Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

ባብኤል አል መንደብ ሰርጥ ለኢትዮጵያ . . .

$
0
0

በእስክንድር ከበደ

የጂቡቲና የኤርትራ የድንበር ውዝግብ የተጀመረው እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 16 ቀን 2008 ነበር፡፡ በወቅቱ የኤርትራ ጦር በጂቡቲ ግዛት ዘልቆ ምሽግ መቆፈሩን በመጥቀስ አቤት ማለቱን ተከትሎ ሁለቱ አገሮች እ.ኤ.አ. ከሰኔ 10 እስከ ሰኔ 13 ቀን 2008 የዘለቀ ግጭት ውስጥ ገቡ። ኤርትራ የጂቡቲ የድንበር አካል የሆነችውን ራስ ዱሜራን ለሁለት ዓመታት በቁጥጥር ሥር አድርጋ ቆየች። እ.ኤ.አ. በ2010 የሁለትዮሽ ድርድር ለማድረግ አካባቢውን ለቃ ወጣች። የኳታር ወታደሮች የሰላም አስከባሪ በመሆን ራስ ዱሜራን በተቆጣጠሪነት እዚያው ሠፈሩ።

ራስ ዱሜራ (Cape Doumeira) በቀይ ባህር 1.5 ኪሎ ሜትር የሚሽፍንና ባህረ ሰላጤውን የሚከፍል አወዛጋቢ ሥፍራ ነው፡፡ በእ.ኤ.አ. በ1900 በተፈረመው ፕሮቶኮል የዓለም አቀፍ ድንበር ሆኖ ከወታደራዊ ቀጣናነት ነፃ እንዲሆን ጣሊያንና ፈረንሣይ መስማማታቸው ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1935 ግጭት ተቀስቅሶ ሁለቱ ኃያላን ባካሄዱት ስምምነት ራስ ዱሜራን ኮረብታዎች ባይካለልም፣ ሰሜናዊ ቁልቁለቱ ለጣሊያን ሆኖ ደቡባዊ ቁልቁለቱን ደግሞ ፈረንሣይ እንድትይዝ ነበር።

እ.ኤ.አ. በ2008 ኤርትራ ለመንገድ ሥራ አሸዋ ለመውሰድ ነው በሚል ሰበብ ድንበር ተሻግራ ሥፍራውን ያዘችው። እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 16 ቀን 2008 ጂቡቲ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ በራስ ዱሜራ አቅራቢያ በሁለቱም የድንበር አካባቢዎች ምሽግ እየገነባች ነው በማለት ክስ አቀረበች፡፡ ጂቡቲ ለፀጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤም ኤርትራ በአዲሱ ካርታዋ ራስ ዱሜራን አካታለች ብላ ነበር፡፡

የኳታር አደራዳሪነት ብዙም ሳይሰማ ቆይቶ አገሪቱ ከባህረ ሰላጤው ጋር በገባችበት ውዝግብ ‹‹በማሳበብ›› ራስ ዱሜራን ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ ሰላም አስከባሪ ኃይሏ ሹልክ ብሎ መውጣቱን ተከትሎ፣ የኤርትራ ጦር አካባቢውን ተቆጣጠረ። ይህ ድርጊት ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም አለው። ጂቡቲ ናት የተወረረችው ብሎ መቀመጥ ብዙ ጉዳት አለው።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በወቅቱ፣ ‹‹የኤርትራ ድርጊት ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታ አደጋ ነው . . .›› ብለው ነበር። ኢትዮጵያ የንግድ ኮሪድር የሆነችውን ጂቡቲ በግጭት ወቅት ለህልውናዋ ስትል ከአደጋ የመጠበቅ መብት እንዳላት ጠቁመው ነበር።

ስዊዝ ካናል ሜዲትራኒያንና ቀይ ባህርን የሚያገናኝ ቦይ ነው። ካናሉ በደመቀ ሥነ ሥርዓት በዳግማዊ ናፖሊዮን ባለቤት የፈረንሣይ ንግሥት ኢዩጊን በተገኙበት ነበር የተመረቀው። እ.ኤ.አ በ1854 የቀድሞ የካይሮ አማካሪ ፈርዲናንድ ዲ ሌሲ ፒ በኦቶማን ቱርክ ትተዳደር ከነበረችው ግብፅ ጋር ውል በመፈራረም 100 ማይሎች ርዝመት ያለው ቦይ ለመገንባት ተስማማ።

የዓለም አቀፍ የመሐንዲሶች ቡድን በማሰባስብ የግንባታ ዕቅድ ወጣለት፡፡ እ.ኤ.አ. በ1856 የስዊዝ ካናል ኩባንያ ተመሥርቶ ቦዩ ከተገነባ በኋላ፣ ለ99 ዓመታት ለማስተዳደር ኩባንያውና ግብፅ ውል ነበራቸው። የካናሉ ግንባታ እ.ኤ.አ. በ1859 ተጀምሮ እ.ኤ.አ. በኅዳር በ1869 የስዊዝ ካናል ለአገልግሎት ክፍት ሆነ፡፡

ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ግብፅ የብሪታኒያ ወታደሮች ከስዊዝ ካናል ዞኖች እንዲወጡ ግፊት ማድረግ ጀመረች፡፡ እ.ኤ.አ. በ1956 የግብፅ ፕሬዚዳንት ጋማል አብደል ናስር ስዊዝ ካናልን ከስዊዝ ካናል ኩባንያ ወረሱ፡፡ ከ87 ዓመታት በኋላ ግብፅ ቦዩን የወረሰችው ለአስዋን ግድብ ግንባታ ገንዘብ ለማሰባሰብ ነበር፡፡

ካናሉን ብሪታኒያ፣ ፈረንሣይና ሌሎች አውሮፓ አገሮች ከመካከለኛው ምሥራቅ የነዳጅ ዘይት በመርከብ በርካሽ ዋጋ ለማጓጓዝ ይጠቀሙበታል፡፡ ናስር ቦዩ እንዲወረስ በማድረጋቸው ፈረንሣይ፣ ብሪታኒያና እስራኤል ግብፅን ለመውጋት ሲዘጋጁ በአሜሪካና ሶቪየት ኅብረት ተፅዕኖ ዳነች፡፡

ስዊዝ ካናል ለአስዋን ግድብ ግንባታ ትልቅ አቅም ከመፍጠሩም በላይ፣ በዓለም የንግድና የፖለቲካ መስክ ተፅዕኖ መፍጠር እንዳስቻላት ይነገራል፡፡ አሁን በቀን 50 መርከቦች መልህቃቸውን የሚጥሉ ሲሆን፣ በዓመት 300 ሚሊዮን ቶን ዕቃዎች በካናሉ ወደብ ይራገፋሉ፡፡

ባብኤል አል መንደብ ህንድ ውቅያኖስን ሜዲትራኒያን ባህርንና ቀይ ባህርን ከስዊዝ ካናል የሚያገናኝ ስትራቴጂያካዊ ሰርጥ መሆኑ ይነገራል። እ.ኤ.አ. በ2006 3.3 ሚሊዮን ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በጭነት መርከቦችን ተጓጉዘውበታል። ከየመን ራስ ሜንሃሊ እስከ ጂቡቲ ራስ ሲያን 30 ኪሎ ሜትር ርቀት አለ።

ብሪታኒያ ብቻዋን በሰርጡ አካባቢ ያሉትን ደሴቶች በህንድ ቅኝ ግዛት ስም እ.ኤ.አ. በ1799 በመያዝና በኋላ በ1857 በግል ንብረትነት ተቆጣጥራ ነበር። እ.ኤ.አ. በ1861 በቀይ ባህርና በስዊዝ ካናል የንግድ መስመሮች አብሪ ሕንፃ (Lighthouse) በመገንባት አካባቢውን ስትቆጣጠር ቆይታለች።

እ.ኤ.አ. በየካቲት 22 ቀን 2008 የኦሳማ ቢን ላደን ወንድም ታሪቅ ቢን ላደን፣ በአፍሪካ ቀንድ ከየመን እስከ ጂቡቲ የሚያገናኝ ግዙፍ ተንጠልጣይ ድልድይ በቀይ ባህር በሰርጡ ላይ ለመሥራት ዕቅድ ነበረው።

ዛሬ ጂቡቲና ኤርትራ የሚወዛገቡባቸው የራስ ዱሜራ ደሴቶች የኤርትራና የጂቡቲ ጉዳይ ብቻ አይደሉም። የአፍሪካ ቀንድ በተለይም የኢትዮጵያ ጥቅሞችን የሚነኩ የንግድና የሰላም ጉዳዮች በውስጣቸው ይኖራል፡፡

አንድ አገር ሌላዋን አገር ስትወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተሰብስቦ ያወግዛል፡፡

በራስ ዱሜራና በዱሜራ ደሴቶች ይገባኛል የሚሉ አገሮች ኤርትራና ጂቡቲ ብቻ አይሆኑም። በኢትዮጵያ በኩል በኢትዮ - ኤርትራ የድንበር ውዝግብ ላይ ከቀረቡትና ኤርትራ ካልተቀበለቻቸው ባለ አምስት የድርድር ነጥቦች ውስጥ ከተዘረዘሩት ‹‹ሰጥቶ መቀበል›› ብዙ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ኤርትራ ድንበርን ለማስመር የምትጠቀመውን ታሪክ ወይም ሕግ አይመስልም፡፡ አንድን ቦታ በመውረር ትኩረት መሳብ ብሎም ያ የወረረችውን ሥፍራ ‹‹የእኔ ነው›› በማለት ውዝግብ ውስጥ ‹‹ድንበሩን›› አድምቃ ማስመር የምትፈልግ ይመስላል፡፡

በጂቡቲ የፈረንሣይ ጦርን ጨምሮ የአሜሪካ፣ የጃፓንና የአውሮፓ ኅብረት ባህር ኃይል (በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን ከሶማሊያ የባህር ወንበዴዎች ለመከላከል) በሚል ምክንያት ሠፍረዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የመጀመርያው  የጦር ሠፈር በጂቡቲ እንዳላት ቻይና ሰሞኑን በስፋት ሲዘገብ ነበር።

የኤርትራ በተደጋጋሚ ከጂቡቲ ጋር ጠብ የለኝም ስትል ይደመጣል፡፡ ይህ ደግሞ በዱሜራ ምሽግ እየሠራች መሆኑንና ለማን እየተዘጋጀች እንዳለች ያመላክታል። በአውሮፕላን ጉዞ በኤርትራ አየር ክልል መጓዝ ባለመቻሉ፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ አዲስ አበባ ለመድረስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋጋ መጨመሩ ተፅዕኖው ቀላል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ መርከቦች ከተለያዩ አገሮች ወደ ጂቡቲ የሚያጓጉዙዋቸውን ግዙፍ ጭነቶች የአገሪቱ ልማትና የኢኮኖሚ ፍጆታዎች አብዛኛውን ይሽፍናሉ፡፡

በዚህ በባብኤል አል መንደብ ሰርጥ የሚገኘው የንግድ መስመር በኤርትራ ጦር እጅ መሆን የሁለት አገሮች ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ጥቅሞች እንዲሁም መረጋጋትን በቀጥታ የሚነካ ሥጋት ተፈጠረ ማለት ይቻላል።

በጋማል አብድል ናስር ዘመን ግብፅ ከሶሪያ ፕሬዚዳንት ጋር እስራኤልን በሁለት ግንባር ሊወጉ ስምምነት ደረሱ። ግብፅ እስራኤልን በሲናይ በረሃ በኩል ተዋግታ ከግብፅ ድንበር 12 ኪሎ ሜትሮች ላይ ጦሩ እንዲቆም አደረገች፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ የግብፅ አየር መቃወሚያዎች ከ12 ኪሎ ሜትር በላይ ለጦሩ ሽፋን መስጠት ስለማይችሉ ነበር። በዚህ ምክንያት የሶሪያ ፕሬዚዳንት በናስር ከፍተኛ ክህደት እንደተፈጸመባችወ ቂም ይዘው እንደነበር ይነገራል፡፡

የአሁኑ የግብፅ ፕሬዚዳንት በምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡትን ፕሬዚዳንት ከሥልጣን ሲያስወግዱ፣ ደጋፊዎቻቸው አደባባይ ይዘው የወጡት የጋማል አብደል ናስርን ፎቶግራፎች ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ሁለት ደሴቶችን ለሳዑዲ ዓረቢያ በቅርቡ ሲመልሱ አርቀው የሚያስቡት ምንድነው? ከሁለቱ ደሴቶች ይልቅ ዱሜራ ለግብፅ ስትራቴጂካዊ ጠቃሚነቷ ሊጎላ ይችላል፡፡ ከግብፅ ተነስተው ኢትዮጵያን ማጥቃት ባይቻልም፣ አጭር ርቀት ላይ የተቀመጠ አየር ኃይል ብዙ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ኤርትራ ዱሜራ ፈጥና መግባቷ ብዙ ችግር ይዞ ሊመጣ እንደሚችል አስቦ መንቅሳቀስ ይጠይቃል፡፡

አፄ ምኒልክ የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር ሲዘረጋ ከፈረንሣዩ ኩባንያ ጋር ፈጥነው ውል መግባት አልፈለጉም ነበር፡፡ በዙላ በኩል ብሪታኒያ የገነባችው አነስተኛ የባቡር ሐዲድ ወታደሮችን በማስገባት አፄ ቴዎድሮስን እንዲወድቁ የባቡር መስመሩ አስተዋጽኦ ስለነበረው፣ ፕሮጀክቱን በጥንቃቄ ያዩት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ከኩባንያው ጋር በተፈራረሙት ውል ላይ ባቡሩ የውጭ ወታደሮችን መጫን እንደሌለበት፣ ሆኖም ኢትዮጵያ ግጭትና ጦርነት ውስጥ ባለችበት ወቅት ወታደሮችን በነፃ ልታጓጉዝበት እንደምትችል ተስማምተው ነበር፡፡

በጂቡቲና በኤርትራ ውዝግብ ዙሪያ ፈረንሣይ የጦር መሣሪያና ወታደራዊ ድጋፍ ከጀርባ ከመስጠት ባለፈ በግልጽ በውጊያ እንደማትሳትፍ ይታወቃል፡፡ ፈረንሣይ እንደ ምዕራብ አፍሪካ የቀድሞ የቅኝ ግዛቶች በምሥራቅ አፍሪካ የዲፕሎማሲ ወይም ወታደራዊ ኃይል መጠቀሙ ላይ ዳተኛ እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡ በተለይ ወጣቱና ፖፕሊስቱ አዲሱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል የማክሮን ቀልብ የማይስብ ሊሆን ይችላል፡፡

ለማንኛውም አሁን ኢትዮጵያ የጦር ሠፈር በጂቡቲ እንዲሰጣት እስከ መጠየቅ የዘለቁ መፍትሔዎችን ከወዲሁ ማማተር ይኖርባት ይሆን?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው eskinder.kebe1996@gmail.com. ማግኘት ይቻላል፡፡.

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231