Quantcast
Channel: ዓለም
Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

ትኩረት የሚሻው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ንዑስ ዘርፍ

$
0
0

በዳዊት ወልደ ኢየሱስ

በአገራችን የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኢንዱስትሪ ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ዳሩ ግን ለበርካታ ዓመታት ለዘርፉ ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል፡፡ በመሆኑም በዘርፉ የነበረው የልማት እንቅስቃሴ ደካማ ነበር፡፡ አገሪቱም ከዘርፉ ልታገኝ የሚገባውን የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ልማት ሳታገኝ ቆይታለች፡፡

የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ በኋላ ሊያሠሩ የሚችሉና ሕዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተቀርፀው ወደ ተግባር ተገባ፡፡ ይኼም ተቀብሮ ለነበረው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኢንዱስትሪ ትንሳዔ ሆነለት፡፡ ምክንያቱም የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂው የግል ባለሀብቱ የኢንዱስትሪው ሞተር መሆኑን በማመኑና ማንኛውም ልማታዊ ባለሀብት በዘርፉ ለመሰማራት ቢፈልግ በሩ ክፍት መሆኑን በማወጁ ነው፡፡

አገራችን ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው የትራንስፎርሜሽን ጉዞ የመጀመርያውን አምስት ዓመታት ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መደላድል ፈጥሮ አልፏል፡፡ በመሆኑም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ኢንዱስትሪው መሪነቱን እየተረከበ እንዲሄድ ለማኑፋክቸሪግ ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ትኩረት ከተሰጣቸው የማኑፋክቸሪግ ዘርፍ አንዱ ደግሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ንዑስ ዘርፍ ነው፡፡

ይህ ንዑስ ዘርፍ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ በመባል በሁለት ይከፈላል፡፡ የመሠረታዊ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ የብረት ማዕድናትን፣ ውድቅዳቂ ብረቶችና የጠገራ ብረቶችን በመጠቀም ለኢንጂነሪንግ ንዑስ ዘርፍ ግብዓት የሚሆኑ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን የሚያካትት ሲሆን፣ በኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፉ የሚካተቱት ደግሞ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ውጤቶችን በግብዓትነት በመጠቀም የተለያዩ የኢንጂነሪንግ ምርቶችን የሚፈበርኩ ናቸው፡፡

በሌላ አገላለጽ መሠረታዊ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ከብረት ማጣራት ጀምሮ የተለያዩ መጠን ያላቸውን የመጀመርያ ደረጃ ምርቶችንና እነዚህን ምርቶች በግብዓትነት በመጠቀም ዝርግና ጥቅል ልሙጥ ብረቶችን፣ የተለያዩ ቅርፅ ያላቸው ድፍንና ክፍት ረጃጅም የብረት ምርቶችን፣ ሽቦዎችን፣ የሽቦ ገመዶችን፣ ቆርቆሮዎችንና ሚስማሮችን የማቅለጥ፣ የማሞቅና የመዳመጥ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚያመረቱ ናቸው፡፡ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች የሚባሉት ደግሞ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ውጤትን በግብዓትነት በመጠቀም የተለያዩ ቅርፅ ማውጫ ቴክኖሎጂዎችን፣ ማለትም በማቅለጥ ቅርፅ ማውጣት፣ በማነጥ፣ በብየዳ፣ በመቀጥቀጥ መሣሪያዎችንና የተለያዩ መገልገያ ዕቃዎችን የሚያመርቱ ናቸው፡፡

ይህ ንዑስ ዘርፍ ለሌሎች የማኑፋክቸሪግ ዘርፎች በግብዓትነት በማገልገል ለኢንዱስትሪ መስፋፋት ከፍተኛ ሚና የሚጫዎት ሲሆን፣ ለአገሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕድገትም የላቀ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በመሆኑም ካለው አገራዊ ፋይዳ አንፃር ንዑስ ዘርፉን የሚደግፍ መንግሥታዊ ተቋም መቋቋም ነበረበትና የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ተቋቋመ፡፡

አገራችን በ2017 ዓ.ም. መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሠለፍ ከድህነት ጋር ከፍተኛ የሆነ ትግል እያደረገች ባለበት በዚህ ዘመን፣ ከሁሉም ዘርፍ ዕምርታዊ ለውጥ እንደሚጠበቅ ይታመናል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግም የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2017 ዓ.ም. በአፍሪካ ቀዳሚና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ቀላል የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ በመገንባት፣ ለከባድ ኢንዱስትሪዎች ልማት መሠረት ተጥሎ ማየት የሚል ራዕይ ሰንቆ መንቀሳቀስ ቀጥሏል፡፡

ራዕዩን ዕውን ለማድረግ ታዲያ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ አቅምን ለማሳደግ የሚያስችል ምርምርና ጥናትን መሠረት ያደረገ የተቀናጀ የኢንቨስትመንት፣ የግብይትና ማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ ድጋፍ ለልማታዊ ባለሀብቱ በመስጠት ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ስለሆነም የሚከተሉት የትኩረት መስኮች ተቀምጠዋል፡፡

ቀዳሚው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ማስፋፋት የሚል ነው፡፡ ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በንዑስ ዘርፉ ልማት እንዲሰማሩ ሊስብ የሚችል የተሟላ የመረጃ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ለንዑስ ዘርፉ ልማታዊ ባለሀብቶች በፕሮጀክት ዝግጅትና ትግበራ የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት ወደ ማምረት የሚሸጋገሩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ማሳደግም ይጠበቃል፡፡

በዚህ ረገድ ኢንስቲትዩቱ ከ2005 በጀት ዓመት ጀምሮ አሁን እስካለንበት የ2008 በጀት ዓመት አጋማሽ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ንዑስ ዘርፍ ለሚሰማሩ ልማታዊ ባለሀብቶች ከ300 በላይ አዳዲስ የፕሮጀክት ሐሳቦችን፣ ወደ 60 የሚሆኑ የምርት መግለጫዎችንና ከ40 በላይ የሚሆኑ የቅድመ አዋጭነት ጥናቶችን በማካሄድ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከጥናቱም በንዑስ ዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች መረጃን በመውሰድ፣ ጥናቱን በማሳደግና በማስፋት ተጠቃሚ በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡

ጥናቶቹ የምርት መግለጫ፣ የገበያ ጥናትና የማምረት አቅም፣ የቴክኖሎጂና ኢንጂነሪግ ሥራው (የምርት ሒደቱ፣ የሚጠቀማቸው ማሽነሪዎችና ኢኩፕመንቶች፣ የመሬት፣ የኮንስትራክሽን ሥራውና የአካባቢው  ተፅዕኖ) የጥሬ ዕቃና ሌሎች ግብዓቶች፣ የሰው ኃይልና የሥልጠና ፍላጎት፣ የፋይናንስ ትንተናና ግምገማን ያጠቃለሉ በመሆናቸው ኢንቨስት ለሚያደርጉ ልማታዊ ባለሀብቶች ጠቃሚ መረጃዎችን ያስተላልፋሉ፡፡

ጥናቶቹ ካጠነጠኑባቸው ኢንቨስትመንቶች መካከልም የኤሌክትሪክ ኬብል፣ የአርማታ ብረታ ብረት፣ የሞተር ብስክሌትና መኪና መገጣጠሚያ፣ የውኃ ቱቦ ሥራና የሞባይል አክሰሰሪ መገጣጠሚያዎች ይገኙበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በትግበራ ሒደት የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ማድረግ ሌላው ኢንስቲትዩቱ የንዑስ ዘርፉ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የሚያከናውነው ተግባር ሲሆን፣ በያዝነው በጀት ዓመት የስድስት ወራት አፈጻጸም እንደሚያመለክተው ለ31 ፕሮጀክቶች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ስምንት ፕሮጀክቶች ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ኢንስቲትዩቱ ድጋፍ አድርጓል፡፡

እነዚህ ወደ ማምረት የተሸጋገሩት ፕሮጀክቶች በሦስት የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዓይነቶች የተሰማሩ ሲሆን፣ ኢንቨስትመንቶችም 3,480 ቶን የማምረት አቅም ያለው የብረታ ብረትና የቤት ውስጥ የማብሰያ ቁሳቁስ ፋብሪካ፣ 8,650 ቶን የማምረት አቅም ያለው የተሽከርካሪ መለዋወጫና ተጓዳኝ አካላት ፋብሪካና በዓመት በቁጥር 30,000 ተሽከርካሪና ሞተር ብስክሌት መገጣጠም የሚችል ፋብሪካ መሆናቸውን በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

ሁለተኛው የትኩረት መስክ ደግሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪን የማምረት አቅም ማሳደግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢንስቲትዩቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱና ዋነኛው ንዑስ ዘርፉን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠት ነው፡፡ ባለሙያ ሲበቃ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደጉም በላይ፣ ከሌሎች አገሮች ጋር ተወዳዳሪ የሚሆን ምርትን በሚፈለገው ጥራትና ጊዜ ለማምረት ያስችላል፡፡ በመሆኑም ኢንስቲትዩቱ በቅድሚያ የሥልጠና ፍላጎት የዳሰሳ ጥናት ያካሄዳል፡፡ ኢንዱስትሪዎችም በሰው ኃይላቸው የሚስተዋሉትን የተለያዩ የሙያ ክፍተቶችን በመለየት ፍላጎታቸውን ያሳውቃሉ፡፡

በዚህ የአሠራር ሥርዓትም ከ2006 በጀት ዓመት ጀምሮ ከ2,000 በላይ የንዑስ ዘርፉ ልዩ ልዩ ባለሙያዎች ሥልጠና የወሰዱ ሲሆን፣ ሥልጠናውም ኢአበላሽ (NDT)፣ አውቶ ካድ፣ የጥራት መፈተሻ (Quality Inspection)፣ ማሽኒንግ (ሌዝ፣ ሚሊንግና ሲኤንሲ)፣ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (Quality Management System)፣ ቤዚክ ሜታል ወርክስ፣ የካይዘን ሥራ አመራር ሥርዓት፣ ሶሊድ ወርክስ ሶፍት ዌር፣ ዌልዲንግ፣ ሒት ትሪትመንትና ሌሎችንም ያጠቃልላል፡፡

ከማምረት አቅም ጋር ተያይዞ ለኮንስትራክሽን ግብዓትነት ከሚያገለግሉ ዘርፎች ጥቂቶችን እናንሳ፡፡ በአገር ደረጃ 11 የሚሆኑ የአርማታ ብረታ ብረት አምራቾች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ወደ 1.2 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም አላቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ስድስት የሚሆኑ ከ1.8 ሚሊዮን ቶን በላይ የማምረት አቅም ያላቸው ፕሮጀክቶች ሲኖሩ፣ ሁለቱ ፕሮጀክቶች 75,062 ቶን የማምረት አቅም ይዘው በሚቀጥለው በጀት ዓመት እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ምርት በመተካት ረገድ አስተዋጽኦዋቸው የጎላ ሲሆን፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ ላይ ለመድረስ የታቀደው የአምስት ሚሊዮን ቶን መሠረታዊ ብረታ ብረት ምርት ለማሳካት አመላካች ይሆናሉ፡፡

