በጌታቸው አስፋው
ሙያዊ ቃላት ዕለት በለት እንደ ዋዛ ሲነገሩና ጥናትና ምርምር ሲደረግባቸው የተለያየ መረዳትና ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ ይኼንን ጽሑፍ ለማቅረብ የፈለግሁት ኢሕአዴግና ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች፣ ሌሎችንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ጨምረው ስለሕዝባዊው አመፅና ሁከት መነሾና መፍትሔ በጥናትና ምርምር አስደግፈው በምሁራን በቀረቡላቸው ጽሑፎች አማካይነት ከአካሄዱት ውይይት ተነስቼ ነው፡፡ በጥቅሉ ስመለከተው የውይይት አቅራቢዎቹን፣ ጠያቂዎቹንና አስተያየት ሰጪዎችን ሐሳቦች ደምሬ ቀንሼ አባዝቼ አካፍዬ በሒሳብ ስሌት ያገኘሁት ውጤት አንድ ቁጥር ሆኖብኛል፡፡
በዝርዝር ስመለከትም ውይይቱ ሁለት ነገሮችን በአዕምሮዬ ጫረብኝ አንዱ የሕዝቡን አመፅ የራሳቸው ለማድረግና የየራሳቸውን ታሪክና ጥንካሬ የውይይቱ ማዕከላዊ ነጥብ ማድረጋቸው ነው፡፡ ሁለተኛው በፖለቲካው፣ በልማቱ፣ በማኅበራዊው መስክ እያሉ ሲከራከሩ ስሰማ ከሠላሳ ዓመት በፊት በአስመራ ዩኒቨርሲቲ ስለልማት ሳስተምር፣ ከልማት ጠበብት አንብቤ የቀሰምኩት ሙያዊ ዕውቀትና የእነርሱ መከራከሪያ አልጣጣም ብሎኝ ነው፡፡ በልማት ጠበብት ትምህርት ልማት የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ለውጥ ሲሆን፣ ፖለቲከኞቹ ግን ልማት ብለው የሚያወሩት ስለኢኮኖሚ ልማት ብቻ ነበር፡፡
ኢሕአዴጎች በፖለቲካውና በማኅበራዊ አገልግሎቱ አንዳንድ ድክመቶች ቢታዩብንም፣ በልማቱ ግን ማንም የማይክደው የተዋጣለት ስኬት አስመዝግበናል አሉ፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም እየተቅለሰለሱም ቢሆን ይኼንን አምነው ተቀብለዋል፡፡ የልማት ጠበብት የልማት ትርጉም ይኼንን አይቀበልም፡፡ ምክንያቱም ልማት ፖለቲካዊም፣ ኢኮኖሚያዊም፣ ማኅበራዊም፣ መንፈሳዊም ሁለንተናዊ ጉዳይ ነውና ነው፡፡
ከዚህም በላይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የኢኮኖሚ ልማትና የገበያ ኢኮኖሚ በመምታታቱ ቀውስ ይመጣል ብዬ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል በሪፖርተር ጋዜጣ በተከታታይ የጻፍኩትና ያልኩት ሆኖ አየሁ፡፡ ያልኩት በመሆኑ ተደስቼ ሳይሆን መቅሰፍቱ ወደፊትም ብቅ ጥልቅ እያለ የልጆቻችንን ሕይወት እንዳይቀጥፍ ሌላ የማስጠንቀቂያ ደወል ለመደወል፣ ዛሬም እንደገና በሙያዬ መነጽር አይቼ ካልተጠነቀቅንና መንገዳችንን ካልቀየርን አደጋ ያጋጥመናል ብሎ ለመጻፍ በድጋሚ ሞራል አግኝቼአለሁ፡፡
መንግሥትንም ደመወዝ ሳይከፍላቸው እንዳይሳሳት ከሚያርሙት የሙያ ሰዎች በነፃ የሚያገኘውን መድኃኒት ችላ ብሎ ደመወዝ ከሚከፍላቸው ሙያተኛ ባለሟሎቹ በሽታን ከሚሸምት፣ የአመፅ ጭላንጭል በታየ ቁጥር እየደጋገመ ቆርጬ እጥለዋለሁ የሚለው በሽታ ይበልጥ ወደ ሰውነቱ እየተሰራጨ ጧት ማታ ለሕዝብ በመሀላ ቃል ከመግባት ይልቅ መድኃኒቱን ወስዶ ቢድን ይሻለዋል ለማለትም ነው፡፡
ልማትና የኢኮኖሚ ልማት ምንና ምን ናቸው?
ገና እ.ኤ.አ ከ1950ዎቹና ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሲሞን ኩዝኔትስን፣ ጉናር ሚርዳልንና ሌሎችም የልማት ጠበብቶች ልማትን በሰፊው ትርጉምና በጠባቡ ትርጉም ለይተው ያስተምሩ ነበር፡፡ በሰፊው ትርጉም የሰው ልማት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ሁለንተናዊ ለውጥ ማለት ሲሆን፣ ከአራትና ከአምስት መገለጫዎቹ አንዱ ሰው በአምሳሉ ለተፈጠረው ለሌላ ፍጡር ሰው አቀንቃኝና አጎብዳጅ ሆኖ ከመኖር ይልቅ፣ በውስጡ በራስ መተማመን ሊኖረው ይገባል ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ የልማት ጠበብቶች አውራውና የኖቬል ተሸላሚው አማርተያ ሴንም ልማትን ሲተረጉሙ፣ ሰው ሕጋዊ የሆነን ማንኛውም ነገር በራሱ ለመሥራት አቅምና ነፃነት ማግኘቱ ነው፡፡ ሁለቱም ትርጉማቸው ተመሳሳይ ሆኖ በግለሰብ ላይ የሚታይ ራስን የመቻል ሁለንተናዊ ለውጥ ነው፡፡
ከምዕተ ዓመታት በፊት ለአሜሪካኖች ብልፅግና የፕሮቴስታንት እምነት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይገመታል፡፡ ምክንያቱም ዕምነቱ አንድ ፈጣሪህን ብቻ አምልክ እንጂ በአምሳያህ ለተፈጠረ ሌላ ሰው እንዳንተው ፍጡር ነውና አትስገድ አትንበርከክ ይላልና ነው፡፡ ዛሬም ድረስ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና አንድ የፅዳት ሠራተኛ አብረው ሻይ ቢጠጡ አንዱ ሌላውን አይንቀውም፣ አይፈራውምም፡፡ ሁለቱም በሰውነታቸውም በሥራቸውም ይከባበራሉ፡፡
እኛ ጋ የቀበሌና የወረዳ ሊቃነመናብርት እንኳ ይኼንን አያደርጉም፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቻችንማ ባለ ማስትሬቱ ለባለ ዶክትሬቱ ሻይ ቤት ውስጥ ተነስቶ ወንበሩን ካልሰጠው ያኮርፈዋል አሉ፡፡ ይኼ ሰው ታዲያ ለምቷል ሊባል ይችላል? እኔማ ባለማስተርስ፣ ባለዶክትሬት ብዬ አልጠራቸውም፡፡ ግራዝማች፣ ቀኛዝማች ነው የምላቸው፡፡ አይበቃቸውም? ምን ለውጥ አምጥተዋል?? ዛሬ በኢትዮጵያ ድህነት እየከበዳቸውም ራሳቸውን ለአምሳያቸው ሰው ከመስገድ ነፃ ያወጡ፣ ከአንድ አምላካቸው በቀር ለሌላ የማይሰግዱና የማይንበረከኩ እየበዙ ነው፡፡ ምድሪቱም በእነርሱ ትባረክ ይሆናል፡፡
‹‹እሳቸው እንዳሉት…..›› ብሎ ዜና የሚያቀርብ ጋዜጠኛ አልለማም፡፡ የሌላ ሰው አቀንቃኝ ነውና፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን ለማስመረቅ መክፈቻ ንግግር የሚያዘጋጅ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የንግግሩን ግማሽ መንግሥትን ለማሞካሸት ከተጠቀመ አልለማም፣ ለሌላ አጎብዳጅ ነውና፡፡ መሳቅ ሳያስፈልገው አለቃውን በሳቅ ለማጀብ የሚስቅ ሰው አልለማም፣ አለቃ አምላኪ ነውና፡፡ ባለሥልጣንን የሚፈራና ለባለሥልጣን የሚሰግድ ሰው አልለማም፣ የራሱን አቅም አያውቅምና፡፡ ኢትዮጵያዊ ያውም የገጠሩ ኢትዮጵያዊ ከእነኚህ ዓይነቶች ያለመልማት ምልክቶች ራሱን ነፃ ለማውጣት ነው አሻፈረኝ ያለው፣ የደማው፣ የቆሰለውና የሞተው፡፡
ወደ ዴሞክራሲያዊ ውክልናው ሳንሄድ በፊት ሳትወከሉ የተወከላችሁ እስኪ ወካዩ በልማት ትርጉም ራሱን ፈልጎ እንዲያገኝ ፍቀዱለት፡፡ ዴሞክራሲያዊ ውክልና የሚያስፈልገውኮ ለአስተዳደር ቅልጥፍና እንጂ ሰው በራሱ ላይ ምድራዊ ንጉሥ የመሾም ሱስ ይዞት አይደለም፡፡ ሕዝብ መገዛት ይፈልግ አይፈልግ ሳታውቁ እኔን ይወደኛል፣ እኔ ልወከልና ልግዛ ብላችሁ ባትጣሉና ባትነታረኩ ጥሩ ነው፡፡ ለመምረጥ ገና ከሌላም ከራሱም ጋር ይታገላል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁለንተናዊ ልማት ከተገዢነትና የበታችነት ስሜት ከመሰማት ያድነኛል ብሎ ለሁለንተናዊ ልማት ነው የደማው፣ የቆሰለውና የሞተው፡፡ ሙሴ ወደ ግብፅ ፈርኦን ሄዶ የእስራኤል ሕዝብ ለአምላኩ ይሰግድ ዘንድ ነፃ ልቀቀው ይልሃል ኃያሉ እግዚአብሔር አለ፡፡ ፈርኦንን ሥልጣን አጋራኝ አላለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም እንደ ሙሴ ነፃ እንዲወጣ የሚታገልለት የሙሴን ልቦና የተሸከመ የሁለንተናዊ ልማት ተሟጋች እንጂ የሚፈልገው ፈርኦኖች ለማቀያየር አይደለም፡፡
በጌዴኦ ሕዝብ ለሕዝብ የተፋጀው ያነቃውና ያስተማረው የፖለቲካ ሰው ስላልነበረ ነው፡፡ በየመሸታ ቤቱ ማንቼ፣ አርሴ ስትሉና ወዝወዝ በሉ ስትባሉ ከርማችሁ የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ ምክር ቤት ስብሰባ ስትጠሩ ሱፍና ከራባታችሁን አጥልቃችሁ፣ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ የምትሉ ፖለቲከኞች ከስብሰባው በፊት አንብቡ፣ ዕወቁ፣ ጻፉ፡፡ ያላነበበ፣ ያላወቀ፣ ያልጻፈና የማያዛልቅ ፀሎት ለቅስፈት ነው፡፡ ሰው ብዙ ከማንበብና ከማወቅ የተነሳ ከራሱ ቀና ያልሆነ አስተሳሰብም ነፃ መውጣት አለበት፡፡
ሌላው ስለልማት በጠባብ ትርጉሙ የልማት ጠበብት ያስተማሩት ስለኢኮኖሚ ልማት ነው፡፡ የኢኮኖሚ ልማት ከቀላል ዓይነት የማምረት ዘዴ ወደ ከባድና ውስብስብ የማምረት ዘዴ ለመሸጋገር በትምህርት፣ በጤና ጥበቃ፣ በመሠረተ ልማቶችና በማኅበራዊ አገልግሎቶች የመንግሥት አቅርቦት ሰውን የማብቃት እገዛ ሰው በግል ጥረቱ ኑሮውን የሚያሸንፍበት አጋዥ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ የኢኮኖሚ ልማት ለታዳጊ አገር ሰው የኑሮ ዘዴ የመጀመርያው ምዕራፍ ሲሆን፣ ውድድራዊ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሁለተኛው ምዕራፍ ነው፡፡ አንደኛው ምዕራፍ ለሁለተኛው ምዕራፍ መንገድ ጠራጊ ብቻ ነው፡፡
‹‹ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም›› እንደሚባለው የኢኮኖሚ ልማት ሰውን የማብቃት ሥራ ነው እንጂ የመጨረሻ ግብ አይደለም፡፡ ሠርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚመግቡ፣ የሚያለብሱና የሚያስጠልሉ ግለሰቦች ከኢኮኖሚ ልማት ቀጥሎ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ተወዳድሮ የሚያሸንፉበት፣ የሚሸናነፉበትና ሊያሸንፉ ወደሚችሉበት ሥራቸውን መቀየር የሚችሉበት የውድድር ሕግና ሥርዓት ተዘርግቶ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ ይኼ ካልሆነ የኢኮኖሚ ልማቱ የውጊያውን ሥርዓት ሳይዘረጋ ድንበር ላይ ስንቅና ትጥቅ ሰጥቶ ወታደር እንደሚያከማች የጦር መሪ ነው፡፡ ጠላትን መምታት ካልቻሉ ወታደሮቹ በጊዜ ብዛትና በመሠላቸት መሪውን ራሱን ይመቱታል፡፡ ኢሕአዴግ በኢኮኖሚ ልማት ፍልስፍናው የገጠመውም ይኼ ነው፡፡
የኢሕአዴግ ኢኮኖሚ ልማት ሰውን በማብቃት እገዛው ላይ የሚያቆም ነው፡፡ ቀጥሎ ባለው የኑሮ ዘዴ ምዕራፍ ሁለት ሰዎች በውድድር ከማግኘት ይልቅ በኢኮኖሚ ልማቱ ሒደትና ወቅት በሽሚያ ታግለው ያሸነፉ ጥቂቶች፣ ሁሉንም ለራሳቸው አግበስብሰው ሠርቶ ከማሠራትም ይልቅ ተቀምጠው ለመብላት ስለወሰኑ ሕዝቦች በውድድር ሊከፋፈሉ የሚችሉት ሀብት ጠፋ፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ አመፁና ሁከቱ የበይ ተመልካች የሆኑት ብዙኃኑ በኢኮኖሚ ልማቱ ሒደት እኛ ጋ ያልደረሰውን ሀብት ተሻምተው ከወሰዱት በጉልበታችን ነጥቀን እንወስዳለን ነው፡፡
ኢሕአዴግ የተባበሩትን ብቻ ለመጥቀም አስቦም ይሁን ወይም በችሎታ ማነስ ምክንያቱን በውል ባላውቅም፣ በኢኮኖሚ ልማቱ ሰዎችን ወደ ውድድር ሜዳው ቢያደርስም የውድድሩ ሕግና ሥርዓት የሆነው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሚናውን እንዲጫወት አላደረገም፡፡ አልሚዎቹና ተባባሪዎቻቸው ድርሻ ድርሻዎቻቸውን ይዘው ለሚዎቹ ባዶ እጃቸውን ቀሩ፡፡ በውድድር የሚከፋፈል ሀብት በጥቂቶች ታንቆ ተያዘ፡፡ የአመፁ ዋና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ይኼ ነው፡፡
ኬኩን በጋራ አተልቀን እንደሚገባን እንከፋፈለዋለን የሶሻሊዝም መርህ የኢኮኖሚ ልማት፣ ከካፒታሊዝም ውድድራዊ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ጋር አልዋሀድ ብሎ ለግለሰቦች ከገበያ ውድድር ይልቅ ሽሚያን የሀብት ማፍሪያ መሣሪያ አደረገ፡፡ የኢኮኖሚ ልማትና የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ካልተመጣጠኑና ካልተመጋገቡ ይኼ ሽሚያ የሰው ቁጥር በጨመረ ቁጥር የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ አይደለም፡፡ ጊዜ አልፎ ጊዜ ሲተካ ሕዝብ በዝቶ መሬት ስትጠብም ሁኔታው ይባባሳል እንጂ አይቀንስም፡፡
የኢኮኖሚ ልማት ለሰዎች የግል ብልፅግና ጥረት እንደ መንገድ ጠራጊ ምዕራፍ በአብዛኛው በጋራ የሚታሰብና በጋራ የሚሠራ መንግሥታዊ የደቦ ሥራ ሲሆን፣ ግቡን ካልመታ በቡድኑ ውስጥ የታቀፉ መንግሥታዊ ሥልጣን የተቆጣጠሩና እነርሱን የተጠጉ ጥቂት አባላቱንና ተሽሎክላኪ ባለሀብቶችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡
በዚህም የኢኮኖሚ ልማት መሠረታዊ ፍልስፍናው በግል ምርታማነትና በግል ትርፍ ላይ ከተመሠረተውና ግለሰብን ማዕከል ከሚያደርገው ውድድራዊ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር በፍልስፍናም በአካሄድም ይለያል፡፡ በውድድራዊ ነፃ ገበያ መርህ ራሱንና ቤተሰቡን የመቀለብ፣ የማልበስና የማስጠለል ግዴታና ኃላፊነት የግለሰቡ ነው፡፡ ውድድር በሽሚያ ሲተካ ብዙዎቹ ግለሰቦች ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለመቀለብ፣ ለማልበስና ለማስጠለል አቅም ሲያጡ ወደ አመፅ ይገባሉ፡፡
‹‹ፈርሳ እንደ አዲስ የተገነባች ከተማ›› በመባል የተደነቀችውና የኢኮኖሚ ልማት ውጤት ታይቶባታል በተባለችው በአዲስ አበባ ሕንፃዎችና መንገዶች ግንባታ ጉልበቱን ያፈሰሰው ወጣቱ ነው፡፡ በግንባታው ወቅት የተከፈለው የጉልበቱ ዋጋ በምግብ፣ በልብስ፣ በመጠለያና በመዝናኛ ወዲያው አልቋል የማታ የማታ የተሠራውን ሕንፃም ሆነ መንገድ ይዘው የቀሩት ግን ባለሀብቱና መንግሥት ብቻ ናቸው፡፡ ወጣቱ ባዶ እጁንና ባዶ እግሩን ይዞ ቀረ፡፡ ጥቂት ገንዘብ የቆጠቡትም ሆቴል ቤቶችን፣ ቡቲኮችን፣ የውበት ሳሎኖችን፣ የድለላ ሥራዎችን የመሳሰሉ ጥቃቅን አገልግሎቶችን በመስጠት ይተዳደራሉ፡፡ የኢኮኖሚ ልማት በግንባታ ላይ ብቻ ሲያተኩርና መንግሥት መሪ ሲሆን ውጤቱ ይኼው ነው፡፡ መንግሥት ሲፈረጥም የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ሞተር ግለሰብ ይኮላሻል፡፡
ስለዚህም የወጣቱ በተቀጣሪነት ሥራ ማግኘት ተጠቃሚነት በግንባታ ወቅት ብቻ ነበር፡፡ የግል ሕንፃ ከግንባታ በኋላ ለባለንብረቶቹ የኪራይ ገቢ አምጥቷል፡፡ የመንግሥት መንገድ ግንባታም ለተጠቃሚዎች ጥቅም ሰጥቷል፡፡ ለወጣቱ ቋሚ የሥራ ዕድል ግን አልፈጠረም፡፡ የኢኮኖሚ ልማት ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ካልተሸጋገረ ልማታዊ መንግሥት ወደ የጨነገፈ መንግሥት (Failed State) ይቀየራል፡፡
በገበያ ኢኮኖሚ የግላዊና የብሔራዊ ኢኮኖሚው መስተጋብር
ለወትሮው እነ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ነበሩ የኢኮኖሚያችን ዕድገት ምስክሮች፡፡ ዛሬ እኛ እንመስክርላቸው ወይም እንጠይቃቸው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት ከማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ጋር ተስተካክሎ ተረጋግጧል ሲሉን ከረሙ፡፡ ለመሆኑ የእነርሱ ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ምንድነው? የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ነው? የዋጋ ንረቱ ነው? በመሬት ሽሚያ ለሁከት የዳረገውን የወጣቱን ሥራ አጥነት ነው የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ሲሉ የከረሙት፡፡
ስለአዲሶቹ ለጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች (New Classical Economists) እና ስለ አዲሶቹ ለኬንሳውያን ኢኮኖሚስቶች (New Keynessian Economists) የግል ኢኮኖሚው መሠረታውያን ለብሔራዊ ኢኮኖሚው (Microeconomic Foundations of the Macroeconomy) ጽንሰ ሐሳቦችን እንደ ውኃ የጠጡት የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ባለሙያዎች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የግል ኢኮኖሚ መሠረታውያን ፈጽሞ እንደሌሉ አያውቁም ነበር ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ ደግሞ ለድሃ አገር ብለው ስለሚንቁን አያስፈልጋቸውም ብለው ደምድመው ይሆናል፡፡ ከዚህ ሌላ ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ልዩ ልዩ ገበያዎች የሆኑት የሠራተኛ፣ የመሬት፣ የካፒታልና የምርት ነፃ ገበያዎች ሳይኖሩ የገበያ ውድድር ባልነበረበት ሁኔታ፣ ስለምን ዓይነት የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ነበር ሲያወሩና ሲመክሩ ሲመሰክሩ የኖሩት? ወጣት ልጆቻችን ለኑሮ ዋስትና የመሬት ሽሚያ ላይ እስከሚወድቁ ድረስ በአሳሳች ምስክርነታቸው ዕድገታችሁ ያስቀናል ሲሉን ኖሩ፡፡ ዛሬስ ምን ሊሉን ይሆን?
ለእኔ እንደ አገር በቀል ኢኮኖሚስት የሚሰማኝና በብዙ ጽሑፎቼም እንዳስገነዘብኩት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የግል ኢኮኖሚው መሠረታውያን ለብሔራዊ ኢኮኖሚው እጅግ በጣም ደካማና ያስተናገድነው አመፅና ሁከትም ዋና መንዔዎች ናቸው፡፡ ይኼንን እምነቴን በልዩ ልዩ መንገዶች ባለፉት ሁለት ዓመታት አስተጋብቼአለሁ፡፡ ከዚህ በፊት በሪፖርተር ባቀረብኳቸው በርካታ ጽሑፎቼ የኢኮኖሚ ልማት እንደ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አጋዥ መሣሪያ እንጂ፣ እንደ ምትክ ወይም የመጨረሻ ግብ ተደርጎ መቆጠር እንደሌለበት አሳስቤአለሁ፡፡ አሁንም አሳስባለሁ፡፡ የኢኮኖሚ ልማት ለሰው ሥራን በማቅለል በቅልጥፍና እንዲሠራ ያግዘዋል እንጂ፣ እያንዳንዱን ሰው ከነቤተሰቡ አይመግብም፣ አያለብስም፣ መጠለያ አይሰጥም፣ መዝናኛም አይሆንም፡፡
