በመታሰቢያ መላከሕይወት ገብረክርስቶስ
ብዙ አገሮች በዓለም አስደናቂ ዕድገት አስመዝግበው የሕዝባቸውን ሕይወት ትርጉም ባለው መንገድ መለወጥ የቻሉበት አንዱና ዋነኛው ምክንያት፣ ሥልጣን የያዘው ኃይል በቂ ጊዜ ወስዶ አገሪቷ በአቋራጭ ማበልፀግ የሚቻልበትን መንገድ በማጥናትና ያንን መንገድ ተከትሎ ሰፊ ሥራ መሥራቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን በርካታ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ብትሆንም አንዱ ከአንዱ የተሻለ ጥቅምና ከፍተኛ ዕድገት ለማምጣት የሚያስችል ነው፡፡
በመሆኑም ይኼንን ጉዳይ በአግባቡ መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኘው ፕላቶ ወይም ደጋማ ቦታ ከ60 በመቶ በላይ ባለቤት መሆንዋ የበርካታ ወንዞች መፍለቂያ እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ይኼ ከፍተኛ ቦታ ደግሞ በመሀሉ የያዛቸው በርካታ ሚሊዮን ዓመታት የፈጠሯቸው ሸለቆዎች ይገኙበታል፡፡
በአንድ ከፍተኛ ቦታ ከፍተኛ ስፋት ያለው ሸለቆ በሚኖርበት ጊዜ ይህ ቦታ በዋናነት እንደ ውኃ ባንክ ሆኖ ማገልገል የሚችል በመሆኑ፣ ይህንም ሰው ሠራሽ ግድብ ተገድቦለት ውኃ እንዲከማች በሚደረግበት ጊዜ (አሁን በአገራችን በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኘው) ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል ማመንጨት ይቻላል፡፡
እዚህ ላይ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ኃይል ማመንጨት ሲቻል፣ ወንዙን እንደ ዋናነት በመቁጠር የሚነገር አባባል ነው በስፋት የሚሰማው፡፡ ነገር ግን ወንዙ ኃይል ማመንጨት ያስቻለው ያለው ሸለቆ ነው፡፡ ወይም በሸለቆው ውስጥ የተጠራቀመው ውኃ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆነችው ኬንያ ውስጥ ከኬንያ ተራራ ተነስቶ ወደ ህንድ ውቅያኖስ የሚሄድ ትልቅ ወንዝ አላት፡፡ ይኼ ተራራ ከፍታው 5,100 ሜትር ሲሆን እኛ አገር ያለውን ራስ ዳሸን በ600 ሜትር ይበልጠዋል፡፡ ነገር ግን ከተራራው የሚነሳው ወንዝ ስሙ ጣና ሲሆን፣ ከተራራው እንደወረደ ምንም ዓይነት ሰፊ ሸለቆ ሳይኖረው ሜዳ ለሜዳ እየሄደ ህንድ ውቅያኖስ ውስጥ ይገባል፡፡ በመሆኑም የኬንያን ሕዝብ ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል ኃይል የማመንጨት አቅም የለውም፡፡ ለዚህም ነው ኬንያ ከኢትዮጵያ 500 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት የተገደደችው፡፡
የኬንያን ጣና ወንዝ እንደ ምሳሌ ወሰድኩ እንጂ፣ በመላው ዓለም ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ኖሮአቸው ሸለቆ አልባ የሆኑ ወንዞች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡
ለተጨማሪ ምሳሌ ግብፅን ብንወስድ ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ የገነባችው አስዋን ግድብ ማመንጨት የሚችለው ከፍተኛው ኃይል 2,100 ሜጋ ዋት ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት ግብፅ የተከዜን ተፋሰስ፣ የብሉ ናይልን ተፋሰስ፣ የባሮ አኮቦን ተፋሰስ፣ የነጭ አባይን ተፋሰስ ሁሉ በአንድ ላይ ወስዳ ማመንጨት የቻለችው የኃይል መጠን ከላይ የተጠቀሰውን ብቻ ነው፡፡ እኛ አገር ግን የዓባይን ያውም የታችኛውን የዓባይ ሸለቆ ብቻ በመጠቀም 6000 ሺሕ ሜጋ ዋት ማመንጨት በቅርቡ የምንችልበት አቅም አለን፡፡ ይህ ማለት ኃይል ለማመንጨት ውኃ ወሳኝ ቢሆንም ሸለቆ ደግሞ ከውኃ ባልተናነሰ ወሳኝነት እንዳለው ነው፡፡ በእኛ አገር በዚህ ጽሑፍ የግድ ሊቃኝ የሚገባው ጉዳይ የተከዜ ሸለቆና ወንዝ ነው፡፡ ተከዜ ከዓባይ በትንሹ የሚያንስ ሸለቆ ቢኖረውም፣ በውስጡ የሚያልፈው ውኃ መጠን በእጅጉ አነስተኛ በመሆኑ ለኃይል ግንባታ አጓጊ ቦታ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የተከዜ ውኃ የሚመነጭባቸው የወሎ ደጋማ ቦታዎች በእጅጉ የተፈጥሮ ሚዛናቸው የተናጋ በመሆኑና ተራሮቹ ሁሉ ደን አልባ በመሆናቸው፣ በጥንት ዘመን በከፍተኛ ደረጃ ከእነዚህ ተራሮች ይመነጩ የነበሩ ምንጮች በሙሉ በመድረቃቸው የተከዜ ሸለቆ ብቻውን ቀርቷል ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ በሌላ አነጋገር በእነዚህ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ መከናወን እንዳለበት የሚያመላክት ነው፡፡
ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደያዘ መጀመሪያ የገነባው የተከዜ ግድብ፣ በአብዛኛው የዓመቱን ወቅት እጅግ ዝቅተኛ ኃይል ለማመንጨት የሚገደደውም ለዚህ ነው፡፡
በቅርቡ ተገንብቶ ያለቀው የጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጨት ደግሞ በሸለቆም በውኃም በእጅጉ የበለፀገ ነው፡፡ በእኔ እምነት ዓመቱን ሙሉ ያለ ምንም መስተጓጎል የተፈለገውን ኃይል ማመንጨት አቅም ያለው የኃይል ማመንጫ መሆኑን ስናይ ለምን ቅድሚያ ተነፈገው የሚያሰኝ ነው፡፡
የዓባይ ወንዝ በዓለም በርዝመቱ አንደኛ ቢሆንም በውኃ መጠን ግን ሌሎች በርካታ ወንዞች ይበልጡታል፡፡ እንደ ሚሲሲፒ፣ አማዞን፣ ዶናው፣ ቮልጋ፣ ኮንጎ፣… የመሳሰሉት ወንዞች እጅግ ከፍተኛ የውኃ ፍሰት ያላቸው ናቸው፡፡ በኮንጎ ወንዝ ላይ 39,000 ሺሕ ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችል የኃይል ማመንጫ የተጠና ቢሆንም፣ እስካሁን ሁኔታዎች ባለመሟላታቸው ግንባታው ሊጀመር አልቻለም፡፡ ይፈጃል ተብሎ የተገመተው ገንዘብ ደግሞ 80 ቢሊየን ዶላር ገደማ ነው፡፡ ይህ ግድብ ከዕለታት አንድ ቀን ተገንብቶ ሲያልቅ በዓለማችን ትልቁ ከውኃ ኃይል ማመንጨት የሚችል ግንባታ ይሆናል ማለት ነው፡፡
አሁን ባለንበት ዘመን አንድ አገር የኤሌክትሪክ ኃይል ለምን ታመነጫለች የሚለው ጉዳይ በእጅጉ ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ከታዳሽ ኃይል የሚመነጭ ኤሌክትሪክና የከባቢ አየር የማይበክል ኃይል ያላቸው ተፈላጊነት በእጅጉ እየጎላ የመጣበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ ዓለማችንን እየበከልንና ከንፁህ ምንጭ የምናመነጫቸው የኃይል አቅርቦት ልዩነታቸው በእጅጉ እየጎላ ነው፡፡ እዚህ ላይ በግሌ አንድ አዕምሮዊ ንብረት ለአገር ኢኮኖሚ ይጠቅማል ብዬ ስለማምን በዚህ ጽሑፍ ለማቅረብ ይፈቀድልኝ፡፡
በኢትዮጵያ ተመርተው ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ ማናቸውም ምርቶች አንድ ምልክት ይለጠፍባቸው፡፡ ይህም ምልክት የሚከተለው ዓርማ እንዲኖረው ይደረግ (The Energy Used to Produce This Product is Clean)፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ በዓለም ገበያ ያለንን ተወዳዳሪነት መጨመር ከመቻላችንም በላይ፣ የዘመኑ ዋና ጉዳይ የሆነውን የከባቢ አየር ብክለትን ለመከላከል ያለብንን አገራዊ ኃላፊነት በሚገባ ተወጥተናል ማለት ነው፡፡ ምርቱም የመሸጥ ዕድሉ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስና በአሁኑ ወቅት እየገነባነው ያለነው የዓባይ ግድብ ሙሉ በሙሉ ውኃ መያዝ ሲጀመር ወደ ኃላ 250 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ይፈጠራል፡፡ ይህ ማለት በሐይቁ ግራና ቀኝ ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የውኃ ዳርቻ ይኖራል፡፡ ይህ አካባቢ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል ማለት ነው፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራው አሳ በማስገር፣ በትራንስፖርት ዘርፍ፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ ከብቶች በማደለብና በተለያዩ የእርሻ ሥራዎች፣ ወዘተ ነው፡፡ ይህ ማለት በዋናነት ይህንን ሁሉ ተግባር ለማከናወን የሚያስችለን ከግድቡ ጀርባ እጅግ ሰፊ የሆነ ሸለቆ በመኖሩ ነው፡፡ ይህ ማለት በእኔ እምነት ሸለቆ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ከወንዝ የበለጠ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አለው ማለት ነው፡፡
ሸለቆ አሁን በአገራችን እየተደረገ እንዳለው ከፍተኛ ግድብ ገንብቶ ኃይል ለማመንጨት ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ሳይሆን፣ ደጋማ ቦታ ባሉ ሸለቆዎች (ወደፊት ሀብት በበቂ ሁኔታ ሲኖር) ውኃ ለማከማቸት ማለትም የክረምቱን ውኃ በመያዝ በበጋና በደረቅ ወቅት ዝቅተኛ ቦታ ወደ አሉ የኃይል ማመንጫ ግድቦች እንዲገቡ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህም ግድቦች ዓመቱን ሙሉ ያለ ውኃ እጥረት እንዲሠሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አሁን እየተገነባ ያለው የዓባይ ግድብ ከአናቱ እጅግ በርካታ ሸለቆ ያላቸው ተፋሰሶች አሉት፡፡ እነዚህ ተፋሰሶች መጠናቸው ኃይል ለማመንጨት ከበቃ በዚያ መልኩ ሊጠኑ ይችላሉ፡፡ ኃይል ለማመንጨት የማይበቃ ከሆነ ግን ተፈጥሮ እንዲሠራ እንደ ጣና ሐይቅ ውኃ በመያዝ ለታችኞቹ ግድቦች የውኃ ባንክ ማገልገል ይቻላል፡፡
አንድ አገር ማደግ ካለበት በአሁን ወቅት ልንሠራቸው የምንችላቸው ተግባራት ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ጥቅም መለወጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በሰዎች አዕምሮ ላይ ሰፊ ሀብት በማፍሰስ (እንደ ጃፓንና ኮሪያ) የአዕምሮ ውጤቶችን በማምረትና ለዓለም ገበያ በማቅረብ የሚደረግ የልማት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ከእነዚህ ሁለት አማራጮች ውጪ ሌላ የአንድን አገር ኢኮኖሚ ሊለወጥ የሚችል ተግባር የለም፡፡ በመሆኑም አገራችን ያላትን ሰፊ የሸለቆ ሀብት ወደ ጥቅም በመለወጥ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ሕይወት ሙሉ በሙሉ መለወጥ ይቻላል፡፡ በዓለማችን እኮ ምንም ሸለቆ የሌላቸው በርካታ አገሮች አሉ፡፡
እዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ልማት ብቻ ሳይሆን ውኃ በሚከማችበት ወቅት የሚፈጠረው ውኃ ወለድ በሽታ ጭምር ነው፡፡ ውኃ በሚከማችበት ወቅት አንድ ቦታ ድሮ ከነበረው ዓመታዊ ምዝን የአየር ሙቀት ከ2.5 እስከ 3.5 ዲግሪ የአየሩ ሙቀት ሊቀንስ ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ በርካታ ነፍሳት በቀላሉ መራባት ይጀምራሉ፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው አካል ለጉዳይ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡
ስለ ሸለቆ ስናነሳ በአገራችን ያሉ ክልሎች ያላቸው የሸለቆ ሀብት በእጅጉ ይለያያል በዋናነት የአማራ ክልል የተራሮችና የሸለቆዎች ባለሀብት ሲሆን፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልል የሁለተኛና የሦስተኛ ቦታዎችን ይይዛሉ፡፡ በአገራችን ከሚገኙ ቁመታቸው ከባህር ጠለል በላይ ከ3,900 እስከ 4,500 ሜትር ከፍታ ካላቸው 23 ተራሮች 20 ያህሉ የሚገኙት በአማራ ክልል ነው፡፡ ወደ ትግራይ ክልል ስናመራ ይህ ክልል በአመዛኙ ወይና ደጋ ተብሎ የሚጠራ የመልክዓ ምድር ባለቤት ሲሆን፣ ከባህር ጠለል በላይ አብዛኛው የክልሉ መሬት 1,600, እስከ 1,800 ሜትር የሚደርስ ነው፡፡ በትግራይ ምሥራቃዊ ክፍል የተሻለ ከፍታ ቢኖርም አብዛኛው በአካባቢው የሚጥለው ዝናብ ተፋሰሱ ወደ አፋር ክልል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የትግራይ ክልል በቂ ዝናብ ወይም እርጥበት እንዳያገኝ ምክንያት ሆኗል፡፡
በትግራይ ክልል አንድ ሰው ከሽሬ ተነስቶ እስከ አዲግራት ወይም መቀሌ መኪና ቢነዳ፣ ይህ ነው የማይባል ትልቅ ድልድይ ወይም ወንዝ መሻገር አይችልም፡፡ በሌላ አነጋገር ትግራይ ውስጥ በርካታ ጉብታዎች ቢኖሩም፣ ክልሉ በአብዛኛው ሜዳማ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ ክልል ደጋማ ከሆነ የራሱ የሆኑ በቂ ዝናብ የሚያገኝበት ዕድል ይኖረዋል፡፡ ቆላማ ከሆነ ደግሞ ከደጋው የሚመጣውን ውኃ በመቀበል ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ የትግራይ ክልል ግን ወይና ደጋ በመሆኑና ከሌሎች ክልሎች ወደ ክልሉ የሚፈሱ ወንዞች በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው፣ ውኃ አጠር የሆነ ክልል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በመሆኑም በክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ሥራና የደን ልማት ከምንም በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡
የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ግን ያላቸውን የሸለቆ ሀብት ብቻ በማልማት የክልሎቹን ኢኮኖሚ ሙሉ ለሙሉ መለወጥ ይቻላል፡፡ አንድ አገር ታላላቅ ተራሮች ካሉዋት ታላላቅ ወንዞች ይኖሯታል፡፡ ወንዝ ካለ ደግሞ ታላላቅ ሸለቆዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ውኃውን ሸለቆው ውስጥ በማከማቸት የውኃ ባንክ በመፍጠር ዜጎችን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፡፡
በመሆኑም በእኔ እምነት የኢትዮጵያ ትልቁ ሀብት የሸለቆ ሀብት ነው፡፡ ይህ ማለት ከላይ የተጠቀሱት የተፈጥሮ ሀብቶች ትርጉም የላቸውም ማለት ሳይሆን፣ ቅደም ተከተል ሲቀመጥ ሸለቆ ትልቁ የሀብት ምንጭ ነው ብለን መደምደም የምንችል ይመስለኛል፡፡
በጥንታዊው አባባል ‹‹ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል›› የሚለው ፈሊጥ አሁን ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ዓባይ ውሎ አድሮ የዜጎቹን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ቀይሮ፣ ሌሎች ሕዝቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ ጉዞውን ይቀጥላል ሊባል ይችላል፡፡ ወይም፣ ደግሞ ‹‹ዓባይ ራሱ ለበርካታ ዓመታት በቆፈረው ሸለቆ ውስጥ ውሉ አድሮ ከፍተኛ ጥቅም ሰጥቶ ጉዞውን ይቀጥላል›› ማለት እንጀምራለን፡፡ ዓባይ ሸለቆ ባይኖረው ኖሮ፣ ‹‹ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል›› የሚለው አባባል ማለቂያ ሳይኖረው ለዘለዓለም ይቀጥል ነበር፡፡
በእኔ ግምት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የዓባይ ግድብን ሲመርቁ ከሚናገሩት አንዱ አባባል፣ ‹‹ለዓባይ ማደሪያና መዋያ ተበጀለት›› የሚል ይመስለኛል፡፡ ሁላችንንም ለዚያ ያድርሰንና ስለግድቡ ስናወራ ልናውቀው የሚገባ ትልቁ ቁም ነገር አጠቃላይ ውኃውን ከሚይዘው ተፈጥሮዓዊ ግድብ ሰው ሠራሹ ከአንድ በመቶ በታች መሆኑን ነው፡፡ ጠባብ ቦታ ተፈልጎ ጠንካራ ግድብ መሸከም የሚችል ቦታ ተፈልጎ ሲገነባ ወንዙ ራሱ ከፈጠረው ሰፊ ሸለቆ ሰው ሠራሹ ግድብ በእጅጉ ዝቅተኛ ነው፡፡ በመሆኑም አንድ አገር በርካታ ግድብ ሊገደብባቸው የሚችሉ ሸለቆዎች ካአሏት ያን ትልቅ ሀብት ነው ኢትዮጵያ አገራችንም መጠቀም ያለባት፡፡ የዚህ ሀብት የተትረፈረፈ ባለቤት በመሆንዋ ሁላችንም ልንኮራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
