Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

የግንቦት 20 ትሩፋቶችና የፀረ ሙስና ትግል እውነታ

$
0
0

በፀዳሉ ንጉሡ

ይህችን ጽሑፍ ለመሞነጫጨር የተነሳሳሁት ሪፖርተር በግንቦት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ዕለተ እሑድ፣ ዕትሙ፣ ‹‹የግንቦት 20 ትሩፋቶችና የፀረ ሙስና ትግል›› በሚል ርዕስ፣ በፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በጽሑፍ የቀረበ ሐሳብ ነው፡፡

በጽሑፉ በቀረበ ሐሳብ ላይ ያለኝን አስተያየት ወደኋላ ላቆይና ስለፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥቂት ልበል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 235/1993 የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ሲያቋቁም በአዋጁ መግቢያ የሰፈረው ሐሳብ እንዲህ ይነበባል፡፡

  • የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝቦች ሙስናና ብልሹ አሠራር የአንድን አገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት የሚገታ ተግባር መሆኑን የተገነዘቡ በመሆናቸው፣
  • አገሪቱ የተያያዘችውን የዕድገት ጎዳናና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለማፋጠንና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በቁጥጥር ሥር ለማዋል አስፈላጊ በመሆኑ፣
  • ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመሸከም የማይፈልግና ይህንኑ በብቃት ለመዋጋት ዝግጁ የሆነ ኅብረተሰብ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፣
  • ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመመርመርና ለመክሰስ፣ ለመቆጣጠርና ለመከላከል መልካም ሥነ ምግባር በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲስፋፋ በማድረግ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን መዋጋት የሚችል ነፃና ራሱን የቻለ መንግሥታዊ አካል ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ይላል፡፡

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች የፖሊሲ ሰነድ፤ ‹‹ሙስና በዬትኛውም አገር ቢሆን መቶ በመቶ የተወገደበት ሁኔታ የለም፡፡ ይሁንና በቁጥጥር ሥር ሲገባ በዝቅተኛ ደረጃና መጠን አልፎ አልፎ የሚከሰት ችግር ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ሙስና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ወደ ምርትና ልማት ከማተኮር ይልቅ ወደ ማጭበርበርና አየር በአየር ንግድ እንዲያዘነብል በማድረግ ልማታችንን ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል፡፡ የመንግሥት አሠራር በአድሎና ጉቦ ተጨማልቆ፣ መንግሥት በልማት ተግባር ላይ በጎ አስተዋፅኦ ማድረግ ተስኖት የልማት ችግራችን የመፍትሔ አካል መሆኑ ቀርቶ ዋነኛው ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ መንግሥት ሕዝባዊ አገልግሎት የሚበረከትበት ሳይሆን ዝርፊያ የሚከናወንበት መድረክ ይሆንና የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ ፉክክር በዘራፊዎች መካከል የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል እንዲሆን፣ ስለሆነም ዴሞክራሲ ከሥረ መሠረቱ እንዲናድ በር ሊከፍት ይችላል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ሁሉ ሙስና ልማታችንን አደናቅፎ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓታችንን ከውስጡ እንዲበሰብስ አድርጎ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተስፋችን እንዲጨልም ማድረግ ይችላል፡፡

‹‹በመሆኑም ሙስናን በሰፊውና በብቃት የመዋጋት ሥራ አንድ አስነዋሪ ሥራን የማውገዝና የመቃወም ሥራ ብቻ አይደለም፡፡ በአገራችን መልካም አስተዳደርን በማስፈን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የልማት ራዕያችን እውን እንዲሆን የማድረግ ጉዳይም ጭምር ነው፤›› ይላል፡፡

በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ከሰፈረው ሐሳብ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝቦች ለፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሰጡትን ተግባራትና ኃላፊነቶች በጥልቀት ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ጥያቄው ኮሚሽኑ ኃላፊነቶቹን ተወጥቷል ወይ ነው? የአደባባይ ሚስጥር የሆነውን የዚህን ጥያቄ መልስ ለመመለስ አልዳዳም፡፡ ‹‹ብዙ ከተናገሩት ትንሽ የሠሩት የበለጠ ይናገራል›› እንዲሉ ብዙ ከመናገር ትንሽ መሥራት ዋጋ እንዳለው ኮሚሽኑ መመከር እንዳለበት ግን እግረ መንገዴን ሳልጠቁም አላልፍም፡፡

በጋዜጣው ወደ ቀረበው ጽሑፍ ልመለስ፡፡ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በጽሑፉ መነሻ የግንቦት 20 ትሩፋቶችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች በሚል ጠቅለል አድርጎ በማቅረብ መዘከሩ መልካም ነገር ነው፡፡ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ራሱም የግንቦት 20 ፍሬ መሆኑ ሳይዘነጋ፡፡

እንቆቅልሹ ግን የትግሉ መሪና ፊትአውራሪ የሆነው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ‹‹የዕድገታችን ማነቆ በመሆን ሲፈታተኑን ከቆዩ ዋና ዋና ችግሮች መካከል ደግሞ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሙስናና የብልሹ አሠራር ችግሮች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፤›› ሲል መደመጡና ወረድ ብሎ ደግሞ በአንቀጽ ሦስት፣ ‹‹የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽንም ባለፉት ዓመታት በአንድ በኩል የግንቦት 20 ድል ትሩፋቶችን ከሙስናና ብልሹ አሠራር አደጋዎች በመጠበቅ ለልማቱ ስኬታማነት የበኩሉን ሲወጣ የቆየ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመልካም ሰብዕና የተገነባ፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን መሸከም የማይችል ኅብረተሰብ እንዲፈጠር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፤›› በማለት ሁለት የሚጋጩ ሐሳቦች በጽሑፉ አስተናግዷል፡፡

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ባለፉት ዓመታት የግንቦት 20 ድል ትሩፋቶች ከሙስናና ብልሹ አሠራር ተጠብቀው ቢሆን ኖሮ፣ በመልካም ሰብዕና የተገነባ፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን መሸከም የማይችል ኅብረተሰብ እንዲፈጠር ተገቢው ጥረት ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ መሬት ላይ የሚታየው እውነታ ሌላ መልክ በኖረው ነበር፡፡ ዛሬ በአገር አቀፍ ደረጃ ዋና ዋና ችግሮች የሚባሉት የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር የመነጋገሪያ አጀንዳዎች ባልሆኑ ነበር፡፡ የግንቦት 20 ድል ትሩፋቶችም አሁን ከተገኙት እጥፍ ድርብ በሆኑ ነበር፡፡

የግንቦት 20 ድል ትሩፋቶች የበርካታ አካላት የጥረት ውጤቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም የተወሰነ አካል የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድበት አግባብ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ለዚህም ነው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የግንቦት 20 ትሩፋቶችን መንግሥትና መላው ኅብረተሰባችን ያስገኟቸው ድሎች እንደሆኑ በሚዲያዎች የሚያዘክረው፡፡ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ‹‹ዋናው እኔ ነኝ›› እያለ ከሆነ ሊታረም ይገባል፡፡ ይህ ማለት ግን እያንዳንዱ አካል (ተቋም) አገራዊ ራዕዩን ከማሳካት አኳያ ምን ያህል ድርሻዬን ተወጥቻለሁ? በማለት ራስን መጠየቁ ተገቢ ነው፡፡ አገራዊ ራዕይን ከግብ ለማድረስ ደግሞ እያንዳንዱ አካል (ተቋም) የራሱን ራዕይ ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት ይወሰናል፡፡ ምክንያቱም አገራዊ ራዕዩ የተለያዩ አካላት (ተቋማት) ራዕይ ድምር ውጤት ስለሚሆን፡፡

ስለራዕይ ከተነሳ አይቀር የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ካስቀመጠው ራዕይ አኳያ በጊዜ ቀመር አፈጻጸሙን ማየቱ ተገቢ ስለሚሆንና ይኼው ከራዕይ አኳያ አፈጻጸም ደግሞ በግንቦት 20 ትሩፋቶች ላይ ድርሻን ማየት ስለሚያስችል ከተቀመጠው ራዕይ አኳያ አፈጻጸሙ እንዲህ ይስተዋላል፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ራዕይ ‹‹በ2015 ሙስና ለልማትና መልካም አስተዳደር እንቅፋት ከማይሆንበት ደረጃ በማድረስ በዓለም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከሆኑ የፀረ ሙስና ተቋማት አንዱ ሆኖ መገኘት፤›› ይላል፡፡ ከዚህ ኮሚሽኑ ካስቀመጠው ራዕይ ሁለት ዓበይት ሐሳቦችን መንቀስ ይቻላል፡፡ እነሱም፡-

  • በ2015 ሙስና ለልማትና መልካም አስተዳደር እንቅፋት ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ፣
  • በ2015 በዓለም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከሆኑ የፀረ ሙስና ተቋማት አንዱ ሆኖ መገኘት፣

እነዚህን ሁለት የራዕዩን ዋና ዋና ጉዳዮች 100 በመቶ ለማሳካት 22 ዓመታት እንደሚያስፈልጉ በ2015 ከሚለው አገላለጽ መረዳት ይቻላል፡፡ በእስካሁኑ (ላለፉት 15 ዓመታት) የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የራዕዩን 68.18 በመቶ አሳክቷል ማለት ነው፡፡ በመጪዎቹ ሰባት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ቀሪ 31.81 በመቶ  በማጠናቀቅ በ2015 ሙስና ለልማትና መልካም አስተዳደር እንቅፋት ከማይሆንበት ደረጃ በማድረስ በዓለም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከሆኑ የፀረ ሙስና ተቋማት አንዱ ሆኖ ይገኛል ማለት ነው ኮሚሽኑ፡፡

ይህ እንግዲህ ኮሚሽናችን ዕይታውን በማቋቋሚያ አዋጁ (ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው) ከሕዝብና ከመንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት፣ ራሱ ኮሚሽኑም ባስቀመጠው ራዕይ ላይ በማድረግ ተንቀሳቅሶ ቢሆን ኖሮ ሊመዘገብ የሚችል የአፈጻጸም ውጤት ነበር፡፡ እንዲህማ ቢሆን ኖሮ በየሥልጠና መድረኮች ከሠልጣኞች፡-

  • ሙስና በአገራችን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
  • የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከተቋቋመ ወዲህ ሙስና ጨምሯል ወይስ ቀንሷል?
  • ራሱ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከሙስናና ብልሹ አሠራር ነፃ ነው?

በሚል ለሚነሱ ጥያቄዎች ደረት ነፍቶ፣ አፍ ሞልቶ መልስ መስጠት በተቻለ ነበር፡፡

ነገር ግን የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በዚህ ቁመና ላይ ይገኛል ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ማየት ግድ ይላል፡፡ ዛሬ ኅብረተሰቡ በመልካም አስተዳደር እጦት በሚናጥበት፣ ዛሬ በኪራይ ሰብሳቢዎች አመለካከትና ድርጊት ልማታዊ መስመሩ ቆም ብሎ በማስተዋል ነገሮችን እንዲመለከት በተገደደበት፣ ዛሬ ሙስናና ብልሹ አሠራር ሥር የሰደዱ ችግሮች በሆኑበት ፈታኝ ወቅት ‹‹… በበላበት ይጮኻል›› እንዲሉ አንዳንድ ጥቅመኞች የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲህ አደረገ፣ እንዲያ አደረገ እያሉ በፈጠራና እንቶ ፈንቶ ወሬ ሚዲያውን ያጨናንቃሉ፡፡ ይኼ መልካም አይደለም፡፡ ሊታረም ይገባል፡፡ ሚዲያዎች ለኅብረተሰሰቡ በእውነት ላይ የተመረኮዘ መረጃ ነው መስጠት ያለባቸው፡፡

ይልቁንስ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ‹‹ድክመቴ ምን ላይ ነው?›› ብሎ በመጠየቅና መላ ሠራተኛውን በማሳተፍ ችግሩን በመለየት ለመፍታት ጥረት ቢደረግ ሕዝባችንን መታደግ የሚያስችል ሥራ መሥራት በተቻለ ነበር፡፡ ድክመትን ለመሸፋፈን የባጡን የቆጡን መቀባጠሩ የትም አያደርስም፡፡ ‹‹የግንቦት 20 ትሩፋቶችና የፀረ ሙስና ትግል›› በሚል ርዕስ ሥር የቀረበውም ከተራ ወሬና ማስመሰል የዘለለ ሚዛን የሚደፋ ቁም ነገር የለውም፡፡ ደግነቱ መንግሥትና ኅብረተሰቡ እውነታውን ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆናቸው በጀ እንጂ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው 6nigusse@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles