Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

በሕክምና አሰጣጥ የደረሰን ጉዳት የማስረዳት ፈተና

$
0
0

   በሰለሞን ጓንጉል አበራ

      አንዳንድ ጊዜ ‹በሙያህ ዕርዳኝ፣ ሸክሜን አንተ ዘንድ ባለው የመፍትሔ መንገድ አቅልልኝ፣› ብሎ ድንገት ለሚጠይቅ ሰው በጠየቀበት ፍጥነት ምላሽ መስጠት፣ ሸክሙን ለማቅለል መሞከርና መቻል መታደል ነው፡፡ ከፍ ያለ መታደል፡፡ ወጣቱ መምህር በግንቦት ወር 2009 ዓ.ም. አንድ ቅዳሜ ማለዳ ከቢሮዬ ደርሶ የዘረገፈው ሸክሙም ይኼንን ጽሑፍ እንድጽፍ ምክንያት ሆነኝ፡፡  ከብቸኝነት ይልቅ በትዳር መኖርን መርጦ መኖር ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ ነበር ባለቤቱ ነፍሰ ጡር የሆነችው፡፡ የጽንሱንና የእሷንም ጤና ለመጠበቅ በአዲስ አበባ በሚገኝ አንድ የመንግሥት ጤና ጣቢያም ክትትል ስታደርግ ከቆየች በኋላ፣ ጽንሱ ምጥን አስቀድሞ በመድረሱ ክትትል ታደርግበት ወደ ነበረ ጤና ጣቢያ ታመራለች፡፡ ጤና ጣቢያው ግን ለማዋለድ ስላልሆነለት ወደ መንግሥት ሆስፒታል በሪፈር እንድትሄድ ያደርጋል፡፡

በገባችበት ሆስፒታል በቀዶ ሕክምና የወለደችው እናት ልጅዋን በሕይወት ለማቀፍ ባትታደልም፣ የእሷን ጤና መሆን ከባለቤትዋ ጋር አመሥግነው ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ቤታቸው ከገቡ በኋላ የእግርና እጅ መደንዘዝ ሲያጋጥማት ወደ ወለደችበት የመንግሥት ሆስፒታል ተመልሳ ብትሄድም፣ ሕክምናውን ወዲያው አግኝታና ተሽሏት አልተመለሰችም፡፡ እዚያው አልጋ ይዛ ሕክምና እየተሰጣት ወራት ቢቆጠሩም በጤናዋ ላይ መሻሻል አልታየም፡፡ ደግሞ ለውጥ ባገኝ በሚል ባለቤትዋ ወደ ግል ሆስፒታል ቢወስዳትም የተገኘ አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ በሁለት እግሮችዋ ወደ ሆስፒታል ሄዳ እጆችና እግሮችዋን ማዘዝ አቅቷት ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡

በጽንስ ክትትል ወቅትም ሆነ ከዚያ በፊት አልጋ ላይ ሊያውል የሚችል ሕመም አልነበረባትም ያለው ባለቤቷ ሕክምና የሰጣቸው የመንግሥት ተቋምና ባለሙያዎች የሕክምና ስህተት በመፈጸም ለጉዳት ዳርገዋታል ሲል በእሷ ስም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አቤቱታ ያቀርባል፡፡ አቤቱታውን የመረመረው ኮሚቴ የሰጠውንና በዋና ዳይሬክተሩ የፀደቀውን ሀለት ገጽ ውሳኔ ተመለከትኩት፡፡ ውሳኔው ምጡ ብዙ ጊዜ ስለቆየና ደም ስለፈሰሰኝ የሚል ምክንያትን ባለሙያዎቹ የፈጸሙት የሥነ ምግባር ጉድለት መሆኑን  በምክንያትነት መጥቀስዋን በመግቢያው አስፍሯል፡፡ ጥር 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥር አ/አ/መ/መ/ክ/አስ/ 443/90 በተሰጠው ውሳኔ ኮሚቴው  በማጣራት ሒደት ሕክምናውን የሰጡትን ባለሙያዎች አስቀርቦ መጠየቁን፣ እንዲሁም የሕክምና ሰነዶቹንም አስቀርቦ መመርመሩ ተጠቅሷል፡፡ በስተመጨረሻም ‹‹ጉዳትዎ ከተሠራልዎት ኦፕራሲዮን ጋር ግንኙነት እንደሌለውና በሆስፒታሉ (ስም ተጠቅሷል) እና የሕክምና ባለሙያዎችም የሕክምና ሙያ ሥነ ምግባር ግድፈት (ስህተት) ያልተፈጸመ መሆኑን እናስታውቃለን፤›› ሲል ውሳኔውን ለእሷና ለባለቤቷ አስታውቋል፡፡ ታዲያ ምን ሆና አልጋ ላይ ዋለች? አልጋ ላይ ለዳረጋት ሕመም ማን ኃላፊነት አለበት? ይኼንንስ ጥያቄ ከኮሚቴው በላይ ማን መልስ ሊሰጥበት ይችላል? ለሚሉት ጥያቄዎች የኮሚቴው ውሳኔ መልስ የሚሰጥ አልነበረም፡፡

