በምንተስኖት ጎበና
ክቡር ከንቲባ ይህችን መልዕክት በጥሞና አንብበው ተገቢውን የእርምት ዕርምጃ ይወስዳሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም ካለብዎት ኃላፊነት የተነሳ እያንዳንዱን ቀዳዳ ለማየት ፍላጐት ቢኖርዎትም፣ ጊዜ አይኖርዎትምና ያለውን ሐቅ እንዲያውቁ ነው፡፡ በሕዝብ ሀብት ላይ ያለአግባብ እየደረሰ ላለው ጥፋት አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጡ ተስፋ አለኝ፡፡
ክቡር ከንቲባ አዲስ አበባ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉባት ከተማ ነች የሚለው ያስማማናል፡፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ እርስዎ የሚመሩት የከተማው አስተዳደር በተለይም ጎልተው በሚታዩ ችግሮ ላይ አትኩሮ እየሠራ ነው የሚገኘው፡፡ ከከተማዋ ዋና ዋና ችግሮች መካከል ትልቁ ለነዋሪዎቹ ምቹ ያለመሆን እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ለዚህም ነው አስተዳደሩ ለነዋሪዎቹ ምቹና ተመራጭ ከተማ አደርጋታለሁ የሚል ራዕይ የሰነቀው፡፡ ቢሆንም ብዙዎች ይህንን የከተማውን አስተዳደር አባባል ከመፈክርና ከምኞት ያለፈ አይደለም ሲሉ ያምናሉ፡፡ ለዚህ ጥርጣሬና እምነት ማጣት ምክንያቱ ምንድነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ በእርግጥ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ቢታወቅም አንዱና ዋናው የተጠያቂነት ማነስ ነው፡፡ በሕዝብ ግብር የተገዛ መኪናና የተገነባ መኖሪያ ቤት ለግለሰቦችና ለጉበኞች ሲሳይ ሲሆን የከተማው አስተዳደር ማስቆም አልቻለም፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ዓይኑ ሥር የሚፈጸሙ በደሎችንና አድሎአዊ አሠራሮችን አይቶ እንዳላየ አልፏል፡፡ በተለይ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ፍላጎት እያደገ ሲሄድ አዲስ አበባ አድሎአዊ አሠራር እየተስፋፋና የጉቦ የሥርዓቱ መገለጫ የሆነባት ከተማ ሆናለች፡፡ ፍትሕ እየራቃትና ተጠያቂነት ቀርቷል የተባለ ይመስል፣ አጥፊዎች ስለማይጠቁ የከተማዋ ነዋሪዎች ችግሮች ተዘርዝሮ የማያልቅባት ከተማ በመሆኗ፣ በየቦታው የሚሰማው ሮሮ እየተበራከተ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር በኃላፊነት ለሚመደቡ ሰዎች ቤት የሚሰጠው ሕጋዊ አሠራርን ተከትሎ ሳይሆን ለሚፈልገው ነው፡፡ ይህ ለምን ይሆናል ብሎ ጠይቆ ምላሽ ማግኘት ይቸግራል፡፡ የከተማው አስተዳደር የሚቆጣጠረውና የሚያዘው ሀብት እያንዳንዱ የከተማው ነዋሪ ከሚከፍለው ግብር የሚገኝ ነው፡፡ ሕዝብ ግብር የሚከፍለው መንግሥትን ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ ፀጥታ እንዲከበር፣ ልማቱ እንዲፋጠን፣ አገሪቱ የምትመኘውን የከፍታ ማማ ወጥታ ለማየት ነው፡፡ እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ፍትሕ አጣን፣ ዲሞክራሲው በጉቦና በአድሎአዊ አሠራር ተጠላልፏል የሚሉ ጩኸቶች ሰሚ እያገኙ አይደለም፡፡ ወጥ አሠራር የለም፡፡ ባለፈው ሳምንት የከተማው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የከተማው አስተዳደር ዕርምጃ እየወሰደ ያለው ታች በወረዳ ደረጃ ባሉ ትናንሽ አመራር ላይ ብቻ ነው፤ ትልልቆቹ ሲያጠፉ ዝም ይባላሉ፤ ይህ ለምን ሆነ? ብሎ የሕዝብ ተወካይ ሲጠይቅ ለዚህ በቂ ምላሽ ሳይሰጠው መታለፉ ክፍተቱን ያሳያል፡፡
ምክንያቱም ከላይ ያለው አመራር ትኩረት በታችኛው ላይ እንጂ አጠገቡ ያለውን መንካት ስለማይፈልግ፣ እንጠቃቀም መርህ ስለሚከተል ነው፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር እስከ ዛሬ ድረስ አንድም ባለሥልጣን በሥልጣን ብልግና ጥፋት ከሥልጣን አውርዶ፣ በሕዝብና በከተማው ላይ ላደረሰው ጉዳት ፍርድ ቤት ከሶ ያቀረበበት ጊዜ የለም፡፡ ምንም ጥፋት የለም ማለት ሥራ አልነበረም ማለት ነው፡፡ የሚሠራ ሰው ያጠፋል፣ ይሳሳታል፡፡ ግን በጥፋቱ የተጠየቀ የለም፡፡ የሚያጠፉት ጥፋት የማያስከስስ ሆኖ አይደለም፡፡ ተጠያቂነት በመላላቱና ፍትሕ በመዛባቱ፣ ሕገወጥነት በመንገሡ ነው፡፡
የከተማው አስተዳደር የሚመድባቸው ግለሰቦች የከተማው ነዋሪ በሚከፍለው ግብር የተገዛን መኪናና የተገነባ መኖሪያ ቤት ከታለመለት የመንግሥት ሥራ ውጪ በግለሰቦች ላልተገባ ጥቅም ሲውል ዝም ብሎ ያያል፡፡ በዚህም ከሕዝብ የተሰጠውን ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ እየተወጣ አይደለም፡፡ በመንግሥት አሠራር ለአንድ በኃላፊነት ሥራ ለሚመደብ ሰው የሚቀርቡ እንደ መኖሪያ ቤትና መኪና ያሉ ሥራውን በአግባቡ እንዲወጣ የሚረዱ ናቸው፡፡ ይህ በክልልም፣ በፌዴራል ደረጃም ይሠራል፡፡ ለምሳሌ መንግሥት አንድን የሥራ ኃላፊ ሲሾም ከኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ እስከ ሚኒስትር ላሉ የመኖሪያ ቤት ቪላ ወይም አፓርታማ፣ የኃላፊነት ደረጃውን የሚመጥን በትንሹ እስከ ሦስት የመኝታ ክፍሎች ያሉትና ለሥራ የሚጠቀመው መኪና፣ እንደ አስፈላጊነቱ ደኅንነት ጠባቂ ይመደብለታል፡፡
በቢሮ አካባቢ ደግሞ ከረዳት ጀምሮ የተሟላ የቢሮ ግብዓት እንዲኖር ይደረግለታል፡፡ በየጊዜው ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያግዙ የውጭ ጉዞ እንዲያደርግና አዳዲስ አሠራሮችን እያቀረበ ሕዝብን በኃላፊነት እንዲያገለግል ይፈቅድለታል፡፡ እነዚህ ሁሉ የመንግሥት ሥራ በኃላፊነትና በተጠያቂነት እንዲወጣ ለማድረግ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ የግለሰቡን የግል ምቾቱን ለመጠበቅ የሚያደርጉት አይደለም፡፡
ምቾትና ጥቅማ ጥቅሞች በኃላፊነት ለሚመደብ ሰው የሚቀርብበት ምክንያት አለ፡፡ የሕዝብን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣ ነው፡፡ የሕዝብ አገልጋይ ስለሆነ ነው፡፡ ምቾቱ የሚጠበቅለት ከሕዝብ በተሰበሰበ ግብር ነው፡፡ ስለዚህ በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ ማዋል አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ በሕዝብ ሀብት ላይ የሚኖር አሠራር ሕዝብን መበደል ነው፡፡ ምክንያቱም ለራሱ በእግር እየሄደና በታክሲ እየተጋፋ እንደዚሁም ጾሙን እየዋለና እያደረ፣ ነጭ ላቡን አፍስሶ ካገኘው ገቢ መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ የከፈለው ግብር ባከነ ማለት ነው፡፡ ግብር ከፋዩ እየተራበ፣ እየተጠማ፣ አገልግለኝ ብሎ ኃላፊነት የሰጠው የመንግሥት ሰው እንደፈለገ እንዲሆን አደረገ ማለት ነው፡፡
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው በቅርቡ በከተማችን መነጋገሪያ የሆነው በሕዝብ ገንዘብ የተገነባ ኮንዶሚኒየም 98 ሕንፃዎች ከነሕይወታቸው መጥፋት ጋር ተያይዞ የተጠያቂነት ክፍተትና ግልጽነት መጓደል ጣሪያ ነካ እየተባለ ስለሆነ የማውቀውን ሐቅ በዜግነቴ ለመግለጽ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ በከተማው ውስጥ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር፣ የሕዝብ ሀብት ላይ እየተፈጸመ ያለን ብክነት ሁላችን ስለሚያሳስበን ጭምር ነው፡፡ እኔና መሰሎቼ በየቀኑ አከራይ ዋጋው በሚጨምር የግለሰብ ቤት ተከራይተን እየኖርን በምንከፍለው ግብር የተሠራ ኮንዶሚኒየም ለጥቂቶች መንደላቀቂያ በመሆኑ የሕዝብ ሀብት ለምን ይባክናል የሚል ቁጭት አለን፡፡ ተጠያቂነት እንዲሰፍንና ፍትሐዊ አሠራር ለማየት እንፈልጋለን፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር በከተማው በቢሮ ደረጃ ለሚሾማቸው የሥራ ኃላፊዎች ደረጃውን የሚመጥን የመኖሪያ ቤትና ለሥራ የሚጠቀሙበትን መኪና ያቀርባል፡፡ የመኖሪያ ቤትና የመኪና አቅርቦት ተሿሚዎች ተረጋግተው ሥራቸውን እንዲወጡ ትኩረታቸውን በሥራ ላይ እንዲያውሉ ጊዜአቸውንና ጉልበታቸውን ለሕዝብ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ እንዲሆን ለማድረግ ነው እንጂ፣ የተለየ ምቾት ስለሚያስፈልጋቸው ወይም ልዩ እንክብካቤ ስለሚገባቸው አይደለም፡፡
ሕዝብን ለማገልገል ከተሰጣቸው ኃላፊነት ሲነሱ በእነሱ ምትክ የሚሾም ኃላፊ በተመሳሳይ መልኩ ኃላፊነቱንና ግዴታውን እንዲወጣ ለሥራው የሚያስፈልጉ ሁሉ ይሟላሉ፡፡ ይህ በዓለም ላይ የተለመደ አሠራር ነው፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ በየአራት ዓመቱ በሚደረግ ምርጫ አሸናፊ ፓርቲ ሁለት መቶ ሺሕ ባለሙያዎችን ይዞ ወደ ታላቁ ቤተ መንግሥት ያመራል፡፡ የሥልጣን ዘመኑን ጨርሶ በምርጫ ሲሸነፍና አሸናፊ ፓርቲ ሲመጣ፣ እነዚያ ሁለት መቶ ሺሕ ሰዎች ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ሁሉንም ነገር ለተተኪያቸው አስረክበው ይሄዳሉ፡፡
በዚህም ረገድ በአዲስ አበባና በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያለው አሠራር ለየቅል ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት ተሿሚዎች ከኃላፊነት ሲነሱ ወደ ሌላ ሥራ ምድብ ያዞራቸዋል፡፡ ነገር ግን የያዙትን ቤት ይዘው ይቀጥሉ መኪናውም በእጅዎ ይሁን አይልም፡፡ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የቀድሞ የፍትሕ ሚኒስትር የነበሩት የደሕዴን ሰው ከኃላፊነት ሲነሱ የሚኖሩበትን መኖሪያ ቤት ለኪራይ ቤቶች፣ መኪኖችን ለመኖሪያ ቤቱ ንብረት አስተዳደር በነፋስ ፍጥነት አስረክበው ወጥተዋል፡፡ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በተመሳሳይ መልኩ የመንግሥት ኃላፊነትን ሲለቁ ሁሉንም ነገር መልሰዋል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤትም ቢሆኑ በጭቅጭቅ ቤተ መንግሥትን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል፡፡ በአጠቃላይ ለመንግሥት ሥራ የሚፈቀድ መኖሪያ ቤትና መኪና ርስት አይደለም፡፡ ማንም ሰው እንደፈለገው የሚጠቀመው የሕዝብ ሀብት አይደለም፡፡ ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ መዋል አለበት፡፡ በፌዴራል ደረጃ ያለው ይህንን አሠራር በግልጽ ያሳያል፡፡
በአዲስ አበባ አስተዳደር በሥራ ምድብ ምክንያት የሚሰጥ መኖሪያ ቤትና መኪና እንደ ግለሰብ ርስት እየተቆጠረ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሰዎች እንደ ምንም ብለው በኃላፊነት ደረጃ ተመድበው የመኖሪያ ቤት ካገኙና መኪና ከተሰጣቸው በኋላ ከተመደቡበት የሥራ ኃላፊነት ሰበብ ፈጥረው ይነሳሉ፡፡ ግዴታ ስለሚሆንባቸው የመንግሥትን መኪና ይመልሱና መኖሪያ ቤቱን የግል ርስት ያደርጉታል፡፡
የሚገርመው ነገር ከኃላፊነት ሲነሱ የመንግሥት ቤት አለመመለሳቸው ብቻ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል ለመኖሪያ ቤትና ለመኪና ያበቃቸውን መሥሪያ ቤት ለቀው ሲሄዱም የከተማው አስተዳደር ተከታትሎ የመንግሥትን ቤት አያስመልስም፡፡ በዚህ የተነሳ የመንግሥት መኖሪያ ቤቱን የግል ያደርጉታል፡፡
አስተዳደሩ በዚህ ጥፋቱ ከፍተኛ ደረጃ ተጠያቂ መሆን ነበረበት፣ አለበትም፡፡ ምክንያቱም ግለሰቦች የመንግሥትን ቤት እንደ ርስት ሲቆጥሩ እያየ ዝም ማለቱ አግባብ አይደለምና፡፡ በዚህ የተነሳ በርካታ ሰዎች ዛሬ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ሆነው የተረከቡትን ቤት ከኃላፊነት ተነስተውም ሳይለቁ ይዘው ይቀጥላሉ፡፡ በሌላ በኩል አዲስ የሚመደቡ ኃላፊዎች ቤት አጥተው ይንከራተታሉ፡፡ ይህ የከተማው አስተዳደር እንዝላልነት አንዳንዶችን ሁለትና ሦስት የመንግሥት ቤቶች ባለቤት አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ብዙዎች በአጋጣሚ ያገኙትን በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው ይገኛሉ፡፡ መልሱ ሲባሉ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ እያለሁ የተሰጠኝ ነው አልመልስም ይላሉ፡፡ ይህንን የሚጠይቅ የለም፣ አስተዳደሩ ችላ ብሏል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ በሚከፍለው ግብር ጥቂት ሰዎች እንደፈለጉ እየሆኑ ነውና የአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ይጠይቁልን፡፡
በአዲስ አበባ አስተዳደር የቢሮ አስተባባሪ ሆነው የሚሠሩ አንድ ሰው ባለሦስት ክፍል መኖሪያ ቤትና በወር 200 ሊትር መኪና ከነሾፌሩ ተሰጣቸው፡፡ ቤቱን እጃቸው መግባቱን እንዳረጋገጡ ከቦርዱ ጋር ጭቅጭቅ በመፍጠር ሥራ እየበደሉ ሲያስቸግሩ ብዙ ከታገሳቸው በኋላ ቦርዱ አሰናበታቸው፡፡ ከዚያም ለሥራ የተሰጣቸውን መኪና አስረከቡ፣ ባለሦስት ክፍል ቤቱ ግን ርስታቸው እንደሆነ አለ፡፡ የሚገርመው እኚህ ግለሰብ ዛሬ የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማትን ሥራ ለቀው በሌላ መሥሪያ ቤት ተቀጥረው እየሠሩ ነው፡፡ መሥሪያ ቤቱን ሙሉ ለሙሉ ለቀው ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት ቢሄዱም፣ መኖሪያ ቤቱን እንደ ርስት ቆጥረውት ወደ ግላቸው ሲያዛውሩ አንድም ጠያቂ የለም፡፡ ዝም ብሏቸዋል፡፡ እኚህን ግለሰብ ለአብነት አነሳን እንጂ በዚህ መልኩ ብዙ የሕዝብ ሀብት በየቦታው እየባከነ ነው፡፡ የመንግሥት ያለህ ያሰኛል፡፡ ለመሆኑ ለሥራ የተሰጠ መኖሪያ ቤት ርስት ይሁን የሚል ደንብ አዲስ አበባ አስተዳደር አውጥቶ ይሆን?
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
