በደረጀ ተክሌ
ኢትዮጵያን ከ1923 እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ የመሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በዚህ ወር ሐምሌ 16 ቀን 2008 ዓ.ም አንድ መቶ ሃያ አራተኛ ዓመት የልደት በዓላቸው በአድናቂዎቻቸው ዘንድ ይከበራል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ከዚህ በፊት ስለ ንጉሠ ነገሥቱ በተጻፉት ጽሑፎች ላይ ተጨማሪ ጽሑፍ በማቅረብ ታሪካቸውን ለመደረት ሳይሆን፣ በሚወዷቸውና በሚጠሏቸው ጸሓፍት ግራና ቀኝ ተወጥሮ የተጻፈውን የፍቅርና የጥላቻ ስሜት በማያንፀባርቅ ሁኔታ፣ በክፉም ሆነ በደግ በታሪክ የተመዘገበውን የንጉሠ ነገሥቱን ገጽታ በአጭሩ ለመዳሰስ ነው፡፡
በ1884 ዓ.ም ሐረርጌ ውስጥ ኤጀርሳ ጎሮ በምትባል መንደር የተወለዱት ተፈሪ መኮንን በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እናታቸውን ወ/ሮ የሺእመቤትን በጨቅላነታቸው፣ አባታቸውን ራስ መኮንንን ደግሞ በአሥራ ሦስት ዓመት የሕፃንነት ዕድሜያቸው ያጡ አብሮ አደግ ወንድምና እህት ያልነበራቸው ሲሆን፣ ከአባታቸው ልጅ ከደጃዝማች ይልማ መኮንን ጋርም የሕፃንነት ዘመን አላሳለፉም፡፡
በወቅቱ የሐረርጌ ገዢ የነበሩት አባታቸው ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል (አባ ቃኘው) ከሣህለ ሥላሴ ንጉሠ ሸዋ ከሚወለዱት እናታቸው ከልዕልት ተናኘ ወርቅ ሣህለ ሥላሴና ከአባታቸው ከአቶ ወልደ ሚካኤል ጉዲሳ የሚወለዱ ሲሆኑ፣ በተመሳሳይ የትውልድ ሐረግ ከንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴ ለሚወለዱት ለዳግማዊ አፄ ምኒሊክ (አባ ዳኘው) የአክስት ልጅ ነበሩ፡፡ ራስ መኮንን ተፈሪን ገና ትምህርት ሲጀምሩ የፈረንሣይኛን ቋንቋ እንዲያጠኑ በማድረጋቸው ንጉሡ በሥልጣን ዘመናቸው ከአማርኛ ቀጥሎ ፈረንሣይኛን እንደ አንድ መግባቢያ ቋንቋ ይጠቀሙበት እንደነበር ይታወቃል፡፡
በልጅነታቸው የጭምትነት ባህርይ ይንፀባረቅባቸው እንደነበር የሚታወቁት ተፈሪ፣ በ1897 ዓ.ም አባታቸው በማረፋቸው ምክንያት የሐረርጌ ግዛት ለወንድማቸው ለደጃዝማች ይልማ መኮንን ሲተላለፍ እሳቸው ከሐረርጌ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተደርጎ፣ ለአምስት ዓመታት ያህል አዲስ አበባ በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት ውስጥ የቤተ መንግሥት ሥርዓት በቅርብ እየተከታተሉ አድገዋል፡፡
ታላቅ ወንድማቸው ደጃዝማች ይልማ መኮንን ከሦስት ዓመታት በኋላ ሲያርፉ ሐረርጌ ከሲዳሞ ጋር እንዲቀላቀል ተደርጎ በወቅቱ የሲዳሞ ገዥ ለነበሩት ለደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ) ተላልፎ በተደራቢነት ሲተዳደር ቆየ፡፡ ይሁን እንጂ ከሁለት ዓመታት በኋላ በ1902 ዓ.ም በእቴጌ ጣይቱ አሳሳቢነት ሐረርጌ ለደጃዝማች ተፈሪ እንዲተላለፍ በመወሰኑ፣ በ18 ዓመት ዕድሜያቸው ወደ ሐረር በመዛወር እስከ 1909 ዓ.ም የልጅ ኢያሱ መንግሥት መውደቅ ድረስ ግዛቱን ሲያስተዳድሩ ቆዩ፡፡ በ1909 ዓ.ም የልጅ ኢያሱ መንግሥት በሸዋ መኳንንት ሴራ እና በቀሳውስቱ ድጋፍ ሲገረሰስና ዘውዲቱ ምንሊክ በንግሥተ ነገሥታትነት ሲሾሙ፣ ከዚያ በፊት ባልተለመደ ሥርዓት ተፈሪ መኮንን የንግሥቲቱ አልጋ ወራሽ ሆነው በመሾም በ25 ዓመት ዕድሜያቸው ወደ አዲስ አበባ ጠቅልለው መጡ፡፡
ተፈሪ መኮንን በአልጋ ወራሽነት ሥልጣን ላይ በነበሩበት የ13 ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በውጭ ፖሊሲ በኩል አገሪቱን ወደ ዘመናዊ አስተዳደር ለማምጣት፣ በአውሮፓ ለመጀመርያ ጊዜ በከፍተኛ ባለሥልጣን ደረጃ ጉብኝት በማድረግና በአገር ውስጥ ከነበሩ ኤምባሲዎች ጋርም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ ታላላቅ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፉ የመንግሥታቱ ማኅበር ቀደምት አፍሪካዊት አገር በማድረግ በአባልነት አስመዝግበዋታል፡፡
በአገር ውስጥም አንፃራዊ ዘመናዊነት እንዲፈጠር ለማድረግ ያደረጉት ጥረት በቀላሉ የሚገመት አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ያከናወኗቸው አብዛኛዎቹ ስኬቶቻቸው በቆየው የባሕላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ለኖረ ኅብረተሰብ ተቀባይነታቸው አናሳ ከመሆኑም በላይ፣ በንግሥቲቱ ዘንድ በጥርጣሬ ሲታዩ በመሳፍንቱና በመኳንንቱ ዘንድ ደግሞ በሥውርም ሆነ በግልጽ የመረረ ተቃውሞ ይገጥማቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡
በ1921 ዓ.ም የንግሥቲቱን አስተዳደር የአስገዳጅነት መንፈስ በተላበሰ የማሳመን ዘዴ ከራስነት ወደ ንጉሥነት ማዕረግ ከፍ ያሉት ንጉሥ ተፈሪ በነበሩበት የአልጋ ወራሽነት መንበራቸው ከዲፕሎማሲያዊ ስኬታቸው በተጨማሪ፣ ሁለት የአገር ውስጥ ማለትም የሰገሌንና የአንቺም ጦርነቶችን በማሸነፍ የልጅ ኢያሱንና የንግሥት ዘውዲቱን ደጋፊዎች አንበርክከዋል፡፡ ከዚህም በላይ የውስጥ ተቃዋሚዎቻቸውን አንድ በአንድ ከጨዋታ ውጭ እያደረጉ በመምጣታቸውና በታሪካዊ አጋጣሚም ሥልጣናቸውን በጥርጣሬ ይከታተሉ የነበሩት ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስና አቡነ ማቴዎስ በተከታታይ በማረፋቸው የተነሳ፣ በ39 ዓመት ዕድሜያቸው ወደ ንጉሠ ነገሥትነት ሥልጣን ሲመጡ በሙሉ የአሸናፊነት ስሜት ነበር፡፡
በትዳራቸውም በኩል ለወሎው ንጉሥ ሚካኤል የልጅ ልጅ ለእቴጌ መነን አስፋው ሦስተኛ ባል ሲሆኑ፣ ከእኚሁ በቁንጅናቸውና በደርባባነታቸው ከሚታወቁ ወይዘሮ ስድስት ልጆች ወልደዋል፡፡ በቁመት አጭር ከሚባሉት ተርታ የሚሠለፉት አፄ ኃይለ ሥላሴ እጅግ መልከ መልካም ሲሆኑ በእነዚያ በጣም ረጃጅም በሆኑት ክብር ዘበኞቻቸው መካከል ሲታዩ የእሳቸው ግርማ ሞገስ ጎልቶ መታየቱ አስገራሚ ነበር፡፡ የ43 ዓመታት ረጅም ዘመን የንጉሠ ነገሥትነት አመራራቸው በአብዛኛው የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት ሲሆን፣ በግላቸውም የሚከተሉት ፍልስፍና እንዲሁ የሰከነ ነበር፡፡
ማለዳ ቤተ ክርስቲያንን ከመሳለም የሚጀምረው የየዕለቱ ተግባራቸው የውጭ አገር ከፍተኛ ባለሥልጣኖችን በመቀበል የልማት መሠረት ለመጣል፣ በሕዝባቸው መሀል በመገኘት የተመራቂዎችን ልብስ ለብሰው ወጣቶችን በመመረቅ፣ በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ጋዜጣዊ መግለጫ የመስጠት ተግባሮቻቸው ጎልተው የሚታዩ ነበሩ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ለየት የሚያደርጋቸው ታድያ ይኼ ሁሉ ሲከናወን የባህርይ መለዋወጥ አለመታየቱ ነበር፡፡
ንጉሡ አዲስ አበባ ካሉ ከማለዳ ቤተ ክርስቲያን ፀሎትና ከእራት በኋላ የሚታዩ የምሽት ፊልም ፕሮግራሞች ምንግዜም አይቀሩም፡፡ አመጋገባቸው በዛ ያለ ቁርስና ለስለስ ያሉ አትክልት የሚበዛባቸው መጠነኛ ምሳና ራት ሲሆኑ፣ መጠኑ አነስተኛ የሆነ ሻምፓኝ ወይም ወይን ይጠቀማሉ፡፡ ጥሬ ሥጋ ባይመገቡም የሚመገብ ሰው ማየቱ ያስደስታቸዋል፡፡ ፀሐይ ረገብ ስትል በቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የእግር ጉዞ በማድረግ ሰውነታቸውንም ሆነ አዕምሮአቸውን ያዝናናሉ፡፡ የጠቅላይ ግዛት ጉዞ ካደረጉ ደግሞ እዚያው በሚያድሩበት ቤተ መንግሥት ማምሻውን ከሚቀርቧቸው ዕውቅ ሰዎች ጋር (ከ1953 ዓ.ም. በፊት እቴጌይቱንና አባ ሃናን ይጨምራል) በጥቂት ብሮች ካርታ በመጫወት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ በንግግራቸው ውስጥ መረር ያለ ቃል ላለመናገር በእጅጉ የሚቆጠቡት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ፈገግ ያሉለትም ሆነ ወስላታ በሚል ቃል የሸነቆጡት ባለሥልጣን ሁለቱም ተደስተው እንዲውሉ የማድረግ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡
የብዙ ኢትዮጵያውያንን ልብ ለማማለልና የግል ሰብዕና ለመገንባት የጋዜጦች የፊት ዓምድና የሬድዮ ግንባር ቀደም ዜና የመሆንና ራሳቸውንና ራሳቸውን ብቻ ከፍ የማድረግ ፍቅር እንደነበራቸው የሚታወቁት ንጉሠ ነገሥት፣ ስሜታቸውን የመቆጣጠር ብቃትና ጠላታቸውን ሚስጢራዊ በሆነ ሁኔታ ጠልፎ ለመጣል ያላቸው ልዩ ችሎታ በቀላሉ የሚገመት አልነበረም፡፡ ይኼ ልዩ ችሎታቸው እንደሳቸው ለውጥ አፍቃሪ በነበሩት ልጅ ኢያሱ ላይ በሰላም ወቅት ባከናወኑት መረጃን የማሰባሰብና የማሰባጠር፣ ከዚያም በችግር ጊዜ አቀናጅቶ በመጠቀም የማሸነፍ ብቃታቸው ተረጋግጧል፡፡ ከዚህም አልፎ የሚቀናቀኑዋቸውንና እኛም የንግሥ ዘር አለን የሚሉትን በዝምድና መረብ ውስጥ በማስገባት ዋነኞቹን በቅርብ ለመቆጣጠር፣ ከአልጋው አጠገብ አስቀምጠው ግዛቱን በእንደራሴ ማስገዛታቸው ለየት ያደርጋቸዋል፡፡ የሥልጣናቸውን አንዲት ነቁጥ መስጠት እንደማይፈልጉ ለማስታወስ ደግሞ ጸሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስን አንስተው የመወርወር ያህል ከሥልጣን ሲያነሱ የተጠቀሙባቸው ሥልቶች ስለጃንሆይ ማንነት መመስከር ይችላሉ፡፡
በአጨካከናቸው ደግሞ ደጃዝማች በላይ ዘለቀን ከእነ ወንድማቸው በአደባባይ ለመስቀል ከባንዶች ጀርባ መሠለፋቸው፣ በእነ ቢትወደድ ነጋሽ በዛብህ መዝገብ ቀርበው ከ1943 እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ለ23 ዓመታት በብረት ሰንሰለት ታስረው የነበሩትን የእነ አለቃ ፈጠነን እስር ማስታወሱ፣ እንዲሁም በጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ መዝገብ ተከሰው ፍርድ ቤት እስር የፈረደባቸውን ሻምበል ክፍሌ ወልደ ማርያምንና የመቶ አለቃ ድጋፍ ተድላን በሞት መቅጣታቸው ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡ እስካሁን መላ ያልተገኘላቸው የንግሥት ነገሥታት ዘውዲቱ፣ የሌተና ጄኔራል መርዕድ መንገሻ፣ የሠዓሊ አገኘሁ እንግዳ፣ የተማሪ ጥላሁን ግዛውና የጋዜጠኛ አሳምነው ገብረ ወልድ ድንገተኛ ሕልፈቶች፣ መሰል ሚስጢራዊ ግድያዎችና አፈናዎች የእሳቸው ዕውቀት እንዳለባቸው ይጠረጠራል፡፡
ጃንሆይ የአገሪቱን የወደፊት ፖሊሲ ለመቅረፅም ሆነ የተቀረፀውን ወደ ግብ ለማድረስ በአማካሪነት የሚጠቀሙባቸው ኃይሎች በሁለት ይከፈላሉ፡፡ እነዚህም በአንድ ወገን በነባሩ የባላባት አስተዳደር ታቅፈው ከጥንቱ ከመሠረቱ አብረዋቸው የመጡት ሲሆኑ፣ በሌላው ወገን በኩል ደግሞ በእሳቸው ዘመን ተምረው ለሥልጣን የበቁና በአንፃራዊነት ወጣት የሆኑት ናቸው፡፡ ጃንሆይ እነዚህን ሁለት በዘመንና በአመለካከት ልዩነት በጣም የሚናናቁ ክፍሎች በተለያየ ሁኔታ በመያዝና ቅራኔያቸውን በመጠቀም፣ ከእነሱም ሆነ ከሌላ ከማይታወቅ አቅጣጫ ወደሳቸው የሚወረወረውን ትችት አቅጣጫ ሲያስቱና “እሳቸው ምን ያድርጉ” የምትሰኘውን አማላይ ሐረግ ሲያንሸራሽሩ ኖረዋል፡፡
በዘመናቸው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደ ሰው ደስታም ሐዘንም ጎብኝቶዋቸዋል፡፡ ሐዘናቸው ግን ከሌሎች ሐዘኖች ይለያልም ይከብዳልም፡፡ እናታቸውንና አባታቸውን በሕፃንነት ወራቸው የተነጠቁት ንጉሠ ነገሥት ባልተሟላ የቤተሰብ ፍቅር ውስጥ በብቸኝነት ማደጋቸው ሳያንስ፣ በዕድሜ ጎልምሰው ትዳርም ሥልጣንም ከያዙ በኋላም ይኸው ሐዘን ከቤታቸው ባለመውጣቱ መሪር ሐዘን በማስተናገድ አብዛኛዎቹን ልጆቻቸውን በተከታታይ ቀብረዋል፡፡ በተደጋጋሚ በሐዘን የተጎዱት እኚህ ሰው ልጅን መቅበር ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ በሚያሳይ ሁኔታ እንደ ንጉሥ ሳይሆን እንደ አባት ወላድ ይፍረደኝ ብለው በአደባባይ አልቅሰው አስለቅሰዋል፡፡ እሳቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ በሕይወት የነበሩት ልጆቻቸው ሁለት ብቻ ነበሩ፡፡ በተጨማሪም የብዙ ዘመን ባለቤታቸውን ለረጅም ዓመታት በፅናት ሲያስታምሙ ቆይተው በሞት ሲለዩዋቸው፣ በመጨረሻዎቹ የአዛውንት ዕድሜያቸው ለ13 ዓመታት በብቸኝነት ኖረዋል፡፡
ጃንሆይ በቀደመው የአልጋ ወራሽነትና የንጉሠ ነገሥትነት ዘመናቸው ከብዙ መኳንንቶቻቸውና መሳፍንቶቻቸው አንፃር ሲታዩ (ልዑል ራስ እምሩን አይጨምርም) አንፃራዊ ዘመናዊ አመለካከት ነበራቸው፡፡ በዚህም አመለካከታቸው ብዙዎች ባለሥልጣኖች ለንጉሡ በጎ ስሜት አልነበራቸውም፡፡ ይኼ ስሜት ሰብዕናን ከመፈታተንም አልፎ እስከ ማስወገድ በሚደርስ ጥረት ተመንዝሯል፡፡ ይኼንን ለመከላከልና የዚህ የተራማጅ አስተሳሰባቸው ደጋፊ የሚሆን ምሁር ለመፍጠር ባልተለመደ ሁኔታ፣ የትምህርት ሚኒስትርነቱን ሥልጣን ደርበው በመያዝ በአገሪቱ ትምህርትን በማስፋፋት ሥራ ላይ ተጠምደው ኖረዋል፡፡ በማብቂያ ዘመናቸው ግን ያለመታደል ሆኖ እንዲያግዙዋቸው የፈጠሯቸው ምሁራን ተራማጅ ሆነው እሳቸውን በአድኅሮት ጎራ መድበው ታገሉዋቸው፡፡ ይኼ ሁኔታ ንጉሡን የሁለት ዘመን ትውልድ አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት በቀደመው ዘመን ተራማጅ፣ በአዲሱ ዘመን ደግሞ አድኃሪ አድርጎ ወገን አልባ አደረጋቸው፡፡
ሰው ለሰው መድኃኒት እንደሆነ ሁሉ ቁስልም ይሆናል፡፡ የጃንሆይ አስተዳደር ወደ ውድቀት እያዘመመ መምጣቱን በማሳየት ለለውጥ እንዲዘጋጁ የሚጠቁሙዋቸው ኃይሎች የመኖራቸውን ያህል፣ ከሕልፈታቸው በኋላም እንኳን ቢሆን ይህቺኑ አገር በአጥንታቸው እንደሚመሩ እየማሉና እየተገዘቱ የሚነግሩዋቸው ዜጎችም ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ በትክክል ከተመዘነ ለንጉሠ ነገሥቱ ክብርና ለአገሪቱ ሰላም የማሰኑት የመጀመርያዎቹ ጠቋሚዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የ1948ቱ የጸሐፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ዘመናዊ አደረጃጀት ምክረ ሐሳብ፣ የ1953ቱ የጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት አንግቦ የተነሳው ሕገ መንግሥታዊው የፓርላማ ሥርዓትና የ1958ቱ የአምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ የምክር ደብዳቤ ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡ ጃንሆይ ግን እነዚህንና በተለይም የገጠሩን ሕዝብ እግር ከወርች ጠፍንጎ የያዘውን የመሬት ሥሪት እንዲያሻሽሉና የመንግሥታቸውንም ፍፃሜ ዘመናዊ በሆነ መንገድ እንዲያሸጋግሩ ከቅርብ ወገኖቻቸው ጭምር የተሰጣቸውን ማሳሰብያ በክህደት መዝግበው፣ አገሪቱንም ሆነ ራሳቸውን ወደ ጥፋት ለመሩ አድናቂዎቻቸው አጉል ምክር ተገዙ፡፡ መጨረሻቸው ከፋ፡፡
ያም ሆነ ይኼ ግን ኢትዮጵያን ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ ዓለም በመወዳጀት የ1950ዎቹንና የ1960ዎቹን የቀዝቃዛው ጦርነትና የሁለቱን ልዕለ ኃያላን ጫና በመቋቋምና ለአገራቸው በሚጠቅም መንገድ በማጫወት የሚደነቁት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አገር የሚመሰክርላቸው፣ ከአንደበታቸው ክፉ የማይወጣ በስሜት የማይነዱ ጨዋ ሰው ነበሩ፡፡ ንጉሡ አዛውንት ነበሩ፡፡ የረጅም ታሪክ ባለቤት የሆነች አገር መሪ ነበሩ፡፡ የአፍሪካም አባት ነበሩ፡፡ ለአንዳንዶቹም የምድር ላይ አምላክ ነበሩ፡፡ ባሳደጉዋቸው ወታደሮች እጅ ተጎሳቁለው ማለፋቸውና ከረጅም ጊዜ በኋላም እንኳን ኦፊሴላዊ ሥርዓተ ቀብር መነፈጋቸው ፈጽሞ ትክክል አልነበረም፡፡
አጭር ማስታወሻዬን ሳጠቃልል ለታሪክ ጸሐፍትና ለሐያስያን፣ እንዲሁም ለቀድሞው መንግሥትና ለገዢው መንግሥት ባለሥልጣናት ማሳሰቢያ በመስጠት ነው፡፡ በቅድሚያ የታሪክ ጸሐፍትና ሐያስያን ንጉሠ ነገሥቱን እንደ ሰው በማየት ለአስተዋፅዎቻቸውም ሆኑ ለስህተቶቻቸው እኩል ዕውቅና ቢሰጡ፡፡ አስተዋፅዎቻቸውን ስናደንቅ ስህተቶቻቸው በሌሎች ደግመው እንዳይፈጸሙ በገሃድ ቢኮነኑ፡፡
በመቀጠልም ሚስጥራዊ ለሆነው ሕልፈታቸውና ከመሞታቸውም በፊት ለደረሰባቸው የሕሊና ጉዳትና የአካል መጎሳቆል ኃላፊነቱን ወስደው የቀድሞ መንግሥት ባለሥልጣናት በጋራ ወይም በተወካዮቻቸው አማካይነት በገሃድ ይቅርታ ቢጠይቁ፡፡
ሥርዓተ ቀብራቸውን በተመለከተም አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ እንደ አንድ ንጉሥ ነገሥት ራሳቸው ባሳነፁት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ውስጥ ሥርዓቱን በሙሉ ንጉሣዊ ክብር ቢያስፈጽም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ይኸው መንግሥት ከማንም በላይ ተጋድሎ አድርገው በፈጠሩት የአፍሪካ ኅብረት ሕንፃ ውስጥ መታሰቢያቸውን በጉልህ እንዲቀመጥ ቢያደርግ ለሚቀጥለው ትውልድ በጎነትንና መከባበርን ከነሙሉ ግብሩ በማስተላለፍ ለአገሪቱ መልካም ገጽታ ለመፍጠር መንደርደሪያ ይሆነናል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሰላም እንሁን
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው dereje460@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