ሰው ሠርቶ ራሱንና ቤተሰቡን ለመመገብ፣ ለማልበስ፣ ለማስጠለልና ለመዝናናት በነፃ ገበያ ውስጥ ተወዳድሮ ኑሮን ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህም በነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ የነፃ ገበያ መሠረታውያንን መለማመድ ከሌሎች ጋር መወዳደር፣ ማሸነፍና መሸነፍን መቀበል ከተሸነፈበት ወጥቶ ወደ የሚያሸንፈው መቀየር እንጂ፣ ገበያው አልተሳሳተም ማለት መቻል አለበት፡፡ አዲሱ ትውልድ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መሠረታውያንን እንዲለማመድ ሳይሆን፣ በተፈጥሮ ያገኘሁትን መሬት ከሌላ አካባቢ የሚመጡ እንዳይጋሩኝ በሚል አደገኛ የሽሚያ አመለካከት እየተቀረፀ ነው፡፡ ዛሬ ብሔረሰብን ማዕከል አድርጎ የተጀመረ ይኼ መሬት የእኔ ብቻ ነው የሀብት ሽሚያ ነገ መንደርን ማዕከል አድርጎ ከነገወዲያ ቤተሰብን ማዕከል አድርጎ፣ ከዚያም ሲያልፍ ግለሰብን ማዕከል አድርጎ ይነሳል፡፡
ወጣቱን ትውልድ የሚያሳትፍ በውድድር ላይ የተመሠረተ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን እንደገና እንደ አዲስ የሚገነባ ሥርዓት መሠረት ካልተጣለ በቀር፣ መንግሥት ጥቂቶች አልምተው ይቀልቡህ በሚል ፍልስፍናው ከቀጠለ የኢኮኖሚ ልማት ወደ ላይ ተሰቅሎ ሰማይ ቢነካም፣ ሀብት እንደ ዝናብ ከሰማይ ቢፈስም፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሙሉ ለመልማታችን ምስክርነት ቢጠሩምና ምለው ተገዝተው ቢመሰክሩም ቀውሱ፣ አመፁና ሁከቱ በሌላ ጊዜ ተመልሶ ለመምጣት ተላለፈ እንጂ አልተወገደም፡፡ በተለይም ደግሞ የቡድን መብትን የሚያቀነቅነው ፌዴራላዊ ሥርዓት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን አስመልክቶ በተነሳው ሁከት ላይ ነዳጅ አርከፍክፎ የአቀጣጣይነት ሚና ተጫወተ፡፡ መሬት የብሔራዊ መንግሥቱ ይሁን የክልል መንግሥታት፣ የአካባቢ መንግሥታት ይሁን ወይስ በቡድን የተደራጁ ወጣቶች መለየት እስከሚያቅት ድረስ ግራ አጋብቷል፡፡ ወደኋላ ተመልሰን እንደ ጥንት አባቶቻችን ‹‹በሚስትና በርስት ቀልድ የለም›› እያልን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ በገዛ አገሩ ለኑሮ ከክልል ወደ ክልል ሲሄድ የውጭ ኢንቨስተር ወይም ስደተኛ መጣ ሊባል ነው፣ ፓስፖርት መግቢያና መውጫ ቪዛም ሊያስፈልገው ነው፡፡
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰው መሬት ለመያዝና ገበሬ ለመሆን የሚፈልገው ሌላ ዘመናዊ የኑሮ አማራጭ ሲያጣ ብቻ ነው፡፡ እንዳይሰደድ ዓለም አቀፍ ኬላዎች የተዘጉበት ወጣት መሰደድ ካልቻልኩ በክልሌ መሬቴ ላይ ከሰፈረው የሌላ ክልል ስደተኛና ኢንቨስተር ነጥቄ እወስዳለሁ አለ፡፡ ምን ይሁን ልሰደድ ብሎ አይኑ እያየ ባህር በላው፡፡ ዓይኑ እያየ የሰው አገር አሸዋ በላው፡፡ አሁን ደግሞ ዓይኑ እያየ የአገሩ ምድር ትዋጠው እንዴ? ለብሔራዊ ኢኮኖሚው የግል ኢኮኖሚው መሠረት መሆን ካልቻለ ብሔራዊ ኢኮኖሚው ከውጭ በሚገኝ ብድር የልማት ሥራና የውጭ ኢንቬስተሮች መጥተው በሚሠሩት የኢኮኖሚ ሥራ፣ ምን ያህል ቢምዘገዘግ ሸንበቆ አደገ አደገ ሲሉት ይሆናል፡፡ ሳይጠነክር የተመዘዘ ጎብጦ ቁልቁል ያድጋል፡፡
ስለግላዊ ኢኮኖሚና ብሔራዊ ኢኮኖሚ መስተጋብርና ትስስር መጽሐፍ ከማሳተምም ባሻገር፣ በሪፖርተር ተሟገት ዓምድ በርካታ ጽሑፎችን ለንባብ አቅርቤአለሁ፡፡ የሚሰማ አንብቦ ከባለሙያ ይሰማል፣ ይማራል፣ የማይሰማ እንደ ሰሞኑ ከመከራ በመከራ ይሰማል ይማራል፡፡ ከመከራም በመከራ አልሰማ ካለ ችግሩ የባሰ ይሆናል፡፡ በሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ አንዱ ቢሊየነር ሌላው ያጣ የነጣ ድሃ የሆኑት በሽሚያ እንጂ በውድድር እንዳልሆነ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መሠረታውያን በኢኮኖሚው ውስጥ አለመስረፅን ጠቅሼ፣ በጽንሰ ሐሳብም በመረጃም አስደግፌ አብራርቼአለሁ፣ አበክሬ አስጠንቅቄአለሁ፡፡ ግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚያችን በሚል ርዕስ በ2007 ዓ.ም. ካሳተምኩት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሁኔታ ባሻገር ይኼ ቀን እንዳይመጣ በሪፖርተር የ2007 ዓ.ም. ግማሽ ዓመትና የ2008 ዓ.ም. ሙሉ ዓመትን በአሥራ ስምንት ወራት ውስጥ አሥራ ሦስት የማስጠንቀቂያ ጽሑፎች በማቅረብ ተሟግቼአለሁ፡፡
የኢትዮጵያ መሪዎቿና ምሁሮቿ እንዳያስተውሉ የዘፈን፣ የስፖርት ወሬ፣ የተረት ተረት፣ ልብ ወለድና ወዝወዝ በሉ መናፍስት እንደ ፈርኦን ልባቸውን ቢያደነድኑትም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሪፖርተር ላይ ስለኢኮኖሚው ከተናገርኳቸው ነገሮች አንዱም መሬት ጠብ አላለም፡፡
‹‹ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ››
መንግሥት የአመፁ ምክንያት የወጣቱ በኑሮው ሁኔታ አለመርካት መሆኑን አውቆ ፀቡን ለማብረድ ለወጣቱ ሥራ ፈጠራ አሥር ቢሊዮን ብር ጥሪት አዘጋጅቼአለሁ ብሏል፡፡ ለወጣቱ ሥራ ፈጠራ ሲባል የተያዘውን ገንዘብ አስፈላጊነት ባምንም ስለውጤታማነቱ ያለኝን ጥርጣሬ ከመግለጽ ግን ወደ ኋላ አልልም፡፡ ጥርጣሬን በማሳየት ሳልወሰንም ጥሪቱን ከመያዝ ጎን ለጎን መታሰብ የሚገባቸውን ጉዳዮች አንድ ሁለት ብዬ አነሳለሁ፡፡ አንደኛ የተያዘው ገንዘብ ወጣቱ በአካባቢው ባሉ ሌሎች አገሮች ጉልበቱን ሽጦ በሁለትና በሦስት ዓመት ውስጥ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚኒባስ ታክሲ መግዣ ገንዘብ ይዞ መምጣት፣ በአገር ውስጥ ሠርቶ ከማደግ ይበልጥ እንደሚጠቅመው በተረዳበት ዘመን መሆኑ ወጣቱን ምን ያህል ሊያማልለው እንደሚችል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ለመነሻ ካፒታል የተበደረውን ለደላላ ከፍሎ ፈትለክ የማይልበት ምክንያት የለውም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ባዶ እጁን ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ወጣት ለሥራ ፈጠራ ሃምሳ ሺሕ ብር ወይም መቶ ሺሕ ብር ብድር ከባንክ ቢያገኝ አሁን ባለው የገበያ ዋጋና የኑሮ ውድነት፣ ከወላጆቹና ከቤተሰቡ ትከሻ ወርዶ ምን በልቶ፣ ምን ጠጥቶ፣ ምን ለብሶ፣ የት አድሮ ነው የተበደረውን ገንዘብ ለኢንቨስትመንትና አዲስ ሥራ ፈጠራ የሚያውለው? ኢንቨስትመንትና ኢንተርፕረኑርሺፕ ከመሠረታዊ ፍጆታ መሟላት በኋላ ይመጣሉ እንጂ አይቀድሙም፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ገንዘቡ ወደ ገበያችን ውስጥ ገብቶ የገንዘብ አቅርቦትን በማብዛት ሸቀጦችን ከማናርና ኑሮን የባሰ ከማክበድ በቀር ለወጣቱ ዘላቂ የኑሮ መሠረት የሚሆን ቋሚ ሥራ ይፈጥራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ ለነገሩ ቋሚ ሥራ የሚባል ነገር አገሪቱን ከከዳት ድፍን ሃያ አምስት ዓመት ሞልቷል፡፡ የያዙትን ሥራ ለዓመት ሁለት ዓመት ይዘው የሚቆዩ የከተማ ወጣቶች ስንቶች ናቸው? ሁሉም ነገር ‹አየር ባየር› ነው፡፡
በአራተኛ ደረጃ ኢንተርፕረኑር የመክሰር ሥጋትን ደፍሮ ገንዘቡን በመዋዕለ ንዋይ መልክ የሚያፈስ ያፈሰሰው ገንዘብም እንዳያከስረው ጥንቃቄ የሚያደርግ ሰው ነው፡፡ ቢከስር የማይጠየቅበትን የባንክ ገንዘብ ወስዶ የሚሠራ ሰው የትኛውን የመክሰር ሥጋትን ደፍሮ ነው ኢንተርፕረኑር ሊባል የሚችለው? አበዳሪ ባንኮችም በኪሳራ ሥጋት ምንም የሚያሳስባቸው ነገር የለም ገንዘቡ ቢከስር በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም የተበላሸ ብድር ተብሎ ይያዛል በቃ፣ ጉዳዩ ይኼው ነው፡፡ በአምስተኛ ደረጃ ወጣቱ የሚያመርተው ምርት ምንድነው? ምርቱን የሚገዛው ሸማችስ ማን ነው? ሸማች ለመፍጠር የሸማቹን ገቢ ማሳደግ ቢያስፈልግ ሸማቹ ባደገው ገቢው የውጭ ምርት ከመሸመት ይልቅ፣ የወጣቶቹን ምርት እንዲሸምት ምን ማድረግ ይቻላል? ከኤክስፖርት ተኮር ፖሊሲዋ ጋር አገሪቱ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ምን አድርጋለች? ቻይና እየከለከለቻት ይሆን እንዴ? ያጠራጥራል፡፡ የቀድሞው ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ሥራ ፈጠራ ሄዶ ሄዶ በየመንገድ ዳሩና በጠባብ ኪዮስኮች በጀበና ቡና ማፍላት ብርቅ ሥራ ተደመደመ፡፡ ቀጣዩ ሥራ ፈጠራና አጓጊ ኢንተርፕረኑርሺፕ በየመንገድ ዳሩ ጠላ ጠመቃ ሊሆን ይችላል፡፡
ኢንተርፕረኑርሺፕና ኢኮኖሚክስ
ኢንተርፕረኑርሺፕ ቁልፍ የኢኮኖሚክስ ቃል ቢሆንም፣ ከሥራ ፈጠራና ከኢንዱስትሪ ዕድገት ጋር ተገናዝቦ ብዙ የመባሉን ያህል ከኢኮኖሚክስ ጋር በተዛመደ ግን ምንም አልተባለም፡፡ ብዙ ሰዎች ዳር ዳሩን ይረግጣሉ እንጂ ኢኮኖሚክስን ይፈሩታል፡፡ ቁጥርን የሚወዱት የኪሳቸውን ብር ለመቁጠር ብቻ ስለሆነ ኢኮኖሚክስ ውስጥ ያለውን ቁጥር እንደ ጦር ነው የሚፈሩት፡፡ ኢንተርፕረኑር ካፒታል ገዝቶ፣ መሬት ተከራይቶ፣ ሠራተኛ ቀጥሮ፣ አደራጅቶና አቀናብሮ ይዞ ለመቆየትም ኃላፊነትን ወስዶ የኪሳራ ሥጋትን በመድፈር ሥራ የሚጀምር፣ የሚመራና የድርጅቱ ህልውናም በእርሱ ጥረት ላይ የሚመረኮዝ ነው፡፡ ከአራቱ የምርት ግብረ ኃይሎች (Factors of Production) አንዱ የሆነ ለአገልግሎቱ ክፍያ መደበኛ ትርፍ የሚያገኝ ሰው ወይም ባለድርጅት ነው፡፡ የኪሣራ ሥጋት ስላለበት ኢንተርፕረኑር እንደማይከስር በጥናት ሳያረጋግጥና ሳያምን በመላምት ብቻ ሌሎቹን የምርት ግብረ ኃይሎች አያደራጅም፣ የንግድ ሥራም አይጀምርም፣ ቢሆንም ሁሌም ጥናቱና ግምቱ ትክክል ይሆናል ማለት ስላልሆነ ለሚወስደው የኪሳራ ሥጋት ድፍረት ክፍያ ትርፍ ያገኛል፡፡
የሸማቾችን ፍላጎት እርግጠኛ ሆኖ መተንበይ በማይቻልበት ሁኔታ ለሚመረተው ዕቃ ገበያ መኖር አለመኖር በመረጃ ሳይረጋገጥ፣ ሌሎች ተመሳሳይ ምርት የሚያመርቱ ድርጅቶች ብዛትና የምርታቸው መጠን በማይታወቅበት ሁኔታ፣ በማይታወቁ የአደጋ አጋጣሚዎች ውስጥ ደፍሮ በተስፋ ግምት (Expectation) ሀብቱንና ጊዜውን በምርት ተግባር ላይ ያውላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የእሳት አደጋዎች፣ የመሰረቅ አደጋዎች፣ የምርት መበላሸት፣ ወዘተ የመሳሰሉ የአደጋ አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ የእሳት አደጋዎች፣ የመሰረቅ፣ የምርት መበላሸት፣ ወዘተ የመሳሰሉት አደጋዎች የመድን ዋስትና በመግባት ከኪሳራ ሊዳን ሲቻል ድርጅቱ የገበያውን ሁኔታ ባለማወቅ ወይም የተሳሳተ ግምት በመገመት ለሚደርስበት ኪሣራ ግን ዋስትና ሊሰጠው የሚችል የመድን ድርጅት አይኖርም፡፡
ስለዚህም ነው አንድ ኢንተርፕረኑር የማይተነበዩና የመድን ዋስትና ሊገባላቸው የማይችሉ የመክሰር ሥጋቶችን ደፍሮ ሀብቱን፣ ዕውቀቱን ጉልበቱንና ጊዜውን በአንድ በመረጠውና ተስፋ ባደረገው የሥራ ዓይነት ስላዋለ ነው፣ የሥጋት መካሻ የማምረት ተሳትፎ ክፍያ ዋጋ መደበኛ ትርፍ (Normal Profit) የሚያገኘው፡፡ ለዚህም የመንግሥት ፖሊሲን በገበያ ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ አጥንቶ የወደፊቱን ስለሚተነብይ ነው ኢኮኖሚክስ በከፊል የተስፋዊ ግምት ጥናት ጥበብ ነው የሚባለው፡፡ ኢንተርፕረኑር ከገቢው ላይ ለመሬት የኪራይ ወጪ፣ ለካፒታል የወለድ ወጪ ለሠራተኛ የደመወዝ ወጪ ከከፈለ በኋላ የሚተርፈው የራሱ ሥጋትን በመቋቋሙ የሚያገኘው መደበኛ ትርፍ ነው፡፡ ይኼ መደበኛ ትርፍም ከሥራ ሥራ ይለያያል፣ ከቴክኖሎጂ ጋርም ይቀያየራል፡፡
ኢንተርፕረኑር ለኪሣራ ሥጋት ከሚገኝ መደበኛ ትርፍ በላይ የሞኖፖል ትርፍም ያገኛል፡፡ እነዚህ የኢንተርፕረኑር መደበኛ ትርፍና የሞኖፖል ትርፍ መጠኖችን መለየትና ማወቅ፣ ከወጪና ከገቢ ዓይነቶች ጋር ማነፃፀር የኢኮኖሚክስ ጥናት መስክ ነው፡፡ ሞኖፖላዊ ትርፍ ለሥጋት ከሚያስፈልገው ትርፍ በላይ የሚገኝ ትርፍ ሲሆን፣ በቂ ውድድር በዘርፉ ውስጥ ባለመኖሩ ምክንያት በዘርፉ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች አቅርቦትን በመቀነስና ዋጋ በማናር ሸማቾችን በዝብዘው ከሚገባቸው በላይ የሚያገኙት ትርፍ ነው፡፡ የሞኖፖሊ ድርጅቶች አቅም የሚፈጥረውም መንግሥት የመሬትና የካፒታል አከፋፋይ ሲሆን ነው፡፡
ይኼ የሞኖፖል ትርፍ ባለፉት ዓመታት እንደ ስኬት ተቆጥሮ በተቋቋምኩ በጥቂት ወራት ውስጥ ሚሊየነር ሆንኩ፣ በአሥር ሺሕ ብር ካፒታል ተነስቼ በዓመቱ አሥር ሚሊዮን ካፒታል አስመዘገብኩ እየተባለ ፕሮፓጋንዳ ሲነዛበትና ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ማማለያ ማስታወቂያ ሆኖ ቆየ፡፡ ጋዜጠኞች ሲጨፍሩና ሲያስጨፍሩ ሲደልቁና ሲያስደልቁ ኖሩ፡፡ የሬድዮና ቴሌቪዥን መገናኛ ብዙኃን ፕሮግራሞች በሚሊዮኖች የሚለካ ትርፍ በሚያስቆጥሩ ሥራ ፈጣሪዎች ሪፖርት ተጥለቀለቁ፡፡ በአካፋ ካልተዛቀ ትርፍ ተገኘ አይባልም፡፡ ከዚያ በታች ማትረፍ ወደ ሥራ የሚጋብዝ አልሆን አለ፡፡ በመቶ ብሮች ይሠራ የነበረ ደላላ እንኳ በሚሊዮኖች ካልሆነ ሺዎችን የናቀበት ዘመን መጣ፡፡ በአንድ በኩል የሚበላ፣ የሚለበስና የሚታደርበት ጠፍቶ በጭንቅ እየኖሩ አቅመ ደካማ እናት አባት ጫንቃ ላይ ተቀምጠው በሌላ በኩል በአጭር ጊዜ ሚሊዮኖች ካላተረፉ ሥራን መናቅ የኢኮኖሚያችን እንቆቅልሽ ሆነ፡፡ ለነገሩ የኑሮ መክበዱ ራሱ ነው ሚሊዮኖች ካልተተረፈ ኑሮን ተስፋ አስቆራጭና ስደትን አስመራጭ ያደረገው፡፡ ሚሊዮን ትርፍ ፍለጋ ሲዞሩ ሚሊዮን ትርፍ ፈላጊ ያጋጥማል፡፡ ገበያዎቻችን ሚሊዮን ፈላጊዎች የሚተራመሱባቸው ሆነዋል፡፡ ሚሊዮን የሰበሰቡ ሚሊዮን ይዘራሉ፣ ሚሊዮን ያጭዳሉ፣ ሚሊዮኖችም ሚሊየነሮችን እያዩ ይናደዳሉ፣ ለአመፅም ይሰናዳሉ፡፡
ስለዚህም ተስፋ እንዲለመልም ኑሮ መቅለል አለበት ኑሮ እስከሚቀልም የኢኮኖሚው ዕድገት መገታት አለበት፡፡ ያለሚሊዮኖች የማንረካ ሰዎች አሥሮችም፣ መቶዎችም፣ ሺሕዎችም ገንዘብ መሆናቸውን ጠንቅቀን እስከምንገነዘብ በምናገኘው የላባችን ዋጋ እስከምንረካ ድረስ ኑሯችን ሊቀል ይገባዋል፡፡ ኑሯችን እንዲቀልልንም የአሥሮች፣ የመቶዎችና የሺዎች ብሮች የመግዛት አቅም ወደ ነበረበት ባይመለስም መጠጋት አለበት፡፡ ወደር የሌለው ትርፍ ፍለጋ በገበያዎች አለመጥራት፣ በሸማቹና በአምራቹ አላዋቂ መሆንና በአቅራቢው የበላይነት መያዝ ምክንያት የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት በፍላጎትና አቅርቦት መጣጣም መስተጋብር አለመሆን ምክንያቶች የመጣ ነው፡፡ ይኼ ሁኔታ ነው በአገራችን ለብሔራዊ ኢኮኖሚው የተመጣጠነ ዕድገት አጋዥ ማዕዘን ሊሆኑ የሚችሉት የግል ኢኮኖሚው መሠረታውያን አለመኖርን የሚያረጋግጠው፡፡ ይኼ ሁኔታም ነው በጊዜ ብዛት አመርቅዞ አመፅና ሁከት የሚፈጥረው፡፡
ይኼንን ደግሞ ያበረታታው መንግሥት ራሱ ነው፡፡ ኢንተርፕረኑር በአጭር ጊዜ ሚሊዮኖችን አትርፎ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ተሸጋግሮ ለመንግሥትም ለኢኮኖሚ ልማት የሚውል የድርሻውን ግብር ማስገባት ይጠበቅበታል ብሎ ሰበከ፣ ለፈፈ፡፡ ከነጋዴው ወስዶ ብዙ ግብር ሰብሳቢዎችን ቀጠረ፡፡ የኋላ ኋላ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብና ቁልፍ ቃል የሆነው የኢንተርፕረኑርሺፕ መሬትና ካፒታልን እየቆነጠረ በሚሰጠው መንግሥታዊ የሕዝብ ሀብት አስተዳደርና በሶሻሊስት ሀብት ይዞታ ሥርዓት ውስጥ እንዴት እንደሚሠራ ግራ አጋባ፡፡ ነጋዴው ከሌለ ግብር ሰብሳቢውም አይኖርም፡፡ ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን እየገነባን ነው ብለን ገበያዎቻችን ከመጥራት ወደ አለመጥራት፣ ከመደበኛ ትርፍ ወደ የሞኖፖል ትርፍ ተጓዙ፡፡ በምርታማነት ያልተደገፈ ሞኖፖላዊ ትርፍ ሀብታሙን ሲያከብር ድሃውን አደኸየ፡፡ የደኸየውም በአመፅ ሁኔታውን ካልቀለበሰ መኖር እንደማይችል አምኗል፡፡ አመፅን ትናንትም ሞክሯል፣ ዛሬም እየሞከረ ነው ነገም ሊሞክር ይችላል፡፡
ማጠቃለያ
ኢንተርፕረኑሮች ለኪሣራ ሥጋት መካሻ የሚሆን መደበኛ ትርፍ እያገኙ ወደ ማምረት ተግባር እንዲገቡ፣ ገበያዎች ካለመጥራት ወደ መጥራት እንዲጓዙ፣ ሸማቹና አምራቹ አዋቂ ተገበያዮች እንዲሆኑ፣ ዋጋዎች እንዲሰክኑ፣ ለአዳዲስ ድርጅቶች መቋቋሚያና የመነሻ ካፒታልና የመሬት ዋጋ ወጪ እንዲቀንስ፣ የኢኮኖሚው ዓመታዊ ዕድገት ለተወሰነ ጊዜ ዝቅ ማለት አለበት፡፡ ለዚህም ተስማሚ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ መንደፍ ያስፈልጋል፡፡ ለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለተመሳሳይ መጠን የዋጋ ንረት ሲባል እስከ ዛሬ በየዓመቱ ከሃያ እስከ ሃያ አምስት በመቶ ሲያድግ የቆየው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት (Money Supply) ከምርት ዕድገቱ ይልቅ ለዋጋ ንረቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላበረከተ በዓመት በተወሰነ መጠን ብቻ እንዲያድግ በማድረግ የታሰበው ዝቅ ያለ የዕድገትና የዋጋ ንረት ደረጃ ላይ ሊደረስ ይቻላል፡፡
የገንዘብ አቅርቦት መጠኑን ተከትሎ ዝቅ የሚለው የኢኮኖሚው ዕድገት የመንግሥት ፕሮጀክቶችን፣ የግል አምራቾችን፣ ሸማቾችን፣ ምን ያህልና ለምን ያህል ጊዜ እንደሚጎዳና እንደሚጠቅም በጥናት ሊረጋገጥ ይችላል፡፡ ዋናው ነገር እንደ ጥንቸል እየሮጡ ያላዩት ገደል ውስጥ ከመግባት እንደ ኤሊ ተጉዞ ግብ ላይ መድረስ ይሻላል ነው፡፡ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገት ይቀንስ ማለት ቀላል ነገር እንዳልሆነ እገነዘባለሁ፡፡ የአገሪቱ የመካከለኛ ዘመን ዕቅድም አምስት ዓመታት ሙሉ በተከታታይ ባለሁለት አኃዝ ዕድገት ለማስመዝገብ ነው፡፡
በአጭር ጊዜ መካከለኛ ገቢ ለመግባት በህልም ቅቤ የመጠጣት አባዜ ናላችን ዞሮ፣ ድህነቱ ተባብሶ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ ከመግባት ነባራዊ እውነቱን እንመልከት፡፡ በመሠረቱ ዕቅድ የሚታቀደው የኢኮኖሚውን ውስጣዊ መስተጋብሮች ነባራዊ ሁኔታን መርምሮ መሆን ቢኖርበትም፣ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶቹ በኢኮኖሚ ልማት ትርጉማቸው የመንግሥትን መሠረተ ልማት መገንባትና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የመስጠት አቅም መሠረት ያደረጉ እንጂ፣ የኢኮኖሚውን ነባራዊ ሁኔታ ያልመረመሩና ያላገናዘቡ መሆናቸውን ከዚህ ቀደምም በጽሑፎቼ አስገንዝቤአለሁ፡፡ ልማትን፣ የኢኮኖሚ ልማትንና የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን ፍልስፍናዎችና አካሄዶች ለያይተን ካልተገነዘብንና ለሁሉም በቂ ትኩረት ካልሰጠን ረጅም መንገድ አንጓዝም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው Getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
