ግምገማ፣ በጳውሎስ ሚልክያስ አመያ (ፕሮፌሰር)
ክፍል ሦስት
ይህ ቅኝት የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭተብሎ የታተመውን የዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን የፈጠራ ቅብዐ ቅዱስ ምኅዳር የሚገመግም ሦስተኛውና የመጨረሻው ትችት ነው። በእርግጥ የደራሲው ፍቅሬን ሒሳዌ መልዕክትን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ጥብቅ ማስጠንቀቂያዎችን ማሳለፍ ተገቢ ነው፡፡ በጤና አዕምሮው ያለ ምሁር፣ እኝህ ጸሐፊ የሰነዘሯቸውን ቁጥር የለሽ አሳሳች ሐተታዎች ወደ ጎን አድርጎ ያልተረጋገጠው ድርሰት በታሪካዊ ተሐድሶ ስም በገፍ ሲሰራጭ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ አይደለም፡፡ እኔ በበኩሌ መምህር እንደመሆኔ መጠን፣ ታሪክ ለማወቅ ለሚጓጉ ወጣት ኢትዮጵያውያን ሥራውን ካነበቡ በኋላ በተምታታና በድንግዝግዝ ሁኔታ ውስጥ ከሚቀሩ ምክሬን በግልጽ በመለገስ ሞግዚታዊ ተግባሬን ለመወጣት የመረጥኩበት ምክንያት ለዚህ ነው፡፡
ዶ/ር ፍቅሬ፣ እርስዎ ራስዎ እስቲ ይገምቱት? አስተማሪ ሲባል እኮ በሁሉም መስክ አለ። ለምሳሌ ያህል እርስዎ የመኪና መንዳት አስተማሪ ነዎት እንበል። ይህ ከሆነ ዘንዳ መኪና መንዳት የሚያስተምሯቸውን ተማሪዎች መንገድ ላይ አደጋ እንዳያጋጥማቸው ማስጠንቀቅ ኃላፍነትዎ መሆኑን ይዘነጋሉን? ይህን ካላደረጉማ ደንበኞችዎን ለአደጋ መዳረግ ብቻ ሳይሆን በራሱ ለራስዎ ሥራ ሳይቀር ትልቅ እንከን ፈጠሩ ማለት ነው።
ለመሆኑ ማን የታሪክ መምህር ነው? ‹‹የሰው ሁሉ ምንጭ ጎጃም ነው›› ብለው የሚለፍፉትን የፈጠራ ወሬ የሚጠቅስ ተማሪን ፈተና የሚያሳልፈው? አልሰሙ እንደሆን አላውቅም እንጂ የሰው ልጅ ከአፋር ረባዳ ሸለቆ መፍለቁን የሰው ቅሪት ሊቃውንት የሔዋን መላምት ዱካን በመከተል በሳይንሳዊ ፈለግ ምርምር የመጀመርያውን ኃይለ ሕዋሳዊ ፍሬ ካረጋገጡ ጊዜው ከርሟል።
የርስዎን ተረት ተረት ማን ተላላ ሊቀበለው? አንድ ተማሪ መጽሐፋቸውን ጠቅሶ፣ በፈተና ወረቀቱ ላይ ቢያሳርፍ ማን ጽኑ የምሁር ተልዕኮን የሚያከብር አስተማሪ ከክፍል ወደ ክፍል ሊያሳልፈው? በአፋር ረባዳ ሸለቆ በአዝጋሚ ለውጥ ከ200,000 ዓመታት በፊት የነበረ የሰው ቅሪት እንደተገኘና ከዚያም በምድር ሁሉ እንደተሰራጨ የሚያረጋግጠውን ጽንሰ ሐሳብ ዘመናዊ የተፈጥሮ ጥበብ ጥናት ሊቃውንት ከአጥናፍ እስክ አጥናፍ የተስማሙበት ጊዜ ከግማሽ ምዕት ዓመት አልፏል፡፡ ለዚሁም የሚከተሉትን ማስረጃዎች በጥሞና መዳሰስ ይጠቅማል፡፡ (አሊሰን ጆሊ፣ የሉሲ ቅርስ፣ ሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ማተሚያ ቤት እ.ኤ.አ. 2001፣ እንዲሁም ኖዋ ሐራሪ ሆሞ ሴፒየንስ እዳልቱ የሰው ልጅ አጭር ታሪክ፣ ራንደም ሐውስ፣ እ.አ.አ. 2014)
ሌላውን የመጽሐፉን ዝግንትል ለመጥቀስ፣ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ አንደሚሉት የባቢሎን ግንብ እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ የሰው ልጅ ቋንቋ “ሱባ” የተባለ ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን በካህናት ቋንቋነት ብቻ ተወስኖ ከመልከ ጼዴቅ ወደ ኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያ ወደ ደሸት፣ ከደሸት ወደ እስራኤል ተላልፎ፣ ኋላ ላይ ንግሥተ ሳባ እሴን ገድላ በዙፋን ከተቀመጠች በኋላ ከሰለሞን የወለደችው ቀዳማዊ ምኒልክ ቋንቋው በአዋጅ እንዲጠፋ አድርጎ በግዕዝ እስኪተካው ድረስ በተግባር ላይ ውሏል ይላሉ። ቀዳማዊ ምኒልክም የሱባን ቋንቋ ሲያጠፋና በሱባ ቋንቋ የተጻፉ መጻሕፍትንም ባቃጠለ ጊዘ፣ ሌሎቹን የሱባ ጽሑፎች ከጥፋት ለማዳን የቻሉት መደባዮች (ኦሮሞዎች) ነበሩ ብለው የፈጠራ አባባሉን አሳምረውታል። በዚህ ትረካ ሒደት ከኦሮሞዎች አንዱ የግል መጽሐፉን ላሙ እንድትበላው አደረገ፡፡ ቆይቶ ላሟ ታርዳ ስትበላለት የመጽሐፉ ቁርጥራጭ ክፍሎች በላሟ ሆድ ተቀርፀው ተገኙ፡፡ በዶ/ር ፍቅሬ ግምት ለዚህ ነው ኦሮሞዎች በባህላቸው መሠረት ከብቶቻቸውን ካረዱ በኋላ ሞራቸውን ዘርግተው በሱባ ቋንቋ የተጻፈውን ጽሑፍ የሚያነቡት ለማለት ነው። እንግዲህ የትኛው መምህር ነው ይህን አንቶ ፈንቶ ወሬ ከተጠቀሰው መጽሐፍ ወስዶ ያቀረበን ተማሪ ከክፍል ወደ ክፍል የሚያሳልፈው? ምታታዊ ተረት እውነት ነው ብለው በቀላሉ ተቀብለው ለሚያምኑ ወጣቶች ይህን ማስተማር ከባድ ኃላፊነትን መተላለፍ አይደለምን? (ለዝርዝር የአጻጻፍ ሥርዓቶች ፒተር ዳንኤልስና ዊልያም ብራይት ያዘጋጁትን የዓለም ጽሑፎች ሥነ ሥርዓት ተብሎ የተጻፈውንና (በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ማተሚያ ቤት እ.አ.አ. 1989 የታተመውን ይመልከቱ፡፡) በተጨማሪም የኢትዮጵያን የአጻጻፍ ሥነ ሥርዓት ለመዳሰስ ከፈለጉና ታሪካዊ ዳራውን ለማወቅ ካሻዎት ሁኔታውን በአግባቡ ለመረዳት የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆነውን በሌላ ቦታ የሚጠቅሱትን የአንዱን የኢትዮጵያ ምሁር የዶ/ር አየለ በከሬን ሥራ ኢትዮፒክ፣ የአፍሪካ የአጻጻፍ ዘዴ፣ ቀይ ባሕር ማተሚያ ቤት፣ እ.አ.አ. 1997) ተብሎ የተደረሰውን በጥልቅ ያንብቡት፡፡
መላ ቅዱሱ ከጠፋው የዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ትረካ አንዱ ጀማይካውያን በግራኝ መሐመድ ወረራ ጊዜ (1522 እስከ 1536 ዓ.ም.) በአዳሉ መሪ በአህመድ ኢብን ኢብራሒም አል ጋዚ ለዓረቦች በባርነት የተሸጡ የጅማና የአማራ ልጆች ሲሆኑ፣ የተጫኑባቸው መርከቦች በስፔናውያን ተማርከው ከካሪቢየን ደሴቶች አንዷ ወደ ሆነችው ወደ አሁኗ ጀማይካ አገር እንደተወሰዱና አሁን እዚያ የሚኖሩት ሕዝቦች የጥንት አማሮች ልጆች እንደሆኑ ይተርካሉ። ይህ ፈር ያልያዘ ትረካ በምዕራባውያንም ሆነ በጀማይካውያን ምሁራን በሚገባ የተዘገበውን የአትላንቲክ የባሪያ ንግድ ፍንገላ ጉዞ ጉዳይና ከምዕራብ አፍሪካ ወደ አዲሱ ዓለም የተሸጋገሩበትን የተረጋገጠ ዜና አያጤንም። (ይሀን ለመቃኘት ከፈለጉ የሚከተሉትን ምሁራዊ ጥናቶች ይዩ፤ ሐርበርት ክላይን የአትላንተክ የባሪያ ንግድ፣ ኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ማተሚያ ቤት እ.ኤ.አ. 1999 የታተመ፤ እንዲሁም አውድራ ዲፕቲ፣ ከአፍሪካ እስከ ተማሪስ፣ የአትላንቲክ የባሪያ ንግድ ኅብረተሰብ አወቃቀር፣ 1775 እስከ 1807 ተብሎ በፍሎሪዳ ዩኒቨርስቲ ማተሚያ ቤት እ.ኤ.አ. 2010 የታተመውን ይመልከቱ፡፡)
ዶ/ር ፍቅሬ ሆይ፤ የአማሮችና የኦሮሞዎች መሥራች ተብሎ የተሰየመው መከረኛውና ልብ ወለዱ “ዳሽት” በኢትዮጵያ ምድር አሰላስሎ ፈጥሮ በዓለም ዙሪያ የኮከብ ቆጠራን ጽንሰ ሐሳብ አቀነባበረው ተብሎ የተቀመጠውን ከመጽሐፍዎ ወስዶ የተጠቀመን የትኛውን ተማሪ ነው የትኛው መምህር ከክፍል ወደ ክፍል የሚያሳልፈው? “ደሸት”ን ለአማራና ለኦሮሞ አባት ነው ብለው ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የኮከብ ቆጠራም ፈልሳፊ አድርገውታል፡፡ የሆነ ሆኖ በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ የኮከብ ቆጠራ ሐሳብ በጥንታዊት ግብጽ እንደ ተጸነሰ፣ ከዚያም በባቢሎናውያን ተውሶ አልፎ በሒደት ግሪኮች ዘንድ ሲደርስ እያንዳንዱን የጨረቃ ዑደት በአንድ የተለየ እንስሳ ስም እንደሰየሙ፣ በዚያም ሰማያዊ አካላት የአንድን ሰው የወደፊት ጉዞ ሊያመለክቱና፣ በሕይወቱ ዋና ዋና ውሳኔዎችን ለመተንበይ ሊረዱት ይችላሉ የሚለው ሐሳብ በምሁራዊ መድረኮች በሰፊው ተተችቶበታል፡፡ ግን አንድ ጥያቄ፤ ከመቼ ወዲህ ነው ኮከብ ቆጠራና ታሪክ ተገናኝተው የሚያውቁት? በስዎስ ግምት ማንኛውም የኢትዮጵያ ታሪክ አዋቂ መምህር ከመጽሐፍዎ በመጥቀስ ይህን እውነት አድርጎ የተቀበለን ተማሪ ከክፍል ወደ ክፍል ያሳልፈዋል ብለው ያምናሉን?
ዶ/ር ፍቅሬ ራምዝስ ተብሎ የግብፅ ንጉሥ የሆነውን ግለሰብ ከ2,850 ዓመታት በፊት ዙፋኑን ከኢትዮጵያ እስከ ግብፅ ሲዘረጋ ከዚያም ከ1,850 ዓመታት የግብፅ ቆይታ በኋላ፣ ከተከተሉት 350,000 አማሮች መካከል ጥቂቶቹ ለመመለስ ቻሉ ይላሉ፡፡ ታላቁ አክሱማይት ብለው የሰየሙት የመላ ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሲሆን፣ ሴት ልጁን ለሜስፖቴሚያ ንጉሥ፣ ለናቡከደነፆር ሲድርለት አጅበውት የሄዱት የአማራ ወታደሮች ስለነበሩ፣ በዛሬዋ ኢራቅ ”አማራ” የተባለች ከተማን ቆርቁረው በስማቸው መሰየማቸው ለአማሮች ክብር ነው ይላሉ። እርስዎ መቼም ስም ሲገጥም በጭፍን ማያያዝ ፈጽሞ አይጨንቅዎትምና የኢራቆች “አማራ” የኢትዮጵያ “አማራ” ሆነልዎት።
በነገርዎ ላይ ዩኤስ አሜሪካ ውስጥ በአሪዞና አገር እንዲሁ “አማራ” ተብሎ የሚጠራ ቦታ አለ፡፡ በመሆኑም ታዲያ በጥንት ዘመን አማሮች የመጀመሪያዎቹን የአሜሪካን ህንድ አገሮች ወረው በስማቸው ከተማ ቆረቆሩ ሊሉ ነው? ኧረ መቼ በዚህ ያበቃል? ሮሜንያ በላሎሚጣ አውራጃም “አማራ” የሚባል ከተማ አለልዎት። እንድዚሁም በቻይናና በሲንጋፖር “አማራ” የተባሉ ቦታዎች ተገኝቶለዎታልና አያምልጥዎት፤ በነካ እጅዎ ያስወርሩን!
ነገርን ለማስተካከል የኢራቅ “አማራ” አመሠራረት ከዚህ ፍፁም የተለየ ነው። የኢራቅ “አማራ” ከተማ የተመሠረተችው እ.ኤ.አ. በ1860 የቱርክ ሥልጣን ሥር የነበሩት ሕዝቦች በየጊዜው ይዋጉ በነበሩበት ጊዜ በአልቡ ሙሐመድና በባኑ ላም ጐሳዎች ላይ የበላይነቱን ለሚያሳዩት የአቶማን ኃይሎች የኢራቅ ጦር ሠፈር ሆና እንድታገለግል ነበር የተቆረቆረችው፤ (የአል አማራ መከበብ የሜሶፖቴሚያ ጦርነት ከ1915 እስከ 1916፤ ኢንዲያና ዩኒቨርሲቲ ማተሚያ ቤት እ.ኤ.አ. 2014 ይመልከቱ፡፡)
ዶ/ር ፍቅሬ እንዲሁም “ኦፌር”ን የመሰለ የወል ስም ሲያጋጥዎት ከ“አፋር” ጋር ማያያዙ ቀሎዎታል፡፡ በአፋን ኦሮሞ “ማሊ” “ለምን” ማለትን ሲያመለክት፣ ኦሮሞዎች ዛሬ ማሊ ወደ ምትባለው አገር እንደፈለሱ ያመለክታል ይላሉ። በደቡብ ዓረብ የምትገኝ “ናግራን” ከተማ ደግሞ “ና ግራ” የተባለ የዓማረኛ ዓረፍተ ነገርን የሚያመለክት ነው ይላሉ፡፡ የጥንቷ ደቡብ ዓረብ አገር “የመን” በአማርኛ አገላለጽ ከ”የማን” እንደመጣ ያመለክታል ብለዋል፡፡ ከዚህም በላይ ጥንታዊ የግብፅ ከተሞች የአማርኛ ስሞች አሏቸው ይሉና ለምሳሌ “አማርና”ን “አማርን” “ቆንጆ ሆንን” ማለት ነው ብለው ጽፈዋል። ወረራዎ በዚህ ሳያበቃ ወደ ሌላ ቋንቋዎችም ዘምቷል። የግብፁ የግሪክ ቃል (የሦስተኛው ፊደላቸው ምልክት) “ዴልታ” “ድሎትንና ደኅንነትን” የሚያመለክት ነው ብለው ተርጉመዋል፡፡ በ”ፌስ ቡክ”ዎ እንደተስተዋለው: በዚህ ወረርሺኝ አተረጓጎምዎ አንባቢዎችዎን ማበሳጨትዎ አልቀረም። ለምሳሌ ሳምሶን ባዩ የተባለ አንባቢዎ በታላቅ ብስጭት ሲጽፍልዎት፣ “እርስዎ ደግሞ ያበዙታል። የሁሉም ቃል ምንጭ አማርኛ ይመስልዎታል፣ አማርኛ የበላይ ነው የሚለው ሥነ ልቦና ስለተጠናወተዎት። አንድ ጊዜ “ግሮሰሪ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ግሮ” እና “ሠሪ” ከሚሉት ሁለት የአማርኛ ቃላት ነው የመጣው ብለው ድርቅ ሲሉ ነበር። አሁን ደግሞ የሌለ ነገር አመጡ። አደብ ቢገዙ ይሻላል። እንዲህ ዓይነት ወለፈንዴ ከበዛ እኮ የአዕምሮ ጤንነትንም አጠያያቂ ያደርጋል፤”(https://www.facebook.com/fikre.tolossa accessed April 19, 2017፡፡)
ለዚህ የእርስዎ መልስ፣ “የማውቀውን ነገርኳችሁ፤ ብትፈልጉ ተቀበሉ፤ ባትፈልጉ ተውት፣ ለምን ትጨቀጭቁኛላችሁ?” ነው። ለምን አይጨቀጭቁዎትም! ለምሳሌ በዚህ አካሄድዎ ብለው ብለው የአሜሪካን የኢንግሊዝኛ የአገር ስም “አሪዞና” የተባለውን ወደ አማርኛ ይመልሳሉ ብለው ቢፈሩሳ!
ወደ ሌላ ጉዳይ ስንሄድ ከ2,850 ዓመት በፊት አክሱሚትን (በኋላ በስዎ አባባል ራምዘስ ተብሎ በግብፅ ላይ የነገሠውን) አማሮች ከኢትዮጵያ አስከ ግብፅ ሲከተሉት ከዚያም 350,000 የሚሆኑት እነዚህ አማሮች ከ1,850 ዓመት በኋላ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ላሊበላን አጅበው ነው ይላሉ። ራምዘስ ግን ዕድሜን ጠግቦ በ95 ዓመቱ አንደሞተ የግብፅ ሃይሮግልፍክስ ሲያረጋግጥ ይሀን ሁሉ ያላነሳው ለምን ይሆን? የግብፅ ታሪክ በሚያሳየው መሠረት ከሆነ በዓለም የታወቀውን “አቡ ስምበል” የተባለ ምኩራብ የገነባው ራምዘስ የ19ኛው የግብፅ ሥረወ መንግሥት ንጉሥ የቀዳማዊ ሴቲና የግብፅ ንግሥት ቱያ ልጅ የነበረ ሦስተኛው ፈርኦን ሆኖ ከ1292 እስከ 1186 ዓመተ ዓለም የኖረ መሆኑ በሐይሮግልፍክስ ተቀርጿል። (ትክክለኛውን ታሪክ ለመረዳት ዊልፍሬድ ሲ ግርግስ ዳግማዊ ራምሰስ ታላቁ ፈርኦንና ጊዜው የደንቨር ቤተ ወመዘክር ብሔራዊ ታሪክ ማተሚያ ቤት እ.ኤ.አ. 1985ን ይመልከቱ፡ በተጨማሪም ዛሂ ሐዋስ፣ የአቡ ስምበል ምስጢር፣ ዳግማዊ ራምዘስና የፀሐይ መውጫ ቤተ መቅደስ፣ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ማተሚያ ቤት እ.ኤ.አ. 2001ን ይዩ።)
አሁንም ወደ ሌላ ርዕስ ስንሸጋገር በዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ አባባል አንዲት “ሸምሸል” የተባለች መነኩሲትና ነቢይት በዓባይ ተፋሰስ ስትታጠብ በውኃው ላይ በነፃ የሚንሳፈፍ የወንድ አባላዘር ወደ ማህፀኗ ሠርጐ በመግባቱ የአማራና የኦሮሞ አባት የሆነውን “ዳሸት”ን ወለደች ይላሉ። በእንደዚህ አባባልዎ አማራና ኦሮሞ ሁሉ የ”ዲቃላ” (ማለት በኢንግሊዝኛ የ”ባስታርድ”) ልጆች ናቸው ብለው በ75 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የስድብ ውርጅብኝ ሲወነጭፉ ትንሽ እንኳ ዝግንን አይልዎትምን? አንድ የኢትዮጵያ ታሪክ መምህር የእርስዎን መጽሐፍ ጠቅሶ እንዲህ በማለት የሚያቀርበውን ተማሪ ከክፍል ወደ ክፍል በማሳለፍ ፋንታ በአርጩሜ ቢገሸልጠው ከመቅፅበት ቀርበው ይማጸኑለታልን? በአስማት ስለሚያምኑ “አዎን” ቢሉ አይገርመኝም!
እስቲ እግዜር ያሳያችሁ፤ ማንንም ጽንስ አልሚ ሐኪም ብንጠይቅ በድንገትና በአጋጣሚ በወንዝ ላይ ከሚንሳፈፍ አባለዘር ይቅርና፣ በአሁኑ ዘመን ሳይንሳዊ ዘዴዎች በልጽገው በሚገኙበት ጊዜ እንኳ ቢሆን፣ አንድን ሕፃን በብርጭቆና በብልቃጥ ለመፈልፈል እጅግ በጣም አስቸጋሪ መሆኑ ግልጽ ነው። የሰውን አባለዘር ምህንድስና በማካሄድ የሳይንስ ሊቃውንት ዓላማውን ከስኬት ለማድረስ ሲሞክሩ የሚያጋጥማቸውን በቀላሉ የማይበገሩ እንቅፋቶች ለመረዳት የሚቀጥሉትን ጥናቶች ማጤን ይጠቅማል። (ኪኤልደር፤ ኢቭ ሜኔዞ፣ የሰሐንና የብልቃጥ ፅንስ፣ ኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ማተሚያ ቤት እ.ኤ.አ. ፳፲)ን ይመልከቱ፡)
በዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው ከሆነ፣ አንድ ጥንታዊ በስም እስኤል የሚባል የኢትዮጵያ ንጉሥ ለ480 ዓመት ኖረ፡፡ በንጉሥነቱ ላይ ደግሞ ተደራቢ የዘር ምሕንድስና ጠቢብ ሆኖ በብውዝ ዲኤንኤ ዓረቦችንና የመካከለኛው ምሥራቅ የጦር ምርከኞች እስረኞችን በማዳቀል በአዝጋሚ ለውጥ ኢትዮጵያውያንን አስገኘ፤ ይህም ለኢትዮጵያውያን አሁን ያለንን የቆዳ ቀለምና ተክለ ሰውነት ሰጥቶናል ብለው ዱብ ዕዳ ታሪክ አፍልቀዋል። ሐበሻ የሚለው ቃልም ከዚሁ የመዳቀል ገጽታ የፈለቀ ነው ይላሉ፡፡ ሐበሻ በእርስዎ አባባል ‹‹አበሳ›› ከሚል ቃል የመነጨ ሲሆን፣ ከመከለስ ወይም ከመዳቀል የመጣ እንከን ያዘለ ክብረ ነክ መጠሪያ መሆኑን ይተርካሉ፡፡ ለአንድ የሳይንስ ጠቢብ በድሮ ጊዜ አንድን የተፈጥሮ ባሕሪይ ለመለየት፣ ከዚያም የተፈለገ የተፈጥሮ ባህሪ ለመስጠት፣ የዘር ምንጭን በማዳቀል ልዩ የሰው ባህሪያትን ማስያዝ አሰቸጋሪነቱ ብቻ ሳይሆን የሥነ ባህሪይው አሠራር ራሱ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በተፈለሰፈው የግሬገር ሜንዴል መላምት እስከ ተከሰተበት ጊዜ ድረስ ሒደቱ አይታወቅም ነበር፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አጥልቆ ለመረዳት የሚከተለውን ጥናት መመልከት ይጠቅማል፣ (ኤቭልን ፎክስ ኬለር፣ ምዕታዊው በራሔ የዘር ምንጭ ሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ማተሚያ ቤት እ.ኤ.አ. 2001ን ይመልከቱ፡፡) በነገራችን ላይ ዶ/ር ፍቅሬ እውነት ታሪክን የሚመራምሩ ቢሆኑ ኖሮ ከ1,687 ዓመታት በፊት ንጉሥ ኢዛና ይገዟቸው ከነበሩት ብሔሮች አንዱ “አበሳ” (ግዕዝ ውስጥ “ሸ” የለምና በዛሬ አባባል “አበሻ”) መሆኑን በአክሱም ሐውልት ላይ እንደከተቡት በተረዱት ነበር፡፡
ለመሆኑ የሰው ልጅ ለ480 ዓመታት ይኖራል ማለትስ አዕምሮን መሳት አይደለምን? በአሁኑ የመዋለድ ሳይንስ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ጊዜ እንኳ የሰው ልጅ 150 ዓመታት ለመኖሩ የተረጋገጠ ማስረጃ ስለሌለ፣ ለማሳያ ሲሉ የሳይንስ ሊቃውንት 150 ዓመታትን የመጨረሻ የላይኛ ገደብ አድርገው ወስነውታል፡፡ እዚህ ላይ ዶ/ር ፍቅሬ ከብሉይ ኪዳን ጠቅሰው የማቱሳላን 969 ዓመት መኖር ያነሱ ይሆናል፡፡ያ ግን ሃይማኖት እንጂ ሳይንሳዊ የሰው ልጅ ዕድሜ መጠን አይደለም፡፡ (ስለዚህ ጉዳይ ጥናት ለማወቅ ከፈለጉ የሚከተሉትን ማስረጃ ይመልከቱ፡፡ ሮበርት ቭ፣ ካይል፣ ጆን ሲ ካቫና፣ የሰው ልጅ ታዳጊ ባሕሪይና ዕድሜ ዕይታ፣ ወድስዎርዝ አታሚ እ.ኤ.አ. 2015)
ዶ/ር ፍቅሬ የመጽሐፋቸውን ሥርጭት ተከትሎ ባላቸው ግምት በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል የጠነከረ የመቀራረብ ዝንባሌን እያመጣ ነው ብለው እጅጉን በተግባራቸው ረክተዋል፡፡ የደቀ መዛሙርቶቻቸውንም ቀልብ አጥብቀው ለመሳብ የቻሉበት ምክንያት አጻጻፋቸው ላይ ላዩን ሲያዩት ከጥላቻ ፍቅርን፣ ከበቀል ርኅራኄን፣ ከልዩነት አንድነትን፣ ከመሻኮት መቻቻልን አንኳር ዓላማ አስመስለው በማር ለውሰው ስለሚያቀርቡ ነው፡፡ በተጻራሪው ግን መጽሐፉ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ አንዱን ከፍ አንዱን ዝቅ የሚያደርግ የደባ ጥንስስ ነው። ለምሳሌ ትግሬዎች (“ተጋሩ” ወይም “ተጋሩዎች” ይሏቸዋል) ከክርስቶስ ልደት በፊት በ330 ዓመተ ዓለም አካባቢ ከጥንቷ ባቢሎን (ማለት ከዛሬዋ ኢራቅ) እና ከሶሪያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ናቸው ብለው ጽፈዋል፡፡ ከዚያም አልፈው የአክሱም ሥልጣኔ እምብርት ትግራይ ሆኖ ሳለ አክሱምን የገነቡት አማሮች ናቸው ብለው ወስነው ትግርኛ ተናጋሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀዬው የለፋበትንና ያካበተውን የሥልጣኔ ሚና ደፍረው ክደዋል። እንዲሁም የሮሐ ተደናቂ አብያተ ክርስቲያናት የተሠሩት በዛጉዌ ሥረወ መንግሥት ዘመን በጥንታዊ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገዛዝ ፈር ቀዳጆች በአገዎች መሆኑ እየታወቀ ሳለ፣ ንጉሥ ላሊበላን ብዙ ቦታ ሲጠቅሱ የአገው ሕዝብን ስም ለምን ለጥልመት እንደዳረጉ አይታወቅም፡፡
ባለፉት ጥቂት ምዕት ዓመታት የነበረው ክፉው የፊዩዳል አገዛዝ ቁንጮዎች ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ ከትግራይ፣ ከጉራጌና ከሌሎችም ብሔረ ሰቦች የተውጣጡ አማርኛ ተናጋሪ የገዥ መደብ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህም በተሳሳተ ግምት አማራ የተባለ ሁሉ ደሃውን የአማራ ገበሬ ሳይቀር ጨቋኝ ገዥ አስመስሎታል። ዶ/ር ፍቅሬ ግን ከዚህ ዘለው የኦሮሞን ሕዝብ ያመሰገኑ አስመስለው ኦሮሞዎች ኢትዮጵያን ላለፉት 7,000 ዓመታት ገዝተዋታል ሲሉ በባላባታዊው ሥርዓት ዘመን የተዘረጋውና በአገራችን ገበሬዎች ላይ የተጫነው ጭቆናና ግፍ አመንጪ ናቸው ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው። ይኼማ ከሆነ ዘንዳ ለምን “አፋን ኦሮሞ” የኦፊሲዬል ቋንቋ አልተደረገም? ለምንስ ኦሮሞ ያልሆነው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ልጆቹን በኦሮሞ ስም ለመሰየም አልተሯሯጠም? ለምን አዲግራት፣ ዛላንበሳ፣ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ አንኮበር፣ ደብረ ሲናና ፍኖተ ሰላም በኦሮሚኛ ስም አልተተኩም?
ይህን ስንል ግን እዚህ ላይ አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ። የአማራ ብሔረ ሰብ የኢትዮጵያ ጨቋኝ ገዥ ነበረ ማለት ትልቅ ስህተት ነው። ነፍጠኛም ሲባል አማራ ብቻ አስመስለው የሚቀርቡ ሞልተዋል። ይኽም ሌላው ትልቅ ስህተት ነው። ነፍጠኛ የሚል ቃል ከነፍጥ የመጣ ነው። ነፍጥ ማለት ደግሞ ጠመንጃ ማለት ሲሆን፣ ነፍጠኛ ማለት “ጠመንጃ ያዥ” ወይም “ወታደር” ማለት ነው። የአገራችን ታሪክ እንደሚያሳየው የጥንቱ የኢትዮጵያ ወታደር ከብዙው ብሔረሰብ የተውጣጣ ሲሆን፣ ቋሚ ደመወዝ አልነበረውም። በዚያም ምክንያት በደቡብ ኢትዮጵያ ከርዕስቱ ሲሶው ተነስቶ ለአገሩ ባላባት ከተሰጠ በኋላ፣ የቀረው የመንግሥት መሬት ተብሎ የተወሰነው ለደመወዝ አልባው ወታደር ወይም ለ“ነፍጠኛ”ው ይሰጥ ነበር። እዚህ ላይ ግን ልብ መደረግ ያለበት ወታደሩ አማራ ብቻ አልነበረም። ኦሮሞም፣ ጉራጌም፣ ትግሬና የሌላም ብሔር ወገን ነበረ። ከዚህ ሁሉ ስህተት ዘሎ ግን የጭቆናውን ኃላፊነት በኦሮሞ ላይ መጫን ሁለት ስህተቶች አንድ ትክክል ውጤት ያመነጫሉ የሚለውን የተሳሳተ አመክንዮ መከተል ይሆናል።
ከዚህ በላይ በተዘረዘሩት አባባሎች ሁሉ ዶ/ር ፍቅሬ እውነትን በልብ ወለድ፣ ታሪክን በሃይማኖት፣ እውነታን በተረት ለመተካት ሞክረዋል፡፡ ይህን በማድረጋቸውም የዛሬ ዘመን ሰዎች ከአወዛጋቢ ሁኔታቸውና ከብቸኝነታቸው በስሜት ገለል ብለው፣ ምንም ያህል ተድላ ደስታ ቢያገኙበትም ቅሉ ሒደቱ አስፈሪ የታሪክ አተላ መተው ሳይታለም የተፈታ ነው። ምክንያቱም ይህ ክስተት ለእውነተኛ የኢትዮጵያ ምሁራን ለማየት እንኳ የሚዘገንን መራራ መፃፃ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለወጣቶቻችን ለመቋቋም እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ውዥንብር የሚፈጥር ሚና አለው። በእንደሻ በመሄድ ብቻ፣ ዶክተሩ ከስሜታዊነት የፀዳ እውነትን ባለማቅረብ ብቻ ስንቶችን ግራ ማጋባታቸውና በሁኔታዎች በመገፍተራቸው መፍትሔ ያግኙ አያግኙ ምንም አስደሳችና አስታማሚ ይሁኑ፣ ድርጊቱ፣ እንደወረርሽኝ በመላዋ ኢትዮጵያና በዳያስፖራ በገፍ እየተሰራጨ ስለሆነ ሒደቱን አለመግታት አደገኛና አሳሳች አርዓያን መከተል ይሆናል፡፡
ይህ ሁሉ እያለ ዶ/ር ፍቅሬ ከልብም ሆነ ለይስሙላ ፍላጎቴ የልዩነትን ተፅዕኖ ለመፃረር፤ ጥላቻን ለማስወገድ፤ ምሕረትን፣ መቻቻልንና ርኅራኄን ለማጎልበት ነው የመጽሐፌ አንኳር ይዘት፣ ብለው በሸነከፉት አሳሳች ወጥመድ ብዙ ተከታዮች ስላገኙ መጽሐፌ ነፍስን የመፈወስ ተልዕኮ አለው እስከማለት ደረሱ። ሥራቸው የማንነት ውዝግብን አንደፈታና አለመግባባትን እንዳስወገደ ለማሳመን ይሞክራሉ። ዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፋቸው የታሪክ መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን ሰዎችን ከመጥፎ ነገርና ከተንኮል ጠብቆ ሰላምንና ፍቅርን የማውረድ ተልዕኮ ያለው ነው ብለው ያምናሉ። በዚሁም ምክንያት ድርሰታቸው በሳቸውም ግምት ቢሆን በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ዓይነት በደብተራዎች ከሚዘጋጁት ከ“ልሳነ ሰብ” ና ከ“ሐጹረ መስቀል” ቡድን ይመደባል፡፡ ሰላምና ፍቅርን በሰፊው በመዘርጋት ነፍሳቸውን ይጠብቃል ስለተባለም ከኅላዌ ሕይወት ጉዞ ድርሳን ከ“ልፋፈ ጽድቅ” ወገን ይቆጠራል፡፡
በዶ/ር ፍቅሬ ግምትና ተስፋ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ራሱን ከአሉታዊ ክስተቶች ለመጠበቅ ጽሑፋቸውን በደብተራዎች አሸንክታብ መልክ አሠርቶ በአንገቱ ላይ ቢያጠልቅ እጅግ ደስ እንደሚላቸው ለመገመት አያዳግትም። የመጽሐፉን በሰፊው መሸጥ ስንመለከት ምክንያቱ ግልጽ ሆኖ እናገኘዋለን። የዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ ከቁጥር በላይ የሆኑ ግድፈቶች እንዳሉት የማያውቅ አንድም የተማረ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፡፡ ግን ሕይወታችን በተቃወሰችበትና አንድነታችን ፈተና ውስጥ በገባችበት በዛሬ ጊዜ ግድፈቱን ትተን የሚያቀራርበውን የዕርቅ መልዕክት ብቻ እንከተል፤ መጽሐፉ እውነት ሳይሆን ተረት ተረት ቢሆንም ችለን እንለፈው የሚሉ አሉ፡፡ ይኼ ግን በእኔ ግምት ትልቅ ስህተት ነው።
የዶ/ር ፍቅሬ ሥራ ከልዊስ ካሮል የአሊስ ጀብድ በአስገራሚ ዓለም (1865) እና ከጃኪ ሮሊንግ ሐሪ ፓተር ጋር ማኅህበርተኛ ነው፡፡ ጸሐፊው ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ለሚቀጥለው መጽሐፋቸው እየቆጠቡ እንደሆነ ከወዲሁ ቃል ገብተዋል። ምንም እንኳ በ145 ዓመታት ጊዜ ቢራራቁም፣ ሁለቱም ተረት ተረት ናቸውና ቀጣዩ የዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ ከልዊስ ካሮል ውስጡን የሚያሳየው መስተዋት ጋር መመሳሰሉ አይቀሬ ነው።
ባጭሩና በቀላሉ ለማስቀመጥ የዶ/ር ፍቅሬ ትረካዎች ለመምህራቸው ለመሪራስና ለራሳቸው ብቻ የተገለጡ የራዕይ ትሩፋት መሆናቸው የማያጠራጥር ነው፡፡ ጽሑፉ ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ ቅዤትና ፈጠራ ሲሆን፣ የተረት አባቱ ዶር ፍቅሬ “ተረት ተረት” ሲሉ “የመሠረት” ብለው ለመቀበል የተዘጋጁ ብዙ ግለ ሰቦች እንዳሉ የመጽሐፋቸው በገፍ መሸጥ ዋና ምልክት ነው፡፡
ግን አንድ ማስጠንቀቂያ፤ ታሪክ ከተጣመመ እንደገና ማቃናት አስቸጋሪ ነው፡፡ እዚህ ላይ በብርቱ የሚያሳስብ ነገር ቢኖር ዶ/ር ፍቅሬ በዚህ መንገድ በሳተ የተረት ታሪክ በርካታ ተከታዮችን ማፍራታቸው ነው። እንዲያውም አዲስ ጴንጤቆስጤ በአድማስ ላይ እያንዣበበ ነው፡፡ ባለፉት ግማሽ ምዕት ዓመታት የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ ካጠቃው እንግዳ ባይታወርነት የተነሳ፣ አንዳንድ ግለሰቦች ደራሲውን አዲስ የአምልኮ ጎራ ለማድረግ ምንም አልቀራቸውም። እንደ ጅም ጆንስ፣ ማርሻል አኘል ኋይት፣ ዴቪድ ኮረሽ፣ ሱን ሚዩንግ ሙን፣ ከተራ ሰው እስከ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች በደመነፍስ በመንቀሳቀስ የማሃሬሹን ትዕዛዛት ያለምንም ጥያቄ የሚፈጽሙትን ተከታዮች ከማግኘት የሚያግዳቸው ነገር ያለ አይመስልም፡፡ ዶ/ር ፍቅሬም ቢሆኑ የመሀሬሽነት ሚናውን ለመጫወት ካሁኑ ዳር ዳር ያላቸው ይመስላል። በ“ፌስቡካቸው” ላይ የ“ክርስቶሎጂ”ን ክርክር እንዲህ ሲሉ ከፍተዋል፤
ፍቅሬ ቶሎሳ “ስሙ እየሱስ ነው። ኢየሱስ ያሉት ኢትዮጵያ የሚኖሩ አይሁድ ናቸው። ኢ ያሉት መድኃኒትነቱን ሲክዱ ነው። የሱስ ያሉት ሱሰኛ ለማለት ነው። ትክክሉ እየሱስ ነው፤”
[እንደገና] ፍቅሬ ቶሎሳ ኢየሱስ (የማያድን) የሱስ (ባለሱስ) ስለሚያደርገው እየሱስ (የሚያድን) የሚለውን እንድንጠቀም ግድ ይላል።
ይህ አዝማሚያ ወዴት ሊያስኬድ? በኢትዮጵያ የተለመደውን የመሲሁን ስም መሸርሸር ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሯ ትሄዳለችን ማመልከት አይመስልምን? የዚህ ሁኔታ መከሰት የማይታሰብ አድርጋችሁ አትቁጠሩት፡፡ እንዲያውም ለዚህ ምሳሌ ሊሆን የሚችል በኢትዮጵያ ታሪክ የቀደመ ክስተት አለ፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን ዘክርስቶስ የሚባል ሰው መንፈሳዊ የዘር ምንጭ እንዳለው በመለፈፍ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎ ሲነሳ፣ ከተዋሕዶ ኦርቶዶክስ፣ ከካቶሊክ፣ እንዲሁም ከእስልምና ሃይማኖቶች ተከታዮች ክፉኛ መሻኮት የተነሳ ግራ የተጋባው ብዙ ሰው ተከታዩ ለመሆን ቻለ፡፡ እሱም በሥርዓት ተደራጅቶ ከኢትዮጵያ ተዋሕዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በመለየት የራሱን ጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት ሾመ፡፡ ይህን በማድረጉ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ዘድንግል በፍትሐ ነገሥት በተደነገገው መሠረት በድንጋይ ተወግሮ እንዲገደል አዘው ሕግ አስፈጻሚዎቹና የአካባቢው ሕዝብ ወደ ጉድጓድ ወርውረው የድንጋይ እሩምታ ሲያወርዱበት ሕይወቱ ከማለፉ በፊት ድምፁን ከፍ አድርጐ “ምን አለ ጋሼንም ሰቀላችሁት!” እያለ ተሰናበተ!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው pmilkias@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
