በአካል ጉዳተኛው
መንግሥታት ይብዛም ይነስም በሌላ በማንኛውም አካል ሊከናወኑ የማይችሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አገልግሎቶችን ለሕዝባቸው ያቀርባሉ፡፡ ይህን ተኪ የሌለውን ሥራ ለማስፈጸም የሚችሉት ደግሞ ብቃትና ጥራት ያለው ሲቪል ሰርቪስ በመፍጠር ነው፡፡ ‹‹ሲቪል ሰርቪስ›› የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ሲሆን ጥሬ ትርጉሙ ‹‹የሕዝብ አገልጋይ›› ማለት ነው፡፡ በአገራችን የነበሩት መንግሥታት በባህሪያቸው ለሕዝብ ተጠሪና የሕዝብ አገልጋይ ባለመሆናቸው፣ የመንግሥት ሠራተኛ የሚመራበት አሠራርና አደረጃጀት አልነበራቸውም፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው አመለካከት ራሱን የሕዝብ ተቀጣሪና አገልጋይ አድርጎ እንዲቆጥር ሳይሆን፣ የሕዝብ የበላይ ተቆጣጣሪና ተገልጋይ አድርጎ እንዲቆጥር የሚያደርገው ነበር፡፡
ከ1983 ዓ.ም በኋላ ያለው መንግሥት ሲቪል ሰርቫንቱ የሕዝብ አገልጋይነት ስሜቱን እንዲያዳብርና በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመተግበር የተለያዩ ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በርካታ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሞችና ሕጎች ወጥተዋል፡፡ ይህን አደንቃለሁ፡፡ የዚህ ጽሑፌ ዓላማ ግን ባለፉት 25 ዓመታት ከመሻሻል ይልቅ እየባሰበት የሄደውን ሲቪል ሰርቪሱን የአንድ ድርጅት ካድሬ መዋቅር የማድረግ ሥራ በተመለከተ ያለኝን ሐሳብ ለማስፈር ነው፡፡
ውድ አንባቢያን በየትኛውም አገር ያለ ሲቪል ሰርቪስ በሕዝቡና በሕዝቡ ቀጥተኛ ተወካዮች አማካይነት የብዙኃኑን ይሁንታ አግኝተው የወጡትን ፖሊሲዎች የማስፈጸም ተልዕኮ ነው ያለው፡፡ በእርግጥ የወጡትን ፖሊሲዎች ለማስፈጸም በጥልቀት ከማወቅ ባሻገር በፖሊሲዎቹ ላይ ሲቪል ሰርቫንቱ ጠንካራ እምነት ቢኖረውና ቢያምንባቸው ለአፈጻጸም ምቹ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሲቪል ሰርቪሱ እምነት ባይኖረውም እንኳ ባለው አቅም ሁሉ ለማስፈጸም መረባረብ የውዴታ ግዴታው ነው፡፡ ሲቪል ሰርቪሱ ፖሊሲዎችን በብቃት ለመፈጸም ብቃትና የተስተካከለ አመለካከት እስካለው ድረስ፣ የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል በመሆኑ ወይም ከፖለቲካ ነፃ ነኝ ማንንም አልደግፍም ካለ የእኔ አባል ካልሆንክ ብቻ ተብሎ እንግልት፣ አድልኦና ጭቆና ሊደርስበት አይገባም፡፡ በእርግጥ በርካታ አገሮች የሲቪል ሰርቪስ መዋቅራቸውን የፖለቲካ ድርጅት ከመሆን የሚከለክሉ ሲሆን፣ በእኛ አገር ግን ይህ ክልከላ በሕግ ደረጃ ባይኖርም በተግባር ግን ቢገባህም ባይገባህም ኢሕአዴግን በመደገፍ ለሁሉም ነገር ከማጨብጨብ ውጪ ውልፍት ማለትና የተለየ ሐሳብ ማቅረብ የሚያመጣው ቅጣት ከባድ ነው፡፡
እንደ ሌሎች አገሮች በአገራችንም መንግሥት በመንግሥትነቱ መሥራት ያለበት የመረጠውንና ያልመረጠውን ሕዝብ በፍትሐዊነት ማገልገልና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማገልገል የሚያስችል እምነትና አመለካከት ያለው ሲቪል ሰርቪስ መፍጠር እንጂ፣ ከቀበሌ እስከ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ድረስ የገዥው ፓርቲ አባላትን ለመመልመል መሆን የለበትም፡፡ አይደለም በአንድ አገር ውስጥ በሚኖሩ ዜጎች መካከል በአንድ ቤተሰብ መካከል በሁሉም ነገር ተመሳሳይ አመለካከት ያለው ሰው ሊኖር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ተመሳሳይ ወይም ከአንድ ፋብሪካ የተመረቱ ዕቃዎች አይደሉምና፡፡ በዚች አገር የሚኖር የትኛውም ዜጋ ፍላጎቱና ምኞቱ አገሩ አድጋና በልፅጋ ማየት ነው፡፡ ምኞቱን ተግባራዊ የሚያደርግበት መንገድ ግን የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ሁሉም ሐሳቦች የመደመጥ ዕድል አግኝተው የሰዎች ሳይሆን የሐሳብ ፉክክርና አሸናፊነት ኖሮ ለአሸናፊው ሐሳብ ሁሉም በጋራ መሥራት አለበት እንጂ፣ ከእኔ ሐሳብ ውጪ ሌሎች ሐሳቦች መደመጥ የለባቸውም የሚል ኢ-ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ካዳበርን አሸናፊ ሐሳቦችን እየገደልንና ‹‹አድርባይነትን›› እያበረታታን ነው ማለት ነው፡፡ የአባላት ምልመላ ሥራ የፖለቲካ ድርጅቶች እንጂ የመንግሥት አይደለም፣ ሊሆንም አይገባውም፡፡ አሁን በአገራችን ያለው መንግሥት ግን የፖለቲካ ድርጅት የሚሠራውን ሥራ የሚሠራ፣ ደጋፊዎችን (አባላትን) ለፓርቲ የሚመለምል፣ አባል ያልሆኑትን ከመንግሥት መዋቅር እየመነጠረ የሚያወጣ፣ ሲቪል ሰርቫንቱን በፖለቲካዊ አመለካከታቸው የሚያስቀምጥበት፣ የእኔ አባል ያልሆነ ሁሉ ተቃዋሚ ነው በማለት ድራሹን ለማጥፋት የሚሠራ ነው፡፡
በአንቀጽ 38 እና በሌሎች በርካታ የኢፌዲሪ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች መሠረት ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ልዩነት እንደማይደረግባቸው ተገልጿል፡፡ ሆኖም ግን ኢሕአዴግ በሕገ መንግሥቱ እንደነገረን ሳይሆን በአገሪቱ ሁለት ዓይነት ዜጎች ፈጥሮ እያሳየን ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ‹‹አይነኬዎች›› ወይም የድርጅት አባላት ሲሆኑ ሌለኞቹ ደግሞ ‹‹ተረፈ ዜጋዎች›› ወይም የድርጅት አባል ያልሆነው ነን፡፡ ከታች ከቀበሌ አንስቶ እስከ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ድረስ የገዥው ፓርቲ አባል አለመሆን በወንጀል ያስቀጣል ተብሎ የታወጀ እስኪመስል ድረስ፣ መንግሥት የመንግሥትነት ሥራውን ትቶ ሁሉም ሲቪል ሰርቫንት ከቅጥር ፎርም ጋር በግዴታ የድርጅት ፎርም በማስሞላትና አባላትን በማጋበስ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ እኔ የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆንም ሆነ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ አልፈልግም ያለ ሲቪል ሰርቫንት አንተ ደጋፊ ካልሆንክ ተቃዋሚ ነህ ተብሎ ተፈርጆ ጫና ይደረግበታል፣ ይዋከባል፣ ክትትል ይደረግበታል፣ ጀርባው ይጠና፣ የአመለካከት ችግር አለበት፣ ፀረ ልማት፣ ተላላኪ፣ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ፣ ጠባብ፣ ትምክህተኛ፣ ወዘተ. የሚል ታርጋ ተለጥፎበት በፍርኃት የድርጅት አባል እንዲሆን አለዚያም አንዱ ከሳሽ አንዱ መስካሪ ሆኖ በእነሱ ቋንቋ ‹‹እንዲመታ›› ወይም መሥሪያ ቤቱን እንዲለቅ ይደረጋል፡፡
እንኳን ፖለቲካ ነገር ውስጥ መግባት አልፈልግም ያለ ሲቪል ሰርቫንት ቀርቶ ሥራውን በአግባቡ እስከሠራ ድረስ የተቀዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባልስ ቢሆን ጥፋቱ ምንድነው? ሲቪል ሰርቫንቱ አሁን ላይ የመጣበት ብሔር እየተጠቀሰ አማራ ከሆነ ትምክህተኛ፣ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ፣ የግንቦት 7 እና የሰማያዊ ፓርቲ ተላላኪ፤ ኦሮሞ ከሆነ ጠባብ፣ ፀረ አንድነት፣ ገንጣይ አስገንጣይ፣ የኦነግና የመድረክ ተላላኪ፤ ትግሬ ከሆነ የሻዕቢያ ቅጥረኛ፣ የአረና ጆሮ ጠቢ፣ ወዘተ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት እዚህ አካባቢ መወለዱን እስኪጠላ ድረስ ነው የሚሰቃየው፡፡ የደረጃ ዕድገት፣ የትምህርት ዕድል፣ አጫጭር ሥልጠናዎች፣ ሽልማቶች ሲመጡ ቅድሚያ ለድርጅት አባላት ነው እየተባለ ምንም የማይሠሩ የድርጅት አባላት ሲሾሙ፣ ሲሸለሙ፣ ሲያድጉ፣ ሲማሩ ለፍቶ የሚሠራ የድርጅት አባል ባለመሆኑ ብቻ እንዲንገላታ፣ እንዲታሰር፣ ከሥራ ተባሮ ያለሥራ እንዲቀመጥ፣ ብሎም በሕገወጥ መንገድ እንዲሰደድ ይደረጋል፡፡ ይኼ ነው በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ልዩነት አይደረግባቸውም ማለት?!! በፖለቲካዊ አመለካከታቸው እየተባለ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን አቅምና ብቃት በሌላቸው የድርጅት አባላት መሙላት ነው እኩልነት?!
በቅርቡ በአንድ መገናኛ ብዙኃን የሚሠራ ጓደኛዬ የድርጅት አባል በመሆኑ በሁለት ዓመት ውስጥ የሠራው ሁለት ፕሮግራም ብቻ ነው፡፡ ግን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ ኮከብ ሠራተኛ ተብሎ ተመርጦ ከመሸለሙም ባሻገር ሹመት ተሰጠው፡፡ ምክንያቱም የድርጅት አባል ነዋ፡፡ አሁን በምሠራበት መሥሪያ ቤት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያገለገለና በ2007 ዓ.ም. ከድርጅት አባልነት በቃኝ ብሎ ወጥቶ ጀርባው ይጠና እየተባለ የሚዋከብ አንድ የሥራ ባልደረባዬ የአገር ውስጥ የትምህርት ዕድል ተጻጽፎ ያገኛል፡፡ እናም በመመርያው መሠረት እንዲያስተናግዱት ሲጠይቅ መሥሪያ ቤታችን የድርጅት አባል ያልሆኑ ሰዎችን አቅም እያጎለበተ ለድርጅታችን ጠላት የምናፈራበት አይደለም፡፡ የድርጅት አባል ያልሆነን ሰው አቅም የማጎልበት፣ የማሳደግና የማስተማር ኃላፊነት የለብንም በማለት ያገኘውን የትምህርት ዕድል እንዲያጣ ተደረገ፡፡ ነገር ግን እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ነዋሪውን አማራችኋል፣ አቅም የላችሁም፣ የትምህርት ደረጃችሁ ዝቅተኛ ነው የተባሉ የወረዳ፣ የክፍለ ከተማና የከተማ የአመራር አካላት በሕዝብ ሀብትና ንብረት በአመራርነት ያገኙት የነበረውን ደመወዝ እያገኙ የትምህርት ወጪያቸው ተሸፍኖላቸው የድርጅት አባል በመሆናቸው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የትምህርት ተቋማት ገብተው እንዲማሩ እየተደረገ ነው፡፡ ይኼ ነው እንግዲህ ኢሕአዴግ በዜጎች መካከል ፈጥሬዋለሁ የሚለው እኩልነት??!!
ጥሩ ደመወዝ ለማግኘትና ሥራ ለመቀጠር የድርጅት አባል መሆን ግድ እየሆነ ነው፡፡ የትምህርት ተቋማት ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ነፃ ናቸው እየተባለ ገዥው ፓርቲ ግን በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ይመለምላል፣ ይሰበስባል፡፡ በተጨማሪም የድርጅት አባላት የሆኑና ተማሪዎችን የሚመለምሉት የተማሪዎች ዲን አባል እንዲሆኑ እየተደረገ የማስተርስ ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ በያዙት የድርጅት ወረቀት አማካይነት ያለ ውድድር እንዲመደቡ ይደረጋል፡፡ በዚህም በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ በትምህርት ጥሩ ግሬድ ከማምጣት ይልቅ በድርጅት “A”፣ “B”፣ “C” ማምጣት ይመረጣል፡፡ በቅርቡ በየክፍለ ከተማው እየተቋቋመ ላለው ‹‹መንገድ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት›› ሠራተኛ እየተቀጠረ ያለው በድርጅት አባልነት ነው፡፡ በየወረዳው ካሉ በማኔጅመንት ተመርቀው ስድስት ዓመት ያገለገሉ፣ የድርጅት አባል ሆነው በድርጅት ግምገማ “A” ያላቸው ሁለት ሰዎች እየተመለመሉ በስምንት ሺሕ ብር እየተቀጠሩ ነው፡፡ ለዚህም በክፍላተ ከተሞች እየተመለመሉና እየተመደቡ (እየተቀጠሩ አላልኩም) ያሉ ሰዎችን ማየትና ማጣራት አልያም …..ሕንፃ ሄዶ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የተመለመሉ ሰዎችን ስም ዝርዝር ማውጣት ይቻላል፡፡ እነዚህ ሰዎች ሰሞኑን ኦረንቴሽን ተሰጥቷቸው ወደ ሥልጠና ገብተዋል፡፡ ከየወረዳው ማደግ ካለባቸው እንኳ ሁሉም ስድስት ዓመት ያገለገሉ የማኔጅመንት ምሩቆች ተመዘግበው እንዲወዳደሩ ማድረግ ይገባ ነበር፡፡ እኔ የማይገባኝ ነገር የድርጅት አባል ያልሆነ ሲቪል ሰርቫንት የሚሠራው ለማን ነው? የሚያገለግለውስ የየትኛውን አገር፣ ዜጋና መንግሥት ነው? ከተቻለ ለዚህ መልስ የሚሰጠኝ አካል ቢኖር ደስ ይለኛል፡፡ በድርጅት አባልነት ብቻ አቅምና ብቃት የሌላቸውን ሰዎች በመቅጠር የመንግሥትን መዋቅር ወደ ድርጅት መዋቅር የመቀየር ሥራ እየተሠራ ለመሆኑ በቂ ማሳያ ነው፡፡
ምንም ሥራ ሳይሠሩ ለመኖር በፈለገው ሥርዓት ለመውጣትና ለመግባት የድርጅት አባል መሆን ግድ ይላል፡፡ የድርጅት አባል ያልሆነ ሰው ሁለት ሴኮንድ እንኳ ቢያረፍድ የሚደርስበት ዘለፋና ቅጣት የትየለሌ ነው፡፡ ታሞ ቢቀርና የሐኪም ማስረጃ ቢያመጣ እንኳ ተቀባይነቱ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ እንዴት ትታመማለህ፣ አውቀህ ሥራ ለመበደል ወይም ወሬ ለማቀበል ነው እንጂ እየተባለ ከተፈጥሮ ጋር እንዲታገል ይደረጋል፡፡ የድርጅት አባል የሆነ ሰው ግን በፈለገው ሰዓት ቢገባ፣ በፈለገው ሰዓት ቢወጣ፣ አንድ ወር ሆነ ሁለት ወር ከሥራ ገበታው ላይ ጠፍቶ ከርሞ ቢመጣ ‹‹የድርጅት ጉዳይ ስለነበረብኝ ነው›› ወይም ‹‹የድርጅት ሥራ ላይ ነበርኩ›› ብሎ መናገር ብቻ ይበቃዋል፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ ይኼው ሠራተኛ ‹‹ኮከብ ሠራተኛ›› ተብሎ ይሸለማል፡፡ የድርጅት ሥራን በብቃት የሚሠራ በዚያ ላይ ኮከብ ሠራተኛ ስለሆነ ተብሎ ይሾማል፣ የደረጃ ዕድገት ይሰጠዋል፣ እንዲሁም ትምህርት እንዲማር ይደረጋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በጣም የገረመኝ ነገር ‹‹አዲሱን የሥራ ምዘናና የደረጃ አወሳሰን›› በተመለከተ ለድርጅት አባላት ብቻ ሥልጠና ተሰጥቶ ለምን ለድርጅት አባላት ብቻ? የሚመለከተው ሁሉንም ሲቪል ሰርቪስ ስለሆነ እኛም ሠልጥነን ግንዛቤው ሊኖረን ይገባል ብለን ሁለት ሰዎች ስንጠይቅ፣ የድርጅት አባል ላልሆኑ ሰዎች አቅም አንገነባም አለን፡፡ ይኼው ሰውዬ መድረክ ላይ ወጥቶ ስለመልካም አስተዳደር፣ ስለፍትሕ፣ ስለዴሞክራሲ ሲያወራ ይሰማል፡፡ አስቂኝ እኮ ነው፡፡ ለነገሩ ከላይ ወርዶላቸው ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡
በአጠቃላይ ለአብነት ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸውን አነሳሁ እንጂ በድርጅት አባል በሆኑና ባልሆኑ ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት ከልጅና ከእንጀራ ልጅ ዓይነትም በላይ ነው፡፡ ስለሆነም ከላይ ያሉት ገዥዎቻችን ይኼን ችግር የማታውቁ ከሆነ በሕግ አምላክ እንለምናችሁ ከዛሬ ጀምሮ ታች ድረስ ፍተሻ አካሂዱ፡፡ የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴርም በየዓመቱ ትርጉም የሌለውን ‹‹የሲቪል ሰርቪስ ቀን›› ከማክበር በዘለለ ታች ድረስ ወርዶ ክትትል በማድረግ የድርጅት አባል ባልሆኑ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ወከባ ለማቃለል ትኩረት ሰጥቶ ይሥራ!!! ከወሬ ይልቅ ተግባር ይቅደም እያልኩ በተዋቂው ፈላስፋ ‹‹በጆን ስቲዋርት ሚል (John Stewart Mill)” ጽሑፌን ላብቃ፡፡
‹‹ከአንድ ሰው በስተቀር የሰው ዘር በሞላ አንድ ዓይነት አስተያየት ቢይዝና ያ ሰው ብቻ ተቃራኒ አስተያየት ቢያዳብር፣ ያ ሰው ማኅበረሰቡን ፀጥ ማሰኘቱ ተገቢ የማይሆነውን ያህል ማኅበረሰቡ ያንን ሰው ፀጥ ቢያሰኘው አግባብነት የለውም፡፡ … አንድን አስተያየት ፀጥ የማሰኘት (እንዳይገለጽ የመከልከል) ልዩ ክፋት የሰው ዘርን በሞላ ያለውንም የሚመጣውንም (የማወቅን ዕድል) መዝረፍ መሆኑ ነው፡፡ … ለመለጎም የምንጣጣራው አስተያየት ስህተት ለመሆኑ ማረጋገጫ የለም፡፡ ማረጋገጫ ቢኖርም እንኳ ለመለጎም መሞከሩ እኩይ ተግባር ነው፡፡ በባለሥልጣናት ሊታፈን የሚሞክረው አስተያየት እንዲያውም ልክ ሊሆን ይችላል፡፡ ሊያፍኑት የሚጥሩት በእርግጥ እውነቱን ይክዳሉ፡፡ ግን እነሱ ስህተት የማይገኝባቸው ፍፁማን አይደሉም፡፡ ለሰው ዘር በሞላ ውሳኔ የማሳለፍና ሌላውን ሰው አይቶ ሰምቶ የመፍረድ ዕድሉን የመንፈግ ሥልጣን የላቸውም፡፡››
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው akalegudatgnawe@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
