በልዑል ዘሩ
በዓለም ወቅታዊ የፖለቲካ ፍልስፍና እንደሚታወቀው መንግሥታት የሚኖሩት ሉዓላዊ አገርን ለመምራት ቢሆንም፣ በሕዝብ እምነትና ውክልና ሲሰጣቸው ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳን በታሪክ አጋጣሚ የያዙትን ሥልጣን የሙጥኝ ብለው ወይም ኃይልን የሥልጣን መንጠላጠያ አድርገው ‹‹መንግሥት›› የሆኑ አምባገነኖች በዚያም በዚህም ቢኖሩም፣ ሁሉንም የሚያግባባው እውነት ‹‹ሥልጣንም ሆነ መንግሥትነት ከሕዝብ መንጭቶ ለሕዝብና በሕዝብ መገልገል አለበት›› የሚለው የፕላቶ አባባል ነው፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት “The End of History and the Last Man” በተባለው መጽሐፍ እየተለዋወጠ የመጣውን የዓለም ፖለቲካ ባህሪ በግልጽ ያሳየው ፈራንሲስ ፉኩማያ፣ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ወይም በፈጣሪው የተቸረው ፀጋ አለው ይላል፡፡ በነፃነትና በሰላም የመኖር መብት፣ የትምህርት ዕድል የማግኘት መብት፣ የሐሳብ ነፃነት፣ የንብረት ባለቤትነት መብት፣ . . . አለው፡፡ መንግሥት ማለት ያንን መብትና ነፃነት የሚያከብርና የሚያስከብር አካል ነው በማለት ይገልጸዋል፡፡
እንግዲህ በየትኛውም መለኪያ ቢሆን የአንድ አገር መንግሥት በልማት፣ በሰላም፣ በዴሞክራሲም ሆነ በመልካም አስተዳደር የሕዝብን ጥቅም፣ እኩልነትና ነፃነት የማስከበር ግዴታ አለበት፡፡ ይህን ሕዝባዊ ኃላፊነት በአግባቡ የማይወጣ መንግሥት ደግሞ ሕጋዊ በሆነ የምርጫ ሥርዓት እየተቀየረ አገር ይበልጥ የሕዝብን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንዲሄድ ይደረጋል፣ መደረግም አለበት፡፡ ይኼ ሲሆን ነው ማንኛውም አገር በመምራት ኃላፊነት ላይ ያለ አካል ተጠናክሮ ኃላፊነቱን መወጣት የሚችለው፡፡
በዚህ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሳይንስ እሳቤዎችን ያግባባ መርህ በእኛ አገር ሁኔታ እየተጠናከረ እንዲሄድ የሁላችንም እምነት ነው፡፡ መንግሥትም ቢሆን ከሕዝብ በጀት እየሰበሰበ፣ ተበድሮም ሆነ የዕርዳታ ገንዘብ ተቆጣጥሮ አገር ለማስተዳደር ደፋ ቀና እያለ ያለው በዚሁ መርህ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡
ይሁንና አገራችን ገና ታዳጊ ከመሆኗ አንፃርም ሆነ ከመንግሥት መዋቅሩም ሆነ በሕዝቡ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ለጋነት የሚታዩ ክፍተቶች መኖራቸው አይካድም፡፡ በተለይ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ረገድም ሆነ በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ተጠቃሚነት ገረድ ያለውን ዕድገትና ድክመት የመፈተሽ ሥርዓት ተጠናክሮ ወጥቷል ለማለት የሚያስቸግር ነው፡፡ በዛሬው ምልከታችንም ለመፈተሽ የምንሞክረው ይህንኑ ነው፡፡
የዴሞክራሲው አሳታፊነት ደረጃ ወደኋላ እንዳይመለስ
የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በጊዜ ሒደት እየተጠናከረ የሚመጣ፣ በጉዞው መደነቃቀፍ ቢያጋጥመውም ይበልጥ እየተሻሻለ ጎልቶ የሚወጣ የሠለጠነ ማኅበረሰብ ባህል ነው፡፡ ብዙዎቹ የበለፀጉትም ሆኑ በፍጥነትና በተረጋጋ ሁኔታ እያደጉ ያሉ ሕዝቦች መንገድ የሚያሳየውም ይኼንኑ እውነት ነው፡፡
ከዚህ አንፃር በአገራችን ለዘመናት ተንሰራፍተው የኖሩ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶች የተለያዩ ጭቆናዎችን አድርሰዋል፡፡ የሕዝባችንን ማንነት፣ ቋንቋና ታሪክ ከመድፈቅ አንስቶ የሐሳብ ነፃነትን፣ የመምረጥና መመረጥ መብትን ደፍቀዋል፡፡ የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነትንና ተሳትፎን በመገደብ በኩልም ቀላል ግምት የማይሰጠው አገራዊ ጉዳት ደርሶብናል፡፡ በዚህ መዘዝም በብሔር ጥያቄም ሆነ በመደብ ሽኩቻ ላይ የተመሠረቱ ብርቱ ፍልሚያዎች ተካሂደዋል፡፡
ያ ሁሉ ፈታኝ ጊዜ ታልፎ 1987 ዓ.ም. ላይ በፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ደግሞ አገራዊ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዋስትና ያገኘ መስሏል፡፡ በእርግጥ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. አምባገነኑ የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ከከሰመ በኋላም፣ በሽግግር መንግሥት ምሥረታውና ከዚያም ወዲህ ባሉ ሒደቶች የዴሞክራሲ ጭላንጭሎች ታይተዋል፡፡
እንደ አገር በተካሄዱ ምርጫዎች የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ኃይሎች ከነጉድለታቸውም ቢሆን ተሳትፈዋል፡፡
በግል፣ በማኅበርና በመንግሥት ደረጃ የሚዘጋጁ የመገናኛ ብዙኃን ውጤቶች የተለያዩ አመለካከቶችን ለማንሸራሸር ረድተዋል፡፡ ምንም እንኳን የፕሬስ ነፃነት መብትን በመጠቀም ረገድ በተለይም ገደብ የተጣለባቸው ክልከላዎችን በመጠበቅ ረገድ ክፍተት መታየቱ ባይታበልም ጉድለቶች ነበሩ፡፡ በመረጃ ሰጪው መንግሥታዊ አካል ረገድም ከኋለኛው ዘመን አንስቶ እስካሁን የተሻገረ ድክመት አለ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ (በተለይ ከምርጫ 1997 ዓ.ም. በኋላ) ደግሞ የኢትዮጵያ የፕሬስ ሁኔታ ጥያቄ እየተነሳበት ይገኛል፡፡ በአንድ በኩል አንዳንዱ የግል ፕሬስ ገና ሲጀመር የተከተለው የስም ማጥፋት፣ የተጋነነና የውሸት መረጃ የመጠቀም ተግዳሮት፣ እንዲሁም በሙያው ሥነ ምግባርና መርህ ለመመራት ጉድለት ነበር፡፡ ‹‹በእንቁላል ጊዜ በቀጣሽኝ . . . ›› እንዲሉ ሒደቱ ተባብሶ በመቀጠሉም የጀመሩትን ያህል የቀጠሉትና እያደጉ የሄዱት መገናኛ ብዙኃንና ሙያተኞች ቁጥራቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
የዚህ አስከፊ እውነታ ማሳያም በሕዝብ ስም የተቋቋሙ የኤሌክትሮኒክና የኅትመት ውጤቶችንም ሰንክሎ በአድርባይነት ባህር እንዲዋኙ እያደረጋቸው መሆኑ ነው፡፡ አንዳንድ የኅትመት ውጤቶች ያሳዩት መነቃቃት መኖሩ ባይካድም፣ አሁንም ብሔራዊ የቴሌቪዥንና የሬዲያ ጣቢያዎችን ጨምሮ ሙገሳና ውዳሴ ላይ ብቻ ማተኮርን እንደመረጡ ነው፡፡ ድክመትና እጥረትን ከመፍትሔ ጋር ማሳየት፣ የሕዝብ ጥያቄን ማጉላትም ሆነ አማራጭ አስተሳሰቦችን በድፍረት ማቅረብንም እንደ ኃጢያት ቆጥረውታል፡፡
በመንግሥትም ሆነ በግል ባለቤትነት የተያዙ ቀላል የማይባሉ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት (በተለይ ኤፍኤም ሬዲዮዎች) በመዝናኛ ስፖርት ላይ ብቻ ተንጠልጥለው መቅረታቸውም ወቅታዊው ፈተና ነው፡፡ የሐሳብ ነፃነትና የአመለካከት ትግልን በተለይ በፖለቲካው መድረክ የሚገድብ ምልክትም ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች የመስኩ ገጽታዎች በነፃ የመንቀሳቀስ ዕድል አገሪቱ ወደኋላ እንድትቀር አድርገውታል፡፡ በዚህ ላይ ለዓመታት በዘገባ ሥራቸው ምክንያት በእስር ቤት የቆዩ ጋዜጠኞችና ጦማርያን መኖራቸውም የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ይታወቃል፡፡፡
ሌላው የዴሞክራሲ አሳታፊነት ማሳያ የሆነው ምርጫም ቢሆን የጎላ ፖለቲካዊ ተፎካካሪነት እየታየበት እንዳልሆነ የሚታመን ነው፡፡ ምንም እንኳን ያለፉት አገር አቀፍ ምርጫዎች በመራጭ ተሳትፎ ቁጥር ዕድገት ቢያሳዩም እንኳ በጠንካራ ፓርቲዎች ተሳትፎ እጥረት፣ በምርጫ ቦርድ አካላትና ታዛቢዎች ገለልተኝነት፣ በፍትሐዊነታቸውና በዴሞክራሲያዊነታቸው በእጅጉ ሲተቹ የቆዩ ናቸው፡፡ ውዝግብና አለመተማመንን ያስከተሉም ነበሩ፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን ገዢው ፓርቲና አጋሮቹ ሙሉ በሙሉ የፓርላማ ወንበር በተቆጣጠሩ በወራት ዕድሜ ውስጥ ሕዝቡ (በተለይ በሁለት ክልሎች) ሕዝባዊ እንቢተኝነትን አሳይቷል፡፡ በመልካም አስተዳደር፣ በፍትሐዊ ሀብት ክፍፍልና በመሳሰሉ ጥያቄዎችም የለውጥ መሻትን አንፀባርቋል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች መንግሥትን ‹‹ለጥልቅ ተሃድሶ‹‹ ቢያነሳሱትም፣ አገሪቱ እስካሁንም ድረስ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንድትተዳደር ጫና ፈጥረዋል፡፡
ከእነዚህ ተጨባጭ እውነታዎች አንፃር ሲመዘን ዴሞክራሲያዊ ሒደቱ ከመዳከም ወጥቶ አንድ ዕርምጃ ወደፊት እንዲጓዝ መደረግ አለበት፡፡ ይበልጥ አሳታፊ፣ ነፃና መተማመን የተላበሰ የፖለቲካ ፈለግንም ይሻል፡፡
ፍትሐዊ ልማት የማግኘት ጥያቄ አይድበስበስ
በአገሪቱ ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና ብዙዎችን እያሳተፈ የመጣ የኢኮኖሚ ዕድገት መኖሩን መካድ አይቻልም፡፡ ይህን አባባል በድፍረት መናገር የሚቻለው ደግሞ የዓለም ባንክ ወይም የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ሪፖርትን በማየት ብቻ አይደለም፡፡ ይነስም ይብዛም በተጨባጭ እየተለወጡ የመጡ ከተሞች፣ የገጠር መንደሮችና ግለሰቦችን በማየትም ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ፣ በቴሌኮም አገልግሎት፣ በመጠጥ ውኃና በመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች ተስፋ ሰጪ ውጤት ታይቷል፡፡ በማኅበራዊ መስክ የትምህርትና የጤና መሠረተ ልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ ሽፋንም እየጎለበተ ለመምጣቱ በየአካባቢው እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ዓይቶ መመስከር ይቻላል፡፡ አሁን ጥያቄ እየሆነ የመጣው ግን የፍትሐዊ ሥርጭቱ ጉዳይ ነው፡፡
ከወራት በፊት በአንዳንድ አካባቢዎች ‹‹ልማት የለንም፣ የሥራ ዕድል አልተፈጠረም፣ ጥቂት የአመራር አካላትና ጥገኛ ባለሀብቶች የገዥ መደብ ባህሪ እየያዙ ነው . . . ›› የሚሉ ድምፆች ተሰምተው ነበር፡፡ በግሌ ከዚያም ወዲህ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የመዘዋወር ዕድል ገጥሞኛል፡፡ እውነትም ታዲያ እንደ አገር አለ የሚባለው ዕድገት እንጥፍጣፊው ያልሸተታቸው ከተሞችና የገጠር መንደሮች በብዛት እንዳሉ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡
ለምሳሌ በትግራይና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ ምርጥ የአፈርና የውኃ ጥበቃ ሥራዎች እንደ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎና ደቡብ ጎንደር ባሉት የአማራ ክልል ዞኖች የሉም፡፡ እንኳን ተራራ ከልሎ ደን በማድረግ ውኃ ማመንጨት ይቅርና ያገጠጡ ኮረብታዎችም እርከን አይታይባቸውም፡፡ ልቅ ግጦሽና መሰል የደን ውድመቱም በአንዳንድ ወረዳዎች ሆን ተብሎ በሚመስል አኳኋን በመፈጸም ላይ ነው፡፡ የግብርና ምርታማነቱም ላይ ጥርጣሬ የሚያስነሱ የድህነት ፊቶችና ጎስቋላ አናኗሮች ዕውን አሁን በኢትዮጵያ ገበሬ ሕይወት ተቀይሯል? የሚያስብሉ ናቸው (ይህን በሀቀኛ ጥናት የሚፈትሽ መንግሥትና የምርምር ተቋም ቢኖር እውነቱ ሊወጣ ይችል ነበር)፡፡
በከተሞች ያለው የሥራ ዕድል ፈጠራና የድህነት ቅነሳ መርሐ ግብር አሻራ የማይታይባቸው አካባቢዎችም አሉ፡፡ ሌላው ይቅር በቅርቡ በሥራ ላይ ይውላል የተባለውን የአሥር ቢሊዮን ብር የወጣቶች ፈንድ ለመተግበር የብድር ዋስትናና የቅድሚያ ተቀማጭ ቁጠባ መመርያው ማነቆ የሆነባቸው ወጣቶች ሌላ ቅሬታ ተፈጥሮባቸዋል፡፡ በአገሪቱ በየዓመቱ ሚሊዮን ሕፃናት እየተፈጠሩ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን እየፈለቁ፣ በቂ ሀብትና መሬት ሳይኖራቸው ያንኑ ያህል ወደ ትዳርና ቤተሰብ ምሥረታ እየገቡ አሁን ያለው የሥራ ፈጠራ በምንም መንገድ በቂ ሊሆን አይችልም፡፡
በእርግጥ ድህነትን ለማስወገድም ሆነ የሥራ ዕድል ለማስፋፋት መንግሥት ብቻ አይደለም መጣር ያለበት፡፡ የግል ባለሀብቱና ሕዝቡም (እንደ አቅሙ) መነሳሳት ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ የማይካዱ ጥረቶች ቢኖሩም ሥርጭታቸው ውስን ነው፡፡ በተጨባጭ እንደሚታየው በኢንዱስትሪና በማኑፋክቸሪንግ መስክ ጎልቶ የሚታየው እንቅስቃሴ በኦሮሚያ፣ በፊንፊኔ ዙሪያና በትግራይ አካባቢ ነው፡፡ አሁን አሁን ደብረ ብርሃን፣ ሐዋሳ፣ ኮምቦልቻና ድሬዳዋም እየተነቃቁ ይመስላል፡፡ ሌላው አካባቢ ግን ከ25 ዓመታት በፊት ከነበረበት የተለየ አይደለም በአነስተኛና ጥቃቅን እንኳን ተስፋ ያለው የአማራጭ ተሳትፎ አይታይም (በብዙዎቹ ወረዳዎች አባባሉን መፈተሽ ይቻላል)፡፡
የመሠረተ ልማት ዝርጋታው በጎ ጅምር ላይ የሚነሳው ጥያቄ (አንዳንዴም ወደ ፖለቲካዊ መድሎ እንደሄደ የሚነገረው) የመንገድ ጉዳይ ነው፡፡ እስከ አንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር ከዋና ከተማዋ የሚርቁት የኦሞራቴ፣ የአፋር ዳሎል፣ የሽሬ/ሁመራ፣ ቀብሪ ደሃርና ጋምቤላ /ኩርሙክ አካባቢዎች የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ አግኝተው፣ በርካታ ከ300 ኪሎ ሜትር ያነሱ ዞንን ከዞን ጭምር የሚያገናኙ መንገዶች እንደተረሱ ነው፡፡ (በተለይ ሰሜን ሸዋ ዞን) በመጠጥ ውኃ ረገድም ሌላው ቀርቶ ከ20 ዓመታት በፊት ከነበራቸው በታች የወረዱ ከተሞች አሉ፡፡ እዚህ ላይ የሕዝብ ብዛት የራሱ ተፅዕኖ ቢኖረውም አቅም በፈቀደው መጠን በቂ ሥራ ባለመሠራቱ መዳከሙ ተከስቷል፡፡
የሰላምና ደኅንነት ጉዳይም ትኩረትን ይሻል
ለሰላምና አገራዊ/አካባቢያዊ ደኅንነት መረጋገጥ ልማትና ዴሞክራሲ ወሳኝ ድርሻ አላቸው፡፡ በዚህ ረገድ እንደ አገር የተገኙ መልካም ውጤቶች መኖራቸው ባይካድም፣ የሚስተዋሉ መገፋፋቶችና ጥፋቶችም የሚናቁ አይደለም፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባቀረበው መረጃ መሠረት እንኳን በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመንግሥት ታጣቂዎች ተገድለዋል፡፡ ሌላው ይቅር ብዙም ባልተነገረለት የቅርብ ጊዜው የጋምቤላ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን በተመሠረተ ክስ ላይ ዓይተናል፡፡
በአገሪቱ በማንነትና በብሔር ስም እየተነሳ የሚከስመው ግጭት የሰላም መደፍረስ ዋነኛ መንስዔና አሁን ያለው ሥርዓት ውጤት እየሆነ መምጣቱም አልተፈተሸም፡፡ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሊያ፣ በአማራና በትግራይ ክልል የተነሱ ግጭቶች በመንግሥት ኃይል ቢገቱም በመሠረታዊነት መፍትሔ የተሰጣቸው አይመስሉም፡፡ በውስጣቸው የሚታይ ፍጥጫ እንዲረግብ አልተደረገም የሚሉ ወገኖችም ትንሽ አይደሉም፡፡
ከዚህም በላይ አሁንም የሽፍትነትና የውንብድና መንገድን እየመረጡ ያሉ ነፍጥ አንጋቾች መታየታቸው አልቀረም፡፡ ዓላማቸው ፖለቲካዊ ነው ባይባል እንኳን በመሀል አገር ጭምር ሰላም የማደፍረሱና ሰዶ ማሳደዱ አሁንም ዋነኛው የፖሊስ ተግባር ሆኗል፡፡ በወንጀል መከላከል ረገድ የእርስ በርስ ግድያና መጠፋፋት ያልከሰመባቸው አካባቢዎችም እንደነበሩ አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የአገር ደኅንነት ሲባል ውጭያዊውና ቀጣናዊውን ሁኔታ ቀድመን ሰላምን መለካት እንጂ፣ በአገር ውስጥ ያለው ሰላምና አብሮነትም በጥልቀት መፈተሽ ያለበትና የሚገባው ነው፡፡
ማጠቃለያ
እስካሁን ለመዳሰስ እንደተሞከረው መልካም ጅምርን ለማስፋትም ይሁን ከድክመት ለመውጣት መንግሥት ሕዝብን እያረካ ስለመሆኑ ደጋግሞ መፈተሽ አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ፉኩያማ እንደሚለው ሊታመኑ የሚችሉ ገለልተኛ ፕሬሶች፣ የዴሞክራሲና የምርምር ተቋማት መጎልበት አለባቸው፡፡ መንግሥትም የዕለት ተዕለት የራሱን የፕሮፓጋንዳ ድምፅ ብቻ ከመስማት ወጥቶ የሕዝቡን ሮሮ፣ ሥነ ልቦናና ወቅታዊ ፍላጎት ማጤን ይኖርበታል፡፡ ከሁሉ በላይ የአገርን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ የሚወስኑ የኅብረ ብሔራዊ አንድነትና የትብብር መንፈሱን ሊዘራ ይገባዋል፡፡ ይህን አለማድረግ ግን እንደ 2008 ዓ.ም. ያለ ዱብ ዕዳና ድንገተኛ ናዳን ይጋብዛል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
