በብሩክ ፈለቀ
አንድ ለቅሶ ቤት ተገኝቼያለሁ፡፡ በሥነ ጽሑፍ ብናስባቸው አንዱ ሐሳብ ያዳከመው፣ አንዱ ደግሞ በጣም የተገረመ ገፀ ባህሪያትን አግኝቻለሁ፡፡ አንደኛው ገፀ ባህሪ የ40/60 ተመዝጋቢ ነው፡፡ ያለውን ጥሪት አሟጥጦ፣ የነበረችውን መኪና ሸጦና በአትራፊነቱ ተማምኖ ሙሉ ክፍያ የከፈለ ነው፡፡ ሲያወራ በስሜት ነው፡፡ ‹‹አስቡት እስኪ? ባለ ሦስት መኝታ ሠንጋ ተራ፣ መገናኛ ወይም ሌላ መሀል ከተማ ያለ 40/60 ቤት ቢደርሰኝ? ካደለኝና ሥራ ከተሳካልኝ እኖርበታለሁ፡፡ ካልሆነም ደግሞ በጥሩ ዋጋ ሸጨው ወደ ለገጣፎ ይሁን ሌላ ቦታ እንደ አቅሜ እኖራለሁ፡፡ ምን ያደርጋል ጥሪቴን ሁሉ ጨርሼ ብከፍል አዲስ ማስተካከያ ዋጋ እየተሠራ ነው ተባለ፡፡ ከየት አባቴ አምጥቼ እንደምከፍል ግራ ግብት ብሎኛል፤›› የሚል ጭንቀቱን አወረደብን፡፡
ሁለተኛው የለቅሶ ቤት ታዳሚ ደግሞ በቅርቡ ቤቱን የሸጠ ነው፡፡ ‹‹እኔ እኮ የሚገርመኝ አንዳንድ ሰው እንደዚህ ተጨናንቆ አንድ ቤት እንኳን ለማግኘት መስዋዕትነት ይከፍላል? ሌላው ደግሞ አምስት ስድስት ኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤት ሆኗል፤›› ሲል፣ ‹‹ምን ለማለት ፈልገህ ነው?›› ከለቅሶ ቤት ታዳሚ የተጠየቀ ጥያቄ ነበር፡፡ ‹‹ይኼውላችሁ ኑሮ ክብድ ቢለኝ ቤቴን ልሸጥ ተነሳሁ፡፡ ደላላው ያመጣልኝ ሰው ቀንስልኝ እያለ ይወተውተኝ ጀመር፡፡ አንድ ቀን ጠዋት ግን ደውሎ ሌላ አማራጭ ሐሳብ እንዳገኘና እንድንገናኝ ቀጠረኝ፡፡ ሐሳቡ ምን መሰላችሁ? በአዲስ አበባ ባሉ አምስት የኮንዶሚኒየም ፕሮጀክቶች ውስጥ አንድ ባለሦስት መኝታ ቤት በራሱ፣ በባለቤቱና በልጆቹ ስም እንዳለው ነገረኝ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱን ከፈለግክ ይተመንና ከዚያ በላይ ያለውን ልክፈል አይለኝ መሰላችሁ? ለማንኛውም ተስማምተንና አንዱን መርጬ የኮንዶሚኒየም ቤት ነዋሪ ሆኜላችኋለሁ፤›› ብሎ ገጠመኙን አጫወተን፡፡ በእነዚህ ታሪኮች መነሻም ላይ ተመርኩዘን ብዙ ተከራከርን፡፡
40/60 እና የምዝገባ ውል
ነሐሴ 2005 ዓ.ም. አዲስና ነባር ምዝገባ ሲካሄድ ከጅማሬው ማኅበረሰቡ የገባበት ውል አረዳድና ሰሞኑን የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚገልጹበት አግባብ አራምባና ቆቦ ነው፡፡ በየትም አቅጣጫ ሄዳችሁ 40/60 የተመዘገቡ ሰዎችን ብትጠይቁ (መቶ በመቶ የከፈሉ ባለሀብቶችን ሳታካትቱ) የነበራቸው ግንዛቤ 40 በመቶ መቆጠብ ከቻሉና በትክክል ቁጠባቸውን ካካሄዱ ዕጣ ውስጥ እንደሚገቡ ነው፡፡ በቅርቡ ‹‹አንዳንድ ነገሮች›› በሚለው የሸገር ሬዲዮ ጣቢያ ላይ የተገኙት የ40/60 ፕሮግራም ባለሥልጣን በወቅቱ ተመዝጋቢዎቹ እጅ ላይ የደረሳቸው ብሮሸር ላይ ግልጽ ባለ ሁኔታ አሠራሩ ተቀምጧል ብለዋል፡፡ ብዙዎች ግን በወቅቱ ተራ አግኝቶ ለመመዝገብ ከነበረው ግብ ግብ ጋር በተያያዘም ይሁን በትክክል ብሮሸሩ ለኅብረተሰቡ እንዲደርስ ባለመደረጉ፣ በወቅቱ የተባለውን ዶክመንት ጨርሶ እንዳላዩ ይናገራሉ፡፡ ለነገሩ እንኳን ብሮሸር የፈረምንበትን ውል እንኳን እንደ ተጠቃሚ ሲዘጋጅ ሳንወያይበት ብሎም ከነበረው የምዝገባ ሩጫ፣ ግፊያና ግርግር አንፃር በአግባቡ የምናነብበት ጊዜ አልነበረንም፡፡ ይህ ስሜት ደግሞ የተናጋሪው ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ተመዝጋቢ የሚጋራው ነው፡፡
