በመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ
ይነስም ይብዛ እያንዳንዱ ዲሲፒሊን ከመደበኛው ቋንቋ ወጣ ያለ የራሱ ቴክኒካዊ ልሳን እንደሚያዳብር ይታመናል። ፖለቲከኞችና ሐዋሪያዎቻቸውም ለዚህ ዓይነቱ ልምድ የተጋለጡ ናቸው። የሐኪሞች፣ የመሐንዲሶች፣ የሕግ ባለሙያዎችም ሆኑ የምጣኔ ሀብት ጠበብት ያላቸውን ያህል ፖለቲከኞችም የራሳቸው ቋንቋ ቢኖራቸው እምብዛም ላያስገርም ይችላል።
ይህንን ጸሐፊ የሚያስገርመውና አንዳንዴም ከልቡ የሚያበግነው ግን፣ በትክክለኛው መስመር አንዱንም ሳይሆኑ አለቆቻቸውን ለመምሰል ብቻ ቋንቋቸውን የሚያጐሳቁሉ ሰዎች ጉዳይ ነው።
እንደየፖለቲካ ዘመኑ እንዲህ ያሉትንና በራስ መተማመን አብዝቶ የሚጐድላቸውን ወገኖች አዘውትሮ ማየት እየተለመደ የመጣ ይመስላል። በደርግ ዘመን ‹‹ኢሠፓና አብዮታዊው መንግሥት›› የሚለው ሐረግ ጆሯችንን እስኪሰለቸው ድረስ ዘወትር የምንሰማው ነበር። በመሠረቱ ኢሠፓና አብዮታዊው መንግሥት በቅርጽም ሆነ በይዘት አንድና አንድ ነበሩ። በፓርቲና በመንግሥትነት ስም የተጠሩ ለማስመሰል የሚደረገው ሙከራ ታዲያ ሰፊውን ሕዝብ ከማደናገር የተለየ ውጤት አልነበረውም።
በተመሳሳይ ሁኔታ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ‹‹ኢሕአዴግና ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት›› የሚለው ሐረግ ዛሬ ዛሬ በከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች አንደበት ሳይቀር ተደጋግሞ ሲደመጥ አጋጥሞን ይሆናል። ለመሆኑ ሁለቱን አካላት በምን ዓይነት ማጣሪያ መለየት ይቻላል? ኢሕአዴግ የመንግሥትን ሥልጣን ተረክቦ አገር ሲመራ በፓርቲነት መጠሪያው ያው ኢሕአዴግ ከሆነ ሁለቱ መሆኑ ከታወቀ፣ ሁለቱ አካላት በይዘት እንደማይለያዩ ግልጽ ነው። ስለዚህ ሁለቱን አካላት ‹‹እና›› በሚለው መስተዋድድ ለማገናኘት ያን ያህል መድከሙ ለምን ይጠቅመናል?
በአገራችን የመንግሥት ሥርዓት ለውጥ ተካሂዶ ኢሕአዴግ በአሸናፊነት መንበረ ሥልጣኑን ከተቆናጠጠ ወዲህ፣ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ አዘውትረን የምንሰማቸው ያልተለመዱ አንዳንድ ጊዜም የአማርኛ ቋንቋ ሕግጋትን ክፉኛ የሚጥሱ ቃላትና ሐረጐች እየበረከቱ መጥተዋል። ቋንቋ ከማኅበረሰቡ አስተሳሰብ ጋር ያድጋል ቢባልም ብዙዎቹ በእርግጥ የዕድገት ምልክቶች አይደሉም። ይበልጥ የሚገርመው ደግሞ መገናኛ ብዙኃኑ እየተቀባበሉ ያላግባብ የሚያስተጋቧቸው መሆኑ ነው።
ከእነዚህ ቃላትና ሐረጐች መካከል በሰፊው ተሠራጭቶ በበርካታ ጥራዝ ነጠቆች ሲደጋገም የምናዳምጠው ‹‹ያለበት ሁኔታ ነው ያለው›› የሚለው የተጥበረበረና ያላግባብ ከመለጠፉ በስተቀር አንዳች ስሜት የማይሰጠው ሐረግ ነው። ለምሳሌ ሰውየውን ምሳ በላህ ወይ? ብላችሁ ብትጠየቁት በቀላሉና በተለመደው አነጋገር አዎ በልቻለሁ ወይም አይ አልበላሁም ብሎ በቀጥታ ከሚመልስላችሁ ይልቅ፣ ‹‹የበላሁበት ሁኔታ ነው ያለው›› የሚል ግራ አጋቢ መልስ ይሰጣችኋል። አሁን ይህንን ሰው ምን ትሉታላችሁ? እንዴትስ ትረዱታላችሁ? ለጥያቄያችሁስ ተገቢውን መልስ አግኝታችኋልን? ለመሆኑ በሰጣችሁ የተጥበረበረ መልስ መሠረት ሰውየው ምሳውን በልቷል ወይስ አልበላም? በቀጥታ በልቻለሁ ወይም አልበላሁም ማለት እየቻለና የቋንቋው ትክክለኛ ሕግም ይኸው ሆኖ ሳለ፣ ያን ሁሉ አጠራጣሪ የቃላት ጋጋታ ማስከተል ለምን አስፈለገው?
አሁን አሁን በተለይ በመካከለኛና በዝቅተኛ የመንግሥት አስተዳደር እርከን ተሹመው ወይም ተቀጥረው የሚያገለግሉ አመራሮችና ተራ ሠራተኞች፣ እንዲሁም እነርሱን ተጠግተው ወይም ከእነርሱ ጋር ወዳጅነት ፈጥረው የምታዩዋቸው አንዳንድ የኅብረተሰባችን አባላት በሕዝባዊ መድረኮችም ሆነ በአደባባይ ከሚያሰሟቸው አሰልቺ ሐረጐች መካከል ምናልባት ዋነኛው ይኸው ‹‹ያለበት ሁኔታ ነው ያለው›› የሚለው ሳይሆን አይቀርም። ‹‹ምንጩ የደረቀበት ሁኔታ ነው ያለው››፣ ‹‹መንገዱ የተሠራበት ሁኔታ ነው ያለው››፣ ‹‹ሆስፒታሉ ቢገነባም በቂ ቁጥር ያላቸው ሐኪሞች ያላገኘንበት ሁኔታ ነው ያለው››፣ ‹‹ሴት ተማሪዎችን ከኃይል ጥቃት የተከላከልንበት ሁኔታ ነው ያለው››፣ . . . ሲሉ የዞን፣ የወረዳ ወይም የቀበሌ አመራሮችን መስማት ምን ያህል አሰልቺ እንደሆነ ያጋጠመው ሁሉ ያውቀዋል። እጅግ በጣም ባጠረና ስሜት በሚሰጥ አነጋገር ምንጩ ደርቋል፣ መንገዱ ተሠርቷል፣ በቂ ሐኪሞች አላገኘንም፣ ሴት ተማሪዎችን ከኃይል ጥቃት ተከላክለናል ማለት እየተቻለ ‹‹ያለበት ሁኔታ ነው ያለው›› የሚለውን ካድሬያዊ ሐረግ ያላግባብ መለጠፍና አድማጮችን ወይም ታዳሚዎችን ማደናገር ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው?
ይህ ችግር በመገናኛ ብዙኃኑ ይብሳል። ‹‹የአንቶኔ ሚኒስቴር ሚኒስትር››፣ ‹‹የእገሌ አባበሉ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር››፣ ‹‹የዚያኛው ወይም የዚህኛው ኮሚሽን ኮሚሽነር”፣ . . . ወዘተ የሚሉትን የቋንቋ ሕግ የማይገዛቸው አነጋገሮች ነጋ ጠባ ከሬዲዮና ከቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችን ሳይቀር ሳንፈልግ እንድንሰማ እየተገደድን መምጣታችን በእርግጥ ያሳዝናል። ሰውየው የአንድ ዘርፍ ሚኒስትር ከሆኑ ዘርፉን ብቻ ጠቅሶ ማዕረጋቸውን ማስከተል ይበቃ ነበር። በሌላ አነጋገር ሚኒስትሩ የሚመሩት ዘርፍ የትምህርት ዘርፍ ከሆነ የትምህርት ሚኒስትር ናቸው ማለት ነው። ድሮ እኮ የምንጠራቸው በዚሁ ስያሜ ነበር። የትምህርት ዘርፉን በአገር ደረጃ የሚመሩትን ከፍተኛ ባለሥልጣን ‹‹የትምህርት ሚኒስትር›› እያልን መጥራታችን ትክክልና ተገቢ ሆኖ እያለ፣ የመሥሪያ ቤቱ መጠሪያ የሆነውን ‹‹ሚኒስቴር›› የሚለውን ቃል ለምን መደረብ ያስፈልገናል?
ወጋችንን በዚሁ መስመር እያዋዛን ትንሽ እንቀጥል። ከጥቂት ዓመታት በፊት የአካባቢ አስተዳደር በጠራው አንድ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ የመገኘት ዕድል አጋጥሞኝ ነበር። በዚያ ስብሰባ ላይ የመጀመሪያውንና አንድ ሰዓት ያህል የወሰደውን ሰፊ ገለጻ ያደረገው አንድ ወዳጄ በገለጻው ውስጥ ያለ ይሉኝታ እየደጋገመ ይሰነቅረው የነበረው ቃል መቼውንም ጊዜ አይረሳኝም። በቅርብ የማውቀው ይህ ሰው የአፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ መሆኑን ጠንቅቄ አውቃለሁ። ይሁን እንጂ ‹‹ነፃነት›› የሚለውን የአማርኛ ቃል ‹‹ናፅነት›› እያለ ሲጠቅስልን እንስቀው የነበረው ሳቅ ጣራ ይነካ ነበር። ሰውየው ይህንን ያደርግ የነበረው ‹‹ነፃነት›› ማለት አቅቶት ሳይሆን፣ ከትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጋር መታገሉን ምክንያት በማድረግ የራሱን ልሳን ረስቶ ‹‹ናፅነት›› የሚለውን ቃል እንደወረሰ ሊያስተጋባልን በማሰብ እንደነበር ለመገመት እምብዛም አላዳገተንም። መታገሉ እውነት ቢሆን ኖሮ እኮ ትንሽ ይሻል ነበር። ሰውየው እስከምናውቀው ድረስ ዘግይቶ የተቀላቀለ የድል አጥቢያ አርበኛ እንጂ በእርግጥ ታጋይ አልነበረም። ሆኖም ከታጋዮች አንደበት ጋር የሚመሳሰሉ አዳዲስ ቃላትና ሐረጐችን እየመረጠና እያጠና አለቆች ናቸው ብሎ የሚገምታቸውን ሰዎች መምሰሉን ሲለማመድብን ነበር።
አሁን አሁን በብዙኃን መገናኛ ተቋማትም ሆነ በተራው ሰው አንደበት ያላግባብ እየተጣመሙ የሚሰሙትን ተመሳሳይ ቃላትና ሐረጐች በእርግጥ ቆጥሮ መጨረስ አይቻልም። ለሁለተኛ ዙርም ቢሆን አንዳንዶቹን ጨምሬ ላስታውሳችሁ። ለምሳሌ ‹‹ግልጸኛ›› እና ‹‹ግልጸኝነት›› የሚሉት ቃላት በየትኛውም የአማርኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ስንፈልግ ውለን ብናድር የማናገኛቸው ናቸው። በተደጋጋሚ ስለሰማናቸው ብቻ ትክክል የሆኑ ሊመስለን እንዳይችል አጥብቄ ለማሳሰብ እወዳለሁ። እንደ እውነቱ ከሆነ የእነዚህ ቃላት ሥርወ-ቃል ወይም መሠረታዊ ግስ ‹‹ገለጸ›› የሚለው ሲሆን፣ የዚህ ቃል ቅጽሉ ‹‹ግልጽ›› እንጂ ‹‹ግልጸኛ›› አይደለም። ‹‹ግልጸኝነት›› የሚለውም ቢሆን ‹‹ግልጽነት›› ተብሎ መታረም በተገባው ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ‹‹ተያይዞ›› የሚለው ቃል ያለቦታው እየተሰነቀረ ጆሯችንን እስኪታክተው ድረስ መስማት እንድናዘወትር ተገደናል። ቢያያዝም ባይያያዝም ‹‹እንዲህ ወይም እንዲያ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ›› የሚለው ሐረግ በበርካታ ተናጋሪዎች ዘንድ ሲዘወተር እየሰቀጠጠንም ቢሆን እንከታተላለን። ከሕዝቡ ሊቀድሙ ይችሉ ይሆናል ብለን ተስፋ የምናደርግባቸው የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጋዜጠኞቻችን ራሳቸው አንዳች እሴት የማይጨምሩ ቃላትና ሐረጐችን ያላግባብ እየደነቀሩ ቀስ በቀስ መገናኛ ብዙኃንን ከመከታተል እንዳያርቁን እፈራለሁ። ‹‹ተከታዩን ፕሮግራም የምናደርስላችሁ ይሆናል›› ከሚለው አዘውትረን ከምንሰማው ሐረግ ውስጥ ‹‹ይሆናል›› የሚለው ቃል አጓጉል ልማድ ካልሆነ በስተቀር ለምን እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ አይደለም። ‹‹ተከታዩን ፕሮግራም እናቀርብላችኋለን ወይም እነርሱ እንደሚሉት እናደርሳችኋለን›› የሚለው እንኳ ይበቃ ነበር። የሚነበብ ይሆናል፣ የሚደመጥ ይሆናል፣ የሚቀርብ ይሆናል፣ የሚተላለፍ ነው የሚሆነው። ብቻ ምን አለፋችሁ ‹‹ይሆናል›› ወይም ‹‹የሚሆነው›› የሚል አጠራጣሪ ትርፍ ቃል ካልታከለበት የሚሰማ ነገር እየጠፋ መጥቷል።
አንዳንዶቹ ቃላትና ሐረጐች መቸውንም ቢሆን የማናስተካክላቸው እስኪመስሉ ድረስ ሥር የሰደዱ መስሎ ይታየኛል። እንደ እንግሊዝኛ ባሉ ሌሎች ቋንቋዎች ባህል ውስጥ የተለመዱትን አነጋገሮች በጥሬው ተርጉሞ በመዋስ ብቻ ‹‹እንደ አጠቃላይ››፣ ‹‹እንደ ምናምን መጠን››፣ ‹‹ብሎ መውሰድ ይቻላል››፣ ‹‹እዛው ሳለ››፣ . . . ወዘተ የሚሉት ባዕድ አባባሎች ክፉኛ ተጣብተውናል።
ለመሆኑ የዚህ ሁሉ ችግር መሠረቱ ምን ይሆን? በእኔ ግምት የሚጀመረው እንደ ዘበት ሊሆን ይችላል። የኋላ ኋላ ግን ሳይታሰብ እየተዘወተረ በቀላሉ ወደማይለቅበት ደረጃ እየተሸጋገረ ይሄዳል። እነዚህ ቃላትና ሐረጐች በተለይ ከፍ ያለ ሥልጣን ባላቸው ሹማምንት አማካይነት ነው መነገር የሚጀምሩት። ከዚያም የበላይ አለቆቻቸውን ትኩረት የሳቡ እየመሰላቸው ዝቅተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የበታች ሠራተኞች አንዱ ወደ ሌላው እየተቀባበሉ ያለ ይሉኝታ ያስተጋቧቸዋል። ከላይ የተቀበሉትን ፈሊጣዊ አነጋገር የመግባቢያ ቋንቋው ሕግ ፈቀደው አልፈቀደው እምብዛም አይገዳቸውም። ከዚህ ይልቅ ለእነሱ ዋናው ቁም ነገር በአደባባይ ሲናገሩ የበላይ አለቆቻቸውን መምሰል መቻላቸው ብቻ ነው። ለዚህ ሲሉ በአጓጉል ኩረጃ የቋንቋ አጠቃቀማቸውን በማወሳሰብ ማንነታቸውን ስለመሸርሸራቸውና ሰብዓዊ ክብራቸውን በገዛ ራሳቸው ዝቅ ስለማድረጋቸው አንዳች ጉዳያቸው አይደለም፣ አይቆረቁራቸውም።
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ተላላፊ በሽታ ፈጽሞ ፈውስ የሌለው አይደለም። በጊዜ ከነቃንበት ሊድን ይችላል። ማንኛውም ሰው መኖር ያለበት የራሱን እንጂ የሌላውን ሕይወት አይደለም። ከሌሎች የምንወርሳቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፀጋዎች ቢኖሩም፣ በጥንቃቄ እየመርጥን እንጂ በግዴለሽነት እየኮረጅን መሆን አይኖርበትም። ራስን የሚያሳጣ ኩረጃ ደግሞ አጥፊ እንጂ አልሚ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። ሌሎችን ለመምሰል ብለን የመግባቢያ ቋንቋችንን አናወሳስብ። ልንመስል የምንገለብጣቸው ወይም ሳናጣራ ኮፒ የምናደርጋቸው ሰዎች ሳይቀሩ ክፉኛ ይታዘቡናል።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው clickmerha1@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡
