Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

ይድረስ ለክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ

$
0
0

‹‹የሠራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የሚለው መጽሐፍ ይታገድ!

በአበበ ተክለሃይማኖት (ሜጀር ጄኔራል)
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር
በተለያዩ ጊዜያት ለመጠቆም እንደሞከርኩት አንዳንድ ጊዜ እንደ ተቋም ሌላ ጊዜ በከፍተኛ መኮንኖች ፀረ ሕገ መንግሥት የሆኑ ድርጊቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ የአገራችን መከላከያ ተቋም ሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥቱን ብቻ መሠረት አድርጎ መንቀሳቀስ ሲገባው በግላጭ ሕገ መንግሥቱን የመጣስ ክስተቶች እየታዩ ነው፡፡ አንድ ፀረ ሕገ መንግሥት ተግባር ሲጠቆም በማረም ፈንታ በማናለብኝነትና በኅብረት በባሰ ሁኔታ እየተደገመ ነው፡፡ ለምን? የሠራዊቱ አመራሮች ሕገ መንግሥቱን ጠንቅቀው አያውቁም ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ አሁን ሥራ ያሉ ከፍተኛ መኮንኖች ሌላ ጊዜ በጡረታ የተሰናበቱ ‹‹እንዲሁም እንከን በሌለው መተካካት›› የተገለሉ ከፍተኛ መኮንኖች ጋር ለመወየያት ዕድል አጋጥሞኛል፡፡ ከወርቃማው የ1997 ዓ.ም. አጠቃላይ ምርጫ በኋላ ሕዝቦችን ለመቆጣጠር እንደ ተወሰዱት ፀረ ዴሞክራሲያዊ ፖለሲዎች፣ መመርያዎች፣ አሠራሮችና ተግባሮች በመከላከያ ተቋም ገብተዋል እንዴ? የሚል ጥያቄ ሲያጭርብኝ ቆይቷል፡፡ ሕገ መንግሥቱን መፃረር የሠራዊቶችን ሕዝባዊነት፣ ጀግንነትና ብቃት የሚሸረሽር በመሆኑና ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግሉን የሚያበላሽ በመሆኑ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚያሳስብ ነው፡፡ ‹‹የሠራዊቱ ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ›› የሚለውን ጽሑፍ ሳነብ ግን መሠረታዊ ችግሩ በከፊልም ቢሆን የት ላይ እንደሆነ ሊገለጥልኝ ቻለ፡፡ ሠራዊቱ የገዥው ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም አራማጅ የኢሕአዴግ ‹‹የመጨሻው ምሽግ›› እንዲሆን ወይም ‹‹ቀባሪው›› እንዳይሆን መገንባት ከተጀመረ አገሪቱን ወደ ከፍተኛ ችግር ማስገባት ግድ ሆኗል፡፡ የፓርቲው ውስጣዊ ፖለተካዊና ዴሞክራሲያዊ ሕይወት በተዳከመበት ሁኔታ ደግሞ የተወሰኑ አመራሮች ‹‹የመጨረሻ ምሸግ›› ይሆናል ማለት ነው፡፡ በመከላከያ ሚኒስቴር ሥር የሚገኙው ‹‹ብራና ማተሚያ ድርጅት›› የታተመው መጽሐፍ 209 ገጾች ያሉት ሲሆን፣ ሕገ መንግሥቱንና ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የሚለውን ርዕዮተ ዓለም በማደባለቅና በማምታት ስለሠራዊት ግንባታ ይዘባርቃል፡፡
ክቡር የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ
መጽሐፉ ‹‹የሠራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ነው የሚለው፡፡ ሰነዱ ከእሱ ጀምሮ ምን ማለት መሆኑ ቢታወቅም የበለጠ ግልጽ ለማድረግ የተለያዩ ጥቅሶችን ማስቀምጥ ይበጃል ከሚል ስለሆነ እንዲፈቀድልኝ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡ በገጽ 20(2፡3) የመከላከያ ኃይል ግንባታ ዓላማችን በሚል ርዕስ፣ ‹‹እኛ የያዝነው ዓላማና ተግባራዊ ያደረግነው ያለመደብ በአገራችን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጦች እንዲካሄዱ ይህ ሥርዓት ሥር እንዲሰድ ማድረግ ነው፡፡›› በገጽ 22 ‹‹እኛ የምንገነባው የመከላከያ ኃይል ለአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ዘብ ነው ብለን በግልጽና በጥሬው ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው፤›› ይላል፡፡ ምን ዓይነት እብሪት ነው? ‹‹ለአንድ ፓርቲ ዘብ በመሆን መልክ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ከፓርቲው ውጭ ሆነም ሥርዓቱን እንደ ሥርዓት ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመጠበቅ አንፃር ሊገለጽ ይችላል፡፡ (23)››
‹‹በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ደኅንነት መከላከል ማለትና የአገር ደኅንነት መከላከያ ማለት በመሠረቱ አንድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከሌለ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ልማትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ወዘተ. አይኖርም፡፡ ይህ ከሌለ ደግሞ አገሪቱ መጨረሻ ወደሌለው ቀውስና ግጭት ገብታ መበታተን ነው፡፡ ስለሆነም አገሪቱ እንደ አገር መቀጠል የምትችለው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው ማለት ይቻለል፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ አገራችንን መከላከልና አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መከላከል አንድና የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡›› (25.26)
‹‹ስለሆነም ለእኛ የአገራችን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ደኅንነት መከላከል (መጠበቅ) የተለያዩ ነገሮች አይደሉም፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ከሌለ እኛ የምንላት አገር አትኖርም፡፡›› (27) የምንገነባቸው በመከላከያ ኃይል ዓላማው የሥርዓታችንን ደኅንነት መጠበቅ ነው ሲባል የሚገነባውና የሚመራው የሥርዓቱ መሪ የሆነው አካል ብቻ መሆን አለበት ነው፡፡›› (28) ‹‹የመከላከያ ኃይላችን ግንባታ ሥራ ዓላማው ምን እንድሆነና ከዚህ የሚመነጩ የመከላከያ ኃይላችን ባህሪያት ምን እንደሚሆኑ በግልጽ ለያይቶ ማስቀመጥ በዚያች ቁርጥ ቀን ማለት የሥርዓታችን ሕልውና በመከላከያ ኃይላችን ብቃትና ምንነት ላይ በምትንጠላጠልበት ጊዜና ወቅት አስተማማኝ መከላከያ ምሽግ መሆኑን በማረጋገጥ በኩል ወሳኝ ሚና ያለው ጉዳይ ነው፡፡ (ገጽ 31) ‹‹ጉዳዩ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሥርዓቱ በመጨረሻ መከላከያ ምሽግ የሌለው ሥርዓት ሆኖ እንዳይቀር በማድረግ ወይም በመከላከል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ጠባቂዬና አለኝታዬ ብሎ የሚለው ሠራዊት ተመልሶ ቀባሪው ሆኖ እንዳይገኝ የማድረግ ጭምር ነው፡፡›› (ገጽ 81)
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር
የኢትዮጵያ መከላከያ ተቋም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ብሎም የኢሕአዴግ ‹‹ጠባቂ›› እንዲሆን፣ በሌላ አነጋገር የጥቂት ሰዎች ‹‹ጠባቂ›› እንዲሆን በተለያየ መንገድ፣ በጭንቀት፣ በልመና የተደጋገመው ጸሎት አይሉት ምህላ በጣም እንደሚሰለች ይገባኛል፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝ፡፡ እኔም ስልችት እያለኝ ነው ደጋግሜ ያነበብኩት፡፡ የመከላከያ ተቋም በምን መልኩ ከሕገ መንግሥታችን ተፃራሪ ሆኖ እየሠራ መሆኑን እንዲያሳይ ነው እንጂ፡፡ ሕገ መንግሥታችን በውል መጠቀስ የተጀመረው በገጽ 87 ነው፡፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ‹‹የቁርጥ ቀን›› መከላከያ መሆኑን በተደጋጋሚ ካስረገጠ በኋላ፣ በ2.1 ሕገ መንግሥታችን እንደ ሠራዊታችን ግንባታ መነሻ በማለት ማብራራት ይጀምራል፡፡ መዘባረቁን በሚያሻማ ሁኔታ እየቀጠለ ፀረ ዴሞክራቲክ አስተሳሰብ ደግሞ ከደርግነት ባላነሰ መንገድ ሲገልጸው እንደገና፣ ‹‹ኢሕአዴግ ከሌለ ይህች አገር የለችም›› በሚለው አባባል ሲያመላልሰው ይታያል፡፡ እባክዎ በስፋት እንድጠቅስ እንደገና ይፍቀዱልኝ፡-
‹‹ሕገ መንግሥታችን ለሠራዊት ለፖለቲካ ግንባታ ሥራችን ወሳኝ መነሻ ነው በምንለው ሕገ መንግሥታችን፣ ሠራዊቱ የሕገ መንግሥቱ ታማኝ ጠባቂ መሆን አለበት በማለት በግልጽ ስለሚያስቀምጥ ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶች እንዲህ ዓይነት አካሄድ ስላልተከተሉም አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህ አባባል በሕገ መንግሥታችን በግልጽ እንዲቀመጥ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት ሕገ መንግሥቱ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጠባቂ የሆነ ሠራዊት ለመገንባት ለሚካሄደው የፖለቲካ ግንባታ ሥራ በቂና ብቁ መነሻ እንዲሆን ስለታመነበት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ቀደም ብሎ እንደተመለከትነው በሁሉም አገሮች በመከላከያ አቅም በሚገነባው አንድን ሥርዓት ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ለመከላከል ተብሎ ነው፡፡ በእኛ ሁኔታም የተለየ ዓላማ ሊኖርው አይችልም፡፡ እኛ የምንገነባው ሠራዊት አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ለመከላከል ተብሎ በሚገነባ ሠራዊት ብቻ ነው መሆን የሚችለው፡፡ በአሁኑ ወቅት አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንና ኢሕአዴግ ተለያይተው ሊታዩ የሚችሉ አይደሉም፡፡ የሊበራል ዴሞክራሲ አስተሳሰብ የበላይነት በነገሠበት ወቅት ሁሉም ፓርቲዎች ማለት ይቻላል መሠረታዊ የሊበራል ዴሞክራሲ አስተሳሰቦችን ተቀብለው፣ በዚህ ዙሪያ ብቻ ነው የሚለያዩት በየጊዜው እየተቀየሩ ወደ ሥልጣን ቢመጡም በሥርዓቱ ላይ የሚመጣ መሠረታዊ ለውጥ የለም፡፡ ስለሆነም ሥርዓቱ ከእያንዳንዱ ፓርቲ ተለይቶ የሚታይና ሊታይ የሚገባው ይሆናል፡፡›› (ገጽ 88 እስከ 89)
ክቡር የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ
የ1997 ምርጫ ሕዝቦቻችን ዕድል ሲያገኙ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ያሳየ ነው፡፡ በቀጣዩ ምርጫ ለምሳሌ መድረክ ቢያሸንፍ የመከላከያ ሠራዊታችን በኢሕአዴግ የቁርጥ ቀን በመሆን መድረክን ሥልጣን እንዲቆጣጠር ይከላከሉ? ጠመንጃቸውን በሕዝቦች በተመረጠና በሕዝቦች ላይ ያዞራሉ ማለት ነው? መድረክ በሊበራል አስተሳሰቦች ዙሪያ የተደራጀ በመሆኑ በምርጫ ካሸነፈ አሁን ያለውን መከላከያ ተቋም እንዳለ አፍርሶ ሌላ የራሱን ሊገነባ ማለት ነው? የሆነ ፓርቲ በሰላማዊ መንገድ ባሸነፈ ቁጥር በሚፈርስና የሚገነባ የመከላከያ ተቋም ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም፡፡ ለተወሰኑ ሰዎች ለኢሕአዴግ ኃላፊዎች ሲባል አገራችንን ለማፍረስ መዘጋጀት ማለት እኮ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ አብዮታዊም ዴሞክራሲያዊም አይደለም፡፡ በእኔ አረዳድ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ‹‹ሊበራል ዴሞክራሲ መራመድ እስከሚችለው ጫፍ መውሰድ ነው፡፡›› በሌላ አነጋገር አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከሊበራል ዴሞክራሲ በላይ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ የሕዝቦቻችንን የመወሰን ሥልጣን በተሻለ የሚያምን ነው፡፡ እኛ ካልተመረጥን አገሪቱ ገደል ትግባ የሚል የጽንፈኞች አስተሳሰብ መሆን አልነበረበትም፡፡
ክቡር የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በእውነትና በቅንነት የታመነበት ቢሆን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምን ማለት እንደሆነ ትርጉም ይሰጠው ነበር፡፡ በአሀኑ ጊዜ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምንነት በአንዳንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ሳይቀር የማይታወቅ መሆኑን በየቀኑ በቴሌቪዥንም በአካል እያስተዋለ ነው፡፡ አንድ ቀን ያጋጠመኝን ላካፍልዎ፡፡ ሦስት ሆነን ስለኢትዮጵያ ሁኔታና ስለአንድ መሪ ስናወራ የልማት መሪም አርበኛም (Champion) ናቸው በሚለው ተስማማን፡፡ አንዱ ተነስቶ የልማት አርበኛ ብቻ ሳይሆኑ የዴሞክራሲ ሻምፒዮን ናቸው አለ፡፡ ሦስተኛው ተነስቶ እስኪ አብራራው አለው፡፡ በጥርነፉ (Centralism) ያምናል አለን፡፡ አፈርን፣ ተሳቀቅን፡፡ ግን ስለዴሞክራሲ ያለው አመለካከት እስከዚያ ድረስ የወረደ መሆኑን በየቀኑ የምናየው ክስተት በመሆኑ አዝነን ይህች አገር ወዴት እየሄደች ነው አልን፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር
አሁንም በተለያዩ መንገዶች የአገር መከላከያ ተቋምና የኢሕአዴግ አባላት የሥራቸውና የአኗኗራቸው ሁኔታ የተለያየ በመሆኑ መጠነኛ የአቀራረብ ልዩነት ይኖር ይሆን እንጂ አንድ ናቸው ለማለት ከገጽ 100 እስከ 101 እንዲህ ይለዋል፡፡ ‹‹በሠራዊታችን የምናካሂደው የፖለቲካ ሥራ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ግንባታ ሥራ ነው፡፡ ስለሆነም መሠረታዊ የአፈጻጸም አግባብ በድርጅታችን ውስጥ ከምናካሂደው የግንባታ ሥራ የተለየ አይሆንም፡፡ ይህ እናዳለ ሆኖ ሠራዊቱና የኢሕአዴግ አባላት የሥራቸውና የአኗኗራቸው ሁኔታ የተለያየ መሆኑ አይቀርም፡፡ ከዚህ የተነሳ በሁለቱም የግንባታው ሥራ አፈጻጸም አንዳንድ ልዩነቶች ሊኖሩት የግድ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ በፖለቲካ ግንባታ ሰፊ መሠረታዊ አፈጻጸሞች እንዳለ ነው የምንወስደው፡፡ የሚዲያው ሥራ በገዛ ራሱ ለኅብረተሰቡ በሚዘረጋውና ሠራዊቱም እንደማንኛውም ሰው በሚሰማው ወይም ገዝቶ በሚያነበው በመንግሥትና በድርጅት ሚዲያ አማካይነት ሊፈጸም ይችላል፤›› ገጽ 116 የግል፣ የሌሎች ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንስ?
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በመጽሐፉ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለማንሳት የሚያስችሉ የተዘበራረቁ ጉዳዮች አሉ፡፡ ‹‹እኛ›› ብለው ስለሠራዊታችን ግንባታ የሚጽፉት አመራሮች ‹‹የቁርጥ ቀን›› ደራሽ እንዲሆንላቸው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሽፋን በማላወስ እኛን አገልግሉ ከማለት ውጪ፣ ያስቀመጡዋቸው የተለዩ የግንባታ ዓላማዎችና አቅጣጫዎች የሉም፡፡ ከሞላ ጎደል ‹‹በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ›› የተቀመጡ ናቸው፡፡ በአደባባይ ለሕዝብ በቀረበው ፖሊሲ ግን ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም የኢሕአዴግ የመጨረሻ መከላከያ ምሽግ አይልም፡፡›› ለምን? ሕገ መንግሥቱ በሰላም እስከታገሉ ድረስ ሕገ መንግሥቱን ራሱን የማሻሻል መብት የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ከበላይ ሕጋችን አኳያ ሁሉም በሰላም የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች እኩል ናቸው፡፡ በሠራዊቱ ልዩ ጥበቃ የሚያስፈልገው ፓርቲ ወይም የሚገለል ወይም የሚመታ ፓርቲ የለም፡፡ የሚገርመው ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕገ መንግሥቱ ይከበር ሲሉ የሕገ መንግሥቱ አቀንቃኝ የነበረው ኢሕአዴግ በግላጭ ሲሸረሽር ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› እንደ አድኃሪያን መሸሸጊያ ሲጠቀምበት በጣም ያሳዝናል፡፡ ገዥ ፓርቲ በመሆኑ ደግሞ ያስፈራል፡፡
አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚል ‹‹ምትሀተኛ›› አስተሳሰብ እንዳለና እጅግ የላቀ ልዩ ነገር ‹‹Mystify›› ተደርጎ የማይተነተን የማይታወቅ ሰው በጭፍን እንዲያምነው የሚደረግ ሙከራ አሳሳቢ ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ይሁን ሊበራል ዴሞክራሲ ሁሉም ካፒታሊስታዊ ሥርዓት ለመገንባት ዓላማ አድርገው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ያውም እስከ ‹‹ነጭ ካፒታሊዝም›› ተብሎ ነበር፡፡ በካፒታሊስት ሥርዓት ከማንም በላይ ተጠቃሚዎች ካፒታሊስቶች ናቸው፡፡ እስከሚገባኝ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሚገባ ከተተገበረ የገበሬዎች፣ የላብአደሮችና የሌሎች ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥቅም በሚረጋገጥበት መንገድ ሥርዓቱን ሊመራ ይችላል፡፡ ሀብት በመፍጠር ሒደት ክፍፍሉ በተቻለ መጠን ፍትሐዊ ማድረግ ነው፡፡ እንደዚያውም ሆኖ አሁንም ዋናው ተጠቃሚ ካፒታሊስቱ ነው፡፡ አሁን እየተመዘገበ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ብቻ እንኳን ብናይ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚዎች ቢሆኑም፣ በሀብታምና በደሃ መካከል ያለው ልዩነት በጣም እየሰፋ ከመሄድ አላገደውም፡፡ ባልሆነ ተስፋ በማይመስል አስተሳሰብ አገር እንዳይጎዳ መጠንቀቅ ጥሩ ነው፡፡
በገጽ 126 ያለውን እስኪ እንየው፡፡ ‹‹ሁሉም በተራ ውትድርና እንዲያልፍ የሚደረግ አሠራር ከሠራዊታችን ባህሪ ጋር የሚሄድ ብቻ ሳይሆን ለሠራዊታችን የተለያዩ ጥቅሞችም የሚያስገኝ ይሆናል፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ይህ አሠራር ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ በከፍተኛ ደረጃ የማይጠቀሙ ወገኖች ወደ ሠራዊቱ በመግባት ፍላጎት እንዳይኖራቸው የሚያደርግና በአንፃሩ በሥርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖች ብቻ ሠራዊቱን እንዲቀላቀሉ የሚያደርግ አካሄድ ነው፡፡››
ይህ ደግሞ ሌላ አስመሳይነት ይመስለኛል! ከሥርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ የማይጠቀሙ ወገኖች ሲባሉ እነማን ናቸው? መሳፍንት? አሁን የሉም የመሳፍንት ልጆች፡፡ ኧረ ተዉ! ኢሠፓ የነበሩ እነሱም ወሳኝ ሚና የላቸውም፡፡ የሚቀሩት ገበሬ፣ ላብአደር፣ ምሁር፣ ካፒታሊስት፣ ወዘተ. ናቸው፡፡ ገበሬው መቼም አይታሰብም፡፡ ላብአደር ተጠቀሚ ተብሏል፡፡ ካፒታሊስቱ የለም፡፡ እሱማ ዋናው ተጠቃሚ ነው፡፡ ምሁሩ ኧረ እንጃ፣ እንዳይፈነግላቸው እየፈሩ ካልሆነ እሱም በጣም ተጠቃሚ ነው፡፡ ታዲያ በከፍተኛ ደረጃ የማይጠቀሙ ወገኖች እነማን ናቸው? ፖለቲካዊ ሥርዓቱ የራሱን ችግር ላለማየት (Externalize) ለማድረግ የሚደረድራቸው ጠላቶች እንዳይሆኑ፡፡ ትምክህትና ጠባብነት በኅብረተሰቡ በሚታዩ ኋላቀር አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ የተወሰኑ ልሂቃን ይህን በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ኋላቀር አስተሳሰብ መሠረት አድርገው ለራሳቸው ጥቅሞች ሲሉ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ሥርዓቱን እንዲናጋ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህንም ቢሆን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ለእነሱ መሠረት የሚሆነው የዴሞክራሲ አስተዳደር እጥረት ነው፡፡ እነዚህን ለማግለል ደግሞ የሠራዊቱን ሙሁራዊ አቅም እየገደለ እንዳይሆን መፈተሹ ተገቢ ነው፡፡
ወደ ሠራዊታችን በመጀመሪያ የሚሠለፈው ከ18 እስከ 23 ዓመት አከባቢ ያለ ወጣት ነው፡፡ የወላጆቹን የመደብ ጀርባ እያዩ ላለማስገባት አሥረኛ ክፍል አስገብቶ በሠራዊቱ በሚደረግ ግንባታ ከፍተኛ አመራር ለመፍጠር በሚደረግ እንቅስቃሴ አደገኛ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የተማረ ሰው የመጥላት አዝማሚያ እንዳይሆን፡፡
‹‹እኛ›› በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አነጋገር አንድ ሰው ነው፡፡ ምናልባትም ንጉሣዊ ቤተስብ ይሆናል፡፡ ‹‹እኛ›› ማለት ከአንድ ሰው በላይ ቢሆን ማነው? 36ቱ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ? የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላት? ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ አባላት ቢሆኑስ? የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ልዕልና እንዳልነገሠ መጽሐፉ በተደጋጋሚ ይገልጽልናል፡፡ ስለዚህ ቢያንስ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ሠራዊታችን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የመጨረሻ ምሽግ እንዲሆን አልወሰነም፡፡ የሠራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ያለው ‹‹እኛ›› አድኃሪ ነው፣ ፀረ ዴሞክራቲክ ነው፣ ፀረ ሕገ መንግሥት ነው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ
በእኔ አመለካከት ሠራዊታችን የሕዝቦቻችንና የአገራችን አለኝታ የሚሆነው ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥቱን መሠረት ተደርጎ የሚወጣ ፖሊሲ፣ መመርያ፣ አሠራራርና ግንባታ ሲኖር ነው፡፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የመጨረሻ ምሽግ ነው ሲባል ግን የሠራዊቱ ምልመላ፣ ሥልጠና፣ ዝውውር፣ ዕድገትና ጡረታ ማራዘም፣ በመተካካተት የሚገለሉት፣ እንዲሁም አጠቃላይ ግንባታ ‹‹በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ›› መዝሙር በሚዘምሩና ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ወሬ በሚያቀብሉ ሕገ መንግሥቱን በግላጭ የሚጥሱ አባላት ያሉበት ሠራዊት እንዳይሆን ሥጋት አለኝ፡፡ በአጠቃላይ ከሕዝቦቻችን በተለይም ደግሞ ከፖለቲካ ድርጅቶች የሚኖረው ግንኙነት በጣም አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
የኦሮሞ ሕዝቦች ለመብታቻው ባደረጉት ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ለደረሰው ጉዳት እርስዎ ይቅርታ ሲጠየቁ በኢትዮጵያ ውስጥ ባልተለመደ መንገድ ሕዝብን የሚያከብር በመሆኑ፣ ለሕዝብ ይቅርታ በማለት ፈር ቀዳጅ በመሆንዎ ብዙዎቻችን ኮርተናል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተወሰደው ዕርምጃ ‹‹ተመጣጣኝ›› ነው ሲል እንደገና አፈርን፡፡ ፓርላማው ሲያፀድቀው የባሰ ተሸማቀቅን፡፡ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን በማበላሸት ዋናው ተጠያቂ የኢሕአዴግ መንግሥት ሆኖ እያለ፣ በዜጎች ላይ የደረሰው ጉዳት ተመጣጣኝ ሲባል ያሳዝናል፡፡ እነዚያ የሞቱት፣ የቆሰሉት፣ የታሰሩት በሙሉ አሸባሪዎች ናቸው ማለት ነው?
በአጠቃላይ የሥርዓቱ ጉዳይ ግን እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤታችን ስለመከላከያ በየጊዜው የሚገመግመው ‹‹እንደ መከላከያ የለም የሚያሰኝ ነው››፡፡ እንዲህ ያለመሠረታዊ የግንባታ ዶክመንትና ሕገ መንግሥቱን በሚፃረር መንገድ የሠራዊቶቻችን ግንባታ ሲካሄድ ‹‹ዓይኑ እንዳላየ›› ‹‹ጆሮው እንዳልሰማ›› ማወደስ የማይሰለቸው ተቋም መሆኑና በእርስዎም የሚመራው የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱም ከዚህ አኳያ ቢፈተሽ መልካም ይመስለኛል፡፡
ሠራዊታችን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የመጨረሻ መከላከያ ምሽግ ነው የሚለው አስተሳሰብ፣ ኢሕአዴግ ከሌለ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሉም፡፡ የዚህች አገር ችግሮች በኢሕአዴግ ብቻና ብቻ ይፈታሉ፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከሌለ አገር የምንለው የለም፡፡ የሕገ መንግሥት ምሰሶ ከሆኑት አንዱ ተቋም የሆነው መከላከያችን ከየትኛውም ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት ወገንተኝነት ነፃ ይሆናል የሚለውንና የሕገ መንግሥቱ አንኳር የሆነውን የመድብለ ሥርዓት ግንባታ የሚፃረር ይሆናል የሚለውን አስተሳሰብ የወለደ በመሆኑ፣ እነዚህ የግንባታ ጽሑፎች እንዲወገዱ ነገር ግን የሕገ መንግሥት ጠማማ አተረጓጎም ለአገር ጥፋት እንዴት እንደሚውል የሚያሳይ በመሆኑ ግን እኛም ልጆቻችንን እንድንማርበት በሙዚየም ውስጥ እንዲቀመጡ፡፡ በአስቸኳይ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወሰድና በአጠቃላይ መከላከያ እንደ ተቋም እንዲፈተሽና ሥርፀት (Reindoctration) እንዲደረግ እንደማንኛው ዜጋ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቀድሞ የኢሕአዴግ ታጋይና የአየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles