Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

ነጠብጣቡን ማገናኘት... ቋጥኙ ውስጥ ፈረሱ መኖሩን እንዴት አወቁ?

$
0
0

በእስክንድር ከበደ

እ.ኤ.አ በጁን 24 ቀን 1812 የፈረንሣዩ ታላቁ ናፖሊዮን 610,000 ወታደሮችን ይዞ ሩሲያን ለመውጋት ወደ ሞስኮ ሲያመራ ወቅቱ በጋ ነበር፡፡ የታላቁ ናፖሊዮን ጦር ሞስኮ ከመድረሱ በፊት የሩሲያውያኑን ጦር ወራሪው ጠላት እንዳይጠቀምባቸው ሰብሎቻቸውንና መንደሮቻቸውን አጋይተው አፈገፈጉ፡፡ ናፖሊዮን ከ500 ሺሕ በላይ ወታደሮቹ አልቀው ወደ 100 ሺሕ ቀሩ፡፡ ቀሪዎቹም ከሞስኮ ሲያፈገፍጉ አሰቃቂ እልቂት ገጠማቸው፡፡ ፈረንሣዮች ለሽንፈታቸው በሩሲያ አየር ንብረት አሳበቡ፡፡ ዳኒስ ዴቪዶቭ እ.ኤ.አ በ1835 ባሳተሙት መጣጥፍ  “Was it frost who devastated the French Army in 1812?" (በ1812 ዓ.ም የፈረንሣይ ጦርን ያሸነፈው የሩሲያ አመዳይ (ውርጭ) ይሆን?) ብሎ ይጠይቃል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግል ከሚተርኩ በርካታ የጥበብ ሥራዎች አንዱ እ.ኤ.አ በ1992 የተሠራው ‹‹ሳራፊና›› የተሰኘው ፊልም ይጠቀሳል፡፡ ይህ ፊልም የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግል በአፓርታይድ ዘመን የሕዝቡን ያልተነገረ ትግል ያስቃኛል፡፡ ያልተነገረውን የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ትግል በጨረፍታ የሚስቃኘን ይህ ፊልም በታሪክ የመማሪያ መጻሕፍት አቀራረብ መጠናት ያለበት መሆኑን ይጠቁመናል፡፡

ፊልሙ ውስጥ የምናገኛት የታሪክ መምህርቷ ገናናው ናፖሊዮን በሩሲያው ጦርነት የተሸነፈበትን ምዕራፍ እያስተማረች ነበር፡፡ በዚህ የታሪክ መጽሐፍ ምዕራፍ ናፖሊዮን የተሸነፈው ‹‹በሩሲያ ነጭ ክረምት›› መሆኑን ነበር፡፡ መምህርቷ በመማሪያ መጽሐፉ የቀረበውን ምክንያት በመቀየር፣ ‹‹የናፖሊዮን ጦር የተሸነፈው በሩሲያ ሕዝብ እንጂ በሩሲያ ክረምት አይደለም፤›› ብላ ስታስተምር በመስኮት የተመለከታት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ከትምህርት ቤቱ እድትባረር ያደርጋል፡፡ አዲሱ የታሪክ መምህር ትምህርቱ ካቆመበት ሲጀመር ይህንን ምዕራፍ ማስተማር ይጠበቅበት ነበር፡፡

''የናፖሊየን ጦር እንዴት ተሸነፈ?''

''በሩሲያ ሕዝብ!''ሳራፊናና የክፍል ጓደኞቿ ምላሽ ነበር፡፡ ገናናው የናፖሊዮን በሩሲያ ባካሄደው ዘመቻ መሸነፉን በተመለከተ የቀረበው ምክንያት የሩሲያ ነጭ ክረምት መሆኑን ተማሪዎቹ ሊቀበሉት አልቻሉም፡፡ ተማሪዎቹ የሩሲያ ሕዝብን ጀግንነት ለማንኳሰስ ነው በሚል የቀድሞ መምህራቸው ያስተማረቻቸውን የታሪክ ዕይታ ይዘው ስለነበር ውዝግብ አስነሳ፡፡

''የናፖሊየን ጦር እንዴት ተሸነፈ?''የመምህሩ ጥያቄ፣

''በሩሲያ ሕዝብ!''የተማሪዎቹ ምላሽ፡፡

ናፖሊዮን በሳይንቲስትነት አይታወቅም፡፡ ግን ራሱን ያስተማረ የፈረንሣይ መሪ ነበር፡፡ በወታደራዊ መሐንዲስነት የሠለጠነ ሲሆን መጠነኛ የሒሳብ ዕውቀት ነበረው፡፡ እ.ኤ.አ በ1797 በፈረንሣይ ቅድመ አብዮት የሳይንስ ማኅበረሰብ በሆነው ብሔራዊ የሳይንስ ኢንስቲትዩት ለአባልነት ተመርጦ ነበር፡፡

ናፖሊዮን የፈረንሣይ ጦር በመምራት ግብፅን ለመውረር ሲነሳ አንድ ስጦታ ለማበርከት ነበር፡፡ ስጦታው ለፈረንሣይ ዘመናዊ ሳይንስን ማበርከት እንደሆነ ይነገራል፡፡  በጁላይ 1 ቀን 1798 ናፖሊዮን 400 መርከቦችና 54 ሺሕ ሰዎች ያሉት ሠራዊት ይዞ ግብፅን ወረረ፡፡ ናፖሊዮን 150 ሲቪል ሳይንቲስቶች፣ መሐንዲሶች፣ ጠቢባንና ምሁራን አብረውት የዘመቱት የግብፅን ምድር ለመያዝ ሳይሆን፣ የግብፅን ተፈጥሯዊናና ባህላዊ ታሪክ እንዲሁም አገር በቀል ዕውቀቶች ለመዝረፍ ነበር፡፡ በወቅቱ ወታደራዊ ዘመቻው ባይሳካም ሳይንሳዊና ምሁራዊ ተልዕኮው ከሚጠበቀው በላይ ስኬታማ እንደነበር ይነገራል፡፡

በጥንቃቄ የግብፅ ሥነ ምድር አቀማመጥ ተፈትሿል፡፡ አገር በቀል እንሰሳትና ዕፅዋት በሚገባ ተጠንተዋል፡፡ ማዕድናት ተሰብስበው በየፈርጁ ተደራጅተዋል፡፡ የአካባቢው ንግዶችና ኢንዱስትሪዎች በጥንቃቄ ተፈትሸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የግብፅ ጥንታዊ ቤተ መቅደሶችና መቃብሮች ሉክሰር፣ ፊሊያ፣ ዴንድራና የንጉሦቹ ሸለቆዎች ታውቀዋል፡፡ እነዚህ ቦታዎች በጥንቃቄ ተለክተው፣ ካርታ ተቀይሶላቸውና ተሠርቶላቸዋል  ተመዝግበዋል፡፡ የፈርኦን ምድር ከዚህ በፊት በማይታወቅ ሁኔታ በናፖሊዮን ባለሙያዎች ተጠንቷል፡፡ ከናፖሊዮን ጦር ጋር የዘመቱት ሳይንቲስቶች ግኝቶችን ዓለም እንዴት ማወቅ አለበት ? የሚለውን ጥያቄ አንስተው ቀድመው ምላሽ ሰጥተው ፈረንሣይ ግብፅን ከመወረሯ ስድስት ወራት በፊት የሳይንቲስቶቹ አቀራረቡን ወስነው መጥተዋል፡፡

ናፖሊዮን በዓባይ ላይ ባደረገው ጦርነት እ.ኤ.አ በ1798 መርከቦቹ ድባቅ በመመታታቸውን ሽንፈት አጋጠመው፡፡ ከናፖሊዮ ጦር የተረፉት ወደ ፈረንሣይ ተመልሰው እ.ኤ.አ በ1801 የሰበሰቡትን ቁሳቁሶች በማደራጀት ከዘጠኝ ዓመት በኃላ በ1809 የመጀመሪያዎቹን ቅጾች “Description de I’ Egypt” በሚል ርዕስአሳተሙ፡፡

በቀጣዮቹ ዓመታት እስከ 1828 ዓ.ም. በጠቅላላው 23 ቅጽ መጻሕፍትን አሳትመው ነበር፡፡ ከእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ሦስቱ ትላልቅ ቅጾች 43 ኢንች ርዝማኔ ነበራቸው፡፡ የግብፅን ባህል የሚያንፀባርቁ በጠቅላላው 837 አስገራሚ ቅርፃ ቅርፆችን ፈረንሣይ ወስዳ ነበር፡፡ ከእነዚህ የመጻሕፍት ቅጾች ጥንታዊ ቅርሶች፣ ግዙፍ ሐውልቶች፣ ቤተ መቅደሶች፣ ሲፊኒክስና ሁሉም ዓይነት የጥበብ ሥራዎች የታተሙባቸው ነበር፡፡ የተፈጥሮ ታሪካዊ ሀብቶች አስገራሚ ነበሩ፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ ዕፅዋትና አዝዕርቶች ተጠንተዋል፡፡ አዞ፣ መርዛማ እባቦች፣ የባህር ውስጥ ዕፅዋቶችና የዘንባባ ዛፍ ዝርያዎች ሳይቀሩ ተወስደው በመጻሕፍቱ ውስጥ ተካተው ለንባብ በቅተዋል፡፡

 

በግብፅ ሥልጣኔ ውስጥ የዓባይ ወንዝ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ የግብፅ ሕዝብን የዕውቀት ማዕከል ስናነሳ አሌክሳንደሪያ ቤተ መጻሕፍት ይወሳል፡፡ በጥንታዊ ዓለም ትልቁ ቤተ መጻሕፍት ሲሆን፣ በዓለማችን የሚገኝ ማንኛውም መጻሕፍት እንዲኖር ይደረግ ነበር፡፡ አሌክሳንደሪያ የደረሰ መርከብ ውስጥ በቤተ መጽሐፍት ውስጥ ከሌለ መጽሐፉ ይወረስና እንዲገባ ይደረግ እንደነበር ይነገራል፡፡ በተለይ በክሊዮፓትራ ዘመን ቤተ መጻሕፍት የዓለም ዕውቀት መገኛ ማዕከል እንዲሆኑ ይደረግ የነበረው ጥረት አስገራሚ ነበር፡፡ የፈረንሣይ ግብፅን መወረር የሳይንስና የዕውቀት ዘመቻ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ ፈረንሣይ ግብፅን ከወረረች ሰባ ዓመታት በኃላ እ.ኤ.አ በ1868 በእንግሊዙ ሰር ጄኔራል ናፒር ፊታውራሪነት ወደ አቢሲኒያ ምድር የተደረገው ዘመቻ የተዘረፉት ተፈጥሯዊና ባህላዊ ሀብቶች፣ እንዲሁም አገር በቀል ዕውቀቶች ምን ነበሩ? አፄ ቴዎድሮስ ካሠሯቸው ሚሲዮናዊ ባለ እጆች (Missionary Artisans) በጨረፍታ ተመልክተን ነጠብጣቡን ለማገናናኘት እንሞክር እስቲ ....

ታዋቂው አፍሪካዊ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ታሪክ ናሺድ “Hidden Colors” (የተደበቁ ቀለማት) በሚል ርዕስ ዘጋቢ ፊልም እ.ኤ.አ. በ2011 ሠርቶ ለዕይታ አቅርቦ ነበር፡፡ የአፍሪካ ጥንታዊ ታሪክና የሥልጣኔዎቿ በምዕራብያውያን ‹‹ታሪክ›› ተመራማሪዎች መዛባታቸውን፣ በበርካታ መረጃዎችና ምሁራን ትንታኔዎች አስደግፎ ይተርካል፡፡ የአፍሪካ ገናና ሥልጣኔዎችን ይተርካል፡፡ የአፍሪካ ጥንታዊ ስም ኢትዮጵያ ይባል እንደነበረ.....የአትላንቲክ ውቅያኖስ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ተብሎ ይጠራ እንደነበር ያወጋል፡፡

የአፍሪካ የአሁኑ ስያሜ መላ አኅጉሪቱን የሚወክል ከመሆኑ በፊት እያንዳንዱ የአፍሪካ ክፍል የሚጠራበት የራሱ ስያሜ ነበረው ይለናል፡፡ በኃላ በአንድ ወቅት አኅጉሪቱን ተቆጣጥሮ በነበረ አፍሪካነስ በተሰኘ የሮማ ጄኔራል አህጉሪቱ ስያሜዋን እንዳገኘች ዘጋቢ ፊልሙ ይነግረናል፡፡

ይህ የታሪክ ፊልም በርካታ የአውሮፓ ሕንፃዎች የኢትዮጵያ ጥንታዊ የኪነ ሕንፃ ጥበቦች አሻራ እንዳረፈባቸው የአውሮፓ የታሪክ ተማራማሪዎችና የሚዲያ ተቋማት ሊነግሩን አይፈልጉም በማለት ይሞግታል፡፡ ይህ ዘጋቢ ፊልም አንድም ኢትዮጵያዊ የታሪክ ተመራማሪ በዋቢነት የቀረበበት አይደለም፡፡ በዚህ ዘጋቢ ፊልም ውስጥ በታሪክ፣ በአርኪዮሎጂ፣ በፍልስፍና፣ በባህል፣ በሥነ ልቦና፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ሙያዎች አንቱ የተሰኙ አፍሪካዊ አሜሪካዊያን ናቸው የተሳተፉት፡፡

“Hidden Colors” (የተደበቁ ቀለማት) ዶክመንተሪ ፊልምን የተመለከተ አውቃለሁ ብሎ የሚያስበው ታሪክ ላይ ትልቅ ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም፡፡ የአገሬን ታሪክ አሰብኩት፡፡ በእንግሊዝኛ የተማርናቸውን የታሪክ መጻሕፍት ወደኋላ መለስ ብዬ እንዳስባቸው አደረገኝ፡፡ ሴቫስቶፖል በደቡብ ምዕራብ በጥቁር ባህር ክራይሚያ ባህረ ሰላጤ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት አካል በኋላ ደግሞ የዩክሬን ግዛት ነበረች፡፡ ሩሲያ እ.ኤ.አ በ2014 መልሳ ወደ ግዛቷ አዋህዳታለች፡፡

የሴቫስቶፖል የሕዝብ ቁጥር 393,304 (እ.ኤ.አ በ2014 ሕዝብ ቆጠራ) ነበር፡፡  የቀድሞዋ ሶቪዬት ዛር የጥቁር ባህር ኃይል ዋና ምድብ ቦታ ናት ሴቫስቶፖል፡፡ “Siege of Sevastopol” (1854-1855) እ.ኤ.አ ከ1854 መስከረም እስከ መስከረም 1855 የክራይሚያ ጦርነት ተካሂዶ ነበር፡፡ ፈረንሣይ፣ ኦቶማን (የአሁኗ ቱርክ) እና ብሪታኒያ በኅብረት ከሩሲያ ጋር በሴቫስቶፖል ባህረ ሰላጤ የከበባ ጦርነት ለአንድ ዓመት አካሄዱ፡፡ አስጊው የሩሲያ ባህር ኃይል የጠላት ጦር ከበባውን ከማድረጉ በፊት የጦር መርከቦቹንና ሴቫስቶፖል መድፎቹን ባህር አስምጦ አፈገፈገ፡፡

ብሪታኒያ ከሴቫስቶፖል የማረከቻቸው መድፎች ገሚሱን ለወታደራዊ ተቋማት የሰጠች ሲሆን፣ መድፎቹ የተሠሩባቸው የብረት ማዕድናት ከየት የመጡ ናቸው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ከባድ ነበር፡፡ የሴቫስቶፖል መድፎችን አቅልጣ ብሪታኒያ ኒሻን በመሥራት ጀግኖቿን አሸቆጥቁጣበታለች የሚሉ መረጃዎች አሉ፡፡ የፈረንሣይና የብሪታኒያ መሐንዲሶች የከበባ መስመሮችን በመዘርጋት፣ የመከላከያ ምሽግ (ግድግዳ) በመገንባት፣ እንዲሁም መድፎችን በመሥራት ኃያሉን የሩሲያ ባህር ኃይል ገጥመው ብዙ ጉዳት ደረሰ፡፡

በሴቫስቶፖል በውትድርና የተሳተፈው ታዋቂው የሩሲያ ደራሲ ሊዎ ቶልስቶይ "Sebastopol Sketches"የሚል መጽሐፍ ጽፏል፡፡ የሩሲያ የመጀመሪያው ተራኪ ፊልም “Defence of Sevastopol” የታዋቂው እንግሊዛዊ ገጣሚ ሥራ " The Charge of the Light Brigade"ግጥም የሚተርከው ስለ ሴቫስቶፖል ነው፡፡ ሴቫስቶፖልን የሚያሳየው "The Thin Red Line"ሥዕል ታሪኩን ከሚዘክሩ የጥበብ ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ንጉሥ ለመውደቃቸው ከሚጠቀሱ ምክንያቶች የአውሮፓ ሚሲዮናውያንን  አስረው "ሴቫስቶፖል"የተሰኘ መድፍ እንዲሠሩላቸው ማድረጋቸው ነበር፡፡ እንደ ብሪቲሽ ኢምፓየር መረጃ ማዕከል እ.ኤ.አ በ1862 አፄ ቴዎድሮስ ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረጉ ጦርነቶች አገራቸውን ከጥቃት ለመከላከል የጦር መሣሪያዎችና ባለሙያዎች እንዲሰጧቸው ከጠየቋቸው አገሮች አንዷ ብሪታኒያ ነበረች፡፡ የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለንጉሡ ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጥ ዘገየ፡፡ ይባስ ብሎ የብሪታኒያው ቆንስል ካፒቴን ቻርልስ ካሜሮን ግብፅን ጎብኝቶ መመለሱ ንጉሡን ይበልጥ አስቆጣቸው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ቻርልስ ካሜሮንና ሌሎች የውጭ ዜጎችን አሰሩ፡፡

በወቅቱ ብሪታኒያን ገዢ ፓርቲዎች ገላድስቶንና ሌበር ነበሩ፡፡ ሁለቱም ፓርቲዎች የቅኝ ግዛት ጀብደኝነት ውስጥ መግባት ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ ፓርቲዎቹ ቸልተኛ ቢሆኑም ይህም ቸልተኝነታቸው ችግሩን እንዲፈጠር ማድረጉ ይነገራል፡፡ የቻርልስ ካሜሮን ለብሪታኒያ ፕሬስ በጻፈው ደብደቤ ከታጋቾቹ መካከል የብሪታኒያ ሴቶችና ሕፃናት እንደሚገኙበት የሚያትት ስለነበር፣ የብሪታኒያ ሕዝብ ዘንድ ጉዳዩ ተጋኖ እንዲደርስ ሆነ፡፡ በወቅቱ በብሪታኒያ አጠቃላይ ምርጫ እየተካሄደ መሆኑ ትንሹ ጉዳይ ጦዞ፡፡ በብሪታኒያ ሕዝብ ዘንድ መነጋገሪያ መሆን ቻለ፡፡ በተለይ የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ አባላት የምርጫ ዘመቻውን የቻሉትን ያህል ሊጠቀሙበት በመሞከራቸው ጉዳዩ ጦዞ ጦር እስከ መላክ ተደረሰ፡፡

የብሪታኒያው ጄኔራል ናፒር 13 ሺሕ የእንግሊዝና የህንድ ወታደሮች፣ 26 ሺሕ የካምፕ ተከታዮች፣ ዝሆኖችን ጨምሮ 40 ሺሕ ከብቶች ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ዘመተ፡፡ የብሪታኒያ ሠራዊት ከህንድ ቦምቤ ወደ ኢትዮጵያ 280 በእንፋሎት የሚሠሩ ቀዛፊ መርከቦች ተጠቅሞ ነበር፡፡ በቅድሚያ ከህንድ ተሳፍረው የመጡት የመሐንዲሶች ሠራዊት ሲሆን፣ በቀይ ባህር ዘይላ ከምፅዋ ወደብ በስተደቡብ 30 ማይሎች (48 ኪሎ ሜትሮች) ሠፍረው እ.ኤ.አ በኦክቶበር አጋማሽ 1867 የዘይላ ወደብን መገንባት ጀመሩ፡፡

በመጀመሪያው ወር 700 ያርድ (670 ሜትር ) ርዝመት የገነቡ ሲሆን፣ በቀጣዩ ወር ሁለተኛ ሳምንት የባቡር ሐዲድ ከትልቅ የብረት ድልድይ ጋር ወደ ውስጥ እንዲደርስ ገንብተው ጨረሱ፡፡ በተጨማሪ መሐንዲሶች የጦር መሳሪያዎችን የሚያጓጉዙ ዝሆኖችን ከነተጎታች ጋሪዎቻቸው መሸከመና ማሳለፍ የሚችል እስከ ሰንዓፌ የሚደርስ 101 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ከፍታው ደግሞ 2,300 ሜትሮች የሆነ መንገድ ገንብተው ጨረሱ፡፡ የብሪታኒያ ወታደሮች በዘይላ ካምፕ ወደብ ቆይታቸው የውኃ ፍጆታቸው ብዙ ስለነበር በእንፋሎት ኃይል የሚሰሩ ጀልባዎች በመጠቀም በቀን 200 ቶን ውኃን በማጤዝ (Condensation) ይጠቀሙ ነበር፡፡ ጦሩ ወደ ርዕሰ ምድር ከገባ በኃላ ጉድጓድ በመቆፈር ፍጆታውን ያሟላ ነበር፡፡ የጄኔራል ናፒር ጦር በሦስት ወራት ጉዞ መቅደላ ገባ፡፡

ጀርመናዊው ጆርጅ ሺምፐር በአትክልትና በአዝዕርት አጥኚነት እንዲሁም በአሳሽነት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ40 ዓመታት በላይ ኖሯል፡፡ በሰሜን ተራሮች፣ በመረብና በተከዜ አካባቢዎች በአሁኖቹ በኢትዮጵያ ደጋማና በኤርትራ ዕፅዋትን በመሰብሰብ ዘመናት አስቆጥሯል፡፡ ሺምፐር በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ዕፅዋትና እንስሳት ዝርያዎችን በማጥናትና በመሰብሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ ተመራማሪዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ከሺምፐር በፊት በኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ዕፅዋት በአውሮፓ አይታወቁም ነበር፡፡ ሺምፐር ዕፅዋትንና አዝርዕትን በመሰበሰብና በማድረቅ ለአውሮፓ የዕፅዋት ሳይንስ ማዕከላት ይልክ ነበር፡፡ በአውሮፓ የሚገኙ ትላልቅ የዕፅዋትና የአዝርዕት ምርምር ማዕከላት ሺምፐር ከኢትዮጵያ የላካቸው ዝርያዎች እንደሚገኙ ጀርመናዊቷ ጸሐፊ ዶርዚያ ማክዋን ስለሺምፐር በጻፈችው መጽሐፍ አሥፍራ እናገኛለን፡፡

ለአውሮፓ ዋና ዋና የእፅዋትና የአዝርዕት ዝርያዎች ምርምር ማዕከላት ከኢትዮጵያ ዝርያዎችን ልኮላቸዋል፡፡ ፓሪስ ለሚገኘው “Jardin des Plantes” የዕፅዋት ሙዚየም፣ ጀርመን በርሊን ለሚገኘው “Botanisches” የዕፅዋት ምርምርና ሙዚየምና እንግሊዝ ለሚገኘው “Royal Botanical Society” የዕፅዋትና አዝርዕት ሙዚየም የኢትዮጵያን ዝርያዎች ለቅሞና ሰብስቦ ልኳል፡፡ ለእንግሊዙ የሮያል ቦታኒካል ሶሳይቲ የዕፅዋትና የአዝርዕት ሙዚየም ብቻ በስሙ የሚጠሩ “schimperiana” የተሰኙ 2,400 ልዩ ዝርያዎች ከኢትዮጵያና ከመካከለኛው ምሥራቅ የተሰበሰቡ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 25 ቀን 1831 ሺምፐር ከጀርመን ወደ ደቡብ ፈረንሣይና አልጀርስ “Botanischer Reiseverein of Esslingen” የተሰኘ የዕፅዋትና አዝርዕት ምርምር ማኅበር ባደረገለት የገንዘብ ድጋፍ ሥራውን ጀመረ፡፡ ከወንድሙ ጋር ከአልጄሪያ ወደ ግብፅ ያመራው ሺምፐር፣ ወንድሙ ካይሮ ሲደርስ በመሞቱ የዕፅዋት መሰብሰቡን ሥራ ብቻውን ተያያዘው፡፡ በዓረቢያ ባህረ ሰላጤ ብቻውን 30 ሺሕ ዝርያዎችን መሰብሰብ ችሏል፡፡

በኋላ በገንዘብ ዕጥረት የማኅበሩ ድጋፍ ሲቋረጥ ቀይ ባህርን ተሻግሮ ዓደዋ እ.ኤ.አ በ1836 ራስ ውቤ ኃይለ ማርያም በኢትዮጵያ እንዲኖር ፈቀዱለት፡፡ እ.ኤ.አ ከ1837 እስከ 1855 ሺምፐር በመረብ ወንዝና በሰሜን ተራሮች በተከዜ ወንዝ በስተደቡብ የዕፅዋትና የአዝርዕት ዝርያዎችን በመሰብሰብ ወደ አውሮፓ ይልክ ነበር፡፡

ጆርጅ ሺምፐር ኢትዮጵዊቷን ወይዘሮ መርሲትን እ.ኤ.አ በ1843 አገባ፡፡ ከመርሲት ጋር በነበረው ጋብቻ አራት ልጆች አፈራ፡፡ ራስ ውቤ ሺምፐርን በምሥራቅ ዓደዋ የምትገኝ "ኢንጢቾ"የምትባል ቦታን  እንዲያስተዳድር ሾመውት ነበር፡፡ በተሰጠው የእርሻ መሬት አዲስ የግብርና ዘዴ በመጠቀም አትክልቶችን ይተክል ነበር ፡፡ ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል የድንች እርሻውም ይጠቀሳል፡፡

ዶርዚያ ማክዋን ስለ ሺምፐር በጻፈችው መጽሐፍ እንዲህ አስፍራለች እ.ኤ.አ ክርስቲያን ፍሬዳሪክ ቤንድር የሺምፐርን በኩር ሴት ልጅ የሺ እመቤትን አገባ፡፡ ፍሬዳሪክ የጀርመናዊ ሚሲዮናዊና ዕደ ጥበብ ባለሙያ ነበር፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ደብረ ታቦር ጋፋት ውስጥ የሚሽን ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ወርክሾፕ ከፍቶ ይሠራ እንደነበር ዶርዚያ ማክዋን ትነግረናለች፡፡ እ.ኤ.አ በ1863 የሚሲዮናውያኑ ቡድን አባል የሆነው ጎትሊብ ኪንዚል የሺምፐርን ፈቃድ በመጠየቅ ሁለተኛ ሴት ልጁን አገባ፡፡ በኋላ ጣይቱ ኬንዝልና ሌሎች ጋፋት ይኖሩ የነበሩ አውሮፓውያን አካባቢውን ለቀው እንዳይሄዱ በቴዎድሮስ እገዳ ተጣለባቸው፡፡ አዲሱ ሙሽራ ወደ ዓደዋ መጓዝ ባለመቻሉ ሺምፐር ጣይቱን ወደ ጋፋት ይዟት መጣ፡፡

ዶርዚያ በመጽሐፏ እንዲህ አስፍራለች፡፡ ሺምፐርም ከሌሎች ጀርመናዊ ፕሮቴስታንት የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ከጋፋት እንዳይወጡና ለቴዎድሮስ የጦር መሣሪያ እንዲያመርቱ ዕገዳ ተጣለባቸው፡፡

የሺምፐርና የሌሎች ጀርመናውያንን ፎቶግራፍ በጀርመናዊቷ መጽሐፍ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ታገኛላችሁ፡፡ ሺምፐርና ቤተሰቦቹ በታሪክ መጽሐፎቻችን እምብዛም አይታዩም፡፡ እንግሊዞቹ ሲጽፉ የእንግሊዝ መነጽር አድርገው ስለሆነ ይህንኑ ሲያሳዩን ቆይተዋል፡፡ በብዛት የምናገኛቸው እንዴት ቴዎድሮስን እንደጣሉና የዘመነ መሳፍንት ክፍፍልን ነው፡፡ ጸሐፊዋ በቅርቡ የሺምፐርን ሁለት ሪከርዶች (ሰነዶች) ብሪቲሽ ቤተ መጻሕፍት አግኝታለች፡፡ የመጀመሪያው “Observations” ሁለተኛው ቅጽ ደግሞ ካርታዎችና የአካባቢ መግለጫዎች መሆናቸውን ጽፋለች፡፡

የሴቫስቶፖል የከበባ ጦርነት ሲጀመር እ.ኤ.አ በ1855 ወደ ሥልጣን የመጡት አፄ ቴዎድሮስ ‹‹የሴቫስቶፖል መድፍ›› ስያሜውን ያገኙት ሩሲያ ከሚገኘው የሴቫስቶፖል ቦታ መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህን እንዴት አሰቡት ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

"የሶፊስት ወርልድ"የፍልስፍና መጽሐፍ ውሰጥ አንድ "ሐሳብ"ወይስ "ቁስ"ይቀድማል ለሚል ጥያቄ ምላሹን የምትሰጠን ወግ አለች፡፡ ሐሳቧን እንዲህ እንጋራት፡፡

---አንድ ሐውልት ቀራጭ ከትልቅ ቋጥኝ ድንጋይ የሆነ ነገር እየቀረፀ ነበር፡፡ ይህንን የተመለከ አንድ ሕፃን ቀራፂውን ይጠይቀዋል፡፡

"ከዚህ ቋጥኝ (አለት) ምን እየሠራህ ነው?"በማለት ሕፃኑ ልጅ ቀራፂውን ይጠይቃል፡፡

"ዝም ብለህ ተመልከት....ስጨርስ ታየዋለህ……"ብሎ ቀራፂው ቋጥኙን ይቀርፃል፡፡

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሕፃኑ ሲመለስ ከዚያ ቋጥኝ "ውብ ፈረስ"ተሠርቶ ይመለከታል፡፡

"ፈረሱ ቋጥኙ ውስጥ መኖሩን እንዴት አወቅክ!?"ብሎ ልጁ ተገርሞ ይጠይቃል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው eskinder.kebe1996@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡      

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles