶቻችንንም እናስብ፡፡ የእነሱስ መከራ ችላ ሊባል የሚገባው ነው ወይ? ወይስ በደልን እንደ ጥገኝነት ለምደነው ይሆን?

ከሁሉም በላይ ግን ሴት ልጆቻችንን እናስብ፡፡ ሴቶች ልጆቻችን አድገው በእናቶቻችን ቦታ ላይ የተሰመረው የመከራና ሐዘን መስመር በእነርሱ ላይ ሲደገም ዝም ብለን እናያለን ማለት ነው?

  የኛ ፕሮግራም ይህን ለመቅረፍ ከሚያስፈልጉት ድርጊቶች አንዱን ለመፈጸም የሚጥር ስለሆነ፣ ከመውደድ በላይ የማከብረው ፕሮግራም ነው፡፡ አዘጋጆችንም ከማናቸውም በላይ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ስለተወጡ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡

አሁን ወደተነሳሁበት የትካዜ ሐሳብ ልመለስ፡፡ ወደ ትካዜ የመራኝ ይህ የተጠናወተን የጥገኝነት አባዜ ነው፡፡ ከጥገኝነት የምንወጣው እንዴት ነው? ሌሎች እንዴት ነው ከጥገኝነት የወጡት? ወይስ እንዴት ነው ለመውጣት እየጣሩ ያሉት?

መቼም የተጠናወተን የቁስ ብቻ ሳይሆን የሐሳብም ጥገኝነት ስለሆነ፣ መፍትሔውንም እንኳን በግድ ከፈረንጆቹ ሠፈር ከተገኙ ሐሳቦች መቃረም ያስፈልጋል፡፡ መሆን የለበትም ይህ ይመስለኛል፡፡ ለዘላቂ የሚጠቅመው ሐሳብ ከየትም ከማንም መውሰድና መተርጎም፡፡ ላነሳ የፈለግኩት ሐሳብ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነት (Corporate Social Responsibility) የሚለውን ነው፡፡ ይህ እሳቤ በግርድፉ ሲተረጎም የትኞቹም ማኅበራዊ ተቋማት ማለትም የንግድ፣ የትምህርት፣ የሃይማኖት ወዘተ ከተቋቋሙበት ዓላማ በተጨማሪ፣ ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ የሆነን ሌላ ማኅበራዊ ጉዳይን የመደገፍ ግዴታ አለባቸው ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት አንድ የትምህርት ተቋም ከማስተማር ጋር ያልተያያዘ ሌላ ማኅበራዊ ጉዳይን መደገፍ አለበት፡፡ አንድ የንግድ ተቋም ከትርፍ ጋር ያልተያያዘ ሌላ ማኅበራዊ ጉዳይን መደገፍ አለበት፡፡

እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ አንጋፋ ተቋማት አንድን ማኅበራዊ ጉዳይ ለምሳሌም የሴቶችን ጉዳይ የመደገፍ ኃላፊነት አለበት፡፡ ባንኮችና የኢንሹራንስ መሥሪያ ቤቶች፣ ፋብሪካዎች ሳይቀሩ ይህን መደገፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የመጀመሪያው ጥያቄ ለምን? የሚለው ነው፡፡ ተቋማት የማያገባቸውን ማኅበራዊ ጉዳይ ለምን ይደግፋሉ? ምን ያገኙበታል? የሚለው መመለስ አለበት፡፡ መልሱም ቀላል ነው፡፡ ተቋማት ልክ እንደ ግለሰብ ዜግነት አላቸው፡፡ ይህም የኮርፖሬት ዜግነት (Corporate Citizenship) የሚባለው ነው፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ የዜግነት መብትና ግዴታ አለባቸው፣ ሊኖርባቸውም ይገባል፡፡ ተቋማት የሚገኙበትን ማኅበረሰብ ሀብት፣ ንብረት፣ ቦታ፣ ጊዜና አካባቢ ይጠቁማሉ፡፡ እያንዳንዱ ተቋም አንድ ግለሰብ ከሚጠቀመው በላይ ማኅበራዊ ሀብትን ይጠቀማል፡፡ ይህ ደግሞ ያለ አንፃራዊ ሁኔታ ሊሆን አይገባም፡፡ ለምሳሌ አንድ ፋብሪካ በምርታማነቱ ለተጠቃሚው ምርትንና ለተቋሙ ጥቅምና ትርፍ የሚያመጣውን ያህል፣ በፋብሪካው ምርት ምክንያት ለሚከተለው የአካባቢ ብክለት ምን አስተዋጽኦ ያደርጋል?

ከማኅበራዊ ግዴታዎች በተጨማሪም ተቋማት የማይመለከታቸውን ማኅበራዊ ጉዳይ የመደገፍ የሞራል ወይም የሥነ ምግባር ግዴታም አለባቸው፡፡ ይህ የሞራል ግዴታ የሚመነጨው ደግሞ የትኛውም ማኅበራዊ ተቋም ጊዜያዊ እንደ መሆኑ ሁሉ፣ ከመጭው ዘመንና ትውልድ የተበደረውን አገርና ሀብት ሲሆን አሻሽሎ አሊያም ባለበት ጠብቆ በማቆየት ነው፡፡

ሦስተኛው የተቋማት ማኅበራዊ ኃላፊነት መመንጨት ያለበት ግን ከራሳቸው ከተቋማት ፍላጎትና ድርጊት ነው፡፡ ይህ ከኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነት መሠረታዊ እሳቤ ጋር ቢጋጭም፣ እውነቱ ተቋማትም እንደ ግለሰቦች ራስ ወዳድነት ስላለባቸው ለራሳቸው በቀጥታ የማይጠቅምን ጉዳይ መደገፍ ሊተናነቃቸው ይችላል፡፡ ሆኖም ተቋማት የራሳቸውን ዘላቂ ስኬት በባዶ ማኅበረሰብ ውስጥ ማሳካት ስለማይችሉ ለሚኖሩበት ማኅበረሰብ ተገቢውን ድጋፍ ካልሰጡ፣ በማኅበረሰብ ዘንድ ያላቸው ተፈላጊነትም በአንፃሩ እየጠፋ ስለሚሄድ በማይፈለጉበት ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር እያዳገታቸው ይመጣል፡፡

በአገራችን የተለያዩ የአገልግሎትና የኢንዱስትሪ ንግድ ተቋማት እየተስፋፉ መሄዳቸው የሚደገፍ ሲሆን፣ በአንፃሩ ግን ማኅበራዊ ዕድገታቸው እየቀጨጨና እየሳሳ ወደኋላ ማሽቆልቆሉን ልናስተውለው ይገባል፡፡ በዚህ መነጽር ነው እንግዲህ የእኛን ፕሮግራም ሁኔታ ልንመረምረው የሚገባን፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በአንዲት ሴት ላይ ሁላችንም የማንፈቅደው ጉዳትና መገፋት ሲደርስ፣ ሁላችንም ትንሽ ጊዜያዊ ጩኸት አሰምተን አልፈናል፡፡ እንደ የኛ ዓይነት ፕሮግራም ግን የሴቶችን ጉዳይ ከሥር መሠረቱ ለማጥራት በተከታታይ ሲታትር የሰነበተ ነው፡፡ የእኛ ፕሮግራም የሴት ልጆቻችንን ጉዳይ እንዳይረሳ ቢያንስ በሳምንት ጥቂት ቀናት ከተኛንበት የቸልታ እንቅልፍ ሲቀሰቅስ ቆይቷል፡፡

ሁላችንም ከሴት ተወልደን እየኖርን እንዲህ ዓይነት የሴት ልጆቻችንን የወደፊት ሕይወት ዕጣ ፋንታ ሊቀይር የሚችል ፕሮግራም ስናገኝ ልንደግፈው ይገባል፡፡ ከዚህ የበለጠም ልናደርግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ሴቶች የሚያድጉበት ማኅበረሰብ ለእነዚህ ሕፃናት የሚገባቸውን እንክብካቤ ለመስጠት ካልጣረ፣ እንደ ማኅበረሰብ መሰንበቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ይህን ማኅበራዊ ቀውስ ለመወጣት ደግሞ ከጥገኝነት ስሜት ወጥተን ወደ ኃላፊነት ስሜት መግባት ግድ ይለናል፡፡ ከዓለማችን ታሪክ የተማርነው አንድ ቁም ነገርም ይኼው ነው፡፡ ለዕድገታችን ኃላፊነትን ካልወሰድን ማደግ አይቻልም፡፡ ይህ መቼም ግልጽ ሐሳብ ይመስለኛል፡፡ ለመረዳት የሚቸግረን ምናልባትም ብዙውን ማኅበራዊ ተቋማት የምንመረምረው ወንዶች ስለሆንን ሊሆን ይችላል፡፡ የ“የኛ’’ ጉዳይ ግን የወንዶችም ጉዳይ ነው፡፡ “ወንዶች” ስል ግን ወንዶች ሰዎችን ብቻ ሳይሆን በወንድ ስም የሚጠሩ ተቋማትንም በሙሉ ነው፡፡

ሁሉም ማኅበራዊ ተቋማት በወንድ ስም መጠራቱ በራሱ የሚያሳየን ይህንኑ ነው፡፡ እኒሁ ተቋማትን ማስታወስ የሚሻው ግን ሁሉም ማኅበራዊ ተቋማት የሚኖሩት በሴት የምትጠራ አገር መሆኑንና የሴት ልጆች መሆናቸውን ነው፡፡ በመሆኑም ማኅበራዊ ኃላፊነትን መውሰድ ብቻ ሳይሆን መወጣትም ግዴታቸው ሊሆን ይገባል፡፡

ይህ የጥገኝነት ስሜት ከመንግሥት ላይም ቢወርድ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ያለ አንገብጋቢ ማኅበራዊ ጉዳይን ለሌሎች እርዳታ አሳልፎ መተው ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ስለሆነ፣ ሌሎች መንግሥታት የተቋማት ማኅበራዊ ኃላፊነትን በሕግ ደንግገው ይተገብራሉ፡፡ በእኛ አገር ይህንን የሕግ ተጠያቂነት ማምጣት ለምን አይቻልም? በጥያቄው ውስጥ መልሱ አለ፡፡

በመጨረሻ ግን ወደ ራሴ ልመለስ፡፡ ወደ ራሴ ስል ወደ እያንዳንዱ ግለሰብ ማለቴ ነው፡፡ እያንዳንዳችን እኔ መወጣት ያለብኝ አንድ ማኅበራዊ ኃላፊነት ምንድን ነው ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል፡፡ በመልሱ ውስጥ አቅማችን ከምናስበው በላይ ምን ያህል የጠለቀና የገዘፈ መሆኑን እንደምንረዳ አምናለሁ፡፡ እስኪ የ“የኛ” ሬድዮን በመደገፍ እንጀምር?!! አመሰግናለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

           

 

Standard (Image)

በሕገወጥ ደላሎች ሕገወጥ ስደት

$
0
0

በዳዊት ከበደ አርአያ

እንደሚታወቀው ስደት ባላደጉና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የምዕራባውያን አገሮች ዜጎችም በስደት ወደ ሌሎች አገሮች እንደሚሄዱ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን በየወቅቱ ከሚያወጣቸው ሪፖርቶች መረዳት ይቻላል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የወንጀል ተግባር ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ነው፡፡

በተለያዩ አገሮች ያለውን የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የወንጀል ተግባር አፈጻጸም፣ በሕገወጥ መንገድ ለስደት የሚሄዱ ዜጎች የሚደርስባቸውን እንግልት፣ አሰቃቂና ኢሰብዓዊ ተግባር በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

የተለያዩ አገሮች ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ለስደት እንዲዳረጉ የሚያደርጋቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ሰፊ ጥናት ማድረግ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ችግሩ ግን እያንዳንዱን ቤተሰብ ያንኳኳ ነው፡፡ ብዙዎችን ለአሰቃቂ ሞትና እልቂት የዳረገ አሳዛኝ የዘመኑ ክስተት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ከሰሞኑ የሰማነው ብዙዎችን ያሳዘነውና ያስደነገጠው ከሊቢያ በሕገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች በአነስተኛ ጀልባ ታጭቀው ወደ ጣሊያን ሊሻገሩ ከተጓዙት 190 ተጓዦች 186ቱ በባህር ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉ፣ ችግሩ ምን ያህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና ጥፋቱም የዚያን ያህል እያደገ እንደመጣ ገሃድ የወጣ ሀቅ ነው፡፡ አሁን በግልጽ የሚታየውን የሕገወጥ ስደት ዋና አቀነባባሪና ለመባባሱ ምክንያት የሆኑት የደላሎች ጉዳይ ጊዜ ሳይሰጠው እልባት ሊደረግበት የሚገባ የወንጀል ተግባር እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ዜጎች አብዛኛዎቹ በደላሎች አማካይነት እንደሆነ ከስደተኞች አንደበት በተደጋጋሚ ሲነገር ተደምጧል፡፡

በአንድ ጥናት ላይ እንደተገለጸው በሞያሌ አድርገው ኬንያ በመግባት ታንዛኒያ ማላዊና ዚምባቡዌን አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሙሉ በሙሉ በሕገወጥ ደላሎች አማካይነት እንደሆነ፣ በእነዚህ ደላሎችም ሆነ በጉዞው አስቸጋሪነት ከፍተኛ ስቃይ እንደሚደርስባቸውና አብዛኛዎቹም ኮንቴይነር ውስጥ ታሽገው እንደሚያልቁ ነው፡፡

ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚወጡ ስደተኞች በእያንዳንዱ ሰው ለደላሎች እስከ 80 ሺሕ ብር ድረስ እንደሚከፈል በጥናቱ ላይ ተጠቅሶ ሕገወጥ ደላሎች ገንዘቡን ከተቀበሉ በኋላ፣ ስደተኞቹ የኬንያን ድንበር ሲያቋርጡ በኬንያ ፀጥታ ኃይሎች ከተያዙ "የአገር ድንበር በመድፈር"ወንጀል ተከሰው ለእስር እንደሚዳረጉ ተጠቁሟል፡፡ ሕገወጥ ደላሎች ግን ወንጀል በመሥራት ያገኙትን ገንዘብ ይዘው በመሄድ ስለታሰሩ ስደተኞች ምንም ደንታ እንደሌላቸው ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

ለኢትዮጵያውያን ሕገወጥ ስደት የደላሎች ሚና የጎላ ሲሆን፣ ኬንያ ውስጥ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የኬንያ ደላሎች እንደሚበዙና ኢትዮጵያውያን ሕገወጥ ደላሎች ስማቸውን እየቀያየሩ ይኼንን ወንጀል እንደሚሠሩ ታውቋል፡፡

በአንድ ወቅት በሕገወጥ መንገድ በደላሎች አማካይነት ወደ ኬንያ ተሰደው የነበሩና የአገር ድንበር በመድፈር በሚል በኬንያ መንግሥት ተከሰው ናይሮቢ ውስጥ በእስር ላይ ቆይተው ከእስር የተፈቱ 66 ኢትዮጵያውያን፣ በድምሩ 4.8 ሚሊዮን ብር ገደማ ለሕገወጥ ደላሎች መክፈላቸው ራሳቸው ስደተኞቹ አረጋግጠዋል፡፡

ወደ ኬንያ የሚደረገው ስደት በእግርና በመኪና ኮንቴይነር ውስጥ ታሽገው ሲሆን፣ ከሞያሌ በኋላ ናይሮቢ ለመድረስ ከፍተኛ ስቃይና እንግልት እንደሚደርስባቸው በጥናቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡ ከናይሮቢ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዋ አሶዮሎየስደተኞች ማከፋፈያ ቦታ ስትሆን፣ ደላሎች ስደተኞቹን ተከፋፍለው በየአቅጣጫው የሚያስማሩባት ከተማ ናት፡፡

ሌላው በጣም አነጋጋሪና ዓለም አቀፍ ሥጋትና ጭንቀት እየፈጠረ የሚገኘው ሥፍር ቁጥር የሌለው የሰው ልጅ እያለቀበት ያለው በሊቢያ በኩል በባህር ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚደረገው ሕገወጥ ስደት ነው፡፡ የዚህን የስደት ጉዞ ለየት የሚያደርገው በተለይ ከምሥራቅና ምዕራብ አፍሪካ በከፍተኛ ሐሩርና በረሃ በደላሎች እየተመሩ፣ ከ10 እስከ 20 ቀናት የእግር ጉዞ ማድረጋቸውና ብዙዎቹ ያሰቡትንና ያለሙትን ሳያገኙ በየበረሃው ማለቃቸው ነው፡፡ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እንደሚያሰራጩት ከሆነ በዚህኛው የስደት መንገድ ያለው ሰብዓዊ ዕልቂት የጨቅላ ሴቶች መደፈርና የሰዎች የኩላሊት ንግድ እጅግ በጣም ዘግናኝና አስከፊ ነው፡፡

 በተለይም ሊቢያ እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ባለመመሥረቷ፣ ለሕገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ስቃዩና ችግሩ በዚህ አያበቃም፡፡ ከሊቢያ በትናንሽ ጀልባዎች ታጭቀው በባህር ወደ አውሮፓ ለመሻገር ተጉዘው ብዙዎች ባህር ላይ አልቀዋል፡፡ የሰሞኑ የ186 ስደተኞች ባህር ላይ መሞትም የዚህ ማረጋገጫ ነው፡፡

 ይህን ሁሉ መከራና ስቃይ አልፈው አውሮፓ የደረሱትም ቢሆኑ፣ ያለሥራና መኖሪያ ፈቃድ በመጠለያ ተጥለውና በየበረንዳው ተበትነው ለከፍተኛ ችግርና ቀውስ ተዳርገዋል፡፡ በተለይም በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ በተከሰተው ከፍተኛ ብርድና ውርጭ ምክንያት ብዙዎች ያለመጠለያ ያሉት  ስደተኞች በውርጭና እርጥበት አዘል ብርድ እያለቁ ነው፡፡

በዚሁ በሊቢያ በኩል አውሮፓ ለመድረስ ለሚደረገው ሕገወጥ ስደት እያንዳንዱ ስደተኛ ለሕገወጥ ደላሎች እስከ 200 ሺሕ ብር ድረስ እንደሚከፈልም ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ዕድለኛ ሆነው ከሞት አፋፍ ወይም ከአንበሳ መንጋጋ የማምለጥ ያህል በሕይወት ከተረፉ ነው፡፡ ብዙዎቹ  ሠርተው መለወጥ የሚችሉበትን ገንዘብ ለሕገወጥ ደላሎች አስረክበው ሀሩር እንደ እሳት በሚለበልበው የሊቢያ በረሃ ወድቀው ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርገዋል፡፡

አውሮፓ የደረሱትም ቢሆኑ እንዳሰቡትና እንዳለሙት ሳይሆን በመቅረቱ፣ ገሚሶቹ በንዴትና ብስጭት በገዛ ራሳቸው ሕይወታቸው ሲያጠፉ ቀሪዎቹ ደግሞ ከገቡበት ድብርትና ጭንቀት ለመላቀቅ የአልኮልና የዕፅ ሱሰኞች መሆናቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን የሚያወጣው መረጃ ያስረዳል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በርካቶቹ የአውሮፓ አገሮች ድንበራቸው መዝጋታቸውና በተለይም የጀርመን መንግሥት ወደ አገሮች የገቡ ሕገወጥ ስደተኞች ወደ መጡበት ለመመለስ መወሰኑን የአገሪቱ የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴር እንዳስታወቀ አልጀዚራ ቴሌቪዥን በዘገባው ገልጿል፡፡

በተለያዩ አቅጣጫዎች በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚሰደዱ ዜጎች በአብዛኛው አገር ውስጥ ባሉ አማላይ ሕገወጥ ደላሎች እየተታለሉና ድንበር እናሻግራለን በሚሉ ሕገወጥ ተቀባይ ደላሎች አማካይነት ሲሆን፣ በርካቶች በጉዞ ላይ ከሚገጥማቸው የአየር፣ የምግብና የውኃ ዕጦት ችግር በተጨማሪ ሕገወጥ ደላሎቹ ለከፍተኛ ስቃይ እንደሚዳርጓቸው የዚህ ሰለባ የሆኑ ይገልጹታል፡፡

በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር ላይ የተሰማሩ ከ80 በላይ ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሆነ በይፋ አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ200 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሕገወጥ ደላሎች ከአገር ውጪ መኖራቸውን ገልጾ፣ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለቀጣይ ደረጃ በደረጃ ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል፡፡

ሕገወጥ የሰው ዝውውር በየትኛውም መልኩ ቀላል የማይባል ወንጀል ካለመሆኑም ባሻገር፣ ለዚህ ተግባራቸው ገንዘብ ከመቀበል በተጨማሪ ስደተኞችን በማሰቃየት፣ ልጃገረዶችንና ሴቶችን በመድፈርና በመግደል የሚፈጽሙት አሰቃቂና ከባድ ወንጀል ነው፡፡

ዛሬ በታዳጊ አገሮች ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በተለይም በአውሮፓ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ጉዳይ ልዩ ትኩረት እየተሰጠው ነው፡፡ ወንጀሉን ከተቻለ ከምንጩ ለማድረቅ፣ አሊያም በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ የችግሩ አሳሳቢነት በልዩ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡

የሕገወጥ ደላሎች መረብ ከአገር አገር የተሳሰረ እንደመሆኑ መጠን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አገሮች የጋራ አቋም በመያዝ ወንጀሉን ለመከላከል፣ የድርጊቱን አስከፊነት በማስረዳት ግንዛቤ በመፍጠር ሁሉም በጋራ ሊንቀሳቀስ ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው kebededawit2016@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

                                                

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Standard (Image)

ጥልቅ ተሃድሶው ውኃ ሲወስድ አሳስቆ ነገር ሲወስድ አራርቆ

$
0
0

በጌታቸው አስፋው

ጥልቅ ተሃድሶው ለመረረውና ሆድ ለባሰው ሰው እንደሚፈልገው ፈጣን ባይሆንም የተደበቀውን ገሀድ እያወጣ፣ የካዱትን እያሳመነ፣ የዋሹትን ዋሽተናል እያሰኘ አዝጋሚ ጉዞ እያደረገ ነው፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን መርህ ሳይገነዘብ ሃያ አምስት ዓመታት በተጓዘው ሥርዓት ላይ ሰዎችን እንደ ውኃ እያሳሳቀም እንደ ነገር እያራራቀም ነው፡፡

እንደ ውኃ እያሳሳቀና እንደነገር እያራራቀም አንዱን በሌላው እያስበላ የሥርዓቱን ልብስ እየገፈፈ እርቃን እያስቀረ ነው፡፡ እንደ ዶፍ ዝናብ ባይረግጥም እንደ ሰደድ እሳት በቀስታ በሰዎች ጭንቅላት ውስጥ ሥር እየሰደደ ነው፡፡ እንደ ማዕበል እንዲነጉድ የሚፈልጉ አንዳንዶች ዱብ ዕዳ እንዲሆንም የሚመኙ ቢኖሩም እኔ ግን አልመክርም፡፡ በደንብ ያልበሰለው በደንብ ይብሰል እላለሁ፡፡

ስለኪራይ ሰብሳቢነት ትርጉም ሳያውቅ በቀን አሥር ጊዜ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት እያወራ ደመወዙን የሚበላው የመንግሥት ሠራተኛና ሹመኛ ነጭ ላብ አልቦታል፡፡ አጎብድዶ ደጅ ጠንቶ ሰብቆ ያለውድድር የተሾመ ሰው ለኢኮኖሚስት እንኳ ረቀቅ የሚለውን የውድድር ጉድለት ጽንሰ ሐሳብ አመልካች ቃል ጠቅሶ ሌላውን ኪራይ ሰብሳቢ ሲል፣ ስለራሱ አሳፋሪ የሆነ ቃል እየተናገረ ነው፣ አለማወቁን እየለፈፈ ነው፡፡

እስከ ዛሬ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ብቻ 'ይኼ ኪራይ ሰብሳቢነት ምንድን ነው? እኔም እኮ አንድ የማከራየው ቤት አለኝ'ብሎ መጠየቁን ነው የማውቀው፡፡ የማያውቁትን ጠይቆ ለመረዳት በመድፈርም ተከታይ ቢያጣም ኃይሌ ሪከርድና ዝምታ ሰብሯል፡፡

ሰሞኑን የነጋዴዎች ተሃድሶ የሚመስል በኑሮና ቢዝነስ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በርበሬ ውስጥ ሸክላ የጨመረውን፣ ዘይት በእግሩ ያቦካውን፣ እንጀራ ውስጥ ጀሶ የጨመረውን፣ ወዘተ እያነሱ ሰዎች ስለንግድ ሥነ ምግባር ሲወያዩ ሰምቼ ነበር፡፡ 

ከኢንቨስትመንት ባለሥልጣን የተጋበዙ ባለሙያ ከአፍሪካ ለመጡ ኢንቨስተሮች፣ 'ሥልጠና ስንሰጥ እናንተ እኛን ኢንቨስት አድርጉ ብላችሁ ትሰብኩናላችሁ፣ የእናንተ ሰዎች ለምን እኛ ጋር መጥተው ኢንቨስት አያደርጉም?'አሉን አሉ፡፡

'የእኛ ሰዎች ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ወዘተ ሄደው የጉልበት ሥራ ሠርተው ይኖራሉ፡፡ የእናንተ ሰዎች ለምን እኛ ጋር መጥተው የጉልበት ሥራ ሠርተው አይኖሩም?'ብለው ለምን አልመለሱም ብዬ አሰብኩ፡፡ 'ለእናንተስ መቼ በቃና?'የሚል መልስ ሰጥተው እንዳያሳፍሯቸው ፈርተው ሊሆንም ይችላል ብዬም ገመትኩ፡፡

እንጀራ እጠግብ ብለው እጃቸውን ለሙስናም ሆነ ለምን ቸገረኝነት የአዕምሮ ዝቅጠት ከሰጡ ብዙ ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ ጥቂት ሺዎች በጥልቅም ሆነ ላይ ላዩን በመታደስ ወዲያው የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡ ቢመጣም 'ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል'ይሆናል፡፡ የመናገርና የመጻፍ ነፃነት ሳያገኙ፣ ሕዝብን ቀድመው ሳያነቁ፣ አመፅ በታየ ቁጥር ለሥልጣን ቋምጠው ቤንዚን የሚያርከፈክፉ የፖለቲካ ሰዎች ፋይዳ ቢስ ናቸው፡፡ ሕዝብ ለትንንሽ ሰዎች ሥልጣን ደሙን አያፈስም፡፡

ፖለቲከኞችና አብዮታውያን ወይም የዴሞክራሲያዊ መብት ታጋዮች ሕዝብ ለማስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት፣ በድብቅና በግልጽ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳቦች ፍልስፍናዎችን፣ ፕሮግራሞችን፣ ታሪኮችን፣ ለውጦችን ይተነትናሉ ይጽፋሉ፡፡ ሕዝብን ያሳምናሉ፣ ያነቃሉ፣ ኅብረ ብሔር ድርጅት ይፈጥራሉ፡፡

የግል ታሪኩን ወይም ልብወለድ ተረት የጻፈና የተረጎመ ወይም በምርጫ ሰሞን የተሰጠውን ጥቂት ሰዓታት ተጠቅሞ በቅጡ የማያውቀውን ነገር የቀባጠረ ሁሉ ሕዝብን ያነቃ ይመስለዋል፡፡ የቢሮ ማኅተምና ቁልፍ ተሰራርቀው ከዛሬ ጀምሮ ሊቀመንበር፣ ፕሬዚዳንት፣ ዋና ጸሐፊ እኔ ነኝ የሚባባሉ ብሎላቸው ለሥልጣን ቢበቁም በጎሳና በጓደኝነት ሥልጣንን ለኔ ለኔ ብለው መልሰው ይጣላሉ፡፡

እያረጀ ያለው የመገነጣጠል መጥበብ ስብከትና ስሜት ከነጀብደኝነቱ ሳይከስም፣ በኢትዮጵያ ስም ከመታገልና ከማታገል ከመታደስና ንቃተ ህሊናን ከማሳደግ በፊት ሁሉም በእኩል ዓይን የሚታይበት የጋራ አገር መገንባት አይቻልም፡፡ መንግሥት ተጥሎ መንግሥት ቢመሠረትም እንኳ የኋለኛው የቀድሞው ግልባጭ (ፎቶ ኮፒ) ይሆናል፡፡ የነፃነት ታጋይ የነበረው ኢሳያስ ወደ ጨቋኝ ኢሳያስነት እንደተለወጠ እንሰማለን፡፡

በልማዳችንና ከአያት ቅድመ አያት በወረስነው ወግ ድህነቱ ዕጣ ፋንታው ስለሆነ ነው እያልን፣ የፈረንጆቹ አልበቃ ብሎ ልጆቻችንን የአጎራባቾቻችን ሎሌና ገረድ ለማድረግ እያሰብን ሳለን በተሃድሶ ጥቂቶች ቢገማገሙ ምን ለውጥ ይመጣል?

እንደ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አስተምህሮት ሰዎች ከምርጫ የሚገኝን ጥቅም የላቀ ለማድረግ አዋቂ እንዲሆኑ፣ ሁሉም ሰው በቂ አዎንታዊ መረጃዎችን መጨበጥ አለበት፡፡ (Acquire Positive Information to be Rational Enough to Optimize Benefits from Choice) ወደን በምርጫችን ሳይሆን ሁኔታው ገፍቶ መጥቶ ምቾቱና ድሎቱ ቀርቶ ለምን እንደተፈጠርንና ከሌሎች ለምን እንደምናንስ ማወቅ ተስኖናል፡፡ እኛ ሁኔታውን አንቆጣጠርም፣ ሁኔታው እኛን ይቆጣጠረናል፡፡

 

በዚህ ሰሞን በጋዜጣ በወጣ ዜና ያለፈቃድ ሄደው በሰው አገር ሲንከራተቱ እስር ቤት ለገቡት ምህረት እንዲደረግላቸው ተማፅነውና በመንግሥት ዕውቅና የተሰጣቸው፣ ገረድና ሎሌ ለመላክ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከዓረብ አገር ባለሥልጣናት ጋር ተዋውለው መጡ ተባለ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ 'ሌሎች አገሮች በእኛ የዕድገት ደረጃ ላይ በነበሩ ጊዜ የሴቶቻቸውን ፀጉር ሽጠው ነበር፡፡ የእኛም የወደፊት ተስፋችን በሀዋላ የሚላክ ገንዘብ ከፍ እንዲል መትጋት ነው'አሉ፡፡ ተገርደን ሁለመናችንን ሽጠን ነው ለአገራችን በሀዋላ ገንዘብ መላክ የምንችለው፡፡ ዕውን እኛ የተፈጠርነው ለዚህ ብቻ ይሆን እንዴ? ዕጣ ፈንታችን ግርድናና ሎሌነት ነው እንዴ? ሌላ ምርጫ የለንም እንዴ፡፡ ጥልቅ ተሃድሶው መሆን የነበረበት ስለዚህና መሰል ጉዳዮች እንጂ፣ የራበው ወይም በዚህ መሰል ኅብረተሰብ ውስጥ ኖሮና ተኮትኩቶ ስርቆትን ዓመል ስላደረገው ሰው አልነበረም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በአንድ ጆሮ ተሰምቶ በሌላ ጆሮ የሚፈስ የቴአትር መድረክ ቀልድ አይደለም፡፡ የአዋጅና የሕግ ያህል ሊቆጠር ይችላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በግልጽነታቸው እውነቱን ሳይደብቁ በመናገራቸው ሊደነቁ ይገባል፡፡ ኢኮኖሚስቶቻችንማ እንደ ሮኬት በዕድገት ወደ ሰማይ ተተኩሰናል ነበር ያሉት፡፡

የፖለቲካ ሰዎች በዓይናቸው ባዩት እርሻው፣ ሕንፃው፣ መንገዱ፣ ወዘተ ሊረኩ ይችላሉ፡፡ የዚህ ዘመን ዕውቀት ያለው ኢኮኖሚስት ግን የሚያምነው ዛሬ ሆኖ በሚታየው ብቻ ሳይሆን፣ ነገ ይሆናል በሚባለው ተስፋም (Expectation) መሆኑን ከትምህርት ቤት ከወጡ በኋላ የኢኮኖሚክስ መጽሐፍ አንብበው የማያውቁ ኢኮኖሚስቶች እንዲያነቡ ምክር ያስፈልጋቸዋል፡፡ የፓርላማ አባል፣ ሚኒስትር፣ አምባሳደር፣ ዶክተር፣ ፕሮፌሰር፣ ጳጳስ፣ ሼህ፣ ወዘተ ነገን ፈርቶ ለሥራ በተላከበት ውጭ አገር የዘበኝነትና የፅዳት ሥራ ፈላልጎ ሲቀር፣ እዚህ የቀረው ምን ነገ አለ ብሎ ተስፋ ያደርጋል፡፡

አዳም ስሚዝ ነፃ ገበያን ሲተነትን ከካፒታሊዝም ሥርዓት በፊት የነበሩት የፊውዶ ቡርዧ ሥርዓተ ማኅበርና የዘመነ-ንግድ (Mercantalism) ኢኮኖሚያዊ ሥርዓትን ልማዶችና አመሎች፣ በአጠቃላይ ማኅበራዊ ሥነ ምግባሮች ለነፃ ገበያ ካፒታሊዝም ስለማይስማሙ ነቅፎ በመንግሥት ጥረት መወገድ እንደነበረባቸው ጽፏል፡፡

በእኛ አገር የፊውዳሉም፣ የሶሻሊስቱም፣ የካፒታሊዝሙም፣ የዱር ቤቴ ፖለቲካውም ልማዶችና አመሎች እንዲሁም ማኅበራዊ መስተጋብሮች ተቀላቅለው ባሉበት ሁኔታ፣ የተዘበራረቀ የኢኮኖሚ ሥርዓት እንጂ ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ የተመቻቸ የኢኮኖሚ ሥርዓት ሊኖር እንደማይችል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ከገባ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ወደ ምኒሊክ ሆስፒታል ታክሲ ልሳፈር ስል ሾፌሩ በእጄ ለያዝኳት በጣም ትንሽ ፌስታል ያስከፍልሀል አለኝ፡፡ እንዴት ይሆናል ብለው ነፃ ገበያ ነው ካልተስማማህ ውረድ አለኝ፡፡ ታክሲው የእርሱ ቢሆንም መንገዱ ግን የተሠራው በሕዝብ ሀብት እንደሆነ ባውቅም፣ ታክሲ የማሽከርከር ፈቃዱንም ያገኘው በሥነ ሥርዓት ሕዝብን ለማገልገል እንደሆነ ባውቅም ልመልስለት አልፈለግሁም፡፡

ይኸን ባለኝ ወቅት እኔ በአስመራ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ አራተኛ ዓመት ተማሪዎችን ኢኮኖሚክስ ሳስተምር ቆይቼ የመጣሁ ከመሆኔም በላይ፣ ስለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መጽሐፍ ጽፌ አሳትሜ ነበር፡፡ ሙያዬን የታክሲ ሾፌር ሊያስተምረኝ መሞከሩ ቢያናድደኝም፣ ያንኑ ሰሞን ‹‹ጊዜ ያነሳው ቅል ድንጋይ ይሰብራል›› የሚል ጽሑፍ በየግድግዳው ላይ ተጽፎ ስላየሁ በዚህ ተጽናናሁ፡፡ ዛሬም ያው ነው፡፡ ጊዜ ያነሳው ቅል ድንጋይ እየሰበረ ነው ያለው፡፡ ነገ ይለወጣል እያልን እየተጽናናን ነው ያለነው፡፡

ብዙ ዓመታት የለፋሁበትን የኢኮኖሚክስ ሙያዬን ጋዜጠኛው ላስተምርህ ይለኛል፡፡ ፖለቲካኛው ላስተምርህ ይለኛል፡፡ ነጋዴው ላስተምርህ ይለኛል፡፡ ለመሆኑ ይህ የኢኮኖሚክስ ሙያ መቼ ይሆን የሚከበረው? እስከ መቼ ይሆን ቅል ሁሉ እየተነሳ ልስበርህ የሚለው? ኢኮኖሚክስ የማንም ሰው የኑሮ ዘዴ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ሊያውቀው ይገባል ቢባልምኮ፣ የኑሮ ዘይቤ ምህንድስና የሆነውን ሙያ የተማረውን ድንጋይ የሰበረ ቅል መንገደኛ ሁሉ ተነስቶ ላስተምርህ ይለዋል ማለት አይደለም፡፡

ምን ያድርጉ እውነታቸውን ነው፡፡ ኢኮኖሚክስን የሚያወቁት በተሰበከላቸው ልክ ነው፡፡ ኢሕአዴጎች ሥልጣን በያዙ እስከ አሥረኛው ዓመት ቢሆን ኖሮ ሊገባኝ ይችል ነበር፡፡ ሳይንሱን ከጣሪያ ላይ የሚያወርድላቸው ሰው ስለሌለ ነው ሊባል ይችላል፡፡ አሁን ግን ዕድሜ ለዚያ ምሁር ማምረቻ ዩኒቨርሲቲ ሁሉም ባችለር፣ ማስትሬት፣ ዶክትሬት የሚለውን የምሁርነት መታወቂያ ሠርተፊኬት ይዘውታል፡፡

የፖለቲካን ችግር ጥቂት ሰዎችን ገንዘብ አጉርሶ ወይም ታምራት ላይኔ ላሱ የተባለውን ነገር አልሶ ዝም በማሰኘት ይወጡታል፡፡ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ሆዱን ያመመውን የኢኮኖሚ ችግር ለማን አጉርሰው ማንን አልሰው ይወጡታል፡፡

ጥልቅ ተሃድሶውን ጥቂት ሰዎች ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት በማለት በጅምሩ እርስ በእርሳቸው በታሸገ ውኃ እየተሳሳቁ ተነቃቅፈው በመጨረሻው በነገር ተወነጃጅለው፣ እንግሊዞች አቅም ያለው አቅም በሌለው አጽም ላይ ቆሞ ይኖራል 'Survival of the fittest'አንደሚሉት ከፊሉ ከፊሉን በልቶ የሚያበቃ ሳይሆን በጊዜ ብዛት በማየት፣ በመገንዘብ፣ በማጤን፣ በመናገር፣ በመስማት፣ በመጻፍ፣ በማንበብ፣ የሕዝብ ሁሉ ንቃተ ህሊና የሚያድግበት ያድርግልን፡፡ ያኔ የጠላነውን ሁሉ በአንድ ጣታችን ብቻ ገፍተር አድርገን አንገዳግደን ራሱ አውቆ እንዲወድቅ አድርገን እንጥላለን፡፡ ለአገራችን ከዚህ ውጪ ምንም መፍትሔም የለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

Standard (Image)

የኢትዮጵያንና የኤርትራን ያልተቋጨ እሰጥ አገባ ለመስበር ምን ይደረግ?

$
0
0

በገራገር ዘበርጋ

   በኢትዮጵያና በኤርትራ በኩል ያላችሁ አንባቢያን የሁለቱም አገሮች የወቅቱ ‹‹ሰላም የለሽ፣ ጦርነት የለሽ›› አቋም ምን ያህል የሁለቱንም ሕዝቦች ኑሮና ሕይወትን በከፋ ደረጃ እየጎዳ እንደሚገኝ የምትገነዘቡት ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ የጉዳቱ መጠን ከአንዱ አገር ወደ ሌላው ሊለያይ እንደሚችል የተለያዩ ማስረጃዎችን እየዘረዘሩ ማቅረብና ማረጋገጥ የሚቻል ቢሆንም፣ የአሁኑ መነጋገሪያ ርዕስ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ስላልሆነ የሕዝቦቹ ቀጣይ ጉዳት መኖሩን ብቻ በመግለጽ ላልፈው እፈልጋለሁ፡፡

   ሁለቱም አገሮች ከከባዱ ጦርነት ወዲህ በጠላትነት ዓይን እየተያዩ እንደቀጠሉና ይኼም ክስተት ከ1990 ዓ.ም. የባድመ ወረራ ወዲህ 19ኛ ዓመቱን ሊደፍን እየተቃረበ እንደሚገኝ ግልጽ ነው፡፡ ጦርነቱ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ቢደመደምም የድንበር ኮሚሽኑ የኃላ ኃላ በሰጠው ውሳኔና ውሳኔውንም ለመተግበር በተከተለው ውዝግብ ምክንያት ሁለቱም አገሮች ዓይን ለዓይን ላለመተያየት የተከተሉት የተሳሳተ መንገድ ነው፡፡ ምናልባትም የዲፕሎማሲ ግድፈት ሊባል በሚችል አካሄድ በድንበር አካባቢ በሁለቱም ወገኖች በኩል ከፍተኛ ጦር በማስፈር የ‹‹ሰላም የለሽ ጦርነት የለሽ›› እውነታን ፈጥረው የውጥረት ሕይወት እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ ለዚህም ይመስላል በሁለቱም ድንበር አካባቢዎች ማለትም በኢትዮጵያ በኩል በቡሬ፣ በኤሊዳር፣ በባዳ፣ በዛላምበሳ፣ በእገላ፣ በአሕሰኣ፣ በራማና በባድመ፣ ወዘተ… በኤርትራ በኩል ደግሞ በአሰብ፣ በማይቲ፣ በበይሉል፣ በምራራ፣ በጾሮና፣ በማይምነ፣ በምሽኳ፣ በሸምቦቆና በኦምሓጀር ወዘተ… አካባቢዎች የረባ ልማት እንቅስቃሴ ለማካሄድ አለመቻሉን ስንመለከት፣ በዚህ አካባቢ የሚኖረው ሕዝብም የቆቅ ሕይወት ማለትም በሥጋትና በፍራቻ መኖር መቀጠሉን ስንመለከት ጉዳቱን እጅግ አሳሳቢ ያደርጓል፡፡

ታዲያ የሚገርመው ጉዳይ የዚህ አካባቢ ሕዝብ በትግራይ ድንበር ያለውም ይሁን በኤርትራ ድንበር የሚገኘው ሕዝብ፣ ከጦርነቱ በፊትና ከዚያም ቀደም ብሎም በማኅበራዊ ሕይወቱ በጣም የሚቀራረብና ብሎም በደስታና በሐዘን ጊዜም የማይለያይ ነበረ፡፡ ከውጥረቱ መፈጠር በኃላም ሳይቀር አንዳንዴ በምልክት፣ በሚስጥርና በጨለማ መገናኘቱ አልቀረም፡፡ ከኢትዮጵያ በኩል ዜጎቹ በኤርትራ መንግሥት ጠባቂዎችና የደኅንነት አባላት እጅ እንዳይወድቁ በመሥጋት ማስጠንቀቁን የቀጠለበት ቢሆንም፣ ከኤርትራ በኩል ግን እንኳንና በሚስጥር ዘመዶቻቸውን ጠይቀው የሚመጡትን ይቅርና ድንበር የመሻገር ዕቅድ ወይም ሐሳብ ሊኖራቸው ይችላል ተብለው የሚጠረጠሩትን ሲያስርና ሲያንገላታ ምናልባትም ሲገድል ከርሟል፡፡

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ቀጣይነት     

የድንበር ውጥረቱ ከተከሰተ ወዲህ በድንበር አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ በተለያየ መንገድ ሲገናኝ ቆይቷል፡፡ ለዚሁም እንደ አብነት ሊጠቀሱ የሚችሉትን ክስተቶች ልጥቀስ፡፡ በዛላምበሳ አካባቢ ሕዝቡ የሚኖርበት ድንበር የሚለያየው በሚታረስ ማሳ ደረት ነው፡፡ ስለሆነም የሁለቱም አገሮች ገበሬዎች ማሳቸውን ማረስ ካለባቸው እስከ ደረቱ ጥግ ነው የሚያርሱት፡፡ በመሆኑም ፊት ለፊት መገናኘታቸው ስለማይቀር የልባቸውን ከማውራት የሚያግዳቸው ነገር የለም፡፡ በዚሁ ድንበር አካባቢ ሰው ሲሞትና ሐዘን ሲያጋጥም መርዶ ነጋሪዎች እየዞሩና እየጮሁ ማን እንደ ሞተና ቀብሩም የት እንደሚፈጸም በግልጽ እየሰሙት ስለሆነ የሚከናወነው፣ ምንም እንኳን ሕዝቡ ድንበሩን ወይም የማሳ ደረቱን አልፎ ለመሄድ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ባይፈቅድለትና በቀብሩ ላይ ለመገኘት ባይችልም፣ ሐዘኑን በለቅሶና በማስተዛዘን ማከናወኑ ግን ደረቱን (ድንበሩን) ሳይሻገርም የሐዘኑን ሒደት ከማከናወን የሚያግደው የለም፡፡ ሐዘናቸው ሲገልጹም የአንዱ አገር ሕዝቦች በኪሎ ሜትር ርቀት እንደሚተያዩ ሆነው በመደዳ ይቆሙና የሌላው አገር ሕዝቦች ደግሞ በወዲያው ድንበር እንዲሁ በኪሎ ሜትር ርቀት በቅጡ እንደሚተያዩ ሆነው በመደዳ ይቆማሉ፡፡ ከዚያ በኃላም አስተዛዛኝ ሕዝቡ ጎንበስ ብሎ ‹‹ጽናቱን ያስጣችሁ!›› የሚል መልዕክት ከማዶው ላለው ለሐዘንተኛው ሕዝብ ያስተላልፋል፡፡ ሐዘንተኛው ሕዝብ ደግሞ ‹‹በእኛ የደረሰ አይድረስባችሁ!›› እያለ ጎንበስ በማለት የመልስ መልዕክት ይሰጣቸዋል፡፡ በዚሁ ሒደትም የሐዘን ሥነ ሥርዓቱ በሁለቱም ወገኖች ይከናወናል፡፡ ይህንን የሕዝብ የተለመደ ባህላዊ ተግባር ምናልባት ጦር የሰፈረበትና ‹‹አትለፉ፣ ከፊታችን አትቁሙ›› የሚል ቁጥጥር ከሌለው በስተቀር፣ በየትኛውም አስተዳደራዊና የፀጥታ ቁጥጥር ሊታገድ የሚችል ክስተት አይደለም፡፡

የድንበር ገበሬዎችና እረኞች በሚያውቁዋቸው የድንበር በርካታ መተላለፊዎችም የተለያዩ የእህልና የቤት ፍጆታ ለማዶዎቹ ዘመዶች በድብቅ ማስተላላፍም የተለመደ ክስተት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ዘመዶችን አሻግሮ ወደ ኢትዮጵያ እንዲያልፉ የማድረግ ተግባርም ምንም እንኳን ለአደጋ የሚያጋልጥ ቢሆንም፣ የመጣው ይምጣ ተብሎ የሚወሰድ የተለመደ የአንዳንድ የድንበር ነዋሪዎች ተግባር እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ለዚሁም ይመስላል ድንበር ተሻግሮ ወደ ኢትዮጵያ እየጎረፈ ያለው ኤርትራዊ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሄዶ በአሁኑ ጊዜ በስደተኛ ማዕከላት ብቻ ወደ 170,000 የሚጠጋ ስደተኛ ተጠልሎ ይገኛል፡፡ ይህ እንግዲህ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገር የወጣውን፣ በኢትዮጵያ ካሉት ዘመዶቹ ጋር ተጠልሎ ቋሚ ሕይወት እየመራ የሚገኘውን፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በሁለተኛና በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተማረ የሚገኘውን፣ ከውጭ ጥሪ ይመጣልናል እያሉ በአዲስ አበባ ኮንደሚንየም ቤቶች በትንሽ ኪራይ በብዛት ሆነው ተከራይተው እየኖሩ የሚገኙትን በርካታ ወጣቶችን፣ ወዘተ… ሳይጨምር ነው፡፡ በዚህ ዓመት ማለትም በ2009 ዓ.ም. የአክሱም ጽዮን በዓልም ከድንበር አካባቢ ተደብቀው ገብተው ኢትዮጵያዊያንም ረድተዋቸውና መርተዋቸው፣ በድብቅም የሚያውቅ አካል እንቅስቃሴያቸውን እያወቀውም አክሱም ድረስ መጥተው ለፈጣሪያቸው ጸሎት አድርሰው የተመለሱ ኤርትራዊያን እንዳሉም ከሁነኛ ምንጭ ያገኘሁት መረጃ አረጋግጦልኛል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ሒደት የድንበር ሕዝቡ የዘወትር ተግባር ሲሆን፣ ከጾረና ጀምሮ እስከ ባድመ አካባቢ በመረብ ወንዝ የሚካለለው ሕዝብ ቢሆንም ማዶ ለማዶ ሲተያይ ስለሚውልና በወንዙ ሲጠቀምም የሚገናኝበት ሁኔታ ስለሚኖር፣ የተለያዩ የጋራ መስተጋብሮች ቢከሰቱ ሊያስደንቅ አይችልም፡፡

 ‹‹ሰላም የለሽ ጦርነት የለሽ›› ፖሊሲ

የሁለቱም አገሮች መንግሥታት ከድንበር ግጭቱ ወዲህ የሚከተሉት ፖሊሲ ሌላ ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳይኖር ‹‹አትንካኝ አልነካህም!›› ወይም ‹‹አትምጣብኝ አልመጣብህም!›› ወይም ‹‹ጦርነት ካልከፈትክብኝ እኔም አልነካህም!›› ወዘተ… የሚመስልና ድንበሩ ግን ለ‹‹ሰላም የለሽ ጦርነት የለሽ!›› ሁኔታ ተጋልጦ እንደሚገኝ ነው፡፡ በአንፃሩ ግን የሁለቱም አገሮች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጦር በድንበር አካባቢ ሰፍሮ እንደሚገኝ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሁኔታ እስከ መቼ የሚቀጥል ነው? ብለን የጠየቅን እንደሆነ ማንም መልስ አለኝ ብሎ የሚቀርብ አካል የለም፡፡ ሁለቱም መንግሥታትም ጭምር ይህ የ‹‹ሰላም የለሽ ጦርነት የለሽ!›› ሁኔታና ክስተት የመቋጫው ጊዜ መቼ እንደሆነ እንደማያውቁት፣ እንዲያውም ክስተቱ የመቋጫ ጊዜ ይኑረው ወይም አይኑረው ብዙም የተጨነቁበት እንደማይመስሉ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴና ካሉት ሁኔታዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለምን? እስከ መቼስ?

በኤርትራ መንግሥት በኩል ያለውን ፖሊሲ የመረመርን እንደሆነ፣ ‹‹በድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ምክንያት ለእኔ የተወሰነልኝን መሬት ኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ ባለመፈለጓ ምክንያት አሁንም መሬቴ ወይም ግዛቴ በኢትዮጵያ ተወሮና ተይዞብኝ ይገኛል፡፡ ለዚሁ ሁነኛ አብነትም ባድመ ለእኔ ተወስኖልኝ ሲያበቃ ኢትዮጵያ በቁጥጥሯ ሥር አድርጋ ማስተዳደሯን ቀጥላለች፡፡ ይህ በውሳኔ ያገኘሁት ግዛቴ ኢትዮጵያ ወዳም ይሁን በኃያላኑ መንግሥታት ተገድዳ እንድትሰጠኝ ካልተደረገ ከኢትዮጵያ ጋር እርቅ ብሎ ነገር የለም፤›› የሚል አቋም በመያዝ ሲቀሳቀስ ከርሟል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ያለውን ፖሊሲ ደግሞ ስንመረምር፣ ‹‹በድንበር ኮሚሽን ውሳኔ መሠረት የተላለፈው ውሳኔ ለመተግበር በባድመ ብቻ ሳናተኩር በርካታ የኤርትራ መሬት ለኢትዮጵያ ይሁን የተባለ አለ፡፡ በርካታ የኢትዮጵያ መሬትም ለኤርትራ ይሁን የተባለ አለ፡፡ ውሳኔውን ሁለታችንም ቁጭ ብለን ካልተነጋገርንበት በስተቀር ጉዳዩ ከአንዱ አገር ወደ ሌላው መሬት በማስተላለፍ ብቻ የሚፈታ አይደለም፡፡ መሬቱ ሲተላለፍ በቦታው ሕዝብም ስላለ ሕዝቡስ ምን ይሁን ሳንል በደምሳሳው አንተ ይህን ውሰድ! አንተም ይህን ውሰድ! በሚል አካሄድ ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጠው አይችልም፡፡ ስለዚህ የሁለቱም አገር የድንበር ሕዝብ ለክፍለ ዘመናት አብሮ የኖረና የተሳሰረ በመሆኑ፣ እንዲሁ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ምን አለ? በሚል ብቻ ሊፈታና ሊስተካከል የሚችል ስላልሆነ ቁጭ ብለን ተነጋግረን እንፍታው፤›› የሚል አቋም እንዳለው በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡

የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የእንነጋገር ሐሳብ ‹‹በፍጹም አልቀበልም! መሬቱ ይሰጠኝና ከዚያ በኃላ እንነጋገራለን›› የሚለውን አቋሙን አጥብቆ በመያዝ የቀጠለ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ‹‹ቁጭ ብለን ካልተነጋገርን አሳልፌ የምሰጠው መሬት የለኝም›› የሚለውን አቋሙን አጠናክሮ ይዟል፡፡ ሁለቱም መንግሥታት ከጦርነቱ ማግሥትና ከድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ በኃላ ከላይ የተገለጸውን ተፃራሪ አቋም በመያዝና በጠላትነት መቀጠላቸው እንዳለ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም አንዱ መንግሥት የሌላውን መንግሥት ተቃዋሚ በማስጠለልና ድጋፍ በማድረግ ተቃራኒውን መንግሥት ወይም አገር የሚጎዳበትን ወታደራዊና ኢንተለጀንሳዊ ተግባርን ሲያካሂዱ ከርመዋል፡፡ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የተጠለሉት የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች ተጠናክረው ባይወጡምና አሥጊ ኃይል ሆነው ለመገኘት ባይችሉም፣ በየጊዜው ስብሰባዎችንና ጉባዔዎችን በማድረግ ተቃዋሚነታቸውን ለማሰማት ሲንቀሳቀሱ ይታያል፡፡ በኤርትራ መንግሥት በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚቃወሙ ወገኖችን በማደራጀት፣ በማሠልጠንና በማስታጠቅ ከዚያም አልፎ አንዳንዶቹን ወደ አገሪቱ ሰርገው እንዲገቡና ጉዳት እንዲያደርሱ በማድረግ ሲንቀሳቀስ ከርሟል፡፡ አሁንም እየቀጠለበት ይገኛል፡፡ እንግዲህ ጠላትነት ጥሩ ጎን ሊኖረው አይችልምና ሁለቱም መንግሥታት የጥላቻቸውን ደረጃ ከጫፍ እንዲደርስ አድርገውታል፡፡ በመሆኑም የጠላትነት ደረጃው መውጫ ቀዳዳ የሌለው እስኪመስል ድረስ ሁለቱንም አገሮች ውጥረት ውስጥ አስገብቶዋቸው ይታያል፡፡ ሁለቱም መንግሥታት አንዱ መንግሥት በሆነ መንገድ እንዲወድቅላቸው እስከመመኘት በሚመስል አካሄድ መውጫ መንገድ አጥተው እየባዘኑ ያሉ ይመስላል፡፡

ሰርጎ ገቦችን ማሰማራትና ተመጣጣኝ የአፀፋ ዕርምጃ  

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ሁለቱም መንግሥታት የያዙትና ያዋጣናል ብለው ተግባራዊ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አለ፡፡ በኤርትራ በኩል የሶማሌ አቦ፣ የኦነግ፣ የግንቦት ሰባት፣ የአርበኞች ግንባር፣ ወዘተ… ጀሌዎችን በማሠልጠንና በማስታጠቅ ከተቻለም ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በማበር ሰርጎ ገቦችን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባትና የልማት ተቋማትን ለማውደም፣ አኅጉራዊ ስብሰባዎችን ለማደናቀፍ፣ ወዘተ… ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሶማሊያ ጦረኞችንና አሸባሪዎችን እስከ መደገፍ፣ ማስጠለል፣ ማሠልጠን፣ ማስታጠቅና ማሰማራት የደረሰ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ኢንተሊጀንሳዊ፣ ወዘተ… ተግባራትን በመፈጸም የኢትዮጵያን ጥቅም ለመጉዳት ያልተቋረጠ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ከርሟል፡፡ በዚህም የኤርትራ መንግሥት ተግባር አብዛኛው የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎችና በሕዝቡ የነቃ እንቅስቃሴ በእንጭጩ የከሸፉ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ጥቃቶች ግን ጉዳትን አድርሰው ያለፉበት ሁኔታም ይኖራል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የተከተለው ፖሊሲ ደግሞ ‹‹የኤርትራ መንግሥት አንዳች ጥቃት በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ያደረሰ እንደሆነ ተመጣጣኝ የአፀፋ ዕርምጃን በመውሰድ ማስታገስ›› የሚል አቋም ይዞ ሲንቀሳቀስ ከርሟል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ሰርጎ ገቦችን በመላክ ወይም ራሱ በአሰማራው ኃይል አንድ ጉዳት ሲያደርስ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ተመጣጣኝ የአፀፋ ዕርምጃ ወስጃለሁ በማለት ሲከላከል እንደቆየና አሁንም ይህንኑ አቋሙን አጠናክሮ እየቀጠለበት ይገኛል፡፡ በመሠረቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ‹‹ተመጣጣኝ የአፀፋ ዕርምጃ›› የሚለውን አቋም ባይዝና ጦርነትን የሚጋብዝ የኃይል ዕርምጃ ለመውሰድ ቢጋበዝ ኖሮ፣ አሁን እያቀላጠፈው የሚገኘውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት በጣም ይቸገር እንደነበር ዕሙን ነው፡፡ ለምን ቢባል በሁለቱም አገሮች ድንበር አካባቢ ጦርነት እንደተቀሰቀሰ በሚመሰል ሁኔታ የሆነ እንቅስቃሴ ቢደረግ ኖሮ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታገኘውን የውጭ ዕርዳታና ብድር፣ የውጭ ኢንቨስተሮች የሚያፈሱትን መዋእለ ንዋይ፣ በአጠቃላይም በአገሪቱ የሚካሄደውን የልማት እንቅስቃሴ ክፉኛ የሚጎዳበት ሁኔታ ይፈጠር እንደነበር ስለሚገመትና ስለሚታወቅ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ሰላም የለሽ ጦርነት የለሽ!›› ፖሊሲው ጠቅሞኛል እንጂ አልጎዳኝም የሚል ይመስላል፡፡ ለነገሩ የጦርነት ሁኔታ በድንበር ማንዣበቡ ቢታወቅ ወይም ቢሰማ ኖሮ ማን ደፍሮ ገንዘቡን በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያፈሳል? በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በባድመና በሌሎችም ድንበር አካባቢዎች ተቀስቅሶ በነበረው ጦርነት ምክንያት የዓለም የገንዘብ ተቋማት፣ የልማት አጋር አገሮችና መንግሥታት እንዲሁም ኢንቨስተሮች ምን ያህል ከኢትዮጵያ መንግሥት የልማት እንቅስቃሴ ተቆጥበውና እጃቸውን ሰብስበው እንደነበረ ከኢትዮጵያ መንግሥት የበለጠ የሚያውቀውና ጉዳቱን የተሰማው ኃይል ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳን በድንበር አካባቢ ሊኖር ይችል የነበረው ልማት በእጅጉ የጎዳው ቢሆንም፣ በሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ ግን ልማቱ መፋጠኑ በግልጽ ይታያል፡፡

በኤርትራ በኩል ያለው የልማት እንቅስቃሴ ውስን እንደ መሆኑና በመንግሥት ራሱ የሚከናወንና አንዳንዴም ከውጭ ባለሀብቶች ጋር መንግሥት በሽርክና የሚያካሂደው የልማት እንቅስቃሴ በመሆኑ፣ የ‹‹ሰላም የለሽ ጦርነት የለሽ!›› ሁኔታው የዓለም የገንዘብ ድርጅቶች ዕርዳታና ብድር እንዳይሰጡ፣ የውጭ ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን ይዘው እንዳይገቡ፣ ወዘተ… እንቅፋት ሊፈጥር ይችላል የሚባልበት ክስተት ሊፈጥር አይችልም፡፡ ምክንያቱም የመንግሥቱ ፖሊሲ እነዚህን ኃያላን የሚያሳትፍ ስላልሆነ፡፡ ነገር ግን አገሪቱ ውስጣዊ ሰላም ቢኖራትና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ሰላማዊ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ገንዘብ ያላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ በኤርትራም ገንዘባቸውን ለማፍሰስ የማይዘጋጁበት ሁኔታ አይኖርም ነበር ለማለት አይቻልም፡፡

ይህ የ‹‹ሰላም የለሽ ጦርነት የለሽ!›› ሁኔታ እስከ መቼ መቀጠል አለበት? ለሚለው ጥያቄ በሁለቱም አገሮች በኩል ግልጽ የሆነ ራዕይ ወይም አመለካከት አለ ለማለት አይቻልም፡፡ ሁለቱም መንግሥታት የአንዱ መንግሥት በሆነ ተዓምር እንዲወገድለት ወይም እንዲወድቅለት የሚጠባበቅ ይመስላል፡፡ ለነገሩ የኤርትራ መንግሥት የሚያስበው ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በዘር በተመሠረተ ፌዴራሊዝም የተዋቀረ ስለሆነ ጊዜ ይፈጃል እንጂ አንድ ቀን ሥርዓቱ እርስ በርሱ ተባልቶ ይፈርሳል›› የሚል የተሳሳተ አቋም እንደሚያራምድ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የፈጣሪም ኃይል ተጨምሮበት ይህ ውድቀት አንድ ቀን እንዲከሰትለት ይጠባበቃል፡፡ አሊያም ይህንኑ ውድቀት ሊያግዝ ይችላል የሚለውን የታጠቀ የሰርጎ ገብ ኃይል በማደራጀትና ወደ ኢትዮጵያ አስርጎ በማስገባት የኢትዮጵያን መንግሥት ለመጉዳት ይሞክራል፡፡ ከተቻለም ከሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በማበር የብሔር ብሔረሰብ ክፍተቶችንና የማንነት ጥያቄዎችን አጉልቶ በማውጣት ሕዝቡን ለማነሳሳት ገንዘብ ይረጫል፣ ያስተላልፋል፣ ኃይል ያደራጃል፡፡ ነገር ግን የኤርትራ መንግሥት በዚህ ዓይነቱ የተሳሳተ ሥልት ይወድቃል ወይም ይበታተናል ብሎ የሚያስበው የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁ ሊወድቅ የሚችል እንዳልሆነ የተገነዘበ አይመስልም፡፡ ስለሆነም አስተሳሰቡ ራሱ ከእውነታ የራቀና ግብዝ ስለሆነ ይህንን መሠረት አድርጎ የሚጠብቀው ውጤት አይሳካም፡፡ ሌላ የሚያዋጣውና ዘላቂነት ያለው አቋም ወይም ፖሊሲ ነድፎ ቢንቀሳቀስ ይበጀዋል እላለሁ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የ‹‹ሰላም የለሽ ጦርነት የለሽ!›› ሁኔታው ወይም ክስተቱ እስካሁን ድረስ ከላይ በተገለጸው መለኪያ ለኢኮኖሚው ልማት እንደጠቀመው የሚታወቅ ቢሆንም፣ ከአሁን በኃላ ግን ይህ ዓይነቱ መቋጫ የለሽ ሁኔታ እንዲለወጥ ሌላ መንገድ ወይም ሥልት መቀየስ ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚገምተው የኤርትራን መንግሥት በውስጥ ችግሩ ተገፋፍቶና ራሱን በራሱ ተጥመልምሎ ይወድቃል ብሎ የሚያስብ ከሆነም የተሳሳተ መንገድ ይመስለኛል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ከልምድ እንደታየው በመፈንቅለ መንግሥት ይሁን በሌላ መንገድ በቀላሉ የሚወድቅ አይመስልም፡፡ የመከላከያና የፀጥታውን ኃይል አንዱ ክፍል በመንግሥቱ ላይ ወይም በሌላው ክፍል ላይ ምንም ዓይነት ተቃውሞ እንዳያስነሳ ተደርጎ የተዋቀረ በመሆኑ፣ ተቃውሞ ቢነሳም በቀላሉ በሌሎች ክፍሎች ለመደፍጠጥ በሚቻልበት ሁኔታ የተደራጀ በመሆኑ የኤርትራ መንግሥት በዚህ ዓይነቱ ሥልት በቀላሉ እንደማይወድቅ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ወገኖች አቶ ኢሳያስ ቢወገዱ ሥርዓቱ ለውጥ ሊያደርግ እንደሚችልም የሚገምቱ አሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብም ስህተት ይመስለኛል፡፡ አቶ ኢሳያስ በሆነ ሁኔታ ከሥልጣን ቢርቁ ወይም ቢወገዱ ከመቅጽበት በኤርትራ ውስጥ ለውጥ ይመጣል ብሎ መገመት የዋህነት ብሎም ግብዝነት ነው፡፡ አቶ ኢሳያስ ቢገለሉ በርካታ ተተኪ ኢሳያሶች ይገኛሉ፡፡ በኤርትራ ለተፈጸመው ወይም ለደረሰው ጉዳት ወይም ክፍተት አቶ ኢሳያስ ብቻ ናቸው ተጠያቂ ብሎ መደምደም ስህተት ይመስለኛል፡፡ አቶ ኢሳያስ ቁንጮው ቢሆኑም ከሥር ተሠልፈውና ተደራጅተው ሥርዓቱን የሚያንቀሳቅሱ በርካታ ኢሳያሶች እንዳሉ እውነታውን አለመቀበል ስህተት ይመስለኛል፡፡ አቶ ኢሳያስን ሊተኩ የሚችሉ በርካታ ሰዎች እንዳሉና የሥርዓቱ መቀጠልም ከህልውናቸው ጋር በማያያዝ የሚንቀሳቀሱ በርካታ መሪዎችና ተከታዮች እንዳሉ አለመገንዘብ የዋህነት ይመስለኛል፡፡ ሰሜን ኮሪያ ለሦስት ትውልድ በአንድ ቤተሰብ እየተመራች እንደምትገኝና ከብዙ አቅጣጫ ተቃውሞ ቢበዛባትም፣ ሥርዓቱን ለመለወጥ በጣም አዳጋች ሆኖ እንደ ቀጠለ ማየቱ ራሱ ለኤርትራ ሁኔታም ትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡

የዓለም ኅብረተሰብ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለመለወጥ ወይም ለማስተካከል አለመቻሉን ስንመለከት ደግሞ ተጠያቂነቱ የሰሜን ኮሪያ ብቻ ሳይሆን፣ የዓለም ኅብረተሰብ ድክመት መሆኑንም ለማየት ቆም ብሎ ማሰላሰልን ሳይጠይቅ አይቀርም፡፡ አቶ ኢሳያስም ዋዘኛ ሰው ናቸው ብሎ መገመት የማይቻለው የአየር ኃይላቸውን ምክትል አዛዥነት ለልጃቸው እንዲሆን ማድረጋቸውን ስንሰማ ለምን እያዘጋጁት ይሆን? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ከሚገፋፋን በስተቀር ‹‹እርሳቸው በቅርብ ጊዜ ሥልጣናቸውን ይለቃሉ ወይም ቢገለሉ ሥርዓቱ ይለወጣል›› ከሚያስብል ድምዳሜ ላይ የሚያደርሰን አይሆንም፡፡ እንዲያውም እዚህ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ፈርጠም ያለ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ አቅም ስላለው ኃይል ተጠቅሞ የኤርትራ መንግሥትን ለምን አይጥለውም? የሚል ጥያቄም አላነሳም፡፡ ምክንያቱም የዚህ ዓይነቱ ሥልት በአሁኗ ዓለማችን በአንድ ሉዓላዊ መንግሥት ላይ ሊፈጸም የማይችል ድርጊት ስለሆነ የሚታሰብ አይደለም፡፡

ቀይ ባህርና ጂኦ ፖለቲካው

የቀይ ባህር አካባቢ ከፍተኛ የዓለም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚደረግበት፣ በርካታ መርከቦች በስዊዝ ካናልና በባብኤል መንደብ ሸርጦች የሚተላለፉበት፣ በርካታ አገሮች ትኩረት ሰጥተውት ፀጥታው የተረጋጋ እንዲሆን የሚጓጉለት፣ በርካታ የአካባቢው አገሮች በባህር መተላለፊያው ላይ ጉልህ የሆነ ተፅዕኖ ሊያደርጉበት የሚፈልጉት፣  አንዳንዶቹ አገሮች ደግሞ ይባስ ብሎም የአካባቢው ሁነኛ አዛዦች ለመሆን የሚፈልጉት ዓለም አቀፋዊ መተላለፊያ ነው፡፡ አንዳንዶቹ አገሮች ደግሞ በአካባቢው ላይ ተፅዕኖ ወይም ኃይላቸውን በማሳየት ሌሎች ተቀናቃኝ አገሮችን ሊጎዱቡት ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም የአካባቢው አገሮች በቀይ ባህር መተላለፊያ ላይ ምንም ሳንካ እንዲፈጠር አይፈልጉም፡፡ ሰላማዊ ሆኖ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተግባራትን ለማከናወን ይመኛሉ፡፡ ሆኖም በጥባጭ በተለይም አሸባሪዎች በበዙባት ዓለማችን እንደ ቀይ ባህር ዓይነቱ መተላለፊያ የጥቃት ወይም የአሸባሪዎች ዒላማ ለመሆን የተመቻቸ ሊሆን ስለሚችል፣ ጥቃቱን ለማስቀረት አገሮች በአካባቢው ላይ ትኩረት ማድረጋቸው የግድ ይላል፡፡

አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ጃፓን ወዘተ… በርቀት ከሚገኙ አገሮች መካከል በቀይ ባህር ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርገው ከሚንቀሳቀሱ አገሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከቅርብ አገሮች ደግሞ እነ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኢራን፣ ግብፅ፣ የተባበሩት የዓረብ ኢምሬትስ፣ ኳታር፣ እስራኤል፣ ቱርክ፣ ወዘተ… ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርጉበትና ፍላጎታቸውንና ኃይላቸውን የሚያሳዩበት አካባቢ ሆኗል፡፡ እንደ አሜሪካ፣ ቻይናና የአውሮፓ ኅብረት የመሳሰሉት አገሮች ከባህር ውንብድና (ፓይረሲ) ጋር በተያያዘ በጂቡቲ ወታደራዊ ካምፕ መሥርተው ከከተሙ ቆይቷል፡፡ አሜሪካ ብቻ በጦር አውሮፕላኖች፣ በድሮኖች፣ ወዘተ…የሚደገፍና ወደ 4.500 የሚጠጋ የወታደራዊ ኃይል በጂቡቲ ካሰፈረች ከራርማለች፡፡ ቻይናም በዚህችው ትንሽ የምሥራቅ አፍሪካ አገር ወታደራዊ ካምፕዋን ሠርታ ጨርሳለች፡፡ በአጠቃላይ ወደ 10,000 ወታደሮች የሚይዝ ካምፕ አቋቁማለች፡፡ ጃፓንም እንዲሁ ለአነስተኛ ኃይል የሚሆን ካምፕ አላት፡፡ ከ4,000 በላይ ወታደር የሚይዘው የፈረንሣይ ካምፕ ቋሚነቱ አገሪቱ ነፃ ከወጣችበት እ.ኤ.አ ከ1977 ጀምሮ የቀጠለ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ሳዑዲ ዓረቢያ የየመን ሁቲዎችን እወጋለሁ በሚል ሰበብ በጂቡቲ ወታደራዊ ካምፕ ለመመሥረት ውሏን ተፈራርማ ካምፑን ለማደራጀት እያሸበሸበች ትገኛለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተባበሩት የዓረብ ኤምሬትስ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በፈጸመችው ወታደራዊ ውል መሠረት በአሰብና በአካባቢው ለፈጣን ወታደራዊ አውሮፕላኖች፣ ሔሊኮፕተሮች፣ ወታደራዊ ጀልባዎች፣ ወዘተ.. የሚሆን ካምፕ በማቋቋም ላይ እንደምትገኝ ይነገራል፡፡ የግብፅ መንግሥት ደግሞ በምፅዋ አካባቢ የራሱን ወታደራዊ ካምፕ ለማቋቋም እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡

 ከላይ የተጠቀሰው ሁኔታና ወታደራዊ አሠላለፍ በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ ለወደፊቱ ምን ዓይነት ጂኦ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል? ሁለቱን አገሮች በመካከላቸውም ይሁን ከሌሎቹ ተዋናይ አገሮች ጋር ወደ በለጠ ፍጥጫ ሊያስገባቸው የሚችል ሁኔታ ሊከሰት ይችላል ወይ? ሁለቱም መንግሥታት አሁን ባላቸው ፍጥጫ ከቀጠሉ የአካባቢውን ወቅታዊ ፖሊቲካዊ አሠላለፍ አንዱ ሌላውን ለመጉዳት ሊጠቀሙበት ይችሉ ይሆን ወይ? ወዘተ… የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለጥያቄዎቹ መልስ መስጠት መሞከር ግምታዊ ከሚሆን በስተቀር በማስረጃ ላይ የተደገፈ አስተያየት ስለማይሆን ወደ ቀጣዩ ርዕስ በቀጥታ ማለፍና ከርዕሱ ጋር አያይዞ ስለመፍትሔ መንገዱ መሻት ግን ሊጠቅም ይችላል፡፡         

የዲፕሎማሲ ጥረት   

ዲፕሎማሲ ሲባል ሁለቱንም አገሮች የሚመለከት የዲፕሎማሲ መንገድን ለመግለጽ ነው፡፡ ሁለቱም አገሮች ከሌሎች መሰልና ግጭት ውስጥ ገብተው ችግራቸውን በዲፕሎማሲ ከፈቱ ወይም ለመፍታት ጥረት ካደረጉ መንግሥታት ጋር አያይዞ ማስቀመጡና ማነፃፀሩ ተገቢ ይሆናል፡፡ እስካሁን ድረስ እንደታየው ሁለቱም አገሮች ችግራቸውን ለመፍታት በዲፕሎማሲው መንገድ ተገቢ ጥረት አላደረጉም፡፡ ሁለቱም አገሮች በሚያለያያቸው ላይ ትኩረት ከማድረግና አንዱ ሌላውን ለመጉዳት ጥረት ከማድረግ በስተቀር ቆም ብለው ‹‹እስቲ ለዲፕሎማሲው መንገድ ወይም መፍትሔ አማራጩን እንፈልግለት›› ብለው ሲንቀሳቀሱ አልታዩም፡፡ ብዙውን ጊዜ እንዳየነው አንዱ አገር ሌላውን ለመጉዳት የሆነ ዕርምጃ ወይም እንቅስቃሴ ሲያደርግ፣ ሌላኛው አገር ደግሞ ‹‹በል እንግዲህ የኔ ምትና አፀፋ ደግሞ ምን እንደሚመስል ቅመሰው›› የሚል ዓይነት ግብረ መልስ ሲሰጣጡ እንጂ፣ በሠለጠነ መንገድ ወይም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ‹‹እኔ ይህንን አድርጊልሃለሁ፣ ከአንተ ደግሞ አዎንታዊ ግብረ መልስ እጠብቃለሁ፣ እኔ አንተን ለመርዳት ይህንን ዕርምጃ ወስጃለሁ፣ አንተ ደግሞ የእኔን ቀና አመለካከትና ዕርምጃ ከግምት ውስጥ አስገብተህ ምን ለማድረግ እንደምትፈልግ አያለሁ፣ ወዘተ…›› የሚመስል ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አልታዩም፡፡

 ካለፉት ዓመታት አካሄዳቸው እንደምንገነዘበው ሁለቱም አገሮች ለዲፕሎማሲው ሒደትና መፍትሔ ትኩረት አድርገው ሲንቀሳቀሱ አልታዩም፡፡ ከሁለቱም አገሮች ዕርምጃ የምናየው ነገር አንዱ በሌላኛው ላይ ምን ያህል ጎል እንዳስገባና ‹‹ጉድ አደረግኩት፣ ሠራሁለት! ወዘተ…›› የሚመስል እንቅስቃሴ ሲያሳዩ ነው የከረሙት፡፡ ይህ ድርጊት ደግሞ የሌሎች ጎረቤት አገሮች መሳቂያና መሳለቂያ ከመሆን በስተቀር ለአገሪቱ ሰላምና የወደፊት የጋራ ዕድገት የሚበጅ አይደለም፡፡ በዕርግጥ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራዊያን ስደተኞችን በመቀበልና በተለያየ ዘርፍ መንገድ በመርዳት ያደረገው አስተዋጽኦ ከላይ የጠቀስነው ጉዳይ ስለሆነ እዚህ ላይ መድገሙ ተገቢ አይሆንም፡፡ ነገር ግን በሁለቱም ኤምባሲዎች አካባቢ የጋራ ግንኙነትን በግልጽም በሚስጥርም በመፍጠር ለዲፕሎማሲው እንቅስቃሴ የሚበጁ ተግባራት ሲከናወኑ አልታዩም፡፡ የሁለቱም አገሮች ዳያስፖራን ዒላማ በማድረግ ለዲፕሎማሲው ግንኙነት ሊረዱ የሚችሉ ግልጽም ሚስጥራዊም እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ አልታዩም፡፡ ስደተኞችን ዒላማ በማድረግ ከአገር ቤት ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው ጋር ግንኙነቶችን በመፍጠር የዲፕሎማሲውን ምኅዳር ለመጠቀም የሚረዱ ተግባራት ሲከናወኑ አልታዩም፡፡ የሁለቱንም አገሮች ምሁራን (በተለይም ከውጭ የሚገኙትን) መሠረት በማድረግ በሁለቱም አገሮች የወደፊት ግንኙነት አስመልክቶ ምን ማድረግ እንደሚበጅ የሚያመላክቱ እንቅስቃሴዎች በስፋት ሲካሄዱ አልታዩም፣ ወዘተ…፡፡ በዚህ ሒደት የተወሰነ ዕርምጃ ቢኬድበት ኖሮ በርካታ ጠቃሚ ውጤቶች ወይም አዎንታዊና ጠቋሚ መንገዶች ይታዩ ነበር፡፡ ይህ ባለመደረጉ ሒደቱ የጠፋ ጊዜ ነበር ከማለት ውጪ በሌላ ሁኔታ መፈረጅ የሚቻል አይመስለኝም፡፡

በዚህ ርዕስ ላይ እየተነጋገርን የምንገኘው የዲፕሎማሲውን ምኅዳር ሁለቱም አገሮች ምን ያህል ተጠቅመውበታል? ምን ያህል ምኅዳሩን በመጠቀም ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት ተሞክሯል? ተነሳሽነቱን በመውሰድ የዲፕሎማሲውን ምኅዳር በጥንቃቄና በብልጠት ለመጠቀም ዋናውን ሚና መጫወት የነበረበት የትኛው አገር ነው? አንዱ አገር ተነሳሽነቱን ሲወስድ ሌላኛው አገርስ ምን ማድረግ ይጠበቅበት ነበር? ወዘተ… የመሳሰሉ ጉዳዮችን አንስተን ለመወያየት የሚረዳ ይመስለኛል፡፡ በመሠረቱ ኤርትራ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ መቆየቷ አሌ የማይባልና የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ኤርትራ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉት አገሮች ከጂቡቲ ቀጥላ ትንሽዋ አገር ናት፡፡ የሕዝቧ ብዛትም ቢሆን ከአምስት ወይም ስድስት ሚሊዮን የሚበልጥ አይደለም፡፡ ነገር ግን የኤርትራ መንግሥት ከእግሩ መጠን በላይ ጫማ ለማድረግ እንደሚሞክርም ይታወቃል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ኢትዮጵያ በአካባቢው ትልቅ አገር ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና በዓለም ውስጥ ከኒው ዮርክና ከብራሰልስ ቀጥሎ ከፍተኛ የዲፕሎማቲክ ጽሕፈት ቤቶች ያሏት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿን አገሮች ማለትም የኬንያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የኤርትራና የጂቡቲ ሕዝብ በአጠቃላይ ተደምሮ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በቁጥሩ ያንሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ወደ 100 ሚሊዮን አካባቢ ደርሷል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህም የሚያሳየው ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር በተለያዩ ንፅፅሮች ማወዳደሩ ተገቢ አይሆንም ለማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሁለቱም አገሮች በተለያዩ ዘዴዎች ማለትም በፖለቲካው፣ በዲፕሎማሲው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊው፣ በወታደራዊና በኢንተሊጀንሳዊ ተግባራት ሲጠቃቁ ከርመዋል፡፡ በእርግጥ አንዱ በሌላኛው ላይ የበለጠ ጉዳት አድርሶበታል በማለት ዝርዝሮችን ማቅረብ ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለአሁኑ ጉዳያችን የሚጠቅም አይደለም፡፡ ጉዳት መድረሱን ብቻ መጥቀሱ በቂ ነው፡፡ ይህ ጉዳት እንዲቀርና ሁለቱም አገሮች ወደ መደበኛው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ገብተው ሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈጥሩ ምን መደረግ አለበት? ወደሚለው ማተኮሩ ነው ሊበጅ የሚችለው፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ኤርትራ ትንሽ አገር በመሆኗና ኢትዮጵያ ደግሞ በተነፃፃሪ ትልቅ አገር በመሆኗ በሁለቱም አገሮች መካከል በሚካሄድ መጠቃቃት፣ በሌሎች ታዛቢ ወይም ተመልካች አገሮች ዘንድ የሚታዘንላት አገር ማን ትሆናለች? ተብሎ ቢጠየቅ ኢትዮጵያ ናት የሚል መልስ ከየትም አቅጣጫ ማግኘት እንደሚከብድ የታወቀ ነው፡፡ ለምን ቢባል ኤርትራ አሁንም ትንሽ አገር በመሆኗ ከፍተኛ ጥፋት የተፈጸመው በእርሷ መሆኑ ከበድ ያለ ማስረጃ ይቅረብ ብለን ብንገምትም፣ ኤርትራ ናት አጥቂዋ ብሎ የሚቀበል አገር ብዙም አይኖርም፡፡ ‹‹እንዴት ትንሽ አገር ትልቅ አገርን ለመጉዳት ትችላለች?›› የሚል ጥያቄ በማንሳት ነው ኢትዮጵያን አጥቂ አድርጎ ለማስቀመጥ የሚሞከረው፡፡ ለምሳሌ በአውሮፓ በተለይም የስካንዴነቪያን አገሮችና የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች በሙሉ (ከጥቂቶቹ በስተቀር)፣ እነ ጣሊያን፣ ስሎቬንያ፣ ክሮኤሽያ፣ ሞንቴኔግሮ፣ መቄዶ፣ ወዘተ… የመሳሰሉት አገሮች የኤርትራ ነባር ደጋፊዎች ሆነው የኖሩና አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያን አጥቂ አድርገው ከመፈረጅ የማይመለሱ አገሮች ናቸው፡፡ ለምን ቢባል ይህ ሁኔታ በተለይም የስካንዴነቪያን አገሮችን ብንወስድ ከትጥቅ ትግሉ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የዘለቀ፣ አንዳንዶቹም ትንንሽ አገሮች በመሆናቸው ኤርትራን አጥቂ አድርገው ለመውሰድ የሚቸገሩ ናቸው፡፡ በዓረቡ ዓለምና በሌሎችም አኅጉሮች የሚገኙ ትንንሽ አገሮችም ቢሆኑ ከላይ ከተጠቀሰው አቋም የተለየ አቋም ለመያዝ ይከብዳቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ ኤርትራ የዓረብ ሊግ ታዛቢ አባል አገር መሆኗንም መዘንጋት የለበትም፡፡ ለማንኛውም እዚህ ላይ ደጋፊና ተቃዋሚ አገር በመፈረጅ ለጉዳዩ ውጤታማነት ተገቢነት ይኖረዋል ለማለት ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር በመሆኗ ‹‹በኤርትራ ተጠቃች›› የሚለውን አባባል ለምን ተቀባይነት ሊያጣ እንደሚችል ለመጠቋቆም ብቻ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ስለመሆኗና በዓለም መድረክ ተሰሚነቷ እየተጠናከረ በመምጣቱ ምክንያት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት ከ190 ተሳታፊ አገሮች የ185 ድጋፍ አግኝታ እ.ኤ.አ ከጀንዋሪ 1 ቀን 2017 ጀምሮ ወንበሯን ለመያዝ ችላለች፡፡ ድጋፍ የነፈጉዋት አምሥቱ አገሮች ኤርትራ፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኳታርና ሰኔጋል ብቻ ነበሩ፡፡ እያንዳንዱ አገር የየራሱ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከኤርትራ ጋር በትንሹም በትልቁም ጉዳይ እንካ ስላንቲያ እየገባች ለመቀጠል መሞከር ያለባት አይመስለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር እየተነታረከች መኖሯ አይምርላትም፣ አይበጃትምም፡፡ ለኢትዮጵያም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ ከኃያላኑ አገሮችና ከመሰል አባል አገሮች ጋር በቀላሉ የሚያገናኛት ፣ መድረኩን ከኤርትራ ጋር ላላት የሻከረ ግንኙነት ለመለወጥ የምትጠቀምበት መሆን ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡ ስለሆነም ለዲፕሎማቲክ ግንኙነቱ ተነሳሽነቱን ወስዳ መንቀሳቀስ የሚኖርባት አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡

አንዱና በቅድሚያ ኢትዮጵያ ልትገነዘበው የሚገባው ጉዳይ የኤርትራ መንግሥት በአንድ ወቅት በራሱ መንገድ ይወድቃል ብላ ከመጠበቅ ይልቅ፣ አሁን በሥልጣን ላይ ካለው የኤርትራ መንግሥት ጋር በጉርብትና በሰላም ለመኖር የዲፕሎማሲ ጥረቷን መቀጠል ያለባት ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ጀምራ ኤርትራ ወደ ክፍለ አኅጉሩ ድርጅት እንድትመለስ የራሷንና የአባላቱን ተሳትፎ ተጠቅማ እንቅስቃሴ ብታደርግ፣ በኤርትራ መንግሥት ዘንድ ጥሩ የዲፕሎማቲክ ዕይታ (ዲፕሎማቲክ ጀስቸር) ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህንን ዕርምጃ መውሰድ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያሳይ እንጂ የኢትዮጵያን ክብርና ሞገስ የሚቀንስ አይሆንም፡፡ ይህ በበይነ መንግሥታቱ ደረጃ የሚወሰድ ዕርምጃ የኤርትራ መንግሥትን ባህርይ ሊለውጥ የሚችል፣ ብሎም ደረጃ በደረጃ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘንድ የተጣለበትን ማዕቀብ ለማንሳት ስለሚረዳው ጠቃሚነቱና ለወደፊቱ ሊከፈት የሚችለውን የጋራ ግንኙነት ወይም በሦስተኛ ወገኖች እገዛ ሊመጣ የሚችልን የዲፕሎማቲክ ግንኙነትን እያጠናከረ ሊሄድ ይችላል፡፡ ተነሳሽነቱ ግን አሁንም በኢትዮጵያ መንግሥት መወሰድ ይኖርበታል እላለሁ፡፡

ኢትዮጵያ አሁንም ሌላ ተጨማሪ አዎንታዊ የዲፕሎማቲክ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁ መሆንዋንና ይህም የሚወሰነው የኤርትራ መንግሥት በሚወስደው ዕርምጃና በሚያሳየው አዎንታዊ ግብረ መልስ እየተመዘነ እንደሚሆን በይፋ መግለጽ መቻል ይኖርበታል እላለሁ፡፡ ለምሳሌ የኤርትራ መንግሥትን ለማጥቃት ፍላጎት ወይም ዕቅድ እንደሌላት፣ ይልቁንም አዎንታዊ ግንኙነቱ እየተሻሻለ የሚሄድ ከሆነ ‹‹ኢትዮጵያ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የኤርትራ ወደቦችን ለመጠቀም እንደምትፈልግ፣ የሕዝብ ለሕዝብና የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነቱን ለማሻሻል እንደምትፈልግ፣ ኢትዮጵያ ለኤርትራ መንግሥትም ቢሆን የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ እንደምትፈልግ ወዘተ…›› የመሳሰሉ ዕቅዶችን በይፋ መግለጽ ትችላለች፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መግለጫ የኤርትራ መንግሥት ከአንዴም ሁለቴ ሊያስብበትና አዎንታዊ መልስ ሊሰጥበት ይችላል፡፡

በኤርትራ መንግሥት በኩል ደግሞ በተግባር ላይ ሊውል የማይችለውን ‹‹የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ አሁኑኑ ይተግበርልኝ›› የሚለውን ጥያቄ ለጊዜው ቢተወውና ከላይ በጠቀስኩዋቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር ግንኙነቱን ለማሻሻል ቢንቀሳቀስ ይጠቅማል እላለሁ፡፡ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ በቀጣዩ ጊዜ ሊታይ ይችላል፡፡ አሁን ግን የድንበር ኮሚሽኑ ጉዳይ ለአጠቃላይ ግንኙነቱ ደንቃራ ሆኖ እንዲቀጥል የኤርትራ መንግሥት መፍቀድ ያለበት አይመስለኝም፡፡ ውድ አንባቢያን ይህ ከላይ ያቀረብኩትን አስተያየት ለመጻፍ የተገደድኩት በጉዳዩ ላይ በርካታ ጸሐፊዎች ከዚህ የተሻለ ሐሳብ ሊኖራቸው እንደሚችልም በመገመት ነው፡፡ ሆኖም ይህ ጽሑፍ እንደ አንድ መነጋገሪያ ጉዳይ ሊወሰድ ከቻለ በቂ ነው፡፡ ጉዳዩ ይመለከተናል የምንል ወገኖች በርዕሱ አጥብቀንና በዝርዝር ልንነጋገርበት ይገባል ባይ ነኝ፡፡ የሁለቱም አገሮች ፍጥጫና ቅራኔ ለቀጣዩ ትውልድ መተላለፍ ያለበት አይመስልኝም፡፡ ችግሩን የፈጠረው ይህ ትውልድ ስለሆነ መፍትሔውንም ማምጣት ያለበት ይህ ትውልድ ነው፡፡ ቀጣዩ ትውልድ ይህ ትውልድ ለፈጠረው ችግር ወራሽ የመሆን ግዴታ የለበትም፡፡  አመሰግናለሁ!

ከአዘጋጁ፡ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

Standard (Image)

ሕገወጥ ስደትና የወቅቱ ሥጋት

$
0
0

 

በዳዊት ከበደ አርዓያ

በዓለም ላይ 15.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ስደተኞች እንዳሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያሳያል፡፡ የሰው ልጆች (ዜጎች) የትውልድ አገርን ጥሎ መሰደድ የነበረ ክስተት ቢሆንም፣ አሁን ባለንበት ዘመን ግን የተለያዩ አገሮች ዜጎች የሚያልቁበት መቅሰፍት እየሆነ ነው፡፡ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት የሚፈጸምበት የሰው ልጅ ከጦርነትና ድርቅ ባልተናነሰ የሚያልቅበት የዘመናችን አሳዛኝ ክስተት ሆኗል፡፡ ያልበለፀጉ አገሮች አምራችና አገር ተረካቢ ዜጎቻቸውን የሚያጡበት ብቻ ሳይሆን፣ የበለፀጉ አገሮችም ከአቅማቸው በላይ የተጋረጠባቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትኩሳት በመሆኑ ነው፡፡ በተለይም የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ይህን አደገኛና የዜጎቻቸውን ህልውና የሚፈታተን ሕገወጥ ተግባር እንደ ዋነኛና ፈጣን ምላሽ የሚጠይቅ አጀንዳቸው አድርገው እየተንቀሳቀሱ ያሉት፡፡

በቅርቡም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ እንደ ዋነኛ መወዳደሪያ አጀንዳቸው አድርገው ነው የተንቀሳቀሱት፡፡ ትራምፕ አይደለም በሕገወጥ መንገድ በሕጋዊ መንገድም አገራቸው አሜሪካ ስደተኞችን የምታስተናግደበት ዕድል እንደሌለ አሳውቀዋል፡፡ ቃለ መሐላ ፈጽመው ሥራ ከጀመሩበት ቀን ጀምሮም በሕጋዊ መንገድ ቪዛ አግኝተው ለመጓዝ የተዘጋጁ የተለያዩ አገሮች ስደተኞች ጉዟቸው እንዲቋረጥ ሲደረግ፣ ቀድመው ወደ አሜሪካ የተጓዙትም ከውሮፕላን ማረፊያዎች እንዳይወጡ ተደርገዋል፡፡ የስደተኞች ጉዳይ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮችን አንድነት አደጋ ላይ የጣለ አደገኛ ክስተት መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ በተለይም የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል ጀርመን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች እንድትቀበል መፍቀዳቸው ‹‹የመቅሰፍት ያህል ስህተት ሠርታለች፤›› ሲሉ ኮንነዋል፡፡

በእርግጥም በአሁኑ ጊዜ የአውሮፓም ሆነ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ራስ ምታትና ቅድሚያ የሚሰጠው የመንግሥታት አጀንዳ እየሆነ መምጣቱ እየተገለጸ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሕገወጥ ደላሎችና የሰው ንግድ አዘዋዋሪዎች መናኸሪያ የሆነችው ሊቢያም ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫቸው አድርገዋታል፡፡ በተለይም በሕገወጥ ስደተኞች ላይ በዚያች አገር የሚፈጸመው እጅግ በጣም ዘግናኝና ኢሰብዓዊ ተግባር በጊዜው ካልተቀጨ፣ ዓለም ከዚህ በፊት ያላየችው የሰው ልጅ የመቅሰፍት ምድር መሆንዋ እንደማይቀር የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

በቅርቡ የስደተኞች ሁኔታ የሚከታተል (North Africa Migration Hub) የተባለ የጥናት ተቋም ሊቢያን መነሻ አድርገው በሕገወጥ መንገድ ጣሊያን የገቡ 341 ስደተኞችን በማነጋገር ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚለው ከሆነ፣ 85 በመቶ በሕገወጥ የስደት ጉዞ ያዩት የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በየእስር ቤቱ ለወራት ያለምግብና ውኃ መታጎርና መሞት፣ የሴት ልጆች በግላጭ በአደባባይ መደፈር፣ የኩላሊት ንግድ፣ እንዲሁም በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ አልፈው አውሮፓ ከደረሱ በኋላ ያጋጠማቸው አሳዛኝ ሕይወትን በተመለከተ ምንም ዓይነት ዕውቀትና ግንዛቤ ሳይኖራቸው ነው ለስደት የተነሱት ብሏል፡፡

 እነዚህ ሕገወጥ ስደተኞች በስደት ጉዞው ውስጥ ያሳለፉት አስፈሪና ዘግናኝ ችግርና አደጋም ሆነ አውሮፓ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ኑሮን በተመለከተ ቀደም ሲል ቢያውቁት ኖሮ ስደትን እንደማይመርጡ ተናግረዋል፡፡ በተለይም ከምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ የሚመጡ ሴቶች ስለስደት ጉዞው ፈተናና አደገኛነት ያላቸው ዕውቀት በጣም አነስተኛ መሆኑን፣ አብዘኛዎቹም በሕገወጥ ደላሎች የተደፈሩ፣ ከዚህም በተጨማሪ አዘዋዋሪዎቹ ስደተኞቹን አሳፍረው ለሚጓዙ አሽርካሪዎች (ሾፌሮች) ሴቶችን እንደ ተጨማሪ ክፍያ ለፆታ ጥቃት አሳልፈው እንደሚሰጡዋቸው ጥናቱ አረጋግጧል፡፡

በቅርቡም በአንድ ማንነቱ ያልታወቀ ጽንፈኛ ቡድን ብዛት ያላቸው የምዕራብና የምሥራቅ አፍሪካ ስደተኞች በሊቢያ በረሃ በጭካኔ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን፣ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ማኅበራዊ ድረ ገጾች በምሥል አስደግፈው አሰራጭተውታል፡፡

በዚህ በሰሃራ በረሃና በሜዲትራንያን ባህር የሚደረግ የስደት ጉዞ በጣም አስፈሪና አደገኛ ቢሆንም ግን፣ አሁንም ብዛት ያላቸው ስደተኞች ከሞት ጋር እየተፋጠጡ ወደ አዉሮፓ መጉረፍን አላቆሙም፡፡ ለዚህም ነው የችግሩ ገፋት ቀማሽ የሆነችው ጣሊያን በሊቢያ ትሪፖሊ ዘግታው የቆየችው ኤምባሲዋን በመክፈት ዋና ሥራውም  በሕገወጥ ደላሎች የሚደረገውን የሰው ንግድ መቆጣጠርና ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማስተባበር እንደሚሆን፣ የአገሪቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ደኅንነት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም የሊቢያን ባህር ኃይል ማሠልጠንና ማጠናከር እንዲሁም በአገራቱ የባህር ክልል ወታደራዊ ቅኝት በማድረግ ሕገወጥ ስደተኞች በባህር ጉዞ ላይ እያሉ ወደ መጡበት የሚያስችል ሰምምነት ከሊቢያው የአንድነት መንግሥት ጋር ተፈራርማለች፡፡

የአውሮፓ መንግሥታት በሕገወጥ ስደት ምን ያህል እንደተማረሩና ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደገቡ በየቀኑ እየተነገረ ነው፡፡ በቅርብ በማልታ የተሰበሰቡት የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች የአገር ውስጥ ጉዳይ ደኅንነት ሚኒስትሮች፣ ከአውሮፓ ውጪ በሰሜን አፍሪካ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በማቋቋም  በጉዞ ላይ ያሉትን ብቻ ሳይሆን አውሮፓ ውስጥ ገብተው የጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸውን ሕገወጥ ስደተኞች ለማስወጣት ውሳኔ ላይ ደርሰዋል፡፡

ይኼም የሚያሳየው የአውሮፓ አገሮች ሕገወጥ ስደተኞችን በራሳቸው ግዛት ውስጥ በካምፕ (Refugee Camp) ለዓመታት ማቆየት መፍትሔ እንዳልሆናቸው ነው፡፡ አሁን በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ጥገኝነት ጠይቀው በመጠለያ የሚገኙ የተለያዩ አገሮች ሕገወጥ ስደተኞችን አስወጥተው፣ በሊቢያና በቱኒዚያ በሚያቋቋሙት አዲስ መጠለያ ለማስፈርም ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በቀጣይም ወደ መጡበት አገር ለመመለስና ለማቋቋም የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ በአውሮፓ ኅብረት እንዲሸፈን ወስነዋል፡፡ በተጨማሪም ሕገወጥ ደላሎችንና አዘዋዋሪዎችን ለመግታት እንዲቻል የሊቢያን ባህር ኃይል ለማሠልጠንና ለማጠናከር የ200 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግ ወስነዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እንደሚለው ከሆነ በአሁኑ ጊዜ በሕገወጥ መንገድ ወደ በለፀጉት አገሮች የሚደረግ ስደት ገንዘብና ራስን የሕገወጥ ደላሎች ሲሳይ ከማድረግ ዉጪ እርባና የለውም፡፡ የአውሮፓ አገሮች ሊታገሱት ከሚችሉት በላይ ስለሆናቸው፣ ማንኛውም የሕገወጥ ስደት የጥገኝነት ጥያቄ ላለመቀበል ብቻም ሳይሆን ያን ሁሉ መከራና ችግር አልፈው የገቡትንም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለማስወጣትና ለመመለስ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡

ዛሬ ሰዎች በፍላጎት ወይም በሕገወጥ መንገድ ተታለው ሳይፈልጉ እንደሚሰደዱ የሚገልጹት በርካታ ድርጅቶች፣ የመሰደዳቸው ምክንያትና ከተሰደዱ በኋላ የሚያጋጥማቸው ያልተጠበቁት ሁኔታ ለአዕምሮ ሕመም ይዳርጋቸዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አውሮፓ ውስጥ ከገቡት ስደተኞች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ድብርት (Dipression) ውስጥ የሚገቡ ሲሆን፣ በተለይም በመጀመርያ ወደ ስደት የተጓዘ ግለሰብ በሄደበት አገር ባሰበው መንገድ መኖር ባለመቻሉና ወደፊት ኃላፊነት ወስዶ የሚያመጣቸው የቤተሰብ አካላት ሕይወትን አስመልክቶ በሚገጥመው መጨናነቅ የአዕምሮ ሕመም ችግር እንደሚፈጠርበት ነው፡፡ ብዙዎቹም የዚህ ችግር ተጠቂ ናቸው፡፡ በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ የዓረብ አገሮች በሕጋዊም ሆነ በሕገወጥ መንገድ ከሚጓዙት 23 በመቶ የሚሆኑት በአሠሪዎቻቸው ይደበደባሉ፡፡ 20 በመቶ የፆታ ጥቃት ስለሚገጥማቸው የአዕምሮ ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

ከስደት ጋር ተያይዞ የአዕምሮ ጤናን ሊያውኩ የሚችሉ ተብለው ከተቀመጡት መካከል አንድ ሰው ስደትን ሲያስብ እንዴት ልጓዝ? ከደረስኩ በኋላ ማረፊያየስ የት ነው? ምንስ እሠራለሁ? እንዲሁም ሊያጋጥመኝ የሚችል ችግር ምን ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች ቀድሞ ከመሰደዱ በፊት በአዕምሮው የሚያሳድረው ፍርኃት አንዱና ዋና መነሻ ነው፡፡

ስለአካባቢው ባህል፣ እምነትና የአኗኗር ዘይቤ ከማወቅ ጋር ተዳምሮ ሊያግባባ የሚችል ቋንቋ ያለመኖር፣ ሲጓዙ ታስቦ የነበረ ጥቅማ ጥቅምና ለውጥ ባሰቡት ልክ ያለማግኘትና በመሳሰሉት ስደተኛው ጭንቀቱ ተባብሶ ለከፍተኛ የአዕምሮ ሕመም ይዳረጋል፡፡ በተለይም ከምሥራቅ አፍሪካ  ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራና ከሶማሊያ የሚሰደዱ ሴቶች ዕውቀትን መሠረት ያላደረገ ስደት በማከናወናቸው በሚገጥማቸው ፆታዊ ጥቃት የጉልበት ብዝበዛና ድብደባ፣ በተለይ ተበድረው ከሄዱ ከገቡበት ዕዳ አንፃር፣ እንዲሁም ለቤተሰብ ሊያደርጉት ከሚያስቡትና በአጠቃላይ ሳይሳካላቸው ሲቀር በአዕምሮአቸው ላይ ከፍተኛ ጫናን ያሳድራል፡፡ ባልተገባ ሥራ በሕገወጥ ሥራ ውስጥም ይገባሉ፡፡ ያልቻሉት ደግሞ ወደ አገራቸው ሲመለሱ በቤተሰብ ሊገጥማቸው የሚችለውን ችግር በማሰብ ለአዕምሮ መታወክ እንደሚዳረጉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በተለይም ኢትዮጵያና ኤርትራን በመሳሰሉ አገሮች ያለው የቤተሰብ ትስስር፣ የማኅበረሰብ ቁርኝትና ማኅበራዊ መስተጋብሩ ከውጭው ጋር ፍፁም የተለየ መሆኑ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ጓደኛ፣ ቤተሰብ፣ ጎረቤት ዘመድም ሆነ ማኅበራዊ ጉዳይ በጋራ ለመምራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ያለመኖር ለብቸኝነትና በራስ የመተማመን መንፈስን ከማሳጣቱም በተጨማሪ፣ የአዕምሮ ሕመም ሊያስከትሉ የሚችሉ ሱሶች ውስጥ እንዲዘፈቁ እያደረጋቸው ነው፡፡ ‹‹አገሬ እያለሁ የገንዘብ እጥረት ነበረብኝ፡፡ እዚህ ግን አሁን በራስ የመተማመን ሰብዕናዬን አጥቻለሁ፡፡ ከእንግዲህም ተመልሼ ሙሉ ሰው የምሆን አይመስለኝም፤›› ብሏል አንድ በጀርመን የመጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ፡፡

‹‹በጉዞዬ ወቅት ስቃይ፣ ድብደባና ችግር እንዲሁም እምቦቀቅላ ሕፃናት ወደ ባህር ሲወረውሩ ያየሁት እስካሁን ድረስ የአዕምሮ እረፍት ነስቶኛል፡፡ እዚህ እንደደረስኩ ያገኘሁትና የጠበቅኩት ለማመን የሚያስቸግር ነው፡፡ የአዕምሮና የልብ ስብራቴን የሚጠግን አንዳችም ነገር አላገኘሁም፤›› ብሏል አንድ በጀርመን የመጠለያ ካምፕ የሚገኝ ኤርትራዊ ወጣት፡፡

ዜጎች በመረጃ ባልተደገፈ መንገድ መጓዝ ሊያመጣ የሚችለውን ከፍተኛ ችግር ተረድተው ሕጋዊ አግባብን እንዲጠቀሙ፣ በአገራቸው ውስጥ ሠርተው መለወጥ የሚችሉበትን  አግባብና ዕድል ለማመቻቸት ማስረዳት፣ በተለይ ያን ሁሉ የበረሃ ስቃይና መከራ ለማለፍ የሚያሳዩት ድፍረትና ቁርጠኝነት በአገራቸው ሠርተው ለመለወጥ ቢያውሉትና ቢተገብሩት ራሳቸውን ጠቅመው አገራቸውን የሚያኮሩ እንደሚሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ከአስፈሪው በረሃና የባህር ማዕበል ጋር ግብግብ እንደሚገጥሙ ሁሉ ኑሮን ለማሸነፍና ለመለወጥ ቁርጠኝነቱና ድፍረቱ ለምን እንደሚያጡ አንዳንዴ ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው፡፡

እዚህ ላይ በሕገወጥ ደላሎች ላይ የሚደረገው ሕጋዊ ዕርምጃ እንዳለ ሆኖ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በተለይም የመገናኛ ብዙኃን በሕገወጥ የስደት ጉዞ ያለው ችግርና አደገኛ የሕይወት ውጣ ውረድ፣ የሚያስከትለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ ስደተኞች እንደ ተስፋይቱ ምድር በናፍቆት የሚጓዙባቸው አገሮች ያለውን እውነታና የመንግሥታቱ ፖሊሲ በማስገንዘብና በማሳወቅ ረገድ የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ በሕገወጥ ስደትም ሆነ ሕጋዊ  ሆኖ ቢጓዙም ያቀዱትን መሆን ባለመቻል የሚገጥሙ ችግሮች ከስደተኛው በተጨማሪ የቤተሰብ መበታተን፣ የተጧሪዎች ቁጥር መጨመር፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑ ልጆች መብዛት፣ የሞት መበራከት፣ የአምራች ኃይል እጥረት፣ የግጭት መብዛት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት፣ ከዚህም በተጨማሪ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ መሆንን እንደሚያመጣ ሁሉም ልብ ሊለው የሚገባ የጋራ ጉዳይ መሆኑን ትኩረት በመስጠት ችግሩን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው kebededawit2016@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

የነገ ሕይወታችንን በዛሬ መስታወት

$
0
0

 

ኢሕአዴግ መራሹ የኢትዮዽያ መንግሥት ሰሞኑን “ብቁና ውጤታማ ፐብሊክ ሰርቪ ለአገራዊ ህዳሴ” በሚል ርዕስ ለአገራዊ ፐብሊክ ሰርቪሱ ጥልቅ ተሃድሶ ያገለግል ዘንድ ባዘጋጀው ባለ ሰላሳ አምስት ገጽ የመወያያ ጽሑፍ ላይ እንደተገለጸው፣ አገራችን በለውጥ ውስጥ እንደምትገኝና ይኼ ለውጥም በከተሞች ብቻ የማይታጠር ይልቁንም ደግሞ በገጠር የጀመረና አርሶ አደሩን መነሻ ያደረገ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ጽሑፉ አገራችን ለበርካታ ምዕተ ዓመታት ከተጓዘችበት የማሽቆልቆል ጉዞ መግታት የተጀመረው ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት ወዲህ እንደሆነ ያብራራል፡፡ በዚህ የማሽቆልቆል ጉዞ ዋነኛ ሰለባ የነበረው ደግሞ የገጠሩ ማኅበረሰብ በተለይም አርሶ አደሩ እንደነበር ያትታል፡፡

በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲነገር እንደምንሰማው አገራችን ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት እንቅልፍ ላይ እንደነበረች ነው (ጉዳዩ አከራካሪ ቢሆንም ቅሉ)፡፡

ታላቁ የዓለም የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር አርኖርድ ቶይንቢም በአንድ ወቅት እንደጻፉት፣ አንድ ሰው አዲስ አበባ ውስጥ ሆኖ የአሥራ አምስት ዓመት እንቅልፍ ቢወስደውና ቢነቃ ያለበትን ሥፍራ በምንም ዓይነት ሊረሳ አይችልም፡፡ ሀቀኛይቱንና ያችው እንደተፈጠረች ያለች ኢትዮዽያን ሳትለወጥ ያገኛታል ብለው አስፍረዋል፡፡

ይኼ ሐሳብ ከላይ ያነሳሁትን ጉዳይ የበለጠ ያብራራዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኛ ኢትዮዽያዊያን ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት እንቅልፍ ላይ ነበርን ወይስ አልነበርንም? የሚለውን ጥያቄ ሊመልስልን የሚችል አባሪ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ የውጭ የታሪክ ባለሙያዎች ሳይቀሩ የአገራችንን የረዥም ጊዜ በእንቅልፍ ማሳለፍና ኋላቀርነት ሲዘግቡና በታሪክ ማኅደራቸው ከትበው ሲያስቀምጡ እንደነበር እንረዳለን፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ አንድ የሚነገር ተረት ነበር፡፡ ክርስቶስና መላዕክት የመካከለኛው ምሥራቅ አውሮፓን ሲጎበኙ ቆይተው ኢትዮጵያ ሲደርሱ፣ “ይች ከሁለት ሺሕ በፊት የነበረችዋ አገር ነች” ብለው እንደተረቱ ይነገራል፡፡ እንግዲህ በአገራችን የተተረተው እስከዚህ ድረስ ነው፡፡ በድሮ ጊዜ ምን ያህል በልማትና በዴሞክራሲ እንዳላደግንና ኋላ ቀር እንደነበርን ያመለክታል፡፡ አንድ ሰው ለብዙ ዓመታት ከአገሩ ቢወጣና ተመልሶ ቢመጣ የሚያገኛት ያችን ድሮ የሚያውቃትን አገር እንደሆነ ለማስረዳት የተተረተ ነው፡፡ የተማረ ዜጋ ባለመኖሩ፣ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ መዳበር የሀቀኛ መሪ ወደ ፖለቲካው መድረክ አለመምጣት፣ በየአካባቢው የነበሩ የብሔር ግጭቶችና ለበላይነት ይደረጉ የነበሩ ትግሎች፣ . . . ወዘተ ደግሞ አገሪቷን ለዘመናት በእንቅልፍ ውስጥ እንድታሳልፍ ምክንያቶች እንደሆኑ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ዲላኖ ሩዝቬልት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዋዜማ የተረከቧት አሜሪካ በኢኮኖሚ መመሰቃቀል፣ በሥራ አጥነት፣ በኑሮ ውድነትና በሌሎች ችግሮች የተተበተበች ነበረች፡፡ ከዚያ ሁሉ ችግር አሜሪካን አውጥቶ፣ ከጀርመን ናዚዝምና ከጃፓን ሚሊታሪስት አምባገነን መንግሥታት ጋር ተዋግቶና ድል አድርጎ፣ አውሮፓን አቋቁሞ (በማርሻል ፕላን አማካይነት) ዛሬ ዓለምን የምትመራ አገር ለመመሥረት መሠረት ጥለው አልፈዋል፡፡

 በ1930ዎቹ አጋማሽ የነበረው የአሜሪካ ውጥረት እጅግ አሳሳቢና ለትንሳዔዋ ትልቅ አመራርን የሚጠይቅ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ነበር ሩዝቬልት፣ “ነገ ለመኖር ዛሬ መንቀሳቀስ አለብን፡፡ የተረሳችውንና በእንቅልፍ ውስጥ ረጅም ጊዜ ያሳለፈችውን  አሜሪካ ማስታወስ ይገባናል፤” የሚል የፖለቲካ መርህ ይዘው የተነሱት፡፡ ይኼ የፖለቲካ መርህ ለዛሬው አሜሪካውያን ዕድገትንና ዴሞክራሲን ይዞ መጣ፡፡ የዛሬዎቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶችም ይኼንን የዕድገትና የዴሞክራሲ ሌጋሲ በማስቀጠልና የበለጠ የተሳለጠ በማድረግ የዛሬ ልዕለ ኃያሏን አገር አሜሪካ መገንባት ችለዋል፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት ደግሞ በተቃራኒው ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት የተረከብኳት አገር ለብዙ ዓመታት በእንቅልፍ ውስጥ እንዲያውም በማሽቆልቆል ሒደት ላይ የነበረች ናት ሲል ይሞግታል፡፡ ይኼን የማሽቆልቆል ጉዞ ለመግታት ደግሞ  የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የነበሩት ፍራንክሊን ዲላኖ ሩዝቬልት እንደወሰዱት ዓይነት ዕርምጃ ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመት ጀምሮ በመውሰድ፣ አገሪቷን ከዚህ ቀውስ መታደግ እንደተቻለ ያብራራል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ አዲስ የመንግሥት ሥርዓት በመዘርጋትና  ሕገ መንግሥት በማርቀቅ በአገሪቷ ላይ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን በመግለጽ፡፡

የስኬታማ ልማታዊ መንግሥት መሠረታዊ የብቃት ምንጮችን በመተግበር ማለትም ለኅብረተሰብ ልማት የቆረጠና የሕዝብ አገልጋይ የሆነ ፖለቲካዊ አመራር በመጎናፀፍ፣ በመንግሥት ራዕይና ተልዕኮ እንዲሁም መመርያዎች ላይ የተሟላ ግልጽነት፣ አመኔታና የመፈጸም ተነሳሽነት ያለው ፐብሊክ ሰርቪስ በመገንባትና ልማታዊ ተነሳሽነት ያለው ኅብረተሰብ በመፍጠር የአገራችንን የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ የተሳለጠ ማድረግ እንደተቻለ ያብራራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ደግሞ ከአሥራ አምስት ዓመታት በኃላ አገሪቷን በልማትና በዴሞክራሲ ጎዳና ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር እንደተቻለ በተዘጋጀው የመወያያ ጽሑፍ ላይ ተገልጿል፡፡ በአገራችን 54 በመቶ የነበረው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ይኖር የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ወደ 22 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡ በገጠርም ሆነ በከተማ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ የመሠረተ ልማት አቅርቦት መጥቷል፡፡ ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት 45 ዓመት የነበረው የዜጎች አማካይ በሕይወት የመኖር የዕድሜ ጣራ ዛሬ ላይ ከ19 ዓመታት በላይ ጭማሪ አሳይቶ ወደ 64 ዓመታት ከፍ ማድረግ ተችሏል ሲል ያስረዳል፡፡

ኢሕአዴግ ይኼንን ይበል እንጂ በተቃራኒው የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ሒደቱን የሚፈታተኑና የሚገዳደሩ ጉዳዮች እየገጠሙት እንደሆነም ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተፈጥረው የነበሩ አገራዊ ችግሮችን በመጥቀስ፡፡ ዋነኛ የችግር ምንጮች ናችው ብሎ ከፈረጃቸው ምክንያቶች መካከል ደግሞ በሥልጣን ላይ ባሉ አንዳንድ አመራሮች ሕጋዊ ሥርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ ተጠቃሚ ለመሆን የመፈለግና በተግባርም የመንቀሳቀስ አዝማሚያ በመፈጠሩ የተነሳ እንደሆነ ያምናል፡፡

ኢሕአዴግም ይችን ተረስታና በማሽቆልቆል ሒደት ውስጥ የነበረች አገር ለመታደግ ደፋ ቀና ስል ይኸው ድፍን 25 ዓመታት ሞሉኝ ሲል በየሚዲያው ይናገራል፡፡

ሮናልድ ሬገን እ.ኤ.አ. በ1966  ለካሊፎርኒያ ገዥነት መወዳደር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በ1981 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እስከሆኑበት ጊዜ ድረስ በየሥፍራው “ስለተረሳችው አሜሪካ” ሺሕ ንግግሮችን አድርገዋል፡፡ በዚህ ንግግራቸውም ሚሊዮን አሜሪካውያን ልባቸውን ሰጥተዋቸዋል፡፡ የተረሳቸውና ለረጅም ጊዜ በእንቅልፍ ውስጥ ነበረች የምትባለዋን አሜሪካ ህዳሴዋንና ልማቷን እንዲሁም ዕድገቷን ለማምጣት በሮናልድ ሬገን ንግግር አማካይነት ሚሊዮን አሜሪካውዊያን ከጎናቸው ሆነው ተንቀሳቅሰዋል፡፡

ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ይችን የተረሳችና በማሽቆልቆል ሒደት ውስጥ የነበረች አገር ለመታደግ ከጎኔ ቆመዋል ሲል ይሰብካል፡፡ ባደረግኩት የመታደስና የመለወጥ ሒደትም አገሬን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር በቁጥጥሬ ውስጥ አውዬዋለሁ፣ የአገሪቷን ዕድገትም እያፋጠንኩ ነው ሲል ይሞግታል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የተወሰኑ ግለሰቦች ከመውቀስና ከመወንጀል ባይቆጠቡም፡፡

በአገራችን የታሪክ ሒደት ውስጥ መወቃቀስና መወነጃጀል የተለመደ ነው፡፡ አንዱ መሪ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ከእሱ በፊት ያለውን ይወነጅላል፡፡ አፄ ዮሐንስ አፄ ቴዎድሮስን ሲወነጅሉ፣ አፄ ምኒሊክ አፄ ዮሐንስን ሲወነጅሉ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አፄ ሚኒሊክን ሲወነጅሉ፣ ደርግ የንጉሡን ሥርዓት ሲወነጅል፣ ኢሕአዴግ ደግሞ ደርግን ሲወነጅል ይኸው እዚህ ደርሰናል፡፡ መሪዎች የሚገመገሙት በሠሩት የአገር ኃላፊነት የሥራ አፈጻጸም ነው፡፡ የኩባ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፊደል ካስትሮ “ታሪክ ነፃ ያወጣኛል (History Absolves Me)” ብለው የተናገሩት በሚሠሩት ሥራ ነገ ሊወነጀሉም ሆነ ሊሞገሱ እንደሚችሉ ቀድመው ያውቁት ስለነበር ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት መሪዎች በዓለም ላይ ተወዳጅነትን አትርፈው ነው የሚያልፉት፡፡

ኢሕአዴግም የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን አሁን ላይ እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች የሕዝብን ውግንና የሚያስገኙና ልማትን የሚያፋጥኑ መሆን አለባቸው፡፡ በመነሻዬ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ለኅብረተሰባችን ለውጥ በቁርጠኝነት መሥራት አለበት፡፡ ለአገራችን አርሶ አደር ከወሬ ባለፈ መሠረተ ልማቶችን ልናፋጥን ይገባል፡፡ መንገዶች ቀበሌን ከቀበሌ ለማገናኘት መሠራት አለባቸው፡፡ የሚሠሩ መንገዶች አስፋልት ዳርና ዳር ላሉ የኅብረተሰባችን ክፍሎች ብቻ ሳይሆን እስከ ታች የገጠሩ ክፍል መዝለቅ አለባቸው፡፡ የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡ አስተማማኝና ዘላቂ የምርት ውጤት እንዲመዘገብ የግብርና ባለሙያዎች ከልብ ከአርሶ አደሩ ጐን ሆነው አዳዲስ አሠራሮችንና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ማድረግ አለባቸው፡፡ 

በከተማ ደረጃም የሚኖሩ በከፋ ድህነት ውስጥ ያሉ ዜጐች አስፈላጊው የሥራና የሌሎች ዕድሎች ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡ ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፈጠር አለበት፡፡ እንደ ሌሎች የአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች መንግሥት የመሪነት ሚናው የጐላ መሆን አለበት፡፡ በታሪክ ያለፈውን ትውልድ ከመውቀስና ከማሽቆልቆል ጉዞ ገትተን ገና አሁን ወደፊት እየሄድን ነው የሚል አጉል ወቀሳና ውንጀላ በመላቀቅ ጊዜያችንን በአግባቡ በመጠቀም ከድህነታችን ልንወጣ ይገባል፡፡ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይም ብዙ ሥራ ያስፈልጋል፡፡

ዛሬ ላይ ሆነን የነገ መንገዳችንን አሻግረን ማየት አለብን፡፡ የነገ ሕይወታችንን በዛሬ መስታወት በመመልከት ወደ ከፍታው ልንወጣ ይገባል፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው zemenutenagne09@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

Standard (Image)

የኢትዮጵያ አንደኛ ደረጃ ሀብት ምንድነው?

$
0
0

በመታሰቢያ መላከሕይወት ገብረክርስቶስ

ብዙ አገሮች በዓለም አስደናቂ ዕድገት አስመዝግበው የሕዝባቸውን ሕይወት ትርጉም ባለው መንገድ መለወጥ የቻሉበት አንዱና ዋነኛው ምክንያት፣ ሥልጣን የያዘው ኃይል በቂ ጊዜ ወስዶ አገሪቷ በአቋራጭ ማበልፀግ የሚቻልበትን መንገድ በማጥናትና ያንን መንገድ ተከትሎ ሰፊ ሥራ መሥራቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን በርካታ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ብትሆንም አንዱ ከአንዱ የተሻለ ጥቅምና ከፍተኛ ዕድገት ለማምጣት የሚያስችል ነው፡፡

በመሆኑም ይኼንን ጉዳይ በአግባቡ መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኘው ፕላቶ ወይም ደጋማ ቦታ ከ60 በመቶ በላይ ባለቤት መሆንዋ የበርካታ ወንዞች መፍለቂያ እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ይኼ ከፍተኛ ቦታ ደግሞ በመሀሉ የያዛቸው በርካታ ሚሊዮን ዓመታት የፈጠሯቸው ሸለቆዎች ይገኙበታል፡፡

በአንድ ከፍተኛ ቦታ ከፍተኛ ስፋት ያለው ሸለቆ በሚኖርበት ጊዜ ይህ ቦታ በዋናነት እንደ ውኃ ባንክ ሆኖ ማገልገል የሚችል በመሆኑ፣ ይህንም ሰው ሠራሽ ግድብ ተገድቦለት ውኃ እንዲከማች በሚደረግበት ጊዜ (አሁን በአገራችን በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኘው) ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል ማመንጨት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ኃይል ማመንጨት ሲቻል፣ ወንዙን እንደ ዋናነት በመቁጠር የሚነገር አባባል ነው በስፋት የሚሰማው፡፡ ነገር ግን ወንዙ ኃይል ማመንጨት ያስቻለው ያለው ሸለቆ ነው፡፡ ወይም በሸለቆው ውስጥ የተጠራቀመው ውኃ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆነችው ኬንያ ውስጥ ከኬንያ ተራራ ተነስቶ ወደ ህንድ ውቅያኖስ የሚሄድ ትልቅ ወንዝ አላት፡፡ ይኼ ተራራ ከፍታው 5,100 ሜትር ሲሆን እኛ አገር ያለውን ራስ ዳሸን በ600 ሜትር ይበልጠዋል፡፡ ነገር ግን ከተራራው የሚነሳው ወንዝ ስሙ ጣና ሲሆን፣ ከተራራው እንደወረደ ምንም ዓይነት ሰፊ ሸለቆ ሳይኖረው ሜዳ ለሜዳ እየሄደ ህንድ ውቅያኖስ ውስጥ ይገባል፡፡ በመሆኑም የኬንያን ሕዝብ ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል ኃይል የማመንጨት አቅም የለውም፡፡ ለዚህም ነው ኬንያ ከኢትዮጵያ 500 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት የተገደደችው፡፡

የኬንያን  ጣና ወንዝ እንደ ምሳሌ ወሰድኩ እንጂ፣ በመላው ዓለም ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ኖሮአቸው ሸለቆ አልባ የሆኑ ወንዞች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡

ለተጨማሪ ምሳሌ ግብፅን ብንወስድ ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ የገነባችው አስዋን ግድብ ማመንጨት የሚችለው ከፍተኛው ኃይል 2,100 ሜጋ ዋት ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት ግብፅ የተከዜን ተፋሰስ፣ የብሉ ናይልን ተፋሰስ፣ የባሮ አኮቦን ተፋሰስ፣ የነጭ አባይን ተፋሰስ ሁሉ በአንድ ላይ ወስዳ ማመንጨት የቻለችው የኃይል መጠን ከላይ የተጠቀሰውን ብቻ ነው፡፡ እኛ አገር ግን የዓባይን ያውም የታችኛውን የዓባይ ሸለቆ ብቻ በመጠቀም 6000 ሺሕ ሜጋ ዋት ማመንጨት በቅርቡ የምንችልበት አቅም አለን፡፡ ይህ ማለት ኃይል ለማመንጨት ውኃ ወሳኝ ቢሆንም ሸለቆ ደግሞ ከውኃ ባልተናነሰ  ወሳኝነት እንዳለው ነው፡፡ በእኛ አገር በዚህ ጽሑፍ የግድ ሊቃኝ የሚገባው ጉዳይ የተከዜ ሸለቆና ወንዝ ነው፡፡ ተከዜ ከዓባይ በትንሹ የሚያንስ ሸለቆ ቢኖረውም፣ በውስጡ የሚያልፈው ውኃ መጠን በእጅጉ አነስተኛ በመሆኑ ለኃይል ግንባታ አጓጊ ቦታ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የተከዜ ውኃ የሚመነጭባቸው የወሎ ደጋማ ቦታዎች በእጅጉ የተፈጥሮ ሚዛናቸው የተናጋ በመሆኑና ተራሮቹ ሁሉ ደን አልባ በመሆናቸው፣ በጥንት ዘመን በከፍተኛ ደረጃ ከእነዚህ ተራሮች ይመነጩ የነበሩ ምንጮች በሙሉ በመድረቃቸው የተከዜ ሸለቆ ብቻውን ቀርቷል ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ በሌላ አነጋገር በእነዚህ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ መከናወን እንዳለበት የሚያመላክት ነው፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደያዘ መጀመሪያ የገነባው የተከዜ ግድብ፣ በአብዛኛው የዓመቱን ወቅት እጅግ ዝቅተኛ ኃይል ለማመንጨት የሚገደደውም ለዚህ ነው፡፡

በቅርቡ ተገንብቶ ያለቀው የጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጨት ደግሞ በሸለቆም በውኃም በእጅጉ የበለፀገ ነው፡፡ በእኔ እምነት ዓመቱን ሙሉ  ያለ ምንም መስተጓጎል የተፈለገውን ኃይል ማመንጨት አቅም ያለው የኃይል ማመንጫ መሆኑን ስናይ ለምን ቅድሚያ ተነፈገው የሚያሰኝ ነው፡፡

የዓባይ ወንዝ በዓለም በርዝመቱ አንደኛ ቢሆንም በውኃ መጠን ግን ሌሎች በርካታ ወንዞች ይበልጡታል፡፡ እንደ ሚሲሲፒ፣ አማዞን፣ ዶናው፣ ቮልጋ፣ ኮንጎ፣… የመሳሰሉት ወንዞች እጅግ ከፍተኛ የውኃ ፍሰት ያላቸው ናቸው፡፡ በኮንጎ ወንዝ ላይ 39,000 ሺሕ ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችል የኃይል ማመንጫ የተጠና ቢሆንም፣ እስካሁን ሁኔታዎች ባለመሟላታቸው ግንባታው ሊጀመር አልቻለም፡፡ ይፈጃል ተብሎ የተገመተው ገንዘብ ደግሞ 80 ቢሊየን ዶላር ገደማ ነው፡፡ ይህ ግድብ ከዕለታት አንድ ቀን ተገንብቶ ሲያልቅ በዓለማችን ትልቁ ከውኃ ኃይል ማመንጨት የሚችል ግንባታ ይሆናል ማለት ነው፡፡

አሁን ባለንበት ዘመን አንድ አገር የኤሌክትሪክ ኃይል ለምን ታመነጫለች የሚለው ጉዳይ በእጅጉ ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ከታዳሽ ኃይል የሚመነጭ ኤሌክትሪክና የከባቢ አየር የማይበክል ኃይል ያላቸው ተፈላጊነት በእጅጉ እየጎላ የመጣበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ ዓለማችንን እየበከልንና ከንፁህ ምንጭ የምናመነጫቸው የኃይል አቅርቦት ልዩነታቸው በእጅጉ እየጎላ ነው፡፡ እዚህ ላይ በግሌ አንድ አዕምሮዊ ንብረት ለአገር ኢኮኖሚ ይጠቅማል ብዬ ስለማምን በዚህ ጽሑፍ ለማቅረብ ይፈቀድልኝ፡፡

በኢትዮጵያ ተመርተው ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ ማናቸውም ምርቶች አንድ ምልክት ይለጠፍባቸው፡፡ ይህም ምልክት የሚከተለው ዓርማ እንዲኖረው ይደረግ (The Energy Used to Produce This Product is Clean)፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ በዓለም ገበያ ያለንን ተወዳዳሪነት መጨመር ከመቻላችንም በላይ፣ የዘመኑ ዋና ጉዳይ የሆነውን የከባቢ አየር ብክለትን ለመከላከል ያለብንን አገራዊ ኃላፊነት በሚገባ ተወጥተናል ማለት ነው፡፡ ምርቱም የመሸጥ ዕድሉ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስና በአሁኑ ወቅት እየገነባነው ያለነው የዓባይ ግድብ ሙሉ በሙሉ ውኃ መያዝ ሲጀመር ወደ ኃላ 250 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ይፈጠራል፡፡ ይህ ማለት በሐይቁ ግራና ቀኝ ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የውኃ ዳርቻ ይኖራል፡፡ ይህ አካባቢ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል ማለት ነው፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራው አሳ በማስገር፣ በትራንስፖርት ዘርፍ፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ ከብቶች በማደለብና በተለያዩ የእርሻ ሥራዎች፣ ወዘተ ነው፡፡ ይህ ማለት በዋናነት ይህንን ሁሉ ተግባር ለማከናወን የሚያስችለን ከግድቡ ጀርባ እጅግ ሰፊ የሆነ ሸለቆ በመኖሩ ነው፡፡ ይህ ማለት በእኔ እምነት ሸለቆ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ከወንዝ የበለጠ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አለው ማለት ነው፡፡

ሸለቆ አሁን በአገራችን እየተደረገ እንዳለው ከፍተኛ ግድብ ገንብቶ ኃይል ለማመንጨት ብቻ አገልግሎት  የሚሰጥ ሳይሆን፣ ደጋማ ቦታ ባሉ ሸለቆዎች (ወደፊት ሀብት በበቂ ሁኔታ ሲኖር) ውኃ ለማከማቸት ማለትም የክረምቱን ውኃ በመያዝ በበጋና በደረቅ ወቅት ዝቅተኛ ቦታ ወደ አሉ የኃይል ማመንጫ ግድቦች እንዲገቡ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህም ግድቦች ዓመቱን ሙሉ ያለ ውኃ እጥረት እንዲሠሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አሁን እየተገነባ  ያለው የዓባይ ግድብ ከአናቱ እጅግ በርካታ ሸለቆ ያላቸው ተፋሰሶች አሉት፡፡ እነዚህ ተፋሰሶች መጠናቸው ኃይል ለማመንጨት ከበቃ በዚያ መልኩ ሊጠኑ ይችላሉ፡፡ ኃይል ለማመንጨት የማይበቃ ከሆነ ግን ተፈጥሮ እንዲሠራ እንደ ጣና ሐይቅ ውኃ በመያዝ ለታችኞቹ ግድቦች የውኃ ባንክ ማገልገል ይቻላል፡፡

አንድ አገር ማደግ ካለበት በአሁን ወቅት ልንሠራቸው የምንችላቸው ተግባራት ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ጥቅም መለወጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በሰዎች አዕምሮ ላይ ሰፊ ሀብት በማፍሰስ (እንደ ጃፓንና ኮሪያ) የአዕምሮ ውጤቶችን በማምረትና ለዓለም ገበያ በማቅረብ የሚደረግ የልማት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ከእነዚህ ሁለት አማራጮች ውጪ ሌላ የአንድን አገር ኢኮኖሚ ሊለወጥ የሚችል ተግባር የለም፡፡ በመሆኑም አገራችን ያላትን ሰፊ የሸለቆ ሀብት ወደ ጥቅም በመለወጥ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን  ሕይወት ሙሉ በሙሉ መለወጥ ይቻላል፡፡ በዓለማችን እኮ ምንም ሸለቆ የሌላቸው በርካታ አገሮች አሉ፡፡

እዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ልማት ብቻ ሳይሆን ውኃ በሚከማችበት ወቅት የሚፈጠረው ውኃ ወለድ በሽታ ጭምር ነው፡፡ ውኃ በሚከማችበት ወቅት አንድ ቦታ ድሮ ከነበረው ዓመታዊ ምዝን የአየር ሙቀት ከ2.5 እስከ 3.5 ዲግሪ የአየሩ ሙቀት ሊቀንስ ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ በርካታ ነፍሳት በቀላሉ መራባት ይጀምራሉ፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው አካል ለጉዳይ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡

ስለ ሸለቆ ስናነሳ በአገራችን ያሉ ክልሎች ያላቸው የሸለቆ ሀብት በእጅጉ ይለያያል በዋናነት የአማራ ክልል የተራሮችና የሸለቆዎች ባለሀብት ሲሆን፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልል የሁለተኛና የሦስተኛ ቦታዎችን ይይዛሉ፡፡ በአገራችን ከሚገኙ ቁመታቸው ከባህር ጠለል በላይ ከ3,900 እስከ 4,500 ሜትር ከፍታ ካላቸው 23 ተራሮች 20 ያህሉ የሚገኙት በአማራ ክልል ነው፡፡ ወደ ትግራይ ክልል ስናመራ ይህ ክልል በአመዛኙ ወይና ደጋ ተብሎ የሚጠራ የመልክዓ ምድር ባለቤት ሲሆን፣ ከባህር ጠለል በላይ አብዛኛው የክልሉ መሬት 1,600, እስከ 1,800 ሜትር የሚደርስ ነው፡፡ በትግራይ ምሥራቃዊ ክፍል የተሻለ ከፍታ ቢኖርም አብዛኛው በአካባቢው የሚጥለው ዝናብ ተፋሰሱ ወደ አፋር ክልል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የትግራይ ክልል በቂ ዝናብ ወይም እርጥበት እንዳያገኝ ምክንያት ሆኗል፡፡

በትግራይ ክልል አንድ ሰው ከሽሬ ተነስቶ እስከ አዲግራት ወይም መቀሌ መኪና ቢነዳ፣ ይህ ነው የማይባል ትልቅ ድልድይ ወይም ወንዝ መሻገር አይችልም፡፡ በሌላ አነጋገር ትግራይ ውስጥ በርካታ ጉብታዎች ቢኖሩም፣ ክልሉ በአብዛኛው ሜዳማ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ ክልል ደጋማ ከሆነ የራሱ የሆኑ በቂ ዝናብ የሚያገኝበት ዕድል ይኖረዋል፡፡ ቆላማ ከሆነ ደግሞ ከደጋው የሚመጣውን ውኃ በመቀበል ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ የትግራይ ክልል ግን ወይና ደጋ በመሆኑና ከሌሎች ክልሎች ወደ ክልሉ የሚፈሱ ወንዞች በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው፣ ውኃ አጠር የሆነ ክልል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በመሆኑም በክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ሥራና የደን ልማት ከምንም በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡

የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ግን ያላቸውን የሸለቆ ሀብት ብቻ በማልማት የክልሎቹን ኢኮኖሚ ሙሉ ለሙሉ መለወጥ ይቻላል፡፡ አንድ አገር ታላላቅ ተራሮች ካሉዋት ታላላቅ ወንዞች ይኖሯታል፡፡ ወንዝ ካለ ደግሞ ታላላቅ ሸለቆዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ውኃውን ሸለቆው ውስጥ በማከማቸት የውኃ ባንክ በመፍጠር ዜጎችን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፡፡

በመሆኑም በእኔ እምነት የኢትዮጵያ ትልቁ ሀብት የሸለቆ ሀብት ነው፡፡ ይህ ማለት ከላይ የተጠቀሱት የተፈጥሮ ሀብቶች ትርጉም የላቸውም ማለት ሳይሆን፣ ቅደም ተከተል ሲቀመጥ ሸለቆ ትልቁ የሀብት ምንጭ ነው ብለን መደምደም የምንችል ይመስለኛል፡፡

በጥንታዊው አባባል ‹‹ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል›› የሚለው ፈሊጥ አሁን ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ዓባይ ውሎ አድሮ የዜጎቹን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ቀይሮ፣ ሌሎች ሕዝቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ ጉዞውን ይቀጥላል ሊባል ይችላል፡፡ ወይም፣ ደግሞ ‹‹ዓባይ ራሱ ለበርካታ ዓመታት በቆፈረው ሸለቆ ውስጥ ውሉ አድሮ ከፍተኛ ጥቅም ሰጥቶ ጉዞውን ይቀጥላል›› ማለት እንጀምራለን፡፡ ዓባይ ሸለቆ ባይኖረው ኖሮ፣ ‹‹ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል›› የሚለው አባባል ማለቂያ ሳይኖረው ለዘለዓለም ይቀጥል ነበር፡፡

በእኔ ግምት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የዓባይ ግድብን ሲመርቁ ከሚናገሩት አንዱ አባባል፣ ‹‹ለዓባይ ማደሪያና መዋያ ተበጀለት›› የሚል ይመስለኛል፡፡ ሁላችንንም ለዚያ ያድርሰንና ስለግድቡ ስናወራ ልናውቀው የሚገባ ትልቁ ቁም ነገር አጠቃላይ ውኃውን ከሚይዘው ተፈጥሮዓዊ ግድብ ሰው ሠራሹ ከአንድ በመቶ በታች መሆኑን ነው፡፡ ጠባብ ቦታ ተፈልጎ ጠንካራ ግድብ መሸከም የሚችል ቦታ ተፈልጎ ሲገነባ ወንዙ ራሱ ከፈጠረው ሰፊ ሸለቆ ሰው ሠራሹ ግድብ በእጅጉ ዝቅተኛ ነው፡፡ በመሆኑም አንድ አገር በርካታ ግድብ ሊገደብባቸው የሚችሉ ሸለቆዎች ካአሏት ያን ትልቅ ሀብት ነው ኢትዮጵያ አገራችንም መጠቀም ያለባት፡፡ የዚህ ሀብት የተትረፈረፈ ባለቤት በመሆንዋ ሁላችንም ልንኮራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

 ከአዘጋጁ፡ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

   

Standard (Image)

ሥልጣን ለማግኘት ስንል የፈጠርናቸውን ቅራኔዎች ሥልጣን ካገኘን በኋላ ለማስወገድ ይከብዳል

$
0
0

በሳሙኤል ረጋሳ

የአገራችን ሰላም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስተማማኝ መሠረት ላይ የቆመ አይደለም፡፡ ሕዝቡም በመጪው ጊዜ ምንም የተረጋገጠ ተስፋ ሳይኖረው ወደፊት የሚፈጠረውን ሁኔታ በፅሞና እየተከታተለ ነው፡፡ የደርግን አሥራ ሰባት ዓመታት የእልቂትና የመከራ ዘመን አልፈን ለጊዜውም ቢሆን አንፃራዊ ሰላም እናገኛለን ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም ለእልቂት የሚጋብዝ ሌላ የጭካኔና የመከራ ዘመን ሊያስከትል የሚችል አዝማሚያ መኖሩን መገመት ይቻላል፡፡

በዚህ ሥጋት መነሻ ይመስላል ሰሞኑን የአገራችን የሃይማኖት አባቶች ጉዳዩ አሳስቦናል በሚል ስሜት ሰላምን ለማውረድ እርቅ እንፈጽማለን በማለት ደፋ ቀና እያሉ ያሉት፡፡ በሐሳብ ደረጃ ይኼ የተቀደሰ ተግባር ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው ማኅበራዊና መንፈሳዊ ደረጃም ይኼንን እንዲፈጽሙ ያስገድዳቸዋል፡፡ ነገሩን በሚዲያ እንደተከታተልነው ግን ድፍንፍን ባለና ግልጽነት በሌለው መንገድ ነው የተላለፈው፡፡ ሰላምን የሚያወርዱት ማንንና ማንን አስታርቀው ነው? ሊያስማሙዋቸው ያሰቡት ወገኖችስ በጉዳዩ ላይ ምን ዓይነት አቋም አላቸው? የተጣላ ሰው የለምና የምታስታርቁት ሰው የለም ቢባሉስ? ይኼንን ለመዘርዘር ያልፈለጉት ተስማሚዎቹ ወገኖች በግልጽም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ አለ ብለው በማሰባቸው መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ ለነገሩማ በየጊዜው የተከሰቱትን ቅራኔዎች አንድ ጊዜ እንኳን ለመፍታት ያለመሞከራችን ሁኔታዎችን ያወሳሰበ ስለሆነ ለእርቅ ያስቸግራሉ ብሎ መፍራት ተገቢ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ መንግሥት፣ ተቃዋሚዎችና ሕዝቡ አንዱ ሌላውን እየወቀሱ ነው፡፡ ለወቀሳ ያደረሳቸውም ቅራኔ ሰፊ ነው፡፡ ለጊዜው የሕዝቡ ብሶት ብዙ ብዙ የተባለለት ስለሆነ እሱን ወደ ጎን ትተነው፣ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች መሀል ያለውን ብቻ እንመልከት፡፡

ሁልጊዜ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች መካከል ተፈጥሮአዊ፣ ሊቀርና ሊወገድ የማይችል እርቅም የማያስፈልገው የሐሳብ ልዩነት ይኖራል፡፡ ይኼ የርዕዮተ ዓለማዊና የአመለካከት ልዩነት ጉዳይ ሁልጊዜ የማይታገድና ተገቢ በመሆኑ ሊኖር የሚገባ ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ ልዩነት ገደቡን አልፎ ወደ ባላንጣነት ወይም ወደ ግጭትና ብጥብጥ አምርቶ የአገሪቱን ህልውና የሚፈታተን ከሆነ ሀይ ባይና አስታራቂ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የአገራችንም ሁኔታ ገደቡን ስላለፈ ነው የሃይማኖት አባቶች በነገሩ ለመግባት የፈለጉት፡፡ እስቲ ከአንድ ጥያቄ እንነሳ፡፡

በመጀመሪያ መንግሥትና ተቃዋሚዎችን አደራድሮ ችግሮቹን መፍታት ይቻላል?  ምንም እንኳን ለዚህ ጥያቄ ቁርጥ ያለ መልስ ማስቀመጥ ከባድና ውስብስብ ቢሆንም መልሱ አዎን ይቻላል ነው፡፡ ይኼ ከባድ ጥያቄ ከተመለሰ በተለያየ ጊዜ ከአንገት ይሁን ከአንጀት ባይታወቅም ከተለያዩ አካላት ሲነሳ የነበረው የብሔራዊ እርቅ ጉዳይ አንዱ ዋና ምዕራፍ ይጠቃለላል፡፡ እውነተኛ እርቅ ከልብ በተፈለገበት ቦታ ሁሉ አለ፡፡ ነገር ግን ከሌላው ጋር እርቅ የሚፈልግ ሁሉ በመጀመሪያ ከራሱ ጋር መታረቅ አለበት፡፡ ዋናውና ከባዱ የእርቅ ደረጃም ከራስ ጋር መታረቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ሌላ ገላጋይ ሽማግሌ የሌለበት ከህሊና ጋር የሚደረግ ሙግት በመሆኑ ነው፡፡ ከራስ ጋር ለመታረቅ የራስን ጥፋትም ሆነ ስህተት ማወቅና መቀበል የመጀመሪያው ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ የሌሎችን ስህተትም ሆነ ጥፋት የማናይበት መንገድ የእኛ ትክክል ነው ብለን በምናስበው መንገድ ብቻ መሆን እንደሌለበት ነው፡፡ እኛ ትክክል ነው ብለን የምናምንባቸው ብዙ ጉዳዮች ስህተት ሆነው ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በብዙኃን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘን እውነት ወይም እውነት መሳይ ነገሮችን ወደ ጎን ገፍተን የእኔ ካልሆነ ብሎ ግትር አቋም መያዝ አደገኛ የሆነ የሕይወት ፍልስፍና ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ በሁሉም የሕይወት ዘርፍ ውስጥ በሁለቱም በኩል አስታራቂ ሐሳብ ማግኘት የማይቻልበት ጊዜ ሊኖር ይችላል፡፡ የዚህ ዓይነት መንታ ሐሳቦች ሲገጥሙን ጉዳዩን በይደር አቆይተን በቂና አሳማኝ መረጃዎች ማሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ለጊዜው ሳናውቀው ቀርተን ነው እንጂ መፍትሔ የሌለው ችግርና መድኃኒት የሌለው በሽታ በዚህ ዓለም ላይ የለም፡፡ የጊዜ ጉዳይና የምርምር ማነስ እንጂ ሁለቱም ውሎ አድሮ ይገኛል፡፡ እየተገኘም ነው፡፡ በዚህ እሳቤ ከራሳችን ጋር ከታረቅን ሌሎችን መታረቅም ሆነ ማስታረቅ የቀለለ ይሆናል፡፡ ቀጥሎ በተዘረዘሩት ቀደምት ኢትዮጵያውያን አባቶች ላይ ያለንን ሐሳብ እስቲ እንመርምር፡፡

ኢትዮጵያ በመንግሥትነት መተዳደር ከጀመረች ጊዜ ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ድረስ እጅግ በርካታ ነገሥታት ተቀያይረው አገሪቱን ገዝተዋል፡፡ ነገር ግን መቁጠር የሚችል ወደኋላ እስከ ንግሥተ ሳባ ቢቆጥር በጦር ሜዳ ከሞቱት ውጪ የሁሉም አሟሟት በግልጽ አልተነገረም፡፡ አንዳቸውንም እንደ አንድ ተራ ደሃ እንኳን  ሕዝቡ ወጥቶ አልቀበራቸውም፡፡ ራስ አሉላ፣ ራስ ጎበና፣ ራስ አባተ፣ ደጃዝማች ባልቻ፣ ሊጋባ በየነ፣ አብዲሳ አጋ፣ . . . ወዘተ በተለያዩ የጦር ሜዳዎች ከጣሊያኖች ከደረሱትና ከሌሎች በውጭና በውስጥ የጀብዱ ሥራን በከፍተኛ ተጋድሎ ፈጽመው የመጨረሻውን የሕይወት ዘመናቸውን ከሚገባቸው ክብር ወደ ተራ ሰውነት ወርደው ነው የኖሩት፡፡ ራስ ሥዩምና ራስ ሙሉጌታ በሰሜኑ የኢጣልያን ጦርነት የኢትዮጵያ ዋና የጦር አዛዦች ነበሩ፡፡ ግን ሁለቱም በወገናቸው ጥይት ነው የተገደሉት፡፡ ራስ መስፍን ስለሺ፣ ራስ አበበ አረጋይ፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ በጅሮንድ ታከለ ወልደ ኃዋርያት፣ ሻለቃ አብዲሳ አጋ፣ ሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ኮሎኔል ቢሹ ገብረ ተክሌ፣ ሜጄር ጄኔራል ኃየሎም አርዓያ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው መኮንን፣ . . . ወዘተ በሚቻላቸው ሁሉ ወቅቱና የጊዜው ሁኔታ በሚጠይቀው መሠረት በከፍተኛ የአርበኝነትና የዲፕሎማሲ ሥራዎችን በቆራጥነት ከፈጸሙ በኋላ፣ ሁሉም ያለጥፋትና ያለፍርድ የተገደሉት በወገኖቻቸው ጥይት ነው፡፡

ከላይ ስለተጠቀሱት ባለሥልጣናት ሁላችንም ያለን አረዳድ አንድ ዓይነት ነው? የምንደግፋቸውና የምንቃወማቸው ቢኖሩ አይገርምም፡፡ ነገር ግን እነሱ በነበሩበት ዘመን ወቅቱንና የነበሩበትን የፖለቲካ ሁኔታ ተጨባጩን ነገር ይዘው ኢትዮጵያን ለመታደግ ተገቢውን መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ሁሉም የየራሳቸው ጉድለት ይኖራቸዋል እንኳን ብንል፣ ኢትዮጵያን ከእነ ድህነትዋም ቢሆን በክብር አቆይተውልናል፡፡ ያለፉት አገራዊ ጉዳዮች ሁሉ የሚለኩት በወቅቱ በነበረው ተጨባጭ ሁኔታ እንጂ ዛሬ ላይ ቆመን በምንሰጠው ፖለቲካዊ ትንታኔ አይደለም፡፡ የእነዚህ ሰዎች ሥራ ከፊልም ቢሆን የማይጥመን ካለን ምክንያታችንን እናስቀመጥ፡፡ እነዚህን ሰዎች የምንደግፋቸው ወይም የምንቃወማቸው በብሔር ማንነታቸው፣ በመደብ ጀርባቸው፣ በሃይማኖታቸው ወይም በእኔ ብሔር ላይ በደል ፈጽመዋል ወይም ጠቁመዋል ከሚል መነሻ ከሆነ ዋናውን ግንድ ጉዳይ ትተን ቅርንጫፉ ላይ እየተንጠላጠልን ስለሆነ፣ መቼም ቢሆን ሐሳባችንን የምናስታርቅበት መነሻ ሐሳብ አይኖረንም፡፡

በጎ በጎውን ስናስብ እነዚህ ሰዎች ሁሉም ክብርና ሞገስ የሚገባቸው እንጂ፣ ሞተው ቀባሪ ማጣት ወይም በወገኖቻቸው ጥይት ተደብድበው መሞት የሚገባቸው አልነበሩም፡፡ በእነዚህ ሰዎች ጉዳይ ለመስማማት ብንሞክር ወደፊት ለምናደርጋቸው የእርቅ ድርድር ጠቃሚ ጉዳዮችን እንማርበታለን፡፡ አገራችን ለክፉ ቀን ልጆችዋና ለአንጋፋ ባለታሪኮቿ ውለታ መክፈል የማትችል ውለታ ቢስ አድርጓታል፡፡

ከላይ የገለጽናቸው ቀደምት ኢትዮጵያውያን ከእኛ ጊዜ ያላነሰ የእርስ በርስ ቅራኔዎች ነበሩባቸው፡፡ ለአብነት ያህል ሊጋባ በየነ በፖለቲካ ቁርሾ ምክንያት ብቻ በአደባባይ እንደ ሌባ አርባ ጅራፍ ተገርፈዋል፡፡ ያም ሆኖ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ለሁለተኛ ጊዜ ሲመጣ ይኼን በደል ከልባቸው አውጥተው ወደ ጦር ግንባር ዘምተው ድንቅ ጅብዱ ከፈጸሙ በኋላ እዚያው በጦርነቱ ላይ ተሰውተዋል፡፡ አገሪቷ የቆየችው በእንዲህ ያለ መስዋዕትነት ነው፡፡ ከእኚህ ሰው ምን እንማር ይሆን? ሊጋባው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በመጀመሪያ ከራሳቸው ጋር ታርቀው በመቀጠልም በዳዮቻቸውን ይቅር ብለው ነው፡፡ መንግሥትን መቀየም፣ መጥላት፣ መታሰር፣ ከሥልጣን መገፋት፣ . . . ሁሉ እያለ ነው ለአገር ጉዳይ አንድ የሚሆኑት፡፡ የፈለገውን ያህል መቃወም ቢኖርም በአገር ጉዳይ እኩል ይዋጋሉ፡፡ እኩል ይሞታሉ፡፡ እኩል ይሰደዳሉ፡፡ ልንከተለው የሚገባን የአባቶቻችን ፈለግ ይኼ ነው፡፡ እነዚህ ጥቂት ማሳያዎች እንጂ ብዙ ሺዎች አሉ፡፡

እንግዲህ ለሥልጣን ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ለሰላማችንና ለነፃነታችን ስንል ብሔራዊ እርቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ለብሔራዊ እርቅ ለመዘጋጀት መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚ ድርጅቶች መጀመሪያ ከራሳቸው ጋር መታረቅ አለባቸው፡፡ ከራስ ጋር ለመታረቅ ደግሞ በቅድሚያ ከሌሎች የሚለዩንን ነጥቦች አውቀን፣ ለምን እንደሚለዩንም እንወቅ፡፡ የሚያስማሙ ነገሮች እንዲበዙ እናድርግ፡፡ ጥቂት የሚለዩን ቅርንጫፎች ወይም ዋና የምንላቸውም ቢኖሩ በተስማማንባቸው ግንድ ጉዳዮች ዙሪያ ተሰባስበን ቀሪዎቹን በሒደት እንፈታለን፡፡ የማይጎዱንና አገሪቱን ለችግር የማያጋልጡ ከሆነም በልዩነት ይዘናቸው ልንዘልቅ እንችላለን፡፡ ያን ጊዜ የሸፈነንን ጉም ጥሰን መውጣት ስንጀምር በምናየው የብርሃን ጭላንጭል እየተመራን ሁሉንም ችግሮች እንቀርፋለን፣ የሚፈቃቀርና የሚከባበር ዜጋ እንፈጥራለን፡፡ ለማንኛውም ከብሔራዊ እርቅ በፊት መታረቅ ከራስ ጋር ነው፡፡

ሁልጊዜ ስለልዩነታችን ብቻ የምናስብና የምናወራ ከሆነ ስለአንድነታችን ያለን ስሜት በየጊዜው እየተሸረሸረና እየተነነ ከአዕምሮአችን ይጠፋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለውም ችግር ይኼ ነው፡፡ አሁን አሁን እንደምናየው ጥላቻዎች ከምናስበው በላይ ስለከረሩ ገሚሱ አገሪቱን በባላ ደግፎ የያዘ ሲመስለው፣ ገሚሱ ደግሞ የሚቃወመውን ክፍል ብቻ ሳይሆን አገሪቱም አብራ እንድትንኮታኮት ይመኛል፡፡ እነዚህ ሁለቱም ጽንፎች እኩል አደገኛ ናቸው፡፡

ስለእርቅ ስናስብ ሁልጊዜ ከተደራዳሪዎቹ መካከል ክፉ የሚያስብና በጎ የሚያስብ ወገን ይኖራል ብለን መገመት አለብን፡፡ ነገር ግን ከማንኛውም ክፉ ሰው ልቦና ጥቂት በጎ ነገር አይጠፋም፡፡ ይቺኑ ጥቂቷን በጎ ነገር ይዘን እንዋሀደውና ክፉ ነገሮችን ከልቡ እናውጣለት፡፡ የሕዝባችን የጋራ የሆነ አገራዊ ፍቅርና መተማመን ከወትሮው በእጅጉ ተጎድቷል፡፡ በአንድ ባለሥልጣን የአንድ ጊዜ የበዓል ዲስኩር ወደ ነበረበት ሊመለስ አይችልም፡፡ የካድሬዎች የፖለቲካ ትምህርትም አልፈየደም፡፡ ሕዝቡ ልቦናውና መንፈሱ መዋሀድ አለበት፡፡ ይኼ ደግሞ የረዥም ጊዜ ሥራ ነው፡፡ ሥራው የሚሠራው በመተማመን ላይ በተመሠረተ ተከታታይ ውይይት ነው፡፡ አንዱ የሌላውን ሐሳብ የማይጫንበት በመርህ ላይ የተመሠረተ የመከባበር ውይይት መኖር አለበት፡፡

ከቀድሞ ጀምሮ በአገራችን ሥልጣን ለመያዝ የሚጥሩ ሰዎች መነሻቸው የሕዝብን ልዩነት ማስፋትና ልዩነቱን ተጠቅሞ ለሥልጣን መብቃት ነው፡፡ ሥልጣን  ከያዙ በኋላ ደግሞ ግዛታቸው እንዳይጠብ ልዩነቱን ቀንሶ አንድነቱን ለመመለስ ይባዝናሉ፡፡ ክፉ አሳቢዎችም በጎ መስለው ይቀርባሉ፡፡ እነዚህ ስናሸንፍና ስንሸነፍ የሚኖሩን ተፃራሪ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ በጉልበት ሥልጣን ለመያዝ የሚያጣላ ቅራኔ መፍጠር ግድ ነው፡፡ ሥልጣን ለማግኘት ስንል የፈጠርናቸውን ቅራኔዎች ሥልጣን ካገኘን በኃላ ለማስወገድ ከባድ ነው፡፡   

የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትና የሸዋው ምንሊክ በግዛት ጉዳይ ተጣልተው እምባቦ ላይ ጦርነት ገጥመው ነበር፡፡ በጦርነቱ ብዙ ሰው ካለቀ በኋላ ምንሊክ አሸንፈው ተክለ ሃይማኖትን ማርከው በክብር ወደ ቤተ መንግሥታቸው አምጥተው አኖሩአቸው፡፡ አብረው ከመቆየት የተነሳ የጦርነቱ ጉዳይ እየተረሳ ወዳጅነታቸው በርትቶ ነበር፡፡ አንድ ቀን በጨዋታ በጨዋታ የጦርነቱ ነገር ተነሳና አፄ ምንሊክ ለተክለ ሃይማኖት፣ ‹‹እኔ ማርኬዎ ክብር ሳይጓደል በንጉሥ ደረጃ አኖሬዎታለሁ፡፡ ለመሆኑ እርስዎ ቢሆኑ እንደኔ ያደርጉ ኖሯል?›› ብለው ጠየቁዋቸው፡፡ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትም፣ ‹‹አላደርገውም፣ እኔ ብሆን ሥጋህን ቆራርጬ ለአውሬ ሰጥቼ ነበር የምመለሰው፤›› አሉ፡፡ ምንሊክም፣ ‹‹ታዲያ የእኔ ነው የእርስዎ የሚሻል?›› ብለው ጠየቁዋቸው፡፡ ተክለ ሃይማኖትም፣ ‹‹ሲያሸንፉ የእርስዎ፣ ሲሸንፉ የእኔ ይሻላል፤›› አሉዋቸው ይባላል፡፡ በጭካኔና በጥፋት አሸንፎ ከድል በኋላ ገራገር የመምሰል ጉዳይ አሁንም ቢሆን በዓለም ላይ የፖለቲካ መርህ የሆነ ይመስላል፡፡ ሥልጣን ለመያዝ የፈጠርነውን ቅራኔ ሥልጣን ለማቆየት ማስወገድ የግድ ነው፡፡

የሃይማኖት አባቶቹ እርቅ ፈጽመው ሰላም ለማውረድ ሲያስቡ በመጀመሪያ መንግሥትና ተቃዋሚዎች ከራሳቸው ጋር ለመታረቅ ፈቃደኛ ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡ መንግሥት ከራሱ ጋር መታረቁን የምናውቀው የሚቃወሙትን ሁሉ በክፉ ልቦና ተነሳስተው ሥልጣኔን በጉልበት ሊነጥቁኝ ነው ብሎ ማሰብን ማቆም ሲችል ነው፡፡ የአገሪቱን ሀብትና ንብረት ጥቂት የመንግሥት ሰዎች ሲቀራመቱትና ሕንፃ በሕንፃ ሲሆኑ፣ ቤተሰቦቻቸውን አሜሪካና አውሮፓ ወስደው ሲያምነሸንሹና ሲያሳክሙ መንግሥት የሚወስደው ዕርምጃ ሲታይና ሲታወቅ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደርን ችግር በሕዝብ ላይ አሳድሮት ያለው ከፍተኛ ቀውስና መንግሥት እንደ ሕዝቡ በአፍ ከማውገዝ አልፎ ከቋቱ ጠብ የሚል ነገር ሲኖር ነው፡፡ አንዳንድ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚውሉ ጥቃቅን ሥራዎች ቢሠሩም ያዝ ለቀቅ እንጂ አስተማማኝነት የላቸውም፡፡ የቀረው ቀርቶ ለመንግሥት ሠራተኞች ትራንስፖርት አቅርቤያለሁ ባለበት ሁኔታ እንኳን ሠራተኞቹ የሥራ ሰዓታቸውን አክብረው በሰዓት መግባትና ተገቢውን ሥራ ሠርቶ በሰዓት የሚወጡ ሁሉም አይደሉም፡፡ መንግሥት በአብዛኛው ሥራውን በሕግ አግባብና ለሕዝብ በሚጠቅም መንገድ መከወን አልቻለም፡፡ ብሔራዊ እርቁን ለማምጣት በመጀመሪያ ከራሱ ጋር ታርቆ ጉዳዩቹን መስመር መያዝ አለበት፡፡ እነዚህንና ሌሎች መሰል ችግሮችን ለመፈጸም ጊዜ የሚወስድና በቂ የሰው ኃይል ባይኖረው እንኳን፣ የችግሮቹን መኖር አምኖ የመፍትሔያቸውን ጉዳይ ለድርድር ማቅረብ አለበት፡፡  

ተቃዋሚ ድርጅቶችም መንግሥት ለሥልጣን ያለውን ጉጉት አይተው ሥልጣን ለመጋራት ወይም ለመንጠቅ የሚፈልጉት በኃይልና በብጥብጥ ጭምር ነው፡፡ አልፎ አልፎም የአገርን አጠቃላይ ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል በሚችል መልኩ በውጭ ካሉ የአገሪቱ ታሪካዊና ወቅታዊ ጠላቶች ጭምር በማበር ነው፡፡ እነሱ የሚከፍቱት ቀዳዳና የሚከተሉት የፖለቲካ ሥልት መንግሥትን መጣል እንኳ ቢችል፣ እነሱ ለሚጓጉለትና ለሚታገሉለት ሥልጣን እንደማያበቃቸው ማወቅ አለባቸው፡፡ ይኼ ሥልት እንዲያውም የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥልና እንኳን የሚገዙት የሚኖሩበትን አገር እንደሚያሳጣቸው ማመን አለባቸው፡፡ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ትዃን ረብቶ ያስቸገረው ባተሌ፣ ለዘለቄታው ከትዃኑ ለመገላገል ሲል ቤቱን እሳት ለኩሶ ያቃጠለው ሞኝ ዓይነት ጨዋታ ነው፡፡   

መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚዎች አብሮአቸው ተወልደው ያደጉትን እነዚህን ባህሪያት በቀላሉ አስወግደው ሰላምን ያመጣሉ ማለት ላይታሰብ ይችላል፡፡ ነገር ግን የምናወራው ከራስ ጋር ስለመታረቅ እስከሆነ ድረስ ጉዳዩን በይቻላል መንፈስ መቀበል አለብን፡፡ እነዚህ ነገሮች መርምረው ገምግመው ቢያንስ በራስ ፍጆታ ወደ ውስጥ አስገብተው ማየት አለባቸው፡፡ ነጥቦቹን ከልብ ከተቀበልናቸው፣ እርቁ ቢዘገይም አሳሳቢ ጉዳይ አይደለም፡፡ እርቅ ማለት የለበጣ መሳሳም ወይም መጨባበጥ አይደለም፡፡ ስለተቃዋሚዎቻችንና ስለአገራችን ያሉንን አሉታዊ ስሜቶች ሁሉ ከልብ አውጥቶ ዘላቂ ሰላምን ብቻ ማሰብ ማለት ነው፡፡ በመጀመሪያ ከራሳችን ጋር ከታረቅን ለብሔራዊ እርቅ የሚያስፈልገን የበሰለ ውይይት ብቻ ነው፡፡ ይኼ ሲሆን አሁን ወደ መስመር መግባት የማይችሉ ሥልጣንንና ገንዘብ ብቻ ግብ አድርገው የሚንቀሳቀሰ ሁሉ በሒደት ጊዜያቸውንና ዕድሜያቸውን ጨርሰው ይወገዳሉ፡፡ ለመሆኑ አስታራቂዎቹ ከተቃዋሚዎቹና ከመንግሥት ይኼን መካከል መንገድ ላይ የመገናኘት መፍትሔ ይቀበሉት እንደሆነ  ባደረጉት ጥናት ያገኙት ፍንጭ አለ? የአስታራቂነትና የአማላጅነት ሚና ስለሚለያይ እንዳይቀላቀሉ፡፡

ለማጠቃለል ያህል ስለአማላጅነት አንድ ትዝብት እነሆ፡፡ ደርግ ከሚታወቅባቸው መለያ ባህሪያቱ ዋናዎቹ ጭካኔውና ነፍሰ ገዳይነቱ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አዋቂዎች፣ ወጣቶችና ለጋ ሕፃናት ከየቤታቸው እየተጎተቱ ተወስደው ያለፍርድና ያለበቂ ምክንያት ተረሽነዋል፡፡ ይኼም ብቻ ሳይሆን ሬሳቸው በየአደባባዩና በየጥሻው ተጥሎ ወላጆች ልጆቻቸው የተገደሉበትን የጥይት ዋጋ እየከፈሉ እስከሬናቸውን ከየቦታው ለቅመዋል፡፡ መንግሥት የሚባሉ ሰዎች ይኼን ሲፈጽሙ ለማስታረቅ ወይም ለማውገዝ የቃጣው አንድም የሃይማኖት መሪ አልነበረም፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በአደባባይ የጣሊያንን መንግሥት አውግዘው በአደባባይ የሞቱት የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ እልቂት ምናልባት ከዚህ ባነሰ የተፈጸመውን አይተው ነው፡፡

ደርግ ይኼን ሁሉ ግድያ እየደጋገመ ሲፈጽም እንኳን ማስታረቅ ወይም ማውገዝ ቀርቶ፣ በየሰንበቴው ቤት ያማው የሃይማኖት መሪ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ዳግማዊ አቡነ ጴጥሮስ ያስፈልጉን ነበር፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ በአራት ኪሎ ሥላሴ ወይ በአራዳ ጊዮርጊስ ንግሥ ላይ ደርግን አውግዘውና ገዝተው እዚያው አራዳ ጊዮርጊስ በአቡነ ጴጥሮስ ሥፍራ መስዋዕትነት ይከፍሉ ነበር፡፡ ያን ቢፈሩ እንኳን እርቅ ለማውረድ ይሞክሩ ነበር፡፡ ታዲያ ይኼን ስናስብ አቡነ ጴጥሮስ ከሃይማኖት ግዴታቸው ይልቅ የአርበኝነት ባህሪያቸው በዝቶ ነው ያን የጀግንነት ውሳኔ የወሰኑትና የተሰውት ያሰኛል፡፡ የሚገርመው ነገር እነዚህ ወንጀለኞች በሕዝብ ላይ ያን ሁሉ ጭካኔ ሲሠሩ ለማስታረቅና ወንጀሉን ለማስቆም ሳይሞከር፣ ወንጀለኞቹ በሕግ የተወሰነባቸውን ቅጣት እንዳይቀበሉ አማላጅ ሁነው ቤተ መንግሥት መግባታቸው ነው፡፡ በእርቅ ጉዳዮችን ከጥፋት ለማዳን መሞከር አንድ ጉዳይ ሆኖ ወንጀለኛ አይቀጣ ብሎ ማማለድ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

     ኸኼሐኼ

Standard (Image)

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 31 ሲፈተሽ

$
0
0

 

 

     በዘለቀ ገብረሐና

1.መንግሥታዊ የፖለቲካ ሥልጣን የመያዝ ጉዳይ

ይህ  ነጥብ  በዓለም  ታሪክ  ውስጥ  ለጦርነቶች  መንስዔ፣ ለሰው ልጆች  የጅምላ  ጭፍጨፋ፣ የዘር ማጥፋት  ተግባሮች፣ ለስደት፣ ለረሃብና ለእርዛት  በማጋለጥ በድምሩ  ለሰው ልጆች  እልቂትና  ንብረት መዉደም ዋናው ምክንያት ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ ለወደፊቱም በቀላሉ የሚቀር ጉዳይ አይሆንም፡፡

1.1.መንግሥታዊ  የፖለቲካ  ሥልጣን  የመያዝ  አካሄድ  በኢትዮጵያ

ረጅም ዘመናትን ወደኋላ  ብንቆጥር መንግሥታዊ  የፖለቲካ ሥልጣን  ለመያዝ  በኢትዮጵያ  ሲደረጉ  የነበሩ  ሁኔታዎችን  በአጭሩ  ስናስቀምጥ፣

          -በዘር ሐረግ (በንጉሣዊ  ዘር)

          -በኃይል (በጦርነት) ነበር፡፡

መንግሥታዊ  የፖለቲካ ሥልጣንን  ለሕዝቦች  ተጠቃሚነት (ዴሞክራሲያዊ) ለማድረግ የፖለቲካ  ትግል ለማካሄድ  ለሚነሱ ዜጎች ወቅቶቹ  ምቹ ስላልነበሩ፣ ዜጎች ለትግላችን ያመቸናል ያሉዋቸውን አማራጮች ማለትም  በአካባቢ ስም፣ በብሔር ስም፣  ወዘተ በመደራጀት ረጅምና እልህ አስጨራሽ ትግሎችን አካሂደዋል፡፡ በዚህም  ምክንያት  አገራችን ቁጥር ሥፍር የሌላቸውን የውድ ዜጎቿን ሕይወት መስዋዕትነት  ከፍላለች፡፡ ዳሩ ግን  የታሰበውን  ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት  በኢትዮጵያ ማስጀመር ተችሏል፡፡

     የትግሎቹ ዋና ዋና ዓላማ  ከሚባሉት ውስጥ የአርሶ አደሩ የመሬት ይዞታ ጥያቄ በአስተማማኝ ሁኔታ መፍትሔ አግኝቷል፡፡

       የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጉዳይም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ላይ በተሟላ ሁኔታ በመቀመጡ ጠቃሚ ውጤት ተገኝቶበታል፡፡ ምንም እንኳ ከጅምሩ እስካሁን ድረስ ተቃውሞ ባይለየውም፡፡ ይኼ አንቀጽ የብዙዎች ሥጋት እንደነበረው ለመበታተንም አላጋለጠንም፡፡ 

1.2  ከ1983 ዓ.ም  ወዲህ  ያለው  መንግሥታዊ  የፖለቲካ  ሥልጣን  አያያዝ

በተከፈሉት መስዋዕትነቶች  ዴሞክራሲያዊ  የሆነ  ሕገ መንግሥት  በኢትዮጵያ  ሲፀድቅ፣  ይኼን  መንግሥታዊ  የፖለቲካ  ሥልጣን  መያዝ የሚቻለው  በሕዝቦች ፈቃድ  በምርጫ  ውጤት መሠረት ብቻ  መሆኑ  ሲቀመጥ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች  መደራጀትም  በሕገ መንግሥቱ  በአንቀጽ 31 ላይ  እንዲህ  በማለት  ተደንግጓል

  ’’ማንኛውም ሰው ለማንኛዉም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው ሆኖም አግባብ ያለውን ሕግ በመጣስ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሠረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ  ድርጅቶች  የተከለከሉ  ይሆናሉ፤’’ ይላል፡፡

እንግዲህ ለዚህች አገር የመበታተን አደጋ ዋና መንስዔ ሊሆን የሚችለው አንቀጽ 39 ሳይሆን ይህ አንቀጽ 31 ሊሆን እንደሚችል፣ ቀጥሎ የተመለከቱትን ዝርዝር ሁኔታዎችን መመልከት በቂ ይሆናል፡፡

 

                                                                                                         

እንግዲህ ይህን አንቀጽ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ከማናቸውም ነጥቦች በላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊብራራ፣ መብትና ገደቦች  ሊቀመጡለት፣  ወይም አሟልተን  በማስቀመጥ  የአገራችንን  የወደፊት  የእልፍ ዘመናት የህልውና ማረጋገጫ ዋስትና  ማድረግ  ሲገባን፣  ዝም ተብሎ  ገደብየለሽ  መብት በመሰጠቱ  ወይም ክፍት  እንዲሆን  በመደረጉ  የችግሮቻችን ዋና መሠረት ሆኗል፡፡

 ገደብ አያስፈልግም የሚል ድምዳሜ ግን ግርድፍ አባባል ወይም ማስተዋል የጎደለው አመለካከት ከመሆን አያልፍም፡፡ ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲባል  ገደብ የለሽ ሥርዓት ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለሁሉም ነገር ልክ፣ መጠን፣ ገደብ፣ ሥርዓት አለው ወይም ሊኖረው ይገባል፡፡ የረጅም ዘመናት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤቶችም ቢሆኑ ሕገ መንግሥታቸውና ሌሎችም ሕጎቻቸው ልክና ገደብ አላቸው፡፡ የአገራችንም ሕገ መንግሥት አብዛኛዎቹ አንቀጾቹ ላይ፣ እንዲሁም ሌሎችም ሕጎቻችን ልክና ገደብ እንዲሁም ግዴታዎች አሉዋቸው፡፡

 ይህ አንቀጽ ግን ድፍን ተደርጎ  ያለገደብ መቀመጡ ሲታይ መቼም ሕዝባችን ሕግና ሥርዓትን እስካልጣሰ ድረስ በፈለገው ሁኔታ ይደራጅ ከሚል ቀና አመለካከት የመነጨ ወይም ገደብ ካስቀመጥን በሌሎች ዘንድ በመጥፎ ሁኔታ እንታያለን ከሚል ሥጋት የመነጨና እንዲሁ ለታይታ ወይም ለስም ብለን ያደረግነው ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳቱ አስተያየት ለሚሰጡን ሳይሆን ለእኛው ነው የዓለም አቀፉን በጎ በጎ ነገሮችን ተቀብለን በጋራ በሚያራምዱ ጉዳዮች አብረን መጓዝ  ብዙ ጥቅሞች  እንዳሉት ይታወቃል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በራሳችን መንገድ መጓዝ በብዙ መልኩ የጠቀመን ስለመሆኑ ብዙ ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ምንም ተባለ ምን አገራችንን የሚጠቅም ነገር መምረጥ የእኛ ኃላፊነት ይሆናል (በመገደብም ይሁን ነፃ በመልቀቅ)፡፡

ይህን ካላደረግን ለችግሮቻችን ሁሉ መሠረታዊ መፍትሔ የምናገኝበትን ጉዳይ አንፈልግም ብለን እንደወሰንን ልናውቅ ይገባል፡፡ እንኳን 60 እና 70 የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀርቶ ለምን ቁጥር ሥፍር የሌላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በየመንደሩ አይደራጁም? የእነሱን የመደራጀት መብት ሊነካ አይገባም፡፡ ውጤት ማምጣት እንደማይችሉ ብናውቅም ይህ መብታቸው ብቻ መከበሩ ይበቃናል ካልን ስለተለዋጭ የአገር የፖለቲካ አመራር፣ ስለሙስና መንሰራፋት፣ ስለመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ወዘተ ችግሮች ማውራት መፍትሔ የለውም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝቦች መብትና ተጠቃሚነትን ቁጥር ሥፍር በሌላቸዉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመቋቋም መብት ለውጠናልና፡፡

 2. የሕገ መንግሥታችን  አንቀጽ 31  ክፍት  በመደረጉ  ያጋጠሙ  ችግሮች

በመሠረቱ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ራሱን  ይወዳል፡፡ ይህን ባሕሪውን  ከግምት ውስጥ ሳናስገባ አንቀጹን ክፍት በመተዋችን በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ  የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድነትም ይሁን በተናጠል ከዚሁ የሰዎች ባሕሪ በመነጨ ሁኔታ ወጥነት ያለው አቋምና ጥንካሬ ይዘው መቀጠል የሚችሉበትን ዕድል  አሳጥቷቸዋል፡፡ የተጠናከረ አቋም ወይም አንድነት ኖሮአቸው ለዚህች አገር ጠቃሚ ነገር ለመሥራት ይበቃሉ ተብለውም ሊጠበቁ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እስከ ዛሬ በተጨባጭ  ያየነው እውነታ ስለሚመሰክር፡፡

 እስካሁን ባለው ሁኔታ ማናችንም የምንረዳው ነገር አለ (ከአዲሱ ሕገ መንግሥት  በኋላ ማለት  ነው) አብዛኛዎቹ  የፖለቲካ ፓርቲዎች   ለግል  ጥቅምና ዝና ፍለጋ  በተነሱ  ሰዎች  ሲቋቋሙ  እንደነበር  ከድርጊታቸዉ አይተናል፡፡ ነገር ግን  ምንም የገንዘብና ዝና ፍላጎት የሌላቸው አገራቸውን በእውቀታቸዉና በጉልበታቸው  ለማገልገል የተነሱ ዜጎች ነበሩ፡፡ አሁንም አሉ፡፡ ለወደፊቱም ይኖራሉ፡፡ ይሁን እንጂ  እነዚህ ጠቃሚ ዜጎች ትግሉን ብቻቸውን ከዳር ማድረስ ስለማይችሉ ከሌሎች ጋር አብሮ ለመሥራት ሁኔታው ግድ ስለሚላቸው ይህን ይፈጽማሉ፡፡ በሒደትም ዓላማቸውን በሚመለከት፣ ስላሉበት ሁኔታ፣ የወደፊት አቅጣጫ፣ ስለተፈጠሩ ስህተቶችና ምክንያቶቻቸው፣ እንዲሁም  መፍትሔዎቻቸውን  በማስመልከት  በሚደረግ ውይይትና  እንቅስቃሴ ውስጥ በሁሉም አባላት ዘንድ አንድ ዓይነት አቋም ላይኖር ይችላል፡፡ 

በመሆኑም  በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መተጋገል ይፈጠራል፣ ተጠያቂነትም ይመጣል፡፡ ነገር ግን ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የሚያግዝ በሕገ መንግሥቱ ወይም በሌሎች ሕጎች የተቀመጠ ጥብቅ ነገር ባለመኖሩ ምንም አቅም በሌለው የፖለቲካ ፓርቲው ደንብና መመርያ ላይ መመሥረት ግድ ይሆንባቸዋል፡፡  በዚህ ምክንያት  ቀድሞውኑ ለግል ጥቅምና ዝና ፍለጋ ብሎ የገባው አካል ተጠያቂነት ሲመጣበት ወይም ጥቅሙን የሚነካ ነገር ሲፈጠር አባላቱን በመበጥበጥ፣ በሌሎች ላይ መግለጫ በመስጠትና ሌሎች አላስፈላጊ ነገሮችን በመፈጸም ፓርቲውን ጥሎ እስከ መውጣት ይደርሳል፡፡ ወጥቶም አርፎ መቀመጥ የለም፡፡ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ወደ ማቋቋም ያመራል፡፡ ታዲያ ይህ ሁልጊዜ የምናየውና የማይቆም ጉዳይ ነዉ፡፡ ለዚህ ችግር ዋናው ምክንያት ደግሞ አንቀጹ ክፍት መደረጉ ነው፡፡

ኢሕአዴግም ቢሆን ሥልጣን ላይ በመሆኑ እንጂ በዚህ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ልክ እንደ ጫካዉ ትግል አብሮ የመጓዙ ሁኔታ አይሳካለትም ነበር፡፡ መበጣበጡ፣ ፓርቲውን ጥሎ ወጥቶ  ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋሙ ሁኔታ ፈታኝ ይሆንበት ነበር ፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ይህ ሁኔታ ገጥሞታልና፡፡ የጫካ ትግል ውስጥ በመበጣበጥ ከአባልነት መውጣትና ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ቀላል ተግባር አይደለም፡፡ አደጋው የከፋ ስለሚሆን፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ የግለሰቦች ጉዳይ ሳይሆን የአገር ጉዳይ መሆኑ እየታወቀ ነገር ግን ትኩረት ስላልተሰጠው የተፈጠረ ስህተት ነው፡፡ ለመሆኑ እኛ ምን የተለየ ነገር ስላለን ነዉ 60 እና 70 አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚኖሩን? እውነት ለአገራችን ይህን ያህል አማራጮች ያስፈልጋታል? እነ አሜሪካ ሁለትና ሦስት አማራጮች ብቻ እንዲኖራቸው ያደረጉት የእኛን ያህል ግንዛቤና የዴሞክራሲ እውቀት  ስለሌላቸው ነው? እነዚህ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነን በማለት የተቋቋሙት  አብዛኛዎቹ በዓላማ ወይም በፕሮግራማቸው ይዘት የተለያዩ ሳይሆኑ፣ ከግል  ጥቅማቸውና ዝና ፍለጋ ጋር በተያያዘ ያቋቋሙዋቸው ናቸው ለዚህም ነው አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ከተቀሩት የፖለቲካ  ፓርቲዎች የሚለይበትን ተጨባጭ ነጥብ  ማቅረብ ቀርቶ  የፓርቲዎችንም ስም እንኳ ጠንቅቆ መግለጽ የማይችለው፡፡

 ስለዚህ አንቀጽ 31 ለይስሙላ  የተዘጋጀ  በመሆኑ  ምንም ነገር ማሳካት  አይችልም፡፡ ይልቁንም ያሳካው አንድ ትልቅ ነገር አለ፡፡ እሱም በዚህ አንቀጽ ምክንያት በአገሪቱ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ እየተቆጠረ ነገር ግን ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስም ብቻ ይዘን ገዢው ፓርቲ ያለ ተቀናቃኝ  ተደላድሎ  እንዲቀጥል ዕድል ፈጥሮለታል፡፡ ሕዝቡም  አማራጭ  የሚያገኝበት ዕድል በዚህ አንቀጽ ዝግ ሆኖበታል፡፡ ምክንያቱም ይኼ አንቀጽ ሽባ ያደረጋቻውና የውስጥ ትግል የማይታይባቸው እንዲሁ አሉ ሲባሉ የሚበተኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አምኖ አገሩን እንዲመሩ መስጠት አስቸጋሪ ስለሚሆንበት፣ እያዘነ ገዢው ፓርቲ አገርን የሚዘርፉ ኃላፊዎችና አባላቶቹን ይዞ እንዲቀጥል ከማድረግ የተሻለ አማራጭ አጥቷል፡፡

 ይህ ሁኔታ ውሎ አድሮ ጠቅሞናል የሚሉትንም ጨምሮ አገሪቱን ከማትወጣበት አደጋ ውስጥ ሊከታት እንደሚችል በቅርቡ ያየነው አዝማሚያ ሊያስተምረን ይገባል፡፡ በዚህ ላይ አንድ ግልጽ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይህ አንቀጽ 31 በተሟላ ሁኔታ ተዘጋጅቶና  ገደቦች ተቀምጠውለት ቢሆን ኖሮ አገራችን እስካሁን ከመጣችበት አካሄድ እጅግ በተሻለ ሁኔታ በተራመደች ነበር፡፡ ምክንያቱም  ኢሕአዴግ ይህ ገደብ ቢኖር ኖሮ ተጠንቅቆና በርትቶ በመሥራት አሁን ከሚያስወቅሱት ጉልህ ጥፋቶች ፀድቶ በዓለም ላይ ስሙ ገናና የፖለቲካ ፓርቲ ይሆን እንደነበር አልጠራጠርም፡፡ ምክንያቱም እስካሁን ባለው ሁኔታ ምንም የሚፈራው ነገር በሌለበት የሠራቸው አርዓያነት ያላቸው ሥራዎቹን መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፡፡

 3. ጠንካራ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ                                                                                                

ጠንካራ ወይም አንድነታቸውን የጠበቁ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች  እንፈልጋለን፡፡ ለምን አይኖሩም የሚለው በየመድረኩና በየቦታው የሚነሳው ተደጋጋሚ ፍላጎትና ጥያቄ የማን ነው? ከገዢው ፓርቲ በስተቀር የሰፊው ሕዝባችን፣ የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተለያዩ አገሮች ተወካዮች፣ ወዘተ መሆኑ ሁላችን የምንስማማበት ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ ለምን ጥያቄያችንና ፍላጎታችን ለረጅም ዘመናት  ሳይመለስና ሳይሟላ ቀረ? መልሱ አንቀጽ 31 የፈጠረብን ጣጣ ነው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራን እስከ ዛሬ ድረስ በዚህ አንቀጽ ላይ ምንም ነገር አለማለታቸው  እንቆቅልሽ ነው፡፡ አንቀጹ ካልተሻሻለ በስተቀር ለህልውናችን እጅግ አደገኛ ነገር መሆኑን  ልንረዳ ይገባል፡፡ የውጫሌው ስምምነት አንቀጽ 17 እንኳ በውስጡ የደበቀውን አደገኛ ነገር አያቶቻችን በጋራ ተሠልፈው በመስዋዕትነት አስተካክለውታል፡፡ ይህ አንቀጽ 31 ግን ለችግሮቻችን በጋራ እንዳንቆም የሚያደርገን ውስጡ በመርዝና በእሳት የተሞላ ስለሆነ አሳዛኝ ነው፡፡

    ለረጅም ዘመናት ስናየው የነበረና አሁንም ያለ ለወደፊቱም አንቀጹ ካልተሻሻለ በስተቀር  የሚቀጥል  የአማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታ፣

        -እገሌ የሚባል  የፖለቲካ ፓርቲ በዚህ አካባቢ ውጊያ ጀመረ፣

  - በውጭ አገር እነ እገሌ የተባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቋቋሙ፣

  -አገር ውስጥ ይህን ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎች  ተቋቋሙ፣ ተወሀዱ፣ ተለያዩ፣ ተካሰሱ፣ ፈረሱ፣….

   -መንግሥት እገሌ ከሚባል የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ተደራደረ፣

    እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚነዙትና በሚያደርጉት ድርጊት የአገሪቱ ሰላምና አንድነት አደጋ ላይ የሚወድቅበትን ሒደት በመስማትና ግራ በመጋባት  ከማሳለፍ የዘለለ፣ ይህች አገር በአንቀጽ 31 የተጠቀመችው ነገር የለም፡፡ ለወደፊቱም  አይኖርም፡፡ በተጨማሪም ምንም ያህል የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገብን ብንጓዝም፣ ይህ አንቀጽ በሚሰጣቸው ክፍተት የሚጠቀሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚፈጥሩት ጣጣ  የተገኘው ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዳልነበረ የሚደረግበትና ወደኋላ  የመመለሳችን  ሁኔታ  ክፍት ነው፡፡ 

  4.   የፖለቲካ  ፓርቲዎች እንዴትና በምን ሁኔታቢደራጁ ነው አገራችን ዘላቂ ዋስትና የሚኖራት?

አገራችን  በሰላም ጎዳና ዕድገቷን እያስቀጠለች ለመሄድ መንግሥታዊ የፖለቲካ ሥልጣን የሚያዝበት ሁኔታ ከጥንስሱ እስከ ፍፃሜው ድረስ ያሉት ወይም መኖር የሚገባቸው ዝርዝር ሁኔታዎች ተመቻችተው በሕገ መንግሥቱ ላይ ባልተቀመጡበት  ሁኔታ  አገር  ሰላም ሆና ትቀጥላለች ማለት  ቀልድ ይሆናል፡፡

    የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲታሰቡ (ይህ አንቀጽ ከተሻሻለና በዚያ መሠረት የሚቀርቡትን  ለማለት ነው) ምትክ ወይም አቻ የማይገኝላቸው  የአገሪቱ የወደፊቱ ዕጣ ፋንታ ወሳኞች ወይም የህልውና መሠረቶች ወይም የዴሞክራሲ አቅጣጫ ቀያሾችና መሪዎችን ምናገኝባቸው ተቋማት መሆናቸውን፣ እያንዳንዱ ዜጋ አውቆ ከማንኛውም ተቋም በማስበለጥ እንደ ዓይኑ ብሌን  ሊጠብቃቸውና ሊንከባከባቸው ይገባል፡፡

     እስካሁን ካለው ሁኔታ የተገነዘብነው ነገር ቢኖር ግን አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች  ከእነርሱ ሥራና አስተሳሰብ በስተቀር እዚህ ምድር ላይ የተፈጠረ ሰው ሁሉ የሚሠራው ሥራም ሆነ አመለካከቱ ስህተት ነው ብለው የሚያስቡ፣ በአፈጣጠራቸው  ወይም በአስተሳሰባቸው ቀና አሳቢነት ጭራሹኑ ያልተፈጠረባቸው ሰዎች የሚሰባሰቡባቸው ነው፡፡ ታዲያ አንቀጹን በማሻሻል ለእነዚህ ዓይነቶቹ የማይመች አሠራር መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡ በሕዝባችን ተጠቃሚነትና በብዙኃን ሐሳብ የበላይነት ለሚያምኑ ሰፊ ዕድል መፈጠር አለበት፡፡

5.  በሕገ መንግሥቱ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሚመለከት ቀጥሎ ያሉት ጥብቅ  የሆኑ ነጥቦች  ጥናት ተደርጎባቸውና በሕዝቡ ውሳኔ  ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው አካሄድ መሠረት ሊካተቱ ይገባል                                                                                                                 

  • ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የገባች አገር ከመሆኗም በተጨማሪ የብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት  በመሆኑም  ሕገ መንግሥታችን ዜጎቻችን  በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ተዘዋውረው የመሥራት፣ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብት እንዳላቸው  ደንግጓል፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ መንግሥቱን  አክብሮና አስከብሮ የአገሪቱን አንድነትና ሰላም  አስጠብቆ መምራት የሚችለው  ኅብረ ብሔራዊ አመለካከትና አደረጃጀት ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ መሆን ስለሚገባው በብሔር ስም፣ በአካባቢ ስም፣ ወይም ሌሎች  አምባገነናዊ  ስያሜዎችን  መሠረት በማድረግ  የፖለቲካ ፓርቲን  ማቋቋም  ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ ፈፅሞ የማያስፈልጋት መሆኑን  ታሳቢ በማድረግ፣  ለአገራችን የሚያስፈልጉ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛትና ስያሜ  በሕገ መንግሥቱ ላይ  መሥፈር እንዳለበት፣
  • መንግሥት እንደ ሌሎቹ መንግሥታዊ ተቋማት በሕገ መንግሥቱ ላይ ለሠፈሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋና መሥሪያ ቤታቸውንና በየክልሉ ቅርንጫፍ  ጽሕፈት ቤቶችን  ገንብቶ ወይም  በኪራይ  እንደሚያቀርብ፣
  • መንግሥት  በጀት እንደሚመድብ፣ 
  • የበጀት አጠቃቀማቸው በሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ቁጥጥር  እንደሚደረግበት፣   
  • በእነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አባል የሆነ ሰው በፓርቲው የውስጥ ደንብና መመርያ መሠረት ወይም በራሱ ፍላጎት ከፓርቲው ከተሰናበተ ዳግመኛ  በየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ አባል የመሆን ዕድል የማይሰጠው ስለመሆኑ (ይህ ነጥብ የሚያስፈልግበት ዋናው ምክንያት ለአገሪቱ ጥቅም እታገላለሁ ያለ አካል  በሕገ መንግሥቱና  በፓርቲው የውስጥ አሠራር መሠረት በፓርቲው ውስጥ  ትግሎችን በማካሄድ ዓላማን ማሳካት  ይጠበቅበታል፡፡ ችግሮች ካጋጠሙም  በእነዚሁ አሠራሮችና  ሕጎች  መጠቀም አለበት፡፡ ከዚያ ያለፈ ነገር ከሆነና ከፓርቲው መሰናበት ግድ ከሆነ  ከአንዱ ወጥቶ  ሌላው ዘንድ በመሄድ  ተመሳሳይ  ችግሮችን  የመፍጠር  ዕድልን  ዝግ  ማድረግ  አስፈላጊ  ስለሚሆን ነው)፣ ይህም ሲጠቃለል  ባሉበት ጠንክሮ  መተጋገልና  ዓላማን  ከግብ ማድረስን ያጠናክራል፡፡ ካልተሳካ ደግሞ አርፎ  መቀመጥን  ግድ ማለት ስላለበት ነው፡፡
  • የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠሪነት  በግልጽ  ሊሠፍር  ይገባል፡፡                                                                
  • ገዢዉ ፓርቲም ይሁን ሌሎች አካላት በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ  ወይም በአባላቶቻቸዉ ላይ  ስለሚያደርሱት ጫና  የሕገ መንግሥቱ  ከለላ እንዳላቸው  በግልጽ ሊቀመጥ ይገባል፡፡                                                                   
  • በሕገ መንግሥቱ  ላይ ከተቀመጡ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጪ በአገሪቱ ውስጥ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም የማይፈቀድ መሆኑን፣ በውጭ አገር ለኢትዮጵያ ብለን የፖለቲካ ፓርቲ  አቋቁመናል  ወይም እናቋቁማለን  ከሚሉ  ጋር አባል መሆን ወይም መተባበር ወይም  ድጋፍ መስጠት  የማይቻል ስለመሆኑ፣                                                           
  • እነዚህ ሁሉ የሚያስፈልጉበት ዋናው ምክንያት የፖለቲካ ፓርቲዎች  የአገር አለኝታነታቸው እየተዘነጋ እየተዋከቡ የግለሰብ ቤት  በመከራየትና በበጀት እጥረት ይህን አገራዊ ጉዳይ በአባላት መዋጮ ብቻ ይወጡ ማለት  ፈጽሞ ተገቢ  ስለማይሆን፣ በተረጋጋ  ሁኔታ ጽሕፈት ቤቶችና  በቂ  በጀት ኖሮአቸው ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች  በመቅጠር  በማንኛውም  የሥራ ዘርፍ ላይ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሥራ በማከናወን ለፖለቲካ አመራር ብቃት ያለው ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግና  ብቃት ያላቸውን የፖለቲካ መሪዎች ማግኘት እንዲያስችለን ነው፡፡ እስኪ አንድ ምሳሌ እንውሰድ፡፡ መንግሥት ለተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንድሁም ለዕምባ ጠባቂ፣ ለሰብዓዊ መብት፣ ለሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና፣ ወዘተ ከበጀት ጀምሮ  ማንኛውንም አስፈላጊ ነገሮችን እንደሚያሟላላቸው የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ዳሩ ግን እነዚህን መሥሪያ ቤቶች እንዲመሩ ዕድሉን ልንሰጣቸው፣ ምርጫ የሚጠባበቁ  የፖለቲካ  ፓርቲዎች  የተሟላ ቁመና ላይ እንዲደርሱ ከጅምሩ አንስተን አስፈላጊውን ነገር ሁሉ አሟልተንላቸው ተንከባክበን ብናሳድጋቸው አገራችን ትጎዳ ይሆን? አንድ ሙሰኛ በመቶ ሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር የአገር ሀብት በሚዘርፍበትና አገራችንን ወደ ቁልቁለት ለማስገባት ሰፊ ጎዳና የያዘበትን ሒደት እያየን ዝም እንድንል የሚፈልጉ የአዛኝ ቅቤ አንጓቾች እንዴት ተደርጎ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ይህ ሁሉ ነገር ይደረግላቸዋል  ማለታቸው የማይቀር ነው፡፡ በመሆኑም እነርሱኑ ተከትለን ይህ ሳይደረግ  ይቀርና በሚፈጠሩ ቀውሶች  የዜጎቻችን  ሕይወት ይጠፋል፣ ንብረት ይወድማል፣ አገር  ሰላም ታጣለች፡፡ ስለዚህ በአሠራርና በገንዘባችን የወደፊቱን ጉዞአችንን ማሳመር  እየቻልን ለአደጋ የሚያጋልጠንን  መንገድ መከተል ለምን አስፈለገን?                                                     
  1. ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱትን በመከተል ፈጸምን ማለት አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ማንኛውም መንግሥታዊ ተቋም በሕገ መንግሥቱ  የተረጋገጠ  ጽሕፈት ቤትና  በጀት  ስለሚኖራቸው፣ ገዢው የፖለቲካ ፓርቲ  ወይም የፖለቲካ ፓርቲው አባላት ወይም ማንም እንዳስፈለገው እየተነሳ የሚያዋክባቸውና የሚያፈርሳቸው አይሆኑም፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥታዊ ናቸውና፡፡ በውጤቱም  አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደምናገኝ አረጋገጥን ማለት ነው፡፡ ይህ ሲሆን የጫካ የፖለቲካ ትግል  እንዲያከትም፣ ለብጥብጥና ሁከት የምንጋለጥበት ሁኔታ እጅግ ውስን  እንዲሆን የሚያደርግና ሕዝቡ ካሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የትኛው ይሻላል ከማለት ውጪ  ኃላፊነት ለመስጠት የሚቸገርበት ሒደት ያበቃል ማለት ነው፡፡

     ይህን ነጥብ ለማጠቃለል ያህል ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች መሠረት  የሚደራጁ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገር ያላቸው ጠቀሜታ ከማንኛውም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ወይም  መንግሥታዊ  ተቋም ያልተናነሰ ወይም የሚበልጥ መሆኑን ልንጠራጠር  አይገባም፡፡   

ወደ ማጠቃለያ ከመሄዴ በፊት አንድ በጣም አስፈላጊ ነገር መጥቀስ ተገቢ  ነው ይኸውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ አስቀድሞ መበላሸቱን የሚያውቀዉ ገዢው  የፖለቲካ ፓርቲ ማንም የፖለቲካ ፓርቲ  ጠንከሮ  በመገኘት ሊተካው  እንደማይችልና  የሚቆጣጠረውም አካል አለመኖሩን ስለሚያውቅ፣ የፈለገውን አሠራር በመከተሉ በቀላሉ ሊፈታው ከማይችልበት  ችግር  ውስጥ  ገብቷል፣ የሙስና ጉዳይ፡፡                                                                                                                                                   

      ለብዙ ነገሮች የዓለም ምርጥ ተሞክሮዎችን  እያመጣ ተግባራዊ  በማድረግ የሚታወቁው ኢሕአዴግ ለሙስናውም መፍትሔ ጠፍቶት አይደለም ዙሪያ ጥምጥሙን የሚዞረው፡፡ የቸገረው ነገር እንዳለ እንውቃለን፡፡ እሱም ሳይገምተው ቀስ በቀስ የራሱ አባላትና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሙስና ውስጥ በመዘፈቃቸውና የሙስናው ኔትወርክ እጅግ በመስፋቱ የተነሳ፣ ማን ማንን ተጠያቂ እንደሚያደርግ ግራ ስለገባው ነው፡፡ በሌላ ወገን ‹‹ደግሞ ሙስናን የሚጠየፍ ዜጋ እንፈጥራለን›› ተብሎ ሲገለጽ እንሰማለን፡፡ ይህ አባባል ግን የፌዞች ሁሉ ፌዝ ነው፡፡ ምክንያቱም ሙሰኛው በዚህች አገር ውስጥ እንዴት የተንደላቀቀ ኑሮ እንደሚኖር፣ የሚያፈራቸው ሀብቶች (ትልልቅ ሕንፃዎች፣ ፋብሪካዎች፣ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች፣ በየወቅቱ  የሚቀያየሩ  ውድ ተሸከርካሪዎች፣ ወዘተ) በተለያዩ  የዓለም ውድና እጅግ ዘመናዊ በሆኑ ከተሞች በመዝናናት አብዛኛውን ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ፣ ዘመዶቻቸውም በዚሁ ሁኔታ ተንደላቀው እየኖሩና ማንም የሚነካቸው ስለሌለ ሌላው ዜጋ እንደ እነርሱ ለመሆን መንገዱን በየት ባገኘሁት በሚልበት አገር ውስጥ፣ ሙስናን የሚጠየፍ  ዜጋን  እንፈጥራለን ማለት ሕዝቡን አላዋቂ ማድረግ ነው፡፡

   ለምሳሌ ሌብነት በሳዑዲ ዓረቢያና  በቻይና ሙስናን እንመልከት፡፡ መፀየፍ የሚኖረው እንደዚያ ዓይነቱ ዕርምጃ ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ ሁሉ ችግሮቻችን ጠንካራ አመራር የምናገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታ መፍትሔ ካገኘ ብቻ ነው፡፡

ማጠቃለያ

 ለዚህች አገር የወደፊት ዕጣ ፋንታ የዜግነቴን ግዴታ ልወጣ የሚል ማንኛውም ዜጋ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ በግልም ይሁን  በተደራጀ መልኩ ይህ የሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 31 በሚሻሻልበት ሁኔታ ላይ ቁርጠኛ አቋም ይዞ ሊታገል ይገባል፡፡ አሁን ባለው አካሄድ መቀጠል ማለት ግን መንግሥታዊ የፖለቲካ  ሥልጣን ለመያዝ አፈር ድሜ ትበላለህ፣ አንተን በተራህ ከሥልጣን የሚያወርድህ  አካል አፈር ድሜ በልቶ ያወርድሃል፣ ከወረድክ በኋላም አፈር ድሜ  ትበላለህ፣ አገርም ቁም ስቅሏን ታያለች (እንደ አገር መቆየት ከቻለች)፡፡ ይህ የማይቆም ሒደት ይሆናል ማለት ነው፡፡

እናንተ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን የፖለቲካ መስመር  ለአንዴና  ለመጨረሻ  ጊዜ  የምታስተካክሉበት  ቁልፍ  አሁንስ  አይታያችሁም?

እስኪ እባካችሁን እስከ ዛሬ ድረስ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ትክክል ነው ብላችሁ የተጓዛችሁበትና ዘመናት ያስቆጠራችሁበትን የፖለቲካ መንገድ ባለበት ደረጃ አንዴ ቆም በማድረግ፣ መንግሥታዊ የፖለቲካ ሥልጣን የሚያዝበት ቁልፍ በኢትዮጵያ  ሕዝብ እጅ እንዲገባ አንድ ሆናችሁ ታገሉ፡፡

      በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አድዋ ጦርነት፣ እንደ ህዳሴዉ ግድብ፣ እንደ ሻዕቢያ ጦርነት፣ ወዘተ መቶ በመቶ ከጎናችሁ ይሰለፋል፡፡

እሰኪ እነማን ተነሳሽነት ወስደው ይህን አገራዊ ጉዳይ መስመር እንደሚያስይዙት ይታያል፡፡ ይህ ሰነድ  በተቻለ መጠን ለሁሉም አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች  እንዲደርስ  ይደረጋል፡፡

ከዚያ በኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴትና በምን ሁኔታ መደራጀት እንዳለባቸው  በኢትዮጵያ  ሕዝብና በሕገ መንግሥቱ ላይ ይወሰናል፡፡ በዚህ  ነጥብ  ላይ የምትወስዱት ዕርምጃ እውነት ለአገራችሁ የምታስቡ መሆን አለመሆናችሁ የሚረጋገጥበት ነው እንደ ሌላው ጉዳይ ዙሪያ ጥምጥም ለመሄድ ዕድል የሚሰጥ  ባለመሆኑ፡፡

አመሰግናለሁ!  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው zelekehabtae@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

       

     

 

 

 

Standard (Image)

ነጠብጣቡን ማገናኘት... ቋጥኙ ውስጥ ፈረሱ መኖሩን እንዴት አወቁ?

$
0
0

በእስክንድር ከበደ

እ.ኤ.አ በጁን 24 ቀን 1812 የፈረንሣዩ ታላቁ ናፖሊዮን 610,000 ወታደሮችን ይዞ ሩሲያን ለመውጋት ወደ ሞስኮ ሲያመራ ወቅቱ በጋ ነበር፡፡ የታላቁ ናፖሊዮን ጦር ሞስኮ ከመድረሱ በፊት የሩሲያውያኑን ጦር ወራሪው ጠላት እንዳይጠቀምባቸው ሰብሎቻቸውንና መንደሮቻቸውን አጋይተው አፈገፈጉ፡፡ ናፖሊዮን ከ500 ሺሕ በላይ ወታደሮቹ አልቀው ወደ 100 ሺሕ ቀሩ፡፡ ቀሪዎቹም ከሞስኮ ሲያፈገፍጉ አሰቃቂ እልቂት ገጠማቸው፡፡ ፈረንሣዮች ለሽንፈታቸው በሩሲያ አየር ንብረት አሳበቡ፡፡ ዳኒስ ዴቪዶቭ እ.ኤ.አ በ1835 ባሳተሙት መጣጥፍ  “Was it frost who devastated the French Army in 1812?" (በ1812 ዓ.ም የፈረንሣይ ጦርን ያሸነፈው የሩሲያ አመዳይ (ውርጭ) ይሆን?) ብሎ ይጠይቃል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግል ከሚተርኩ በርካታ የጥበብ ሥራዎች አንዱ እ.ኤ.አ በ1992 የተሠራው ‹‹ሳራፊና›› የተሰኘው ፊልም ይጠቀሳል፡፡ ይህ ፊልም የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግል በአፓርታይድ ዘመን የሕዝቡን ያልተነገረ ትግል ያስቃኛል፡፡ ያልተነገረውን የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ትግል በጨረፍታ የሚስቃኘን ይህ ፊልም በታሪክ የመማሪያ መጻሕፍት አቀራረብ መጠናት ያለበት መሆኑን ይጠቁመናል፡፡

ፊልሙ ውስጥ የምናገኛት የታሪክ መምህርቷ ገናናው ናፖሊዮን በሩሲያው ጦርነት የተሸነፈበትን ምዕራፍ እያስተማረች ነበር፡፡ በዚህ የታሪክ መጽሐፍ ምዕራፍ ናፖሊዮን የተሸነፈው ‹‹በሩሲያ ነጭ ክረምት›› መሆኑን ነበር፡፡ መምህርቷ በመማሪያ መጽሐፉ የቀረበውን ምክንያት በመቀየር፣ ‹‹የናፖሊዮን ጦር የተሸነፈው በሩሲያ ሕዝብ እንጂ በሩሲያ ክረምት አይደለም፤›› ብላ ስታስተምር በመስኮት የተመለከታት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ከትምህርት ቤቱ እድትባረር ያደርጋል፡፡ አዲሱ የታሪክ መምህር ትምህርቱ ካቆመበት ሲጀመር ይህንን ምዕራፍ ማስተማር ይጠበቅበት ነበር፡፡

''የናፖሊየን ጦር እንዴት ተሸነፈ?''

''በሩሲያ ሕዝብ!''ሳራፊናና የክፍል ጓደኞቿ ምላሽ ነበር፡፡ ገናናው የናፖሊዮን በሩሲያ ባካሄደው ዘመቻ መሸነፉን በተመለከተ የቀረበው ምክንያት የሩሲያ ነጭ ክረምት መሆኑን ተማሪዎቹ ሊቀበሉት አልቻሉም፡፡ ተማሪዎቹ የሩሲያ ሕዝብን ጀግንነት ለማንኳሰስ ነው በሚል የቀድሞ መምህራቸው ያስተማረቻቸውን የታሪክ ዕይታ ይዘው ስለነበር ውዝግብ አስነሳ፡፡

''የናፖሊየን ጦር እንዴት ተሸነፈ?''የመምህሩ ጥያቄ፣

''በሩሲያ ሕዝብ!''የተማሪዎቹ ምላሽ፡፡

ናፖሊዮን በሳይንቲስትነት አይታወቅም፡፡ ግን ራሱን ያስተማረ የፈረንሣይ መሪ ነበር፡፡ በወታደራዊ መሐንዲስነት የሠለጠነ ሲሆን መጠነኛ የሒሳብ ዕውቀት ነበረው፡፡ እ.ኤ.አ በ1797 በፈረንሣይ ቅድመ አብዮት የሳይንስ ማኅበረሰብ በሆነው ብሔራዊ የሳይንስ ኢንስቲትዩት ለአባልነት ተመርጦ ነበር፡፡

ናፖሊዮን የፈረንሣይ ጦር በመምራት ግብፅን ለመውረር ሲነሳ አንድ ስጦታ ለማበርከት ነበር፡፡ ስጦታው ለፈረንሣይ ዘመናዊ ሳይንስን ማበርከት እንደሆነ ይነገራል፡፡  በጁላይ 1 ቀን 1798 ናፖሊዮን 400 መርከቦችና 54 ሺሕ ሰዎች ያሉት ሠራዊት ይዞ ግብፅን ወረረ፡፡ ናፖሊዮን 150 ሲቪል ሳይንቲስቶች፣ መሐንዲሶች፣ ጠቢባንና ምሁራን አብረውት የዘመቱት የግብፅን ምድር ለመያዝ ሳይሆን፣ የግብፅን ተፈጥሯዊናና ባህላዊ ታሪክ እንዲሁም አገር በቀል ዕውቀቶች ለመዝረፍ ነበር፡፡ በወቅቱ ወታደራዊ ዘመቻው ባይሳካም ሳይንሳዊና ምሁራዊ ተልዕኮው ከሚጠበቀው በላይ ስኬታማ እንደነበር ይነገራል፡፡

በጥንቃቄ የግብፅ ሥነ ምድር አቀማመጥ ተፈትሿል፡፡ አገር በቀል እንሰሳትና ዕፅዋት በሚገባ ተጠንተዋል፡፡ ማዕድናት ተሰብስበው በየፈርጁ ተደራጅተዋል፡፡ የአካባቢው ንግዶችና ኢንዱስትሪዎች በጥንቃቄ ተፈትሸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የግብፅ ጥንታዊ ቤተ መቅደሶችና መቃብሮች ሉክሰር፣ ፊሊያ፣ ዴንድራና የንጉሦቹ ሸለቆዎች ታውቀዋል፡፡ እነዚህ ቦታዎች በጥንቃቄ ተለክተው፣ ካርታ ተቀይሶላቸውና ተሠርቶላቸዋል  ተመዝግበዋል፡፡ የፈርኦን ምድር ከዚህ በፊት በማይታወቅ ሁኔታ በናፖሊዮን ባለሙያዎች ተጠንቷል፡፡ ከናፖሊዮን ጦር ጋር የዘመቱት ሳይንቲስቶች ግኝቶችን ዓለም እንዴት ማወቅ አለበት ? የሚለውን ጥያቄ አንስተው ቀድመው ምላሽ ሰጥተው ፈረንሣይ ግብፅን ከመወረሯ ስድስት ወራት በፊት የሳይንቲስቶቹ አቀራረቡን ወስነው መጥተዋል፡፡

ናፖሊዮን በዓባይ ላይ ባደረገው ጦርነት እ.ኤ.አ በ1798 መርከቦቹ ድባቅ በመመታታቸውን ሽንፈት አጋጠመው፡፡ ከናፖሊዮ ጦር የተረፉት ወደ ፈረንሣይ ተመልሰው እ.ኤ.አ በ1801 የሰበሰቡትን ቁሳቁሶች በማደራጀት ከዘጠኝ ዓመት በኃላ በ1809 የመጀመሪያዎቹን ቅጾች “Description de I’ Egypt” በሚል ርዕስአሳተሙ፡፡

በቀጣዮቹ ዓመታት እስከ 1828 ዓ.ም. በጠቅላላው 23 ቅጽ መጻሕፍትን አሳትመው ነበር፡፡ ከእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ሦስቱ ትላልቅ ቅጾች 43 ኢንች ርዝማኔ ነበራቸው፡፡ የግብፅን ባህል የሚያንፀባርቁ በጠቅላላው 837 አስገራሚ ቅርፃ ቅርፆችን ፈረንሣይ ወስዳ ነበር፡፡ ከእነዚህ የመጻሕፍት ቅጾች ጥንታዊ ቅርሶች፣ ግዙፍ ሐውልቶች፣ ቤተ መቅደሶች፣ ሲፊኒክስና ሁሉም ዓይነት የጥበብ ሥራዎች የታተሙባቸው ነበር፡፡ የተፈጥሮ ታሪካዊ ሀብቶች አስገራሚ ነበሩ፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ ዕፅዋትና አዝዕርቶች ተጠንተዋል፡፡ አዞ፣ መርዛማ እባቦች፣ የባህር ውስጥ ዕፅዋቶችና የዘንባባ ዛፍ ዝርያዎች ሳይቀሩ ተወስደው በመጻሕፍቱ ውስጥ ተካተው ለንባብ በቅተዋል፡፡

 

በግብፅ ሥልጣኔ ውስጥ የዓባይ ወንዝ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ የግብፅ ሕዝብን የዕውቀት ማዕከል ስናነሳ አሌክሳንደሪያ ቤተ መጻሕፍት ይወሳል፡፡ በጥንታዊ ዓለም ትልቁ ቤተ መጻሕፍት ሲሆን፣ በዓለማችን የሚገኝ ማንኛውም መጻሕፍት እንዲኖር ይደረግ ነበር፡፡ አሌክሳንደሪያ የደረሰ መርከብ ውስጥ በቤተ መጽሐፍት ውስጥ ከሌለ መጽሐፉ ይወረስና እንዲገባ ይደረግ እንደነበር ይነገራል፡፡ በተለይ በክሊዮፓትራ ዘመን ቤተ መጻሕፍት የዓለም ዕውቀት መገኛ ማዕከል እንዲሆኑ ይደረግ የነበረው ጥረት አስገራሚ ነበር፡፡ የፈረንሣይ ግብፅን መወረር የሳይንስና የዕውቀት ዘመቻ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ ፈረንሣይ ግብፅን ከወረረች ሰባ ዓመታት በኃላ እ.ኤ.አ በ1868 በእንግሊዙ ሰር ጄኔራል ናፒር ፊታውራሪነት ወደ አቢሲኒያ ምድር የተደረገው ዘመቻ የተዘረፉት ተፈጥሯዊና ባህላዊ ሀብቶች፣ እንዲሁም አገር በቀል ዕውቀቶች ምን ነበሩ? አፄ ቴዎድሮስ ካሠሯቸው ሚሲዮናዊ ባለ እጆች (Missionary Artisans) በጨረፍታ ተመልክተን ነጠብጣቡን ለማገናናኘት እንሞክር እስቲ ....

ታዋቂው አፍሪካዊ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ታሪክ ናሺድ “Hidden Colors” (የተደበቁ ቀለማት) በሚል ርዕስ ዘጋቢ ፊልም እ.ኤ.አ. በ2011 ሠርቶ ለዕይታ አቅርቦ ነበር፡፡ የአፍሪካ ጥንታዊ ታሪክና የሥልጣኔዎቿ በምዕራብያውያን ‹‹ታሪክ›› ተመራማሪዎች መዛባታቸውን፣ በበርካታ መረጃዎችና ምሁራን ትንታኔዎች አስደግፎ ይተርካል፡፡ የአፍሪካ ገናና ሥልጣኔዎችን ይተርካል፡፡ የአፍሪካ ጥንታዊ ስም ኢትዮጵያ ይባል እንደነበረ.....የአትላንቲክ ውቅያኖስ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ተብሎ ይጠራ እንደነበር ያወጋል፡፡

የአፍሪካ የአሁኑ ስያሜ መላ አኅጉሪቱን የሚወክል ከመሆኑ በፊት እያንዳንዱ የአፍሪካ ክፍል የሚጠራበት የራሱ ስያሜ ነበረው ይለናል፡፡ በኃላ በአንድ ወቅት አኅጉሪቱን ተቆጣጥሮ በነበረ አፍሪካነስ በተሰኘ የሮማ ጄኔራል አህጉሪቱ ስያሜዋን እንዳገኘች ዘጋቢ ፊልሙ ይነግረናል፡፡

ይህ የታሪክ ፊልም በርካታ የአውሮፓ ሕንፃዎች የኢትዮጵያ ጥንታዊ የኪነ ሕንፃ ጥበቦች አሻራ እንዳረፈባቸው የአውሮፓ የታሪክ ተማራማሪዎችና የሚዲያ ተቋማት ሊነግሩን አይፈልጉም በማለት ይሞግታል፡፡ ይህ ዘጋቢ ፊልም አንድም ኢትዮጵያዊ የታሪክ ተመራማሪ በዋቢነት የቀረበበት አይደለም፡፡ በዚህ ዘጋቢ ፊልም ውስጥ በታሪክ፣ በአርኪዮሎጂ፣ በፍልስፍና፣ በባህል፣ በሥነ ልቦና፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ሙያዎች አንቱ የተሰኙ አፍሪካዊ አሜሪካዊያን ናቸው የተሳተፉት፡፡

“Hidden Colors” (የተደበቁ ቀለማት) ዶክመንተሪ ፊልምን የተመለከተ አውቃለሁ ብሎ የሚያስበው ታሪክ ላይ ትልቅ ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም፡፡ የአገሬን ታሪክ አሰብኩት፡፡ በእንግሊዝኛ የተማርናቸውን የታሪክ መጻሕፍት ወደኋላ መለስ ብዬ እንዳስባቸው አደረገኝ፡፡ ሴቫስቶፖል በደቡብ ምዕራብ በጥቁር ባህር ክራይሚያ ባህረ ሰላጤ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት አካል በኋላ ደግሞ የዩክሬን ግዛት ነበረች፡፡ ሩሲያ እ.ኤ.አ በ2014 መልሳ ወደ ግዛቷ አዋህዳታለች፡፡

የሴቫስቶፖል የሕዝብ ቁጥር 393,304 (እ.ኤ.አ በ2014 ሕዝብ ቆጠራ) ነበር፡፡  የቀድሞዋ ሶቪዬት ዛር የጥቁር ባህር ኃይል ዋና ምድብ ቦታ ናት ሴቫስቶፖል፡፡ “Siege of Sevastopol” (1854-1855) እ.ኤ.አ ከ1854 መስከረም እስከ መስከረም 1855 የክራይሚያ ጦርነት ተካሂዶ ነበር፡፡ ፈረንሣይ፣ ኦቶማን (የአሁኗ ቱርክ) እና ብሪታኒያ በኅብረት ከሩሲያ ጋር በሴቫስቶፖል ባህረ ሰላጤ የከበባ ጦርነት ለአንድ ዓመት አካሄዱ፡፡ አስጊው የሩሲያ ባህር ኃይል የጠላት ጦር ከበባውን ከማድረጉ በፊት የጦር መርከቦቹንና ሴቫስቶፖል መድፎቹን ባህር አስምጦ አፈገፈገ፡፡

ብሪታኒያ ከሴቫስቶፖል የማረከቻቸው መድፎች ገሚሱን ለወታደራዊ ተቋማት የሰጠች ሲሆን፣ መድፎቹ የተሠሩባቸው የብረት ማዕድናት ከየት የመጡ ናቸው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ከባድ ነበር፡፡ የሴቫስቶፖል መድፎችን አቅልጣ ብሪታኒያ ኒሻን በመሥራት ጀግኖቿን አሸቆጥቁጣበታለች የሚሉ መረጃዎች አሉ፡፡ የፈረንሣይና የብሪታኒያ መሐንዲሶች የከበባ መስመሮችን በመዘርጋት፣ የመከላከያ ምሽግ (ግድግዳ) በመገንባት፣ እንዲሁም መድፎችን በመሥራት ኃያሉን የሩሲያ ባህር ኃይል ገጥመው ብዙ ጉዳት ደረሰ፡፡

በሴቫስቶፖል በውትድርና የተሳተፈው ታዋቂው የሩሲያ ደራሲ ሊዎ ቶልስቶይ "Sebastopol Sketches"የሚል መጽሐፍ ጽፏል፡፡ የሩሲያ የመጀመሪያው ተራኪ ፊልም “Defence of Sevastopol” የታዋቂው እንግሊዛዊ ገጣሚ ሥራ " The Charge of the Light Brigade"ግጥም የሚተርከው ስለ ሴቫስቶፖል ነው፡፡ ሴቫስቶፖልን የሚያሳየው "The Thin Red Line"ሥዕል ታሪኩን ከሚዘክሩ የጥበብ ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ንጉሥ ለመውደቃቸው ከሚጠቀሱ ምክንያቶች የአውሮፓ ሚሲዮናውያንን  አስረው "ሴቫስቶፖል"የተሰኘ መድፍ እንዲሠሩላቸው ማድረጋቸው ነበር፡፡ እንደ ብሪቲሽ ኢምፓየር መረጃ ማዕከል እ.ኤ.አ በ1862 አፄ ቴዎድሮስ ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረጉ ጦርነቶች አገራቸውን ከጥቃት ለመከላከል የጦር መሣሪያዎችና ባለሙያዎች እንዲሰጧቸው ከጠየቋቸው አገሮች አንዷ ብሪታኒያ ነበረች፡፡ የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለንጉሡ ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጥ ዘገየ፡፡ ይባስ ብሎ የብሪታኒያው ቆንስል ካፒቴን ቻርልስ ካሜሮን ግብፅን ጎብኝቶ መመለሱ ንጉሡን ይበልጥ አስቆጣቸው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ቻርልስ ካሜሮንና ሌሎች የውጭ ዜጎችን አሰሩ፡፡

በወቅቱ ብሪታኒያን ገዢ ፓርቲዎች ገላድስቶንና ሌበር ነበሩ፡፡ ሁለቱም ፓርቲዎች የቅኝ ግዛት ጀብደኝነት ውስጥ መግባት ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ ፓርቲዎቹ ቸልተኛ ቢሆኑም ይህም ቸልተኝነታቸው ችግሩን እንዲፈጠር ማድረጉ ይነገራል፡፡ የቻርልስ ካሜሮን ለብሪታኒያ ፕሬስ በጻፈው ደብደቤ ከታጋቾቹ መካከል የብሪታኒያ ሴቶችና ሕፃናት እንደሚገኙበት የሚያትት ስለነበር፣ የብሪታኒያ ሕዝብ ዘንድ ጉዳዩ ተጋኖ እንዲደርስ ሆነ፡፡ በወቅቱ በብሪታኒያ አጠቃላይ ምርጫ እየተካሄደ መሆኑ ትንሹ ጉዳይ ጦዞ፡፡ በብሪታኒያ ሕዝብ ዘንድ መነጋገሪያ መሆን ቻለ፡፡ በተለይ የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ አባላት የምርጫ ዘመቻውን የቻሉትን ያህል ሊጠቀሙበት በመሞከራቸው ጉዳዩ ጦዞ ጦር እስከ መላክ ተደረሰ፡፡

የብሪታኒያው ጄኔራል ናፒር 13 ሺሕ የእንግሊዝና የህንድ ወታደሮች፣ 26 ሺሕ የካምፕ ተከታዮች፣ ዝሆኖችን ጨምሮ 40 ሺሕ ከብቶች ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ዘመተ፡፡ የብሪታኒያ ሠራዊት ከህንድ ቦምቤ ወደ ኢትዮጵያ 280 በእንፋሎት የሚሠሩ ቀዛፊ መርከቦች ተጠቅሞ ነበር፡፡ በቅድሚያ ከህንድ ተሳፍረው የመጡት የመሐንዲሶች ሠራዊት ሲሆን፣ በቀይ ባህር ዘይላ ከምፅዋ ወደብ በስተደቡብ 30 ማይሎች (48 ኪሎ ሜትሮች) ሠፍረው እ.ኤ.አ በኦክቶበር አጋማሽ 1867 የዘይላ ወደብን መገንባት ጀመሩ፡፡

በመጀመሪያው ወር 700 ያርድ (670 ሜትር ) ርዝመት የገነቡ ሲሆን፣ በቀጣዩ ወር ሁለተኛ ሳምንት የባቡር ሐዲድ ከትልቅ የብረት ድልድይ ጋር ወደ ውስጥ እንዲደርስ ገንብተው ጨረሱ፡፡ በተጨማሪ መሐንዲሶች የጦር መሳሪያዎችን የሚያጓጉዙ ዝሆኖችን ከነተጎታች ጋሪዎቻቸው መሸከመና ማሳለፍ የሚችል እስከ ሰንዓፌ የሚደርስ 101 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ከፍታው ደግሞ 2,300 ሜትሮች የሆነ መንገድ ገንብተው ጨረሱ፡፡ የብሪታኒያ ወታደሮች በዘይላ ካምፕ ወደብ ቆይታቸው የውኃ ፍጆታቸው ብዙ ስለነበር በእንፋሎት ኃይል የሚሰሩ ጀልባዎች በመጠቀም በቀን 200 ቶን ውኃን በማጤዝ (Condensation) ይጠቀሙ ነበር፡፡ ጦሩ ወደ ርዕሰ ምድር ከገባ በኃላ ጉድጓድ በመቆፈር ፍጆታውን ያሟላ ነበር፡፡ የጄኔራል ናፒር ጦር በሦስት ወራት ጉዞ መቅደላ ገባ፡፡

ጀርመናዊው ጆርጅ ሺምፐር በአትክልትና በአዝዕርት አጥኚነት እንዲሁም በአሳሽነት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ40 ዓመታት በላይ ኖሯል፡፡ በሰሜን ተራሮች፣ በመረብና በተከዜ አካባቢዎች በአሁኖቹ በኢትዮጵያ ደጋማና በኤርትራ ዕፅዋትን በመሰብሰብ ዘመናት አስቆጥሯል፡፡ ሺምፐር በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ዕፅዋትና እንስሳት ዝርያዎችን በማጥናትና በመሰብሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ ተመራማሪዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ከሺምፐር በፊት በኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ዕፅዋት በአውሮፓ አይታወቁም ነበር፡፡ ሺምፐር ዕፅዋትንና አዝርዕትን በመሰበሰብና በማድረቅ ለአውሮፓ የዕፅዋት ሳይንስ ማዕከላት ይልክ ነበር፡፡ በአውሮፓ የሚገኙ ትላልቅ የዕፅዋትና የአዝርዕት ምርምር ማዕከላት ሺምፐር ከኢትዮጵያ የላካቸው ዝርያዎች እንደሚገኙ ጀርመናዊቷ ጸሐፊ ዶርዚያ ማክዋን ስለሺምፐር በጻፈችው መጽሐፍ አሥፍራ እናገኛለን፡፡

ለአውሮፓ ዋና ዋና የእፅዋትና የአዝርዕት ዝርያዎች ምርምር ማዕከላት ከኢትዮጵያ ዝርያዎችን ልኮላቸዋል፡፡ ፓሪስ ለሚገኘው “Jardin des Plantes” የዕፅዋት ሙዚየም፣ ጀርመን በርሊን ለሚገኘው “Botanisches” የዕፅዋት ምርምርና ሙዚየምና እንግሊዝ ለሚገኘው “Royal Botanical Society” የዕፅዋትና አዝርዕት ሙዚየም የኢትዮጵያን ዝርያዎች ለቅሞና ሰብስቦ ልኳል፡፡ ለእንግሊዙ የሮያል ቦታኒካል ሶሳይቲ የዕፅዋትና የአዝርዕት ሙዚየም ብቻ በስሙ የሚጠሩ “schimperiana” የተሰኙ 2,400 ልዩ ዝርያዎች ከኢትዮጵያና ከመካከለኛው ምሥራቅ የተሰበሰቡ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 25 ቀን 1831 ሺምፐር ከጀርመን ወደ ደቡብ ፈረንሣይና አልጀርስ “Botanischer Reiseverein of Esslingen” የተሰኘ የዕፅዋትና አዝርዕት ምርምር ማኅበር ባደረገለት የገንዘብ ድጋፍ ሥራውን ጀመረ፡፡ ከወንድሙ ጋር ከአልጄሪያ ወደ ግብፅ ያመራው ሺምፐር፣ ወንድሙ ካይሮ ሲደርስ በመሞቱ የዕፅዋት መሰብሰቡን ሥራ ብቻውን ተያያዘው፡፡ በዓረቢያ ባህረ ሰላጤ ብቻውን 30 ሺሕ ዝርያዎችን መሰብሰብ ችሏል፡፡

በኋላ በገንዘብ ዕጥረት የማኅበሩ ድጋፍ ሲቋረጥ ቀይ ባህርን ተሻግሮ ዓደዋ እ.ኤ.አ በ1836 ራስ ውቤ ኃይለ ማርያም በኢትዮጵያ እንዲኖር ፈቀዱለት፡፡ እ.ኤ.አ ከ1837 እስከ 1855 ሺምፐር በመረብ ወንዝና በሰሜን ተራሮች በተከዜ ወንዝ በስተደቡብ የዕፅዋትና የአዝርዕት ዝርያዎችን በመሰብሰብ ወደ አውሮፓ ይልክ ነበር፡፡

ጆርጅ ሺምፐር ኢትዮጵዊቷን ወይዘሮ መርሲትን እ.ኤ.አ በ1843 አገባ፡፡ ከመርሲት ጋር በነበረው ጋብቻ አራት ልጆች አፈራ፡፡ ራስ ውቤ ሺምፐርን በምሥራቅ ዓደዋ የምትገኝ "ኢንጢቾ"የምትባል ቦታን  እንዲያስተዳድር ሾመውት ነበር፡፡ በተሰጠው የእርሻ መሬት አዲስ የግብርና ዘዴ በመጠቀም አትክልቶችን ይተክል ነበር ፡፡ ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል የድንች እርሻውም ይጠቀሳል፡፡

ዶርዚያ ማክዋን ስለ ሺምፐር በጻፈችው መጽሐፍ እንዲህ አስፍራለች እ.ኤ.አ ክርስቲያን ፍሬዳሪክ ቤንድር የሺምፐርን በኩር ሴት ልጅ የሺ እመቤትን አገባ፡፡ ፍሬዳሪክ የጀርመናዊ ሚሲዮናዊና ዕደ ጥበብ ባለሙያ ነበር፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ደብረ ታቦር ጋፋት ውስጥ የሚሽን ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ወርክሾፕ ከፍቶ ይሠራ እንደነበር ዶርዚያ ማክዋን ትነግረናለች፡፡ እ.ኤ.አ በ1863 የሚሲዮናውያኑ ቡድን አባል የሆነው ጎትሊብ ኪንዚል የሺምፐርን ፈቃድ በመጠየቅ ሁለተኛ ሴት ልጁን አገባ፡፡ በኋላ ጣይቱ ኬንዝልና ሌሎች ጋፋት ይኖሩ የነበሩ አውሮፓውያን አካባቢውን ለቀው እንዳይሄዱ በቴዎድሮስ እገዳ ተጣለባቸው፡፡ አዲሱ ሙሽራ ወደ ዓደዋ መጓዝ ባለመቻሉ ሺምፐር ጣይቱን ወደ ጋፋት ይዟት መጣ፡፡

ዶርዚያ በመጽሐፏ እንዲህ አስፍራለች፡፡ ሺምፐርም ከሌሎች ጀርመናዊ ፕሮቴስታንት የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ከጋፋት እንዳይወጡና ለቴዎድሮስ የጦር መሣሪያ እንዲያመርቱ ዕገዳ ተጣለባቸው፡፡

የሺምፐርና የሌሎች ጀርመናውያንን ፎቶግራፍ በጀርመናዊቷ መጽሐፍ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ታገኛላችሁ፡፡ ሺምፐርና ቤተሰቦቹ በታሪክ መጽሐፎቻችን እምብዛም አይታዩም፡፡ እንግሊዞቹ ሲጽፉ የእንግሊዝ መነጽር አድርገው ስለሆነ ይህንኑ ሲያሳዩን ቆይተዋል፡፡ በብዛት የምናገኛቸው እንዴት ቴዎድሮስን እንደጣሉና የዘመነ መሳፍንት ክፍፍልን ነው፡፡ ጸሐፊዋ በቅርቡ የሺምፐርን ሁለት ሪከርዶች (ሰነዶች) ብሪቲሽ ቤተ መጻሕፍት አግኝታለች፡፡ የመጀመሪያው “Observations” ሁለተኛው ቅጽ ደግሞ ካርታዎችና የአካባቢ መግለጫዎች መሆናቸውን ጽፋለች፡፡

የሴቫስቶፖል የከበባ ጦርነት ሲጀመር እ.ኤ.አ በ1855 ወደ ሥልጣን የመጡት አፄ ቴዎድሮስ ‹‹የሴቫስቶፖል መድፍ›› ስያሜውን ያገኙት ሩሲያ ከሚገኘው የሴቫስቶፖል ቦታ መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህን እንዴት አሰቡት ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

"የሶፊስት ወርልድ"የፍልስፍና መጽሐፍ ውሰጥ አንድ "ሐሳብ"ወይስ "ቁስ"ይቀድማል ለሚል ጥያቄ ምላሹን የምትሰጠን ወግ አለች፡፡ ሐሳቧን እንዲህ እንጋራት፡፡

---አንድ ሐውልት ቀራጭ ከትልቅ ቋጥኝ ድንጋይ የሆነ ነገር እየቀረፀ ነበር፡፡ ይህንን የተመለከ አንድ ሕፃን ቀራፂውን ይጠይቀዋል፡፡

"ከዚህ ቋጥኝ (አለት) ምን እየሠራህ ነው?"በማለት ሕፃኑ ልጅ ቀራፂውን ይጠይቃል፡፡

"ዝም ብለህ ተመልከት....ስጨርስ ታየዋለህ……"ብሎ ቀራፂው ቋጥኙን ይቀርፃል፡፡

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሕፃኑ ሲመለስ ከዚያ ቋጥኝ "ውብ ፈረስ"ተሠርቶ ይመለከታል፡፡

"ፈረሱ ቋጥኙ ውስጥ መኖሩን እንዴት አወቅክ!?"ብሎ ልጁ ተገርሞ ይጠይቃል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው eskinder.kebe1996@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

 

Standard (Image)

የኢሕአዴግ መንግሥት የኢኮኖሚ ልማት ሞዴል አለው?

$
0
0

በተክለ ብርሃን ገብረ ሚካኤል

የኢሕአዴግ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ የግንባሩ አባላትና ደጋፊዎች መንግሥት ግልጽ የሆነ የኢኮኖሚ ልማት እንዳለው አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡ መንግሥት ከመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ተነስቶ፣ በመዋቅራዊ ማስተካከያ አልፎ፣ የድህነት ቅነሳ መርህ ያካተተ የዕድገትና የትራንስፎሜሽን ፕሮግራም እያካሄደ በመሆኑ፣ በመሠረቱ የልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ሞዴል እየተከተለ መሆኑን አበክረው ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡

በዚህ የልማት ሞዴልም አያሌ የሚያኮሩ ውጤቶች እንደተገኙ ይገልጻሉ፡፡ በተለይ በመሠረተ ልማት ግንባታ የተመዘገቡትን ስኬቶች ይደረድራሉ፡፡ እውነትም በኃይል ማመንጫ፣ በባቡር፣ በመንገድ፣ በአውሮፕላን ማረፊያ፣ በሕንፃ፣ በቴሌ፣ በትምህርት ቤት፣ በጤና ጣቢያ ግንባታና በሌሎች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች የታዩት የልማት ሥራዎች የሚካዱ አይደሉም፡፡ ይኼንንም መሠረት አድርገው በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የልማት እንቅስቃሴ እንደተካሄደ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ፣ ይከራከራሉ፡፡

ከላይ የተዘረዘሩትን የልማት ሥራ ውጤቶችን እየደረደሩ፣ የአገሪቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) በተከታታይ በአሥራ አንድ በመቶ ያህል ማደጉን ይነግሩናል፡፡ እነ ዓለም ባንክና አይኤምኤፍ የአሥራ አንድ በመቶ የዕድገት አኃዙን ባይቀበሉትም፣ ኢኮኖሚው በከፍተኛ መጠን ማደጉን አይክዱም፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በዓለም ፈጣን ዕድገት ካሳዩት አገሮች ተርታ ይመድቡታል፡፡ በየደረጃው አያሌ የትምህርት ተቋማት ተገንብተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ከሰላሳ በላይ እየሄደ ነው፡፡ በርካታ የጤና ጣቢያዎች ተከፍተዋል፡፡

እንደ መሠረተ ልማት ግንባታው ባይሆንም በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በማዕድን ዘርፎች የማይናቁ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውም ተገልጿል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የልማት ሞዴል አለው የሚሉት ወገኖች ይኼን ይበሉ እንጂ፣ የለውም የሚሉት ምሁራን ክርክርም እንዲህ በቀላሉ የሚጣጣል ሆኖ አልተገኘም፡፡ መንግሥት የልማት ሞዴል የለውም፣ ልማቱንም የሚያካሂደው ‹‹በጨበጣ›› ነው የሚሉት ወገኖች ክርክራቸውን የሚመሠርቱት በቀላል የማክሮ ኢኮኖሚ ፅንሰ ሐሳብ ላይ ነው፡፡ ሀብት የሚፈጠረው መሬትን፣ የሰው ኃይልንና ካፒታልን በማቀናጀት ቢሆንም፣ ሕያው የሀብት ምንጭ የሰው ኃይል በመሆኑ፣ አስተማማኝ የኢኮኖሚ ልማት ሞዴል በሰው ኃይል ትምህርትና ሥልጠና ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ ይኼም ብቻ አይደለም፡፡ ትምህርትና ሥልጠና ዓለም አቀፋዊ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ መሆን እንደሚገባው አበክረው ይገልጻሉ፡፡ መሬትን በተመለከተ የተፈጥሮ ሀብት እንደመሆኑ፣ ለቤት ሠሪዎችና አምራቾች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል እንዳለበት ያምናሉ (ከሞላ ጎደል በነፃ)፡፡ ካፒታል ላይ ያላቸውም አመለካከት በመሠረታዊ መርህ ላይ የተመሠረተ ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ካፒታል ማለት በአብዛኛው የባንክ ብድርና ይኼም ሊያስገኝ የሚችለው የውጭ ምንዛሪ ማለት ነው፡፡ እርግጥ በዕቁብና በሌሎች ዘዴዎች የሚቆጠብ ገንዘብ፣ ከሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ድርሻ ተጣምሮ በካፒታልነት ሥራ ላይ ሊውል እንደሚችል ይታወቃል፡፡ የባንክ ብድር በአዋጭነት መሥፈርቶች ላይ ተመሥርቶ ካልተሰጠ፣ ውጤቱ ኪሳራ ብቻ ሳይሆን የዋጋ ንረትም መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡

እዚህ ላይ የኢሕአዴግ መንግሥት የልማት ሞዴል የለውም፣ አለው ከተባለም የተሳሳተ ነው የሚሉትን ወገኖች ክርክር በግልጽ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ የትምህርት ቤት ሕንፃዎች ተገነቡ እንጂ፣ የሚሰጠው የትምህትና የሥልጠና ጥራት ደረጃ አሽቆልቁሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የኢሕአዴግ የልማት ሞዴል የትምህርት ጥራትን በመሠረታዊ ግብዓትነት አልተቀበለውም፡፡ በሌላ በኩል መሬት ከሞላ ጎደል በነፃ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል ሲገባው፣ እንዲያውም መንግሥት መሬትን ዋና የሀብት ምንጭ ነው በሚል የተሳሳተ እሳቤ፣ አንዷን ካሬ ሜትር ከሦስት መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር በላይ እየሸጠ ነው፡፡ በዚህ አሠራር እንደ ሀብት ምንጭ የተወሰደው የሠለጠነ የሰው ኃይል ሳይሆን መሬት መሆኑ ነው፡፡ ይኼ ስህተት ነው ይላሉ ተቃዋሚዎቹ፡፡ በሌላ በኩል የባንክ ብድርን በተመለከተ በአብዛኛው ‹‹በበላይ ትዕዛዝ›› ስለሚሰጥ፣ የአዋጭነት መሥፈርቶች አይከበሩም፡፡ በመሆኑም የባንክ ብድር ከምርት ዕድገት ይልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው ለዋጋ ንረት መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

የትኛው ወግ ነው ትክክል?

አብዛኛው የኢኮኖሚክስ እውቀት የሌለው የኅብረተሰብ ክፍል በቴሌቪዥንና በዓይኑ በሚያያቸው መሠረተ ልማቶችና ሕንፃዎች መደነቁ አይቀርም፡፡ ልማትና ዕድገትም ይኼ ቢመስለው የሚያስገርም አይደለም፡፡ ግን ከመሠረተ ልማቶቹ ስንቶቹ እንዳከሰሩና እንደ ከሸፉ የሚያውቀው ሕዝብ ምን ያህሉ ነው? የጠቅላላ ኢንቨስትመንት አፈጻጸም ደረጃ ከአርባ በመቶ እንደማይበልጥ የሚገነዘበው ሰው ስንት ነው? በደንብ ባልተጠኑ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታና እሴት በማይፈጥሩ ሙሰኞች በሚሠሩ ሕንፃዎች ምክንያት በተፈጠረው የዋጋ ንረት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች እየተሰቃዩ መሆኑን የሚገነዘበው ሕዝብ ስንት ይሆናል? በአጭሩ መሬት የሀብት ምንጭ የሆነበትና የባንክ ብድር በትዕዛዝ የሚሰጥበት የልማት ሥልት የልማታዊ መንግሥት ሞዴል ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲሁም ሰብዓዊ ልማትን (የሰው ኃይል ልማትን) ማዕከል ያላደረገ የልማት ሞዴል ሊኖር አይችልም፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የልማት ሥልት የመሬትን ዋጋ ያላግባብ ሰማይ የሰቀለ፣ በአንፃሩ እውቀትን ዋጋ ቢስ ያደረገና የባንክ ብድርን (ዋናውን የካፒታል ምንጭን) ለአዋጭነት መሥፈርት ሳይሆን ለበላይ ትዕዛዝ ተገዢ ያደረገ በመሆኑ፣ በማንኛውም ዓይነት የልማት ሞዴል ሊመደብና ሊፈረጅ የሚችል አይመስለኝም፡፡

ይልቁኑም በመዋቅራዊ ደረጃ ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን (ይህም የሙስና ዓይነት ነው) የሚያራምድ ሞዴል ነው ማለቱ ይቀላል፡፡ ሌላው የኢሕአዴግ የልማት ሞዴል (ሞዴል ከተባለ) ሊገመገምበት የሚችለው መሥፈርት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ተመሥርቶ ዘመናዊ ሥልጣኔን ለማፍጠን በቀየሰው ሥልት ነው፡፡ ለዚህ በዋናነት ተቀባይነት ያገኘው ሥልት በግሉ ዘርፍ፣ በመንግሥት ኢንቨስትመንት ኩባንያና በቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ቅንጅት የሚካሄድ የጋራ ልማት ማኅበር የኢንቨስትመንትና የምርት እንቅስቃሴ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የግሉን የኢኮኖሚ ክፍል ከማበረታታት ይልቅ እያቆረቆዘው በመሆኑ፣ በዚህ መሥፈርት መሠረትም የኢኮኖሚው አፈጻጸም ደካማ ነው፡፡ ወደ አገር የገባው ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመት ከሚጠበቀው በታች ከመሆኑም በላይ፣ የራስን ብሔራዊ ጥቅም በማስቀደም ላይ የተመሠረተ ስለሆነ የሚፈለገውን ፈጣን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሊያስገኝ አልተቻለም፡፡

በአጠቃላይ የኢሕአዴግ መንግሥት የኢኮኖሚ ልማት ሞዴል (ሞዴል አለው ከተባለ) የልማታዊ መንግሥት ስትራቴጂ ተብሎ ይሰየም እንጂ፣ ከማንኛውም የልማት ሞዴል ባፈነገጠ ሁኔታ የሚከተሉትን ዓበይት ባህሪያት ያካተተ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

  • በግል፣ በቤተሰብ፣ በማኅበርና በድርጅት የሚካሄድ ሥራና የሚደረግ ጥረት ሳይሆን፣ የገንዘብና የሀብት ምንጭ የሆኑት የፖለቲካ ሥልጣን፣ ቡድናዊ ግንኙነቶች፣ መሬትና በትዕዛዝ የሚሰጡ የባንክ ብድሮች ናቸው፡፡
  • የመንግሥትና የፓርቲ የኢኮኖሚ ድርጅቶች በከፊል ሞኖፖል ቅርፅ (ኦሊጎፖሊ) ኢኮኖሚውን ስለተቆጣጠሩት፣ የግሉ የኢኮኖሚ ክፍል ዋናው የልማትና ዕድገት ሞተር መሆን ሲገባው በእነዚህ ጥገኝነት ሥር እየቀረቆዘ ነው፡፡
  • እውቀት ከሞላ ጎደል ዋጋ ቢስ ሆኗል፡፡
  • ሙስና ተቋማዊ ተደርጓል፡፡
  • የይስሙላ ዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ልማትን እያጋነኑ ለማቅረብ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ነግሷል፡፡

ከላይ እንደተጠቆመው፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ልማት የሚለው በአብዛኛው ‹‹በጨበጣ›› የሚገነባቸውን መሠረተ ልማቶች ናቸው፡፡ ይኼ በልማት ኢኮኖሚክስ ቋሚ ኢንቨስትመንት የሚባለው ነው፡፡ የዚህ መጠን ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አርባ በመቶ መድረሱን መንግሥት ተናግሯል፡፡ ይህ መቶኛ ድርሻ በጣም ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ኢንቨስትመንቱ ለጠቅላላ ፍጆታ ማደግ ምን ያህል አስተዋጽኦ አድርጓል? ኢንቨስትመንት ለጠቅላላ ፍጆታ ዕድገት አስተዋጽኦ የማያደርግ ከሆነ፣ ጠቃሚነቱ ዝቅተኛ እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ የመስኖ ግድብ ለምግብ እህል ምርት ዕድገት አስተዋኦ የማያደርግ ከሆነ፣ ጠቃሚነት የለውም፡፡ ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያውያን የነፍስ ወከፍ ፍጆታ እየቀነሰ እንጂ እየጨመረ አልሄደም፡፡ የሥጋ፣ የወተት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ በአጠቃላይም የምግብ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ እንደቀነሰ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ በተመሳሳይ በመኖሪያ ቤትና በትራንስፖርት በኩል ያለው ከፍተኛ ዕጥረትና ችግር በሚገባ የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ ይኼ ሁሉ ኢንቨስትመንት የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ካላሻሻለ ጥቅሙ ምንድነው? እስኪ ችግሩን ይበልጥ ለመረዳት የሚከተለውን ቀላል የማክሮ ኢኮኖሚ ቀመር እንጠቀም፡፡ ጠቅላላ ገቢ (ጂዲፒ) = ጠቅላላ ፍጆታ + ጠቅላላ ኢንቨስትመንት + (ኤክስፖርት ሲቀነስ ኢምፓርት)፡፡    

የኢሕአዴግ መንግሥት ብዙ መሠረተ ልማቶችን ስለገነባ ጠቅላላ ኢንቨስትመንት ያደገ ሊመስለን ይችላል፡፡ የተገነቡትን የኃይል ማመንጫዎች፣ የትምህርት ቤት ሕንፃዎች፣ መንገዶች፣ ወዘተ ስናይ፣ ብዙ ሊመስሉን ይችላሉ፡፡ ግን ይኼ ዕይታችን የሚፈጥረው የተጋነነ የግንዛቤ ትርዒት ሊሆን እንደሚችል መርሳት የለብንም (ኦፕቲካል ኢሉዥን)፡፡ በሌላ በኩል ጠቅላላ ፍጆታ በጠቅላላ መጠኑ ማደጉን መካድ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የሕዝብ ብዛት አድጓልና፡፡ ይሁንና የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ስለቀነሰ የጠቅላላ ፍጆታ ዕድገት ከሕዝብ ብዛት ዕድገት በታች መሆኑን እንረዳለን (ማለትም ከሦስት በመቶ በታች)፡፡ ኢምፖርት ኤክስፖርትን በከፍተኛ መጠን ስለሚበልጥ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርትን ይቀንሰዋል፡፡ እንግዲህ ከላይ ከተመለከተው ቀመር በከፍተኛ መጠን እንዳደገ በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ኢንቨስትመንት (መሠረተ ልማት) ነው፡፡ ግን ይኼ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የነፍስ ወከፍ ፍጆታን ሊያሳድግ አልቻለም፡፡ ለምን? ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንደኛው ኢንቨስትመንት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ነው ከአርባ በመቶ አይበልጥም፡፡ ሁለተኛ ምርታማነቱ አነስተኛ ነው፡፡

ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) በዓመት በአሥራ አንድ በመቶ ሊያድግ ይችላል? የጠቅላላ አገር ውስጥ ምርት ስልሳ በመቶ ገደማ የሆነው ጠቅላላ ፍጆታ ያደገው ከሕዝብ ዕድገት በታች ከሆነ፣ እንዲሁም የጂዲፒው አርባ በመቶ ያህል የሆነው ኢንቨስትመንት አፈጻጸምና ምርታማነት ዝቅተኛ ከሆነ፣ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት እንዴት ነው በአሥራ አንድ በመቶ ሊያድግ የቻለው? የኢሕአዴግ መንግሥት ይህን ውጤት ሊያስገኝ የሚችል የኢኮኖሚ ልማት ሞዴል እንደሌለው በግልጽ መገንዘብ ይቻላል!

ማጠቃለያ

አስተማማኙ የልማት ሞዴል በሚከተሉት ወሳኝ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ጥራት ባለው ትምህርትና ሥልጠና ላይ የተመሠረተ ሰብዓዊ (የሰው ኃይል) ልማት፣ ፍትሐዊ የመሬት ክፍፍል፣ ከአድልኦ ነፃ የሆነና በታወቁ መሥፈርቶች ላይ የተመረኮዘ የባንክ ብድር አሰጣጥ ሥርዓት፣ በግሉ የኢኮኖሚ ክፍል፣ በመንግሥት የኢንቨስትመንት ኩባንያና በቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ቅንጅት የሚካሄድ የጋራ ልማት ማኅበር፣ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ መዋቅርና ማዕቀፍ ደግሞ የሚከተሉት ዓበይት ባህሪያት ያካተተ ይሆናል፣ የነፃ ገበያና የነፃ ውድድር ካፒታሊስት ሥርዓት (ፍትሐዊ ካፒታሊዝም) ለእውቀት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጥበት ሥርዓት፣ የፖለቲካ ሥልጣን የሀብት ማግኛ መሣሪያ ያልሆነበት ዓውድ፣ መሬት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈልበትና ዋና የሀብት ምንጭ ያልሆነበት የኢኮኖሚ ማዕቀፍ፣

የመንግሥት ዋና የኢኮኖሚ ተግባር የግል የኢኮኖሚ ክፍሉን ማበረታታት የሆነበት ሥርዓት፣ ማንም ሰው ተመጣጣኝ እሴት ሳይፈጥር ገንዘብ የማያገኝበትና ሙስና ከሞላ ጎደል የጠፋበት ሥርዓት፡፡

እነዚህ ሁሉ በኢሕአዴግ መንግሥት ‹‹የልማት ሞዴል›› ውስጥ የሌሉ ስለሆኑ፣ እንደገና መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ ባለመኖራቸውም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የተፈጠሩት ችግሮች እጅግ በርካታ ሆነዋል፡፡ የዋጋ ንረት ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል፡፡ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የገበያ ዋጋ ከሰላሳ እጥፍ በላይ ንሯል፡፡ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን በ93 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተባባሰ ነው፡፡ የሸቀጥ ንግድ ጉድለቱ እየሰፋ ሄዷል፡፡ በአንፃሩ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የኤክስፖርት ድርሻ ከመጨመር ይልቅ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ የወጣቶች የሥራ አጥነት ምጣኔ ከስልሳ በመቶ አያንስም፡፡ የውጭ እዳ ጫና ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደደረሰ ተዘግቧል፡፡ በዚህ ላይ የምግብ፣ የመኖሪያ ቤትና የትራንስፖርት እጥረትና ችግር ሕዝቡን ክፉኛ እያማረረ ነው፡፡ ሙስና የሥርዓቱ ዓይነተኛ መለያ ሆኗል፡፡ የገቢና የሀብት ልዩነቱ ጣሪያ ነክቷል፡፡ የሙሰኞች ሞራላዊ ዝቅጠት በሕዝቡ ግብረ ገባዊ ሥነ ምግባር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፡፡

ለምሳሌ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ በተሠሩት ትልልቅ ሕንፃዎች (ከአራት ፎቆች በላይ ወደ አሥራ አምስት ሺሕ ያህል ይገመታሉ)) ከስድስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ከሚገመተው የአዲስ አበባ ሕዝብ ተጠቃሚዎቹ (ከእነ ቤተሰቦቻቸው) ከ75 ሺሕ አይበልጡም፡፡ አብዛኛዎቹ ባለመኪናዎችም እነሱና መሰሎቻቸው ናቸው፡፡ ገንዘቡን ያገኙት በእሴት ፈጠራ ሒደት አልፈው ስላልሆነ፣ የኅብረተሰቡን ሞራል በሚነካ ሁኔታ ሲያባክኑት ይታያሉ፡፡ ባለመኪኖችም በሕዝብ ላይ አቧራና ጢስ ሲያቦኑ፣ አየር ሲበክሉና በመኪና አደጋ ሕይወት ሲቀጥፉ ነው የሚውሉት! እሴት ሳይፈጠር ሚሊዮነር የሆነ በዝባዥ መደብ ተፈጥሯል፡፡ ሰላም!፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

   

 

  

Standard (Image)

ዓደዋ በመቶ ሃያ አንደኛ ዓመቱ ሲታወስ

$
0
0

    በተሾመ ብርሃኑ ከማል

የ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በአንድ በኩል በአውሮፓውያን የግዛት መስፋፋት፣ በአፍሪቃውያን ደግሞ የእነሱ ቅኝ ተገዥ የመሆን ምኞት ዘመንም ነበር፡፡ ይኸው ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን እንደነበረም ይታወቃል፡፡ የኢንዱስትሪው አብዮት ደግሞ አውሮፓውያን ጥሬ ዕቃ እንዲፈልጉና በአነስተኛ የጉልበት ዋጋ ከፍተኛ ምርት እንዲያመርቱ፣ እንዲሁም ገበያ እንዲፈልጉ አስገድዷቸው ነበር፡፡ በዚህ ረገድ መካከለኛው ምሥራቅና ሩቅ ምሥራቅ አስፈላጊ ቅኝ ግዛቶች መሆናቸው አስተማማኝ ቢሆንም፣ አፍሪካ ግን ያኔ ጨለማው ዓለም ተብላ ትታወቅ ስለነበር እምብዛም ትኩረት አልተሰጣትም ነበር፡፡ ቀደም ብሎ የአፍሪካንና የተቀረውን ዓለም የንግድ ግንኙነት በአብዛኛው በባሪያ ንግድ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ባሪያዎችም ከማዕከላዊ አገሮች ወደ ድንበር እየተገፋፉና እየተገፈተሩ ይመጡላቸው ስለነበር ወደ ውስጥ ዘልቀው መግባት እምብዛም አላስፈለጋቸውም፡፡ ከዚያም አውሮፓውያን የባሪያ ንግድን በሕግ ስለከለከሉ በዚህ ረገድ የነበረው ግንኙነት ደረጃ በደረጃ እየተቋረጠ ሄደ፡፡

ይሁንና ከአፍሪካውያን ባሪያዎች አንዳንድ መሠረታዊ ቁም ነገሮችን በመረዳትም ይሁን የክርስትናን ሃይማኖት ለማስፋፋት ወይም የቅኝ ግዛት ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግና ገበያ ለማግኘት ሲሉ ‹‹አሳሾቻቸውን›› መላክ ጀመሩ፡፡ ለምሳሌ ጁሴፔ ሳፔቶ የተባሉትን ኢጣሊያዊ ሚሽነሪ ወደ አሰብ የላካቸው ሩባቲኒ የተባለ የንግድ ኩባንያ ነበር፡፡ እንደ አባ ሰላማ ያሉትም ቢሆኑ የክርስትናን ሃይማኖት ለማስፋፋት በሚል ምክንያት ከአገራቸው ይነሱ እንጂ፣ የአፄ ምኒልክ የፖለቲካ አማካሪ የመሆን ዕድል ገጥሟቸው ነበር፡፡ ከአፄ ምኒልክ ዘመን መንግሥት በፊትም ቢሆን የአፄ ቴዎድሮስን መድፍ የሠሩት የሃይማኖት አባቶች የተባሉት ጭምር እንደነበሩ ይታወቃሉ፡፡ ይኸው ሰርጎ የመግቢያ ዘዴ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተሠርቶበታል፡፡

የስዊዝ ካናል መከፈት የቀይ ባሕር ጠቃሚነትም በእጅጉ ከፍ አደረገው፡፡ የቀይ ባሕር ጠቃሚነትም በአካባቢው የሚገኙ አገሮች የባሕር ዳርቻዎችን አስፈላጊነት አጎላው፡፡ የባሕር ለባሕር ጉዞው ከኢኮኖሚ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ስለነበርም ከሰሜን ቁልቁል እስከ ደቡብ አፍሪካ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ አፍሪካ ፈረንሣይ በባቡር ሐዲድ ለማገናኘት ትልቅ ፍላጎት አሳደረባቸው፡፡ ይኼም ሆኖ በፈረንሣይና በእንግሊዝ መካከል የጥቅም ግጭት መፈጠሩ አልቀረም፡፡ ለምሳሌ ከደቡብ ወደ ሰሜን ወይም ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ አቋርጦ ለማለፍ ያኔ የብሪታኒያ ቅኝ ግዛት የነበረችው ሱዳንን መጠቀም አስፈላጊ ሆነ፡፡ ፈረንሣይ በሱዳን በኩል አቋርጣ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ለመድረስ የብሪታንያን ይሁንታ ማግኘት ነበረባት፡፡ ከዚህም ሌላ ጂቡቲ በፈረንሣይ ብትያዝም ኢትዮጵያ ነፃ አገር ስለነበረች ይህች ነፃ አገር አንድም በእንግሊዝ ካለበለዚያም እንግሊዝ በምትፈልጋት አገር ካልተያዘች ሁኔታው አመቺ አልነበረም፡፡ ይኼም በበኩሉ የፖለቲካ ጨዋታውን ሳይወዱ በግድ ውስብስብ እንዲሆን አደረገው፡፡ እንዲሁም ናይልን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ኢትዮጵያን መቆጣጠር ያስፈልግ ነበርና የኢትዮጵያ በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ በአውሮፓ ቅኝ ገዥ ሥር መዋል የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜም በወቅቱ ገናና የነበረችው ታላቋ ብሪታኒያ ከፈረንሣይ ይልቅ ደካማዋ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ብትይዝ ለኋለኛው ዕቅዷ አስቸጋሪ ስለማይሆን የቅኝ ግዛት ይሁንታን ለወዳጅዋ ሰጠች፡፡

 

የኢጣሊያውያን  ወደኢትዮጵያመምጣትና ኢጣሊያ በእንግሊዝ ድጋፍ ምፅዋን መያዝ

ጁሰፔ ሳፔቶ እ.ኤ.አ. ከ1811 እስከ 1895 የኖረ ኢጣሊያናዊ የላዛሪስት ሚሽን ተከታይ ሲሆን፣ ይህም የላዛሪስት ሚሽን የተባለ ድርጅት ድሆችን በመርዳት ስም ፓሪስ እ.ኤ.አ. በ1625 ውስጥ ሴንት ቪንቸንት ፖል በተባለ የሃይማኖት አባት የተቋቋመ ነበር፡፡ ጁሰፔ ሳፔቶ የላዛሪስት ሚሽን ተከታይ የሆነው በ18 ዓመቱ ሲሆን፣ ወደ ምፅዋ ከመምጣቱ በፊትም በ1837 ወደ ሊባኖስና ግብፅ ሄዶ እንደነበር የሕይወት ታሪኩን የጻፉ ሰዎች በማስታወሻቸው ውስጥ አስፍረዋል፡፡ ይሁንና ድርጅቱ ለድሆች ዕርዳታ ለመስጠት የተቋቋመ ይባል እንጅ ያቋቋመው የፖለቲካ ድርጅት እንደነበር ይነገራል፡፡ የታሪክ ጸሐፊዎች ወደዚህ ሥፍራ የመጣው ከሁለት ፈረንሣውያን ወንድማማቾች ጋር እንደሆነና ከእነርሱ ጋር እ.ኤ.አ. ከ1837 እስከ 1847 ባለው ጊዜ ወደ መሀል ኢትዮጵያ በመግባት በዓደዋና በጎንደር ጉብኝት እንዳደረገ ጽፈዋል፡፡ ስለሆነም ጁሰፔ ሳፔቶም ፍራንቺስካ ጆቫኒ ከተባለ ሌላ ሚሽነሪ ጋር በምፅዋ በኩል ወደ ከረን እ.ኤ.አ. ኦገስት 23 ቀን 1851 መጣ፡፡ በእነዚህ ጸሐፊዎች መረጃ መሠረት የላዛሪስት ሚሽን ተልዕኮውን ለመፈጸም የመጣው በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጉዞው በፀና ታሞ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ነው፡፡ በሁለተኛ ጊዜ ጉብኝቱም እንደ ሚሽነሪ ሳይሆን እንደ ጎብኚ ወደ ምፅዋ በመምጣት ደናኪል (የአፋር) ጨዋማ ሥፍራዎችን፣ ቦጎስንና ሓባብን እ.ኤ.አ. በ1851 ጎበኘ፡፡ በዚህም ጊዜ ግዕዝ፣ ትግርኛና ቢለን ቋንቋዎችን በማጥናት መዝገበ ቃላት አዘጋጀ፡፡ ከዚያም ወደ አሰብ መጣ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1858 አፄ ቴዎድሮስ በመንግሥታቸው ላይ ያመፀውን የአገው ንጉሥ ድል አድርገው በገደሉበት ጁሰፔ ሳፔቶን እስረኛ አድርገው እንደ አስተርጓሚ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ሆኖም አፄ ቴዎድሮስ ከጊዜ በኋላ ነፃ አድርገው ስለለቀቁት ወደ ፓሪስ ተመለሰና በፓሪስ የቤተ መዘክር ሠራተኛ ሆነ፡፡ ስዊዝ ካናል እ.ኤ.አ. በ1869 ሲከፈትም የኢጣሊያ መንግሥት በቀይ ባህር ዳርቻ እንደ ወደብ የሚጠቀሙበትን ቦታ እንዲያስገኝ አደራ ተሰጠው፡፡ ወደ አሰብ ከመጣ በኋላም የተሰጠውን አደራ ሳያሳውቅ ከአፋር ሡልጣኖች ጋር ወዳጅ መስሎ በመቅረብ ከአሰብ የተወሰነውን መሬት በአፋር ግዛት በሚኖርበት ጊዜ ሊጠቀምበት ውል መሠረት ገዛ፡፡

ሲኞር ጁሴፔ ሳፔቶ ኃላፊነቱን ከተወጣ በኋላ ወደ ኢጣሊያ ተመለሰ፡፡ በዚህም ጊዜ ከሚያውቁት ሰዎች ጋር እምብዛም አይገናኝም ነበር፡፡ ሲኞር ጁሴፔ ሳፔቶ ወደ ኢጣሊያ ከተመለሰ በኋላ በአራተኛው ዓለም አቀፍ ኦሪየንታሊስቶች ጉባዔ በ1878 ተካፋይ ነበረ፡፡ በዚህ ጊዜም የተለያዩ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርቧል፡፡ ከጁሴፔ ሳፔቶ በፊት የምናገኘው የሃይማኖት ሰው ጉግልየሞ ማሳይ፣ በተለምዶ አባ ማስያስ (እ.ኤ.አ. 1809-1889) የምንለው ቄስ ሲሆን፣ ይኼም ሰው ኢጣሊያ ቦቫ በምትባል ሥፍራ የተወለደ ነው፡፡ በአገራዊ አባባል አባ ማስያስ የተባለው የካቶሊክ እምነት ተከታይ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ውስጥ ለ25 ዓመታት ኖሯል፡፡ አባ ማስያስ ወደ ኢትዮጵያ የተላከው ጉግልየሞ ስም ሲሆን፣ ከጁሴፔ ከተባለ ሌላ ፈረንሣዊ ጋር በመሆን ወደ ሮም ሄዶ ስለኢትዮጵያ ሁኔታ ሪፖርት ካቀረበ በኋላ በ1846 ዓ.ም. ኦሮሞዎችን ክርስቲያን ለማድረግ በሚል ሰበብ ‹‹የኦሮሞ ቄስ›› ተብሎ እንደገና መጣ፡፡ ድሮውንም አባ ማስያስ እየተባለ የነበረው ኢጣሊያዊ አቡነ ባርቶኔሊ በሚል ስም ወደ ጎጃም ተልኮ እንደነበር እርሱን በሚመለከት የተጻፉ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ በ1849 ዓ.ም. ደግሞ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሞንሲኞር ተባለ፡፡ ይኼ ሰው በ1879 ዓ.ም. ውስጥ ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡ በ1880 ዓ.ም. ላይ በፈረንሣይ በተካሄደው ጉባዔ በመገኘት ለኦሮሞዎች ተጨማሪ ሚሺነሪዎች እንደሚያስፈልጓቸው አበክረው የገለጹ ሲሆን፣ በ1884 ዓ.ም. የካርዲናንነት ሲመት በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በአቡነ ሊዮ 33ኛ (1878-1903 ዓ.ም.) ተሰጠው፡፡ በአገሩም ውስጥ ሕይወቱ አለፈ፡፡ ይሁንና እርሱ ከሞተ ከ75 ዓመታት በኋላ የኢጣሊያ መንግሥት የአባ ማስያስ በኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ለኢጣሊያ ቅኝ ግዛት መመቻቸት ቅድመ ሁኔታ እንደነበር አስታውቋል፡፡ ነገር ግን አባ ማስያስ ፖለቲካዊ ሚና ይኑረው አይኑረው ያሳየው ፍንጭ አልነበረም፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክም የዚህ ሰው ጥሩ ወዳጅ እንደነበሩ ሲታወቅ፣ በአማርኛና በኦሮሚኛ ያዘጋጀውን የሰዋሰው መጽሐፍ አሳትመውለታል፡፡ አባ ማስያስ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹በኢትዮጵያ ደጋማ ሥፍራዎች በሚሽን የቆየሁባቸው 35 ዓመታት›› በሚል ርዕስ ያዘጋጀ ሲሆን፣ ይኼም ስለኢትዮጵያውያን ማንነት የሚያወሳ መጽሐፍ በ1936 ዓ.ም. መታተሙ ይታወቃል፡፡ መጽሐፉ ጠቃሚ ሆኖ በመገኘቱም ወደ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሣይኛና ጀርመንኛ ተተርጉሟል፡፡

እነ አባ ጁሴፔ ሳፔቶና እነ አባ ማስያስ በአንድ በኩል ሃይማኖት በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ አማካሪ፣ በዋነኛነት ስለኢትዮጵያ ሁኔታ ለመንግሥታቸው መረጃ አስተላላፊ ሆነው ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ ተልዕኳቸውን ሲፈጽሙም ወደ አገራቸው እየተጠሩና ሹመት ሲቀበሉ፣ የኢጣሊያ መንግሥት ደግሞ ያገኘውን መረጃ በመጠቀም ቅኝ ግዛት የማስፋፋት ዓላማውን ለማስፈጸም መጠቀም ጀመረ፡፡ ይኼንን በአጭሩም ቢሆን እንደሚከተለው እንመልከተው፡፡ ስለዓደዋ ጦርነት በሚያወሳው ምዕራፍ እንደተጠቀሰው ሁሉ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን መውረር የጀመረችው በነጋሪባልዲና ማዚኒ ተበታትና የነበረችው ኢጣሊያ 1861 ዓ.ም. በተዋሃደች በ17 ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ ያኔ ኢጣሊያ ከተዋሃደች በኋላ ብዙዎች ታላቋን ኢጣሊያ የመመሥረት ሕልም ነበራቸው፡፡ በወቅቱ የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ፍራንሲስኮ ክሪስፒ ‹‹ኢጣሊያን ትልቅ ማድረግ የሚቻለው በአፍሪካ ውስጥ ቅኝ ግዛት ለማስፋፋት የተቻለ እንደሆነ ነው›› ብሎ ያምን ነበር፡፡ ስለሆነም ቀደም ሲል በተጠቀሰው ውል መሠረት ጁሰፔ ሳፔቶ የአሰብ የተወሰነ ክፍል በ1869 ዓ.ም. ሲገዛ ዓላማው ለራፌኤል ሩባቲኖ ኩባንያ የመርከብ ከሰል መሙያ የነበረ ሲሆን፣ የኢጣሊያ መንግሥት ግን በውሉ ውስጥ የነበሩትን ቀዳዳዎች ተጠቅሞ የቅኝ ገዥነት እግሩን የሚተክልበት ቦታ አደረገው፡፡

‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል›› እንዲሉም ሲኞር ጁሰፔ ሳፔቶ ሆን ብሎ በውሉ ውስጥ እርሱ ለመኖሪያነት በገዛው መሬት ላይ ሌሎች የእርሱ ሰዎች መጥተው ቢኖሩ ምንም ዓይነት ተንኮል በአፋሮች ዘንድ እንደማይደርስባቸው ቅዱስ ቁርዓን አስይዞ አስምሏቸው ስለነበር በእርሱ እግር የሩባቲኖ ኩባንያ፣ በሩባቲኖ ኩባንያ እግር የኢጣሊያ ቅኝ ገዥዎች እስከ መጨረሻው እያታለሉና እየሸፈጡ ቦታ ያዙ፡፡ ከፊል አሰብ ለሩባቲኖ ኩባንያ በ1870 ዓ.ም. መሸጡን ተከትሎም ዘመናዊ ወደብ ተደርጎ ተሠራ፡፡ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላም ኩባንያው ከአሰብ እስከ መሀል ሐበሻ የነበረውን ንግድ ሰለማዊ በሆነ መንገድ ለማካሄድ የጦር መርከቦች እንደሚያስፈልጉት ገለጸ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ካሮሊም የኢጣሊያ መንግሥት ምክር ቤት የተቀደሰ ሐሳቡን የደገፈው መሆኑን ገልጾ፣ ‹‹ቅኝ ግዛታችንን ለመጠበቅ ሁለት የጦር መርከቦች ልኬልሃለሁ›› የሚል መልዕክት አስተላለፈለት፡፡ ክሪሲፒ በሁለተኛው ደብዳቤው በአሰብ የንግድ ማዕከል መቋቋሙ የአገሪቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማሳደግ በኩል ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጦ፣ በንግዱ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የኢጣሊያን የባህር ኃይል ለማደራጀትም አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገለጸለት፡፡ ከዚህ ደብዳቤ በግልጽ እንደምንረዳው ምንም እንኳን ጁሰፔ ሳፔቶ ለመኖሪያነት ገዝቶ ለነዳጅ መሙያነት ለራፋኤሎ ሩባቲኒ ቢያስተላልፈውም፣ አሰብን ወደ ኢጣሊያ ቅኝ ግዛትነት የመቀየር ፍላጎት የነበር መሆኑን ነው፡፡

‹‹የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል›› እንዲሉ የኢጣሊያ መንግሥት በ1882 ዓ.ም. ላይ አሰብ ቅኝ ግዛቱ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲኞር ማቺኒ የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ በአሰብ ወደብን ከአውሮፓ ገበያ ጋር በቀጥታ የሚያገናኛቸው ማዕከል አድርገው ያላንዳች ችግር እንዲጠቀሙበት ጋበዘ፡፡ በእርግጥም አሰብ ለማደግ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚሄድና ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ንግድ ያስፈልገው ነበር፡፡ የአሰብ ጉዳይ በዚህ ሁኔታ መልክ ከያዘ በኋላ በምፅዋ የነበረው የግብፅ ጦር በአቅም ማነስ ምክንያት ጓዙን ጠቅልሎ ሲወጣ የፈረንሣይ ተቀናቃኝ በነበረችው በእንግሊዝ ድጋፍ ምፅዋን ተቆጣጠረች፡፡ ይኼም አፄ ዮሐንስ በሱዳን ማህዲ ታግቶ የነበረውን በጄኔራል ጎርዶን የሚመራው የእንግሊዝ ሠራዊት ካስለቀቅክልኝ ድሮውንም የአንተ የግዛት አካል የነበረችውን ምፅዋን መልሼ አስረክብሃለሁ በማለት የገባችውን ቃል በማጠፍ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች መወሳቱ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የእንግሊዝ ክህደት በሰፊው የተጻፈ ስለሆነ በድጋሚ እዚህ ለማቅረብ አልተፈለገም፡፡ የሆነ ሆኖ ምፅዋ በእንግሊዝ ትብብር ለኢጣሊያ ተላለፈችና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ‹‹አይዞሽ ኢትዮጵያ፣ ምፅዋ የትም አልሄደችም፣ እዚያው ድሮ ከነበረችበት ናት›› በሚል ስሜት እንደ አሰብ ሁሉ ነፃ የወደብ አገልግሎት ልታገኝ እንደምትችል እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 5 ቀን 1885 ይፋ አደረገ፡፡ ኢጣሊያ በምፅዋ ብቻ ሳትወሰን ይዞታዋን ወደ ዶጋሊ በማስፋፋቷ አፄ ዮሐንስ ሠራዊታቸውን በመላክ 500 ወታደሮቿን ደመሰሱባት፡፡ በዚህ የተበሳጨው የቀይ ባህር ጦር አዛዥ ለኢጣሊያ ማደግ አሰብንና ምፅዋን ብቻ መያዝ በቂ እንዳልሆነ ጠቅሶ ወደ ማዕከላዊ የኢትዮጵያ ግዛት ለመግባት የሚያስችለው ተጨማሪ የጦር ኃይልና በጀት እንዲመደብለት የኢጣሊያ መንግሥትን ጠየቀ፡፡ ምንም እንኳን ለጊዜው ኢጣሊያ የቅኝ ግዛቷን ወደ መሀል አገር ለማስፋፋት ዕቅድ እንደሌላት ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ (1887-1896 ዓ.ም.) ለአፉ ቢገልጥም፣ በኋላ ግን የኢጣሊያን የጦር ኃይል በቀይ ባህር ማጠናከርና የንግድ እንቅስቃሴዋን ማፋጠን እንደሚገባ ያምን ነበር፡፡ ሁኔታዎች ሲመቻቹለትም ኢጣሊያ በቀይ ባህር የንግድ መስመር ለምታደርገው እንቅስቃሴ ከሐበሻ ጋር የተሳሰረ መሆኑን አመነ፡፡ የውጫሌ ስምምነትን ከአፄ ምኒልክ መንግሥት ጋር የተፈራረመውም እርሱ ሲሆን፣ ስለውጫሌና ስለዓደዋ ጦርነት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ራሱን የቻለ ምዕራፍ ተሰጥቶታል፡፡

ምንም እንኳን ጁስፔ ሳፔቶ አሰብን ለሃይማኖታዊና ለንግድ እንቅስቃሴው አነስተኛ ቀበሌ ቢከራይም፣ እስከ 1880 ዓ.ም. ድረስ የቅኝ ግዛት መንፈስ እንዳልነበረ ደግሞ መታወቅ አለበት፡፡ ይልቁንም ዘመኑ አፄ ዮሐንስ አራተኛ በሥልጣን ላይ የነበሩበት በመሆኑ እኚህ ንጉሠ ነገሥት በሥራቸው የነበረችውን አንዲት የአሰብ ቀበሌ ለኢጣሊያ አሳልፈው ስለመስጠታቸው ወይም ለአሰቡ ሥልጣን ይሁንታቸውን የሰጡበት የሚገልጽ መረጃ ባለመኖሩ፣ የአሰብን ሡልጣን መሬት መሸጥና መለወጥ ለአንድ በሥራቸው ላለ ሡልጣን ለአሥር ዓመታት ፈቅደዋል እንደማለት ይቆጠራል በሌላ አገላለጽ የአፋር ምድር (ኤርትራን ጨምሮ) የኢትዮጵያ አካል አልነበረም እንደ ማለት ይሆናል፡፡ ይሁንና ዘመኑ አውሮፓውያን አፍሪካን የሚቀራመቱበት ዘመን ስለነበረ የኢትጵያ ግዛት መያዝ አስቸጋሪ ቢሆንም ዳሩ ግን አሰብን በሸፍጥ፣ በማታለል ወይም የቀበሮ ባህታዊ የሆኑትን መነኩሴ በመጠቀም ቅኝ ግዛት አድርጋ ለመያዝ ከአሥር ዓመታት በላይ ወስዶባታል፡፡

የትግራይ ሕዝብ ፀረ ኮሎኒያሊዝም እንቅስቃሴውን የጀመረው አውሮፓውያን በተለያ ምክንያቶች ዓይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ ማሳረፍ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ጥንት ቱርኮችን መክቶ እንደያዘ ሁሉ የእንግሊዞችም ምኞት እንዲመክን ያልተቆጠበ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ1882 ታላቋ ብሪታኒያ ግብፅን ከያዘች፣ እ.ኤ.አ. ጁን 26 ቀን 1885 በበርሊኑ ስምምነት አፍሪካ እንደ ቅርጫ እንድትከፋፈል ከታወጀበት፣ ይልቁንም የበርሊኑ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመያዝ ከወሰነችበት ጊዜ ጀምሮ የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ የሆነ ተጋድሎ ሲያደርግ እንደነበር የታሪክ ማስረጃዎች ይመሰክራሉ፡፡ ያ ሕዝብ በአንድ በኩል አገሩንና ነፃነቱን ከጠላት እየተከላከለ በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር በነበረው ምኞት ለበጎ ነገር ሁሉ ይስማማ እንደነበረም አይካድም፡፡ ለምሳሌ ማሕዲስቶች ግብፅን ትገዛ የነበረችውን የብሪታኒያ ጦር በስተሰሜን ሱዳን በኩል እንዳይወጣ ቢከለክሉ በምፅዋ በኩል እንዲያልፍ ፈቃደኛ ሆኗል፡፡ በሰር ዊሊያም ሔዊት የሚመራውን የብሪታኒያ የልዑካን ቡድንም በእንግድነት ተቀብሎ አስተናግዷል፡፡ ሁለቱ መግሥታት ቢዋዋሉም የአፄ ዮሐንስ ጦር አዛዥ የነበሩት ራስ አሉላ ሱዳን ውስጥ የነበሩ ስድስት ክፍለ ጦሮችን በመርዳት ሲያሳልፉ  ሕዝብ ሁነኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

ይሁንና ብሪታኒያ በሰር ዊልያም ሔዊት አማካይነት የተዋዋለችውን የውል ቃል በማጠፍ ኢጣሊያ ምፅዋን እንድትይዝ አደፋፈረቻት፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የትግራይ ሕዝብ ከጦር መሪዎቹ ጋር በመሆን ለአገሩና ለራሱ ነፃነት እጅግ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ የኢጣሊያ ተስፋፊው ጦር የሌሎች የአውሮፓ አገሮች የማቴሪያልና የሞራል ድጋፍ ስለነበረው በገንዘብም፣ በጦር መሣሪያም እጅግ የላቀ ቢሆንም እስከ አምባላጌ ጦርነት ባለው ጊዜ ሁሉ ትውልድ ሊዘነጋው የማይችል ፍልሚያ አካሂዷል፡፡ የጉራዕ፣ የጉንደት፣ የሰሐጢ፣ የዊዓና የሌሎችም ሥፍራዎች ጦርነት ሲወሳ ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ጀግንነት የተሞላበት ጀብዱ አለ፡፡ የአፄ ምኒልክ ጦር ወደ ሰሜን እስከተንቀሳቀሰበት ጊዜ ሁሉ እያንዳንዱ ቀን የትግራይ ውድ ልጆች ደማቸውን ያፈሰሱት አጥንታቸውን የከሰከሱበት ዕለት ነበር፡፡ በዓደዋ ዘመቻ ጊዜም ቢሆን ስንቅና ትጥቅ እንዲሁም አስፈላጊውን መረጃ ከማቅረብ ጀምሮ ግንባር ቀደም ተፋላሚ ሆነው ለፀረ ኮሎኒያሊዝም ድል አድራጊነት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ መሬቱም የነበረውን ዛፍ፣ እህል፣ የዱር እንስሳት መስዋዕት አድርጓል፡፡  

ወደዓደዋጉዞ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የኢጣሊያን ወረራ በመቃወም ወደ ዓደዋ ሲያመሩ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሁሉ ለመቀስቀስ ሁኔታው አስገድዷቸው ነበርና የሚከተለውን የክተት አዋጅ መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም. አሳወጁ፡፡

‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ግን ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፡፡ ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠረጥረውም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያስፈራራ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም፡፡ አሁንም ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ዕርዳኝ፣ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን ዕርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም፡፡ ማርያምን!! ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታው ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፡፡››

በዚህ ጥሪም እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ ጦሩም አምባላጌ ደረሰ፡፡ ስለአምባላጌው ጦርነት በርክሌይ ሲገልጽ፣ ‹‹አምባላጌ በተለይም ቡታ በተባለው ቦታ ላይ በአንድ በኩል በጀግናው ራስ አሉላና በራስ መንገሻ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በራስ መኮንንና በራስ ሚካኤል የሚመራው ጦር የጠላትን ወገን እንዲሸሽ አደረጉት፤›› ይላል፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹የኢጣሊያ ጦር በጀግንነት የተዋጋ ቢሆንም ሁኔታውን የሚቋቋመው አልሆነም፡፡ ከዚህ መዓት የተረፉት ኢጣሊያኖች እንዳሉት የሐበሾች ቁጥር ከመጠን በላይ ብዙ ነው፡፡ ብዙ ይሞታል፣ ነገር ግን ሌላው ወደፊት ይገፋል፡፡ የምድሩም ተኩስ አይገታቸውም፡፡ ሁኔታው ከመሬት የሚፈሉ አስመሰላቸው፡፡ ጦሩ እየተኮሰ ይገድላቸዋል፣ ነገር ግን ቁጥራቸው እየበረከተ ይሄዳል፤›› ማለታቸውን አስፍሯል፡፡ ‹‹መድፈኞች ተኩሱን እንዳቆሙ በየአቅጣጫው የራስ አሉላ ጦር ፈጥኖ እየደረሰ ጨፈጨፈው፡፡ ጄኔራል ቶዘሊም አምባለጌ ላይ ተገደለ፡፡ መቀሌም ከአርባ ቀን ጦርነት በኋላ ተያዘች፤›› በማለት በርክሌይ ስለጦርነቱ ገጽታ ጽፏል፡፡

ምንም እንኳን ኢጣሊያኖች ሽንፈት ቢደርስባቸውም ታኅሳስ 10 ቀን 1887 ዓ.ም. የኢጣሊያ ፓርላማ ባደረገው ስብሰባ ለጦርነቱ መቀጠል ከፍተኛ በጀት መመደቡ ይታወሳል፡፡ ምፅዋ ወደብ የሚደርሰው መሣሪያ ወደ አዲግራት ለማድረስ 21 ሺሕ ግመል ያስፈልግ የነበረ ሲሆን፣ አሪሞንዲ ባደረገው ጥረት ስምንት ሺሕ 200 ግመልና ሦስት ሺሕ በቅሎ ተገኝቶ እንዲጓጓዝ አደረገ፡፡ 38 ሺሕ የሚሆኑ ወታደሮች፣ 8,584 በቅሎዎችንና 100,000 በርሜሎች ከመርከብ ወርደዋል፡፡ ምንም እንኳን ይኼ ስንቅ ትጥቅም ለጊዜው ፋታ የሰጣቸው ቢመስልም ጦርነቱ ቀጥሎ መቀሌ ሙሉ በሙሉ ጥር 4 ቀን 1888 ዓ.ም. ከኢጣሊያኖች ፀዳች፡፡ የአፄ ምኒልክም ጦር አቅጣጫውን ወደ አዲግራት በማድረግ ፋንታ ፊቱን ወደ ሰሜን ምዕራብ በማዞርና ጥር 22 ቀን ከሐውዜንም ጉዞውን ወደ ዓደዋ ቀጠለ፡፡

የአፄምኒልክዘመንበጨረፍታ

የአፄ ምኒልክ ዘመን የሚባለው ንጉሠ ሸዋ ከሆኑት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ የታሪክ ጸሐፊ የሆነው አርኤችኮፊ የምኒልክ ዘመንን በሦስት ከፍሎ ይመለከተዋል፡፡ አንደኛው አውሮፓውያን ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ ወደ ሸዋ ገብተው የልማት ሥራ እንዲያከናውኑ ያደረጉበት ሲሆን፣ ሁለተኛውም በሰሜን በኩል የተሰነዘረባቸውን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም የገነቡበት ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅና ደቡብ ምዕራብ ግዛትን አንድ ለማድረግ ያደረጉት እንቅስቃሴ ይሆናል፡፡ አርኤችኮፊ እነዚህን ሦስት መሠረታዊ ወቅቶች ሲያብራራ ምኒልክ በ1865 ዓ.ም. ከአፄ ቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት ከወጡበት ጀምሮ ኤደን (የመን) ከሚገኙት የብሪታኒያና የፈረንሣይ ተወካዮች ጋር ግንኙነት የሚጀመርበትን መንገድ ማመቻቸት እንደ ጀመሩ ገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ለምኒልክ ጥያቄ እንግሊዞች ወዲያውኑ መልስ ስላልሰጧቸው ፊታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ፈረንሣይ መለሱ፡፡ ምኒልክ አውሮፓውያኑን የጠየቋቸው የጦር መሣሪያ ብቻ ሳይሆን ለሸዋ ዕድገት የሚበጀውን የልማት ሥራ ሁሉ እንዲያከናውኑላቸው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ፓቲዮ የተባለ ፈረንሣዊ ተቀጥሮ የሸዋ ወጣቶችን ዘመናዊ ውትድርና ማስተማር ጀመረ፡፡ ስዊሳዊው ኢንጂነር ፒያኖም በራስ ጎበና ትዕዛዝ ሥር በነበረው ጦር ውስጥ መኮንን ሆነ፡፡ አልፍሬድ ኤልግ ዝመርማን የመንገድና የድልድይ ግንባታውን የሚያካሂድ ሆኖ መሥራት ጀመረ፡፡ እንደ ዶ/ር አልፊዮሪና፣ ዶ/ር ትንቪርስ ያሉ ኢጣሊያዊያን የሕክምና ሰዎችም በሙያቸው አገልግሎት መስጠታቸውን ቀጠሉ፡፡

በ1869 ዓ.ም. ላይም ካቶሊካዊው ሚሽነሪ ማሳያ (አባ ማስያስ የሚባሉት) ሸዋ ገቡ፡፡ የእኚህም ሰው አመጣጥ ደቡብ ወዳለውና ከ1852-1864 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ወደ አቋቋሙት ሚሽናቸው እንዲሄዱ የምኒልክን ፈቃድ ለመጠየቅ ነበር፡፡ ምኒልክ ግን ማሳያ የመጡላቸውን ከአውሮፓ ኃይሎች ጋር ወዳጅነት እንዲፈጥሩ የሚያስችላቸውን ሰው ሲፈልጉ በነበረበት ጊዜ በመሆኑ፣ ከ1868-1879 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ለዓላማቸው መሳካት ሲሉ ሸዋ ውስጥ እንዲቀመጡ አደረጓቸው፡፡ በዚህ የሃይማኖት ሰው ምክርም አባ ሚካኤል የተባሉ ሰው በ1872 ዓ.ም. ወደ ኢጣሊያ፣ ፈረንሣይና እንግሊዝ ተላኩ፡፡ የአባ ሚካኤል መልዕክት እንደታሰበው ባይሳካም ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ኢጣሊያ በ1879 ዓ.ም. ላይ አንድ የሳይንስና ምርምር ተልዕኮ ያለው የመልክዓ ምድር ማኅበረሰብ ላከች፡፡ ለዚህም ልዑክ ምኒልክ ‹‹ልጥ ማረፊያ›› የሚባል ሥፍራ ፈቀዱለት፡፡ በታሪክ ሰዎች እንደሚባለው ከሆነ የዚህ ቡድን ሥራ በአመዛኙ ስለላ ለማካሄድ ነበር፡፡ በኢጣሊያና በንጉሥ ምኒሊክ መካከል የነበረው ግንኙነት እየተጠናከረ ሲሄድ፣ በወቅቱ የኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው ማንቺኑ አንቶኖሊ የተባለ መስፍን የኢጣሊያ ተወካይ ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ፡፡ አንቶኖሊም ከኢጣሊያ አሰብ እንደደረሰ ከአውሳው ሡልጣን ከመሐመድ ሐንፋሪ ጋር በመነጋገር እስከ ሸዋ ያለውን መንገድ ክፍት እንዲያደርግ ተስማማ፡፡ አንኮበር ላይ እ.ኤ.አ. ኤፕሪል (29) 1883 ዓ.ም. እንደደረሰም የሹመት ደብዳቤና ለምኒልክ የተላከውን ገጸ በረከት አቀረበ፡፡ ወዲያውኑም ባለ 19 አንቀጽ የወዳጅነት ስምምነት በኢጣሊያ መንግሥትና በሸዋው ንጉሥ ምኒልክ መካከል እንዲፈረም አደረገ፡፡

በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መካከል ያለው ወዳጅነት በዚህ ሁኔታ በተጠናከረ ወቅት በፈረንሣይና በኢትዮጵያ መካከል እንደዚሁ ግንኙነቱ ቀጥሎ ነበር፡፡ ይልቁንም ቀይ ባሕር በሜድትራንያን በኩል ከአውሮፓ ጋር የሚያገናኝ በገልፍ አድርጎ በህንድ ውቅያኖስ በኩል ደግሞ ወደ እስያ የሚወስድ በመሆኑ፣ በእንግሊዝ በኩል ጉዳዩ ለፈረንሣይ የሚተው አልነበረም፡፡ በመሆኑም የኦቶማን ቱርክ መንግሥት የቀይ ባሕርን አካባቢ ቢቆጣጠረውም እንግሊዝ ከ1849 ዓ.ም. ጀምሮ ዕውቅናን እንደማትሰጠው በይፋ አሳውቃ ነበር፡፡ በሁኔታው አስገዳጅነት ጭምር እንግሊዝ የጦር መሣሪያውን ብትልክም እንኳን መልዕክተኞቿን ማሰማራቷ አልቀረም፡፡ በ1869 ዓ.ም. ስዊዝ ካናል ሲከፈት ሜዲትራንያን ባሕርና ቀይ ባሕርን በማገናኘት እንግሊዝ ከኢትዮጵያ የምታገኘው ጥቅም ከፍተኛ እንደሆነ አወቀች፡፡ የእንግሊዝ ፍላጎት ሲያድግ የፈረንሣይም ማደጉ አልቀረምና በ1874 ዓ.ም. ላይ አርክኖስ የተባለው ቱጃር በአገሩና በኢትዮጵያ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር እንደሚረዳ አስታወቀ፡፡ ይኸው ሰው ገበሬዎች አስተራረሳቸውን እንዲያሻሽሉ፣ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ፣ የአውሮፓ መድኃኒት እንዲገባ፣ ወታደሮች በአውሮፓ ዓይነት እንዲሠለጥኑ፣ የአካባቢ ፀጥታ በአስተማማኝ እንዲጠበቅ ፍላጎት መሆኑን ይፋ አደረገ፡፡ ይኼም የአርክኖስ ፕሮጀክት ፈረንሣይ በቀይ ባሕር ላይ ለሚኖራት ሥፍራ አስተማማኝ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሆነ ግልጽ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1879 ካውንት ፔየትሮ አንቶኖሊ የተባለው ኢጣሊያዊው መስፍን የመጀመሪያው የመንግሥት መልዕክተኛ ሆኖ ወደ አንኮበር መጣ፡፡ እ.ኤ.አ. ሜይ 21 ቀን 1879 ላይም የወዳጅነትና የንግድ ስምምነት ተፈረመ፡፡ ስምምነቱም የሁለቱም አገሮች ዜጎች አንዳቸው የሌላውን አገር ለመጎብኘት ቢፈልጉ ነፃ ሆነው ሊጎበኙ እንደሚችሉ፣ ሁለቱም ተዋዋይ ወገኖች በሸዋና በአሰብ መካከል ያለውን መንገድ ክፍት እንደሚያደርጉና ኢጣሊያ በሸዋ ውስጥ ተጨማሪ ሥፍራ እንድታገኝ የሚያወሳ ነበር፡፡ የዚህ ስምምነት አንቀጽ አሥራ ሦስትን (XIII) ስንመለከተው የኢጣሊያ ባለሥልጣናት ምኒልክ ከአውሮፓውያን ጋር እንዲገናኙዋቸው ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ስለሚጠቅስ፣ እ.ኤ.አ. በ1889 በውጫሌ የተደረገው ስምምነት በተለይም አንቀጽ አሥራ ሰባትን አስቀድሞ ማየት ይጠቅማልና በትኩረት የምንመለከተው ነው፡፡

በዚህና ቀደም ሲል በቀረበው ምክንያት የአውሮፓ ሥልጣኔ በምድረ ሸዋ ብቅ ብቅ ሲል ታየ፡፡ ጥቂት ሰዎችም ከአውሮፓ ቋንቋዎች ጋር ተላመዱ፡፡ በ1886 ዓ.ም. ላይ የመልክዓ ምድሩ ማኅበረሰብ በእንጦጦ ሆስፒታል እንዲቋቋም ተስማማ፡፡ ምኒልክ ይህን ሁሉ ሲያደርጉ ቆይተው አፄ ዮሐንስ በመተማው ጦርነት ሲሞቱ እ.ኤ.አ. በ1889 ንጉሠ ነገሥት ተብለው ዘውድ ጫኑ፡፡

በርክለይ እንደገለጠው ከሆነ ምኒልክ ፍፁም ጥንቁቅ፣ ብልጥና ዕቅዳቸውን ለመፈጸም የታጠቁና የዕድላቸውን ዘለቄታ አስቀድመው ያወቁ የሚመስሉ ሰው ስለነበሩም በተለመደው ብልኃታቸው በመጠቀም፣ እንዲሁም የጊዜውን አመቺነት በመመልከት ከኢጣሊያ መንግሥት ጋር ንግግር ጀመሩ፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ራስ መንገሻን ለማስገበር ወደ ትግራይ ሲዘምቱ ኢጣሊም የራሷ የሆነ ዕቅድ ነድፋ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ምኒልክ የትግራይን ራስ መንገሻ ዮሐንስን ለማስገበር በጥር ወር 1882 ዓ.ም. ወደ ትግራይ ሲዘምቱ የኢጣሊያው ጄኔራል ኦሬን፣ ወደ ደቡብ ዘመቻውን ቀጥሎ ችግር ሳይገጥመው ዓደዋን ያዘ፡፡ ከዚያ በኋላም የአፄ ምኒልክ ባሕርይ እየተለወጠ ከኢጣሊያ መንግሥት ጋር የነበራቸው ግንኙነትም እየሻከረ ሄደ፡፡ ኦንቶኖሊ ለማረጋጋት ቢጥርም እንኳ አልሆነለትም፡፡

ይህም ቁልጭ አድርጎ የሚያመለክተው ኢጣሊያ ኤርትራን አጠቃልላ ከያዘች በኋላ በዚያው ለመቆየት አልቻለችም፡፡ ይልቁንም ኢጣሊያ የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ውጥረቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለባት ይሄድ ስለነበር ይኼንን የኢኮኖሚ ውጥረት ለማርገብ ከኤርትራ የእርሻ ሥፍራዎች ባሻገር ወዳሉት የኢትዮጵያ ለም መሬቶች ትኩረቷ አረፈ፡፡ ማዕከላዊው የኢጣሊያ መንግሥት ጄኔራል አርሞንዲ የራስ መንገሻን ኃይል በመደምሰስ መላው ትግራይን እንዲቆጣጠር ስላዘዘው እየገሰገሰ መቀሌንና አምባላጌን ያዘ፡፡ እስከ አሸንጌ ድረስ ከተቆጣጠረ በኋላም ኤርትራንና ትግራይን ቀላቅሎ አንድ ቅኝ ግዛት ማድረጉን እ.ኤ.አ. በ1895 አስታወቀ፡፡ በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መካከል የነበረው ግንኙነት አዲስ መልክ በመያዙም እ.ኤ.አ. ሜይ 2 ቀን 1889 በሁለቱ አገሮች መካከል አዲስ የወዳጅነትና የንግድ ውል ተፈረመ፡፡ ይኼም ውል የተፈረመው በአፄ ምኒልክና በአንቶኖሊ መካከል ሲሆን፣ ቦታውም ንጉሠ ነገሥቱ ሠፍረውበት በነበረው ወሎ ውስጥ ‹ውጫሌ› ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ በመሆኑ የውጫሌ ስምምነት ተብሎ ይታወቃል፡፡ በኢጣሊያውያን ደግሞ ‹‹የውጫሌ ውል›› ይባላል፡፡

የውጫሌ ውል ለሁለቱም ወገኖች የሚጠቅም አንቀጾች ሲኖሩበት በዚህም ስምምነት ኢጣሊያ አስመራን ጨምሮ የኤርትራን ደጋማ ክፍሎች እንድትገዛ፣ የኢጣሊያ መንግሥትም ለምኒልክ የንጉሥ ነገሥትነት ዕውቅና እንዲሰጣት፣ እንዲሁም አፄ ምኒልክ በኢጣሊያ ግዛት በኩል የጦር መሣሪያ ሊያስገቡ እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡ ይሁንና ለሁለቱም ተዋዋይ ወገኖች ወዲያውኑ ወደ አለመግባባት እንዲያመሩ ያደረጋቸው ዝነኛው አንቀጽ አሥራ ሰባት (XVII) ተደንቅሮ ተገኘ፡፡ ይኸው አንቀጽ ወደ አለመግባባት እንዲያመሩ ያደረጋቸውም በአማርኛና በኢጣሊያንኛ ሁለት ትርጉም ያለው ሐሳብ ይዞ በመገኘቱ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የውሉ የአማርኛ ትርጉም ምኒልክ ከሌሎች ኃይሎች ጋር ለመገናኘት ቢፈልጉ የኢጣሊያውያን አገልግሎት ሊጠይቁ ይችላሉ ሲል፣ የኢጣሊያንኛው ደግሞ ግንኙነታቸው በኢጣሊያ በኩል ብቻ ማድረግ እንዳለባቸው ያሰምርበታል፡፡ ምንም እንኳን የውጫሌ ውል በኢጣሊያ በኩል እንደ የኢትዮጵያ የበላይ ጥቅም አስጠባቂ (ፕሮቴክቶሬት) የሚያስቆጥራት ቢሆንም፣ በወቅቱ ወደ ግጭት ለመግባት የሚያስችላት አልነበረም፡፡ ምኒልክም ከውሉ በኋላ የውጫሌ ስምምነት ይስተካከል ዘንድ የአክስታቸው ልጅ የሆኑት ራስ መኮንን ወደ ኢጣሊያ ላኩ፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ያኔም ኢጣሊያ ቅኝ ገዥ ሹም የነበረው ጄኔራል አንቶኒዮ ባልዲሴራ ከመረብ ባሻገር ለሚያደርገው ወረራ ይዘጋጅ ነበር፡፡ ኢጣሊያ አስመራን እ.ኤ.አ. በኦገስት 1889 እንደያዘችም በዚሁ ዓመት ጥቅምት ወር ራስ መኮንን ከኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከክሪስፒ ጋር ተጨማሪ ስምምነት ተፈራረመው ነበር፡፡ በዚህ ስምምነት ኢጣሊያ የአፄ ምኒልክን ንጉሠ ነገሥትነትን በድጋሚ ከማወቋም በላይ፣ የአንድ ሚሊዮን ሊሬ ብድር እንደምትሰጣቸው ተጠቅሷል፡፡ ኢትዮጵያም የኢጣሊያን የቀይ ባሕር ባለይዞታነትን አውቃለች፡፡ (ይህም ሆነ ራስ መኮንን ሮም በነበሩበት ጊዜ የመስፋፋት ጅምራቸውን ቀጥለውበት ነበር፡፡)

በተጠቀሰው ውል መሠረት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በበላይነት የማስተዳድር ነኝ ብላ በሙሉ አፍ ለመናገር በምትችልበት ሁኔታ ላይ ስለነበረችም፣ እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 11 ቀን 1889 በበርሊኑ ስምምነት በተለይም በአንቀጽ ሰላሳ አራት (XXXIV) መሠረት ለዋና ዋናዎቹ የወቅቱ ኃያላን መንግሥታት፣ አፄ ምኒልክ በውጫሌው ውል በአንቀጽ አሥራ ሰባት ከሌሎች አገሮች ጋር የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት በኢጣሊያ በኩል እንዲከናወን የተስማሙበት መሆኑን በክሪስፒ በኩል አስታወቀች፡፡ አውሮፓውያኑም ይኼንን ማጭበርበር የተሞላበትን ልፈፋ ተቀበሉት፡፡ ከአውሮፓውያኑም በፊት ብሪታንያ ኢጣሊያ በበላይነት አስተዳድራለሁ በምትለው ግዛት እሷ በምትገዛው አገር መካከል የሚገኘውን ድንበር የሚመለከት የፕሮቶኮል ስምምነት ተፈራረመች፡፡ ይሁንና ምኒልክ የውጫሌ ስምምነት ትርጉምን ያለማወላወል ተቃወሙት፡፡ ከማንኛውም ግዴታ ራሳቸውን ነፃ ለማድረግ ይችሉ ዘንድም ብድራቸውን መለሱ፡፡ በዚህም ጊዜ ረዥምና ዕርባና የሌለው ውይይት ማካሄድ ተጀመረ፡፡ በአንድ ወቅትም ከአንቶኖሊ ጋር ሲወያዩ፣ ‹‹ኢጣሊያ ክብሯን ከመጠበቅ ይልቅ የውጫሌን ስምምነት አንቀጽ አሥራ ሰባትን በስህተት በመተርጎም ለሌሎች ኃይሎች ማሳወቅ አልነበረባትም!›› ሲሉ ምኒልክ አስታወቁ፡፡ የምኒልክ ሁነኛ አማካሪ የነበሩትም እቴጌ ጣይቱም፣ ‹‹እኛም በበኩላችን የተባለው አንቀጽ በቋንቋችን ምን ተብሎ እንደተጻፈ ለሌሎች ኃይሎች አስታውቀናል፡፡ እኛም ደግሞ እንደ እናንተ ሁሉ የምንጠብቀው ክብር አለን፡፡ የኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂ ሆናችሁ በሌሎች ኃይሎች እንድትወከሉ ብትመኙም በፍጹም የማይሆን ነው!›› በማለት መለሱ፡፡

የጦር መሣሪያ ጥይት ያለመታከት ሲገዙ የነበሩት ምኒልክ ከኢጣሊያ ጋር የተጀመረውን ውዝግብ በውይይት እንደማይፈቱት ሲገነዘቡ እ.ኤ.አ. ፌብሪዋሪ 12 ቀን 1893 የውጫሌን ውል ማፍረሳቸውን ለዓለም አስታወቁ፡፡ ፌብሪዋሪ 27 ላይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሰው ሁሉ፣ ‹‹ኢትዮጰያ የማንንም አትፈልግ፣ እጆቿን ለእግዚአብሔር ዘርግታለች›› በማለት በኩራት አወጁ፡፡ ምኒልክም ይኼን ባሉ በዓመቱ የራሳቸውን ገንዘብ አሠሩ፡፡ ከኢጣሊያ ጋር የሚደረገው ጦርነት አይቀሬ ሲሆን ኢትዮጵያ እንደሷ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ከምትከተለው ሩሲያ፣ እንዲሁም በቱኒዝያና በምሥራቅ አፍሪካ፣ ከኢጣሊያ ጋር የጥቅም ግጭት ካላት ከፈረንሣይ ጋር ወዳጅነት መሠረቱ፡፡ ወዲያውኑም ከሩሲያው ዛር ከዳግማዊ ኒኮላስ የተላከውን ልዑክ በክብር ተቀበሉ፡፡ ቆይቶም በፊታውራሪ ዳምጠው ከተማና በደጃዝማች ገነሜ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ላኩ፡፡ ወደ ፈረንሣይ የበለጠ በመቅረብም ፈረንሣዊው ካሲሚር ሞንዶን ቪዳይሌንት የመንግሥት አማካሪ በማድረግ፣ ሊዮን ቼፍንና ሲዊዛዊው አልፍሬድ ኢልግን ከፈረንሣይ ጂቡቲ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እስከነበረችው እንጦጦ ድረስ የባቡር ሐዲድ እንዲዘረጋ የተስማሙ መሆናቸውን አረጋገጡ፡፡

ምኒልክ የጦር መሣሪያ በአገራቸው እንዲመረት የነበራቸው ጥረት ከፍተኛ ስለነበረም ይኼም ፍላጎታቸው ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ሌዮን ቺፍ፣ ብሬሞንድ፣ ታይላርድና ሳቮርድ እንዲሁም አርመናዊው ሳርኪሰ ቴርዚያን ይረዷቸው ነበር፡፡  በዚህ መካከል ከኢጣሊያውያን ጋር የታማኝነት ቃለ መሐላ ፈጽመው የነበሩት ራስ መንገሻ ዮሐንስ ማንኛውንም ግንኙነታቸውን በማቋረጥ አዲስ አበባ ወደ ሚገኘው የምኒሊክ ቤተ መንግሥት ሰተት ብለው ገቡ፡፡ እ.ኤ.አ. ጁን 9 ቀን 1894 ታማኝነታቸውን አረጋገጡላቸው፡፡ ይህም በመሆኑ በሰሜን የነበረው ሁኔታ ለምኒልክ የሚያመች ሆነ፡፡ እ.ኤ.አ በ1894 ኢጣሊያውያን በዲፕሎማሲያዊ መንገድም ሆነ በተፅዕኖ ያደረጉት ሙከራ ባለመሳካቱ የቅኝ ገዥዎች ዓላማቸው የሚሳካው በጦርነት ብቻ እንደሚሆን ተገነዘቡ፡፡

ኢጣሊያውያን እ.ኤ.አ በዲሴምበር 1894 የባህታ ሐጎስን አመፅ ካከሸፉ በኋላ መረብን ተሻግረው ዓደዋ በመግባታቸው፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስም የዚህን አፀፋ በመመለስ መረብን ተሻግረው ኢጣሊያውያን ጠንካራ ምሽግ (ይዞታ) የነበረችውን ኩዓቲትን አጠቁ፡፡ በዚህ ዓደዋን ይዞ የነበረው ኤርትራ ገዥ ጄኔራል ባራቲየሪ ኩዓቲትን ለመከላከል ጦሩን አስወጣ፡፡ በጄኔራል አሪሞንዲ ጦር በመታገዝም እጅግ ከፍተኛ ውጊያ አድርጎ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 13 ቀን 1895 ራስ መንገሻ ተሸነፉና የትግራይ ጦር ወደ ሰንዓፌ አፈገፈገ፡፡ ኢጣሊያውያንም የራስ መንገሻ ጦር ከነበረበት ከሰንአፌ ተራሮች ሥር ሳይታሰብ በመጠጋት ጃንዋሪ 15 ቀን በተደረገው የአጭር ጊዜ ጦርነት ለሁለተኛ ጊዜ አሸነፏቸው፡፡ ኢጣሊያውያን በኩዓቲትና በሰንአፌ ያገኙትን ድልም ወደ ትግራይ ለመግባት የሚያስችለው በር እንዲከፈትላቸው አደረገ፡፡ ይኼንንም አጋጣሚ በመጠቀም ዓደዋን፣ ዓዲ ግራትንና መቀሌን በተከታታይ እንዲይዙ ረዳቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ራስ መንገሻ ሕንጣሎ አጠገብ ወደ ምትገኘው ደብረ ሐይላ ቢያፈገፍጉም የኢጣሊያ ጦር ኦክቶበር 9 በመውጋት እንደገና ድል አደረጋቸው፡፡ በዓደዋው ዘመቻ የመጀመሪያው ግጭት የተደረገው ኢጣሊያውያን ከሰሜን ወደ ደቡብ ዘልቀው በመግባት ደርሰውበት በነበረበውና የተፈጥሮ ምሽግ በሆነው በአምባላጌ ላይ ነበር፡፡ በዚህ ጦርነት ቀጥ ያለውን ተራራ ጦራቸውን በመምራት የወጡት ጀግናው ፊታውራሪ ገበየሁ ሲሆኑ፣ ከእርሳቸው በኋላም ግራዝማች ታፈሰ ዓባይነህና ፊታውራሪ ታከለ ተከትለዋል፡፡ ከዚያም ሌሎች የኢትዮጵያ ኃይሎች ደርሰውላቸዋል፡፡ በጦርነቱም የኢጣሊያ ጦር ክፉኛ በመመታቱ የጦር አዛዥ ሜጀር ፒየትሮ ቶዜሊ ከሞቱት አንዱ ሆነ፡፡

ምኒልክ ኢጣሊያውያን ትግራይ ውስጥ ዘልቀው መግባታቸውን እንደተገነዘቡ ሕዝባቸውን ለዘመቻ እንዲንቀሳቀስ ወሰኑ፡፡ ዝናቡ በሚያቆምበት ማለትም መስከረም ወር ላይም ወደ ሰሜን የሚዘምቱ ስለሆነ የሸዋ ሰዎች እስከ ጥቅምት መጨረሻ እሳቸው እስከሚገኙበት ሥፍራ፣ ማለትም ከአዲስ አበባ 200 ኪሎ ሜትር ያህል ከምትርቀው ወረኢሉ ድረስ እንዲመጡ አወጁ፡፡ የጎጃም፣ የደንቢያ፣ የቋራና የጎንደር ወታደሮችም ጨጨሆ ላይ፣ የሰሜን የወልቃይት ጠገዴ መቐለ ላይ እንዲገናኙ ታዘዘ፡፡ የራስ መኮንን ጦርም በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ከሐረር ተነስቶ አዲስ አበባ ደረሰ፡፡ የዓደዋ ጦርነት ዶ/ር ዓለሜ እሸቱ እንዳጠናቀሩት አፄ ምኒልክ የጦርነቱን ክተት አውጀው ከአዲስ አበባ የተነሱት ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም. ነበር፡፡ ኅዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም. አምባላጌ ላይ፣ ታኅሳስ 1888 ዓ.ም. መቀሌ ላይ በተደረገው ዘመቻ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የፍልሚያው ሥፍራ ዓደዋ ላይ የነበረ ሲሆን፣ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ያዘመቱት ጦር ቁጥር ግን በልዩ ልዩ ጸሐፊዎች የተሰላው በተለያየ ቁጥር ነው፡፡

አፄ ምኒልክ ዓደዋ ላይ ካሠለፏቸው ወታደሮች በተጨማሪ የራስ ወልደ ጊዮርጊስ ከስድስት እስከ ስምንት ሺሕ፣ የራስ ተሰማ ናደው ከአራት እስከ አምስት ሺሕ፣ የራስ ዳርጌ ሦስት ሺሕ የደጃዝማች ወልደ ፃድቅ ሦስት ሺሕ፣ የደጃዝማች ልዑል ሰገድ ሦስት ሺሕ፣ ወዘተ ግማሹ አዲስ አበባን ሲጠብቁ ሌላው ኢጣሊያውያን በአፋር በኩል ያስገቡትን ጦር ለመግጠም በመዝመቱ ዓደዋ ላይ ሳይዋጉ መቅረታቸው፣ እንዲሁም ከአፋሮች ሌላ ኢጣሊያኖች በዘይላ በኩል ሶማሌዎችን አነሳስተው ኢትዮጵያን እንዲወጉ ለማድረግ የነበራቸው ዕቅድ፣ የእንግሊዝና የፈረንሣይ መንግሥት ሳይስማሙ በመቅረታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ 

በዓደዋ ጦርነት 20 ሺሕ ያህል የኢጣሊያ ጦር የተከማቸው ሳውሪያ (ኢንቲጮ) ላይ ሲሆን፣ ይኼም ከዓድዋ በስተምሥራቅ 16 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ ሥፍራ ነው፡፡ የኢጣሊያ አሠላለፍ በአራት የተከፈለ ነበር፡፡ እርሱም፡-

ጄኔራል ዳቦርሜዳ … የቀኝ ብርጌድ 3,500 ወታደሮችና 18 መድፎች

ጄኔራል አልቤርቶኒ … የግራ ብርጌድ 8,300 ወታደሮችና 12 መድፎች

ጄኔራል አሪሞንዲ … የመሀል ብርጌድ 2,900 ጠመንጃዎችና 12 መድፎች

ጄኔራል ኤሌና … ተጠባባቂ (ሪዘርቭ) ብርጌድ 3,350 ወታደሮችና መድፎች ነበሩት፡፡

አፄ ምኒልክ ከነጦራቸው ዓደዋ ላይ የካቲት 7 ቀን 1888 ዓ.ም. ኢጣሊያውያን ደግሞ ኢንቲጮ ላይ የካቲት 6 ቀን ከሠፈሩ በኋላ፣ የሁለቱ ወገን ሠራዊት ተፋጠው እስከ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ድረስ ቆዩ፡፡ እስከዚያ ዕለትም ሁለቱም የተፋጠጡ ወገኖች ሌላውን ሲሰልለው ሰነበቱ፡፡ በመጨረሻም ኢጣሊያውያን ‹‹ኢትዮጵያ ሠራዊት ገሚሱ ቀለብ ፍለጋ ወደ ሽሬና ወደ ተንቤን እንዲሁም ተከዜን ተሻግሮ ወደ ፀለምት ተበትኗል፡፡ ሌሎች በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ወታደሮች ወደ አክሱም ጽዮን እሑድ የሚውለውን የጊዮርጊስ በዓል ለማስቀደስ ሄደዋል…›› የሚል መረጃ ስለደረሳቸው በዚሁ ዕለት ማለትም የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም. እሑድ የጊዮርጊስ ዕለት በአጥቂነት የኢትዮጵያን ሠራዊት ለመውጋት ወሰኑ፡፡ የአፄ ምኒልክ ጸሐፊ ገብረ ሥላሴ እንደሚሉትም (ገጽ 262) ቀለብ ፍለጋ አክሱም ጽዮን ከሄዱት እሑድ ለጦርነቱ የተመለሱት ከሦስት እጅ ሁለት እጅ ነበሩ፡፡

ጆርጅ ኤፍ በርክሌይ የተባለ ጸሐፊ ‹‹የዓደዋ ዘመቻን የምኒልክ አነሳስ›› በሚል ርዕስ ያሳተመው መጽሐፉ በዳኛው ወልደ ሥላሴ ተተርጉሞ እንደምናነበው፣ አፄ ምኒልክም ሆኑ የኢጣሊያው የጦር መሪ ባራቲየሪ ቀድመው ለማጥቃት ሳይሽቀዳደም አንዱ የሌላው ጠላት ስንቅ እንዲያልቅ እየተመኘ ጦርነቱን ሳይጀመር በመቆየቱ፣ ሁለቱም  ስንቃቸውን ወደ መጨረሱ ተቃርበው ነበረ፡፡ ድል በመምታት መበቀልን የፈለገው የሮማ ሕዝብ ውሎ ባደረ ቁጥር ተስፋ እየቆረጠ በመሄዱ የባራቲየሪም ክብርና ዝና ወደቀ፡፡ የካቲት 15 ቀን 1888 ዓ.ም. በሚስጥር ባራቲየሪ ተሽሮ ጄኔራል ባልዲሴራ የጦሩ አዛዥ እንዲሆን ተሾመ፡፡

ይሁንና ይኼው የጦር መሪ የካቲት 21 ቀን 1888 ዓ.ም. በማይ ገበታ በኩል ወደ ማይ ማረት ለማፈግፈግ ወስኖ መንገድ ከጀመረ በኋላ፣ በዚሁ ምሽት አራቱን ጄኔራሎች ሰብስቦ ያለው ምግብ እስከ የካቲት 23 ቀን ወይም የካቲት 24 ቀን ድረስ ብቻ የሚያቆያቸው መሆኑን ካስረዳ በኋላ፣ ወደ ሰንአፌ ለመሸሽ ወይም አስፈላጊው ጥናትና ዝግጅት እንዲያደርጉ አማከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጄኔራል ዳቦር ሜዳ የጄኔራል ባራቲየሪን ንግግር ከሰማ በኋላ መሸሹ የማይደረግ ነው ብሎ ስሜቱን ገልጾ ምክንያቱን ማስረዳት ጀመረ፡፡ አንደኛ የኢጣሊያን ሕዝብ ከምናሳፍር ሦስት ሺሕ ወታደር ቢሞትብን ይመረጣል፡፡ ሁለተኛ የወታደሩ ሞራል በጣም ይወድቃል፡፡ ሦስተኛ ጠላቶቻችን ከእኛ ፈጥነው ለመጓዝ ስለሚችሉ አሁንም በመሸሽ ላይ ሳለን ደርሰው ለራሳቸው ከሚያመቻቸውና ከመረጡት ቦታ ላይ አደጋ ሊጥሉብን ይችላሉ፡፡ ይኼ ከሚሆን ወጥተን ማጥቃቱ ይሻላል ሲል አሳሰበ፡፡

ጄኔራል አልቤርቶኒም የጄኔራል ዳቦር ሜዳን ሐሳብ ደግፎ፣ ‹‹የጠላት ጦር ምግብ ለመሰብሰብ የተበታተነ ከመሆኑም በላይ ብዙውም ወደ አገሩ በመመለስ ላይ ነው፤›› በማለት የሐበሻው ጦር ሠፈር በሁለት መሪዎች የተከፈለ ከመሆኑም በላይ፣ ከ14 ሺሕ ወይም ከ15 ሺሕ ጦር በላይ እንደማይኖረው ገለጸ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሁኔታው አፄ ምኒልክም በጣም ተጨንቀዋል፡፡ የቀራቸው ለሦስት ወይም ለአራት ቀናት የሚሆን ስንቅ ብቻ ነበር፡፡ ጠላት ከምሽጉ ወጥቶ ማጥቃት እንዲጀምር ብርቱ የሆነ ፀሎታቸው ነበር፡፡ ይኼንንም ዕድል ለማግኘት ለባሪያቲየሪ እንዲደርስ የሚያስወሩት ፕሮፓጋንዳ  ‹‹በአፄ ምኒልክ የጦር ሠፈር ችግርና ረሃብ ፀንቶ ሠራዊቱ እየሸሸ በመሄድ ላይ በመሆኑ በዙሪያው የሚገኘው ሕዝብ ተነስቷል፤›› የሚል ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ እንደተመኙትም የካቲት 22 ቀን 1888 ዓ.ም. አመሻሽ 11፡00 ሰዓት ጄኔራል ባሪያቴሪ ወጥቶ ለማጥቃት የመጨረሻ ውሳኔ ሰጠ፡፡

የባሪያቴሪ ዓላማ በሦስት አቅጣጫ ሌሊቱን ሲጓዝ አድሮ የጠላት ጦር ሳያውቅ በተራራው ገመገም ሥር ለመመሸግና የመከላከያ ቦታ ለመያዝ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ የጠላት ጦር ቢያጠቃ መልካም፣ ካልሆነም የሐበሻን ጦር ፍርኃት እንዲያድርበት በዙሪያው ለሚገኘው ሕዝብ ማሳየት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢጣሊያ ጦር ተንቀሳቅሶ የእነዚህን ተራራዎች ገመገም በሚይዝበት ጊዜ የሐበሻው ጦር በርግጎ ወደኋላ ይመለሳል የሚል እምነትና ተስፋ ነበረው፡፡ ይህም ከሆነ ዓደዋን በሰላም (ያለ ችግር) ለመያዝ እንደሚችልም ገምቶ ነበር፡፡ የጦሩ አሠላለፍም፣

ሀ. በቀኝ በኩል በጄኔራል ዳቦር ሜዳ የሚመራው የበላህን ተራራ አምባ፣ የበላህን ጎጥና በዙሪያው ያለውን ቦታ፣

ለ. በመካከል በጄኔራል አሪሞንዲ የሚመራው የበላህን ተራራ፣

ሐ. በግራ በኩል ‹‹በጄኔራል አልቤርቶኒ የሚመራው ኪዳነ ምሕረት ብለው የጠሯትና (ለዚች ተራራ የተሰጠው ስም በትክክል አልነበረም) ራይ የተባሉትን ተራራዎች እንዲዝ፣

መ. በጀኔራል ኤሌና የሚመራው ተጠባባቂው ጦር ረቢ አርኧየኒ በተባለው ቦታ ሆኖ እንዲጠባበቅ፣

የቀኑ ትዕዛዝም ‹‹የካቲት 22 ቀን 1888 ቁጥር 87 ዛሬ ማታ ጦሩ በሦስት አቅጣጫ ወደ ዓድዋ በሚከተለው ሁኔታ ይቀንሳል፡፡

‹‹… የቀኙ ክፍል ጄኔራል ዳቦር ሜዳ 2ኛ እግረኛ ጦር ብርጌድ የሞባይል (ተንቀሳቃሽ) ሻለቃ ጦር የ2ኛ ባትሪ ብርጌድ አባሎች፣ የአምስተኛ፣ የስድስተኛ፣ የሰባተኛ ከባድ መሣሪያ ጓድ፡፡ ‹‹…ግራው መስመር በጄኔራል አልቤርቶኒ (የሚመራ ሆኖ) አራት የአገሬው ተወላጅ ሻለቃ ጦር የአንደኛ ባትሪ ብርጌድ አባሎች፣ ከአንደኛ፣ ከሁለተኛ፣ ከሦስተኛ፣ ከአራተኛ ከባድ መሣሪያ ክፍል ጋር፡፡ ተጠባባቂ ጄኔራል ኤሌና፣ ሦስተኛ እግረኛ ብርጌድ፣ ሦስተኛ የአገሬው ተወላጅ ሻለቃ ጦር ሁለት የመትረየስና የከባድ መሣሪያ ጓድና አንድ ሻምበል መሐንዲሶች፡፡ ‹‹…ጄኔራል ዳቦር ሜዳ፣ በአርሞንዲና በአልቤርቶኒ የሚመራው ጦር ከሌሊቱ ሦስት ሰዓት ከቦታው እንዲንቀሳቀስ ሲታዘዝ ከአንድ ሰዓት በኋላ ደግሞ ተጠባባቂው ጦር የመካከለኛውን መሥመር ተከትሎ ይንቀሰቀሳል፡፡

‹‹…የቀኙ ረድፍ በዛሃላ ጎጥ አድርጎ ጎልደም ጎጥን አልፎ ወደረቢ አርእየኒ ጎጥ ይጓዛል፡፡ የመካከለኛው ተጠባባቂ ረድፍ በአዲ ዳኪ አድርጎ በጉንድብታ በኩል ረቢ አርእየኒ ይጓዛል፡፡ የግራው ረድፍ በአዲ ዳኪ አድርጎ በጉንደብታ በኩል ረቢ አርእየኒ ይጓዛል፡፡ የግራው ደግሞ ከሶሎዳ በአዲ ቸራይራ በኩል ወደ ኪዳነ ምሕረት ይጓጓል…›› የሚል ነበር፡፡ (በዚህም ዓይነት ኢጣሊያኖች ብዛቱ 100 ሺሕ የሚሆን የጦር መሣሪያ ጦርና ጋሻ የያዘውን የሐበሻ ሠራዊት ለመግጠም 17,700 ወታደሮችና 56 መድፎች ጠምደው ተሰናድተዋል፡፡ (በዶ/ር እሸቴ ዓለሜ የተጠናቀረውን ልብ ይሏል)

በአፄምኒልክግንባርየተሠለፈውጦርበዶ/እሸቴዓለሜጥንቅር

አፄ ምኒልክ ከነጦራቸው ዓድዋ መጋቢት 3 ቀን 1888 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ ኢጣሊያውያን ኢንቲጮ ድረስ ሄደው ለመውጋት ያልፈለጉበት ምክንያት ቦታው ለአጥቂ ጦር የማያመች መሆኑን ገብረ ሥላሴ ለሞንድ ቬዳይሌት በየካቲት 7 ቀን 1888 ዓ.ም. ገልጸዋል፡፡ ከዚያም ጊዜ አንስቶ እስከ የካቲት 23 ቀን ቆይተዋል፡፡

የካቲት 22 ቀን 1888 ..

…አልቤርቶኒ የታዘዘውን ትክክለኛ የጦር ሠፈር በመፈለግ ከሌሎቹ የኢጣሊያ ብርጌዶች ተነጥሎ ኪዳነ ምሕረት ኮረብታ ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት አካባቢ ሲደርስ፣ በሜጀር ቱሪቶ ይመራ የነበረው የብርጌዱ ግንባር ቀደም ጦር ብሎ በመድረሱ፣ በዚህ ቀን በጥበቃ ተራ ላይ ከነበረው ከራስ መንገሻ ዮሐንስ እንዲሁም ጥቂት ቆይቶም ከዋግ ሹም ጓንጉል፣ ከደጃች ገሠሠና ከበጅሮንድ ባልቻ ሠራዊት ጋር ውጊያ እንደጀመረ፣ ኮንቲሮዘኒ የተባለው የታሪክ ጸሐፊ መዝግቦታል፡፡

ይኼው ኮንቲሮዚ የተባለው ጸሐፊ ዓደዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከእቴጌ ጣይቱና ከአቡነ ማቴዎስ ጋር ያስቀድሱ የነበሩት አፄ ምኒልክ፣ የኢጣሊያ ወታደር በዚህ ቀን ጦር ለማድረግ መወሰኑን በተረዱ ጊዜ ሠራዊታቸውን በያለበት ቀስቅሰው ከእቴጌ ጣይቱና ከአቡነ ማትያስ ጋር ሆነው ከዓደዋ ተነስተው በምሥራቅ በኩል በሚገኘው አባ ገሪማ ኮረብታ ላይ ሠፍረው ነበር፡፡ የአልቤርቶኒ ብርጌድ ኪዳነ ምሕረት እንደሰፈረና ግንባር ቀደሙም ጦር አልፎ መምጣቱን እንደሰሙ በነፊታውራሪ ገበየሁ፣ በነደጃዝማች በሻህ አቡ የሚመራውን የራሳቸው ጦር ፊት ለፊት፣ የእቴጌ ጣይቱንና የጎጃሙን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጦር በስተግራና በስተቀኝ እንዲዘምቱ አዘው ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት ሲሆን ጦርነቱ ተጀመረ፡፡

…ከዚያ በኋላ ነጋሪት መቺው ‹‹ውጋ! ውጋ!›› እያለ እየተበረተታ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት በግራና በቀኝ በሁሉም አቅጣጫ ከቦ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ አብረው በሚያዙት ላዳት (አባ ገሪማ አጠገብ) 3 ኪሎ ሜትር ከጠላት ሠፈር ርቆ ይገኝ የነበረውን የኢትዮጵያ ከባድ መሣሪያ (መድፍ) እየተደገፈ፣ በጄኔራል አልቤርቶኒ ይመራ የነበረውን የኢጣሊያ ጦር ደመሰሰው፡፡ ከዚህ በኋላ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ተኩል ሲሆን ጄኔራል አልቤርቶኒ የተረፉ የኢጣሊያ ወታደሮችና መድፈኞች ወደኋላ እንዲሸሹ አዞ ነበር፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ሠራዊት ማየል ጄኔራል አልቤርቶኒ ከብዙ መቶ ኢጣሊያውያን ጋር ተማረከ፡፡ … ጦርነቱም ከረፋዱ አምስት ሰዓት አካባቢ ሲሆን አበቃ፡፡ ኤርትራንና ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የመግዛት ህልምም ዕውን ሳይሆን ቀረ፡፡ ታላቁ የዓደዋ ድል የመላው ዓለም ጥቁሮች መመኪያ ሆነ፡፡ ይህ ታሪካዊ ድል 121 ዓመታት ቢያልፉትም፣ አሁንም አንፀባራቂ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሲኮራበት ይኖራል፡፡

ወደሰላምማስፈን

ታላቁ የዓደዋ ፀረ ኮሎኒያስት ጦርነት በኢትዮጵያዊያን የበላይነት ከተጠናቀቀ በኋላ የኢጣሊያ ቅኝ አገዛዝ መሐንዲስ እየተባለ ይጠራ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ ከሥልጣኑ ለቀቀ፡፡ በዚያም ወቅት ኢጣሊያ በአፍሪካ ስለሚኖራት የወደፊት ዕጣ ፋንታም የሞቀ ክርክር ይደረግበት ጀመር፡፡ አንዳንዶቹ የቀኝ የፖለቲካ ሰዎች ኢጣሊያ የብቀላ ዕርምጃ ትውሰድ ብለው ሲጮሁ፣ የግራ አዝማሚያ ተከታዮች ደግሞ ከአኅጉሩ ፈጽማ መውጣት አለባት ብለው ጠየቁ፡፡ ያም ሆነ ይህ የጄኔራል ባራቲየሪ በጦር አመራር ብቃት ማነስ ምክንያት በሕግ ተጠያቂ ሆነ፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ የተመረጠው የሩንዲው መሥፍን አንቶኒዮ ስታራባም ክሪስፒ ያራምደው የነበረውን የመስፋፋት ፖሊሲን እንደማያራምድ በማስታወቅ ሁለቱን አገሮች የሚያስማማ መንገድ መከተል መረጠ፡፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት (ፓፕ) ሊዮ አሥራ ሦስተኛን በማሳመን አፄ ምኒልክ ለያዟቸው የኢጣሊያ ምርኮኞች ምሕረት እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ደብዳቤ እ.አ.አ. ሜይ 1896 እንዲጽፉ አደረገ፡፡ አፄ ምኒልክም በምሕረቱ በመስማማት ምርኮኞችን የመልቀቁ ሁኔታ ኢጣሊያ የሰላም ስምምነት ለማድረግ ባላት ፍላጎት ላይ የሚወሰን መሆኑን አሳወቁ፡፡

አብዛኛው ጊዜ ‹‹የአዲስ አበባ ውል›› እየተባለ የሚታወቀውና በውሉ ርዕስ እንደሠፈረው ለዘለዓለም የሚዘልቅ የሰላም የወዳጅነት ተብሎ የሚታወቀውን ስምምነት ኦክቶበር 26 ቀን 1896 ተፈረመ፡፡ በዚህ ውል ኢጣሊያ የውጫሌ ውል እንዲሰረዝና ኢትዮጵያ ፍፁም ነፃ አገር መሆኗን አወቀች፡፡ ይሁንና አፄ ምኒልክ ያለፈው ስምምነት ያስከተለውን ውስብስብ ችግር በማስታወስ ይኼ ውል በኢጣሊያንኛ ሳይሆን በአማርኛና በፈረንሣይኛ እንዲጻፍ ወትውተው ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ በሁለቱ አገሮች መካከል መግባባት የተመላበት ወዳጅነት ደረጃ በደረጃ ሲመሠረት የዲፕሎማቲክ መልዕክተኞችም ተለዋውጠው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የዓደዋ ጦርነት በሁለቱም አገሮች በኩል በቀላሉ የሚረሳ ሊሆን አልቻለም፡፡ ከአርባ ዓመታት በኋላም ቤኒቶ ሞሶሎኒ በተባለ ፋሺስት መሪ ግፊት አዲስ ወረራ ተካሄደ፡፡

ማስታወሻ

ይኼንን ጽሑፍ ያጠናቀርኩት ቤካ ነሞ ዓደዋና ምኒልክ፣ ጆርጅ ኤፍ በርከላይ የዓደዋ ዘመቻ፣ የአፄ ምኒሊክ አነሳስ ቀኛዝማች ታደሰ ዘውዴ፣ ጣይቱ ብጡል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓደዋ በዓል አዘጋጅ ኮሚቴ የኤግዚቢሽን መግለጫ አይቼ መሆኑንና አቶ አህመድ ዘካሪያና ፕሮፌሰር ፓንክረስትም አንዳንድ መረጃዎችን ስለሰጡኝ በትህትና አስታውሳለሁ፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

Standard (Image)

የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበት ትክክለኛ ጊዜ አሁን አይደለም?

$
0
0

 

በመታሰቢያ መላከሕይወት ገብረ ክርስቶስ

በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በተለይ የቅኝ ግዛት ካበቃ በኋላ የባንክ ሥራን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የምዕራባውያን ባንኮች ተቆጣጥረውት ነበር፡፡ ይህም ወቅት ዳግማዊ ቅኝ ግዛት እየተባለ የሚታወቅ ሲሆን፣ እነዚህ ባንኮች ለአፍሪካ ሕዝብ ድህነትን  እንጂ ማኅበራዊ ዕድገትን አላመጡለትም፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ ዘዴዎችንና የረቀቁ ተንኮሎችን በመጠቀም ራሳቸውን ብቻ ተጠቃሚ ሲያደርጉ ቆዩ እንጂ፣ ለማኅበራዊ ዕድገት ያበረከቱት አስተዋፅኦ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

በወቅቱ የነበሩ ፖለቲከኞችም ሆኑ ምሁራን የሚሠሩትን ተንኮል በአግባቡ የተረዱ ባለመሆኑ፣ ለዕድገት ምንም ተጨባጭ አጋር መሆን አልቻሉም ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ ግን መላው የአፍሪካ አገሮችም ሆኑ የእኛም አገር ይህንን ሁኔታ ማወቅና መቆጣጠር የተቻሉበት በመሆኑ፣ አስፈላጊውን ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ለዕድገትና ለልማት አጋሮች ማድረግ የሚቻልበት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘባቸው ባለፉት 26 ዓመታት (ምንም እንኳን ሕዝባዊ እርካታን የፈጠረ ባይሆንም) መላው አገሪቱን ያዳረሰ የመንገድ መሠረተ ልማት፣ ከፍተኛ የሆነ የኃይል አቅርቦት፣ የቴሌኮም መረብ፣ የትምህርት ተቋማት፣ የሲሚንቶና የብረት ፋብሪካዎች፣ ወዘተ በስፋት ተገንብተዋል፡፡

እነዚህ ተግባራት አንድ አገር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ለመሳብ ከሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ከእነዚህ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶች አንዱና ዋነኛው በቂ የካፒታል አቅርቦት የሚያመጡ የውጭ ባንኮች ናቸው፡፡

መንግሥት ከውጭ የሚበደራቸው ብድሮችን ተጠቅሞ የሚገነባቸው መሠረተ ልማቶች የግሉ ዘርፍ እየተጠቀመና ቶሎ ቶሎ ታክስ እየከፈለ መንግሥት ዕዳውን መክፈል እንዳይችል ዋነኛው ማነቆ፣ የግሉ ዘርፍ እንደ ልቡ የሚበደረው የገንዘብ አቅርቦት አለ መኖር ነው፡፡ አሁን በአገራችን ያሉት ባንኮች እንኳን ምንም መያዣ ለሌለው ተበዳሪ ቀርቶ፣ በርካታ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሀብት ላለው ተበዳሪ እንኳን በተገቢው መጠንና ፍጥነት ገንዘብ ማበደር አይቻሉም፡፡

ብዙ ጊዜ ከመንግሥት ባለሥልጣናት የሚሰማው የአገር ውስጥ ባንኮች እስኪጠናከሩ ነው የውጭ ባንኮችን የማናስገባው የሚል አባባል ነው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት የአገር ውስጥ ባንኮች እስኪጠናከሩ ስንት ትውልድ (የሚለማ ሀብት፣ መሬት፣ በርካታ ነገር እያለን) በድህነት ለመኖር የሚገደደው?

ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በአገራችን በበቂ ሁኔታ እየተመረተ ያለው የሲሚንቶ ምርትን ብንወስድ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሰፊውን ገበሬ በበቂ ሁኔታ ሊደርስ አልቻለም፡፡ ፋብሪካዎቹም በሙሉ አቅማቸው ሠርተው ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፡፡ ገበሬው እንደ ልቡ ተበድሮ የመስኖ ሥራ፣ የውኃ ማጠራቀሚያ፣ የከብት በረት፣ ሽታ አልባ መፀዳጃ ቤት፣ የእህል ጎተራ፣ አነስተኛ ድልድዮች፣ ወዘተ በመገንባት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ መሠረታዊ ለውጥ ማየት ይቻላል፡፡

ሲሚንቶ ደግሞ ሙሉ በሙሉ የአገር ውስጥ ምርት በመሆኑ ገጠርን መሠረት ያደረገ የኢኮኖሚ ዕድገት ማየት ይቻላል፡፡ በአሁኑ የባንኮች የማበደር ፖሊሲ ምናልባት ለማዳበሪያ የሚሆን ብድር ይቀርቡለታል እንጂ፣ ሕይወቱን በመሠረቱ ሊለወጥ የሚችል የረጅም ጊዜ ብድር የሚያቀርብ የገንዘብ ተቋም የለም፡፡ በመሆኑም የድህነት አዙሪት ሊቆም አልቻለም፡፡

እዚህ ላይ የግል አስተያየቴን ለመግለጽ ከተፈቀደልኝ በእኔ እምነት የአገር ውስጥ ባንኮች አደጉ አላደጉ ለተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምኑ ነው? አሁን አደጉ የተባሉትን ባንኮችን ብንመለከት ለባለአክስዮኑ ከትርፍ ላይ ተቀንሶ የተገነባ ሕንፃን የባለቤትነት ሰነድ እንኳን ለመስጠት የሞከረ ባንክ የለም፡፡ የዛሬ 20 ዓመት የተሸጠ አንድ አክሲዮን ለምሳሌ አንድ ሺሕ ብር ቢሆን አሁንም ዋጋው ያው አንድ ሺሕ ብር ነው፡፡ በቅርቡ አክሲዮናቸውን እንዲተው የተገደዱት ትውልደ ኢትጵያውያን ይህንን መጠን ይዘው ነው እንዲወጡ የተደረገው፡፡

በአገር ደረጃ ደግሞ ስንመለከት አትራፊ ለሆኑ የሥራ ዘርፎች ያለ ብዙ ውጣ ውረድ ብድር በበቂ ሁኔታ ማቅረብ የቻሉበት ሁኔታ የለም፡፡ እነዚህ የግል ባንኮች አሁንም ከራሳቸው ትርፍ በስተቀር ምንም ዓይነት አገራዊ ኃላፊነት መሸከም የቻሉበት አግባብ አልተፈጠረም፡፡

የውጭ ባንኮች ያለ ገደብ ወደ አገር ውስጥ መግባት ቢችሉ ኢትዮጵያ እጅግ በርካታ የገንዘብ ያለህ የሚሉ ሊለሙ የሚችሉ ሀብቶች ያላት አገር በመሆንዋ በአገሪቱ ውስጥ ተጨባጭ ዕድገትን ማየት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ባንኮቹ ራሳቸው አዋጭ የሆኑ ሌሎች የሥራ ዘርፎችን በማጥናት ኢንቨስት ስለሚያደርጉ ከፍተኛ የሥራ ዕድልና የታክስ ገቢ ማመንጨት ይቻላል፡፡

መንግሥት ደጋግሞ እንደሚነግረን መሬት ሳይሆን ገንዘብ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ ውስን ሀብት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ማንኛውንም ባለሀብት ሥራህን ለማስፋፋት ያለህ ችግር ምንድነው ቢባል፣ ሁሉም ባለሀብቶች በአንድነት የሚናገሩት ገንዘብ የሚል ነው የሚሆነው፡፡

መሬት እንኳን ለእኛ ለልጅ ልጆቻችን ከበቂ በላይ ያለ ሀብት ነው፡፡ ባለፉት 26 ዓመታት በሲሚንቶ አቅርቦት፣ በኃይል፣ በመንገድ፣ በቴሌ፣ በፋብሪካዎች፣ ወዘተ በተጨባጭ ለውጥ ታይቷል፡፡ የገንዘብ አቅርቦት ግን ምን ዓይነት መሻሻል ማሳየት አልቻለም፡፡ ገንዘብ የሌላ ሀብት ሳይሆን በዓለማችን በተትረፈረፈ መጠን ያለ ሀብት በመሆኑና የውጭ ባንኮች ደግሞ ይዘውልን ሊመጡ ስለሚችሉ ይህንኑ ተገንዝበን ፖሊሲያችንን በቶሎ ማረም አለብን፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው በአገራችን ውስን የሆነ የመሬት ሀብት ሳይሆን ያለው፣ አሠሪ ሳይሆን አሳሪ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ከአገሪቱ የተፈጥሮና የሰው ሀብት ጋር በፍፁም የማይሄድ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ነው፡፡

በቅርቡ ደረጃ በደረጃ በመገባደድ ላይ ያለው የዓባይ ግድብ የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሰው በመሆኑ፣ ይህንን የኃይል አቅርቦት የሚመጣጠን የገንዘብ አቅርቦት መኖሩ የግድ ይላል፡፡ ለዚህ ነው የውጭ አገር ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ይህንን ክፍተት ይሙሉት የምለው፡፡

ፈረንጆች አንድ አባባል አላቸው፣ “Putting the dots together” ይላሉ ይህ አባባል በሁሉም የሕይወት ዘርፍ ውስጥ ትክክለኛ ነው፡፡ ለማብራራት ያህል አንድ ሰው የተለያዩ ነጥቦችን አስቀምጦ እነዚህን ነጥቦች ሲያገናኛቸው አንድ ምሥል ይፈጥራሉ፡፡ አሁን በአገራችን በቂ ኃይል እየተመረተ ነው፡፡ ሲሚንቶ፣ የቴሌ ኔትወርክ፣ መንገድ፣ ባቡር፣ በቂ የሰው ኃይል፣ ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት ሌሎችም እንደ ብረት የመሳሰሉት የግንባታ ውጤቶች፣ ወዘተ በበቂ ሁኔታ ይመረታሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን ነጥቦች አገናኝተን አንድ ምሥል ለመፍጠር ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ምሥሉ የተሟላ ይሆናል፡፡ በዜጎች ላይ የሚታይ የኑሮ መሻሻል ይታያል፡፡ የውጭ ባንኮች ይህንን ነጥብ በመሙላት የተሟላ ያደርጉታል፡፡ በመሆኑም መንግሥትም ሆነ ማንኛውም ዜጋ ይህንን መገንዘብ አለበት፡፡

ሌላው የውጭ ባንኮች እንደ አገራችን ባንኮች ሌሎች ባጣኑት ላይ ብቻ ተመርኩዘው ሳይሆን ብድር የሚያቀርቡት፣ ራሳቸው የጥናቱ አካልና በቂ ሥራ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ይህንንም ለማድረግ በቂ የሠለጠነ ሰው ኃይል አላቸው፡፡ ከዚህም አልፈው በራሳቸው አነሳሽነት የተለያዩ የገበያ ጥናቶችን አጥንተው ኑ በዚህ ዘርፍ ኢንቨስት አድርጉ፣ እኛ ገንዘብ እናቀርባለን የሚሉበት አሠራርም ስላላቸው በአገሪቱ ውስጥ ተጨባጭ የሆነ እመርታ ማየት ይቻላል፡፡ ይህ አሠራር እስካሁን ባለው የአገራችን ባንኮች አሠራር የሚታሰብ አይደለም፡፡

መንግሥት ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ ፍንጭ ቢያሳይም፣ ቁርጥ ያለና ግልጽ የሆነ የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ አልቻለም፡፡ ይህ ደግሞ በዕቅድ የሚመራ ኢኮኖሚ መገለጫ አይደለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ሊለማ ከሚችለው ሀብቷ አኳያ ያለው የገንዘብ አቅርቦት (በተለይ ለግሉ ዘርፍ) እጅግ አናሳ ከመሆኑ የተነሳ፣ በርካታ ባለሀብቶች በእጅጉ ከአቅማቸው በታች ለመሥራት የተገደዱበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

ባንኮቻችን ያላቸው ጥሬ ገንዘብ (Liquid Cash) ሥራ ከሚፈልገው ወጣት ቁጥር፣ ማደግ ከሚፈልገው ባለሀብት፣ ከአገሪቱ አጠቃላይ ሀብት ወይም (Resource) ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ እጃችንን አጣጥፈን በድህነት ለመኖር ተገደናል፡፡ ሌላው ቀርቶ ምንም ዓይነት የመክሰር አደጋ የሌለባቸው የሥራ ዘርፎች እንኳን ገንዘብ ለማግኘት በእጅጉ የሚቸገሩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ያላቸውን ገንዘብ ማስቀመጫ ያጡ በርካታ አገሮች አሉ፡፡ አንድ አገር ለማደግ እጅግ ተመራጩ መንገድ የዜጎችን ጉልበት መበዝበዝ ወይም ሌላ አማራጭ ሳይሆን፣ ይህንን የተትረፈረፈ የገንዘብ ክምችት ወደ አገር ውስጥ እንዲመጣ በማድረግ በቀላሉ ከመሬት መነሳት የሚቻልበት ወቅት ነው፡፡

ከጥቂት አሥርት ዓመታት በፊት ዛሬ የተትረፈረፈ ገንዘብ ያላቸው አገሮች ራሳቸው በድህነት ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት ግን በዓለማችን ያሉ በርካታ አገሮች አስደናቂ ዕድገት በማስገንዘባቸው ከተረጂነት ወደ ዕርዳታ አቅራቢነትና አበዳሪነት የተሸጋገሩበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡

ታዲያ ይህንን የዜጎችን ሕይወት በአስተማማኝ ሁኔታ ሊለወጥ የሚችል ሀብት ወደ አገራችን እንዳይገባ በሩን ዝግ አድርገን መቀመጥ ትክክል ያልሆነ ተግባር ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በርካታ አገሮች በአገራቸው ሊጠቀሙበት ያልቻሉትን ገንዘብ ወደ ሌሎች አገሮች ኤክስፖርት በማድረግ የሚቀጥለውን ትውልድ ተጠቃሚ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ እኛ ደግሞ ይህ በጣም ያስፈልገናል፡፡ የአገራችን ኢኮኖሚ ለማንኛውም ዘርፍ በበቂ ሁኔታ ገንዘብ ማቅረብ እስኪጀምር ድረስ ይህንን መሞከር አማራጭ የሌለው ተግባር ይመስለኛል፡፡

ዋናውና ትልቁ ቁምነገር መንግሥት የቁጥጥር ሥርዓቱን በሠለጠነ መንገድ በማጠናከር ያልተጠበቀ ችግር እንዳይፈጠር ተግቶ መሥራት ነው፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ሲበደር ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በዜጎች ላይ ይህ ነው የሚባል የኑሮ መሻሻል አልታየም፡፡ ምክንያቱም ብድሩ ለሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች በበቂ ሁኔታ መቅረብ ባለመቻሉ ነው፡፡ የውጭ ባንኮች በአገር ውስጥ ቢኖሩ ግን በራሳቸው ጥናት ጉድለቶችን በመሙላት በዓይን የሚታይ ለውጥ ማየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ መንገድ ለመገንባት መንግሥት ከውጭ ባንክ ቢበደርና መንገዱ ቢገነባ የግሉ ዘርፍ ደግሞ ከአገር ውስጥ ወይም የውጭ ባንክ ተበድሮ ሆቴል ቢሠራ መንገዱ ገቢ ማመንጨት ቻለ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም መንገዱ መሥራቱ ብቻ ኢኮኖሚ ለውጭ ሊኖር አይችልም፡፡ መንገዱን ተከትሎ ባንኮች ቶሎ ቶሎ የገንዘብ አቅርቦት ካዘጋጁና በመንገዱ ግራና ቀኝ ኢንቨስትመንት ሲስፋፋ መንገዱ አገራዊ ፋይዳ ኖረው ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ዜጎቻችን ሥራ ፍለጋ ወደ ሌሎች አገሮች እየተሰደዱ ነው፡፡ መሆን የነበረበት ግን ካፒታሉ ወደ አገራችን ቢሰደዱ ዜጎች እዚሁ ሥራ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ ስደት ይቆማል ማለት ነው፡፡

በኢኮኖሚ የበለፀጉ አገሮች ውስጥ ያሉ አንዳንድ ባንኮች ለአስቀማጮች ገንዘብ የአገልግሎት ክፍያ ያስከፍላሉ፡፡ በተቃራኒው በእኛ አገር አንድ ሰው አሥር ወይም 20 ሚሊዮን ብር ባንክ ቢያስቀምጥ በወለዱ ብቻ መኖር ይችላል፡፡ ይህ አሠራር መለወጥ አለበት፡፡ ሰው ገንዘብ አስቀምጦ ሳይሆን ጥሩ ኑሮ መኖር ያለበት፣ በገንዘብ ሠርቶ ነው መጠቀም ያለበት፡፡

ይህ ሊሆን የቻለው ባንኮች ባላቸው ውስን የማበደር አቅም ምክንያት ለአስቀማጮች ከፍተኛ የሚባል ወለድ እየከፈሉ ኪራይ ሰብሳቢነትን እያስፋፋ ነው፡፡ የውጭ ባንኮች ከፍተኛ የሚባል ካፒታል ይዘው ወደ አገር ውስጥ ቢገቡ ይህ ጨዋታ በአንድ ጀንበር ያቆማል፡፡

አሁንም መንግሥት በተደጋጋሚ እንደሚነግረን መሬት ውስን ሀብት ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ በአገራችን የተትረፈረፈ የመሬት ሀብት አለ፡፡ ውስን የሆነው ሀብት የገንዘብ አቅርቦት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዓለማችን በተትረፈረፈ መጠን የሚገኝ ሀብት ነው፡፡ የጎደለን ትክክለኛውን ፖሊሲ የሚከተል አሠራር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ይህንን የተትረፈረፈ የገንዘብ ሀብት ሥራ ላይ ልታውል የምትችልበት በቂ ቅድመ ሁኔታዎች ያሟላች አገር በመሆንዋ፣ የግሉ ዘርፍ ኪራይ ሰብሳቢ በሆኑ ተግባራት ላይ እንዳይሰማራ በሩን በማጥበብ አምራች እንዲሆን የሚያስችለውን በር በርግዶ መክፈት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ነው በዓይን የሚታይ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው፡፡

እነ ቻይና አገራቸውን ሲገነቡ በዚህ መልክ ወደ አገራቸው ገንዘብ ይዞ ሊመጣ የሚችል ኢንቨስተር አልነበረም፡፡ በመሆኑም የሕዝባቸውን መብት በመርገጥና ጉልበቱን በመበዝበዝ የካፒታል ክምችት መፍጠር ቻሉ፡፡ እኛ በአሁኑ ዘመን ይህንን ማድረግ አይጠበቅብንም፡፡ ትክክለኛ ፖሊሲን ከገንዘብ ጋር ማገናኘት ብቻ ነው ያለብን፡፡

በግብርናው ዘርፍ ያለውን የገንዘብ እጥረት ለመግለጽ የሚረዳ አንድ መንግሥት ያወጣው መረጃ አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ከ40 ሚሊዮን ሔክታር በላይ የሚታረስ መሬት አለ፡፡ እየታረሰ ያለው ግን ከ13 ሚሊዮን አይበልጥም፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ከ26 ዓመታት በኋላም አሁንም ስንዴ ከውጭ እያስገባን ነው፡፡ ይህ እውነታ የሚያሳየው ምን ያህል በብልሹ አሠራር ተተብትበን እንዳለን ነው፡፡ ሊሠሩ የሚችሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እጆች እያሉ፣ በቂ መሬትና ዝናብ እያለ ለ26 ዓመታት ይህንን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ማስወገድ እንዴት አቃተን? ለዚህ ነው መንግሥት ከተራ የችርቻሮ ሥራ ወጥቶ የመንግሥት ሥራ የሆነውን ትክክለኛ ፖሊሲ ማውጣት ላይ በበቂ ሁኔታ ቢጠመድ ተገቢ ነው የምለው፡፡

የብዙ ሰዎች ሥጋት የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ቢገቡ ያገኙትን የተጣራ ትርፍ በውጭ ምንዛሪ ይወሰዱታል የሚለው ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ያተረፉትን የተጣራ ትርፍ መልሰው ኢንቨስት ሊያርጉ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል በመኖሩ፣ ለሚቀጥሉት ከአሥር እስከ 20 ዓመታት ወደ አገራቸው ገንዘብ ለመውሰድ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ያቀርባሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡

ከዚህ ቀደም ባቀረብኳቸው ጽሑፎች ደጋግሜ እንደገለጽኩት የውጭ ባንኮች ሲገቡ ሁሉም ዓይነት የፖሊሲም ሆነ የሕግ ማዕቀፎች በአንድ ላይ በአንድ ፓኬጅ ሆነው መሄድ ስላለባቸው፣ ይህም ጉዳይ በተፋጠነ ሁኔታ ይታሰብበት እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው metasebyamelaku@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

 

Standard (Image)

ተደምሮ ዜሮ - አገርን በዘመቻ የመምራት ጥበብና ውጤቱ

$
0
0

በብርሃኑ ዘለቀ

      ሪፖርተርን ጨምሮ ከተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘመቻ ሊጀመር መሆኑን ስሰማ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ራሴን እንድጠይቅና ከቅርብ ጓደኞቼ ጋር ውይይት እንዳደርግ አስገድዶኛል፡፡ በዓለም ላይ እንደኛ ሁልጊዜ ሥራን በዘመቻ የሚሠራ አገር ይኖር ይሆን?

አገርን በዘመቻ የመምራት ውድድር ቢኖር ኢትዮጵያን የሚስተካከላት አይኖርም ብል እያጋነንኩ አይደለም፡፡ እንዲያውም ዘመቻዎችን መዝግቦና ቀምሮ የሚያዘጋጅ ተቋም ቢኖረን ኖሮ፣ የዘመቻዎችን ተሞክሮ ለሌሎች ጥሩ ማስተማሪያ ሳይሆን የውድቀት ማስተካከያ የሚሆን ምርጥ ትምህርት ይሆን ነበር እላለሁ፡፡

አገራችን ጦብያ ለዘመቻ አዲስ ባትሆንም በእኛ ዕድሜ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ብቻ እንኳን ስንት ዘመቻዎች መጥተው ስንት ዘመቻዎች ተፈራረቁ? የውኃ ማቆር ዘመቻ፣ የጤና ልማት ሠራዊት ግንባታ ዘመቻ፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ዘመቻ፣ የግብርና ምርታማነት ማሳደግ ዘመቻ፣ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዘመቻ፣ የመልካም አስተዳደር ማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነት ማክሰም ዘመቻ፣ የሲቪል ሰርቪስ አሠራር ማሻሻያ ዘመቻ፣ የፀረ ሙስና ዘመቻ የጥልቅ ተሃድሶ ዘመቻ… ዘመቻ… ዘመቻ… በኢትዮጵያ ገዥ መንግሥታት ይመጣሉ ይሄዳሉ፡፡ ዘመቻ ግን ለዘለዓለም ትኖራለች፡፡

አንድ ወዳጄ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕይወት ሠልፍ ናት ብሎኝ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ እንዲህ እላለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕይወት ዘመቻ ናት፡፡ እስኪ ያለ ዘመቻ የሚሠራ አንድ ነገር ጥቀሱልኝ?

ስለዘመቻ ሥራዎች ስናስብ የሚከተሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች መጠየቅ የግድ ይሆናል፡፡ ሥራን በዘመቻ ስንል ምን ማለታችን ነው? ሥራን በዘመቻ መሥራት ለምን አስፈለገ? ከዘመቻ የተሻለ የአሠራር ዘዴ መጠቀም አይቻልምን? እንዲያው ለመሆኑ የዘመቻ ሥራዎች ውጤታማ ናቸውን? የእስከ ዛሬ ዘመቻዎች ምን ያስተምሩናል? ወደፊትስ እንደዚህ መቀጠል አለብን?

ለእነዚህና የመሳሰሉት ቁልፍ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስና ጥልቅ ሳይንሳዊ ማብራሪያ መፈለግና ግንዛቤን ማሳደግ ለአገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የመኖርና ያለመኖርን ያህል እጅግ ወሳኝ ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የዚች አጭር ጽሑፍ ዓላማም በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ጥቂት ሐሳብ በመወርወር፣ ሌሎች ምሁራንና ባለሙያዎች ሐሳባቸውን እንዲሰነዝሩ በማነሳሳት ውይይት የምናደርግበት መድረክ መፍጠር ነው፡፡

ሥራን በዘመቻ ስንል ምን ማለታችን ነው?

እንደተገኘበት ቦታና ሁኔታ ብቻ ሳይሆን እንደ የሥራ ዘርፉ ዓይነት ሊለያይ ቢችልም፣ በአጠቃላይ ሥራን በዘመቻ ማለት በአንድ ጉዳይ ላይ ያላግባብ ወደኋላ መቅረታችንን በምንገነዘብበት ወቅት ያጠፋነውን ጊዜ ለማካካስና በፍጥነት ወደ ምንፈልግበት ግብ ለመድረስና ስኬታማ ለመሆን፣ በስሜት ሲልም በፍርኃትና በጉጉት የሚቀየስ ሥራን የመተግበሪያ መንገድ ነው ብሎ በግርድፉ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ በአገራችን የተለያዩ ዘመቻዎች በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፎች ሲካሄዱ ኖረዋል፣ አሁንም መካሄዳቸውን ቀጥለዋል፡፡

በሩቅ አሳቢዎች ህልምና ሐሳብ ወይም በረጅም ጊዜ ዕቅድ ሳይሆን በእሳት ማጥፋት ወከባና በሕመም ማስታገሻ መድኃኒት የምትኖረው አገራችን፣ ዘንድሮም በቀውስ ዑደት መሽከርከሯን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ ማነህ ባለሳምንት ተብሎ ሲያበቃ አዲስ መጤው የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ በዘመቻ ፕሮፓጋንዳ በይፋ ሊጀመር ፊሽካው ተነፍቷል፡፡ ያው እንደተለመደው ተጠንቶና ታስቦበት ሳይሆን፣ በጠርምሰህ ንዳውና በጅምላ አስታጥቀው በተደራጀ የአቦ ሰጥ ባህላዊ ዘዴ ብቻ ሳይሆን በደመ ነፍሳዊ የአመራር ጥበብ ታግዞ ሊተገበር ዝግጅቱ ተጠናክሯል፡፡

ይህ ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበና የብክነት ሩጫ መውጫው ያው የተለመደው ነው፡፡ ሌላ ዘመቻ ማስጀመር፣ ሌላ የእሳት ማጥፋት ዘመቻ፡፡ ሁልጊዜ ማለት ይቻላል እነዚህ ዘመቻዎች የሚካሄዱት በመንግሥት አነሳሽነትና ፖለቲካዊ አንድምታ ታጅበው በመሆኑ፣ ዜጎች ፖለቲካዊ ግቡን በማሰብ ቀድመው ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው በማድረግ ከልባቸው ወደ ሥራ እንዳይገቡ በማድረግ ተንገዳግዶ ከመውደቅ አያድነውም፡፡ የአሁኑ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘመቻም ከዚህ ጥርጣሬ ነፃ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ወጣቶቹ ባለፉት ዓመታት የተካሄዱ ተመሳሳይ የጥቃቅንና አነስተኛ ዘመቻ ሥራዎች ላይ የተመለከቱትን አድሎአዊና ኢፍትሐዊ አሠራሮች በማሰብ የሞራል ተነሳሽነታቸው ላይ ተፅዕኖ መፈጠሩ አይቀርም፡፡

የዘመቻ ተፈጥሮዓዊ ባህሪው በጥልቀት የማሰብ ጊዜ አለመስጠቱ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ መነሻው ፍርኃትና ድንጋጤ ስለሆነ ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ፕሮጀክት ማለፍ ያለበትን ሳይንሳዊ ደረጃዎች (የጥናት፣ የማቀድና የአተገባበር ስትራቴጂ መንደፍና በቂ ክትትልና ግምገማ ማድረግ) ሊያልፍ አይችልም፡፡ ሁኔታው ጊዜ አይሰጥም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሥራው የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያስገድድ መሆኑ በተግባር ሒደት ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡

ስለዚህ አብዛኞቹ የዘመቻ ሥራዎች ተጠናቀው ሲገመገሙ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ሲነገር ብንሰማ ሊገርም አይገባም፡፡ በቅርቡ የተከሰቱትን የባቡር ሐዲድ ግንባታ ያለሥራ መቅረትና የስኳር ፕሮጀክቶች የውኃ ሽታ መሆን ለዚህ አባባላችን ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ የባቡር ሐዲድ ግንባታው በበቂ ጥናትና ሌሎች ተያያዥ መሠረተ ልማቶችን ታሳቢ አድርጎ ባለመሠራቱ ነዳጅ እንኳን ከጅቡቲ ማመላለስ ባለመቻሉ (ሠርቶ የሚመልሰው ገንዘብ ባለመኖሩ) አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የዕዳ ክምር እንዲቆለልባት አድርጓል፡፡ በእያንዳንዱ ቀንም ዕዳው ከወለዱ ጋር እየጨመረ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እየሆነብን ይገኛል፡፡    

ሥራን በዘመቻ መሥራት ለምን አስፈለገ?የተሻለ የአሠራር ዘዴ መጠቀም አይቻልምን?

እዚህ ላይ እንዲህ የዘመቻ ሥራ የማይጠቅም ብቻ ሳይሆን የኪሳራ መንገድ ከሆነ ለምን መንግሥታችን ሁሉን ነገር በዘመቻ ካልሠራሁ ይላል? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ለዚህ አጭሩ መልስ ሊሆን የሚችለው የዚህ መንግሥት ተፈጥሯዊ ባህሪው ስለሆነ የሚለው ነው፡፡ ይህ መንግሥት ሲፀነስም ሆነ ሲወለድ ይህንን ባህሪ ተላብሶ ከመሆኑም በላይ፣ ወላጆቹ ያሳደጉትም እንዲህ እንዲሆን አድርገው ነው፡፡

ከላይ እንደጠቀስነው አንድ ሥራን በብቃት አቅዶ በስኬት ለማጠናቀቅ ሳይንሳዊ ዕውቀት ያለው ባለሙያና አመራር ይፈልጋል፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር የሚፈስበት እንዲህ ዓይነት ከባድ ሥራ ይቅርና ለጥቂት የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚቀረፁ ትንንሽ ፕሮጀክቶች እንኳን በስኬት ለማጠናቀቅ መሠረታዊ ግንዛቤ ይጠይቃሉ፡፡ ይህ መንግሥት ደግሞ በግልጽ እንደምናውቀው ብቃትን ሳይሆን ፖለቲካዊ ታማኝነትን ብቻ መሠረት አድርጎ የሚያሠራ በመሆኑ ውጤቱ ያለው ከአሞራ ርግብ እንደ መጠበቅ ነው፡፡ ከላይ እስከታች ባለው የመንግሥት መዋቅር የተሰገሰገው ካድሬ ፖለቲካዊ ቃላትን እያነበነበ ብቻ የሚኖር መሆኑን ራሱ መንግሥት ሳይቀር የሚናገረው ነው፡፡ ስለዚህ ችግሮችን በጊዜው ተረድቶ፣ መሠረታዊ መንስዔያቸውን ተገንዝቦ፣ በአግባቡ አቅዶ ለመፈጸም ብቃቱም ሆነ ተነሳሽነቱ በሌለው ፈጻሚ የተጠቀጠቀ መንግሥት መቼውንም ከዘመቻ ራሱን ሊያድን እንደማይችል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ ሁሉ ነገር በአፍ ላይ ያለ ነው፣ ጊዜውን ጠብቆ አንድ ቀን ይፈነዳል፡፡ ያን ጊዜ እሳቱን ለማጥፋት ወደ እሳት አደጋ መደወል ግድ ነው፡፡ ዘመቻው ተጀመረ፣ ችግሩ ተዳፈነ፣ ሌላ ቦታ ሌላ እሳት እስከሚንቀለቀል የዘመቻ ዑደቱ እንዲህ ይቀጥላል፡፡ ዘመቻ ለጥቂት ለደም መጣጭ ሙሰኞች አመቺ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ዘመቻ ወከባ ነው፣ እሳት ለማጥፋት ጊዜ አይሰጥም፡፡ ይህ ሁኔታ በአንድ ሌሊት ለመክበር ተዘጋጅተውና አሰፍስፈው ፊሽካ እስከሚነፋ ለሚጠብቁ ነቀዞች መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ እነዚህ ደም መጣጭ ሙሰኞች የዚህን ጥቅም መገኛ በርና መስኮት ጠንቅቀው የሚያውቁና መንገዱን የሚያሳዩ ከቀበሌ እስከ ፌደራል መሥሪያ ቤት ኔትወርክ የዘረጉ የሌሊት ወፎች፣ ስለሆኑ ማንም መሰሪ ሥራቸውን እንዳያውቅባቸው ወከባው ይመቻቸዋል፡፡ ሥራቸውን በድንግዝግዝና በጨለማ ለመከወን፡፡ እስኪነጋ ድረስ ፀሐይ እስክትወጣ፡፡

ልምዶቻችን ምን ያስተምሩናል?ለመሆኑ የዘመቻ ሥራዎች ውጤታማ ናቸውን?

ሌላው መሠረታዊ ጥያቄ ይህ ነው? ባለፉት ዓመታት ከተገበርናቸው ዘመቻዎች ምን ያህሉ ውጤታማ ነበሩ? ምን ምን ችግሮች አጋጠሙን? እንዴትስ ተወጣናቸው? ያቀድነውን አሳካን? ወይስ እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ለኪሳራ ተዳረግን? እነዚህ ሒደቶች ምን ትምህርት ይሰጡናል? ቀጣይ ዘመቻዎቻችንን በዚሁ መንገድ ማካሄድ አለብን? ወይስ መሠረታዊ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅብናል? የታሪክ ምሁራን “ከስህተቱ ያልተማረ ሊደግመው ተዘጋጅቷል የሚል አስተማሪ አባባል አላቸው፡፡ ከልምዳችን ተምረን ካልተስተካከልን ነገ በተመሳሳይ ኪሳራ እንደማንመታ መተማመኛ የለንም፡፡

በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በርካታ ዘመቻዎች ቢካሄዱም፣ ሒደታቸውንና ውጤታቸውን መርምሮ ሪፖርት ማቅረብ ፖለቲካዊ ትርጉም ስላለው እንደ ሞት መንገድ ይቆጠራል፡፡ በመሆኑም ትክክለኛ አኃዛዊ ማስረጃ ለማቅረብ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ የቀበሌና የወረዳ ሪፖርቶች የካድሬዎች መገምገሚያ ነጥቦች ስለሆኑ በውሸት የተሞሉ መረጃዎች ናቸው፡፡ መሬት ላይ ያለውን ሳይሆን ሹመቱን የሰጧቸው አለቆቻቸው መስማት የሚፈልጉትን ብቻ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡

አንድ የማይካድ ሀቅ ግን አለ፡፡ አብዛኞቹ የዘመቻ ሥራዎች የሚጠበቅባቸውን ለውጥ ሩቡን እንኳን አላመጡም፡፡ ተዘርዝረው የማያልቁ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

አዲሱ ዘመቻስ ዕጣ ፈንታው ምን ይሆናል?

እንደ ተለመደው የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘመቻ መነሻው መንግሥት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሱ አውዳሚ አመፆችን ተከትሎ መንግሥት ችግሩን ተረድቸዋለሁ አለ፡፡ ወጣቶች ተነስተውብኛል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ቢሆንም፣ እሱን በጥልቅ ተሃድሶ እየታገልኩ በተጓዳኝ እነዚህን ጉልበተኛና ንዴታም ወጣቶችን ማስታገስ የሚያስችል የሥራ ዕድል እፈጥራለሁ፡፡ የገንዘብ ችግር የለብኝም፡፡ አሥር ቢሊዮን ይኸው ላለፉት አሥር ዓመታት የጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር ሞክሬ ችግሩን መፍታት እንዳልቻልኩ ባውቅም፣ ችግሩን ለማስታገስና ትንፋሽ ለመሰብሰብ ያስችለኛል፡፡ የኢሕአዴግ ሐሳብ ነው፡፡

ሲጀመር መንግሥት የወጣቶቹን የሥራ አጥነት ችግር በቅርቡ የተፈጠረ ሊያስመስለው ቢሞክርም፣ ላለፉት 25 ዓመታት እየተነገረው ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የቆየበት ነው፡፡ ይባስ ብሎም ‹አደገኛ ቦዘኔ› እያለ ሲፈርጃቸውና በኢፍትሐዊ የፖለቲካ አደረጃጀቶች ሲያሰቃያቸው የኖረው ይኸው ገዥ ፓርቲ መሆኑን ማንም አይረሳውም፡፡

ሪፖርተር የፌደራል ከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞን አነጋግሮ ያወጣውን ረጅም ቃለ ምልልስ በጥንቃቄ ካነበብኩ በኃላ፣ የጨለምተኛ አመለካከቴን በብርሃን ላፈካው አልቻልኩም፡፡ እንዲያውም ባሰኝ፡፡ እንደ አቶ ዘነበ ገለጻ ያለፉት ዓመታት ተግዳሮቶች አሁንም አሥጊ ሁኔታዎች ሆነው መቀጠላቸውን፣ እንዲያውም አንዳንዶቹ በከፍተኛ ሁኔታ ተወሳስበው የሚገኙ እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡ በወጣቶቹ በራሳቸው ከሚታዩ ዝቅተኛ ዕውቀትና ክህሎት፣ እንዲሁም የተዛባ አመለካከት (በአቋራጭ መክበር) ጀምሮ በየደረጃው ባለው የአስፈጻሚው አካል ሥር የሰደደ ኪራይ ሰብሳቢነት በተጨባጭ ካለው አነስተኛ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ጋር ተዳምሮ አስፈሪ ተራራ መደቀኑን መረዳት ቀላል ነው፡፡ ለእነዚህ ተግዳሮቶች ዘመቻው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ መሆኑን ከመገለጹ በዘለለ ምንም አዲስ ነገር አለመኖሩ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ አምላክ ይርዳን ከሌላ እሳት እንተርፍ ዘንድ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው berzelekew@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

 

Standard (Image)

የአክሲዮን ኩባንያዎች ሕግ በሻሞ መክበርንና በሻሞ መደህየትን ማስቆም አለበት

$
0
0

በጌታቸው አስፋው

ሪፖርተር የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው ዕትሙ በውጭ ‹‹ዜጎች የተያዙ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አክሲዮኖች ጨረታ ሁለት ገጽታ›› በሚል ርዕስ፣ ባለ አንድ ሺሕ ብር የአዋሽ ባንክና የኅብረት ባንክ አክሲዮኖች ጨረታ ዋጋ ሃያ ሺሕና አሥራ አራት ሺሕ ተሸጡ ብሎ አስነብቦ ነበር፡፡

አክሲዮኖቹን በዚህ ዋጋ የገዙ ሰዎች አሁን ባለው 40 በመቶ ከፍተኛ የትርፋማነት መጣኝ እንኳ ወጪያቸውን ለመመለስ እስከ ሃያ ዓመታት ሊፈጅባቸው እንደሚችልና አክሳሪ እንደሆነ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ይኼ ዋጋ የባንኮቹን ሀብት ግምትም ያዛባል፡፡

የአክሲዮኖች ትርፋማነት እንዳሁኑ በዓለም ታይቶ የማይታወቅ 40 በመቶ መሆኑ ቀርቶ ከባንክ ቁጠባዎች ወለድ መጣኝ በጥቂቱ ብቻ በልጦ ስድስትና ሰባት በመቶ ደረጃ ሊወርድም ስለሚችል፣ አክሲዮኖቹን የገዙ ሰዎች ዋናቸውን ለመመለስ ምን ያህል ዓመታት ሊፈጅባቸው እንደሚችል ማስላት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ ይኼ ክስተት የሚነግረን በገፍ የተረጨውን ጥሬ ገንዘብ ሀብት ያገኙና የከበሩ ሰዎች የነገዱት ‹‹በሻሞ ገበያ›› ውስጥ እንጂ በነፃ ገበያ ውስጥ እጅና ጭንቅላት ሠርቶ ከሌላው ተወዳድሮ አለመሆኑን ይነግረናል፡፡ የአገሪቱ ዕድገት የሻሞ እንደሆነ ይነግረናል:: ለዚህም አገሪቱ ዛሬም ዋጋ እየከፈለች ነው፡፡ ወደፊትም እጅግ በጣም ብዙ ዋጋ ትከፍልበታለች፡፡

በዚሁ ዕለት አክሲዮን ኩባንያዎች የሚገዙበት አዲስ ረቂቅ ሕግ ለአስተያየት ሊቀርብ ነው በሚል ርዕስ በንግድ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተካሄደ በኋላ፣ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አማካይነት ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል የሚል ዘገባ ቀርቧል፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ ፈቃድ ወስደው የተመዘገቡ የአክሲዮን ኩባንያዎች 472 ሲሆኑ፣ ነገር ግን እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ከ200 አይበልጡም ሲል ንግድ ሚኒስቴርም ገልጿል፡፡

የካቲት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣ የሪፖርተር ጋዜጣ የኦሮሚያ መንግሥት በኢኮኖሚ አብዮት ፕሮግራም ጠብደል ያሉ የአክሲዮን ኩባንያዎችን ለማቋቋም ከባለሀብቶች ጋር በትብብር ለመሥራት እየመከረ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ለባከኑት በርካታ ዓመታት ተቆጭቶ ለማካካስ መነሳሳቱ የሚያስመሰግነው ነው፣ እንዲሳካለት እመኛለሁ፡፡

ለኢንዱስትሪ መነሻ ካፒታል እንደ ውኃ ለጠማት ኢትዮጵያ ይቅርና ካፒታል ሞልቶ ለተረፋቸው አገሮችም ሳይቀር ዋናው የመነሻና የማስፋፊያ ካፒታል ምንጭ ኩባንያዎችን በአክሲዮን ማደራጀት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ብቸኛ የአገር ውስጥ ካፒታል ምንጭ ስለሆነ ሰፋ አድርጎ ማየት ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህም ሕግ የሚወጣው ሲያጠፉ ለመቅጣት ሳይሆን ጥፋት እንዳይፈጸም መሆንም አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ የአክሲዮን ኩባንያዎች ለማቋቋም ሕግ ከማውጣት ጋር አብረው የሚሄዱ ቅድመ ሁኔታዎቸ መሟላት አለባቸው፡፡

እኛ አገር ገንዘባችንን በዕቃ ላይ ብቻ ማዋል ስንችል በብዙ የበለፀጉና ታዳጊ አገሮች ግን ገንዘባቸውን በሰነድ መልክም ይይዛሉ፡፡ የሰነዶቹ በገበያ ውስጥ ተሸራርፈው መሸጥና መለወጥ መቻል ደግሞ ሰነዶቹን ጥሬ ያደርጋቸዋል፡፡ ሰነድ በመሸጥ ብቻ ማምረቻ ድርጅቶችንም ሸራርፈው መገበያየት ተቻለ ማለት ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ሲቸግር ሙሉውን ድርጅቱን ለመሸጥ ወይም የሥራ መስክን ለመለወጥ ያለውን ጣጣ በማስወገድ ችግርን ቀረፈ ማለት ነው፡፡

የባንክ ተቀማጭ ሰርተፊኬት፣ አክሲዮን፣ ቦንድ፣ ከዕቃ ይልቅ በገበያ ውስጥ ተመልሰው ወደ ጥሬ ገንዘብ በቀላሉ ሊለወጡ ስለሚችሉ ለባለቤቱ እንደገና በፈለገው መንገድ ለመገልገል የጥሬነት (Liquidity) ዕድል ይሰጡታል፡፡ 

ይኼ ገንዘብን መልሶ በፈለጉት መንገድ የመገልገል ዕድል ነው እንግዲህ ገንዘብን ጥሬ ገንዘብ የሚያሰኘው፡፡ በኪሳችን ውስጥ የምንይዘው ብርና ሳንቲም ምንዛሪ በጣም ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ የባንክ ተንቀሳቃሽ ተቀማጭ ሙሉ በሙሉና የቁጠባና የጊዜ ተቀማጮችም በተወሰነ ደረጃ በፈለግን ጊዜ በደቂቃዎች ውስጥ አውጥተን ልንገለገልባቸው ስለምንችል ጥሬ ገንዘብ ናቸው፡፡ ሰነዶችን ለመሸጥ ጊዜ ስለሚወስድና ወደ ጥሬ ገንዘብነት ሲቀየር ትርፋማነትንም ስለሚያሳጣ ሰነዶች ገንዘብ እንጂ ጥሬ ገንዘብ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ሰነዶችም ከዕቃ ይልቅ በመሸጥ ፍጥነት ለጥሬነት የቀረቡ ንብረቶች ናቸው፡፡

ሆኖም በኢትዮጵያ የአክሲዮን ኩባንያ ታሪክ በአክሲዮን የተቋቋሙ ባንኮች እንኳ ባለ አክሲዮኖች ለሦስተኛ ወገን እንዳይሸጡ ስለሚከለክሉ በመካከላቸው መልሶ የመግዛትና የመሸጥ ውል (Repurchase Agreement) ከሌለ በስተቀር፣ ንብረትህን አትሸጥም የሚል ክልከላ ምን ያህል ሕጋዊ መሠረት አለው? ምን ያህሉ ባለ አክሲዮንስ ስለ መልሶ መግዛትና መልሶ መሸጥ ውል ያውቃል? መልሶ የመግዛትና መልሶ የመሸጥ ውል ከነበረ እንዴት የዳያስፖራዎቹ አክሲዮን በነፃ ገበያ ለሽያጭ ሊቀርብ ቻለ?

በዕድሜ የገፉ ሰዎችና ወጣቶች አክሲዮኖቻቸውን ወደ ጥሬ ገንዘብ ለውጠው ለመጠቀም የሚፈልጉባቸው ምክንያቶችና ጊዜያቶችም የተለያዩ ናቸው፡፡ ከዕድሜያቸው አንፃር ወጣቱ በማስፋፊያ ፕሮግራም ካፒታሉ (ሀብቱ) እንዲያድግለት፣ በዕድሜ የገፋው ደግሞ  ዲቪደንዱ (ገቢው) ላይ ሊያተኩርም ይችላሉ፡፡

አክሲዮንና ቦንድን ለጥሬ ገንዘብነት ቅርብ የሚያደርጋቸው የተደራጀ የሰነዶች ሁለተኛ ገበያ ኖሮ ሰዎች በፈለጉ ጊዜ በእነዚህ ገበያዎች ውስጥ ሰነዶቻቸውን መግዛት ለሚፈልግ ሰው ሸጠው ጥሬ ገንዘባቸውን መመለስ ሲችሉ ነው፡፡ ያኔ ነው የሰነዶች አቅርቦትና ፍላጎት መስተጋብር ዋጋ ተፈጥሮ ሰዎች ሰነዶችን በትክክለኛ የገበያ ዋጋ ለመገበያየት የሚችሉት፡፡ 

ሌላው ትልቁ የአክሲዮኖች የገበያ ዋጋ ጥቅም ከአክሲዮኖቹ ጀርባ ላለው ምርት ትርፋማነትና ውጤታማት ምልክት ሰጪ መሆኑ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ዕውቀት ሳይኖራቸው በሻሞ የከበሩ ሰዎች በብራቸው ብዙ ሺሕ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በዕውቀታቸው ሥራ ፈጥረው በጋራ መሥራት ይችላሉ፡፡

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ በታሪኳ ባስተናገደቻቸው አንድ መቶ ሃምሳ ሺሕ አውቶሞቢሎች ላይ በ2008 ዓ.ም. ብቻ አንድ መቶ አሥር ሺሕ አውቶሞቢሎች ቀላቅላለች አሉ፡፡ ባለቤቶቹ በሻሞ የከበሩ ሰዎች መሆናቸውን ያወቁ አልመሰለኝም፡፡ ከንግግራቸው ቃና የተረዳሁት ባለመኪኖቹን የፋብሪካ ወዛደሮች አድርገው እንደሚገምቱና አገሪቱም እየበለፀገች እንደሆነ ነው፡፡ 

ሰዎችን በሻሞ ለማክበር ብቻ የጠቀመው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወጣቱን ሥራ አሳጥቶ፣ የሸቀጥ ዋጋን አንሮ፣ አገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አሳጥቶ፣ በአጠቃላይ አገሪቱን አውላላ ሜዳ ላይ ጥሎ፣ ክልሎች ግራ ቢገባቸው በወሰዱት መሬትና የማዕድን ሥፍራ ከኢንቨስተሮች ነጥቀው ለወጣቱ ሥራ ፈጠራ ማዋል ያልታቀደ የተናጠል ዕርምጃ አፈር እየበላ ነው፡፡

ከአክሲዮን ኩባንያ ሕጉ በፊት የተጠና በአጭር የማይቀጭ  ዕቅድ አውጥቶ ለመንቀሳቀስ ለአክስዮን ገበያ የሚያስፈልጉ ተቋማትን ማደራጀት ይቀድማል፡፡ የጥቂቶቹን ጥቅም እንደሚከተለው እዘረዝራቸዋለሁ፡፡

አንደኛ አዲስ የሚቋቋሙ የአክሲዮን ኩባንያዎች አክሲዮኖቻቸውን በሽርፍራፊ ሸጠው ሥራ ለመጀመር ሁለትና ሦስት ዓመት መጠበቅ ስለማይኖርባቸው፣ እግረ መንገዱን የኩባንያዎቹን ትርፋማነትና የአክሲዮኖቹን አዋጭነትም ለክቶ የሚያረጋግጥና በጥቅል ገዝቶ በኮሚሽን ትርፍ ለሕዝብ በሽርፍራፊ የሚሸጥ የኢንቨስትመንት ባንክ ያስፈልጋል፡፡

ሁለተኛ በግለሰብ ደረጃ በአክሲዮን የሚቋቋሙ ድርጅቶችን የወደፊት ትርፋማነት ከመንግሥት ፖሊሲና ከብሔራዊ ኢኮኖሚውና ከክፍላተ ኢኮኖሚዎች ዕድገትና ገበያ ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ የሚታይ ስለሆነ፣ ሙያው ለሌላቸው ግለሰቦች ለመለካት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህም አክሲዮን ገዢዎች ግለሰቦች ራሳቸው በግል ከሚሆኑ በአባልነት ተደራጅተው በተቋም መልክ አክሲዮን እንዲገዙ የጋራ ጥሪትን (Mutual Fund) የመሳሰሉ የጥሬ ገንዘብና የካፒታል ገበያ ተቋማት ተቋቁመው፣ የግል ኢንቨስተሮችን ገንዘብ በባለሙያ ዕውቀት በልዩ ልዩ የሰነድ ገበያዎች በመደልደልና በማስተዳደር ወይም ለግል ኢንቨስተሮች ምክር በመስጠት ማገልገል አለባቸው፡፡

ሦስተኛ የተደራጀ ሁለተኛ የሰነድ ገበያ ለማቋቋም የሚያስፈልጉ ለገበያው መመርያ ሕግ አውጥተው የንግድ ሥነ ምግባር ጉዳዮችን የሚከታተሉና የሚቆጣጠሩ መንግሥታዊ የቁጥጥር ተቋማት መቋቋም አለባቸው፡፡

አራተኛ አክሲዮኖቻቸውን በሁለተኛ የአክሲዮን ገበያ ለመነገድ የሚፈልጉና የብቃት መሥፈርት የሚያሟሉ ኩባንያዎችን በአባልነት መዝግበው፣ ሰነዶቻቸውን የሚያገበያዩ የተደራጁ ገበያዎችና የግብይት አፈጻጸም ማወራረጃ ማዕከላዊ የተገበያዮች ተቀማጭ ሒሳቦችና ሌሎች መሰል አገበያይና ንግድ አቀላጣፊ ተቋማት መቋቋም አለባቸው፡፡

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የኒውዮርክ አክሲዮን ገበያ፣ የለንደን አክሲዮን ገበያ፣ የቦምቤ አክሲዮን ገበያ እየተባሉ ከሚታወቁት ታላላቅ የሰነድ ገበያዎች ባሻገር የእኛው የምርት ገበያ ድርጅትም እንደ ምሳሌ ሊወሰድ ይችላል፡፡

አምስተኛ የአክሲዮን ተገበያዮችን ጉዳይ የሚያስፈጽሙ፣ የገበያውን ባህሪይ ለይተው የሚያውቁና ሙያዊ የድለላና የኮሚሽን ሥራ የሚሠሩ ተቋማት መቋቋም አለባቸው፡፡ እነዚህም ለምሩቃን ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡

ስድስተኛ ነባር የግል ድርጅቶቻቸውን ወደ አክስዮን ኩባንያነት መቀየር ወይም ድርጅቶችን ለመቀላቀል ለሚፈልጉ የድርጅት ሀብትና የንግድ ሥራ ዋጋ ገማች ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ ለሒሳብ ሥራ ባለሙያ ትልቅ የሥራ ገበያ ነው፡፡

እነዚህ ከዚህ በላይ የተገለጹት ጥቂቶቹ ብቻ ሲሆኑ፣ የአክሲዮን ኩባንያዎች ሕግ ከመውጣቱ በፊት ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው፡፡

እነኚህ ሁኔታዎች ካልተሟሉ እንደ ቀድሞው ሚሊዮኖችን ሰርቄ ወይ እጠፋለሁ . . . .  ወይ አምስት ዓመት ታስሬ እወጣለሁ በሚል ብር እንጂ ዕውቀት የሌለው መንገደኛ ሁሉ የውሸት የእጥፍ እጥፍ ትርፋማነት የመኃይም ፕሮጀክት እያዘጋጀ፣ የሕዝብ ንብረት መዝረፍ ሥራ ላይ እንዲሰማራ መፍቀድ ነው፡፡

ለሽያጭ ከመቅረቡ በፊት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ በፕሮጀክቱ ትርፋማነት ሥሌት ላይ መስማማት ስላለበትም፣ የገንዘብ ኢኮኖሚን መምራትና ማስተዳደር የግብርና ኢኮኖሚን እንደማስተዳደር በካድሬ ሲቪል ሰርቪስ ሊወጡት የሚችሉት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በዕድገት ጎዳና ወደፊት ለመዝለል እየፈለገች ነው መንግሥት በካድሬ ሲቪል ሰርቪሱ እንዳትዘል  አስሮ ይዟታል፡፡ በሻሞ መክበርና በሻሞ መደህየት ይብቃን፡፡

በነፃነት በመሥራት ሳይሆን በሚገድቡ ሕጎች የሚያምነው ካድሬ ሌላ የፖለቲካ ሥራ ቦታ ይፈለግለትና የዩኒቨርሲቲ ምርቶች የሆኑ ወጣት ምሩቃን የበሰለ ዕውቀት ካላቸው አንጋፋ ምሁራን ጋር ተቀናጅተው ዕውቀታቸውንና ትኩስ ወኔያቸውን በነፃነት ተጠቅመው፣ ሠርቶ የመኖር ዕድልና መሠረታዊ የሰብዓዊ መብታቸውን ያግኙ፡፡ የኢኮኖሚው በፖለቲካው መተብተብ ወደኋላ ጎታች ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

Standard (Image)

የስምረት አበሳ

$
0
0

 

በሚካኤል መድኅን

በምዕራብ ትግራይ የሚገኙ ማይ ዓይኒ፣ ዓዲ ሐሪሽ፣ ሕንፃፅና ሽመልባ የሚባሉት የመጠለያ ጣቢያዎች የኤርትራ ስደተኞችን ያስተናግዳሉ፡፡ በየወሩ በአማካይ 3,000 ሰዎች ድንበር አቋርጠው ይገባሉ፡፡ ከዚያች አገር ፈልሰው በኢትዮጵያ የሚኖሩት ስደተኞች በአሁኑ ጊዜ በድምሩ 161 ሺሕ መድረሳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡

የመጀመሪያ ጉብኝቴን ያደረኩት በማይ ዓይኒ ነበር፡፡ ከሽሬ ወደ ሑመራ በሚወስደው መንገድ በስተቀኝ በኩል የተቋቋመ ካምፕ ነው፡፡ ቀኑ እሑድ ስለነበር ብዙ ሰዎች በአብያተ ክርስቲያናት ይፀልያሉ፣ በርከት ያሉ ወጣቶች ደግሞ ለተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ ጊዜያቸውን ሙሉ ተቀምጠው የሚያሳልፉት ስደተኞቹ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሲገኙ በብዛት ይሳተፋሉ፡፡ በጋራ ጉዳያቸው ላይም ይወያዩባቸዋል፡፡ በዕለቱ ከተከናወኑት ሥነ ሥርዓቶች አንዱ የብስክሌት ውድድር ነበር፡፡ በትግራይና በኤርትራ ወጣቶች ዘንድ በእጅጉ የሚወደድ ስፖርት ነው፡፡ ብቸኛው የጊዜ ማሳለፍያ ግን አይደለም፡፡ እግር ኳስና ቴኒስን የመሳሰሉ ጨዋታዎችም ይዘወተራሉ፡፡

የብስክሌት ውድድሩን በተመልካች ለማድመቅ ቅስቀሳ ተደረገ፡፡ በዚህ የተካኑ የማስታወቂያ ነጋሪዎችና የመድረክ መሪዎች አሏቸው፡፡ በጥሪ ማስታወቂያው ተነሳስተው በርካታ ተመልካቾች ከያሉበት ወጥተው ውድድሩን በድጋፍ ለማድመቅ ወደ አስፋልት መንገድ ተመሙ፡፡ የሚበዙት ወጣቶች ናቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ ሕፃናት፡፡ የኤርትራ ስደተኞች የከተሜ ወጣቶችና ሕፃናት ይበዙባቸዋል፡፡ ከጠቅላላው 15 በመቶ የሚሆኑት ሕፃናት ናቸው፡፡  

ይህንን ያየ ሰው “በቃ ያች አገር ቀጣይ ትውልድ ላይኖራት ነው?” ብሎ መደምደሙ አይቀርም፡፡ በቀጣይ አገሪቱን ማን ይሆን የሚረከባት? በተፈጠሩበት ምድር ተስፋ የራቃቸው ወጣቶች፣ ሕፃናትና አዛውንት በአገራቸው ሁኔታ ተማርረው ድንበር አቋርጠው ይሰደዳሉ፡፡ የተወሰኑት በለስ ቀንቷቸው በአጎራባች አገሮች ይጠለላሉ፡፡ ጥቂቶቹ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሦስተኛ አገር ይሄዳሉ፡፡ አብዛኞቹ በሱዳንና በግብፅ በረሃዎች አበሳቸውን አይተው፣ አካላቸውንና ሕይወታቸውን ገብረው የበረሃ ሲሳይ ሆነው ይቀራሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የአውሮፓን ምድር ለመርገጥ በሚያደርጉት ትግል በሜዲትራኒያን ባህር ሰምጠው የዓሳ ነባሪ ቀለብ ይሆናሉ፡፡

የብስክሌት ውድድሩን ለማስጀመር ተወዳዳሪዎች ቦታ ቦታቸውን እንዲይዙ፣ ተመልካቾችም በሞራል እንዲያበረታቷቸው በመድረክ መሪው ተነገረ፡፡ ሙዚቃ ከፍ ብሎ ተለቋል፡፡ ለጆሮ የሚጥም ለስለስ ያለ የናፍቆት ዜማ ነው፡፡ አብዛኞቹን ተመልካቾች ቀልባቸውን አስቶ በትዝታ ማዕበል እንደሚወስዳቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስሜታቸውን፣ ምሬታቸውንና ናፍቆታቸውን በእነዚህ ዜማዎች ነው የሚገልጹት፡፡ ይህን የናፍቆት ዜማ የሚቀምሩ በርካታ ከያንያን አሏቸው፡፡ ከዜማው ውጪ ሁሉም ነገር ይናፍቃቸዋል፡፡ በሚወዷት አገራቸው ያሳለፉት ሕይወት፣ የልጅነት ዓለም፣ የወጣትነት ጊዜ፣ ቤተሰቦቻቸው፣ የትውልድ ቀያቸው፣ አፈር ምድሩ፡፡ በተለይ ሕፃናቱ ኢትዮጵያ ከደረሱ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ በቤተሰብ ናፍቆት እንደሚሰቃዩ የካምፑ አስተባባሪዎች ነግረውኛል፡፡  

 

ውድድሩ ብስክሌተኞቹ በከፍተኛ ፍቅር የከወኑት፣ ታዳሚዎቹም በጋለ ሞራል የደገፉት አዝናኝ ጨዋታ ነበር፡፡ በደመቀ ሁኔታ ተጀምሮ ሁሉንም አዝናንቶ በድል ተጠናቀቀ፡፡ ከአንድ እስከ ሦስት የወጡ አሸናፊዎች ሽልማት ተበረከተላቸው፡፡ ሽልማቱ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ምርትና አገልግሎታቸውን ካስተዋወቁ የንግድ ተቋማት የተገኘ ነበር፡፡

የኤርትራ ወጣቶች በመጠለያ ጣቢያዎቹ ጊዜያቸውን በዚህ መልኩ ያሳልፉታል፡፡ ይህ አምራች ኃይል ትኩስ ጉልበቱን ሳይጠቀምበት፣ ለስደት የዳረገውን ምክንያት እያሰበ፣ ለዚህ አበሳ ያበቃውን ሥርዓት እየረገመ፣ የዛሬውን እያሰላሰለ፣ የወደፊቱን እያማተረ፣ የሚወዳት አገሩን እየናፈቀ የስደት ኑሮውን ይገፋል፡፡ ተስፋቸው መቼ እውን እንደሚሆን ግን አይታወቅም፡፡ ከዛሬ ነገ የተሻለ ይሆናል እያሉ እስከ ዘጠኝ ዓመት ድረስ የኖሩ ስደተኞች አሉ፡፡

የውድድር ሥነ ሥርዓቱ እንዳበቃ ከካምፑ አስተባባሪዎች ጋር ተገናኘሁ፡፡ ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ስለስደተኞች ሕይወትና አኗኗር፣ ስለገጠመኞቻቸውና በኤርትራ ስለሚደርስባቸው ግፍ መጫወት ጀመርን፡፡ የዓለማችን ትልቋ እስር ቤት ተብላ በተፈረጀችው ኤርትራ ውስጥ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ለስደት ስለዳረጓቸው ምክንያቶች፣ እንዲሁም በጉዞዋቸው ስለአጋጠሟቸው ችግሮች አንድ በአንድ ሊያጫውቱኝ ተዘጋጁ፡፡ ሲበዛ ግልጽ ናቸው፡፡ በራሳቸው የደረሰባቸውንና በሌላውም ላይ የደረሰውን የግፍ ታሪክ በግልጽ አጫወቱኝ፡፡ ታሪኮቹ እንኳንስ ለመናገር ለመስማትም የሚዘገንኑ ቢሆኑም እነሱ ግን ቀለል አድርገው ይተርኳቸዋል፡፡

“የትኛውን አንስተን የትኛውን እንደምንተወው አስቸጋሪ ነው፤” አለኝ አንደኛው፡፡ “ለማንኛውም በጣም አሳዛኝ ከምላቸው ታሪኮች ልጀምርልህ፡፡ እንትና እስር ቤት ውስጥ በደረሰበት ድብደባ ምክንያት ብልቱ ፈሳሽ መቆጣጠር ስለማይችል አሁንም ድረስ በቀን እስከ 20 ኮንዶም ይቀይራል፡፡ እንትና በ70 ዓመቱ እጆቹ በሰንሰለት እንደ ታሰሩ ከእስር ቤት አምልጦ ኢትዮጵያ ደረሰ፡፡ እንትና ለረዥም ጊዜ በጨለማ ውስጥ በመታሰሩ ዓይኖቹ ጠፍተው በሰው እየተመራ ወደዚህ መጥቷል፡፡ እከሌ አካል ጉዳተኛ ልጇን ይዛ በሱዳን በኩል ወደዚህ ተሰዳለች፡፡ 15 ወጣቶች የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው ወደዚህ ሊመጡ ሲሉ በኤርትራ ወታደሮች ተይዘው እዚያው ለሕዝብ ማስተማሪያነት ተብሎ በአደባባይ ተረሽነዋል….” እያለ ቀጠለ፡፡

አንዳንዶቹን ታሪኮች ከባለቤቶቹ አንደበት መስማት እችል እንደሆነ ጠየቅኳቸው፡፡ ከተወሰኑት ጋር አስተዋወቁኝ፡፡ ስምረት አንዷ ነች፡፡ ታሪኳን ልታጋራኝ ፈቀደች፡፡ ጥቁር ሱሪ አድርጋለች፡፡ ከላይ ነጭ ከነቲራ ለብሳለች፡፡ ዓይኖቿ እንደ ኮከብ የሚያበሩ፣ መካከለኛ ቁመት ያላት፣ የተስተካከለ ተክለ ሰውነት የተቸረች፣ የጠይም ቆንጆ፣ ለግላጋ፣ በተስፋ የተሞላ፣ በወኔ የጋለ፣ በጽናት የበረታ ሕይወት የምትመራ ትመስላለች፡፡ ፊቷ በፈገግታ ያበራል፡፡ ሰውነቷም የድሎት ነፀብራቅ ሆኗል፡፡ ውስጧ ግን ሌላ ነው፡፡

ነጭ ከነቲራዋ ላይ “ሓውኻ አበይ ኣሎ” (ወንድምህ ከወዴት አለ) የሚል የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል ተጽፏል፡፡ የወጣቶች ፍልሰትና መከራ ያሳሰባቸው የካቶሊክ ቄሶች በዚህ ሃይማኖታዊ ጥቅስ አስደግፈው ያወጡት መረር ያለ መግለጫ በኤርትራ ምድር ለተወሰነ ጊዜ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ወንድሞቻቸው፣ ልጆቻቸውና ወላጆቻቸው የት እንዳሉ የማያውቁ በርካቶች ይህን ጥያቄ ዘወትር ያነሱታል፡፡ ስምረትም እንዲሁ፡፡ በለበሰችው ከነቲራ ላይ የታተመው ጽሑፍ፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት በልቧ ውስጥ ታትሞ የሚኖረውን ህያው ስሜት ያንፀባርቃል፡፡ እናቷና ታናሽ ወንድሟ እሷን ተከትለው ወደ ኢትዮጵያ ሲሰደዱ ድንበር ላይ ተይዘው በኤርትራ እስር ቤት ውስጥ ይማቅቃሉ፡፡ አሁን በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ አታውቅም፡፡ እናም “ወንድምህ ከወዴት አለ” የሚለው ጥያቄ 24 ሰዓት ሙሉ ከምናቧ የሚጠፋ አይደለም፡፡ በአንዱ ቀን አንዳች ምላሽ እስክታገኝለት ድረስ፡፡

ስምረት ቃለ መጠይቁን በፈገግታ ጀመረችው፡፡ ለአቅመ ሔዋን አልደረሰችም፡፡ በዚህ ዓመት 18 ይሞላታል፡፡ ሆኖም ከሚጠበቀው በላይ የተረጋጋች፣ አንደበተ ርቱዕ፣ በሳልና አስተዋይ ልጅ ነች፡፡ ዕድሜ ከቁጥር የዘለለ ትርጉም እንደሌለው እሷ ምስክር ነች፡፡ ገና ትንሽ እንደ ተጫወትን ንግግሯ በእንባ መታጀብ ጀመረ፡፡ ከውብ ዓይኖቿ የሚፈልቀው እንባ በጠይም መልከ መልካም ፊቷ ላይ ጎረፈ፡፡ ድንቡሽቡሽ ጉንጮቿ በእንባ ታጠቡ፡፡ “እንባ አንድ በመቶ ውኃ ሲሆን ዘጠና ዘጠኙ ግን ስሜት ነው፤” ይባላል፡፡ አዎ! በደስታም ሆነ በሐዘን የሚያጅበን እንባ ከውስጣችን ፈንቅሎ የሚወጣ ስሜት ነው፡፡ የስምረት ደግሞ በድርብርብ ሐዘን የመሰበር ስሜት፡፡

በስሜት የታጀበ አነጋገሯ ተሰምቶ አይጠገብም፡፡ ታሪኳን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ያለማዛነፍ ተረከችልኝ፡፡ “እናቴ በወታደሮች ካምፕ ውስጥ የምግብ አዘጋጅ ነበረች፡፡ በሒደት ከአንድ ወታደር ጋር ተዋውቃ ግንኙነት ጀመሩ፡፡ ከዚያም እኔ ተወለድኩ፡፡ እሱ ግን አባትነቱን ካደ፡፡ እናም ያለ አባት አሳደገችኝ፡፡ የምትሠራበት ካምፕ ከምንኖርበት ከተማ ትንሽ ይርቅ ስለነበር ተመላልሳ መሥራት አልቻለችም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ብቻዬን ማደርና መዋል ስለሚከብደኝ ብዙውን ጊዜ ከአያቴ ጋር ነበር የምኖረው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን እናቴ በአንድ ወታደር ከሰል ላከችልኝ፡፡ እኔም ከሰሉን ተቀብዬ ወታደሩን በባህላችን መሠረት ቡና አፍልቼ፣ ምሳ አቅርቤ አስተናገድኩት፡፡ ያኔ ገና የአሥር ዓመት ልጅ ነበርኩ፡፡ ሰውዬው ከተስተናገደ በኋላ ግን አስገድዶ ደፈረኝ….”፡፡ ይህን ተናግራ ሳትጨርስ በውስጧ ታምቆ የነበረው ስሜት ገንፍሎ ወጣ፡፡ ፈቷ ከመቅፅበት በእንባ ታጠበ፡፡  

በመደፈሯ የደረሰባትን ጉዳትና ተከትሎ የመጣውን የሕይወት ዘመን መዘዝ ለመግለጽ ቃላት አቅም ያንሳቸዋል፡፡ ስምረት በውስጧ ያለውን ጉዳት እያሰበች በሳግ ብዛት አንደበቷ ቃላት ሲያጥረው፣ እነዚያ ውብ ዓይኖቿ ውስጣዊ ስሜቷን በእንባ ይናገሩታል፡፡ መልሳ እስክትረጋጋ ድረስ በድንጋጤ ፈዝዤ አያታለሁ፡፡ ምንስ ብዬ ላረጋጋት? ውስጡ የዓመታት መከራ ተሸክሞ በስሜት ያለማቋረጥ የሚያነባን ሰው እንደ ቀላል “አይዞህ በቃ” ማለት እንዴት ይቻላል? ሕመሟን የሚያስታግስ፣ ስሜቷን የሚያበርድ ቃላት ከዬት ላመጣ እችላለሁ? በመሀላችን ፀጥታ ሰፈነ፡፡ ትንሽ ቆይቼ ዝምታውን ለመስበር ያህል፣ ጨዋታውንም ለመቀጠል ብዬ፣ “በቃ ቻል አድርጊው ስምረት” ብዬ ተነፈስኩ፡፡ “የሰው ልጅ የማይችለው ነገር የለም” የሚለውን አባባል እያስታወስኩ፡፡  

በለጋ ዕድሜዋ የወረደባት ዱብ ዕዳ ከሥነ ልቦና ቀውስ አልፎ የሕይወት ዘመን ጠባሳ አስከትሎባታል፡፡ ስምረት ለጊዜው ስሜቷን ዋጥ አድርጋ የሰቆቃ ታሪኳን መተረክ ቀጠለች፡፡ “ወታደሩ እንደ ደፈረኝ ለማንም አልተናገርኩም፡፡ በነገታው ከትምህርት ቤት ቀረሁ፡፡ በቀጣዮቹ ቀናትም አልሄድኩም፡፡ ጓደኞቼ መጥተው ለምን እንደቀረሁ ጠየቁኝ፡፡ ምላሼ ‘አሞኛል’ የሚል ነበር፡፡ ከዘመዶቼ ተመሳሳይ ግፊት ሲበዛብኝ ለአያቴ አንድ ወታደር እንደደፈረኝ ነገርኳት፡፡ እሷም ለእናቴ ነገረቻት፡፡ እጅጉን ደነገጠች፡፡ እኔን ለማሳደግ ቤት ንብረቷን ትታ ኑሮዋን በረሃ አድርጋለች፡፡ አሁን በእኔ ላይ ይህ ችግር መድረሱን ስትሰማ ማመን አልቻለችም፡፡ ሳትውል ሳታድር መጣች፡፡ በነገታው ወደ ካምፑ ተመልሳ ወታደሩን ለመክሰስ ሞከረች፡፡ ‘የት እንዳለ አጣነው’ አሏት፡፡ ትንሽ ቆይተው ደግሞ ‘አርፈሽ ተቀመጪ’ ብለው አስጠነቀቋት፡፡ በዚህ ጊዜ እናቴ ሁሉንም ነገር ትታ ወደኔ መጣች፡፡”

እናቷ ሁሉንም ነገር ትታ የተደፈረችውን ልጇን ለመንከባከብ ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ ስምረትም እንደ ምንም ትምህርቷን ቀጠለች፡፡ በዚህ መሀል የጤና እክል ገጠማት፡፡ በቀላሉ የጀመራት ሕመም እየጠናባት ሄደ፡፡ እናቷ በየጠበሉ ይዛት ትዞር ጀመር፡፡ ሕመሟ በቀላሉ ፈውስ የሚገኝለት አልሆነም፡፡ የስምረት የልጅነት ሰውነት እየመነመነ፣ ወዘናዋ እየነጠፈ፣ ልምላሜዋ እየጠወለገ፣ ሁለመናዋ እየገረጣ ሄደ፡፡ ወዳጅ ዘመድ ሁሉ ወደ ዘመናዊ ሕክምና እንድትወስዳት እናቷን መከራት፡፡ በምክራቸው ተስማምታም ወደ ሆስፒታል ወስዳ አስመረመረቻት፡፡ ሕመሟ ተደረሰበት፡፡ መድኃኒት መውሰድም ጀመረች፡፡ ልጅቱ ይህን ስትነግረኝ እንደ አዲስ ትደነግጥ ነበር፡፡ የምርመራው ውጤት ለእናቷ ሲነገራት ስምረት ልጅ ስለነበረች ምን ዓይነት በሽታ እንደያዛት አላወቀችም፡፡ ለረዥም ጊዜ የማያቋርጥ መድኃኒት የመውሰዷ ነገር ግን ያስገርማት ነበር፡፡  

መቼም ችግር ሲመጣ ጓዙን ጠቅልሎ ነው፡፡ ስምረት በመደፈሯ የደረሰባት የሥነ ልቦና ችግር ሳያንስ፣ የዕድሜ ልክ ታማሚ ሆናለች፡፡ ይባስ ብሎ መገለሉ ሊያሳብዳት ተቃረበ፡፡ የመታመሟ ወሬ በፍጥነት ተዛመተ፡፡ መጀመሪያ በጎረቤት፣ ከዚያም በመንደር፣ አልፎም በትምህርት ቤት ተዳረሰ፡፡ የምትናፍቃቸውና የሚናፍቋት የሠፈርና የትምህርት ቤት ጓደኞቿ በአንዴ ይሸሹዋት ጀመር፡፡ ይህን መገለል በጨቅላ ዕድሜዋ፣ በሕፃን አዕምሮዋ የምትቋቋመው አልሆነም፡፡ እናም እናቷን ጠየቀቻት፡፡ “ምንድነው የሆንኩት?”፣ ሰዎች ለምን እንደሚጠቋቆሙባት፣ ለምን እንደሚሸሹዋት፣ ለምን እንደሚያገሏት እንድትነግራት ተማፀነቻት፡፡ እሷም የማይቀረውን ዜና እንዲህ በማለት ተነፈሰችው፡፡ “በቫይረሱ ተይዘሻል፣ እንግዲህ ቻይው፣ እስከ ዛሬ ድረስ ዕድሜሽ ስለማይፈቅድ ነበር ያልነገርኩሽ፡፡”

ስምረት ቀጠለች፡፡ “በዚህ ጊዜ ድንጋጤ መላ አካላቴን ወረረኝ፣ አዕምሮዬ ተረበሸ፣ ተረጋግቼ መማር አቃተኝ፡፡ ‘ከዛሬ ነገ ልጄ ለቁም ነገር ትበቃለች’ ብላ ስትመኝ የነበረችው እናቴ፣ መታመሜን ከሚያውቁ ሰዎች ለመሸሽ ይዛኝ ከቦታ ቦታ መንከራተት ጀመረች፡፡ ከምንኖርበት ከተማ ለቀን ሌላ ቦታ መኖር ጀመርን፡፡ እዚያ ትምህርት ጀመርኩ፡፡ ብዙም ሳልቆይ ወሬው ተሰማ፡፡ አድልዎና መገለሉ ቀጠለ፡፡ ትምህርቴን አቋረጥኩ፡፡ በምግብ ቤት ሥራ ጀመርኩ፡፡ እዚያም አልሆነም፡፡ ሁኔታው እየተባባሰ መጣ፡፡ ችግሬ እየከፋ ሄደ፡፡ አማራጭ ሳጣ፣ በአገሬ መኖር ሲያቅተኝ፣ በመጨረሻ ከአንዲት ጓደኛዬ ጋር ወደዚህ ተሰደድን፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላም ኢትዮጵያ ደረስን፡፡”

ስምረት በማይ ዓይኒ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አዲስ ሕይወት ጀመረች፡፡ የተለያዩ አገልግሎቶች እየተሰጣት፣ መድኃኒቷንም በአግባቡ እየተጠቀመች ሰውነቷ መሻሻል አሳየ፡፡ በኤርትራ የነበረው የመገለል ችግር ግን ተከትሏት መጥቷል፡፡ በመጠለያ ጣቢያው ስደተኞቹ እየተበራከቱ ሲመጡ የሚያውቋት ሰዎች እየበዙ ሄዱ፡፡ በበሽታው የመያዟ ወሬም መናፈስ ጀመረ፡፡ መገለሉም አገረሸ፡፡ በዚህ ምክንያት ብቻዋን ቤት ውስጥ መዋል ጀመረች፡፡ እንቅስቃሴዋ ተገደበ፡፡ ዓለሟ ጠበበ፡፡ ከሰዎች ዕይታ ለመሸሽ ብላ ቤት በምትውልበት ጊዜ ዋናው ሥራዋ በሽታዋን ማዳመጥ፣ ጭንቀቷን ማሰብ ሆነ፡፡ በዚህ ላይ የቤተሰብ ናፍቆትና ሐሳብ ተጨምሮበት ነገሩ ሁሉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነባት፡፡ ዓለም ፊቷን አዞረችባት፡፡

 

ይህን ሁሉ ታሪክ ስትነግረኝ ከዓይኖቿ የሚጎርፈው እንባ አላቋረጠም፡፡ “የሚቻል ቢሆን ከዚህ የመጠለያ ጣቢያ ወጥቼ የከተማ ስደተኛ ሆኜ ሰፋ ባለ ከተማ ውስጥ ከሰው ጋር ተመሳስዬ መኖር ነው፡፡ የሆነ ሙያ ተምሬ ሕይወቴን መምራት ብችል ደስ ይለኛል፡፡” ይህ ቀላል እንዳልሆነ ልቧ ያውቀዋል፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ለኤርትራ ስደተኞች የሰጠው አንድ ዕድል አለ፡፡ በከተማ የመኖር፡፡ ይህን ለማድረግ ግን የመተዳደሪያ ገቢ ያስፈልጋል፡፡ የከተማ ስደተኛ ሆኖ የመኖር እንጂ የመሥራት ፈቃድ አልተሰጣቸውም፡፡ ስለሆነም ደጋፊ ያላቸው ስደተኞች ናቸው በዚህ ዕድል የሚጠቀሙት፡፡ ይህን ማድረግ የማትችለዋ ስምረት ያላት አማራጭ ሌላ ነው፡፡ እግዚአብሔር ብሎ ለወደፊት ወደ ሦስተኛ አገር የመሄድ ዕድል እስኪገጥማት ድረስ ባለችበት የመጠለያ ጣቢያ ሆና በመገለል የታጀበ የስደት ሕይወቷን መምራት፡፡

ከስምረት ጋር በፈገግታ የተጀመረው ቃለ መጠይቅ በእንባ ሊቋጭ ተቃርቧል፡፡ “አሁን የወደፊት ተስፋሽ ምንድነው?” ብዬ ብሶቷን ያባባሰ ጥያቄ ሰነዘርኩ፡፡ በቁስሏ ላይ እንጨት ሰደድኩበት፡፡ የሰጠችኝ ምላሽ ልብ የሚሰብር ነበር፡፡ “እኔ ምን ተስፋ አለኝ? ራዕዬ ጨልሟል፣ ተስፋዬ ከስሟል፣ ህልሜ መክኗል፡፡ የሰው ልጅ ተስፋው የሚጀምረው ከእናቱ እቅፍ ወርዶ ትምህርት ቤት በሚገባበት ቀን ነው፡፡ እንደ ሰው ይህን ሒደት ጀምሬዋለሁ፡፡ ከዚያም ተስፋህ ከዕድሜህና ከትምህርት ደረጃህ ጋር እያደገ ይሄዳል፡፡ የእኔ ግን ገና በአሥር ዓመቴ ነው ሳይታሰብ የተቀጨው” ብላ መቼም የማልረሳውን መራራ ዓረፍተ ነገር ሰንዝራ በእንባ ተሰናበተችኝ፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው mikyidr2012@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

                                                 

Standard (Image)

አብረን ካልጮኽን አብረን እንሰምጣለን

$
0
0

በበቃኸኝ አንተነህ

ትውልድ ከሞተ አገር ያለጥርጥር ትሞታለች፡፡ የትውልድ ሞት በተለያየ ነገር ይገለጻል፡፡ በአደንዛዥ ዕፅ፣ በጫት፣ በአልኮልና በዝሙት የናወዘ ትውልድ አገር ብትወረር፣ ብትሸጥ ግድ አይኖረውም፡፡ ሱሪውን ቢያወልቁበት ወይም መንገድ ላይ ቀሚሷን ቢገልቡት ደንታ ላይሰጠው ወይም ላይሰጣት ይችላል፡፡ በሐሽሽ የናወዘ ትውልድ ወንጀል ለመፈጸም እጅግ ቅርብ ነው፡፡ አገርን ከሚያፈራርስ የጥፋት ቡድን (አሸባሪ) አድርግ የተባለውን ተልዕኮ ሁሉ ከመሸከምና ከመፈጸም ወደኋላ  አይልም፡፡

በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በአንዳንድ የክልል ከተሞች ለጆሮ የሚሰቀጥጥ፣ ሰው መሆናችን እስክንጠራጠር ድረስ የሚደመጡ ተደጋጋሚ ወንጀሎች ከዕለት ወደ ዕለት እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በጠራራ ፀሐይ ‹ካላፈቀርሽኝ› ብሎ በጩቤ ወግቶ የሰውን ክቡር ሕይወት ማጥፋት፣ አሲድ በፊት ላይ መድፋት፣ የትዳር ጓደኛን በጭካኔ መግደልና በድን አካሏን መቆራረጥ፣ ልጅ ከእናት ጋር ተባብሮ አባትን መገደል ወይም እናትን መግደል፣ ወንድም በወንድሙ ላይ አነጣጥሮ ተኩሶ መግደል፣ ክህደት፣ ስርቆት የመሳሰሉ የአንድ ማኅበረሰብ (አገር) ማኅበራዊ ህፀፆች የማኅበረሰብ ሕመም (Social Ills) ዓብይ ምልክቶች ናቸው፡፡

የዛሬን አያድርገውና ድሮ እያንዳንዱ የማኅበረሰብ አባል አንዱ ለአንዱ የሚኖር ነበር፡፡የአንዱ ጉዳት ልክ እንደ ራሱ ጉዳት አድርጎ ይመለከት ነበር፡፡ በእሱ ላይ እንዳይፈጸም የሚፈልገውን ነገር በሌሎች ላይ አይሞክረውም ነበር፡፡ አንድ የጎረቤት ልጅ ማኅበረሰቡ የማይቀበለውን ነገር ሲፈጽም ያየ ሌላ ጎረቤት ይህን ተግባር የፈጸመውን ግለሰብ ወይም ልጅ የመገሰፅና የመቅጣት ማኅበራዊ ኃላፊነት ነበረበት፡፡ ምክንያቱም የጎረቤት ልጅ ሥነ ምግባር ከጎደለው ለአካባቢው ጠንቅ እንደሆነ ሁሉም ስለሚረዳ፣ ልጆቹን በሥነ ሥርዓት ለማሳደግ ሁሉም ኃላፊነት ነበረበት፡፡ እኔን ወላጆቼ ብቻ አይደለም ያሳደጉኝ፡፡ ጎረቤቶቼ፣ አልፎ ሂያጅ መንገደኛ ሳይቀር በልጆች መልካም ሥነ ምግባር ሁሉም አስተዋጽኦ ነበርው፡፡ ጥፋቱን የፈጸመው አዋቂ ሰው ከሆነም በማኅበረሰቡ እንዲመከር ይደረጋል፣ ይወገዛል፣ አልመለስም ካለም ከማንኛውም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲገለል ይደረጋል፡፡ እነኚህ ሁሉ ድሮ የነበሩ የማኅበረሰብ እሴቶች ናቸው፡፡

ዛሬ ያ ሁሉ ተቀይሯል፡፡ ጎረቤት አይደለም አባት ወይም እናት፣ ወይም ታላቅ ታናሽን መቅጣት በፍጹም አይችልም፡፡ መቅጣት ስል በጥሬ ትርጉሙ መደብደብ (አካላዊ ጉዳት) ማድረስ እንዳልሆነ ይያዝልኝ፡፡ የዚህ ሁሉ ውጤቱ ትውልዱን ጥፋት በቀላሉ እንዲፈጽም አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ግብረ ገብ ከጠፋ ውሎ አድሯል፡፡ ወላጅና ልጅ በአንድ ላይ የወሲብ ፊልም አብረው ማየት ጀምረዋል፡፡ እናት ወይም አባት ልጅን እንዲያጠና፣ ለትምህርቱና ለሥነ ምግባሩ አርዓያ ከመሆን ይልቅ ከዚህ በተቃራኒ ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ በአንድ ቻናል የሚተላለፍ ፊልም ከልጆች ይልቅ የወላጆችን አዕምሮ የበለጠ አደንዝዞታል፡፡

ለዚህች መጣጥፌ መነሻ የሆነኝ በአዲስ አበባ አንዳንድ የግልም ሆነ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች እየታየ ያለው ሥርዓት አልበኝነትና ጋጠ ወጥነት ይህችን አገር ወደ ጥፋት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ሊከታት እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ ዛሬ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት በአዲስ አበባ ምድር ነውር መሆኑ እየቀረ ይመስላል፡፡ ኧረ ክልል ድረስ አልፎ ሄዷል፡፡ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ሴት ልጆች የጎንዮሽ የገቢ ምንጫቸው (Sideline Income) ሴተኛ  አዳሪነት ከሆነና ሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎች ከጎበኘ ውሎ አድሯል፡፡

በተለይ በተገቢው መንገድ ሳይሆን የሕዝብን ደምና አጥንት ግጠው (በሙስና) ሀብታም የሆኑ የአንዳንድ ግለሰብ ልጆች ገንዘብ የሁሉም ነገር መጨረሻና የገነት በር ጭምር መቆጣጠሪያ አድርገው በማየት፣ ለልጆች ሥነ ምግባር መበላሸት የእነዚህ ‹‹የገንዘብ ሀብታም ነገር ግን የሥነ ምግባር ደሃ›› ቤተሰብ ልጆች ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ገንዘብ ለልጆቻቸው  ለምን እንደሚሰጧቸውና ለምን አገልግሎት እንደሚያውሉት ፈጽሞ ማወቅ አይፈልጉም፡፡ ገንዘብ ለልጆቻቸው በመርጨት ከኃጥያታቸው የነፁ ይመስላቸዋል፡፡ ግን ሌላ ኃጢያት በገንዘቡ እየተሠራ እንደሆን አይረዱም፡፡ ቢረዱም ግድ የላቸው፡፡

በዚህች የጉድ ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች የሚደረገውን ከሞራል፣ ከግብረ ገብና ከሃይማኖታዊ አስምህሮ የራቀ ድርጊት ማየት እጅግ ቀላል እየሆነ መጥቷል፡፡ ከእኔ መሥሪያ ቤት አጠገብ አንበሳ ጋራዥ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ የግል ትምህርት ቤት አለ፡፡ እዚህ ትምህርት ቤት የሚማሩ የመክፈል አቅማቸው ደህና የሆኑ ቤተሰብ ልጆች ናቸው፡፡ ከዚህ ትምህርት ቤት በቅርብ ርቀት  አንድ ቁርስ ቤትና የመጠጥ ግሮሰሪ አለች፡፡ የዚህ ትምህርት ቤት ሴት ተማሪዎች ጠዋት ጠዋት ዩኒፎርማቸውን እንደለበሱ (ምንም ኃፍረት ሳይሰማቸውና ለለበሱት የተማሪ ዩኒፎርም ሳይጨነቁ) ከዚች ቁርስና መጠጥ (መሸታ ቤት ልበለው) በመምጣት ደረቅ ጅን ጠጥተው ወደ ክፍል ይገባሉ፡፡ ቁጭ ብለው ለመጠጣት ከረፈዳባቸው ደግሞ በውኃ መያዣ ኮዳ (የውኃ ፕላስቲክ) ደረቅ ጅን አስቀድተው ወደ ትምህርት ቤት ይዘው መግባት የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡

ይህን ለሚያይና አዕምሮ ላለው ሰው ወዴት እየሄድን እንደሆን መገመት ቀላል ነው፡፡ ይህ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹን በኑባቤ (ቲዎሪ) ብቻ ቆዝሮ ከሚያወጣቸው ይልቅ ምን አለ ጭንቅላታቸው ላይ ትንሽ ሥራ ቢሠራ? ይህ ትምህርት ቤት ልጆቹን እንደ ፈረንጅ እንግሊዝኛ አቀላጥፈው እንዲናገሩ ከማድረግ ባለፈ አረቄ ይዘው ወደ ትምህርት ቤቱ እንዳይገቡና ሰክረው አስተማሪም ተማሪም እንዳይበጠብጡ ምን ሥራ እየሠራ ነው? ወላጆች የልጆችን አዋዋል ከትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን ይከታተላሉ? ይህ ትምህርት ቤት እነዚህን ልጆች አስተምሮ ገንዘብ ከሚሰበሰብ ይልቅ ለምን ተዘግቶ ለአገርና ለወገን በሚጠቅም  ሌላ ሥራ ላይ ቢሰማራስ? ወላጆች ደግሞ ለማይጠቅሙ ልጆች ገንዘብ ከሚያጠፉ ለነዳያን ይህን ገንዘብ ሰጥተው የገነት በራቸውን ቢያስከፍቱ ምን አለበት?

በዚህ ትምህርት ቤት የማስተምረው ልጅም ሆነ የሚማር የማውቀው የዘመድ ልጅ የለኝም፡፡ ከትምህርት ቤቱ ጋርም የተለየ ቂምም ሆነ ሌላ ግንኙነት የለኝም፡፡ የእነዚህ ልጆች መበላሸት ነገ በማኅበረሰቡ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ቀውስ እጅግ ያሳዝነኛል፡፡ የእነዚህን ተማሪዎች ሥነ ምግባር የጎደለው ትርዒት ማየት የፈለገ ሰው ቁርስ ቤቷን ከሰኞ እስከ ዓርብ ሄዶ ቢጎበኝ ድርጊቱን መታዘብ ይችላል፡፡ ማን ያውቃል ጠጥተው የሚያሸክርክሩ ለትውልድ የማይጨነቁ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር፣ በአሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ የአልኮል ምርመራ እንደሚደረገው በትምህርት ቤቶችም ይህ የአልኮል መመርመሪያ መሣሪያ (Alcohol Detector) በሒደት ማስፈለጉ የሚቀር አይመስለኝም፡፡

ሌላው ማኅበረሰብስ እነዚህ ወጣት ሴት ልጆች ዩኒፎርም ለብሰው አረቄ ሲጠጡ ሲያይ ለምን አይገስፅም? አረቄ የሚሸጥላቸው መሸታ ቤትስ ለእነዚህ ክፉና በጎውን በቅጡ ላለዩ ሴት ልጆች አረቄ ሸጦ ከሚያገኘው ሽርፍራፊ ገንዘብ ይልቅ ለትውልድ ሞት ለምን ደንታ ቢስ ሆነ? መንግሥትስ ቢሆን የአረቄ ወይም የአልኮል መሸጫና መጠጫ ሰዓት ሥርዓት ለምን አያበጅም? የወጣት ጥፋተኛነት (Juvenile Delinquency) አንዱና ምንጩ ሥርዓት ያጣው የአልኮል መጠጥ፣ ጫትና ሐሽሽ ያስከተለው ውጤት ነው፡፡

የአንድ አገር የልማት አውታርንና በመንግሥት ላይ የሚደረግን ተቃውሞ በቅጡ የማይለይ ትውልድ ሊያስከትል የሚችለውን ጥፋት ባለፈው ዓመት በዓይናችን በብረቱ ዓይተናል፡፡ መንግሥትን በመቃወም ሰበብ ለአገር ልማት  የተገነቡ የልማት አውታሮች በአንድ ላይ ሲወድሙ ተመልክተናል፡፡

እነዚህ ልጆች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሚያደርሱት ሕገወጥ ተግባር እኔን አይነካኝም ማለት አይቻልም፡፡ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በጨካኝ የወጣት ጥፋተኛ በጩቤ ተወግታ የሞተችው ልጅ የሁላችንም ልጅ፣ የሁላችንም እህት ናት፡፡ በተማሪ ሀና ላይ የተፈጸመው በቡድን መደፈር የተበላሹ የማኅበረሰቡ አባላት የፈጠሩት ሰቆቃ ነው፡፡ ዛሬ ዝምታውን መስበር ካልቻልን ነገ የእያንዳንዳችን ቤት ተራ በተራ መንኳኳቱ የማይቀር ነው፣ ጊዜውም ሩቅ አይሆንም፡፡ ዛሬ በሚደረግ ከሥነ ምግባር የወጣ ተግባር አብረን በመጮህና በመከላከል ካላስቆምነው አብረን ወደ አዘቅት  እንደምንገባ ጥርጥር የለውም፡፡

'ሳይቃጠል በቅጠል'አልልም፡፡ ምክንያቱም ቃጠሎውን ከዚህም ከዚያም እያየን ነውና፡፡ ይህን ቃጠሎ በጋራ ማጥፋት የግድ ይለናል፡፡ በሚቀጥለው ጹሑፌ በሌላ የግል ትምህርት ቤት የተፈጸመውን የተማሪዎችን አስነዋሪ ተግባር፣ ይህንን የተማሪዎች አስነዋሪ ተግባር በገሰፀ የትምህርት ቤቱ መምህር ላይ የተማሪዎች ወላጆችና የትምህርት ቤቱ አመራር በእሳት ላይ ቤንዚን ዓይነት ዕርምጃ አቀርብላችኋለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው bekahegn2016@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

 

 

Standard (Image)
Viewing all 231 articles
Browse latest View live