በሰለሞን ወርቁ
‹‹አቢጃታን ተዪው
ሻላንም ጨምረሽ
አለማያም ደርቋል
ጥምሽን ሳይቆርጥልሽ፡፡››
ይህንን ግጥም አንድ የቆጨው ገበሬ ያለው ይመስለኛል፤ እኔ ከማለቴ በፊት፡፡ አንድምታው ይህ ነው፤ አለማያን ዓይናችን እያየ ሲሞት ዝም ብለንው አፋፍሰን ወስደን ቀብረን ስናበቃ የዋጥነውን ሀቅ ለማስመለስ (ለይምሰል) እንደጓጉጥ መያዛችን ቢደንቅ ነው፡፡ የሞተን መሸኘት ባህላችን ከህንድ ቡዲሂስቶች ባይስተካከልም የሚተናነስ አመስለኝም፤ (ሳይበልጥ ይቀራል ብለህ ነው) የታመመን ማስታመም እንደምን አናውቅበት አልን? ያልታመመን ማሳመም እንደምን ተካንበት?
ነገሬ ወዲህ ነው፤ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በፊት ገጹ ላይ “በሻላ ሐይቅ አካባቢ የሶዳ አሽ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፤” ሲል ያወጣውን መረጃ አንብቤ ነገሩ ግራ ቢገባኝ ነው፡፡ በዜናው ውስጥ በሁለተኛው ምዕራፍ እንዲህ ይላል፤ “. . . የአቢጃታ ሐይቅ ውኃ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ድርጅቱ በሐይቁ ላይ ያለው የሶዳ አሽ ምርት ቀንሷል፡፡ በመሆኑም በሻላ ሐይቅ ላይ 550 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ግንባታ ለማከናወን ጥናት እየተካሄደ ይገኛል፤” በሁለተኛው ገጽ የዞረው መረጃ ደግሞ ከሚያትተው ነጥብ ለነገሬ አባሪ ልውሰድ፤ “. . .ሐይቁን በባቱ ከተማ ላይ የመስኖ ሥራ የሚያከናውኑ የአበባ እርሻና የወይን ማምረቻዎች በስፋት እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ በአካባቢውም 6,000 የሚደርሱ የመስኖ ውኃ መሳቢያ ‹‹ፓምፖች›› ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የሐይቁ መጠን እየቀነሰ ሲሆን፣ ከመጥፋት ለመታደግ ውኃውን በፈረቃ መጠቀም አስፈላጊ ነው፤” እንዲህም ያለ ተቆርቋሪነት አላየንም አትሉም? ይህንን መስመር ስትጨርሱ? አቢጃታ ይኼው ተቆርቋሪን ጨምሮ እንደ መዥገር የተተከሉ 6,000 ፓምፖች ግብዓተ ሞቱን ዕውን ለማድረግ ላለፉት አጭር ዓመታት ሲታትሩ ኖረው እነሆ ድላቸውን በጋራ ለማክበር የቀራቸው አጭር ቀን ቢሆን ነው፡፡ የአቢጃታ ውኃ መቀነስ ያስከተለው ተፈጥሯዊ ሳንካ በውል ሳይመዘን፤ ወደ ሻላ ለመሸጋገር ዕቅድ የነደፈው ፕሮጀክት ከገንዘብ ባሻጋሪ ምን እንደታየው እንድትጠይቁልኝ እማጸናለሁ፡፡
ለዓለማችን ድንቅ ከሚባሉት የአዕዋፍ መዳረሻ ቦታዎች በታላቁ የስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙት አቢጃታ፣ ሻላና ጭቱ ሐይቆች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ሐይቆች በአገራችን ውስጥ ብቻ ላሉት አዕዋፍ ሳይሆን በዓለማችን አህጉራትን አቋርጠው ተሰዳጅ ለሆኑት ጭምር ማረፊያና መራቢያ ሆኖ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ 453 የሚያህሉ የአዕዋፍ ዝርያዎችን የያዘው የአቢጃታ ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ ከሞት እየተናነቀች ትርትር የምትል ነፍሱ የቆመችው ትንሽም ቢሆን ተስፋ ባለው በሻላ ሐይቅ አማካይነት ነው (ነበር ልንል የቀረን ጊዜ ከአንድ አንጓ ያጠረ ነው)፡፡ 144 የሚያህሉት የአዕዋፍ ዝርያዎች ሐይቁን ተገን አድርገው የሚኖሩ ናቸው፤ (በቅርቡ ነበሩ እንላለን)፡፡
ሻላ ሐይቅ በአፍሪካ ካሉት የካልዴራ ሐይቆች ቀዳሚው ሲሆን፣ ዓመቱን ሙሉ የሻሎ (Pelican) መራቢያነት የሚያገለግል ሲሆን፣ በዚህም ከታንዛኒያው ሩኩዋ ሐይቅ ቀጥሎ በሁለተኛነት የሚገኝ ሐይቅ ነው፤ እስከ 5,000 የሚደርሱ ሻሎዎችም በየዓመቱ ይራቡበታል፡፡ 50,000 ፍላሚንጎዎች (Flamingo)፣ 40,000 የሚሆኑ መንቁረ ግልብጥ (Pied Avocet) በተፈጥሯዊ ስደታቸው በማረፊያነትና በመመገቢያነት ይገለገሉበታል፡፡
በኢትዮጵያ በጥልቀቱ ቀዳሚው ሐይቅ ነው፤ ሻላ፡፡ በዚህ ሐይቅ ላይ የሚከሰት ማንኛውም ዓይነት የሰዎች ንክኪ የሐይቁን ህልውና የሚጋፋ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያትም ለሚከሰት የተፈጥሮ ሀብት መመናመን ይዳርጋል፡፡ ይህ ሥፍራ ማለትም የአቢጃታ ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠቃሚ የአዕዋፍ መዳረሻ (Important Bird Area) በመሆኑ ኢትዮጵያ ለፈረመቻቸው (Africa-Eurasian Migratory Waterbird Agreement) እና ሲኤምኤስ (CMS) ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ቀዳሚው መነሻ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ቦታ አካባቢ የሚደርስ የተፈጥሮ መዛባትን የሚያስከትል ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ የተፈረመውን ስምምነት የሚጻረር ለመሆኑ ምንም ዓይነት ማስተባበያ የማያሻው ሐቅ ነው፡፡ ይህንን ስምምነት በመጣስ የሚተገበር ማንኛውም እንቅስቃሴ ደግሞ ምን መጣስ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፤ አውቀን እንጥሳለን. . .፡፡
ተከታዩ ነጥብ፤ አገራችን የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ ሲባል ለሚደረገው የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ በአፍሪካ ቀዳሚዋ አገር ሆና እየታተረች ነው፤ አረንጓዴ ልማት ማለት ዛፍ ከመትከል ያለፈ ጉዳይ መሆኑን አሌ የምንለው ሀቅ አይደለም፡፡ እንደ አቢጃታና ሻላ ያሉትን እነዚህን ሐይቆች ህልውና መጋፋት ደግሞ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ የአረንጓዴ ልማትን መጻረር ለመሆኑ አዋቂ ወይም ወልይ ሊነግረን የሚገባ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ሦስተኛው ነጥብ፤ የአገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዲያንሰራራ ደፋ ቀና በሚባልበት በዚህ ወቅት ይህንን ጉዳይ መመልከት እጅግ አስደንጋጭ ነገር ነው፡፡ ከሃይማኖታዊ ጉዞ ቀጥሎ ቱሪዝም እያደገ የሚገኝበት ቦታ ካለ መዳረሻው በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ባሉት በእነዚህ ሐይቆች አካባቢ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም በርካታ ሊባሉ የሚችሉ ኢኮቱሪዝምን መሠረት ያደረጉ ሆቴሎችና ሎጅዎች በዚያ አካባቢ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፤ ሌሎችም በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ ተወደደም ተጠላም፤ ተጠልቶ አንገሸገሸም የሚዋጠው ሀቅ የእነዚህ ሁሉ መሠረት የሐይቆቹ ህልውና ነው፡፡
ተፈጥሮን መሠረት ያደረገ አግባብነት ያለው አጠቃቀም ደግሞ ለአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ለአገርና ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ ዘላቂ ተጠቃሚነት ዋስትና ይሰጣል፡፡ በእነዚህና ሌሎች አገራችን በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እያደረገችላቸው በሚገኙ አካባቢዎች ሊኖር የሚገባው የአጠቃቀም መርህ ደግሞ ተፈጥሮን የማይጎዳ መሆን አለበት፡፡ እነዚህን ዓይነት በተፈጥሮ ጥበቃ ቦታዎች ዙሪያ የሚካሄድ ማንኛውም ዓይነት የማዕድን ቁፋሮና መሰል ተግባርት ደግሞ እጅ እግር የሌላቸው ጥፋት ብቻ ናቸው፡፡ ይህንን ጉዳይም የብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን ሊያስብበት ይገባል፡፡
እሺ እንጥቀስ፤ መቼም ሕግ ካልተጠቀሰ ሕግ የማይከበርበት አገር ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ አዋጅና ደንብ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 163/2001 ስለዱር እንስሳት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ፤ ክፍል ሁለት ቁጥር አምስት በብሔራዊ ፓርኮች፣ በዱር እንስሳት መጠለያዎችና በዱር እንስሳት ጥብቅ ክልሎች ውስጥ እንዳይከናወኑ ስለተከለከሉ ተግባራት፤ ሸ/ የማዕድን ፍለጋ ወይም ቁፋሮ ማካሄድ ተጠቅሷል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ እንግዲህ አንዱና ዋናው የዚህን ደንብ ጥሰት የሚያሳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምን ይሠራል ካላችሁ? በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ተግባሩ የተፈጥሮ ሀብትን እንደሚጎዳ አስረድቷል፤ ሆኖም ግን ሒደቱን ለማስቆም አልቻለም፡፡ የዚህ ሶዳ አሽ ፋብሪካ ባለቤቶች ከሆኑት ውስጥ የመንግሥት ተቋማት ከፍተኛ ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶች በአክሲዮን እንደተካተቱበት ጋዜጣው በመግቢያው ላይ ጠቅሷል፡፡ የዚህ ጉዳይ አስረጅነትም ሕጉ የተጣሰው በሌላ የመንግሥት አስፈፃሚ አካል መሆኑን ነው፡፡ ይህ ጉዳይ አሁንም ቆም ተብሎ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡
‹‹የሞተው ወንድምሽ
የገደለው ባልሽ
ሐዘንሽ ቅጥ አጣ
ከቤትሽ አልወጣ፡፡››
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ግንቦት 2 ቀን (ሜይ 10) የሚከበረውን የዓለም አቀፍ ስደተኛ አዕዋፍ ቀን መነሻ በማድረግ፣ በየዓመቱ በእነዚህ ሐይቆች ዳርቻ በመገኘት በተለያዩ ተግባራት ያከብራል፡፡ በቀጣይ ቅርብ ዓመታት ደግሞ ሐይቆቹ የነበሩበት ቦታ ላይ ቆሞ ታሪካቸውን ይዘክራል!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው solwors@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡
