በተክለ ብርሃን ገብረ ሚካኤል
የኢሕአዴግ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ የግንባሩ አባላትና ደጋፊዎች መንግሥት ግልጽ የሆነ የኢኮኖሚ ልማት እንዳለው አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡ መንግሥት ከመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ተነስቶ፣ በመዋቅራዊ ማስተካከያ አልፎ፣ የድህነት ቅነሳ መርህ ያካተተ የዕድገትና የትራንስፎሜሽን ፕሮግራም እያካሄደ በመሆኑ፣ በመሠረቱ የልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ሞዴል እየተከተለ መሆኑን አበክረው ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡
በዚህ የልማት ሞዴልም አያሌ የሚያኮሩ ውጤቶች እንደተገኙ ይገልጻሉ፡፡ በተለይ በመሠረተ ልማት ግንባታ የተመዘገቡትን ስኬቶች ይደረድራሉ፡፡ እውነትም በኃይል ማመንጫ፣ በባቡር፣ በመንገድ፣ በአውሮፕላን ማረፊያ፣ በሕንፃ፣ በቴሌ፣ በትምህርት ቤት፣ በጤና ጣቢያ ግንባታና በሌሎች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች የታዩት የልማት ሥራዎች የሚካዱ አይደሉም፡፡ ይኼንንም መሠረት አድርገው በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የልማት እንቅስቃሴ እንደተካሄደ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ፣ ይከራከራሉ፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን የልማት ሥራ ውጤቶችን እየደረደሩ፣ የአገሪቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) በተከታታይ በአሥራ አንድ በመቶ ያህል ማደጉን ይነግሩናል፡፡ እነ ዓለም ባንክና አይኤምኤፍ የአሥራ አንድ በመቶ የዕድገት አኃዙን ባይቀበሉትም፣ ኢኮኖሚው በከፍተኛ መጠን ማደጉን አይክዱም፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በዓለም ፈጣን ዕድገት ካሳዩት አገሮች ተርታ ይመድቡታል፡፡ በየደረጃው አያሌ የትምህርት ተቋማት ተገንብተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ከሰላሳ በላይ እየሄደ ነው፡፡ በርካታ የጤና ጣቢያዎች ተከፍተዋል፡፡
እንደ መሠረተ ልማት ግንባታው ባይሆንም በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በማዕድን ዘርፎች የማይናቁ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውም ተገልጿል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የልማት ሞዴል አለው የሚሉት ወገኖች ይኼን ይበሉ እንጂ፣ የለውም የሚሉት ምሁራን ክርክርም እንዲህ በቀላሉ የሚጣጣል ሆኖ አልተገኘም፡፡ መንግሥት የልማት ሞዴል የለውም፣ ልማቱንም የሚያካሂደው ‹‹በጨበጣ›› ነው የሚሉት ወገኖች ክርክራቸውን የሚመሠርቱት በቀላል የማክሮ ኢኮኖሚ ፅንሰ ሐሳብ ላይ ነው፡፡ ሀብት የሚፈጠረው መሬትን፣ የሰው ኃይልንና ካፒታልን በማቀናጀት ቢሆንም፣ ሕያው የሀብት ምንጭ የሰው ኃይል በመሆኑ፣ አስተማማኝ የኢኮኖሚ ልማት ሞዴል በሰው ኃይል ትምህርትና ሥልጠና ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ ይኼም ብቻ አይደለም፡፡ ትምህርትና ሥልጠና ዓለም አቀፋዊ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ መሆን እንደሚገባው አበክረው ይገልጻሉ፡፡ መሬትን በተመለከተ የተፈጥሮ ሀብት እንደመሆኑ፣ ለቤት ሠሪዎችና አምራቾች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል እንዳለበት ያምናሉ (ከሞላ ጎደል በነፃ)፡፡ ካፒታል ላይ ያላቸውም አመለካከት በመሠረታዊ መርህ ላይ የተመሠረተ ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ካፒታል ማለት በአብዛኛው የባንክ ብድርና ይኼም ሊያስገኝ የሚችለው የውጭ ምንዛሪ ማለት ነው፡፡ እርግጥ በዕቁብና በሌሎች ዘዴዎች የሚቆጠብ ገንዘብ፣ ከሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ድርሻ ተጣምሮ በካፒታልነት ሥራ ላይ ሊውል እንደሚችል ይታወቃል፡፡ የባንክ ብድር በአዋጭነት መሥፈርቶች ላይ ተመሥርቶ ካልተሰጠ፣ ውጤቱ ኪሳራ ብቻ ሳይሆን የዋጋ ንረትም መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡
እዚህ ላይ የኢሕአዴግ መንግሥት የልማት ሞዴል የለውም፣ አለው ከተባለም የተሳሳተ ነው የሚሉትን ወገኖች ክርክር በግልጽ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ የትምህርት ቤት ሕንፃዎች ተገነቡ እንጂ፣ የሚሰጠው የትምህትና የሥልጠና ጥራት ደረጃ አሽቆልቁሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የኢሕአዴግ የልማት ሞዴል የትምህርት ጥራትን በመሠረታዊ ግብዓትነት አልተቀበለውም፡፡ በሌላ በኩል መሬት ከሞላ ጎደል በነፃ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል ሲገባው፣ እንዲያውም መንግሥት መሬትን ዋና የሀብት ምንጭ ነው በሚል የተሳሳተ እሳቤ፣ አንዷን ካሬ ሜትር ከሦስት መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር በላይ እየሸጠ ነው፡፡ በዚህ አሠራር እንደ ሀብት ምንጭ የተወሰደው የሠለጠነ የሰው ኃይል ሳይሆን መሬት መሆኑ ነው፡፡ ይኼ ስህተት ነው ይላሉ ተቃዋሚዎቹ፡፡ በሌላ በኩል የባንክ ብድርን በተመለከተ በአብዛኛው ‹‹በበላይ ትዕዛዝ›› ስለሚሰጥ፣ የአዋጭነት መሥፈርቶች አይከበሩም፡፡ በመሆኑም የባንክ ብድር ከምርት ዕድገት ይልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው ለዋጋ ንረት መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
የትኛው ወግ ነው ትክክል?
አብዛኛው የኢኮኖሚክስ እውቀት የሌለው የኅብረተሰብ ክፍል በቴሌቪዥንና በዓይኑ በሚያያቸው መሠረተ ልማቶችና ሕንፃዎች መደነቁ አይቀርም፡፡ ልማትና ዕድገትም ይኼ ቢመስለው የሚያስገርም አይደለም፡፡ ግን ከመሠረተ ልማቶቹ ስንቶቹ እንዳከሰሩና እንደ ከሸፉ የሚያውቀው ሕዝብ ምን ያህሉ ነው? የጠቅላላ ኢንቨስትመንት አፈጻጸም ደረጃ ከአርባ በመቶ እንደማይበልጥ የሚገነዘበው ሰው ስንት ነው? በደንብ ባልተጠኑ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታና እሴት በማይፈጥሩ ሙሰኞች በሚሠሩ ሕንፃዎች ምክንያት በተፈጠረው የዋጋ ንረት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች እየተሰቃዩ መሆኑን የሚገነዘበው ሕዝብ ስንት ይሆናል? በአጭሩ መሬት የሀብት ምንጭ የሆነበትና የባንክ ብድር በትዕዛዝ የሚሰጥበት የልማት ሥልት የልማታዊ መንግሥት ሞዴል ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲሁም ሰብዓዊ ልማትን (የሰው ኃይል ልማትን) ማዕከል ያላደረገ የልማት ሞዴል ሊኖር አይችልም፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የልማት ሥልት የመሬትን ዋጋ ያላግባብ ሰማይ የሰቀለ፣ በአንፃሩ እውቀትን ዋጋ ቢስ ያደረገና የባንክ ብድርን (ዋናውን የካፒታል ምንጭን) ለአዋጭነት መሥፈርት ሳይሆን ለበላይ ትዕዛዝ ተገዢ ያደረገ በመሆኑ፣ በማንኛውም ዓይነት የልማት ሞዴል ሊመደብና ሊፈረጅ የሚችል አይመስለኝም፡፡
ይልቁኑም በመዋቅራዊ ደረጃ ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን (ይህም የሙስና ዓይነት ነው) የሚያራምድ ሞዴል ነው ማለቱ ይቀላል፡፡ ሌላው የኢሕአዴግ የልማት ሞዴል (ሞዴል ከተባለ) ሊገመገምበት የሚችለው መሥፈርት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ተመሥርቶ ዘመናዊ ሥልጣኔን ለማፍጠን በቀየሰው ሥልት ነው፡፡ ለዚህ በዋናነት ተቀባይነት ያገኘው ሥልት በግሉ ዘርፍ፣ በመንግሥት ኢንቨስትመንት ኩባንያና በቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ቅንጅት የሚካሄድ የጋራ ልማት ማኅበር የኢንቨስትመንትና የምርት እንቅስቃሴ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የግሉን የኢኮኖሚ ክፍል ከማበረታታት ይልቅ እያቆረቆዘው በመሆኑ፣ በዚህ መሥፈርት መሠረትም የኢኮኖሚው አፈጻጸም ደካማ ነው፡፡ ወደ አገር የገባው ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመት ከሚጠበቀው በታች ከመሆኑም በላይ፣ የራስን ብሔራዊ ጥቅም በማስቀደም ላይ የተመሠረተ ስለሆነ የሚፈለገውን ፈጣን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሊያስገኝ አልተቻለም፡፡
በአጠቃላይ የኢሕአዴግ መንግሥት የኢኮኖሚ ልማት ሞዴል (ሞዴል አለው ከተባለ) የልማታዊ መንግሥት ስትራቴጂ ተብሎ ይሰየም እንጂ፣ ከማንኛውም የልማት ሞዴል ባፈነገጠ ሁኔታ የሚከተሉትን ዓበይት ባህሪያት ያካተተ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
- በግል፣ በቤተሰብ፣ በማኅበርና በድርጅት የሚካሄድ ሥራና የሚደረግ ጥረት ሳይሆን፣ የገንዘብና የሀብት ምንጭ የሆኑት የፖለቲካ ሥልጣን፣ ቡድናዊ ግንኙነቶች፣ መሬትና በትዕዛዝ የሚሰጡ የባንክ ብድሮች ናቸው፡፡
- የመንግሥትና የፓርቲ የኢኮኖሚ ድርጅቶች በከፊል ሞኖፖል ቅርፅ (ኦሊጎፖሊ) ኢኮኖሚውን ስለተቆጣጠሩት፣ የግሉ የኢኮኖሚ ክፍል ዋናው የልማትና ዕድገት ሞተር መሆን ሲገባው በእነዚህ ጥገኝነት ሥር እየቀረቆዘ ነው፡፡
- እውቀት ከሞላ ጎደል ዋጋ ቢስ ሆኗል፡፡
- ሙስና ተቋማዊ ተደርጓል፡፡
- የይስሙላ ዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ልማትን እያጋነኑ ለማቅረብ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ነግሷል፡፡
ከላይ እንደተጠቆመው፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ልማት የሚለው በአብዛኛው ‹‹በጨበጣ›› የሚገነባቸውን መሠረተ ልማቶች ናቸው፡፡ ይኼ በልማት ኢኮኖሚክስ ቋሚ ኢንቨስትመንት የሚባለው ነው፡፡ የዚህ መጠን ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አርባ በመቶ መድረሱን መንግሥት ተናግሯል፡፡ ይህ መቶኛ ድርሻ በጣም ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ኢንቨስትመንቱ ለጠቅላላ ፍጆታ ማደግ ምን ያህል አስተዋጽኦ አድርጓል? ኢንቨስትመንት ለጠቅላላ ፍጆታ ዕድገት አስተዋጽኦ የማያደርግ ከሆነ፣ ጠቃሚነቱ ዝቅተኛ እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ የመስኖ ግድብ ለምግብ እህል ምርት ዕድገት አስተዋኦ የማያደርግ ከሆነ፣ ጠቃሚነት የለውም፡፡ ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያውያን የነፍስ ወከፍ ፍጆታ እየቀነሰ እንጂ እየጨመረ አልሄደም፡፡ የሥጋ፣ የወተት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ በአጠቃላይም የምግብ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ እንደቀነሰ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ በተመሳሳይ በመኖሪያ ቤትና በትራንስፖርት በኩል ያለው ከፍተኛ ዕጥረትና ችግር በሚገባ የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ ይኼ ሁሉ ኢንቨስትመንት የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ካላሻሻለ ጥቅሙ ምንድነው? እስኪ ችግሩን ይበልጥ ለመረዳት የሚከተለውን ቀላል የማክሮ ኢኮኖሚ ቀመር እንጠቀም፡፡ ጠቅላላ ገቢ (ጂዲፒ) = ጠቅላላ ፍጆታ + ጠቅላላ ኢንቨስትመንት + (ኤክስፖርት ሲቀነስ ኢምፓርት)፡፡
የኢሕአዴግ መንግሥት ብዙ መሠረተ ልማቶችን ስለገነባ ጠቅላላ ኢንቨስትመንት ያደገ ሊመስለን ይችላል፡፡ የተገነቡትን የኃይል ማመንጫዎች፣ የትምህርት ቤት ሕንፃዎች፣ መንገዶች፣ ወዘተ ስናይ፣ ብዙ ሊመስሉን ይችላሉ፡፡ ግን ይኼ ዕይታችን የሚፈጥረው የተጋነነ የግንዛቤ ትርዒት ሊሆን እንደሚችል መርሳት የለብንም (ኦፕቲካል ኢሉዥን)፡፡ በሌላ በኩል ጠቅላላ ፍጆታ በጠቅላላ መጠኑ ማደጉን መካድ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የሕዝብ ብዛት አድጓልና፡፡ ይሁንና የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ስለቀነሰ የጠቅላላ ፍጆታ ዕድገት ከሕዝብ ብዛት ዕድገት በታች መሆኑን እንረዳለን (ማለትም ከሦስት በመቶ በታች)፡፡ ኢምፖርት ኤክስፖርትን በከፍተኛ መጠን ስለሚበልጥ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርትን ይቀንሰዋል፡፡ እንግዲህ ከላይ ከተመለከተው ቀመር በከፍተኛ መጠን እንዳደገ በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ኢንቨስትመንት (መሠረተ ልማት) ነው፡፡ ግን ይኼ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የነፍስ ወከፍ ፍጆታን ሊያሳድግ አልቻለም፡፡ ለምን? ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንደኛው ኢንቨስትመንት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ነው ከአርባ በመቶ አይበልጥም፡፡ ሁለተኛ ምርታማነቱ አነስተኛ ነው፡፡
ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) በዓመት በአሥራ አንድ በመቶ ሊያድግ ይችላል? የጠቅላላ አገር ውስጥ ምርት ስልሳ በመቶ ገደማ የሆነው ጠቅላላ ፍጆታ ያደገው ከሕዝብ ዕድገት በታች ከሆነ፣ እንዲሁም የጂዲፒው አርባ በመቶ ያህል የሆነው ኢንቨስትመንት አፈጻጸምና ምርታማነት ዝቅተኛ ከሆነ፣ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት እንዴት ነው በአሥራ አንድ በመቶ ሊያድግ የቻለው? የኢሕአዴግ መንግሥት ይህን ውጤት ሊያስገኝ የሚችል የኢኮኖሚ ልማት ሞዴል እንደሌለው በግልጽ መገንዘብ ይቻላል!
ማጠቃለያ
አስተማማኙ የልማት ሞዴል በሚከተሉት ወሳኝ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ጥራት ባለው ትምህርትና ሥልጠና ላይ የተመሠረተ ሰብዓዊ (የሰው ኃይል) ልማት፣ ፍትሐዊ የመሬት ክፍፍል፣ ከአድልኦ ነፃ የሆነና በታወቁ መሥፈርቶች ላይ የተመረኮዘ የባንክ ብድር አሰጣጥ ሥርዓት፣ በግሉ የኢኮኖሚ ክፍል፣ በመንግሥት የኢንቨስትመንት ኩባንያና በቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ቅንጅት የሚካሄድ የጋራ ልማት ማኅበር፣ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ መዋቅርና ማዕቀፍ ደግሞ የሚከተሉት ዓበይት ባህሪያት ያካተተ ይሆናል፣ የነፃ ገበያና የነፃ ውድድር ካፒታሊስት ሥርዓት (ፍትሐዊ ካፒታሊዝም) ለእውቀት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጥበት ሥርዓት፣ የፖለቲካ ሥልጣን የሀብት ማግኛ መሣሪያ ያልሆነበት ዓውድ፣ መሬት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈልበትና ዋና የሀብት ምንጭ ያልሆነበት የኢኮኖሚ ማዕቀፍ፣
የመንግሥት ዋና የኢኮኖሚ ተግባር የግል የኢኮኖሚ ክፍሉን ማበረታታት የሆነበት ሥርዓት፣ ማንም ሰው ተመጣጣኝ እሴት ሳይፈጥር ገንዘብ የማያገኝበትና ሙስና ከሞላ ጎደል የጠፋበት ሥርዓት፡፡
እነዚህ ሁሉ በኢሕአዴግ መንግሥት ‹‹የልማት ሞዴል›› ውስጥ የሌሉ ስለሆኑ፣ እንደገና መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ ባለመኖራቸውም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የተፈጠሩት ችግሮች እጅግ በርካታ ሆነዋል፡፡ የዋጋ ንረት ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል፡፡ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የገበያ ዋጋ ከሰላሳ እጥፍ በላይ ንሯል፡፡ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን በ93 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተባባሰ ነው፡፡ የሸቀጥ ንግድ ጉድለቱ እየሰፋ ሄዷል፡፡ በአንፃሩ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የኤክስፖርት ድርሻ ከመጨመር ይልቅ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ የወጣቶች የሥራ አጥነት ምጣኔ ከስልሳ በመቶ አያንስም፡፡ የውጭ እዳ ጫና ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደደረሰ ተዘግቧል፡፡ በዚህ ላይ የምግብ፣ የመኖሪያ ቤትና የትራንስፖርት እጥረትና ችግር ሕዝቡን ክፉኛ እያማረረ ነው፡፡ ሙስና የሥርዓቱ ዓይነተኛ መለያ ሆኗል፡፡ የገቢና የሀብት ልዩነቱ ጣሪያ ነክቷል፡፡ የሙሰኞች ሞራላዊ ዝቅጠት በሕዝቡ ግብረ ገባዊ ሥነ ምግባር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፡፡
ለምሳሌ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ በተሠሩት ትልልቅ ሕንፃዎች (ከአራት ፎቆች በላይ ወደ አሥራ አምስት ሺሕ ያህል ይገመታሉ)) ከስድስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ከሚገመተው የአዲስ አበባ ሕዝብ ተጠቃሚዎቹ (ከእነ ቤተሰቦቻቸው) ከ75 ሺሕ አይበልጡም፡፡ አብዛኛዎቹ ባለመኪናዎችም እነሱና መሰሎቻቸው ናቸው፡፡ ገንዘቡን ያገኙት በእሴት ፈጠራ ሒደት አልፈው ስላልሆነ፣ የኅብረተሰቡን ሞራል በሚነካ ሁኔታ ሲያባክኑት ይታያሉ፡፡ ባለመኪኖችም በሕዝብ ላይ አቧራና ጢስ ሲያቦኑ፣ አየር ሲበክሉና በመኪና አደጋ ሕይወት ሲቀጥፉ ነው የሚውሉት! እሴት ሳይፈጠር ሚሊዮነር የሆነ በዝባዥ መደብ ተፈጥሯል፡፡ ሰላም!፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