ቆርቆሮ ሌላው ለኮንስትራክሽን ግብዓትነት ከሚያገለግሉ ዘርፎች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢንስቲትዩቱ የሚደግፋቸው ከ25 በላይ የቆርቆሮ አምራች ድርጅቶች በአገራችን እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ ሁለት ደግሞ በፕሮጀክት ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ታዲያ በዓመት ከ700 ሺሕ ቶን በላይ የማምረት አቅም አላቸው፡፡ ይኽም በአገር ውስጥ ያለውን የቆርቆሮ ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ያሳያል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የትቦላሬን (Hollow Section) የማምረት አቅምን እንመለከታለን፡፡ መረጃዎች  እንደሚያሳዩት ዘጠኝ የትቦላሬ አምራች ኢንዱስትሪዎች በአገራችን ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ታዲያ ከ269 ሺሕ ቶን በላይ የማምረት አቅም ያላቸው ሲሆኑ፣ ከዚህም ውስጥ 50 በመቶ ምርቱ ብቻ የገበያውን ፍላጎት ማርካት ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንድ ፕሮጀክት 300 ሺሕ ቶን የማምረት አቅም ይዞ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በመጨረሻም ኤክስፖርት የሚያደርግ ድርጅት ያለበትን የኬብል የማምረት አቅምን ስንመለከት በዚህ ዘርፍ ስድስት ኢንዱስትሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ወደ 48 ሺሕ ቶን በዓመት የማምረት አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ አንድ ፕሮጀክትም ከአምስት ሺሕ ቶን በላይ ማምረት የሚችል በማምረት ሒደት ላይ ካሉ ኩባንያዎች ጋር ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ምርቶችን የገበያ ድርሻ ማስፋት ሦስተኛውና የመጨረሻው የትኩረት መስክ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ በዚህ ሥርም ገቢ ምርቶችን ለሚተኩ ኢንዱስትሪዎች የገበያ ድርሻቸውን ማስፋት የሚያስችሉ የተሟላ ድጋፍና አገልግሎት መስጠት፣ ለንዑስ ዘርፉ ምርቶች የውጭ ገበያ ማፈላለግ የሚሉትና ሌሎች ተያያዥ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ በመሆኑም ንዑስ ዘርፉ ገቢ ምርትን ከመተካት ባለፈ ከ2006 በጀት ዓመት ጀምሮ የንዑስ ዘርፉን ምርቶች ወደ ውጪ በመላክ በወጪ ንግድ ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል፡፡

በዚህ መሠረት በ2006 ዓ.ም የንዑስ ዘርፉን ምርት ኤክስፖርት ማድረግ ሲጀመር ከአሥር የማይበልጡ ድርጅቶች 3,189,172.99 ዶላር ገቢ ያስገኙ ሲሆን፣ በያዝነው በጀት ዓመት የሰባት ወራት የኤክስፖርት አፈጻጸም የሚያሳየን ደግሞ ኤክስፖርት የሚያደርጉ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር ወደ 14 ከፍ እንዳሉና ከኢንዱስትሪዎች የተገኘው የኤክስፖርት ገቢ 11,020,963.59 ዶላር መድረሱን ነው፡፡

ኤክስፖርት ከተደረጉት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ምርት ውጤቶች መካከል ሞባይል፣ የኤሌክትሪክ ኬብል፣ የግብርና መሣሪያዎች፣ ቆርቆሮ፣ ጌጣ ጌጦችና የቤት ቁሳቁሶች ተጠቃሽ ሲሆኑ የምርቶቹ መዳረሻ አገሮችም አሜሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓና የአፍሪካ አገሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም ኤክስፖርት የሚያደርጉ ድርጅቶችና የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት ቢያሳይም ከዚህ በላይ መሠራት እንዳለበት ግን አመላካች ነው፡፡

በአጠቃላይ ኢንስቲትዩቱ ከእነዚህ የትኩረት መስኮቹ በመነሳት ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ንዑስ ዘርፍ ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም፣ አገሪቱ ከዘርፉ የምትጠብቀውን ውጤት ለማግኘትና ኢንስቲትዩቱም ራዕዩን ለማሳካት ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠበቅ ይታመናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ኢንዱስትሪው የመንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂን በመከተልና ከመልካም አስተዳደር ችግርና ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የፀዳ አሠራርን በመዘርጋት ለአገር ዕድገት በጋራ መረባረብ ይጠበቃል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው dawit.keha@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 231

Trending Articles