ብዙዎች እንደሚሉት ከጅምሩ መንግሥት ይህን አስቦበት የጀመረው ከሆነ ፕሮግራሙ 40/60 መባል አልነበረትም፡፡ በትክክልም ቆም ብለን ስናስብ መቶ በመቶ ለከፈሉ ቅድሚያ የሚገኝበት ፕሮግራም እስከሆነ ድረስ፣ ማኅበረሰቡን ቁጠባችሁን 40 በመቶ ከደረሰ የሚል ግንዛቤ ውስጥ መክተት ባላስፈለገ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው በዚህ ፕሮግራም 164 ሺሕ ሕዝብ ተመዝግቧል፡፡ በዕቅዱ መሠረትም በሦስት ዓመት 20,000 ቤቶች ለመገንባት ታልሞ ነበር፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ ቆመን ግን በጣም ትንሽ ቤቶች ብቻ ለመተላለፍ እንደደረሱ እየሰማን ነው፡፡ መቶ በመቶ የከፈሉ ተመዝጋቢዎች ቁጥር ግን 16 ሺሕ ያህል ነው፡፡ ይቅርታ የከፈሉ ለማለት አፌን ከብዶኝ ነው፡፡ ታዲያ ምዝገባ ከተካሄደ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ የቁጠባ ቤቶች ጽሕፈት ቤት የሚል ቢሮ መቋቋሙ ለምን አስፈለገ? ማለቴ የቁጠባ ቤቶች ከሚባል የሙሉ ክፍያ ፕሮግራም ቢባል የተሻለ ነበር፡፡ ሙሉ ክፍያ ለመክፈል ያልቻሉ ትጉህ ቆጣቢያን ዕጣ ፈንታስ ምን ይሆን? ከላይ እንደገለጽኩት 16 ሺሕ ሙሉ ከፋዮች እንዳሉ ሰምተናል፡፡
ሰሞኑን በሰማነው መረጃ ደግሞ (የነገሩንን እንመንና) ቤቶቹ በሦስት ምዕራፍ ተከፋፍለው 39 ሺሕ ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን ነው፡፡ በአንደኛ ምዕራፍ 292 ቤቶች ለባንክ የሚተላለፉ ናቸው ተብሏል፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍና በሚቀጥለው ዓመት ይጠናቀቃሉ የተባሉት 932 ቤቶች ናቸው፡፡ በሦስተኛ ምዕራፍ 17,500 ቤቶች በ2011 ዓ.ም. በኮንትራታችን መሠረት ይጠናቀቃሉ ተብሏል፡፡ በዚህ ቀመር መሠረት ራሱ መቶ በመቶ የከፈሉትን ለማዳረስ እንኳን ከሦስት ዓመት በላይ ይፈጃል፡፡ ትክክለኞቹ ቆጣቢዎች ደግሞ የዛሬ ሦስት ዓመት ላይ እንኳን ሙሉ ክፍያ ላይ ይደርሳሉ ማለት ዘበት ነው፡፡
በዕቅዱ መሠረት እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ በሦስት ምዕራፍ ይደርሳሉ የተባሉት ቤቶችን ስንደምራቸው 18,724 ናቸው፡፡ የተመዝጋቢው ቁጥር 164,000 ነው፡፡ ተሳክቶልን እንኳን በዚህ መልኩ ቢጓዝልን ለማዳረስ ከ26 ዓመታት በላይ ይፈጃል ማለት ነው፡፡ ትክክለኞቹ ቆጣቢዎች ደግሞ ቤቱ በቶሎ ደርሶላቸውና ከቤት ኪራይ ወጪ ካልተላቀቁ ጊዜ የሚፈጥርባቸውን ጫና መቆጣጠር የሚችሉ አይመስለኝም፡፡
40/60 እና አከራዮች
ከላይ እንደ መነሻ በሰማነው ታሪክ ብዙ ሰዎች በአዲስ አበባ ውስጥ የብዙ የመሬት ይዞታ የሆነ የኮንዶሚኒየም ባለቤት ሆነዋል፡፡ ለዚህም ብዙዎች በዋነኛነት የመሬት ፖሊሲውን፣ ሙስናን፣ ብሔርተኝነትን፣ ቡድናዊነትን (የፓርቲ አባልነትን)፣ ድህነትንና የመሳሰሉትን እንደ ምክንያትነት ይጠቅሳሉ፡፡ ወጣም ወረደ ግን አዲስ አበባችን በቤት አከራዮች ተወራለች፡፡ ለኑሮ መደጎሚያ በግቢው ውስጥ ቤት ቢጤ ሠርቶ ከሚያከራየው ጀምሮ በጣም ትልልቅና ቅንጡ የሆኑ ቤቶችን ሠርተው በዶላር እስከሚያከራዩ ግለሰቦች ድረስ እየተመለከትን ነው፡፡ ከላይ ያነሳው ባለታሪክ የነገረን ሰውዬ በአምስት ኮንዶሚኒየም ፕሮጀክቶች ላይ ባለቤት የሆነው አንድም ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች ተጠቃሚ ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ካልሆነም ደግሞ ባለዕድል ከሆኑና አቅም ከሌላቸው ወገኖቻችን ላይ ገዝቶ ይሆናል፡፡ በተለይ ዕጣ የወጣላቸው ዕድለኞች ቅድሚያ ክፍያቸውን በሚከፍሉ ሰሞን እነዚህ አከራዮች (Land Lords) በከተማዋ ላይ ደላሎችን በመበተን አቅም ለሌላቸው ቅድሚያ ክፍያ በመክፈል የሽያጭ ድርድር ያካሂዳሉ፡፡ ዋናው ጥያቄ ይኼ ሐሳብ ከ40/60 ፕሮግራም ጋር ምን ያገናኘዋል? የሚለው ነው፡፡
በመጀመርያ ደረጃ ሙሉ በሙሉ ማለት ባንችልም የዚህን የመቶ በመቶ ክፍያ በድፍረት የመፈጸም አዕምሯዊ ብቃት ሊኖራቸው የሚችለው ከላይ የገለጽናቸው ትልቅ አቅም ያላቸው ማለትም መሬትን የመሸጥና መለወጥ፣ የማከራየት ልምድ ያካበቱ ሰዎች እንደሚሆኑ መገመት ሞኝነት አይመስልም፡፡ እነዚህ ሰዎች በራሳቸውና ለአካለ መጠን በደረሱ ልጆቻቸው ስም መቆጠባቸው ይቅርታ ሙሉ ክፍያ መክፈላቸው አያጠራጥርም፡፡ ይህንንም ለመሞከር ዘርፈ ብዙ የሆነ ልምዳቸው ማለትም ከተማዋ በምታወጣው የመሬት ሊዝ ጨረታ ተሳትፏቸው፣ በተለያየ መንገድ ቦታም ሆነ ኮንዶሚኒየም ለማግኘት ያደረጓቸው ትግሎች፣ የዕጣ ተጠቃሚ ሳይሆኑ እንኳን ከባለ ዕድሎች እየገዙ ያከራዩዋቸው ብሎም ቦታው ሲሞቅና የቤቱ ካርታ ዘመን ሲደርስ በርካሽ ከችግረኞች ላይ የገዙትን ኮንዶሚኒየም ሞቅ ባለ ትርፍ እየሸጡት ሀብት በማካበታቸው፣ የ40/60 ፕሮግራም ልፋት የሌለውና ለጥ ያለ ጎዳና ሆኖላቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ ወጣም ወረደ ይህ የሚያሳየን በመሬት፣ በቤት ኪራይና በሽያጭ ዙሪያ እየሠሩ ትልቅ ጡንቻ ያበጁ ሰዎች አሻራ በ40/60 ፕሮግራም ላይ ተንሰራፍቶ ይታያል፡፡
40/60 እና የመነሻ ዋጋ
ሰሞኑን ሌላው መከራከሪያ ነጥብ የሆነው በ2005 ዓ.ም. በተደረገው የውል ስምምነት ላይ ያለው የመነሻ ዋጋ እንጂ፣ የመጨረሻ ዋጋ አይደለም የሚለው ነው፡፡ እንዲያውም በሸገር ሬዲዮ ጣቢያ ላይ በሚተላለፈው ‹‹አንዳንድ ነገሮች›› ፕሮግራም ላይ የቀረቡት የፕሮጀክቱ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ ኃላፊ ከፍተኛ ሙግት ከጋዜጠኞችም ሆነ ከማኅበረሰቡ የገጠማቸው በዚሁ ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ ጊዜ የሚያመጣውን ልዩነት ለመክፈል ደንበኛው ተስማምቶ ውል ፈርሟል የሚል ነው፡፡
በእውነት ተመዝጋቢው ይህንን ጉዳይ በግልጽ አውቆት ውል የገባ ከሆነ ዛሬ ቆሞ ለምን ይከራከራል? እኔም ባገኘሁት አጋጣሚ ያነጋገርኳቸውም ሆነ በሬዲዮ ፕሮግራሙ ላይ በቀጥታ ስልክ ገብተው ሐሳባቸውን የገለጹ ሰዎች፣ ለዚህ ጉዳይ ባይተዋር የመሆናቸውን እንቆቅልሽ ማን ይፈታልን ይሆን? ባለሥልጣኑ ግን በግልጽ ኮሚቴ ተቋቁሞ የዋጋ ጭማሪውን ጉዳይ አጣርቶ እንደጨረሰና ለበላይ አካላት ለውሳኔ እንዳቀረበ ነግረውናል፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ ብዙዎች የሚያነሱት ሌላው ጉዳይ ደግሞ በጽሕፈት ቤቱ የአፈጻጸም ድክመት፣ የገንዘብ አቅም ማነስ፣ በኮንትራክተሮቹም ሆነ በአማካሪ ድርጅቶቹ ብቃትና ሥነ ምግባር መጓደል ምክንያት በተጓጓዙ ጊዜ አማካይነት የመጣውን የዋጋ ልዩነት ተጠቃሚ ላይ ለመለጠፍ መሯሯጥ ተገቢ አይደለም የሚለው ነው፡፡
የዓለምም ሆነ የአገሪቷ አኮኖሚ በተለያዩ ነባራዊ ምክንያቶች በተነቃነቀ ቁጥርም ሌሎች እውነታዎችን ሳይዳስሱ በአንድ አቅጣጫ መንደርደር ምን የሚሉት ነገር ነው የሚለው የብዙዎች ሐሳብ ነው፡፡ ተመዝጋቢው የዛሬ አራት ዓመት ያስገባው ገንዘብ የመግዛት አቅሙ ከዛሬው ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱም የትየለሌ ነው፡፡ ስለዚህም የበላይ አካላት ውሳኔዎችን ከማስተላለፋቸው በፊት ብዙ ነገሮችን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ግድ ይላቸዋል፡፡
40/60 እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የአዲስ አበባ የቁጠባ ቤቶች ጽሕፈት ቤት ለርክክብ ይበቃሉ ያላቸውን ውስን ቤቶች ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያስረከብኩ ነው ብሏል፡፡ ዕጣውንም የሚያወጣው ይኼው ባንክ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ አሁን ይህን ጽሑፍ በምታነቡበት ወቅት የእነዚህ ቤቶች ርክክብ ያለቀ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ኃላፊዎቹ የሰጡን ቃል ያረጋግጣል፡፡
የብዙዎች ጥያቄ ግን ጽሕፈት ቤቱ ፕሮጀክቶቹን ካስመረቀ በኋላ ለባንኩ የማስረከብ ሒደትም ሆነ ዕጣውን ከራሱ አሳልፎ የመስጠቱ አስፈላጊነት ላይ ነው፡፡ እንደከዚህ በፊቱ አበዳሪው አካል ጋር ዕጣው ከወጣ በኋላ ማገናኘት ለምን አልተቻለም? ንግድ ባንክ ቤቶቹን የመረከብ ሙያዊ አቅሙ ምን ድረስ ነው? ወይስ ሌላ ብዙ ያልተፈቱ ጥያቄዎች፣ መሠረታዊ አካሄዱ ላይ ያሉ ውዝግቦች ስላልተፈቱ ወይም ያልሰማናቸው የተለያዩ አካላት ፍላጎቶችና የመሳሰሉት መልስ እስኪያገኙ ድረስ ጊዜ መቁጠሪያ ነው የሚለውን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ ያልገባንም ምክንያታዊነት ካለ አልተገለጸልንም ወይም አልሰማንም ማለት ነው፡፡ ለማንኛውም ግን ይህ ፕሮግራም ሲጀመርም በቂ ጥናትና ምርምር እንዳልተደረገበት ለመናገር ጠንቋይ መሆን አይገባንም፡፡ ለዚህም ነው ፕሮግራሙ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ሁሉንም እያነጋገረ የሚገኘው!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው felekebruk@yahoo.comማግኘት ይቻላል፡፡
Clik here to view.
