በአበበ ተክለሃይማኖት (ሜጀር ጄኔራል)
ባለፉት 25 ዓመታት ኢትዮጵያ ሰላም ባጣው በምሥራቅ አፍሪካ የሰላም ተምሳሌት ሆና የራሷን ሰላም አረጋግጣ ለሌሎች የምትደርስ አገር ሆናለች፡፡ እሰዬው፡፡ ይህ ሰላም የመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ውጤት ነው፡፡ የተሟላ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት አፅድቀው መተግበር በመጀመራቸው ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችንና የግለሰብ መብቶችን አጣምሮ በተሟላ ሁኔታ የሚያረጋግጥ ሕገ መንግሥት በከፊልም ቢሆን መተግበር ሲጀምሩ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማምጣት ድህነትን በተነፃፃሪ ፍጥነት በመቅረፍ ዴሞክራሲያዊ የአገር ግንባታ ተያያዙ፡፡
ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ ለማድረግ ባደረጉት ያልተቆጠበ ጥረት ሰላም ማረጋገጥ ሲጀምሩ፣ በአንፃሩ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ሲሸረሸር በተለያየ ደረጃ የሚገለጽ የሰላም ማጣት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ በሰላም ላይ አደጋ ሊከሰት የቻለበት አንዱ ምክንያት የዴሞክራሲ እጥረት፣ የተጠያቂነት መጥፋት፣ የሕግ የበላይነት መዳከም፣ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል፣ የሙስና መስፋፋት ወይም የፍትሕ ማጣት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ሌላው የሁሉም ድክመትና ድምር ጥፋት ያመጣው ነው ሊል ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ግን ሕገ መንግሥታችንን መተግበር ሰላም እንዳመጣ ሁሉ፣ ሲሸረሸርም ለሰላም ማጣት ዋነኛ ምክንያት ይሆናል፡፡
ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባለመከበራቸው፣ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ሥርዓቱ ያስቀመጠላቸውን ግዴታ መወጣት ባለመቻላቸው፣ ሰላም፣ ፈጣንና ቀልጣፋ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በመረጋገጡ እየተፈጠሩ ካሉት ማኅበራዊ ኃይሎች ፍላጎት ጋር ተጣጥሞ መሄድ ያልቻለው ፖለቲካዊ ሥርዓት ወደኋላ በመጎተቱ ምክንያት መረጋጋት እየታጣ ሄዷል፡፡ አዲሱ ትውልድ ለሚያነሳው ጥያቄ አሮጌው አመራር የሚመጥን መልስና ፖለቲካዊ መፍትሔ ማቅረብ ባለመቻሉ ቅራኔ ተፈጥሯል፡፡
በውስጥ ችግሮቻችን ምክንያት ሁከቱ ተፈጠረ፡፡ ፅንፈኛ ኃይሎች ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር ተባብረው የሕዝቦችን ተቃውሞ ወዳልሆነ አቅጣጫና ወደ አመፅ ቀየሩት፡፡ በርካታ የሰው ሕይወት ጠፋ፣ ንብረት ወደመ፣ የልማት ተቋማት ጋዩ፣ ጠላቶቻችን ጊዜያችን አሁን ነው ብለው አቀጣጠሉት፡፡ ሁከት ቀጠለ፡፡ ለ25 ዓመታት የተገነቡት ተቋማት የተነሱትን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ባለመቻላቸውና በሰላማዊ መንገድ ማካሄድ ስላልቻልንና ስለተሸነፍን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር እንገኛለን፡፡ ይኼ ሽንፈት ነው፡፡ ከዚህ ሽንፈት እንዴት እንወጣለን የሚለው መፍትሔ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአማርኛው፣ በእንግሊዝኛው “article 93, Declaration of state of emergency” በጉዳዩ ላይ የተጻፉ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት ሁለቱ አገላለጾች በተለይ ‹‹አስቸኳይ ጊዜ›› እና “emergency” የሚሉት ቃላት መስማማታቸውን ለባለሙያዎች በመተው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ/ደንብ ዓይነት፣ ተፈጥሮ፣ ዓላማና ውጤቱ ላይ አስተያየት መስጠት ተገቢ ይመስለኛል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ (emergency) ዓይነቶች
በሁለት መሠረታዊ ዓይነቶች ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊና በወታደራዊ ክስተቶች ምክንያት የሚታወጁ ደንቦች/አዋጆች፡፡
ማኅበረ ኢኮኖሚ ስንል በተፈጥሮ ወይም ሰው ሠራሽ አደጋ ምክንያት በዋናነት በማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ላይ የሚደርስ ቀውስ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ጎርፍና ማዕበል፣ ከፍተኛ ድርቅ ወይም በሽታ ወይም ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት የሚፈጥሩዋቸውን ቀውሶች በአጭር ጊዜ ለመፍታት የሚደነገጉ አዋጆች ናቸው፡፡ ይህን ቀውስ ለመታደግ የአገሪቱን የሰውና ተፈጥሯዊ ሀብት ለማንቀሳቀስ ያለምንም እክልና ጊዜ የማይወስድ መፍትሔ ለማምጣት ሲያስፈልግ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማገድና በተወሰነ ደረጃ ኃይል መጠቀምን የሚያሳዩ ክስተቶች ናቸው፡፡
ሁለተኛው ፖለቲካዊና ወታደራዊ የሚባል ሆኖ ኃይልን በኃይል የመመከት ባህርይ ሲሆን፣ ዋናው ፖለቲካዊና ወታደራዊ ኃይል የሚለው እንደ ሁኔታው ደረጃው የሚለያይ ነው፡፡ ዋናው ኃይል መፍትሔ ሆኖ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች የሚጠይቁ፣ ሌሎች ደግሞ ዋናው ፖለቲካዊ ሆኖ በኃይል የሚታጀቡ ናቸው፡፡ የአገር መወረር ፖለቲካዊ አንድምታ እንኳን ቢኖረውምና ዲፕሎማቲክ ሥራዎች ቢኖሩትም፣ ዋናው መፍትሔው ወታደራዊ ነው፡፡ መፈንቅለ መንግሥት በተመሳሳይ ሊታይ ይችላል፡፡
የውስጥ አመፅ ወይም የእርስ በርስ ጦርነት ግን ወታደራዊ ገጽታና የግጭት መልክ ቢኖረውም ቁምነገሩ ግን ፖለቲካዊ ነው፡፡ መነሻውም መፍትሔውም ፖለቲካዊ ነው፡፡ በሕዝቦችና በመንግሥት መካከል የሚኖረው የመብትና ግዴታ በተሟላ መንገድ አለማሟላት ነው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ሆነ በደርግ ጊዜ የነበረው የአገሪቱ ቀውስ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታችንን ይረጋገጥልን የሚል ሲሆን፣ ገዢዎች ደግሞ እነዚህን መብት ለጠየቀ መልሳቸው ኃይል በመሆኑ የእርስ በርስ ጦርነት ተጧጡፎ ባለመብቶቹ አሸንፈዋል፡፡
በ2008 ዓ.ም. የተከሰተው ሁከትም የዴሞክራሲ፣ የፍትሕና የእኩልነት ጥያቄ መነሻ የፈጠረው እንቅስቃሴ ነው፡፡ ገዢውን ፓርቲ በየደረጃው በሰላማዊ መንገድ መታገል እየጠበበ በመምጣቱ፣ የመንግሥት ተቋማት ለሚነሱት ጥያቄዎች የሚመጥን መፍትሔ መውሰድ ባለመቻላቸውና የወጣቶች ችኩልነትና ግልፍተኝነት ተጨምሮበት በፅንፈኞችና በውጭ ጠላት ኃይሎች ቆስቋሽነት የተካሄደ ነው፡፡ መነሻው ፖለቲካዊ ሆነ በሁከት የተደራጀ ሁከት ለማቀዝቀዝ ኃይል በሚያስፈልገው ቢሆንም ዋናው መፍትሔ ግን አሁንም ፖለቲካዊ ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጥሮ
በዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶች በ‹‹ብሔራዊ ደኅንነትና በሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መካከል ቀጣይነት ያለው ቅራኔ (tension) መኖሩ የግድ ነው፡፡ የአመፅ ቀውሶች እነዚህን መሠረታዊ የሆኑ መብቶች የሚፃረሩ በመሆናቸው ሥርዓቱ ራሱን ለመከላከል ግድ ይለዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ራሱን ከማጥፋት ለመከላከል መደራጀት አለበት፡፡ የሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 93 ራሱን በኃይል ከሚንዱት ለመጠበቅ ማለትም ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ አንቀጽ ግን ዴሞክራሲያዊ የሆነን ሕገ መንግሥት ለመከላከል የተደራጀ ነው፡፡ የሕዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለመጠበቅ ለአጭርና ለተወሰነ ጊዜ ቢሆንም፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በጠቅላላ የተወሰኑ ሰብዓዊ መብቶችን በተወሰነ ደረጃ ይነፍጋል፡፡ ምን ዓይነት ምፀት ነው?
አምባገነን በሆኑ ሥርዓቶች ግን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁኔታዎ ሁልጊዜም የሚኖሩና ስታንዳርድ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማያረጋገጥ አገር የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሁልጊዜ እንዳለ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ መንግሥት ተቃውሞን ውጤታማ በሆነ መንገድ በመከላከል አምባገነን ሥርዓቱን የመጠበቅ እንጂ፣ የሕዝቦችን መብቶች ማረጋገጥ ደንታ ስለሌለው ሁልጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚኖር ታሳቢ ሊደረግ ይችላል፡፡
ሰብዓዊ መብቶች የሚረጋገጡት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲረጋገጡ ብቻ ነው፡፡ ሕዝቦች ሰብዓዊ መብቶቻቸውን የሚያስጠብቁት ዲሞክራሲያዊ መብቶችን መሠረት አድርገው በሚያደርጉት ትግል ነው፡፡ ከመንግሥት የሚሰጥ ስጦታ (መና) ከሆነ ግን ዘላቂነት የሌለውና አባታዊ (Paternalistic) ነው የሚሆነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ሥርዓት በሕገ መንግሥትና በሕገ መንግሥት መንፈስ የወጣ አዋጅ እስከሆነ ድረስ ልክ፣ ‹‹ልጅህ ራሱን ለመግደል ሲከጅል እንዳይሞት ሽጉጡን ለመንጠቅ እጁን በጥይት መምታት ያህል ነው›› ክፉኛ ይቆስላል፣ ያሳምመዋል፡፡ ከሁኔታው ጋር የሚሄድ ዝግጅት ካልተደረገ ደግሞ ደሙ እየፈሰሰ ሊሞት ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ እጁን ለመምታት ተብሎ ልቡን ወይም ራሱን ከተመታ ሊሞትም ይችላል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝቦች መብትንና ሥርዓቱን ለመጠበቅ ተብሎ የሚያቆስልና የሚያሳምም ከሆነና ዝግጅት ካልተደረገ፣ ወይም የተወሰደው ዕርምጃ ተመጣጣኝ ካልሆነ የሕዝቦችን መብት መጠበቅና ሥርዓቱን መታደግ መሆኑ ቀርቶ ‹‹የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች›› እንደሚባለው ሊሆን ይችላል፡፡ ፀረ ዴሞክራሲ ሊያገነግን ይችላል፡፡ አዋጁ ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት የግድ በሚል ነው፡፡ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ችግሮቻችንን ለመፍታት ስላልቻልን የመጣ አስፈላጊ ግን የሽንፈት መንገድ ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታሳቢ ዓላማዎች
አዋጁ ወላፈንን ያዳፍናል እንጂ እሳቱን ሊያጠፋ አይችልም፡፡ ችግሩና መፍትሔው ፖለቲካዊ ነው ማለታችን የተፈጠረው ሁከት የእሳቱ ወላፈን መሆኑን በመገንዘብና ረመጡ የሚጠፋው ወይም እንዳይቀጣጠል የሚያደርገው ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን በማመን ነው፡፡ አዋጁ የእሳቱ ወላፈን እንዳይፋጅ በመከላከል ዓላማና መሠረታዊ የሆኑ ችግሮች የሚፈቱበት የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር እንጂ፣ ከዚያ በላይ የሚቆም ዓላማ ሊኖረው አይችልም፡፡ ጊዜያዊ መፍትሔ ስለሆነም፣
- የሁከቱ ዋና ተዋናይ የሆነው ወጣት ዓመፅ ማስነሳቱ ወይም መሳተፉ ወይም ደግሞ መደገፉ ስህተት መሆኑን የሚያምንበት ሒደት መሆን ይኖርበታል፡፡ በፅንፈኞችና በወራሪዎች ላይ አይቀጡ ቅጣት የሚያስፈልግ ቢሆንም ምናልባት 99 በመቶ የሚሆነውን ወጣት በሚመለከት መቅጣት ሳይሆን ማስተማር፣ በተደረገው ተመጣጣኝ ዕርምጃ ተማምኖ ጥያቄዎች ፍትሐዊና ሕገ መንግሥታዊ ቢሆንም አካሄዱ ግን ስህተት እንደነበረ አምኖ አዋጁ ሲነሳ እፎይ ብሎ፣ ሕዝቦችንና መንግሥትን አመስግኖ ወደ ልማቱ የሚዘጋጅበት ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አብዛኛው ወጣት ጥቃት ደርሶብኛል ካለ ግን መሠረታዊ ቅሬታና ቂም ይዞ ስለሚወጣ አዋጁ ዓላማውን አላሳካም ማለት ነው፡፡
- በብሔሮችና ብሔረሰቦች እየታየ ያለው መጠራጠር የሚቀንስ ካልሆነም ባለበት የሚገታ መሆን አለበት፡፡
አዋጁ ‹‹መጣልን›› የሚሉ እንደሚኖሩ ሁሉ ‹‹መጣብን›› የሚሉ እንዳይኖሩ ከመጀመሪያው ግምት ውስጥ አስገብቶ እንደየአካባቢው ሁኔታ እጅግ በጣም ብዙው ሕዝብ መጣልን እንዲል መደረግ ይኖርበታል፡፡ እነዚያ መጣልን የሚሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ያላግባብ መጠቀሚያ እንዳያደርጉት መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡
እንደየአካባቢው ሁኔታ ብሔር/ብሔረሰቦች ልዩ ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
- አዋጁና አተገባበሩ ማዕከላዊነት ያለው በመሆኑ ከፌዴራል ሥርዓቱ ጋር ግጭት አለው፡፡ ልክ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን በዴሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ ለመታደግ የሚደረግ ሙከራ ያለው ዓይነት ግጭት ነው፡፡ የአዋጁ ዓላማ ሰላም ከማስፈን ጎን ለጎን ብሔር ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን የሚወክሉ ክልሎችና ልዩ ዞኖች ሥልጣንና ግዴታ በመጠበቅ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተጠናክሮ እንዲወጣ ማድረግ ይገባል፡፡
ምንም እንኳን ሕገ መንግሥቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን ተከትሎ ከአባላቱና ከሕግ ባለሙያዎች መርጦ የሚመድባቸው ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ያቋቁማል የሚል ቢሆንም፣ መፍትሔውን በዘላቂነት ለማምጣት ችግሩ የተከሰተባቸው ቦታዎች ላይ ያሉ ሕዝቦች ዋነኛ የችግሩ የመፍትሔ አካላት ተደርገው ሊወሰዱ ይገባል፡፡ የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት ከምክር ቤቱና ከሕግ ባለሙያዎች ከሚመረጡት ሰባት አባላት በተጨማሪ፣ ችግሩ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤት አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ እናቶች፣ ወጣቶችና በሕዝቡ ዘንድ አመኔታና ከበሬታ ያላቸው ከልዩ ልዩ ሙያዎች የተውጣጡ ግለሰቦች የችግሩ አፈታት በውስጡ ቂምን ያረገዘ እንዳይሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማድረጉም በላይ፣ በሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ዋስትና እንዲያገኝ የላቀ ሚና ይጫወታሉ፡፡
ኪራይ ሰብሳቢነትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
አውቶክራቲክ (ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ አካሄድ) የግድ ቢልም ከረዥም ጊዜ አንፃር በሚገባ ካልታየ አደገኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢዎች አውቶክራቲክ አካሄድን ይወዱታል፡፡ መሸሸጊያቸው ነውና፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አውቶክራቲክ አካሄድ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሰፋ፣ ጥልቀት እንዲኖረውና ቀጣይነት እንዲለብስ የተመቻቸ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ይመጋገባሉ፡፡
ስለዚህ በመንግሥት ደረጃ የሚደረገው የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል የተለየና ጥልቀት ያለው መሆኑን ተገንዝቦ መታገል ያስፈልጋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊ ቢሆንም የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ በከፍተኛ ደረጃ ሊያኮላሸው ይችላል፡፡
መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነት ተጠናውቶኛልና እታገለዋለሁ ብሎ ዝግጅት በጀመረበት በዚህ ጊዜ ሁኔታው አስገድዶት አስቸኳይ ጊዜ ታዋጀ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት እንኳንስ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ ይቅርና የተሟላ ዴሞክራሲያዊ ምኅዳር ባለበት እንኳን ተግዳሮቶቹ ከፍተኛ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ማሸነፍ የሚቻለው ዴሞክራሲያዊ ምኅዳሩ በማስፋት ነው፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይነፍጋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ኪራይ ሰብሳቢነትን በተሟላ ሁኔታ መታገል አይቻልም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢዎች እንዲያሸንፉ የተመቻቸ ሁኔታ ይፈጥራልና፡፡
የመንግሥት ሥልጣን ለግል መጠቀሚያነት በሽታ እስከ ቀበሌ (ሚሊሻ) ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢዎች ጊዜያችን አሁን ነው ብለው የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት ከማናቸውም በላይ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ቂም በቀል፣ ዛቻ፣ ወዘተ መሣሪያቸው ይሆናል፡፡ ሕዝቡ ተበድያለሁ ብሎ እንዳይናገር አይቀጡ ቅጣት ሊያወርዱበት ይከጅላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በሕዝቡ ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጭ እየሰፋ ይሄዳል፡፡
በአጠቃላይ መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነት ዋናው ችግሬ ብሎ ባወጀበት ወቅት፣ ሁከት ተፈጥሮ ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መተዳደርም የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉን እጅግ የሚያወሳስብና የሚያራዝመው መሆንን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ከላይ ጀምሮ በየደረጃው እስከ ቀበሌ (ሚሊሻ) ድረስ የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ኪራይ ሰብሳቢዎች የተሻለ ጊዜ መጥቶልናል በማለት ዳንኪራ ሊመቱ ይችላሉና፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት የሲቪል/ፖለቲካዊ ቁጥጥር ወሳኝነት
ባደጉት አገሮች ቀውስ ቢኖርም ባይኖርም ሲቪል/ፖለቲካዊ ቁጥጥር ለዴሞክራሲ ሥርዓቱ አለኝታ ነው፡፡ በማደግ ላይ ላሉ አገሮች ግን ወሳኝ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማቱ ገና ያልተደላደሉ በመሆናቸው፣ የሕዝቡ ንቃተ ህሊና ያልዳበረና ድርጅቶች ደካማ ስለሆኑ ራሱን መከላከል አይችልም፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት የሥልጣን ክፍፍሉ የሚዳከምበት፣ ሥራ አስፈጻሚው የመሪነት ሚና ስለሚወሰድ ሌሎቹ የመንግሥት አካላት ጥግ የመያዝ ዝንባሌ ይታይባቸዋል፡፡ ሆኖም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት በአንቀጽ 93 መሠረት ሥራ አስፈጻሚው የደነገገውን አዋጅ በመሻር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ አንቀጽ በንዑስ አንቀጾች 5 እና 6 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በማቋቋም ሒደቱን የሚከታተልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ምክር ቤቱ አዋጁ በማፅደቅ/በመሻር፣ ብቃትና ማንነታቸውን ያረጋገጡ አባላት ለመርማሪ ቦርድ በመመደብ ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል በማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሚፈለገው በላይ እንዳይቀጥል በመወሰን ለሕገ መንግሥቱ፣ ለህሊናውና ለሕዝቡ ብቻ እንዲያገለግል በልዩ ሁኔታ ልዩ ዕድል ያገኘ ይመስለኛል፡፡
በቀውስ ወቅት መደናገጥ፣ ፍራቻ፣ ጥላቻና ስሜታዊነት ሊጎለብቱ ቢችሉም ዋናው ችግር ግን ሕዝቡና መሪዎቹ አገሪቱ እየገጠማት ያለውን ቀውስ በትክክል መገምገማቸው ላይ ነው፡፡ ወይ ቀውሱን አሳንሰው ያዩትና የበለጠ እንዲሰፋና አደገኛ እንዲሆን ያደርጉታል፡፡ አልያም ቀውሱን በጣም አጋንነው በመገምገም አውቶክራቲክ አካሄድ እንዲጠነክርና ጊዜውም እንዲራዘም በማድረግ የሚያመረቅዝ አደጋ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ እያንዳንዱ አላስፈላጊ የአዋጁ ቀን ደም የምናነባበት ስለሚሆንና መሠረታዊ ችግሩም የሚያመረቅዝ በመሆኑ፣ በተቻለ መጠን የአዋጁን ጊዜ ማሳጠሩ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በሚዛናዊነት እየገመገሙ ፈጣን የማስተካከል ዕርምጃ ይጠበቃል፡፡
ለቀውሱ ምክንያት ፖለቲካዊ ነው፡፡ መሠረታዊ መፍትሔውም ፖለቲካዊ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም እሱ የወከለው ኮማንድ ፖስት ከማናቸውም ጊዜ በላይ ፖለቲካዊ ቁጥጥሩ መጎልበት አለበት፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያላግባብ ተግባራዊ ቢደረግ ጥፋቱ ከፍተኛ ስለሚሆን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቀድሞ የኢሕአዴግ ታጋይና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