ስህተት ሰው የመሆንና የመሥራት ድምር ውጤት ሊያመጡት የሚችሉት ነገር ነው፡፡ የስህተት መጠኑና ደረጃው እንዲሁም ሊፈጠር የቻለበት ምክንያት የተለያየ ይሁን እንጂ፣ በየትኛውም የሥራ መስክ  ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ስህተት እያልኩ የምጠራው ሆነ ተብሎ ወይም በቸልተኛነት ከሚፈጸም ድርጊት በተቃራኒ የሚጠቀሰውን ድርጊት ብቻ ነው፡፡ በየትኛውም ሙያ የሚያጋጥም ስህተት ሊታረም የሚችልበት ዕድል፣ እንዲሁም ሊያስከፍለው የሚችለው ዋጋ እንደየሙያውና የሥራው ዓይነት የተለያየ ነው፡፡ እንደ ምሳሌ በአንድ የግንባታ ሥራ ላይ የዲዛይን ስህተት ቢያጋጥምና ስህተቱን ማረም ግድ ቢል የሚያስከፍለው ዋጋ የገንዘብና የጊዜ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ በተመሳሳይ በሌሎች የሥራ መስኮች የሚያጋጥሙና የስህተት ክፍያ ዋጋቸው ሰው የፈጠረው ገንዘብ ብቻ ሆነው የሚያልፉ ብዙ ድርጊቶችን መጥቀስ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡  

    የሰው ልጅም ከፈጣሪው ወይም ከራሱ እምነት ቀጥሎ ሙሉ እምነቱን በመስጠት ለጤናው ጥያቄ መልስ በመሻት መዳንን የሚለማመነው ሐኪም ጋር ይመስለኛል፡፡ ምንም የተማረም ቢሆን  የአብዛኛው ሰው የሕክምና ዕውቀት ውስን ወይም ፈጽሞም የሌለ በመሆኑ፣ የሐኪሙን የሕክምና መንገድም ሆነ የተሰጠውን ሕክምናና መድኃኒት እንዳለ ከመቀበል ባለፈ ምን ዓይነት ምርመራ ተደረገልኝ? ውጤቱስ ምን ሆነ? ለምን? ወደፊትስ ምን ላድርግ? እና መሰል ጥያቄዎችን  የመጠየቅ ልምድ እምብዛም የለም፡፡ ይህም ሐኪሙ የሰጠው ሕክምና ስህተት እንኳን ቢሆን ስህተቱን የማረም ዕድሉን እጅግ አነስተኛ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍም ስለሐኪምና ታካሚ ግንኙነት፣ ግንኙነቱን ስለማወቅ፣ በግንኙነቱ በሕክምና ስህተት በታካሚው ላይ ስለሚደርስ ጉዳት፣ ጉዳቱን አውቆ ለማስረዳት ስላለው ፈተናና ስለመካስ የአገራችንን ሕግጋት መሠረት በማድረግ በመጠኑ ለማንሳት ተሞክሯል፡፡

 የሕክምና ባለሙያና የታካሚ ግንኙነት

አንድ የሕክምና ባለሙያ ለታካሚ ሕክምናውን መስጠት ከመጀመሩ አስቀድሞ ስለሚሰጠው ሕክምና ታካሚውን በሚገባው መንገድ የማሳወቅና ፈቃዱን የማግኘት ግዴታ አለበት፡፡ የምግብ የመድኃኒትና ጤና እንክብካቤና አስተዳደርና ቁጥጥር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 299/2006 የሕክምና ባለሙያው ሕክምናውን ለመስጠት፣ የታካሚው በግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ፈቃድ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

አንቀጽ 52 የታካሚውን ሙሉ ፈቃድ ስለማግኘት

  1. የታካሚዉ በግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ፈቃድ ሳይገኝ የሕክምና አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው፡፡

በንዑስ ቁጥር 2 ድንጋጌ መሠረት በቃል ወይም በድርጊት እንዲገልጽ በመመርያ ካልተፈቀደ በስተቀር ታካሚው ለመታከም የሚሰጠው ፈቃድ ሁልጊዜም በጽሑፍ መሆን አለበት፡፡ ይህ ድንጋጌ ታካሚው ስለሚያገኘው ሕክምና የማወቅና የመወሰን መብትን የሚሰጠው ቢሆንም፣ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብሎ ለመናገር አይቻልም፡፡ እያንዳንዱን ምክንያት ለታካሚው ሳያሳውቁ የላብራቶሪ ምርመራዎችን ማድረግ፣ እንዲሁም ለማዋለድም ሆነ ለውስብስብ ቀዶ ጥገና ፈቃድ ለማግኘት በተመሳሳይ ፎርም ታካሚን ማስፈረም ሕክምናን እናስተምራለን በሚሉ ተቋማት ጭምር ሲሠራበት አጋጥሞኛል፡፡

ከታካሚው በግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ፈቃድ ከተገኘና ሕክምናው ከተጀመረ በኋላም የሕክምና ባለሙያው በጤናው ተቋም ከታካሚው ጋር በነበረው እያንዳንዱ ግንኙነት የተገኙ የግል ጤና መረጃዎችን መዝግቦ የመያዝ ግዴታ አለበት፡፡ የምግብ የመድኃኒት ጤና እንክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ 661/2002 አንቀጽ 37 ከሕክምና ባለሙያዎቹ በተጨማሪም፣ መረጃዎች በአግባቡ መያዛቸውንና መጠበቃቸውን እንዲያረጋግጡ በጤና ተቋማት ላይ ግዴታን ያስቀምጣል፡፡ ተመዝግበው የሚገኙት መረጃዎች በሙሉም በሚስጥር የሚጠበቁና እንዲገለጹ በሕግ ከተፈቀዱ ሁኔታዎች ውጪ ይፋ የማይደረጉ ናቸው፡፡ ሚስጥር ሆነው መጠበቅ አለባቸው የሚለውንና ሁኔታዎቹን የሚደነግገውን የአዋጁ አንቀጽ 77 ድንጌን በመተላለፍ የሕክምና ሚስጥርን ይፋ ማድረግ በሙያው ሥነ ምግባር የሚያስጠይቅበት ሁኔታ እንዳለ ሆኖ የወንጀል ኃላፊነትንም ያስከትላል፡፡ የተሻሻለው የወንጀል ሕግ ሚስጥር የመጠበቅ ኃላፊነት ከጣለባቸው ሙያዎች መካከል ሕክምና አንዱ ሲሆን፣ የሕክምና ባለሙያው ሚስጥሩን እንዲገልጽ በሕግ ከተፈቀደለት ሁኔታ ዉጪ ይፋ አድርጎ ከተገኘና ታካሚው ይኼንን በመቃወም አቤቱታ ካቀረበበት በቀላል እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡

     የታካሚን ፈቃድ የማግኘት፣ የተሰጠውን እያንዳንዱን ሕክምና በካርዱ ላይ የመመዝገብና የታካሚውን ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታዎች በሙሉ ከመብትም ባለፈ በታካሚና በባለሙያው መካከል የሚፈጠረውንና መተማመን መሠረት ያደረገውን ጥብቅ የሆነ ግንኙነት የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሁኔታዎች መሟላት ሕክምና የሚያሻው ሁሉ ወደ ሕክምና ተቋማት እንዲሄድ ዋስትና ይሰጡታል፡፡ በተለምዶ በሕክምና ባለሙያውና በታካሚው መካከል ያለውን የሕክምና ግንኙነት ሊያስረዱ የሚችሉ ሰነዶችን በሙሉ ለማለት በሚቻል ሁኔታ የሚገኙት ሕክምናውን የሰጠው ተቋም ዘንድ ብቻ ነው፡፡ አልፎ አልፎ እንደ ቀላል ጻፍ ጻፍ ተደርጎ ለታካሚው ከሚሰጥ የሕክምና ሰርተፊኬት ባለፈ ታካሚው ስለተሰጠው ሕክምና ሒደት የሚገልጽ ማስረጃ በተሟላ ሁኔታ በእጁ አይኖረውም፡፡ ደንብ ቁጥር 299/2006 አንቀጽ 56  በአንድ የሕክምና ሰርተፊኬት ላይ ለታካሚው የተሰጠውና ወደፊት የሚያስፈልገው ሕክምና በዝርዝር መጻፍ እንዳለበት አስገዳጅ ድንጋጌን አስቀምጧል፡፡ የሕክምና ምስክር ወረቀት  ለታካሚ ሲሰጥ፣

  1. የታካሚውን ስም፣ ዕድሜና አድራሻ
  2. የምርመራውን ውጤትና ለታካሚው የተደረገለትን ሕክምናና እንደ ሁኔታው የተሰጠውን ዕረፍትና የቦርድ ውሳኔ
  3. የሕክምና ማስረጃው የተሰጠበት ቀን
  4. ተከታታይ ሕክምና ስለማስፈለጉና የታካሚውን ወቅታዊ የጤና ሁኔታ
  5. ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ሊይዝ ይገባል፡፡

ድንጋጌው አስገዳጅ ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ያጋጠሙኝ የሕክምና ሰርተፊኬቶች ግን በዚህ አግባብ ተሟልተው የቀረቡ አልነበሩም፡፡ በጥንቃቄ በሕጉ መሠረት አሟልተው የሚጽፉ እንዳሉ ሆነው እንደ ቀልድ ጫር ጫር አድርገው የሚሰጡም ያጋጥማሉ፡፡

 የሕክምና ስህተት መፈጠሩን የማወቅ ፈተና

ታካሚው በጥቅሉም ማኅበረሰቡ ለሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጠው እጅግ ከፍ ያለ ከበሬታና አመኔታ በሕክምና ወቅት ስህተት ተፈጥሮ ይሆን ወይ? ብሎ ለመጠራጠርም ሆነ ጥያቄውን በራሱ እንዳይነሳ ለማድረግ ቀዳሚ ምክንያት ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ የምንከተለው የሕክምና አስተዳደር፣ በባለሙያዎች መካከል አንዱ የሌላውን ስህተት ለማጋለጥ ያለመፈለግ፣ የታካሚ መብትን የተመለከተ ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖርና ሌሎችም መሰል ምክንያቶች በታካሚው ላይ የተፈጠረው የሕክምና ስህተት እንዳይታወቅ በማድረግ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሐኪሙ ሙያውን አክብሮና የፈጠረውም ስህተት ካለ ተቀብሎ ለታካሚው ካልነገረው ወይም በተፈጠረው ስህተት ታካሚው ሕመም አጋጥሞት ወደ ሌላ ሕክምና ሄዶ በምርመራ ካልተነገረው፣ በራሱ አካል ውስጥ ስለተፈጠረው ነገር የማወቅ ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 661/2002  አንቀጽ 36 ሙያዊ ስህተት መፈጸሙን ያወቀ የጤና ባለሙያ ወይም ማንኛውም ሰው አግባብ ላለው አካል ሪፖርት ማድረግ አለበት ሲል ያስቀመጠውን ድንጋጌ፣ ምን ያህሉ ሐኪም ተጠያቂነትን ሳይፈራ ያደርገዋል? ለሚለውም ጥያቄ በሰነድ የተደገፈ ማስረጃ ማቅረብ አስቸጋሪ ነው፡፡

የሕክምና ስህተትና ተጠያቂ ስለመሆን

      በአንድ ባለሙያ የተሰጠ ሕክምና ስህተት ነው ሊባል የሚችለው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ሲፈጸም ነው? መለኪያውስ ምንድን ነው? ለሚሉና መሰል ጥያቄዎች መልስ መስጠት የሚቻለው የሕክምና ስህተትን በመተርጎም ቢሆንም አዋጁም ሆነ ደንቡ ያስቀመጡት ትርጉም የለም፡፡ አዋጁ የሕክምና ስህተትን ስለማሳወቅ የሚገልጽ ድንጋጌ ይዞ፣ እንዲሁም ባለሙያውና ማንኛውም ሰው የሕክምና ስህተትን ሪፖርት እንዲያደርጉ ግዴታን እያስቀመጠ የሕክምና ስህተትን አለመተርጎሙ፣ በተዘዋዋሪ ድንጋጌው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚያደርግ ይመስለኛል፡፡ ሕክምና በባህሪው የሕክምና ባለሙያውን ፍፅምና የማይጠብቅ በመሆኑ አንድን ታማሚ ለምን አላዳንከውም ተብሎ ባለሙያው የሚጠየቅበት አግባብ የለም፡፡ በእርግጥ ባለሙያው ራሱ ለሰጠው ሕክምና መልካም ውጤት አስገኛለሁ ሲል በጽሑፍ ዋስትና የሰጠ እንደሆነ ኃላፊነት ሊኖርበት እንደሚችል የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2648 ይደነግጋል፡፡  የሕክምና ሥራ ተጠያቂነት ሊያስከትል የሚችለው ባለሙያው የሙያውን ሥነ ምግባርና ሕግን በተቃረነ መንገድ ጉዳት ባያደርስም እንኳን ለታካሚው ሕክምና ከሰጠ፣ ሆነ ብሎ ወይም በቸልተኛነት በተፈጸመ ሕክምና በታካሚው ላይ ጉዳት ካስከተለ ብቻ ነው፡፡

የተፈጠረው የሕክምና ስህተት ወዲያው ሊታይ ወይም ሊታወቅ የሚችልበት ዕድሉ እንዳለ ሆኖ፣ ታካሚው ራሱ ፈጽሞ የተፈጸመበትን ስህተት ወይም ሕክምናው ያስከተለበትን ጉዳት ሳያውቅ ዓመታትን ሊያስቆጥር ወይም ጨርሶ ላያውቅ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ በመሆኑም በሕክምና በተፈጠረ ስህተት ባለሙያውን  ተጠያቂ ለማድረግ  የሕክምና ስህተቱ መፈጠሩን ታካሚው የግድ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ በእኛ አገር ሕግ የተፈጠረው ስህተት ከታወቀ በኋላ ባለሙያውንም ሆነ ለታካሚው አገልግሎቱን የሰጠውን ተቋም ተጠያቂ ለማድረግ፣ ታካሚው ወይም ቤተሰቡ አስተዳደራዊ መንገድንና ፍርድ ቤትን ሊጠቀም ይችላል፡፡ በፍርድ ቤት አቤቱታው የሚቀርበው በወንጀል እንዲቀጡ ወይም በፍትሐ ብሔር ለመካስ ነው፡፡

     አንድ የሕክምና ባለሙያ ወይም የሕክምና ተቋም በሰጡት የሕክምና አገልግሎት ላይ የሚኖርባቸው የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት ውልንና  ከውል ውጪ ያለ ግንኙነትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የምግብ መድኃኒትና ጤና እንክብካቤ አዋጅና ደንብ የሕክምና ባለሙያውም ሆነ ተቋሙ የአዋጁንና የደንቡን ድንጋጌዎች ተላልፈው በተገኙ ጊዜ፣ ከመቅጣት ባለፈ ለታካሚው ስለሚሰጥ ካሳ ያወጡት ድንጋጌ የለም፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ከቁጥር 2639 እስከ ቁጥር 2652 ያሉ ድንጋጌዎች የሕክምና አገልግሎት ውልን የሚገዙ ሲሆኑ፣ የውሉ መጣስም ሊያስከትለው ስለሚችለው ኃላፊነት በደምሳሳው ይደነግጋሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ከውል ውጪ ባለ ግንኙነት ጥፋትን ወይም የሙያ ሥነ ምግባርን በመተላለፍ ለተፈጠረ የሕክምና ስህተት ተጠያቂነት አይኖርም ከሚል ድምዳሜ የሚያደርስ አይሆንም፡፡ ለተጠያቂነት ጥብቅ የሆነ መለኪያን ያስቀመጠው የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2031 በሙያ ሥራ ስለሚደረግ ጥፋት ስለሚኖር ተጠያቂነት ያሰፈረው ድንጋጌ ለሕክምና ሥራ ተፈጻሚ የሚሆን ነው፡፡ ስለሐኪም ኃላፊነት የሚደነግገው የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2647/1 ከዚህ ድንጋጌ ጋር ተገናዝቦ የሚታይ ነው፡፡

የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2651 እና 2031 ሕክምናውን የሰጠው ባለሙያም ሆነ አገልግሎቱ የተሰጠበት ተቋም ኃላፊነት እንዳለባቸው የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ የሕክምና አገልግሎት ሁሉ በታካሚውና በሐኪሙ ወይም በተቋሙ መካከል በሚፈጠር የውል ግንኙነት (በጽሑፍም ባይሆን) የሚፈጠር በመሆኑ፣ ከውል ውጪ ያለ ግንኙነት በመካከላቸው ሊፈጠር አይችልም የሚል ክርክር ሊቀርብ ይችላል፡፡ የውል ግንኙነቱን ተከትሎ የሚፈጠረው ስህተት የሚያስከትለው ኃላፊነትም ሆነ የሚስጠይቀው የካሳ መጠን ግን በውላቸው ላይ ሊካተት የሚችልበት አጋጣሚ ጠባብ በመሆኑ፣ ኃላፊነት የሚያስከትል የካሳ ጥያቄ በተነሳ ጊዜ ከውል ውጪ ያሉ ግንኙነቶችን የተመለከቱ የፍትሐ ብሔር ሕግጋት ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

የሕክምና ባለሙያውንም ሆነ አገልግሎት የሰጠውን ተቋም አስቀድሞም ተጠያቂ ለማድረግ ታካሚው ማስረጃ ሊኖረው ግድ ይለዋል፡፡ ከላይ በዝርዝር እንዳነሳሁት ሁልጊዜም ለማለት በሚቻል ሁኔታ የታካሚው መረጃዎች በሙሉ ተመዝግበው የሚቀመጡት አገልግሎቱ በተሰጠበት ተቋም በመሆኑ፣ ታካሚው ስለራሱ የሚገልጹትን እነዚህን ማስረጃዎች ለማግኘት ይቸገራል፡፡ ያለእነዚህ ማስረጃዎች የተፈጸመበትን ጥፋትም ሆነ የደረሰበትን ጉዳት በተሟላ መንገድ ለማስረዳት ስለሚቸገር መብቱን ለመጠየቅም ሆነ ከጠየቀ በኋላ ፍትሕ ለማግኘት ከባድ ፈተና ይሆንበታል፡፡

ኃላፊነትን ከጉዳቱ ጋር የማስረዳቱና የካሳው ነገር

      ከሙያዊ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ አቤቱታ ተቀብሎ የሚመረምርና አስተያየት የሚሰጥ በአዲስ አበባ የምግብ የመድኃኒትና ጤና እንክብካቤ ሥር የሚገኝ ኮሚቴ ተቋቁሞ በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ የአዋጅ ቁጥር 661/ 2202 አንቀጽ 55/2 አዋጁን ለማስፈጸም የሚረዱ ሕጎችን የማውጣት ሥልጣንን በግልጽ የሰጡት ለክልሎች ብቻ ሲሆን፣ በደንብ ቁጥር 299/2006 መሠረት የተቋቋመው ኮሚቴም በፌዴራል ባለሥልጣኑ ሥር እንዲሠራ የተቋቋመመ  በመሆኑ  የአዲስ አበባው የምርመራ ኮሚቴ በየትኛው የሕግ አግባብ እንደሚሠራ ግልጽ አይደለም፡፡ ይህ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የጤና ተቋምና ባለሙያዎችን በተመለከተ የሚቀርብለትን አቤቱታ እንዲመረምር ኃላፊነት እንዴት እንዳኘ ግልጽ ባይሆንም፣ ቅሬታዎችን እየተቀበለና እየመረመረ ውሳኔ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ግልጽ አይደለም በማለት ያነሳሁትን ጉዳይ እናቆየውና በዚህ ጸሐፊ እምነት የአዲስ አበባው ጽሕፈት ቤት ውስጥ ያለው ኮሚቴ ሥራውን በአግባቡና በፍጥነት እየሠራ ነው ለማለት ይቸገራል፡፡ ለአንድ አቤቱታ በምን ያህል ጊዜ ምላሽ እየተሰጠ እንደሆነ ቀረብ ብላችሁ ተመልከቱና ራሳችሁ ፍረዱ፡፡ በግሌ ለኮሚቴው ቀርቦ፣ ምርመራ ተደርጎና ለባለሥልጣኑ ዳይሬክተር ቀርቦ ውሳኔ ሳይሰጥበት አንድ ዓመት ያለፈው አቤቱታን በማስረጃነት ለመቁጠር እችላለሁ፡፡ እንባም በጊዜ ካልታበሰ ጉዳትም በወቅቱ ካልተካሰ ትርጉም አልባ ነው የሚሆነው፡፡ ቢሮው አቤቱታዎችን የሚመረምርበት መንገድም ሆነ የሚፈጀው ጊዜ በምንም ዓይነት መለኪያ ቢሆን ተገቢ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እንደዚህም ሆኖ የኮሚቴው የምርመራ መንገድና የውሳኔ ሐሳቦቹ የጉዳቱን መንስዔ ማሳየት አለመቻላቸው፣ ስለአሠራሩና ፍትሕ መስጠት ስለመቻሉ ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኖብኛል፡፡

በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ የጠቀስኳትን ተጎጂ በተመለከተ የውሳኔ ሐሳብ የሰጠው ኮሚቴ በምርመራ ወቅት ዝርዝር የሕክምና ሰነዶችንና የሐኪሞቹን ቃል እንደተቀበለ፣ የባለሥልጣኑ ዳይሬክተር ባፀደቁት ውሳኔ ላይ ገልጸዋል፡፡ ኮሚቴው ተከሳሾች የሰጡትን ቃል ወይም የባለሙያዎችን ማብራሪያ በሰማበት ወቅት ግን፣ የጉዳዮቹ ባለቤቶች የሆኑትና አቤቱታውን ያቀረቡት ተጎጂዋም ሆነች ባለቤቷ በቦታው ስላልነበሩ ምን እንደተባለ አልሰሙም፡፡ ታካሚና አካሚን አንዳቸው ስሌላኛቸው ምን እንዳሉ እንኳን ለመስማት ዕድሉን ባላገኙበት ሁኔታ በተናጠል በማናገር የሚሰጥ ፍርድ እውነታውን ለማወቅ ያስችላል ብዬ በግሌ አላምንም፡፡ ልክ እንደ ቃል ምርመራው ሁሉ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ያቀረቡት የጽሑፍ ማስረጃም ምን እንደሆነ የማወቅ ዕድሉ የላቸውም፡፡ በሕግ በተደነገገው መሠረት የሐኪምና የታካሚ እያንዳንዱ ግንኙነት በዝርዝር በማይመዘገብበት፣ የሕክምና ምስክር ወረቀት በሕጉ መሠረት ተሟልቶ የማይሰጥበት ሁኔታ በሚያጋጥምበት፣ እንዲሁም ሰነዶች ሁሉ ከሕክምና ተቋም ብቻ በሚገኙበት እውነታ በዚህ መልኩም ምርመራ በማድረግ በመግቢያዬ ላይ ለጠቀስኳት ተጎጂ የተሰጠውን ዓይነት ሆስፒታሉና ሐኪሞቹ የሥነ ምግባር ጉድለት አልፈጸሙም ዓይነት ድፍን ያለ ውሳኔ ከትክክለኛው ፍትሕ ሊያደርስ አይችልም፡፡

ለአቤቱታውም ሆነ ለምርመራው መንስዔ የሆነው የተጎጂዋ መታመም በመሆኑ ምላሽ ሊሰጥ ወይም የምርመራው ውጤት ሊሆን የሚገባውም የሕመሟን መንስዔ ማወቁ ላይ ነው፡፡ ኮሚቴው የተቋቋመበትም ዓላማ ይኼው ነው፡፡ መንስዔውን ሳያውቁ የተከሰሰውን ሆስፒታልና ባለሙያዎች ስህተት አልፈጸሙም ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደምን ይቻላል? ሆስፒታሉም ሆነ ባለሙያዎቹ ጥፋተኛ አይደሉም የሚል ውሳኔ እየሰጡ፣ በማን ጥፋት ወይም ተፈጥሯዊም ሆነ ተፈጥሯዊ ባልሆነ ምክንያት ጉዳቱ እንደደረሰ አለመንገር ለእኔ የኮሚቴውን ሥራ ያጎድልብኛል፡፡

የታካሚውንም መብት የጎሪጥ ዓይቶ እንደ ማለፍ ያለ ስሜት ያሳድርብኛል፡፡ ታማሚው ምን ሆኖ ታመመ? ለሚለው ጥያቄ እርግጠኛ የሆነ መንስዔውን፣ እርግጠኛ መሆን ካልተቻለም በዚህ ምክንያት ነው ተብሎ ይገመታል ተብሎ መልስ መስጠት እስካልተቻለ ድረስ የታማሚው ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ አይችልም፡፡ በሙያም ሆነ ይኼንን ሥራ ለመሥራት ኮሚቴው መቋቋሙ ሲታይ፣ ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት ካልቻለ ማን ሊሰጥ ይችላል? የሚል ጥያቄን ማስከተሉ አይቀርም፡፡ በመሆኑም ባለሥልጣኑ አሠራሩን በአግባቡና በፍጥነት ሊመረምረውና ሊያስተካክል ይገባል፡፡

የሕክምና ስህተትን የማስረዳት ፈተና

የሕክምና ስህተትን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያሉ የማስረጃ አቀራረብ ሥነ ሥርዓቶች ይኼንን መሰል የታካሚውን ማስረጃ የማቅረብ ፈተና ለማቃለል፣  ከተለመደው የማስረጃ አቀረራብና የማስረዳት ሸክም ዘወር ያለ አካሄድን ይጠቀማሉ፡፡ ይህንን የማስረጃ ምዘና መንገድ በላቲን ‹‹Res Ipsa Liquita›› ይሉታል፡፡ የቀረበው የእንግሊዝኛ ትርጉሙም ‹‹The Thing Speaks for Itself›› የሚል ነው፡፡ ድርጊቱ በራሱ ሁኔታዎችን እንዲያስረዳ የሚጠበቅ ሲሆን፣ አቤቱታ የቀረበበት ወገንም የሰጠውን አገልግሎት በማስረዳት ኃላፊነቱን ከራሱ ላይ እንዲያወርድ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ የማስረዳት ሸክምን  በተከሰሰው ሆስፒታልና ባለሙያው ላይ በመጣል ንፅህናቸውን እንዲያረጋግጡ የማድረግ አሠራር፣ ከላይ ያነሳኋቸውን የሕክምና የተለየ ባህሪ መሠረት ያደርጋሉ፡፡ ታካሚው ዕውቀቱ ስለሌለው የተሰጠው ሕክምናም ሆነ የተሰጠው መድኃኒት ስለሚያመጣለትም ጤና ሆነ ስለሚያመጣበት አሉታዊ ውጤት ሊያውቅ አይችልም፡፡ ሐኪሙ ይኼንን ሕክምና ሰጥቼሃለሁ ይለዋል እንጂ፣ በእርግጥም ባለው ሁኔታ ስለመታከሙም ሆነ ስላለመታከሙ የሚያውቅበት ዕድልም የለም፡፡ ደጋግሜ እንዳነሳሁትም ታካሚው ምንም ዓይነት የሰነድ ማስረጃ በእጁ ላይ ላይኖረው ይችላል፡፡ ይኼንን የማስረጃ ምዘና መንገድ ለሕክምና ስህተት ማስረጃ ምዘና ከመጠቀም ባለፈ፣ ለሌሎች አቤቱታዎች የማዋሉ ነገር እየታየ የመጣ ይመስላል፡፡ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደ ቀላልም እንደ ቀልድም የሚታይባት ህንድ በቅርቡ ባደረገችው የሕግ ማሻሻያ፣ አስገድዶ በመድፈር የተጠረጠሩ ሰዎች አለመድፈራቸውን ወይም የግብረ ሥጋ ግንኙነቱ በፈቃድ የተፈጸመ መሆኑን እንዲያስረዱ ኃላፊነቱን በተጠርጣሪዎች ላይ ጥላለች፡፡

 የሕክምና ስህተትና ካሳው

    ለፍርድ ቤት ለቀረበ የጉዳት አቤቱታ የካሳ መጠንን የማስረዳቱ ጉዳይ ከጉዳቱ ጋር በተመዛዘነ መንገድ የሚለካ ነው፡፡ የካሳ ዋናው ዓላማ ተጎጂን በጉዳቱ መጠን መካስ እንጂ፣ በደረሰ ጉዳት ማትረፍ ባለመሆኑ የጉዳቱን መጠን ማስረዳት የካሳ ጠያቂው ፈተና ይሆናል፡፡ ከሕክምና ውጪ ባሉ የካሳ ጥያቄዎች የጉዳቱን መጠን ማስረዳት እምብዛም አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል፡፡ በሕክምና ስህተት የተፈጠረን ጉዳት የካሳ መጠን መጥቀስ ግን ጤናን በገንዘብ ለመተመን የመሞከር ያህል ከባድ ነው፡፡ ጉዳቱንም በካሳ ክፍያ መልሶ ቀሪ ማድረግና ታካሚውን ድሮ ወደነበረበት የጤና ሁኔታ መመለስ በእርግጠኛነት ይሆናል የሚባል አይደለም፡፡ በእኔ እምነት የሕክምና ስህተትን በፍርድ ቤት ውሳኔ በሚሰጥ የካሳ ክፍያ ሙሉ በሙሉ መካስ የሚቻል አይደለም፡፡

በሕክምና ስህተቱ በታካሚው ላይ የደረሰውን ጉዳት በሌላ ሕክምና ለማስቀረት የሚወጣ ወጪን፣ ስህተቱን ተከትሎ ለመጡ አዳዲስ ጉዳቶችና የአካል መጠገኛ ወጪዎች፣ እንዲሁም በስህተቱ ሳቢያ ወደፊት የሚደርስ ጉዳትን (ፊውቸር ዳሜጅ) የመካስ ኃላፊነት በባለሙያው ወይም አገልግሎቱን በሰጠው ተቋም ላይ ሊወሰኑ ይችላሉ፡፡ ለካሳው የገንዘብ መጠን ተጎጂው እንዳቀረበው የካሳ ጥያቄ ዓይነት  በሚያቀርባቸው ማስረጃዎች ማስረዳት የሚችል ሲሆን፣ ማስረጃ ሊቀርብባቸው ባልቻሉትም ሆነ ዳኛውን ባላሳመኑ የካሳ መጠን ጥያቄዎች ላይ ግን ዳኞች በርትዕ የመሰላቸውን ውሳኔ የመስጠት ሥልጣኑ አላቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው  yenemenged@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles