Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

እግር ኳሳችን ከቻይና እግር ኳስ ቢማርስ?

$
0
0

ስለ እግር ኳሳችን ስናወሳ ሁሌም የኋላ ታሪኩን መነሻ አድርገን መጻፋችን ክፋት አለው የሚል እሳቤ ባይኖረኝም፣ ታሪክ እንዳለን ማሳያ መሆኑ እሰየው የሚባልለት ነው ብዬ መግለጽ እወለዳሁ፡፡ ነገር ግን ሁሌም ያለፈውን ታሪክ እንደ ጀብዱ ቆጥረነው መሥራች በመሆናችን ብቻ፣ ልንኮራበትና አለፍ ሲልም ልንኮፈስበት የሚያስችለን ዘመን እያበቃ ለመሆኑ ራሳችን ደፍረን መናገር መቻሉ ነውር ያለው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ሆነን ለመገኘት በታሪክ ዋሻ ተደብቆ በመኖር ብቻ ዋስትና ሊሆን አያስችለንምና፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መሥራች ነን በማለት ራሳችንን የአፍሪካ ቁንጮ አገር አድርገን ስንተርክ፣ በጣም ብዙ አገሮች የእግር ኳስ ሥራን እንዴት መሥራትና አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ተገንዝበውና አውቀው በተግባር በማዋል ቀድመውንና ጥለውን ትልቅ ደረጃ አድርሰውታል፡፡ እኛ ግን አሁን ‹አትንኩኝ! አትንኩኝ!› እያልን በቀረርቶና በሽለላ ዕድሜያችንን በመቁጠር ላይ እንገኛለን፡፡

ለእግር ኳሳችን አዲስ ሐሳብ ይዞ የመጣን ግለሰብ እንደ ጠላት ቆጥረን በማዋከብና በማብጠልጠል ሌላ ለዕድገት የሚጠቅም ሐሳብ ይዞ እንዳይመጣ በማድረግ፣ ወይም ሁለተኛ ‹‹ይቺን ደጃፍ እንዳትረግጥ›› በሚል ዛቻና ማስፈራሪያ አዘል ማስጠንቀቂያ ማስተናገድ የተመደበለት አካባቢ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የተለያዩ ሐሳቦችን ማስተናገድ የማይችለው እግር ኳሳችን የትውልድ ቅብብሎሽን የማይቀበል፣ ለተሻለ ለውጥና ዕድገት የማይተጋ፣ ሁሌም ‹‹ኳስ በእኛ ጊዜ ቀረ›› በሚል ኋላቀርና ልማዳዊ አሠራር የተተበተበ አካባቢ ሆኗል፡፡ ይህን ፀረ ዕድገትና ፀረ ለውጥ አስተሳሰብና አመለካከት የወረረውን እግር ኳሳችን ችግሩን ተረድቶ ለመለወጥና ለማሳደግ የተለያዩ አገሮች ተሞክሮ መቅሰምና መቀበል እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

በዋናነት የዚህ ጽሑፍ መልዕክት በእግር ኳሳችን ዙሪያ ያሉትን ብልሹ አሠራሮችና በአጠቃላይ ኋላ ቀር ባህሎችን በመጠቆም ሌላውን አካል ለማብጠልጠል የሚሞክር ሳይሆን፣ ላለፉት 70 ዓመታት በአንድ ዓይነት ቅኝት ተቃኝቶ ለሚጓዘውና አሁን አሁን ግራ ለገባው አማተር አይሉት ፕሮፌሽናል እግር ኳሳችን ለለውጥ እንዲዘጋጅ ለመጠቆም ነው፡፡ በመሆኑም ከዚያ አልፈው በምጽፈው ጽሑፍ የማይደሰቱ ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ ብዬ ብገምትም እንኳን፣ ተነካንና ተደፈርን ብለው ሊቆጡኝና ሊያስፈራሩኝ ይችላሉ ብዬ ግን አልገምትም፡፡ ምክንያቱም ዘመኑ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕገ መንግሥታችን የተደነገገበት ነውና፡፡

በተጨማሪ እየጻፍኩኝ ያለሁት ስለግለሰቦች ክብርና ጥቅም ሳይሆን ሕዝባችን እየተቃጠለበትና ስሜቱ እየተጎዳበት ስላለው ደካማው እግር ኳሳችን ነው! እየጻፍኩኝ ያለሁት የወጣቶችንና የሕፃናቶቻችን ሥነ ልቦና በተሸናፊነት ሞራሉንና ጉልበቱን እየሰለበው ስለመጣው እግር ኳሳችን ነው፡፡ እየጻፍኩኝ ያለሁት ራሱን መቻል አቅቶት እየተንገዳገደና እየተልፈሰፈሰ ስለሚገኘው እግር ኳሳችን ነው፡፡ እግር ኳሳችን ከተጠቀሱት ችግሮች እንዴት አድርጎ ወጥቶ ሕዝባችንን ያስደሰትና በደስታ ይጨፍር ነው፡፡ እየጻፍኩኝ ያለሁት እግር ኳሳችን እንዴት ሀብታም ሆኖ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትና ወጣቶችን አሠልጥኖ ውጤታማ ተጫዋቾች ተፈጥረው አገራችንን የዓለም እግር ኳስ የበላይ ትሁንልን ነው፡፡ እየጻፍኩኝ ያለሁት እንዴት በሺሕ የሚቆጠሩ ሜዳዎችን ሠርተን ሕፃናትና ወጣቶች ይሠልጥኑባቸው ነው? እየጻፍኩኝ ያለሁት ኢትዮጵያችን እንዴት አድርጋ አሸናፊ ትሁንና የዓለምን ቀልብ ትሳብ ነው! እንግዲህ ሐሳቤ ሲጠቃለል እግር ኳሳችን እንዴት ጠንካራ፣ ሀብታምና አሸናፊ ሆኖ ሕዝባችን ያስፈንድቅ፣ ያዝናና፣ በኢኮኖሚም ይጥቀመን ነው፡፡ በዚህ የማይስማማ ግለሰብ ካለ ሌላ ስም አልሰጠውም፡፡ የአገር ልማት የማይመኝ ስለሆነ ደካማ አስተሳሰቡን እንዲያሻሽል መምከር ነው፡፡

በመሠረቱ የአሁኑ እግር ኳስ ከማዝናናቱ ባሻገር ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ኢንዱስትሪ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ ቢሊዮን ዶላሮች እያንቀሳቀሱበት የሚገኘው ይህ ኢንዱስትሪ የብዙ ኃያላን አገሮች ሕዝቦችን ቀልብ እየሳበ በመሄዱ መንግሥታትም እየገቡበት መሄድ አጀማመሩ ሰንበትበት ብሏል፡፡ የሕዝቦችንም ቀልብ እየሳበ በመሄዱ መንግሥታትም እየገቡበት መሄድ ከጀመሩ ሰንበትበት ብሏል፡፡ በቅርቡ የቻይና እግር ኳስ ማኅበር እየሄደበት ያለውን በእርግጥም አስፈሪና ድፍረት የተሞላበት ጅማሮ እየታዘብን ነው፡፡ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የአገራቸውን እግር ኳስ ወደ ተፎካካሪነት ጎራ ለመቀላቀል አቅደው ተነስተዋል፡፡ ኳታርና ሩሲያም የዓለም ዋንጫ ውድድርን ለማዘጋጀት እያወጡት ያለው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር አሁንም ደግሜ ልጥቀሰው የእግር ኳስ ኃያልነት፣ ሀብት አመንጪነትና የሕዝቦች ቀልብ ሳቢነቱ እየጨመረ ለመሄዱ ማሳያ ምልክት ነው፡፡

በዓለማችን በአሁኑ ጊዜ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካዊና በማኅበራዊ ይዞታዋ ተጠቃሽ እየሆነች ስለመጣችው ቻይና ብዙ እየተነገረ ነው፡፡ በአጠቃላይ በሥልጣኔ ተራምደዋል ከተባሉ ኃያላን የዓለማችን አገሮች ግንባር ቀደምትነት ተራ ይዛ የምትገኝ አገር ናት፡፡ በቴክኖሎጂ፣ በወታደራዊና በኮንስትራክሽን … ወዘተ. ተወዳዳሪ በመሆን መላውን ዓለም እንደ ሞዴል እየተጠቀመባት ያለች አገር ነች፡፡ ነገር ግን በእግር ኳስ ወደ ኋላ የቀረች፣ በዓለም ደረጃ ይቅር በእስያም እዚህ ግባ የሚባል እግር ኳስ የላትም፡፡ በዓለም ዋንጫም እ.ኤ.አ. በ2002 ጃፓንና ኮሪያ ባዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ከመሳተፍ የዘለለ ሪከርድ አልነበራትም፡፡

የቻይናውያን ስሜትና ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ከዓለም እግር ኳስ ቀደምት ተርታ እንዴት አልተሠለፍንም በሚል ቁጭት ተነሳስተው፣ ለቀጣይ 30 እና 40 ዓመታት ራዕይ ሰንቀውና ዕቅድ ነድፈው የዓለም እግር ኳስን በበላይነት ለመጎናፀፍ ተነስተዋል፡፡ ከዚህ ከመንደርደርም ራዕያቸውንና ዕቅዳቸውን ለመተግበር ሌት ተቀን ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ዕቅድ ትግበራ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቻይናውያን ሕፃናትና ወጣቶች ተሳታፊ የሚሆኑበት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ነድፏል፡፡

በዕቅዳቸው ትልቁ በረዥም ጊዜ ሊሳካ ይችላል ብለው ተማምነው ያስቀመጡት ግብ እ.ኤ.አ. በ2050 ቻይና የዓለም እግር ኳስ ኃያል አገር እንሆናለን በማለት ለዛሬ 34 ዓመታት ለመሥራት ማቀዳቸው በእርግጥም ልንማርበት ይገባናል፡፡ በዕቅዱ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2050 የዓለም እግር ኳስ ኃይል (World Football Super Power) ለመሆን የሚያስችላቸውን ሥራ ለመጀመር የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ተግባራዊ በማድረግ ተነስተዋል፡፡ በዚህ መሠረትም በአጭር ጊዜ እ.ኤ.አ. በ2020 ግባቸው ሃምሳ ሚሊዮን ሕፃናትንና ወጣቶችን እግር ኳስ መጫወት እንዲችሉ ተሳታፊ ያደርጋሉ፡፡ በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ2030 ለአሥር ሺሕ ሰዎች አንድ የእግር ኳስ ሜዳ እንዲኖር የሚያደርግ ዕቅዱ ውስጥ አስቀምጠዋል፡፡

በሌላ በኩልም የአገሪቱ እግር ኳስ ዕድገት መገለጫ ከሆኑት ውስጥ የብሔራዊ ቡድኖቻቸው ጥንካሬ አንዱና ወሳኙ ሥራ ነው ብለው አስቀምጧል፡፡ በዚሁ መሠረትም የቻይና ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በእስያ አገሮች በቅርብ ጊዜ የበላይነት እንዲጎናፀፍ ማስቻል ሲሆን፣ በሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድናቸው ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2030 በዓለም ደረጃ በበላይነት የሚጠቀስ እንዲሆን መሥራት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ግባቸው ነው፡፡

በአጠቃላይ እ.ኤ.አ. በ2050 ቻይና ለዓለም አቀፍ እግር ኳስ በስጦታ ልታበረክተው ያሰበችው ዕቅዷ ውስጥ የተቀመጡና ለተግባራዊነቱም በመንቀሳቀስ የዓለማችን እግር ኳስ በአንደኛ ደረጃ ኃያል የእግር ኳስ አገር መሆኗን ማረጋገጥ ነው፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ የፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ከ204 አገሮች 81ኛ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ይህንን ሁሉ እመርታ ለማሳየት ከ30 እና ከ40 ዓመታት በኋላ ስለሚሆነው አቅዶ መነሳት ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡ ከነፓናማ፣ ሐይቲና ቤኒን በታች የምትገኘው ቻይና አሁን ያለው ደረጃዋ እኔን አይገልጽም ብላ በቁርጠኝነት ተነስታ ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡

ሌላው የእግር ኳስን ጥራት ለማስጠበቅ የቻይና ሱፐር ሊግ ውድድርን ወደ ፕሮፌሽናል ሊግነት ማሳደግና ከአውሮፓ ሊጎች ጋር ተወዳዳሪ ማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም ይህንን ለመተግበር የአውሮፓ ታላላቅ፣ ስመ ጥርና ገናና ተጨዋቾችን እየገዙ በየክለቦቿ ተመዝግበው በመጫወት ላይ ናቸው፡፡

ብራዚላዊው የቼልሲ ተጨዋች ራሚረስ፣ አሌክስ ቴክሴራና ጃክሰን ማርቲኔዝ የመሳሰሉትን በሊጉ ውስጥ ተካተው እንዲጫወቱ በማድረግ የሊጉን ደረጃን ከፍ ለማድረግ እየሠራች ነው፡፡ ነገር ግን የውጭ ተጨዋቾች ቁጥርን ከአራት ተጨዋቾች በላይ ሜዳ ገብተው መጫወቱን አይፈቅዱም፡፡ የውጭ አገር በረኛ ቻይና ክለቦች ውስጥ ተመዝግቦ መጫወት አይፈቀድም፡፡ ምክንያቱም የአገር ውስጥ በረኞች በትልልቅ የሊጉ ጨዋታዎች የመጫወት ዕድል እንዲያገኙና ልምድ እንዲቀስሙ ያበረታታሉ፡፡ ይህ ትልቅ ውሳኔ የሚፈልግ ሐሳብ ለኢትዮጵያ እግር ኳስም ወሳኝነቱ አያጠራርጥም፡፡ ፌዴሬሽናችንም እነዚህን የመሳሰሉ ውሳኔዎችን የመወሰን ድፍረት መማር ይኖርበታል፡፡ ለአንድና ለሁለት ክለቦች ጥቅም የአገርን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ አሠራር ነው እየተከለተ ያለው፡፡ ስለዚህ አርቆ የሚያስብ ፌዴሬሽን ቅድሚያ ከ90 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚወክለውን ብሔራዊ ቡድን ለማጠናከር ነው ማቀድ ያለበት፡፡

የቻይና እግር ኳስ ተወዳዳሪነቱን በዓለም ደረጃ ከፍ ለማድረግ የፕሮፌሽናል ሊግ ምሥረታን አስቀድሞ እ.ኤ.አ. በ2004 ጀምሮ እያሟሟቀው ይገኛል፡፡ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚያፈሱ ክለቦችን ለመመሥረት የዓለማችን ታዋቂ አሠልጣኞችን ወደ ቻይና ክለቦች ለመሳብ ችሏል፡፡ ኤሪክሰን የቀድሞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ፣ ፍሊፕ ስኮላሪ የቀድሞ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ የመሳሰሉ አሠልጣኞችን በየክለቦቻቸው ተቀጥረው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

በአጭሩ ቻይናውያን የአገራቸውን እግር ኳስ ዕድገት በመመኘት በእግር ኳስ ዙሪያ እየሠሩዋቸው ያሉት ሥራዎች እጅግ የሚያኮሩና ተስፋ የተጣለባቸው ዕቅዶች ናቸው፡፡ የአገሪቱ መሪዎች ፕሬዚዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የበኩላቸውን ዕገዛ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከያዙዋቸው ዕቅዶች መካከል ፕሬዚዳንቱ የሚፈልጉት በሚቀጥሉት 15 ዓመታት የዓለም ዋንጫ በቻይና እንዲዘጋጅ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለቻይና በጣም ቀላል ይሆንላታል ተብሎ ይገመታል፡፡ እ.ኤ.አ. 008 ኦሊምፒክን ያዘጋጀች አገር የዓለም ዋንጫ ማዘጋጀት አይከብዳትም፡፡ በመሆኑም የቻይናውያንን ህልም ለማሳከት ሕዝቡ፣ ባለሀብቱና መንግሥት ተረባርበው ለውጥና ዕድገት ለማምጣት ተነስተዋል፡፡

ትልቁ የዚህ ጽሑፍ መልዕክት እግር ኳሳችን ከቻይና እግር ኳስ ምን ይማራል? የሚል ነውና የእግር ኳስ መሪዎቻችን ከቻይናውያን እግር ኳስ መሪዎች ተምረው ለለውጥ መነሳት አለባቸው፡፡ ከረዥም ዓመታት ጀምሮ አቅጣጫው የጠፋበት መርከብ ሆኖ የሚንገዋለለውን እግር ኳሳችን፣ አቅጣጫውን ለማሳየት የተደገፈ ሙያተኛ የሚመራው አካሄድ መከተል አለበት ነው የምንለው፡፡ በስሜትና በፍላጎት ሳይሆን በእግር ኳስ ዕውቀት እየተመራ ለዘላቂ ዕድገት የሚያስብ ሩቅ አስቦ ተግቶ የሚሠራ አመራር መሆን አለበት፡፡ ስለአሁን ማሸነፍና መሸነፍ ሳይሆን እግር ኳስን በሕፃናትና በወጣቶች ተወዳጅ ስፖርት በማድረግ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ተሳታፊ ሕፃናትና ወጣቶች በመቶ የሚቆጠሩ ጥበበኛ ባለክህሎት ተጨዋቾች ማፍራትን ነው፡፡ አሁን እየጠፋ ያለው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የመንግሥትና የሕዝብ ገንዘብ ከንቱ አይቅር! መፍሰስ ባለበት ይፍሰስ፡፡ ለእግር ኳስ መዋል ያለበት በእግር ኳስ ይዋል ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ በአጠቃላይ በእከክልኝ ልከክልህ፣ በአድርባይነት፣ በመንደርተኝነትና በመሳሰሉት የተዘፈቀው እግር ኳሳችን ይፅዳና ውጤታማ ይሁን ነው፡፡

ለማንኛውም በዚሁ ጽሑፍ ቅሬታ የሚያድርበት ካለ እሱ የአገራችን እግር ኳስ ዕድገት የማይመኝ ‹‹ለሆዱ አዳሪ›› ብቻ መሆን አለበት ብዬ ነው ልገልጸው የምችለው፡፡ በሌላ ጽሑፍ እስከምንገናኝ መልካሙ ይግጠማችሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው  abrhilo14@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles