Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

የኦሮሚያ ዕርምጃ ‹‹ጉልበቴ በርታ . . . በርታ . . .››

$
0
0

 በአስፋው ትሁኔ

አንድ አሥርት ለአንድ አገር ልማት ‘ውቅያኖስን በጭልፋ’ ነች፡፡ በአሥር ዓመታት ውስጥ የአንድ ሴክተር ዕቅድ እንኳ ሩቡ ላይከናወን የሚችልባቸው አያሌ አጋጣሚዎች መኖራቸው የተለመደ ነው፡፡ አገር መልማቱ የሚለካው በአንድና ሁለት የተመቻቹ አሥርታት መንበሽበሽ ብቻ ሳይሆን፣ ከቶውንም ለበለጡ አሥርታት ክፉ ቀናት በእጅጉ ዝቅተኛ ጉዳት አስተናግዶና ከዚያም ጉዳቱን ተቋቁሞ ልማትን መቀጠል መቻሉ ሲረጋገጥ ነው፡፡ የልማት ዕቅድ፣ ክንዋኔዎችና አፈጻጸሞች ግን የየዕለት ስኬቶች የግድ ይላቸዋል፡፡ የልማቱ ብሎኬቶች ወይም ግድግዳዎች ማለት ይቻላል፡፡ ሸክላዎች፣ ማገሮች አሊያም የምትሉትን በሏቸው እንጂ የየዕለቱ ስኬቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ይደር የሚባል ነገር አይኖራቸውም ተሠርተው ተከውነው ማደር እንጂ፡፡ አራት ነጥብ፡፡

መንግሥታችን በተሃድሶ በጣም የታወቀ ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ካለፉት ከደረስንባቸውም ሆነ ዝናቸውን ከሰማንላቸው መንግሥታት በተለየ ሁኔታ በሕዝብ ፊት ቀርቦ ማንነቴን ንገሩኝ፣ ጉድፌን አሳዩኝ ብሎ በመጠየቅና የራሱንም ነውር ሲነገረው አምኖ በመቀበል የደረሰበት የለም፡፡ ከዚህ አንፃር ሕዝብን ያከብራል ማለት ሲሆን፣ ባያደርገው መሠረቱን መናዱን ጠንቅቆ የተረዳ መንግሥትም ነው፡፡ የገባው ነው እንደሚባለው፡፡ ግን ደግሞ መንግሥት ነው፡፡ የመንግሥት ባህሪያትን ሁሉ የተላበሰ፣ በመንግሥት መዋቅር የተደራጀ፣ የመንግሥትን ሥራ የሚከውንና በሰው ልጆች የተሞላ፡፡ ከሁሉም በላይ መታወቅ ያለበት አንቀሳቃሾቹ የሰው ልጆች እንጂ መላዕክቶች አለመሆናቸውን ማስተዋል ነው፡፡ ብፁዓን አይደሉም ለማለት ያህል፡፡

ኢሕአዴግ/ኦሕዴድም በዚሁ መንግሥት በሚባለው ‘ካታጎሪ’ (ምድብ) ውስጥ የተደራጁ እንጂ የተለዩ ስብስቦች አይደሉም፡፡ ይህንንም ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ በመቶ ሺዎች የሚንቀሳቀሱ ሠራተኞችን የተፈጥሮ ባህሪ፣ ፍላጎትና ብቃት መለያየትን አርቆ በአንድ አቅጣጫ ማንጎድ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነም አይዘነጋም፡፡ የአገሪቱ የድህነት መሠረት፣ የኋላ ቀር ባህልና ልምዶች ለዴሞክራሲ ሥርዓት መዘርጋት የሚፈጥሩት እንቅፋትና ብርታት፣ የውስጥና የውጭ ፖለቲካ ውስብስብነትና ተፅዕኖ. . . . ወዘተ የሚጫወቱት ገንቢና አፍራሽ ሚናዎችን ሳንዘነጋ ኢሕአዴግ መንግሥትም ቢሆን እንኳ ያሰኛሉ፡፡ ኢሕአዴግ መንግሥትም ቢሆን የተለየ ነው፡፡ ዓላማው፣ ትግሉ ድሉና ታሪኩ በደም ቀለም፣ በአጥንት ብዕርና በሕይወት ብራና የተጻፈ ስለሆነ የተለየ ነው እንላለን፡፡ የተለየ የሚሆነው ግድግዳና ማገር፣ ዋሻና መሸሻ፣ ጋሻና መከታ ሆኖ አብሮት ሞቶ አብሮት ድኖ ለመንግሥትነት ያበቃው ሕዝብ ስለሆነም ብቻ ሳይሆን ዛሬም ከሁሉም ወገን የሚምዘገዘግበትን ጦር የሚሰነዘርበትን ፍላፃና የሚበቅልለትን አሜኬላ የሚመክትለት፣ የሚነቅልለት ሕዝብ ስለሆነ ሕዝባዊ ወገናዊነቱ ከሌሎች መንግሥታት በእጅጉ የተለየ ስላደረገውም ነው፡፡ ማንኛውም መንግሥት ‹የሕዝብ ነኝ› ማለቱ የተለመደ ቢሆንም እንኳ ኢሕአዴግ የይስሙላ ሕዝባዊነት ሊኖረው ስለማይገባ የተለየ የሆነው በዚህ ሳቢያ ነው፡፡ በአጭሩ ድርጅቱ አልፎ አልፎ ቢያንቀላፋም ደግሞም አንዳንዴ ስንፈተ ምግባር ቢጠናወተውም፣ የሕዝባዊ ወገናዊነቱ እምብርት ‘ክሊክ’ ሲያደርግ ያው ኢሕአዴግ ነው፡፡

ከሞላ ጎደል ማለት ይቻላል ከ1987 ዓ.ም. ወዲህ ኦሕዴድ በፈታኝ ሰላማዊ ትግል ውስጥ ሲዳክር እንደነበር፣ ይህም ወረርሽኝ ሆኖ የኦሮሚያን ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የጭንቀት ምጥ ሲያስምጠው በፈጣን ዕርምጃ መጓዝ ሳይሆን ሲያስነክሰው ሁለት አሥርታትን እንዳሳለፍን መካድ አይቻልም፡፡ በዕድሜ ለጋ በተግባር ግን በሳል የሆነው መንግሥት ከመወለዱ የተጋረጠበትን ፈተና ተቋቁሞ ዛሬ ድረስ ዘልቆ፣ እንደገናም ታሪክን ደግሞ ተዓምራዊ ዕርምጃዎችን መውሰድ የጀመረው ሕዝባዊ ወገናዊነቱ ‘ክሊክ’ ሲደረግ ነው፡፡ ኦሕዴድ በሕዝብ ውስጥ የተከለው የዴሞክራሲ ዓምድ ሕዝቡ ለመብቱ ተሟጋች እንዲሆን አስችሎት፣ በሕዝብ ይሁንታ የተመሠረተው መንግሥት ደግሞ የሥልጣኑ ምንጭና ባለቤት ለሆነው ሕዝብ ምላሽ ሰጪ መሆኑን ዛሬ ድረስ ቆይቶ ከማየት የበለጠ መታደል አይኖርም፡፡ በተለይም የኦሮሚያ መንግሥት ሲመሠረት የተፈለገው የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ‘ቱታ ከኒሳ’ በአንድ ላይ ተምሞ፣ በአንድ አፍ በአንድ ልብ መብቱን ማስከበር መቻሉ ላይ ተደርሶ፣ ደግሞም የእዚህን ሕዝብ ውክልና የተቀበለው መንግሥት የሕዝቡን ድምፅ ሰምቶ ወደ ተግባራዊ ምላሽ መስጠቱ ዘመን ላይ በሕይወት ደርሼ ማየቴ፣ መንግሥቱን በመመሥረት ሒደት ውስጥ የግንባር አጥንት መሆኔን ወደድኩት፡፡ የያኔ ሥራዬ በሕዝብና በታሪክ ፊት እንዳላስኮነነኝ ተገነዘብኩ፡፡ የኦሮሚያን መንግሥት ለማቋቋም መዳከሬን እሰየሁ አልኩት፡፡ ይህንን ሳያዩ የተሰውትን የትግል ጓዶች አከበርኩ፡፡

የኦሮሚያ መንግሥት መመሥረታችንን ስናውጅ ያኔ እኛ በቁም ነገር ነበር ያደረግነው፡፡ የታሪክን ስንክሳር የሚገለባብጥ፣ የታቹን ከፍ የላዩን ዝቅ አድርጎ የጎንዮሽ የሚያስቀምጥ፣ ጌታና ምንዝር ሕዝብ አለመኖሩን የሚያረጋግጥ፣ ባለአገርና አገር አልባ አለመኖሩን፣ የደስ ደስም፣ መርዶም የሚያስደምጥ ዜና በቁም ነገር አበሰርን፣ አረዳን፡፡ የዛሬ ሁለት አሥርት ዓመታት ግድም የአዲስ አበባን የክርስትና ስም ፊንፊኔን ከታሪክ መዘክር ውስጥ አውጥተን ጉልህ ሥዩም ስናደርግ ያኔ ለዋዛ ፈዛዛ አልነበረም ለቁም ነገር እንጂ፡፡ ከቶውንም ከስያሜ አልፎ የአዲሱ መንግሥት መዲናነትን ስናጎናጽፋት እንዲሁ በእመ አልቦ ሳይሆን የታሪክን ምርኩዝ ተደግፈን፣ የሕዝብን መብት ተንተርሰን፣ ሀቅን አክብረን በቁም ነገር ነበር፡፡ የኦሮሞ ዘመንኛ መንግሥት የሥራ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ ሆኖ ጽሑፋ በቁቤ ይደረጋል ስንል ለፌዝ አልነበረም፡፡ የእዚህ መንግሥተ ትንሳዔ ሰንደቅ ዓላማ ሲቀረፅ እንዲሁ በምናብ ለጉራና ለይሁን ማለት ያደረግው ሳይሆን፣ በ1940ዎች መጀመርያ ላይ የአርሲ ኦሮሞ ታጋዮች ‹‹የጋላ›› ባንዲራ ይዛችሁ ተገኛችሁ ተብለው በጢቾ አውራጃ ፍርድ ቤት በአምስት አምስት ዓመታት ፅኑ እስራት የታደቡበትን ቁራጭ የነተበች ግን በፍቅርና በጥንቃቄ ተሰውራ ኖራ የተገኘች ናሙና ባንዲራ መሠረት አድርገን፣ የኦሮሞ ሕዝብን ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ እሴቶችን ከትግል መስዋዕትነቱና ከድል ራዕዩ ጋር አናበን በቁም ነገር ነበር፡፡ የትግል ቀልድ የድል ከንቱ ታይቶም ተሰምቶም ስለማይታወቅ ሁሉንም ስናደርግ ለይስሙላ ለ‹ከማን አንሼ› ብለን አንዳችም የሠራነው አልነበረም፡፡ ዳሩ ግን ያኔ ‹‹አሁን ኦሮሞ መንግሥት መሥርቶ ራሱን ሊያስተዳድር ደግሞ አዲስ አበባን ቀይረው ሌላ ስም እንስጥ አሉ በቦቲአቸው . . . ፣ ጥቁር ፈረንጆች . . . ›› በማለትና ለጽሑፍ የማያመቹ ስላቆች ሲዥጎደጎዱ እንደተፈለገው አልተሸማቀቅንም፣ ግንባራችንንም አላጠፍንም፡፡

ለማንኛውም ለቀልድ የሠራነው ነገር አልነበረም፡፡ ሕዝባችንን መታገያ  አስታጥቀን ተቀጣጣይ ችቦ ነበር የለኮስነው፡፡ የትግል አቅጣጫ፣ የድል ፋና ነበር የቀደድነው፡፡ የማይፈርስ ዓምድ፣ የማይናድ ሐውልት ነበር የገነባነው፡፡ የእኩልነት ማሳ አርሰን የነፃነት ዘር ነው የዘራነው፡፡ የአብሮ መኖርና የመቻቻል ቦይ፣ የመከባበር መንገድ ቀድደን የልማትና የብልፅግና ዘዴ ነበር የዘየድነው፡፡ እስከ ጨፌ ኦሮሚያ የመጀመርያው ‘ያኢ’ በአራት ወራት ዕድሜ ውስጥ ብቻ በታሪክ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የኦሮሞን ዘመናዊና ሁሉን ኦሮሞ አቀፍ መንግሥት መሥርተን፣ የኦሮሚያን የመንግሥት ቢሮክራሲ ከሁሉም አቻ መንግሥታት በፊት አዋቅረን ተንቀሳቀስን፡፡ ይህ ሲሆን 12 ወንበሮችና ስድስት የመጻፊያ ወንበሮችን በፈረቃ እየተጠቀምን፣ አንድ የመስመር ስልክ ብቻ ኖሮን የወር ደመወዝ የማይታሰብ ሆኖ እያለና ሥራ አስፈጻሚ በየዘመድና ወዳጅ ቤት ተጠልሎ ሳያቅማማ በቁርጠኝነት በሚታገልበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበር፡፡ ለቀልድም ለይስሙላም ደግሞም አይሆን ይሆን በሚል ጥርጣሬም አልነበረም፡፡ በቁርጠኝነትና በልበ ሙሉነት ሕዝባቸውን ባለራዕይ ያደረጉትን እነዚያን መንግሥት መሥራቾች ቁም ነገረኞችና አገር ሠሪዎች እኔ ቢያንስ ዛሬ አሞገስኳቸው፣ ዘከርኳቸው፡፡ ክብር ለእነሱ፣ ሞገስ ለእነሱ ብዬ አደነቅኋቸው፡፡ ምርጥ አርቆ አስተዋይ የኦሮሞ ልጆች፡፡ ድካማቸውና ራዕያቸው እያስተጋባ ለዝንተ ዓለም እየደመቀ እየጎላ የሚሄድ ብጹዓን!!

ለምን ቢባል የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ዘበት ያልቆጠረው የእርሱ የራሱ አድርጎ የወሰደውን አስጨበጡት፡፡ ዘመን የማይሽረውን፣ አልፋና ኦሜጋ የማይቀይረውን ቤቱን መሠረቱለት፡፡ ዘመናት የነፈጉትንና መንግሥታት የቀሙትን መንግሥቱን አቆሙለት፡፡ እንዲሁ እንደ ዘበት አሳልፎ ለማንም የማይሰጠውን መብቱንና የመብቱ ትክል የሆነውን ማንነቱን፣ ደግሞም ለመብቱና ለማንነቱ መከበሪያ የሆነውን ግዙፍ መሣሪያ መንግሥቱን፣ አገሩንና በከፊል ሀብቱን አስታጠቁት፡፡ ዛሬ ለመብቱ በብርቱ የሚሞግትና የሚታገል ሕዝብ ደግሞም የሕዝብን ቅሬታና ተቃውሞ ለመስማት ጆሮ ያለውና አድምጦም ከሕዝቡ ጋር በመመካከር መፍትሔ የሚሻ መንግሥት ሊገኝ የቻለው ተቁሞ የሚነገርበት፣ የእኔ ነው ተብሎ የሚሟገቱለት መሬት፣ ሀብትና መንግሥት ስላለ ብቻ ነው፡፡ የፊንፊኔ ልዩ ጥቅም  የሙግታችን አንዱ አካል ሊሆን የቻለው ፊንፊኔ የእኛ መሆኗ ስለተረጋገጠ እንጂ፣ ስለጥቅሟ ሳይሆን ስለየኛነቷ በሆነ ነበር ዛሬ ትግሉ ይሆን የነበረው፡፡ ትግል የሚወስነው በወቅት፣ በቦታና በሁኔታዎች ውስጥ ነው፡፡ እነዚህን አመቻችቶ የተወሰደ ዕርምጃ ይሰምራል፡፡ እነዚያ ድንቅዬዎች ይህን ተገንዝበው ሌላው ሳይባንን እነርሱ ነቅተውና መጥቀው የወሰዱት ዕርምጃ፣ ዛሬ ማንነታችንን አላቀው፡፡ ይህ ከንቱ ውዳሴ አይደለም፡፡

‘ትግል አይሞትም ታጋይ ይሞታል እንጂ’ የሚባለው ለእኛ ታጋዮች ሲገጥም እውነት አይሆንም፡፡ ምን ዓይነት ሞት የሚለው በውሉ መመለስ አለበት፡፡ ዝርዝር ውስጥ መግባት አያሻም፡፡ የኦሮሚያ ጉዳይ እስከ መጨረሻውና ለሁሌም በውል ካልተመለሰ፣ የኦሮሞ ሕዝብ እስከ ወዲያኛው በአገሪቱ ውስጥ በልኩ የሚመጥን መብት ካላገኘ፣ ትግሉም ሞቷል ታጋዮቹ በሕይወት ኖሩ አልኖሩ ሞተዋል፡፡ ዘወር አድርገን ተጨባጩን ስናየው ግን ትግሉም ወቅትና ሁኔታን ተንተርሶ እየገሰገሰ፣ ድሉም የትግሉን አኳያ ተከትሎ እየተመዘገበ ሲነጉድ እንመለከታለን፡፡ ‘ሮማ በአንድ ጀምበር አልተሠራችም’ እንዲሉ ሁሉም በአንድ ጨረቃ ይፈጸም ብሎ በሐሳብ መስከር ካልሆነ በስተቀር የታጋዮቻችን ትግል ድል ከማስመዝገብ፣ የወረወሩት ጦር ከመውጋት ተስተጓጉሎ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ትግሉም እነርሱም አልሞቱም፡፡ ፊንፊኔን ወደ አዳማ ለመቀየር ይዋትቱ የነበሩት ምላሰ ረዣዥምና ቀልማዳ ግንባር ቀደሞች ዛሬ የይስሙላ ስደት ላይ ሆነው ጥሩምባ የሚነፉትም ሆነ፣ እዚህ አገር ውስጥ ሆነው በአደባባይ ያፀደቁትን ሕገ መንግሥት ፊርማቸው ሳይደርቅ የሚያብጠለጥሉት በቁም ሞቱ ማለት እነርሱን ነው፡፡ ስለዚህ ትግላችን አልሞተም፡፡ የፊንፊኔ ጉዳይ ከ25 ዓመታት በኋላ ለዚያውም የኦሮሞ ሕዝብ በአንድ ቃል ውሳኔ ማስገኘት የቻለበት የፖለቲካ አጀንዳና ድል ለዚህ ጠንካራ ማስረጃ ነው፡፡

ፊንፊኔ የኦሮሚያ መሆኗ የዛሬ ሦስት አሥርት ግድም በይፋ ሲታወጅ እንደሆነው ሁሉ የሚሰጠውም መፍትሔ ሀቀኛና በሕዝባዊ ወገናዊነት የተቃኘ መሆኑ የግድ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች መከበራቸው የግድ ነው፡፡ በፖለቲካው አኳያ በፊንፊኔ ምክር ቤት ውስጥ የከተማይቱ ነዋሪ ኦሮሞ ተመራጮችን ሳይጨምር፣ በቀጥታ ከኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች የሚወከሉ አባላት ቁጥር ከ33 በመቶ በላይ መሆኑን ማረጋገጥ፣ የምክር ቤቱ ከንቲባዎች፣ አፈ ጉባዔዎችና ካቢኔዎች ሹመትና ሥርጭት በዚሁ መልኩ ሆኖ ችሎታን ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበት ማረጋገጥ፣ ቋንቋና ሰንደቅ ዓላማ ጥምር፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ቅጥር ተመጣጣኝ፣ ወዘተ ተብሎ ለአብነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ከኦሮሚያ ድንበርና በተለይም የረዥም ጊዜም ሆነ የአጭር ጊዜ የከተማይቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጦችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ውሳኔ ላይ የኦሮሚያ ሕዝብና መንግሥት ይሁንታ የግዴታ መሆኑ ተሰምሮበት፣ ፊንፊኔ ቻርተርድ ከተማ መሆንዋ እንጂ የኦሮሚያ አካል እንደሆነች በሕግ መንደንገጉ አስፈላጊ ነው፡፡ መሆኑ ከቶውንም ሊቀር የሚችል ስላይደለ ዛሬ የምንሠራው መሬት ላይ ከመድረሱ እንዳያነታርከን ለማለት ነው፡፡ በኢኮኖሚውም አንፃር በጥቅሉ ፊንፊኔ ከምታገኘው ገቢ ሩቡን በቀጥታ ለኦሮሚያ ፈሰስ ማድረግ ይኖርባታል፡፡ ምክንያቱም ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ ነገር አንዳችም ከኦሮሚያ ውጪ አሊያም የኦሮሚያን ምድር ሳይነካ ፊንፊኔ የሚደርስ ነገር የለም፡፡

በመጨረሻ እየከሰመ የሚሄደው ሀብት የኦሮሚያ ስለሆነ ታክስ ኤክስፖርት በማድረግ የቀውስ ተሸካሚ መሆን ስለሚመጣ፣ የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል ጉዳይ በቂ ትኩረት ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ለእያንዳንዱ ኦሮሚያ ውስጥ ተተክሎ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ፊንፊኔ የሚያስተላልፈውን ፖል፣ ከኦሮሚያ ተዘርግቶ ፊንፊኔ ውኃ የሚያጓጉዘውን እያንዳንዱን ሜትር የውኃ ቱቦና . . . ወዘተ ለክቶ የሮያሊቲ ክፍያ መጠየቅ መቻሉ እየታወቀ ቀርቶ ማለት ነው፡፡ ይህንን የራስን ሀብት ለሁሉም በነፃ መገልገያ ያደረገ ሌላ የክልል መንግሥት ከኦሮሚያ ውጪ የለም፡፡ የፌዴራል መንግሥቱን መቀመጫ በመስጠቷ ኦሮሚያ የኛ የኛ ነው፣ ያንቺም የኛ ነው ልትባል አይገባትም፡፡ ደግሞም ፍትሐዊ አይሆንም፡፡ የልማታዊ መንግሥት አቅጣጫ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ማስገኘት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡  

አንባቢያን ግን ልብ ይበሉ፡፡ ሁሉም የኦሮሞ የፖለቲካ ጥያቄዎች ተመልሰዋል የሚል አንዳችም ቃል እንዳልተነፈስኩ፡፡ ደግሞም በአንድ ጀምበር ሁሉንም አምጣችሁ ውለዱም አልወጣኝም፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደ ተሞከረው ሁሉም ነገር በቦታ፣ በጊዜና በሁኔታዎች ውስጥ ነው የሚተገበረው፡፡ በሕዝብ ውስጥ ዘወትር የማያቆም እንቅስቃሴና ዕድገት አለ፡፡ ቅስቃሴውም ዕድገቱም መልስ የሚሹ ጥያቄዎችን ተሸክመው ይጓዛሉ፡፡ ላለፉት ሁለት አሥርታት የተፈጠሩ ችግሮች ካለፉት መንግሥታት ከወረስናቸው በሽታዎች ተዛምደው ለአገር ልማት እንቅፋት ሆነው እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ በተለይም ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት እነዚህ ችግሮች ጎልተው ሕዝቡን በአደባባይ ተቃውሞ እንዲያደርግ ቀስቅሰውታል፡፡ ከዚህ አንፃር ኦሮሚያ ክፉኛ ታምሳለች፡፡ እነዚህን ችግሮች የእኔ ነው ብሎ የተቀበለ፣ ችግሮቹንም ለማስወገድ ቃል ገብቶ ዕርምጃ መውሰድ የጀመረ መንግሥት መኖሩና ሕዝባዊ ወገናዊነት መልሶ ነፍስ ሲዘራና ኦሕዴድም በሕይወት መኖሩን ሲያሳየን፣ ወቅትና ሁኔታዎች ወሳኝ መሆናቸውን አስገንዝቦን የተከሰከሰው ሞራላችንን ነቃ ነቃ አድርጎታል፡፡ የግድ ደግሞ ሕዝብ ብሶተኛ እስኪሆን መጠበቅ አያስፈልግም፡፡ ሌሎች እንደሚሉት ገዢው ፓርቲ ሳይሆን እኔ እንደምለው መሪ የኦሮሞ ፓርቲ ግንባር ቀደም፣ አቅጣጫ ቀያሽና ዒላማ አመልካች የሕዝብ መሪ ፓርቲ ሆኖ መገኘቱን በጣም እጠብቃለሁ፡፡ ተመሪም፣ ተገዢም፣ ተጎታችም መሆን አይጠበቅበትም፡፡ ከሰሞኑ ሁኔታ አንፃር ጉልበቴ በርታ . . . በርታ . . . መባሉ አግባብ ነው፡፡

ቢሆንም ግን የመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት ጉዳይ አሁንም ምኑ ተይዞ ጉዞ ዓይነት ነው፡፡ የጥቂት ካቢኔዎች መታሰር መፍትሔ ሆኖ ተወስዶ ከሆነ ከዚቅ ይቆጠራል፡፡ ጥልቅ ተሃድሶው መሀል መንገድ ላይ ተቸክሎ እንዳይቀርና ሌላ ጥልቅ ተሃድሶ ጠይቆ የልማት ጊዜ እንዳያቃጥልብን፣ በነካ እጅ እስከ ታችኛውና የጎንዮሽም ማጥራቱ የግድ ይላል፡፡ ወደ ላይም ጭምር፡፡ በሕገወጥ አንቨስትመንት ስም በደን ጭፍጨፋ በመቶ ሚሊዮኖች የሚወድመውን የአገር ሀብት ኡኡ ብሎ ጮሆ ድምፁን የማያሰማው የደን ኤጀንሲ አፉ በምን ታሽጎ፣ ድምፁ በምን ተቀርቅሮ እንደሆነ ይታይ፡፡ ለነገሩማ አያሌ አይነኬዎች አሉ፡፡ አንዳንድ በክልል ደረጃ ላይ ሰፊ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት የተሸከሙ የፌዴራል መንግሥቱ ተጠያቂ መሥሪያ ቤቶች በተለይም መብራት ኃይል፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽንና የውኃ አገልግሎት አካላት የሕዝብን ብሶት በመቀስቀስ በኩል ሸጋ ሰበብ ሊሆኑ የሚችሉ ዓይነቶች ናቸው፡፡ ክልሎችን አያደምጡ፣ ባለቤታቸው ፌዴራል አያውቃቸው፡፡ ለአሥራ ምናምን ቀናት የውኃ፣ የመብራትና የቴሌፎን አገልግሎቶች በተከታታይ ያጣ ሕዝብ መንግሥት የለም ቢል ማን ደፍሮ ሐሰት ነው ይለዋል? ያሳፍር አይደል!!! ተሃድሶው እዚህ አካባቢ ላይ የሥልጣን መማከል ችግርን መፍታት ይጠበቅበታል፡፡ እነዚህ በክልሎች ውስጥ የሚሠሩትን መሥሪያ ቤቶች አስተዳደር ክልሎች ቢረከቡ ሰማይ አይደፋብን፡፡ እየተካሄደ ያለው የጥልቅ ተሃድሶ ቁርጠኝነት ሁሉንም በተመሳሳይ ዘልቆ ያድስ እንጂ ተንጠልጥሎ አይቅር፡፡ አጠቃላይ ተሃድሶውን ግን ‹‹ጉልበቴ በርታ… በርታ…››፡፡ አሊቬ ዴርች!!! 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው tihuneasfaw@gmail.com. ማግኘት ይቻላል፡፡

 

                   

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231