ባለፈው ወር የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ተወካዮች በኒውዮርክ ባካሄዱት ስብሰባ ለኢትዮጵያ አንድ ለየት ያለ ውሳኔ ማሳለፉቸው ይታወቃል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ተለዋጭ የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገር አድርጐ የሹመት ደብዳቤ በመስጠት የሁለት ዓመት አባልነቷን አረጋግጧል፡፡ አንድ መቶ ሃያ ሰባት አገሮች ድምፅ ቢሰጧት አባል የመሆን ዕድል የነበራት ኢትዮጵያ፣ የአንድ መቶ ሰማኒያ አምስት አገሮችን ድምፅ ተችራ የምድራችንን ፖለቲካዊ ሁኔታ ይወሰናል ተብሎ በሚገመተው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆናለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ1959 እና በ1981 አባል የነበረች አገር በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ ዕድሉን አግኝታለች፡፡
ዕድሉን ለምን አገኘች? የሚል ጥያቄ ብናነሳ መልሱ ሊሆን የሚችለው ኢትዮጵያ ከቀጣናዊ ሚናዋ ባሻገር በአኅጉራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዓለም ሕዝብ ሰላምና ፀጥታ መስፈን በተጫወተችው ሚና፣ የተሰጣት አረንጓዴ ካርድ ነው የሚል ምላሽ ልናገኝ እንችላለን፡፡
ይህች አገር እንደ አገር ከተቆረቆረችበት ከ3,000 ዓመታት ጀምሮ የነበራት ኃያልነትና ተሰሚነት ከፍ ያለ እንደነበር ከታሪክ እንረዳለን፡፡ ዕድለኛው ደቡብ ዓረቢያ ተብሎ ይጠራ የነበረውን ግዛት ከማስተዳደር ጀምሮ በወራሪው ጣሊያን ላይ ያሳየችው የጀግንነትና የበላይነት ተጋድሎ ተፍቆ የማይጠፋና ብል የማይበላው የታሪክ አካሏ ነው፡፡ ይህ ታሪክ ደግሞ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ታሪክ ሆኖ ሲታወስ እንደሚኖር ጸሐፍትና ባለሙያዎች ብዕራቸውን አንስተው በነጭ ወረቀታቸው ላይ አስፍረውት ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል ባርትንስኪ ማኬል የተባሉ የእንግሊዝ የታሪክ ተመራማሪ፣ ‹‹የግዮን ወንዝ መፍለቂያ የሆነችና በምሥራቅ አፍሪካ የምትገኝ አንድ ኃያል አገር አለች፡፡ ስሟም ኢትዮጵያ ይባላል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ እንደ ባርትንስኪ ገለጻ ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ (The Water Tower of East Africa) ብቻም ሳትሆን ኃያሏና ስመ ገናናዋ አገር ተብላ ትጠራ እንደነበር እንረዳለን፡፡
እንግዲህ ኢትዮጵያ ይህን የመሰለና የተከሸነ ታሪክ ባለቤት መሆኗ የዓለም ምሁራንና ባለሙያዎች በየብዕሮቻቸውና ሚዲያዎቻቸው ሲጽፉ ማንበብና ሲናገሩ መስማት አዲስ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ጉዳይ ብርቅ ባልሆነበት አገር ውስጥ ተለዋጭ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆኖ መሾም ምን ይደንቃል የሚል አስተያየት ሊቀርብ ይችላል፡፡ ይህ አስተያየት እውነታነትና ተቀባይነት ያለው ጉዳይ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የምሥረታ ቻርተር ከማርቀቅ አንስቶ እስከ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምሥረታ ድረስ ከፍተኛ ሚና የነበራት አገር፣ ዛሬ በስንት ዓመት አንዴ ያውም አብዛኛዎቹ የአኅጉሮቹ አገሮች ዕድል እንዲያገኙ ተደርጐ በሚሰላው ሒሳብና በሚሰጠው ድምፅ አገራችን ዕድሉን ማግኘቷ አዲስ ጉዳይ እንዳልሆነ፣ እንዲያውም ከዚህ የተሻለ ኃላፊነት ብትታጭ እንኳ የሚያንሳት መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለችበት ነባራዊ ሁኔታስ ምን ይመስላል? የሚል ጥያቄ ብናነሳ ገና ውስጣዊ ችግሮቿ ፊቷ ላይ አፍጥጠው ያሉባት አገር በመሆኗ ለራሷ ቅድሚያ ብትሰጥ የሚል አስተያየት አስፍረን እናልፋለን፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በጅማሮ ላይና ይበል የሚያሰኙ መሠረተ ልማቶች ላይ ብትሆንም፣ በተቃራኒው ደግሞ የአገሪቱን ኢኮኖሚና የቆየ ታሪክ ጥላሸት የሚቀቡ ድርጊቶች እየተከናወኑባት ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል በመልካም አስተዳደር ዕጦት እየተከሰቱ ያሉ ኢ-ፍትሐዊ አሠራሮችና ሙስና ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ይፋ ባደረገው ሪፖርት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንኳ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ በሕገወጥ መንገድ ግለሰቦች እጅ እንደገባ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ የብዙ ሺሕ ኢትዮጵያውያንን ድህነትና ረሃብ ሊቀርፍ የሚችል ገንዘብ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት በአገራችን በተለይም በአዲስ አበባ የሙስናና የኢ-ፍትሐዊ አሠራር ደረጃዎችና ውስብስብነታቸው ከፍ እያለ እንደመጣ እንረዳለን፡፡
ሌላው ጉዳይ ደግሞ በኢኮኖሚያዊ ችግር የተነሳ እየተስፋፋ የመጣው ስደትና የጐዳና ተዳዳሪነት ጉዳይ ነው፡፡ የዓለምን ሕዝብ ችግር ለመፍታት የተሰየመችው አገር የራሷን ችግር ለመፍታት ስትቸገር ስናይ ለመረዳትና ምን ብለን ማለፍ እንዳለብን እንቸገራለን፡፡
ሦስተኛ ችግር ተደርጐ ሊወሰድ የሚችለው ጉዳይ ደግሞ ከገጠር ወደ ከተማ ያለው ፍልሰት ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ መንግሥት ብዙ ትኩረት እንዳልሰጠው ብንረዳም፣ በአገሪቱ በተለይም በከተሞች የኑሮ ውድነት ላይ እያደረሰ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ ከባድ ሆኗል፡፡ ይህ ጉዳይ በከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ዕጦትና ሌሎች ማኅበራዊ ቀውሶች እያስከተለ እንደሆነ ግልጽ ጉዳይ ነው፡፡
ከአገሪቱ ውስጣዊ ችግሮች አለፍ ስንል ደግሞ ኤርትራን እናገኛለን፡፡ ወንድምና እህት የሆነው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ በኤርትራው ገዥ መንግሥት ፖለቲካዊ አቋም የተነሳ ሁለቱ ሕዝቦች ተራርቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር አስመራ ላይ የከተመው የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት የሚፈትል የሚቋጥረው ጉዳይ ቢኖር ኢትዮጵያን የማተራመስ አጀንዳ ቀርፆ መንቀሳቀስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንጀለኛና አሸባሪ ተብለው የተፈረጁትን ቡድኖች ወታደራዊ ሎጅስቲክስ ከማሟላት ባሻገር ሥልጠና በመስጠትና በማስታጠቅ ኢትዮጵያ እንደ ሶሪያና ሌሎች የአሸባሪዎች መናኸሪያ እንደሆኑት አገሮች ለማድረግ ሌት ከቀን እየሠራ መሆኑ የዘወትር ድርጊቱ ገላጮች ናቸው፡፡
በእነ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ብርቱ ትግል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ በኢትዮጵያና በኤርትራ እ.ኤ.አ በ1952 ተመሥርቶ በ1962 ዓ.ም የፈረሰውን ፌዴሬሽን ተከትሎ፣ የተከፉ ኤርትራውያን የተወሰኑ የዓረብ አገሮችን ድጋፍ አገኙ፡፡ በዚህም የተነሳ እነዚህ አገሮች ኤርትራ ዓረባዊ ናት መገንጠልና የራሷን እስላማዊ መንግሥት ማቋቋም አለባት በማለት እ.ኤ.አ በ1961 ‹‹ተጋድሎ ሓርነት ኤርትራ›› ወይም በዓረብኛ አጠራሩ ‹‹ጅብሃት ታህሪረል ኤሪትሪያ (ጀብሃ)›› የተባለ ቡድን እንዳቋቋሙ ታሪክ ይናገራል፡፡ እንግዲህ ይህ ቡድን እርስ በራሱ ሲጨፋጨፍ ኑሮ ነው በመጨረሻ ‹‹ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ)›› በሚል ኃይል የተተካው፡፡ ሻዕቢያም በተወሰኑ የሙስሊም ዓረብ አገሮች ዛሬ በዘሩት ልክ እያጨዱ ያሉትን ኢራቅና ሶሪያን ጨምሮ ትጥቅና ስንቅ በገፍ እየቀረቡለት ኤርትራን የመገንጠል ህልም እውን ያደረገው፡፡
ዛሬ አስመራ ላይ ከትሞ የገዛ ወገኑን ለባህር አዞና ለበረሃ ሰለባ እያደረገ ያለው የኤርትራው አምባገነን መንግሥት ኢትዮጵያን የአገሮች ሁሉ ጭራ የማድረግ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለተለዋጭ የፀጥታው ምክር ቤት የሰጣትን አረንጓዴ ካርድ ጥላሸት ለመቀባትና ካርዱ እንዳይሠራ የማድረግ አባዜውን አጧጡፎ የነበረው፡፡
ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ኤርትራና በዙሪያዋ ያሉ አሸባሪዎች የኢትዮጵያን ህልውና እስከ ማፈራረስ የሚደርስ አጀንዳ ቀርፀው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ቡድኖች በመሆናቸው፣ የአገራችን መንግሥት በውጭ ፖሊሲ ግንኙነት ላይና በዓለም ላይ ተሰሚነትንና ዝናን ለማትረፍ ደፋ ቀና ከሚል፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ቢሠራ የተሻለ እንደሚሆን አስተያየቴን ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡
ውስጣዊ ችግሮች ለውጫዊ ችግሮች በር የሚከፍቱ ጉዳዮች በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት የአገራችን መንግሥት እዚህም እዚያም እየታዩ ያሉ ውስጣዊ ችግሮች ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት፡፡ ለእያንዳንዱ ችግር ተገቢው ምላሽ መሰጠት አለበት፡፡ የችግር ከባድና ቀላል ስለሌለው እዚህም እዚያም እየታዩ ላሉ ችግሮች አፋጣኝ መልስ መስጠት ይገባል፡፡ በየቴሌቪዥኑና ጋዜጣው የአገራችንን ዕድገትና ከየትኛው አገር ጋር የንግድና ሌሎች ተያያዥ ስምምነቶችን መፈራረማችንን የማስተጋባት አባዜ ወጥተን በትክክልና የሕዝባችንን ችግር ሊፈታ በሚቻል ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን፡፡
የሚነሱ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በተገቢ ሁኔታ ምላሽ ማግኘት አለባቸው፡፡ ተለዋጭ የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገር ሆነን የዓለምን ችግርና ኢ-ፍትሐዊ አሠራር እንታገላለን እያልን ወደ ውጭ ከማሰብ አባዜ ወጥተን፣ እየተሠሩ ያሉ ኢ-ፍትሐዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አሠራሮችን በቁርጠኝነት መታገልና ማስወገድ አለብን፡፡ የችግሮቹን ምንጭና መንስዔ ከሥሩ በመለየት መፍትሔ መስጠት ይገባል፡፡ ያኔ ለውጫዊ ኃይሎች ተጋላጭ አንሆንም፡፡ ውጫዊ ኃይሎችም ቢሆኑ መግቢያ ቀዳዳ አያገኙም፡፡ ቢገቡ እንኳ ሕዝቡ ራሱ ያጋልጣቸዋል፡፡ ያኔ ለፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ብንሆን ተሰሚነታችንና ተፅዕኖ ፈጣሪነታችን ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ኤርትራም ካርዳችንን ወደ ቢጫነትና ቀይነት የመቀየር አቅምም ተቀባይነትም አይኖራትም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው zemelove@gamil.comማግኘት ይቻላል፡፡
,
